"የባሕር ዳር ዩኒቨርስቲ ጥበበ ግዮን ሆስፒታል ካለፈው ሰኞ ጀምሮ አገልግሎቱ ተስተጓጎለ" https://www.bbc.com/amharic/articles/c8dm85jvl8zo የፎቶው ባለመብት, BAHIR DAR UNIVERSITY 21 ህዳር 2024 "በባሕር ዳር ዩኒቨርስቲ ሕክምና እና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ስር የሚገኘው ጥበበ ግዮን ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ሠራተኞች በሚደርስባቸው ተደጋጋሚ ዝርፊያ እና የደኅንነት ስጋት በከፊል ሥራ ማቆማቸውን ተናገሩ። ባለፈው ሳምንት “ጭምብል የለበሱ” እና ማንነታቸው አይታወቅም የተባሉ ታጣቂዎች በሆስፒታሉ ቅጥር ጊቢ ስምንት ሰዎችን መዝረፋቸው የሆስፒታሉ ባለሙያዎች ሥራ እንዲያቆሙ አድርጓል ተብሏል። በአማራ ክልል ባለው የትጥቅ ግጭት ምክንያት በሆስፒታሉ “አልፎ አልፎ” የአገልግሎት መስተጓጉሎች እንዳሉ የጠቆሙ አንድ የሆስፒታሉ ሠራተኛ፤ ከሰሞኑ በተፈጸመ ጥቃት ባለሙያዎች የደኅንነት ስጋት ውስጥ መውደቃቸውን ተናግረዋል። ቢቢሲ ያነጋገራቸው የሆስፒታሉ ሠራተኞች እና የሕክምና ተማሪዎች ጊቢው ያልታጠረ እና ጥበቃውም ያልተጠናከረ በመሆኑ ተደጋጋሚ ጥቃቶች እንደሚፈጸሙ ተናግረዋል። “ከምሽቱ አንድ ሰዓት በኋላ ማንም አይወጣም። ከሕንጻው ወጥቶ ውሃ ለመቅዳት እንዲሁም ለመዝናናት መውጣት አይቻልም። ስጋቱ ያን ያህል ስለሆነ ሁሉም በሩን ዘግቶ ቁጭ ነው የሚለው” ሲሉ አንድ የዩኒቨርስቲው የሕክምና ተማሪ ስጋቱን ገልጿል። “ምንም ዋስትና የለንም” ያሉ ጊቢው ውስጥ የሚኖሩ እና ሌላ የመጨረሻ ዓመት የሕክምና ተማሪ (ኢንተርን ሐኪም) ባለፈው እሁድ ታጣቂዎቹ ለመዝረፍ ሲሉ ተኩስ ከፍተው እንደነበር ጠቁመዋል። የሆስፒታሉ ሠራተኞች እና ባለሙያዎች ባለፈው ሳምንት የተፈጸመውን ዝርፊያ ተከትሎ “እስከ መቼ” በሚል ጥ...