ሃይለመድህን አበራ።

        የጀግና ውለታው ሁልጊዜም ያሰበለ ነው።
                  ተግባሩም ምንጊዜም መሪ ነው
                ከሥርጉተሥላሴ 11.04.2018 (ከጭምቷ ሲዊዘርላንድ)

የእግዚአብሔርም እሳት ወደቀች፣ የሚቃጠለውን ምሥዋዕቱንም እንጨቱንም ድንጋዮቹንም አፈሩንም በላች፣ በጉድጓዱ ውስጥ
                 ያለውን ውሃም ላሰች (መጽሐፈ ነገሥት ቀዳማዊ ምዕራፍ ፲፰ ቁጥር ፴፰ እስከ ፴፱“)



  • ጀግናዬን ሳስበው።

እንዴት አላችሁልኝ ውዶቼ የሐገሬ ልጆች፣ —-ዛሬ ላይ ሆኜ ጀግናዬን ሳስበው ይህቺን የብርሃን ማዕለት ለማምጣት ነበር ያን ያህል ማይልስ ርቆ ሰማይን ቀዝፎ፤ ጉሙነን ተሻግሮ መነኮሲያዋን ሲዊዝን ራፊ፤ ብጣሽ፤ የሰላም መሬት የጠዬቀው። በሐገሩ መቀመጫ በማጣቱ፤ በሐገሩ በመሳዳዱ ምክንያት። ይህ ጀግና አዬር ላይም ባልተለመደ ሁኔታ በሌሎች ሐገሮች ተመሳሳይ አውሮፕላን ታጅቦ ነበር መሬት ላይ ያረፈው። አፈፃፀሙም ዓለምን በእጅጉ ያሰደደመመ ነበር። እትዮጵውያን አርበኝነታቸውን በባእድ ሐገር ሲፈጽሙ አምደ እርሰ ጉዳይ ሆነው ነው። ኢትዮጵውያን በዓለም አደባባይ ስመጥር ጀግኖች መሆናችን በሚገባ ይታወቃል።
የእርምጃ አወሳሰዱ ጥበብ ዛሬ እኛም በማናውቀው፤ ባልገባን መንገድ፤ ረቂቅ፤ የልቤ ሊባልት የሚገባውን ተግባራት የሚከውኑትን ኢትጵያዊ የፖለቲካ ወጣት ሊሂቃን መሰል ነው ክንውኑ። ልክ እንደ አቦ ለማ መግርሳ፤ እንደ ዶር አብይ አህመድ እና እንደ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው። ለስላሳ ግን ጉልባታም ውጤታማ ሰላማዊ ትግል። አሁን በኢትጵያ ፖለቲካ ግንዛቤ ፍቹ፤ ትልሙ፤ ርምጃው፤ ግቡ ጭንቅ የሆነው የእነዚህን የሦስቱ ሥላሴ ሊቃናት ታክቲክ እና ስትራቴጂ፤ ጥበብና ስልት መሸከም የሚችል የፖለቲካ አቅም በማነሱ ምክንያት ነው።

43 ዓመቱ የትግል መከራ የተቋጨው ሰላማዊ በሆነ ሽግግር መሆኑ በራሱ ትውልዱ በዚህ መስመር ነገን ተስፋ ማድርግ እንዲችል ቋሚ ተቋም ነበር የተከፈተውለሚያውቀው። የወድሞው / ሚር አቶ ሐይለማርያም ደሳለኝ የፈጸሙት በጎ ተግባርም የመጀመሪያው ቢያሰኛቸው የሚጎረብጥ አይሆንም። መልካም ነገር ነው የሰጡን። ነገም የትኛውም ፓርቲ ተወዳድሮ ቢያሽንፍ በአቅሙ ልክ እኩል ተሳትፎ ማድረግ የሚችልበት ሥርዓት ነው የተዘረጋው። ጠበንጃ እና ሥልጣን የተፋቱበት ድንቅ የታሪክ ዘመን ነውዛሬ። አዕምሮ ላለው ዕውነተኛ የነፃነት ራህብተኛ ይህ ድንቅ ሂደት ብልሃትም ታስቦ የማያወቅ ነው። የትውልዱ ብክነት ለጠናበት፤ ኑሮውን ላባከነው ባተሌ የትግሉ ቤተሰብ ይህ ፈጣሪ የሰጠው ሽልማቱ ነው አብሶ እንደ ሥርጉተ ለደከመው። ይህ የተጋድሎ ምዕራፍ አቅጣጫው ምን ይሆናል ብሎ መተንበዩ ስላቃተን ነው በመላመት ስንራመድ የከረምነው፤ ዛሬም ያለነው። ወያኔ ሃርነት ትግራይን ያህል ጉድጓድ ድርጅት፤ ሳጅን በረከት ስምዖንን የመሰለ ገደል አስቀምጠን እኛ አቅም ለዚህ እሾኽ ጋንታ እያቀበልን፤ ስንቅና ትጥቅ እዬሆን ሌላ ያልታሰብ የሃሳብ ጉግስ እያመረትን እንታገለዋለን። ተስፋ ያደረገው ትውልድ ተስፋው እንዲባክን ላይ የሚመስሉ መልካም ነገሮችን ይደረደርና ሥር ላይ ህሊናውን የሚወጥር ጥያቄ ትተን እንደለመደብህ ባዝን እንለዋለን። መቼም ሃዘኔታ አልሰራልንም። በትኩስ ሬሳ ላይ፤ በትኩስ ዕንባ ላይ ለቆዬ ነፍስ ትንሽ ልብን፤ ቀልብን የሚያሳርፍ ነገር ሲገኘም በበጎ ማስተናገድ ካቃተን ትግሉ እድሉን ከሰጠን ከፈጣሪ ጋር ብቻ ነው።
  • ትዕይንት።

በበቃ እውቀት የሚመራ የለውጥ ሂደት የተጋድሎ ሂደቱ ለእኛ ባልተገለጠልን ሁኔታ ቁጥብ ስለሚሆን፤ ጊዜን በአግባቡ ለማስተዳደር ምቹ ሁኔታ ማግኘት ይቻላል። ገረጭራጫ ባህሬ ያለው የፖለቲካ አመራር ስልት ውስጥን ሰላም በማሳጠት ጊዜን የሚበላ፤ ሥልጡን ያልሆነ ዳተኛ የአያያዝ ስልት ነው። ገረጭራጫ እርምጃ በመጀመሪያ ራስን ያዳክማል፤ በሁለተኛ ደረጃ ማህበራዊ መሠረትን ያሳጣል፤ በሦስተኛ ደረጃ የሃይል አስላለፍን አቅጣጫም ሊያስቀይር ስለሚችል ጠቀሜታው በባዶ የተባዛ ይሆናል። በሴራ ከደነደነ አንድ የሃሳብ ልዕልና ከነበረው የገነገነ ጉድ ጋር ተጋድሎ ለማድረግ እጅግ ጥንቃቄ፤ እጅግ የበዛ ማስተዋል፤ በጥበብ የተሞላ እርምጃ ያስፍልገዋል። ይህ የአዋቂዎች ጉዞ እዬሄ ከአውሬ ጋር እዬተላተመ አላስፈላጊ ብክነት መፈጸም ድርሻውም ተልዕኮውም አይደለም። ያን በስሜት ፈረስ ለሚጋልብ መንፈስ

ስልት፣ ጥበብ፣ በልክ መያዝ፤ ከማናቸውም አምክንዮዎች ወይንም ገጠመኞች ጋር እልህ አለመጋባት፤ አብዝቶ ማድመጥ፤ እርምጃን አቅዶ መከወን ግን የውስጥን ሰላም ይጠብቃል። ጠላትንም ይቀንሳል። ስኬትንም ያጎናጽፋል። አሁን ኢትዮጵያን የሚመራው የለውጥ መንፈስም የወያኔ ሃርነትን ትግራይ ማንፌስቶን ገረጭራጫ፤ ብስጩ፤ ሸርና ደባ የከተመበትን ትብትብ በረቀቅ ብቃት እና በትሁት የፖለቲካ አያያዝ እያሸነፈ ወደፊት በመገስገስ፤ ቀልብ ሳቢ፤ መንፈሳዊ ሃብት ሰብሳቢም መሆን ችሏል። አቅሙ በሚገባ የታሰበበት፤ መሬት ላይ የተነሳ፤ የእኔ የሚለው የሃሳብ አቅም እና የማያቋርጥ ጅረት ባለቤት የሆነ፤ እንቅስቃሴው የተጠና እና እርጋታው ድርጁ መሆን ሊያጠቁት የሚያስቡትን መስናክሎች እያባበለ እና እያስማማ ፍቅርን መግቦ በመምህርነቱ ትውልዳዊ አደራውን ይወጣል ብዬ አስባለሁ እኔው። ጉዞው ለብለብ፤ በሞቅታ ፈረስ የሚጋልብ አይደለም።

