ክቡር ተዋናይ ኪሮስ ኃ/ሥላሴ።

                       ለባለግርማው የጥበብ ክህሎት
                         ለተዋናይ ኪሮስ ኃ/ሥላሴ
                            ምህረቱን ይላክ አዶናይ 
                                      „አሜን!“

                              ከሥርጉተ ሥላሴ 25.05.2018 (ከጭምቷ ሲዊዘርላንድ።)


„ምንም እንኳን በለስም ባታፈራ፣ በወይን ሐረግ ፍሬ ባይገኝ፤ የወይራ ሥራ ቢጓደል፤ እርሾችም መብልን ባይሰጡ፤ በጎችም ከበረቱ ቢጠፉ፤ ላሞችም በጋጥ ውስጥ ባይገኙ፤ እኔ ግን በእግዚአብሔር ደስ ይለኛል፤ በመዳህኒቴ አምላክ ሐሴት አደርጋለሁኝ። ጌታ እግዚአብሄር ሃይሌ ነው። „አሜን!“ ይሁንልን! ይደረግልን! (ትንቢተ ዕንባቆም ምዕራፍ ፫ ከቁጥር ከ፲፯ እስከ ፲፰)



  • የውስጥ መስመር ...

ጥበብ ዘር የላትም፤ ጥበብም ፍቅር ናት፣
ጥበብ ቅርጽ የላትም፤ ጥበብ ብርሃን ናት፣
ጥበብ ፎርም የላትም፤ ጥበብ ነባቢት ናት፣
ጥበብ ቀለም የላት፤ ጥበብ የሁሉም ናት፣
ጥበብ መኖርም ናት መልካም ሐዋርያ ትርሲታዊ ሰናይ፣
ለፈቀዳት ሁሉ የምታደላድል የመንበር የበላይ።
  • ·         ጥበብ እንዲህም ናት …

የትህትና መዝሙር የአገልግሎት ዝክር
የድካም ዕንቢልታ የጥንካሬ በር።
መች ሆና ስታውቀው ጥበብ ወረተኛ
የትውፊት ውሃዋ የዓይን ዘበኛዋ።
·         ጥበብ ፊት አትሰጥም …
ጥበብ አይደለችም የጉድፍ አንቀልባ የልዩነት ዳባይ
ጥበብ ጎታ የላት ለኩፉኝ እኩይ።
ጥበብ ፊት አትሰጥም ለስንኩሉ ገደል ለሃሰት ቃል አባይ፤
ጥበብ አይደለችም የክፋት ኩነኔ የክፉ ላብ ብካይ።
ሰነፍ ጥበብ የለች አልተፈጠረችም፤
ሸረኛ ጥበብም አልተወለደችም፤
ንዑድ ጥበቢት ናት የዘመን ብርሃን።
  • ·         ጥብብ አይደለችም …. የጥላቻ አምራች የደከመች ዝላይ …

ንዑድ ናት ጥበቢት ቅኗ መንገደኛ
ኪሮስን ያጋባች ከቅኔ ቤተኛ።
አንተ የሁሉ ጌታ የማዳን አምላክ፤
ንጉሠ ክርስቶስ ሆይ! የዓለም አማላክ፤
አንተ የሁሉ ልዑል የፍጥረት አምላክ፤
ሃይልህን ታዳገው ሳይዘጋ ሰርክ።
·         አላዛር ኢትዮጵያ …
ለዚህ ታላቅ ዋርካ የአገር ሲሳይ
ምን አለሽ ከጓዳሽ? ምን አለሽ ከባንክሽ ውለታ ደልዳይ?
ብርሃኑ ሲዝል ልጅሽ ሲደክምብሽ፤
አለሁልህ በይው ከጎኑ ተገኝተሽ።
አይዞህ! ልጄ በይው በእቅፍሽ አባብለሽ፤
ስለ አንቺ ለኖረ ስለንቺ ሲደክመው፤
ማዕድሽ ይበለው ከካሳ ያውለው።
  • ·         እናት ዓለምዬ ናፍቆቴ አገሬ …

የመኖር መስምሬ
ብትኗ አፈሬ …
ብሌኑ ሲታጣ ጥቁር ብትለብሽ ቃልን ብት
ዓይንሽ ሲሾልክብሽ ድንኳን ብትሰፍሪ