ገና ይመጣሉ የሚባሉ ሳንኮቹ ሁሉ ቀድመው ተጠንተው፤ ከዚያ በላይ በሆነ ሥልጡን የወል አመራር መራመድ በመቻሉ ዛሬ እዚህ ተደርሷልኢትዮጵውያዊነት ሱስ ነው እስከ አሁን በሚታዬው ሁኔታኢትዮጵያዊነት ሱስ ነውአሸናፊ ነው። ነገም የተሻለ ዕድል ይኖረዋል። ይህ ሂደት የክህሎት ደረጃ ልቅናም ነው። ለዚህም ነውኢትዮጵያዊነት ሱስ ነውብሄራዊ ንቅናቄ እርምጃዎቹ ባልተጠበቁ አዲስ ክስተቶችን እያዋዛ፤ በተሟላ ሥነምግባር እያያያዘ፤ ልብ አንጠልጣይ ክነውኖችን መከወን የቻለው። በሂደቱ ውጤቱን ጋር መመጠን ስላልተቻለ ወጣ ገባነታዊ ግንዛቤ እያስተናገድን የምንገኘውም በዚህ ምክንያት ነው። አልተመጣጠነም። ይሆናል ተብሎ ሟርት የተተነበዬለት ሃሳቡ ገና ታቱ ሳይል አዬር ላይ እያለ እነሱ በተግባር ይረቱት እና ይሞታል፤ ቀንዲሎቹ ሌላ ድንገቴ ውብ ትወናን ፈጥረው ፈቅደን እንከተለው ዘንድ በትህትና ይሸለሙናል። ብዙ ሰው በአንድ አእምሮ ብቻ የሚመራ ይመስለዋል። አይደለም ባሉ ብዙ አዕምሮዎች በወጥ ፍላጎት ላይ በተመሠረተ ቅንነት በአይህትዮሽ እዬመሩት ነው ያለው።ሽግሽጉ እንደ ኳስ ጨዋታ ተጫዋቾች ነውያሉት አቮ ለማም ለዚህ ነበር። ቦታ አይደለም ጉዳያቸው። በኢትዮጵያኢትዮጵያዊ ተፈጥሮ ያለው የዴሚክራሲ ሥርዓት በራስ ጥሪት እና ትውፊት ላይ የተመሰረት አዲስ ዓለም መፍጠር ነው ህልሙ።የሃይማኖት መሪው ኡስታዝ ራያ እኮ ለመላ ኢትዮጵያ ህዝብ ተናግረዋልራሳችሁን አዘጋጁብለው።
  • ዜና ፖለቲካ።

ፖለቲካ ህይወትን እና ተዛማጅ ሁነቶችን መሠረት አድርጎ ነው የሚነሳው። ህይወት ደግሞ ተከታታይ ነው። ስለሆነም የፖለቲካ ትግል የመዋዕለ ዕድሜ ቋሚ ተግባር ነው ማለት ነው። አይቆምም፤ ማስቆምም አይቻልም፤ ፖለቲካ አዳጊ እና ተግባቢ ሊሆን የሚችለው ግን የህዝቡን ማህራዊ ንቃተ ህሊና ከፍ ባለ የዐዕምሮ አቅም ለመምራት ሲታደሉት ብቻ ነው። ሰውኛ ሲሆን ጠበንጃን ሲጸዬፍ፤ ተፈጥሮን አክብሮ ሲነሳ

ይህም በዛው በዘመኑ ውስጥ መሆን ሲቻል ደግሞ የበለጠ ስኬቱ ይፋፋል። ለዘመኑ የሚቀርብ ሥነልቦናዊ አቅም ያስፈልገዋል። የትውልድ ክፍተት ከኖረ ብዙ ነገር ጋዳ ነው የሚሆነው። የመረዳት ችግር ይኖራል።አንድነት ማለት አንዳዊነት ማለት አይደለምያሉት ጠቅላይ / አብይ አህመድም ለዚህ ነው። በትውልዱ ውስጥ ስላሉ፤ ተውልዱ የሚሰማውን እሳቸውም ይሰማቸዋል። የዘመን ክፍተት ስሌለው። የሥነልቦናዊ አቅም በዬዕድሜ ደረጃው ሰለሚለያይ የለውጥ መንፈስ ሁልጊዜ ከሚቀርበው ጋር ይቀራረባል። ከዚህ ካለፈ ግን ይገረዝዛል። ዘመን ወደፊት እያዬ ነው የሚራመደው። ስልቱ ለስላሳ እና ዘዴያዊ ከሆነ ደግሞ መስዋዕትነቱን ከመቀነሱ በላይ ከሚመጡ አላስፈላጊ ጫናዎች፤ ቅራኔዎች መዳንም ይቻላል። ብዙ ነገር ይቆጥባል።

ስለሆነምየኢትጵያዊነት ሱስን አርበኞችጊዜም ራሱ አልተረዳቸውም እንኳንስ ሰውኛው ቤተሰብ። ምኞታቸውን ሆነ ሃሳባቸውን ብቻ እንጂ ተረገጡን ገና አላገኘውም። የወያኔ ሃርነትም ሰንበሌጣዊ አቅሙ ከአጠገቡ ደርሶ ሰው ሰራሽ መሰናክሉ ሁሉ የድል ባለቤት ሊሆን አላስቻለውም። በቅርብ እና በሩቅ የሚያገኘው የመቅኖ የምክር አገልግሎትም ብላሽ ነው የሆነው። ትንኮሳው፤ የህዝብ እልቂቱ፤ መፈናቀሉ ሁሉ ሊገታው አላስቸለውም ይህን የአዲስነት የመንፈስ ጉዞ። የነፃነት ትግሉና የነፃነት ትግሉን መንፈስ የሚመሩት ወጣት የፖለቲካ ሊሂቃንን ለማወቅ ያዳገተውን ያህል ነው፤ የዚህ ሩቅ ወጣት ራዕይ እና ጥበብ የጀግና ሃይለመድህን አበራ ውሳኔም፤ እርምጃም ክንውንም ተመሳሳይ ነውአሁን ለእኔ። በእውቀት የተመራም ነው። የትኛውም ጥረት ጸጋው በፈርሃ እግዚአብሄር ከሰከነ ደግሞ ፈጣሪ አምላክ የታከለበት ይሆናል።
  • ጥሪ!

ይህ ሳተና ወጣት ቢሳካለት፤ ቢሆንለትማ ኖሮ በመጀመሪያ የተመረቀብትን (ምህንድስና ይመስለኛል) ሙያ ጥሎ፤ የወደደውን የተመኘውን የልጅነት ህልሙን አውሮፕላን አብራሪነትን በሐገሩ መሬት፤ የኢትዮጵያ አንባሳደርነቱን በፈቀደው ነበር። ከናፍቆቱ ጋር ከፍ ብሎ አዬር ላይ ንጹህ አዬሩን በፍስሃ እና በሐሴት በተቃኘበት ነበር።

አዬር ላይ ዋናተኛው ህልሙን በመዳፉ አድርጎ ኑሮዬ ብሎ የተመቻቸ ህይወቱን፤ በትውልድ ሐገሩ፤ በዚህ ልቅናው ልክ ትዳር መሥርቶ፤ ልጆቹን ወልዶ፤ በሚወዳት ሐገሩ ኢትዮጵያ በተቀመጠ ነበር። ግን ተስፋውን፤ ራዕዩን፤ ምኞቱን፤ መልካም ፍላጎቱን በማጨናጎል በማን አለብኝነት ጎሳዊ የወያኔ ሃርነት ሥርዕዎ አስተዳደር ህልሙን ተቀማ። በእነ ሳጅን በረከት ሴራዊ የስላላ መረብ ራዕዩ ተነጠቀ። ይህ ጀግና፤ ይህ ብርቅ፤ ይህ የማስተዋል ሐዋርያ አንድም የኢትዮጵያን አዬር መንገድ እንግዳን ሳያውክ፤ ሐገሩን ኢትዮጵያን በክፉ ሥም ሳያስነሳ፤ ሐገሩን ልዕልት ኢትዮጵያን ከሌሎች ሐገሮች መንግሥታት ህዝብ ጋር ደም ሳያቃባ፤ ቂም ሳያስቋጥር የዓለምን ህዝብ በደንዳና ጭካኒያዊ እርምጃ በሃዘን ሳይቀጣ፤ የዛችን ደሃ የሐገሩን ጥሪትም ለማወደም ሳያቅድ፤ ሳይፈቅድም እጅግ በጥንቃቄ፤ በብርቱ ብልህነት፤ በላቀ ክህሎት በተሞላበት ሁኔታ ትውፊቱን፤ ታሪኩን ጠብቆ በከፍተኛ ብሄራዊ ስሜት ታሪካዊ ገዴታውን ተዋጣው። የሰብዕዊ መብት የነጠረ ተሟጋችም ነው። ጥሪ ነበረበት የነፃነት ብርቱ ጥሪ። የተፈጠረውም ለዚህ ነው። የፈቀደለትም ፈጣሪ እዬሱስ ክርስቶስ ለዚህ ቅብዕ ነበር። 

አንግዲያውስ የመጀመሪያ ሙያውም እኮ ተፈልጎ የማይገኝ ነበር። ግን የተፈጠረበት መንገድ ለሌላ ሐገረዊ ጀግንነት ነው። ጥሪውንም እንደ ቀደምቶቹ ትንታግ አርበኛ ወገኖቹ በሰው ሐገርም ድልን በዝምታ ከወነው። አልገዛም ለዘረኝነት፤ አልገዛም ለጭቆና፤ ነፃነቴን ሰጥቼ ከምኖር በመዳፌ ባለው ሙሉ አቅም ተጠቅሜ ነፃነቴን አውጃለሁኝ፤ የነፃነት ራህብተኞችም በምከፍለው መስዋዕትነት ደወል እሸልማቸዋለሁኝ ብሎ በጭምቱ ስብዕናው በጨዋነት በጭምቷ ሲዊዝ ጀግንነቱን በድል ከወነው። የዓደዋ ድልን ድጋሚ ትንሳኤውን አወጀለት። አንተ እና እኔ እኩል አቅም፤ እኩል ክህሎት እያለኝ፤ አያቶች እስገድደው ያስጎነጩህን ሽንፈት እኔም አስጎነጭሃለሁኝ፤ የአንተን የበታችነት አላስተናግድልህም ብሎ ሃሞቱንም ጋተውለጣሊያናዊ አለቃው። የባንዳ ትርፍራፊም ቅጠቱን በእጥፍ አወራረደው። ጮርቃ፤ ዕንቡጥ፤ ፍሬዘር  የአያት ቅድመ አያቶቹን ጀግንነት በድርብ ደገመው። አዳበረው። አለመለመው! ተባረክ የእኔ ጀግና!
  • ጥበብ።

ሌላው ቀርቶ በመደበኛው በር ወጥቶ ቢሆን ኖሮ ሊደርስ የሚችለውን ያልተፈለገ ድንገተኛ ገጠመኝ በወጉ አጢኖ በመስኮት ነበር የወረደው። ሲዊዘርላንድ ከዛ በፊት ይህን ህግ የምታስተናግድበት ሁኔታ እንብዛም ሲሆን፤ በደረሰበት ሰዓትም ሌላ ልዩ መርኽ እንድትነድፍ በዝምታ አስተምሯታል። በማናቸውም ጊዜ ተሰናድቶ መጠበቅን በጭምቱ ተፈጥሮው ጭምታዊ ስብከቱን አሳክቷል።በመላ ኢትዮጵያ የሚገኙ ወገኖች ከወያኔ ሐርነት ትግራይ ደጋፊዎች በስተቀር በዜናው በቅጽበት በአንድ ድምጽ ጀግናችን ብለው አከበሩት፤ በወል ዘመሩለት። በወል አዜሙለት። በውል ጌጣችን፤ ክብራችን ብለው ቅኔ ተቃኙለት። በውል የነፃነት አርበኝነቱን ድርጊት ዕውቅና ሰጡለት፤ የጀግንነት ዕውቅናውንም ያለማወላወል ምንም የሃይማኖት፤ የፖለቲካ አስተሳሰብ ልዩነት፤ የጾታ ልዩነት፤ የጎሳ ልዩነት ሳይገድባቸው በውል በአንድ ድምጽ በአድናቆት ፈረሙበት። እናት ሲዊዘርላንድ ላደረገችው መልካም ነገር ሁሉ በአድራሻም አመሰገኑድንቆቹ። 

በባለቤትነት ስሜት የተከወኑ ተግባራት ሁሉ የኢትዮጵያ ጸጋ እና በረከት ናቸው። ወገኖቹ እክሌ ተከሌ ሳይባል በተለይም ኢትዮጵያዊነትን ውስጣቸው፤ ትንፋሻቸው፤ መቅደሳቸው ያደረጉት ትውልደ ኢትዮጵውያን ከሊቅ እስከ ደቂቅ ! ብለው ቁር፤ ሙቀት ሳይገድባችው ትንሽ ትልቅ ሳይባል ለጀግናቸው ክብር በሙሉ ልብ እና ተቆርቋሪነት ፍቅራቸውን በገፍ ለገሱት። የለገሱትንም ንጹህ ፍቅር ሰላማዊ ስልፍ በማድረግ፤ ፊርማ በማሰባሰብ፤ በግልም በጋራም ለሲዊዝ መንግሥት የወል ጥያቄያቸውን በማቅረብ፤ የተለዬ የግል ጸሎት በማድረግ ነበር። ጀግናው የሁሉም ልጅ፤ የሁሉም ወንድም ሆነ።ኢትዮጵውያን ማንታችን ኢትዮጵዊነት ነው ያሉት በአንድ ድምጽ ጀግናቸውን በመስማማት አጀንዳቸው አደረጉት።

ከወያኔ ሃርነት ደጋፊዎች እና ተባባሪዎች በስተቀር ኢትዮጵያ ሚስጢሬ ናት ያለ ሁሉም ሚዲያ እከሌ ተከሌ ሳይባል፤ ሁሉም ትጉሃን እክሌ ተከሌ ሳይባል፤ ሁሉም የፖለቲካ ሊሂቅ እከሌ ተከሌ ሳይባል፤ ሁሉም ጸሐፍት እከሌ ተከሌ ሳይባል፤ ሁሉም አክቲቢስት እከሌ ተከሌ ሳይባል፤ ውስጣቸውን ያለመሰሰት፤ ድምጻቸውን ያለተዕቅቦ ሚሊዮኖች በተፈለገው ሁኔታ ሁሉ ተጉለት። በጋራ የተደረገው ዘማቻ ሁሉ በሚገርም እና በሚደንቅ ሁኔታ መከራውን ለመገራት የቆረጡ ትውልደ ኢትዮጵውያን ሚሊዮኖች ነበሩ። አርበኛውን ረዳት አውሮፕላን አብራሪውን ሀይለመድህን አበራን ከወሰደው እርምጃ ጋር አብረው ሁሎችም በንዑድ ፍቅር አብረው ከተሙ። መልካሙን ነገር ሲታሰብ በመልካሙ ነገር የሚገኘው አቅምም የሰማይ ነው። በዚህ ጀግና ዙሪያ የባከነ የነፃነት ታጋይ መንፈስ አልነበረም። አቅማችን ሁሉ ተማከለ። አቅማችን ወጥ ሆነ። ድምጻችን አንድ ሆነ። ፍላጎታችን አንድ ሆነ። ሐገር አለኝ ኢትዮጵያ ለምንል ሁሉ ትጋቱን በፍቅር ተከወነ። አንድነቱ፤ ተቆርቋሪነቱ፤ ተገንነቱ፤ ዝማሬው፤ ሙገሳው፤ ውደሳው፤ አለህልን ማለቱ፤ አይዞኽባይነቱ አንድ ትውልድ ይፈጣራል። እጅግ ቀለማም፤ እጅግም ውብ፤ እጅግም ድንቅ ተሳትፎ ነበር የተደረገው። ታሪኩ በተግባር ጥልፍ የተሞናሞነ ነበር። ተባረኩ! ድንግልዬ ትጠብቃችሁ።
  • ሙሉልብ።

ይህ ሙሉልብ፤  ይህ የሁሉም ኢትዮጵዊ ነኝ የሚለውን ወገን በአህትዮሽ የእኛ የተባለለት ጀግና ነው። ሁሉም በአንድ ልብ ሆኖ በመንፈሳዊ ዓለም ከውስጡ በመነጨ ጸለዬለት። ፆመለት፤ ሰገደለት፤ ሱባኤ ያዘለት። እያንዳንዷን ቀን፤ ሰከንድ ደሙን ከደሙ ጋር አድርጎ የነቀፉትን፤ የተቃወሙትን ሳይቀር ፊት ለፊት በአደባባይ ሆኖ ሞገተለት፤ ቅራኔ ገባለት፤ ጠበቃው ዋስ ሆነው። ድንቅ ታሪክ ድንቅ የወልዮሽ ተጋድሎ፤ ውብ የኢትዮጵያዊነት ጸዳላዊ ብሄራዊነትን፤ ፍጽምና፤ ብሄራዊ ሰንደቅ ዓላማውን አረንጓዴ ቢጫ ቀዩን ያደመቀያከበረያዘመነ ከዘመን ዘመን ደመቆ ሊታይ የሚችል የአብሮነት ልዩ ጸደይ ነበር።
እኛዊነትን፤ ሰዋዊነትን፤ ተፈጥሯዊነትን ሳይሰስት ፍቅር የተለገሰው የወል የተደሞ ቅኔ ዛሬን ሠራ። እኔ ራሴ እጅግ ከማከብራቸው ቤተሰቦቼ የተለዬሁበት ያልተመቼ አጋጣሚ ነበርአሸባሪንእንዴት ትደግፊያለሽ ተብዬ ተወረፍኩኝ። በእነሱ አቅም ልክ ማሰብ ነበረብኝ። በእነሱ አእምሮ ልክ መኮድኮድ ነበረብኝ። ልባቸውን በልቤ ውስጥ ሊገጥሙ ብዙ ህግ ተላለፉ። ድንበር ጥሰው ማስጠንቀቂያውን አዥጉደጎዱት። ከትጋቴ ለማስተጓገል በእጅጉ በጣማራ ተፈታተኑኝ። እስከ መጨረሻው ደንበር ድረስ ሄደው ታገሉኝ።

ግን አልተሳካም። የፈጠሩትን ሳንክ፤ የገሃዱ ዓለም ጉዳይ ነበር። የሆኖ ሁሉ ያን ሁሉ አጣብቂኝ አሸንፌ ይሄው አለሁኝ እስከዛሬ ድረስ። እነሱም እኔን ያጡትን ያህል እኔም እነሱን አጥቻቸዋለሁኝ። ሰው ሊመጣም ሊቀርም ይችላል ህሊና ግን ቋሚ ዳኛ ነው። ሳላውቅ በምሰራው ልሳሳት እና ልጸጸት እንጂ አውቄማ ሊሆን አይገባም ነበር። የነበረው ማስፈራሪያ፤ የነበረው ጫና፤ የነበረው የአዬር ላይ ውጥረት እጅግ የከፋ ነበር። ግን ተቻለ። ዘመኑም አለፈ። እንዲያውም ያን ጊዜ በጸጋዬ ራዲዮ ፕሮግራሜ ቋሚ ፕሮግራም ነበረኝ፤ ለተከታታይ ዓመት በዬወሩ የካቲት 24 ቀን ዘሃበሻ እና ሳተናው ተባብረውኝ በብራናም አስበው ነው። የጠ/ / አብይ አህመድ መድህን ንግግር የኢትጵያ እናቶች ሲያወሱ የእኔን መከረኛ ደግ እናት ቆይኝ ብዬ የእሱን ብልህ እናት / የዝባለም እምሩን አሰብኩኝ። ወንድማቸው ባልተወቀ ሰው ተገድሎ፤ ባለቤታቸው ታስረው፤ ልጃቸው ደግሞ በዚህ ሁኔታ መሆኑ ያቺ ቅጽበት፤ ያቺ የቀራንዮ ሰሞናትን በምን ሁኔታ እንዳሳለፉ ከውስጤ አሰብኩት። እንዲህ ናቸው የኢትጵያ እናቶች/ ሴቶች በአንድ ሰሞን ባለቤታቸው እስር ቤት፤ ወንድማቸው ባልተወቀ ሰው ግን የታቀደ ግድያ፤ ልጃቸው ነፃነት ፍለጋ ስደት

የሚገርመው ነገር ኮሽ አይሏም ሲዊዝዬ ከእናትም እናት ሆና ሽሽግ፣ ሽክፍ አድርጋ አደራዋን ስትወጣ ፎቶውን እንኳን እንዳይወጣ፤ በቀጠሮው ቀን ለሚዲያ እንዳይጋለጥ በጥንቃቄ የተገባውን ሁሉ አደረገችለት፤ እያደረገችለትም ነው ብዬ አስባለሁኝ። እናት ሲዊዝ እንደ ተፈጥሯዋ ያደረገችው ብርቱ ጥንቃቄ ነፈስ በላ የአራዊት ጋንታ እዚህ ድረስ ልዑኩን ልኮ ለማረድ ቢማጸንምሞት በህግ በጸደቀበት ሐገር አሳልፌ አልሰጥም ብላቅንጡን አብራ መለሰችው። እናት ዓለም ሲዊዝ ራሷ ጠበቃ ሆና፤ ራሷ ጠበቃ ቀጥራ ከመከራ ሁላችንም አዳነችን። ከጥቃት ታደገችን። በመላ ዓለም የሚገኙ ወገኖችንም ሰላም እንዲያገኙ አደረገች። የተመሰገነችው መነኩሲት ሲዊዝዬ።

ዛሬ ላይ ሆኜ የውርሰ ጽናቱን የአቶ አንዱዓለም አራጌን ቁመና ገጹን፤ የአባ ትርጉሙን ጋዜጠኛ እስክንድርን ዓይኑን፤ እና ቀደም ብሎም የሊቀ ትጉሃኑን የጋዜጠኛ ተመስገን ደሰላኝ እርጅና፤ ጉስቁልና፤ መገርጣት፤ በሽበት መወረር ስመለከተው ይሄ ወጣት ጀግና ቢያገኙት ምን ሊያደርጉት እንደሚችሉ ሳስበው ይሰቀጥጠኛል። አሁን እራሱ ልለምደው አልችልም የሰው አዎሬዎች በምን ሁኔታ ሰውን ለማሰቃዬት እንደ ተፈጠሩ፤ ምን ዓይነትስ መልክ እና ቁመና እንዳላቸው፤ እንደ ሰው እንደ እኛ ስለመፈጣራቸው ሁሉ ያጠራጥረኛል። አሁን አሁንም እማ ከሥር ቤት የተፈቱትን አርበኞቼን ፎቶቸውን ማዬት እራሱ እዬከበደኝ ነው። የቁም ሰማዕቶችን ፎቶ እዬሸሸሁት ነው። ሆዴ ይረብሽብኛል። እንግዲህ እኒህ ከነሙሉ አካላቸው ግን አጥንታቸውን ብቻ ያገኘናቸው ናቸው። ጭራሽም አካላቸው የጎደለው ደግሞ፤ በክራንቻ፤ አልጋ ላይ ያሉ፤ በሚበሉት ምግብ ላይ መርዝ እዬተጨመረ የተሰጣቸው የት እንዳሉ እንኳን የማያውቅዩ ዐዕምሯቸውን የሳቱ ወገኖቻችን ሌላው የመከራዎች ሁሉ፤ የፍዳዎች ሁሉ ሾለቄ ነው። ተፈተን። በዚህ ሁሉ የኢትዮጵያ እናቶች አብረው ይቀቀላሉ።

ልበሙሉ ጀግናው ከእጃቸው ሳይገባ ቀደማቸው። እስኪ መጨረሻውን ያሳምረው። መቼም የእሱ ነገር ልብ አያስጥልም እናመርዞች ናቸው። በምን ቀን እንደተጠፈጠሩ፤ ስለምንስ እንደተፈጠሩ የቅዱሱ መጸሐፈ ሄኖክ ሰማያዊ ሚስጢር ይፈጸም ዘንድ እርግማኑም … „በዚህ ዓለም ክፉ ልጆች ይሆናሉ፤ ክፉ ልጆችም ይባላሉይላል፤ በቀጣዩም ምዕርፍ ቁጥር ላይ እርግማኑሞታቸውም ሁሉ ሞት ይሁንይላል። አሜን!

ጀግና ረዳት አውሮፕላን አብራሪ ሀይለመድህን አበራ እግዚአብሄር ምን ቢወደው ይህን እንዳሰመለከተው ሳሰበው ረቂቅ ጸጋውን፤ ረቂቅ ተፈጥሮውን፤ ረቂቅ ሁለመናውን ተመራምሮ ለመድረስ ይቸግረኛል። በደረሰበት ማሳደድ፤ በደረሰበት መከራ፤ የረዳት አውሮፕላን አብራሪ ሃይለመድህን አበራ አጎት / ዶር እምሩ ስዩም ታክሲ ውስጥ ደመ ከልብ ሆነው መቅረታቸው ላያንስ በማስፈራራት እና በጫና ብዛት ቀድመውት ቢሆን ኖሮ ይህን ምርጥ ወጣት እናጣው ነበር። በቀጥታ ኮተቤ ክንፈ የደህነንት ማሰቃያ ቦታ ነበር እሚቀብሩት የነበረው።
  • ሰብዕናን ማትረፍ ከቁስ በላይ ነው።

በአሳቻ ሁኔታ እዬጠበቁ በተጠናከረ መረብ ሲያሳድዱት፤ ማስጠንቀቂያ ሲሰጡት፤ የገዛቸውን አዳዲስ ዕቃዎቹን እንኳን ሳይጠቀምበት ለቆላቸው ወጣ። ቢያቅድ ኖሮ አዳዲስ ዕቃዎች አይገዛም ነበር። በሌላ በኩልም አቅዶ ሌላ ቦታ ሐገር ሄዶ ሰላማዊ ኑሮውን መኖር ይችል ነበር። የወላጅ እናቱ ወንድም እሱንም እንደ አባት ያሳደጉት የሐገር ሐብት / ዶር እምሩ ስዩም ለኢትዮጵያ የነፃነት ትግል አስፈሪ፤ ምንአልባትም ዛሬ ወያኔ ሃርነት ትግራይ አንድ ቀን መሪ ተፎከካሪ ሆነው ሊወጡ ይችላሉ ብሎ በስለላ መረቡ ካጠመዳቸው አንዱ ሊሂቅ ናቸው። በተለይም በሰላዩ በሳጅን በረከት ስምኦን ልዩ የዘመቻ ትእዛዝ መረብ የተከወነ ነው። አቶ በረከት ስምዖን እያሉ ልብ ተጥሎ አይተኛም። ሁሉም ራሱን መጠበቅ አለበት። ከጸጸት በፊት ራስን መጠበቅ። ኢትዮጵያን ሰው አልቦሽ አድርጎ ለመመንጠረ ታስቦ እና ታልሞ 27 ዓመት በዚህ መልኩ ነው ሊሂቃን ያተጨዱት፤ የተሰወሩት፤ የተሰደዱት። ጊዜ መልካም ነው ዛሬ የሳጅን በረከት ስምዖን መንፈስ የፈራው ነገር ሁሉ ደረሰ። ካለሰበው ቦታ፤ በላሰበው እና ባላቀደው ሁኔታ አቅም ጎልቶ ወጥቶ እዚህ ተደረስ። እሳቸውን ቅርሻ ዝገት የሚረከብ ጠፋ። ይህም ሆኖ እነሱን ታምነው መዘናጋት መቼውንም ቢሆን፤ ሊታሰብ አይገባም። እኛ የማናውቃቸው ብዙ ነገሮች ተፈጽመዋል። ብዙ ሊሂቃን የውሃ ሽታ ሆነው ቀርተዋል። በስደትም አያርፉም ባለ በሌለ ሃይላቸው ሁሉንም አማራጭ ይሞክራሉ። ያሳድዳሉ። እረፍት የሚባል የላቸውም፤ ርጉሞች።

የተሰወረው በቀል እና ሴራ እንዳለ ሆኑ አሁን ደግሞያ ለነፃነት የተደረጉ ተጋድሎዎች ሁሉ በአደባባይ ክብር፤ ልዕልና አገኙዛሬ። የነፃነት አረበኞቻችን ሁሉ ለከፈሉት ማንኛውም መስዋዕትነት ዕወቅና ተሰጣቸው። ለደረሰባቸው ማናቸውም ሰቆቃ፤ የሥነልቦናዊ ድቀት እና መከራም በአደባባይ እንደ መንግሥት ይቅርታ ተጠዬቀበት። ለዚህ ያበቃን አምላክ የተመሰገነ ይሁን። መጨረሻውን ያሳምረው። አሜን! የመጨረሻ ጊዜም ያድርግልን። አሜን! ነገ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር 12.04 ደግሞ የስቢል ድርጅቶች እና ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር / ሚር ዶር አብይ አህመድ ውይይት እንደሚያደርጉ ዜና ነገር አዳምጫለሁኝ። እሰዬው ነው ማለፊያ ነው። የመጀመሪያ አጀንዳ መሆናቸው በራሱ መልካም የህሊና ስንቅ ነው። ደቀዋል። ቢሯቸው ተዘርፏል። በአዋጅ ፈርሰዋል። ታስረዋል፤ ተገድለዋል። ተሳዳዋል። ተሰደዋልም።
  • ደወል።

ጀግና ሃይለመድህን አበራ ቀዝቀዝ ብሎ ለወያኔ ሃርነት ዘረኛ አገዛዝ ባርነት ያደገደገውን መንፈስ ሁሉ እንዲንነቃቃ በክንውኑ የነፃነት ደወለ ደወለ። እርምጃ እንደ ዘመኑ ለመኖር ላልተፈቀደለት ለአዲሱ ትውልድ እዮራዊ ጥሪ ለማቅረብ ነበር በጸጥታ ውስጥ መሆንን በተግባር ያሸለመው። የፓይለቱ ጠንቃቃ እርምጃ እንዳለፈው የመቀሌ አካባቢ የመሬት መንቀጥቀጥ እዮራዊ ደወል ነበር። ነፃነቱን ተቀምቶ፤ መቀመጫ በማጣቱ ራሱን ለመከላከል ብቻ ሳይሆን በዘመኑ ሊያገኝ የሚገባው የህሊና ሰላም የመነጠቁ እልህ እና ቁጭት፤ የሌሎችም ስለመሆኑ መርምሮ እና ተረድቶ ነበር ያነን የእንብኝ አልገዛም ባይነትን ሰላማዊ እርምጃ የወሰደው። ስለሆነም ወንጀለኛ አይደለምለእኔ፤ ሰላሙን የነሳው ነው ወንጀለኛ። 

የተነሳበት ዓላማ የነፃነት ትግል ነው። ይሄው ዛሬስ በውስጡ በራሱ ኢህአዴግ ውስጥ በቃኝ አጎምርቶኢትጵያዊነት ሱስን ነውንተገላግሎ አደራውን ለመወጣት መንገድ ጀመሯልአይደል? የዚህ ሁሉ ጥረትና ድምር ውጤት ነው የመጋቢት 24ቱን ፍስሃቃለ ምህዳንያቋደሰን። እያንዳንዱ በግል፤ ሁሉም በጋራ በአደረገው ጥረት፤ ልፋት፤ ድካምና ብርታት፤ ሐገር ቤት የሚገኘው ወገን በከፈለው 27 ዓመት የመኖር እግዳ ያስገኘው ውጤት ነው የዛሬው ድል። በውርርስ፤ በቅብብል፤ በተከታታይ የተካሄዱ ማናቸውም የሐገር ውስጥ እና የውጪ ተሳትፎዎች ተጠራቀመው ይህን ቀን አዋለደ። እጅግ የሚመስጠው ሽግግሩ ሰላማዊ መሆኑ፤ የአፈፃፀሙ ሥርዓቱ ሁሉ የሰከነ፤ የተሟላ መሆን በውንም ፈጣሪ አምላካችን የእኛ ቀርቶ እስር ቤት የካቴና ስንቅ የሆኑት፤ ክብራቸው በማያምኑ አህዛቦች የተዳፈረው ሰማዕትነት ጸሎት ዕንባ ፍሬ ነው። ሁለቱም ሃይማኖቶች እስረኞች ነበሩ። ኦርቶዶክስ ተዋህዶ እና እስልምና። በህግ ተሳሩ። በህግ ተደበደቡ። በህግ ተቀጠቀጡ። ዕንባቸው ግን እዮርን አንኳኳገዳማት በመከራ ተንገበገቡ።
  • የሚሊዮኖች ጠበቃ ዶር. ሸክስፒር ፈይሳ።

እጅግ የማከብራችሁ የሐገሬ ልጆች ዛሬ አንድ ብሄራዊ የተግባር ጀግናዬን ላመሰግን ነው ብዕሬን ያነሳሁት። እሳቸውን የመሰለ በህግ አውጪው፤ በህግ ተርጓሚው፤ በህግ አስፈጻሚው ማእከላዊ አካል እንዲህ ዓይነት ሙሉሰው፤ ሙሉስብዕና ያለው ባለሙያ ኢትዮጵያ ቢኖራት ፍትህ ኢትዮጵያ መሬት ላይ ትሞሸር ነበር። ከእናትም እናት፤ ከወንድምም ወንድም በላይ በመሆን ብሄራዊነትን በራሳቸው ላይ ጭነው፤ ብሄራዊ ሃላፊነት በቆራጥነት የተወጡ ምርጥ የኢትዮጵያ ጌጥ ናቸው ጠበቃ ዶር. ሸክስፒር ፈይሳ። በራሳቸው ወጪ እና ጊዜ አሜሪካ ተነስተው እዚህ ሲዊዘርላንድ ድረስ መጥተው ብሄራዊ ጀግናችን አከበሩት። ሁኔታውን ለማጥናት የቆረጡ አንቱ ብሄራዊ አርበኛችን ናቸው። ነግ ለእኔ ማለትም የተጋባ ነው።አለሁላችሁ! አይዟችሁ!“ የሚል ስደት ምድር ምድራዊ መላዕክ ነውለእኔ። ብቸኛውም ጠያቂውም ናቸው። መወለድ ቋንቋ ነው ይላል የጎንደርዬ ኗሪ። ስደት ላይ እኮአይዞኽ፤ አይዞሽአትገኝም። ጸበል ነው። እንኳንስ ጥሪኝ አፈር እና የሐገር ሽታ አገር አቋርጦ እንዲህ ጉዳዬ ሲል ቀርቶ። እግዚአብሄር ይመስገን ልክ እንደ ዶር አባንግ ኢትዮጵያ ሜቶ አሉን የተከበሩ የህግ ባለሙያው ዶር ሼክስፔር ፈይሳ። ለክፉ ቀናችን ድብቅ አድርገን ብልቦናችን መስጥረን የያዝናቸው።

ያን ቅን እርምጃ ሲወስዱ የወያኔንየአሸባሪነትንክስ አልቀበለውም በማለት ነበር የደፈሩት። እሱንአሸባሪ ካላችሁት እኔንም በሉኝ፤ እኔም ረዳት አውሮፕላን አባራሪ ሃይለመድህን አበራ ነኝነበር ዕድምታው። ለወንድማቸው የፈጥኖ ደራሽ ተልዕኳቸውን የከወኑት በርህርህና ነው። ዛሬ እሳቸው ጀግናዬ ያሉት አንበሳ ሐገሩን ጥሎ ህጋዊ ሆኖ መሰደድ እዬቻለ፤ ስንት አማራጭ እያለው፤  ቋሚ ቪዛ እያለው ግን መምህር ሊሆን የሚችል፤ የወጣቱን መንፈስ ለበቃኝ አደራ በመንፈስ ለማደራጀት፤ በተግባሩ መከረ፤ በእርምጃው ትልሙን አቀናበረ፤ በሂደቱ የነፃነት ተጋድሎን የጥበብን መጠን የምርምር ማዕከል ፈጠረ፤ ብብልህነቱ ዓለምን አስደመመ። የእሱን መሰል አርበኞቻችን ተጋድሎ መሆን መቻል ዛሬን አሳምሮ ሠራ። ጀግና / አውሮፕላን አብራሪ ሃይለመድህን አበራ የሚሊዮኖች የነፃነት ድምጽ ሲሆን የዚህ ሚሊዮን ድምጽ የፊት ለፊት ልዩ ጠበቃ ደግሞ ዶር ሸክስፒር ፈይሳ ናቸው። ቆራጥ ናቸው። አዛኝ እናት አንጀትም ናቸው። በፍጹም ሁኔታ መከታጋሻ እና ጥላከለላም ናቸው። ይኑረልን። ክፉም አይንካብን።
ዛሬ ሌላ ቀን ላይ ነው ያለነው። በተለይ እንደ ህግ ሊቀሊቃውንትነታቸው ዶር ሼክስፒር ፈይሳ የዛሬውን የኢትዮጵያን ተጨባጭ ሁኔታ ከስሜታዊነት በጸዳ ሁኔታ ትክክለኛ ቁመና እናዳለው አይጠራጠሩትም ብዬ አስባለሁን። 

ምክንያቱም በዛ በክፉ ቀን ለወንድማቸው ራሳቸውን ሲገብሩ የማስተዋላቸውን ልኬታ ያመላክት ስለነበረ። አማላካችን ቅንነታቸውን ተመልክቶ፤ እሳቸውም ራሳቸውን የቀለጡበት ቅናዊ መስዋዕትንት ዛሬ አፍርቶ እንሆ የምሥራች ተደመጠ። ውጥን ነው፤ ግን በር መከፈቱ በራሱ መልካም ነገር ነው። ፈሶ አልቀረም ድካማቸው። ባክኖ አልቀረም ልፋታቸው። ፍሬ አፍርቷል። ስለዚህምእንኳን ደስ አለዎትየታገሉለት ዓላማ አንድ እርምጃ ወደፊት ተነቀሳቅሷል። ትግል አያልቅም ነገም ይቀጥላል። ስለምን? የሰው ልጅ ፍላጎት ሙሉ ለሙሉ ማርካት ስለማይቻል። ትግል እና ውጤቱ የሂደት ቅምረትም ስለሆነ። ዛሬው ባለው ሁኔታ ተስፋ ለቅኖች ጥምልም ያለ ሳይሆን፤ ወይንም ቀጥ ያለ ብቻ ሳይሆን በፈተና ውስጥ ግን የማድረግ አቅሙ የፈጣሪ የሆነ ረቂቅ መንፈስ አለ ኢትዮጵያ ላይ።
ስለዚህም እጅግ የማክብረዎት፤ ሁልጊዜም እማስበዎት ጠበቃ ዶር ሼክስፒር ፈይሳ እርሰዎም ሆኑ ከወያኔ ሃርነት ደጋፊዎች በስተቀር ቅኖቹ የታተሩበት መሰረታዊ የነፃነት ታገድሎ በአዲሱ የጠቅላይ / የመጀመሪያ ንግግር ዕውቅና ስለ አገኘ ተስፋዎት ምልካም ይሆናል ብዬ አስባለሁኝ። እጅግ የሚገርም፤ የሚደንቅ፤ የሚያስተምር የተግባር ክንውን ነበር የፈጸሙት። ምዕራፍ ነዎት። ዘመን ነዎት። የፊደል ገበታ ነዎት። በዝምታ ውስጥ ተግባር እንዲህ አለሁልህ ተብሎ ሲገኝ ለዛውም ስደት ላይ ለሚገኝ አንድ ብቸኛ ሥጋና ደም ከሥጦታዎች ሁሉ ታላቅ ሥጦታ ነው። ራስን ረምጦ፤ ራስን ለማንኛውም ጥቃት አጋልጦ፤ ራስን እንዲህ ፈቅዶ መገብር ክቡር ተግባር ነው። እናም የእኛ የክብር ተክሊል ነውት። ተግባረዎት ኢትጵያዊነትን በብዙ ሁኔታ ያለቀ ምስክር ነው።እንኳንም ደስ አለውትበድጋሚ። እኔም ንግግሩን ባደመጥኩበት ሰዓት እዚህም ያለውን ጀግናዬን በምለሰት አስታውሼ፤ እርስዎም እንደ እኔው ጉዳዬዎት ነውና የእኔ ጀግናም ሲዊዝ አለኝ ማለተዎት እንደማይቀር ነው። ብቸኛውን ጀግና ወንድመዎት ነውና ስሜቱን ይጋሩታል ብዬ አስባለሁኝ። እሴቴዎትን ፈቅደውና ወደው አፈሰውበታል። በውነቱ ትውፊት ነዎት። የቁርጥ ቀን ቁርጠኛ።
ልብ ላለውማ።

ይህ ጀግና ሲዊዘርላንድ ጄኔባ ሲገባ ሰላማዊ በሆነ ሁኔታ ነበር። ማላዥያስ? ዓለምን ያሳተፈ የመከራ ጊዜ ነበር። የፈሰሰው ጊዜ፤ መዋለ ንዋይ፤ የነበረው የተጠናከረ ዘመቻ መረጃውን ፍንጭ ለማግኘት የነበረው ድካሙ፤ ብክነቱ እጅግ መጠነ ሰፊ ነበር። ፍለጋው በሚሊዮን የሚቆጠር ሃብት ፈሶበታል። በዓመቱ በጀርመን ዊንግ አውሮፕላን የተፈጸመው አሰቃቂ ሁኔታም የጠፋው ህይወት፤ የባከነው ንብረት ብቻ ሳይሆን አዬር መንገዱ ለተጎጂዎች ሁሉ በነፍስ ወከፍ የከፈለው ካሰ ሲሰላ ይህ የእኛ ጀግና የፈጸመው ገደል አውሮፕላኑን እራሱ በሥሙ የሚያስጠራ፤ ግቢው ሁሉ በእሱ ፎቶ በክብር ሊቀመጥለት በተገባ ነበር እንኳንስ ሊያስከስሰው። እንኳንስ ሊያሰወቅሰው። የሐገርን ክብር የጠበቀ የነፃነት ተጋድሎ ነው ያደረገው፤ ፍርዱ የሚገርመው አንድም ቀን አፋቸውን ሞልተው እስከ ደጋፊዎቻቸው ድረስ ሐገሬ በማይሉ ፍጥረቶች። የዚህ ቀንበጥ ልቅናው፣ ብልህነቱ፣ ልበ ሙሉነቱ፣ ድፍረቱ፤ ሰብዕናው ዘመን ይተርጉመው።

ውስጡ ራሱ ለስላሳ ነው። በቤተሰቡ፤ በናዋሪዎቹ፤ በጎረቤቶቹ ሁሉ የተመሰገነ ነው። የአባት አደሩን ዶሮ ለማረድ የማይደፍር ይህ ሩህሩህ ለቤተሰቡ ታዛዥ ወጣት ሐገር አጥቶ፤ መቆሚያ ብትን አፈር አጥቶ፤ መቀመጫ መቆሚያ አጥቶ ያልፈቀደውን ተገዶ ፈቀደው። ስደት ላይ እስር ቤት ከባድ ነው ለአንድ ቀንበጥ። እናት እህት ወገን ቤተሰብ በሌለበት። ስደቱ እራሱ እስር ቤት ነው እንኳንስ እስር ቤት ተጨምሮበት። ግን የፈቀደው ስለሆነ፤ ፈጣሪ አምላክ፤ እናቱ ድንግል ማርያም፤ ጻድቃን ሰማዕታት ጥበቃቸው አይለዬውም፤ ያጽናናዋል ይደግፋዋል። የተፈቀደለት ይህ ህይወት ነው አንድ ቀን ብርሃን ይወጣለታል። ትስስሩ ደግሞ ከመጸሐፍ ቅዱስ ጋር ስለሚሆን ያልፋል እንዳለፈ ሁሉ።

ቂመኞች እና ሸረኞችን፤ ዘረኞች እና ተንኮለኞችን አምላካችን እራሱ በጀመረው ጥበብ መልክ ያስይዘዋል። ይኸው የተኖረ ተኑሮ፤ የተለፋ ተለፍቶ፤ የተደከመ ተደክሞ አሁን እኮኤች አር128 በአሜሪካን ምክር ቤት ፀደቀ።ሃይማኖት ያለው፤ በዕምነቱ ለፀና ወገን የመቀሌው የመሬት መንቀጥቀጥ ደወል እና የሌሊቱ የሥልጣን ሽግግር የትንሳዔ ዜና፤ ከዛ ቀጥሎ የተፈጸሙ ክንውኖች ሁሉ በፈጣሪ ጥበብ እራሱ ፈጣሪ ወርዶ እዬሠራው መሆኑ አመሳካሪ አያስፈልገውም። ሁሉ ነገር ተገጣጠመ። በዕንባ መሃል ሳቅ
ፈጣሪ አምላክ ቃልኪዳኑን እዬፈጸመ ነው፤ እኔ እማዬው እንደዚህ ነው።

እሱ የወደደው ነው እዬተከወነ ያለው። የዕምነት ጽናት ካለ ነገም ከነገ ወዲያም የምሥራች ይኖራልእዮባዊነትን ለሰነቀ። ከመቅድሙ ጀምሮ በቅደም ተከተል ባልተለመደ ሁኔታ እዬተከወነ ያለው ተግባር በራሱ በሱባኤ ልንቀበለው እና ልናከብረው ልንከባከበውም ይገባል። ተያያዥ ነገሮችን፤ ተወራራሽ ነገሮችን ላስተዋላቸው፤ የእኔ ላለ በእውነት አምላክ አለኝ ብሎ ለሚያምን ፍጡር ሂደቱ የሰማይ ነው። በሰውኛ ዳንቴል እንዲህ እና እንዲያ እያደረገን ከማወጃወጅ ፈጣሪን እያመሰገኑ፤ የሚችሉትን በሚችሉት መልክ እዬቀጠሉ ታምራቱን ዕወቅና መስጠቱ የተገባ ይመስለኛል። መደገፍ አቅም መዋጣት። ቢቀር ሳር እየመዘዙ ሰላሙን አለማወክ። ልቡ ከተኖረበትሌላው ደግሞ የሚችል በሚችለው መንገድ መቀጠል። ትግል እኮ ቀጣይ ነው አንድ ቦታ በበቃኝየሚተው አይደለም።
  • በምልሰት አንዳንድ ነገሮችን ለማስታዋስ።

የማከብራችሁ የሐገሬ ልጆች …. የተከበሩ ዋቢያችን፤ የክፉ ቀን ደራሻችን፤ አይዟችሁ ባይ የተግባር ሙሴያችን የጠበቃ ዶር ሼክስፔር ቃለ ምልልስን ለጥፌዋለሁኝ። ለእኔ ድርሳኔ ነው። ሲደክመኝ እርፍ የምለው በዚህ ቃለ ምልልስ ነው። ልክ እንደ ሜዴቴሽን ነው የማዬው። በሦስት ምክንያት። አንደኛው ይህ ጀግና ለሲዊዝ ለምንገኝ ኢትጵውያን በተለዬ ሁኔታ እንግዳችን ነው፤ ስለሆነም ሁልጊዜም እንደ ዜጋ ልናሰበው ይገባል ባይ ነኝ፤ ትውልዳዊ ድርሻም አለብን። ሁለተኛው የዋቢያችን የጠበቃ ሼክስፒር ትንተና መምህር ነው። ማወቅ ጠቃሚ ነገር ነው። ሦስተኛው ቃለምልስ ያደረገላቸው የኔታ እንደልቡ ወርቁ የሂደቱ አፈጻጸም ዘይቤው ሥነምግባሩ የተለዬ አቀራረብ ነው ያለው። ጉዳዩን በባለቤትነት እዬከወነ፤ በባለቤትነት የእኔ ያለውን የወንድሙን ጉዳይ ከእሱ አርቆ፤ ከስሜታዊነት በፍጹም ሁኔታ ወጥቶ ከኢሞሽናል ሽርፍራፊ ነገሮች ጋር ሳይወዳጅ፤ እጅግ በሚመስጥ እና የጋዜጠኝነት ሙሉ ሥነምግባር በአሟላ ሁኔታ ነበር ቃለ ምልልሱን ያደረገው። ይሄ መቼም በእኛ ያልተለመደ ነው። ዶቼ ቬሌ ላይ ሁለት ሴት ጋዜጠኞች ሲያወያዩ፤ ቃለምልልስ ሲያደርጉ ይህን ሙሉ ሰብዕና በቋሚነት አይባቸዋለሁኝ። የቀደሙትም እንደዛ ነበሩ። SBS መንገዱ ይሄው ነው። ለዚህ ነው አክብሮቱ የሚሰጠውም።

ከራስ ስሜት ጋር እንዳይጠጋጋ አፈፃጸሙን በርቀት እንዲሆን መርኸ ማድረግ የጥቂቶች ጸጋ ብቻ ነው። መርህኸም ነው የምትማሩት። የሆነ ሆኖ ይሄን ሙሉ ጣዕም አገኝበታለሁኝ ከዚህ ቃለ ምልልስ። ከራስ ስሜት፤ ከራስ ራዕይ፤ ከራስ የፖለቲካ አቋም እንዲህ ርቆ ጥርት ባለ ሁኔታ ቃለ ምልልስ ሲካሄድ ለሚዛን ይመቻል፤ ተከተሉኝ ብሎ አይጫነም፤ አድማጭ ዳኝነት ዕድል ይሰጣል። በጸዳ ሥነምግባር ሁናቴ ነበር ቃለ ምልልሱ የተከናወነው። ጀግናው በፈጸመው ብልህነት ልክ የሚመጥን ነበር ማለት እችላለሁኝ እኔ።ግልጽና አጭር ጥያቄዎች ነበሩ። ቅርንጫፍ ጥያቄዎች እዬተፈጠሩ ዋናውን አውራ ጉዳይ እንቅፋት አልፈጠሩበትም። በጠያቂውም በመላሹን የነበረው ግንኙነት ሰውኛ፤ ገለልተኛ፤ መርኽኛ፤ ማዕከላዊ ነበር። አይሰለቸኝም። ስለዚህም አዳምጠዋለሁኝ።

ይሄ በጣም የሚያነስን ነገር ነው። የአስተውሎት የሙያው ምግባር መጨፈላለቅ፤ መጫን ብዙ ጊዜ በአብዛኞቹ አያለሁኝ። ቃለ ምልልስ አድራጊዎችም ሆነ አወያዮች እንዲሁም ተወያዮችም መድፊያቸው ጎጇቸውን ነው የሚያደርጉት። አንዳንድ ጊዜምነው የጤና?“ እስኪአሰኝ ድረስ ብስጭትም፤ ውርጭትም አለበት። ጥቂቶች መኖራቸው እንደተጠበቀ ሆኖ።
በውነቱ በዚህ ቃለ ምልልስ ሰው ሊሰለጥነበት ይገባል፤ በጣም ሰውኛ ነው፤ ወገንተኛነቱም መርሃዊ ነው። ገለልተኛ ሆኖ ነበር ጭብጡን ያስተናገደው። በባህሪው ራሱ ችሎት ነበር። አድማጩ ላይ ተጽዕኖ አይፈጥርም። ጭራሽ የፕሮፖጋንዳ ንፈስ አልዞረበትም። ስለሆነም ለጥፌዋለሁኝ።

https://www.youtube.com/watch?v=MhduiSgK8WE
Ethiopian Airlines Co-pilot case: Interview with Attorney Shakespear Feyissa
ሌላው የመለጠፊ ምክንያት ያን ጊዜ እስር ቤት የነበሩ፤ በተለያዬ ሁኔታ ከነፃነት ትግሉ ጋር ያልነበሩ፤ እንዲሁም አዲስ ገቦችም ሊኖሩ ስለሚችሉም ጹሑፌን በተሟላ ማመሳከሪያ ማቅረቡን መርጨለሁኝ። እዚህም ዓራት ዓይናማ 35 ዓመት ወጣት ጀግና እንዳለን ማሳወቅ ያስፈልጋል። ከጀግኖቻችን ዝርዝር ውስጥ መኖር አለበት፤ ሌላው ብርቱ / አብዲሳ አጋ፤ ትንታግ አርበኛ ዘራዕይ ደረስ እኮ ነው።

በሌላ በኩል ኢትዮጵያም ለእኔ አዲስ ምዕራፍ ላይ ስለሆነች እንደዚህ ያሉ ጉዳዮች ባሊህ ባይ አልባ ሆነው ባክነው መቅረት ስሌለባቸው፤ እግረ መንገዴንም በዚህ ዙሪያ ነገ ተመሳሳይ ችግር እንዳይከሰት በትህትና ማስገንዘብ እፈልጋለሁኝ፤ ከሁሉም በላይ ኦህዴድ ላይ ጽኑ ዕምነት ስላለኝም፤ ሥርጉተ ሥላሴም ለማውያን ስለሆነች ይህን አብይ ጉዳይ የልባቸው አጀንዳ እንዲያደርጉት ዝቅ ብዬ ላሳስባቸው እወዳለሁኝ። ልብ አላቸው አቅም አላቸው ብዬ አስባለሁኝኦህዴዶች፤ የአቶ ገዱንም መንፈስም እንዲሁ ጀግናውን መዘንጋት የለበትም። የተጋባውን ክብር እና ሞገስ ሊሰጠው ይገባል። የሰባዕዊ መብትም ተሟጋች እኮ ነው። ያን ያህል ነፍስ ማዳን፤ የዓለምን የሃዘን መከራ መቀነስ ከዚህ በላይ ሰብዕዊነት ምን አለና? ለእኛም ጉልህ የበራ የተጋድሎ ታሪካችን ነው።
  • ብልህ ጉዳይ።

ሌላው ብልህ ጉዳይ በጀግና / ደመቀ ዘውዱ የደረሰው የግፍ እና የማንአህሎኝነት ጥቃት እና መከላከል እርምጃ ዓለም ዐቀፍ አዎንታዊ የህግ ጥብቃ እንዳለውም እግረ መንገዴን ማስገንዘብን ወደድኩኝ። የተገባ እርምጃ ነበር።
ኢትዮጵያ ህግ ናት።

አዎን! ኢትዮጵያ ህግ ናት። እናት ሐገር ኢትዮጵያ በተፈጥሮዋ ህግ ናት ብዬ አምናለሁኝእኔው። ይህን የምለው ያለምክንያት አይደለም። ውሃዋ ህጋዊነት አጠጥቶ ነው የሚያሳድገን። አዬሯ ህጋዊነት መግቦ ነው መንፈሳችን በሙሉ ስብዕና የሚያደራጀው። በዬትም ቦታ ኢትያጰውያን ያለን ረቂቅ ጸጋ ከሌሎች ሐገር ስደተኞች ጋር በብዙ ነገር እንለያለን። ማህበራሰባችንም እንዲሁ። ሲፈጠር ህግ አዋቂ ሆኖ ነው የሚፈጠረው። ትምህክት አይደለም የእውነት ነው። በወያኔ እብሪት እና ማን አለብኝነት የፈረሰው የአንድነት ፓርቲ በዘመኑ ጠንካራ ነበር። ጉዳዩ በተፈጸመበት ወቅት ባህርዳር ተልዕኮ ነበረው የአንድነት ፓርቲ። ለዛ በሄዱበት ጊዜ ነበር ይሄን ቃለ ምልልስ ከጀግናው ረዳት አውሮፕላን አብራሪ ከሃይለመድህን አበራ እናት ከክብርት / የዝባለም እምሩ ጋር ቃለ ምልልስ ያደረጉት።

የሚገርሙ እናት ናቸው። የቀለም ትምህርት አልተማሩም። ልጆቻቸው ሁሎችም ከከፍተኛ ደረጃ የደረሱ ናቸው። ያው ታውቃላችሁ አይደል ናፍቆቶቼ የመጀመሪያው የህይወት / ቤት ነው መኖሪያ ቤት ነው። መምህሯ ደግሞ እናት ናት። እናት የመጀመሪያዋ የህይወት / ቤትም መምህርም ናት።

የጀግና እናት ክብርት / የዝባለም ስዩም ቀደም ብዬ ከላይ ለማያያዣ እንደተጠቀምኩበት ወንድማቸው በግፍ በአደባባይ ገደዩ ሳይታወቅ የተገደለባቸው፤ ደመ ከልብ ሆነው ነው የቀሩት፤ ባለቤታቸው በማያውቁት ሁኔታ ለእስር ተዳርገውባቸዋል፤ ልጃቸው መቀመጫ አጥቶ በሦስተኛ ዜግነት እንኳን ሊያስቀምጡት አረመኔዎች ስላልቻሉ ሐገር ጥሎ ሲሰደድ ሁሉንም መከራ ተነባብሮ ነበር አንድ ሰሞን የመጣባቸው። በወንድማቸው ሞት ቀብር አለፋ ደልጊ ሲባክኑ፤ ባለቤታቸው እንዳያጽናኗቸው ታሥሩባቸው፤ ልጃቸው ደግሞ ሌላ ታምር ሠርቶ ሲዊዝ ገባ፤ ሦስቱም ባህሪ አንድ ጊዜ አዳጠዳፋቸው፤ ለእናት፤ ለሚስት ለእህት ሁሉም ከባድ የጎለጎታ ፈተና ነበር፤ ግን አቅማቸው ይገርማልየበሰበሰ ዝናብ አይፈራምይለሉ። ጽናታው ዲካ የለውም። ጋዜጠኛውመንግሥት ምን እንዲያደርግለዎት ነው የሚፈልጉት?“ ሲሏቸውመንግሥት የራሱ ህግ አለው። የዛኛውም ይሁን የዚህኛው መንግሥት ወክዬ መናገር አልችልም። በራሱ ህግ ይጠቀም።ነበር ያሉት። ማዕላዊ እና ሚዛናዊ ነበር አገላለጻቸው። የውስጣቸው ጥንካሬያቸው ይደንቃል፤ ምቱ ለዛው እና ውስጡ ቃናውና ቀለሙ ልዩ ነበር። ያን የመሰለ ትኩስ ግራ ቀኝ ሀዘን ተሸክመው ግን ብርታታቸው የሚገርም ነበር። ለተጠየቁት ጥያቄ ሁሉ የሰጡት መልስ ኢትዮጵያ ያላት የህሊና አቅም መደበኛ / ቤት ገብቶ በመማር እና ባለመማር ያለውን የአስተሰሳብ የዝበት ግድግዳ ይንደዋል። ሊቅ ናቸው ለእኔ። ቅኔ።

https://www.youtube.com/watch?v=Bh0F16exJHg
የጀግናው ሀይለመድን እናት ይናገራሉ from Dawit Solomon“
የቃላቸው ብርታት፤ በራስ የመተማመናቸው አቅም፤ ያን ሁሉ መከራ በጣምራ ተሸክመው ግን የነበራቸው ልበ ሙሉነት ጉልበቱ የኔታዊነታቸውን የላቀ ያደርገዋል። የኢትዮጵያን ሴቶችን ይህን የመሰለ አቅም ትቶ በጨለማ የሚጓዘው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ምን ያህል ንጠረ ነገር ከእያንዳንዱ ብልህ ሴት እንደቀረበት ቁሞ ያሰተምራል። የተራራው ቅዱስ ስብከት ነውለእኔ። አሁን እንኳን በቃችሁ ሊሊን ብራ እዬሆነ ይመስላልመቼም የእኔ የልደት ቀን ወደ መጋቢት 24 ቀን 2010 እንዲሸጋገር ምኞቴ ነው።
  • ባለዘመኖች።

ባለዘመኖች ደግሞ በተተበተበው የሴራ እና የጫና እንዲሁም የስለላ መረብ ጥሶ እጄን አልሰጥም ለበላህሰብ በማለት በመሬቱ መኖርን የተነፈገውን የነፃነት ትንታግ ወጣት የህዝብ የነፃነት ድምጽ ወክሎ ሰማይ ላይ ተጋድሎውን ፈጸመ። ጄኔባ ላይ የአድዋን ዳግም ድል ያበሰረውን ጀግና በሚመለከት የወያኔ ሃርነት ትግራይ ካቢኔ ውክል አካል ያደረገቱ ቃለ ምልልስ ደግሞ ይሄው ነው። ለንጽጽር ያግዛል።ነገርን ከሥሩእንዲሉ
https://www.youtube.com/watch?v=v6rJxDOWHbM
„Redwan on hijacked Ethiopian Flight ET 702“

  • ጉዳዩ።

አሁንመንግሥት ማለት ስለሚቻልለኢትዮጵያ መንግሥት የጀግና / አውሮፕላን አብራሪ ሃይለመድህን አበራ ነገረ ጉዳይ ከአንድ ተፎካካሪ ፓርቲ በላይ ነው። የፈጸመውም ገድል አንደዛው። ጥልቅ ነው። በሁለት ሐገሮች መሃከል ያለ ጉዳይ ነው። ለዛውም ከሲዊዝ ህግ ጋር ነው። ሲዊዝ ብሄራዊ መዝሙራቸው እንኳን የተለዬ ነው። ሰባዕዊነቱ፤ ተፈጥሯዊነቱ፤ ጽናቱ በፈጣሪ ያለው ፍጹም እምነት ሊመራመሩት የማይችል ነገር ነው። ተፈጥሯቸውም በእጅጉ የረጉ እና የሰከኑ፤ ዓለም የማይደንቃቸው ናቸው። ሥነምግባራቸውም ልዩ ትምህርት ቤት ነው፤ ሁሉ ነገር በቀስታ እና በዝጋታ ነው። እና የኢትዮጵያ አዲሱ የለውጥ መንፈስ ይህን ጀግና፤ ብሄራዊ ጀግናዬ ይለው ይሆን ወይንስ እንደ ዘረኛው እና ኢትዮጵያን በባዕድ ስሜት ሲገዘግዛት እንደኖረው የወያኔ ሃርነት ትግራይአሸባሪ?“ ይለውን?

መቼም ጀግና ሃይለመድህን አበራ እሱአሸባሪከተባለ እኔም ሥርጉተ ሥላሴአሸባሪነኝ ማለት ነው። ጀግናዬ ምልክቴ፤ ልክ እንደ ልሙጡ አረንጓዴ ቢጫ ቀዩ ብሄራዊ ሰንደቅዓላማዬ ዓርማዬ ነው። ብዙ ነገር ነው ያጣሁት። ብዙ ነገሮች ናቸው የተሰናከሉብኝ። እጅግ ረቂቅ የሆኑ ጥቃቶችም ደርሰውብኛል። በመቻል ተችሎ ነው የተቀጠለው።ጊዜ ገቢረ ለእግዚአብሄርሆነ እንጂ። ያሳደዱኝን፤ ያስከፈኙን፤ ብዙ ነገር ያሳጡኝ አመክንዮዎች ረቂቅ ናቸው። ፈፃሚዎችን አላኮረፍኳቸውም። አልተጣላኋቸውም። ይልቁንም በነበረው በለመዱት ፍቅሬ ልክ መቀጠሌ ለእነሱ ህሊና ከበዳቸው፤ የህሊናም ቋያ ሆናቸው። ግን እንደተፈለኩኝ ልገኝ አልቻልኩም። ውስጥ ተፈቅዶ ሲሰጥ የተሸለመን ውስጥነት በጥንቃቄ መያዝ ያስፈልጋል። የሰው ልጅ ለሰው ልጅ የሚሰጠው ታላቅ ስጦታ ውስጥን መፍቀድ ብቻ ነው። ያን የጣሰ ዝምታ ይፍታው
  • ክወና።

እኔ በእሱ ዙሪያ ቁጥር ሥፍር አልበረውም በጸጋዬ ራዲዮ ፕሮግራም የሠራሁት፤ በማህበራዊ ሚዲያም አንዲሁ። ወንድሜ ቢሆንስ በማለት? በሰው ሐገር ምንም ባላደርግለት ለመንፈሱ ጥበቃ ማድረግ ትውልዳዊ ድርሻዬ ነበር። እስኪ ለማስታወስ እንዱን ብቻ ለጥፌያለሁኝ። ጀግኖቻችን በምልሰት ማስታወስ ይገባል። ቅኖቹ ጀግናችሁን የወደዳችሁ ዘሃበሻ አርኬቡ ላይ ካልሞላባችው ሊኖር ስለሚችል ማንበብ የምትችሉ መሆኑን በትህትና አሳስቤ ፊት ለፊት ያገኘሁትን ግን ለጥፌዋለሁኝ።

የሰማዩ የሥራ ማቆም ሰላማዊ እንቢተኝነትምርጥ ዘርና ፍሬ (ሥርጉተ ሥላሴ)“
http://www.zehabesha.com/amharic/archives/30314 በመጨረሻ ክንውኑ ምን ይመስል እንደ ነበር አንድ ተጓዥ ያለውን አድናቆት አክሎ የሰጠውን ቃላ ምልልስም ለጥፌዋለሁኝ። የዛ ሁሉ የነፍስ አባት ነው / አውሮፕላን አብራሪ ሃይለመድህን አበራ። ነፍስን የሰጠ ነፍስን ያደነ ነፍስ የሆነ የጀግኖች ቁንጮ፤ የብልሆች ቀንዲል። ሊከበር ይገባዋል።
http://ethiopiaforums.com/ethioforum/viewtopic.php?t=3751&p=6380#p6380
አውሮፕላኑ ካረፈ በሆዋላ ተሳፋሪው የተደነቀው በረዳት አብራሪው ችሎታ ነበር በተለጠፈው እሮፕላን ውስጥ የነበረው ወጣት ይናገራል ይላል። አድማስ ነበር የዘገበው።
ግን እውነት ማነው ወንጀለኛው? አርበኛ / አውሮፕላን አብራሪ ሃይለመድህን አበራ ወይንስ የወያኔ ሃርነት ትግራይ ሥርዐዎ መንግሥት? ሚዛን ለራስ ነው።

ከዚህ ክስተት በኋዋላስ እንኳን በአንድ ሰሞን ብቻ ከኦሮምያና እና ከአማራ ክልል ብቻ 50 ሺሕ እሰረኞች ነበሩ፤ በሬቻ በቀን 600 ወገኖች እንደወጡ ቀርተዋል፤ ባህርዳር ላይ በአንድ አጋዚ 50 ወገኖች ተረሽናዋል፤ አንባ ጊዮርጊስ ላይ 27 ህጻናት ተጨፍጭፈዋል፤ በዬጓዳው ካለቀው ሌላ። አሁን ደግሞ አንድ ሚሊዮን 50 ሺኽ ዜጎች ከመኖሪያቸው ተፈናቅለዋል፤ ተሰደዋል፤ ሙተዋል በጨለንቆ፤ በወልድያ፤ በራያ እና ቆቦ፤ በሞያሌ፤ በአንቦ ፤በነቀምት፤ አንደቅጠል ወገን ረግፏል፤ እስር ቤቱ ያለው ወገናችን የናዚዎች መፍንጫ ነው። ምኑ ይነገራል፤ በተለይ ጎንደር እንደ ጥንቸል መሞከሪያ ጣቢያ ሆኗል።

እግዚአብሄርን ሲፈቅድ እንዲህ ነው። አሁን ደግሞ ይህ ጥቃት አውጪ ቅዱስ መንፈስ ጸደቀ።ኤች አር 128 በአሜሪካን ምክር ቤት ፀደቀታምሩ የሰማይ ነው። በወገን በትውልድ በሐገር ልጅ ይህ ሁሉ መከራና ፍዳ?
የእግዚአብሔርም እሳት ወደቀች፣ የሚቃጠለውን ምሥዋዕቱንም እንጨቱንም ድንጋዮቹንም አፈሩንም በላች፣ በጉድጓዱ ውስጥ ያለውን ውሃም ላሳች (መጽሐፈ ነገሥት ቀዳማዊ ምዕራፍ ፲፰ ቁጥር ፴፰ እስከ ፴፱“)
የኔዎቹ መረጃው ላልነበራችሁ የተወሰነ መረጃ ይኖራችኋዋል ብዬ አስባለሁኝ። በስሙ ጉግል ብታደርጉም በዓለም አቀፍ ሚዲያ የነበረውን ሽፋንም ታገኙታላችሁ። አጀንዳ ነበር። በሌላ በኩል ደግሞ የነፃነት ዋጋ ምን ያህል እንደሆን በማወቅ ዕድሉን ያገኘ ባለድል ተጠንቅቆ መያዝ ያለበት ይመስለኛል። የደም ዋጋየህይወት ዋጋየመኖር ዋጋየወጣትነት ዋጋየተከፈለበት ነው እና ዝቅ ብሎ አጋጣሚውን በመቀበል ልዕልት ኢትዮጵያን ከደም መንደርነትከዋይታ ቀዬነትከጭንቅ ባድማነትወደ ህይወት መንደር እንድትሸጋገር ማድረግ ግድ ይላል። እኔ እውነቱን ለማናገር ደክሞኛል፤ ዕንባዬም ደርቋል። ፈጣሪ ይርዳን። አሜን። የኔዎቹ ቅኖቹ —- ቆይታችሁ ተስፋዬ ነው ለዚህም ጀርጋድ ያለ አክብሮትን እንሆ ኑሩልኝን በመጨመር።

ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው አራት ዓይናማ መንገዳችን ነው።
የነፃነት ጀግኖቻችን ተግባር ምንጊዜም ህያው ነው!
ኢትዮጵያዊነት ፈተናን አሸንፎ የተጠረ ሚስጥር።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ። መሸቢያ ጊዜ።፡





አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።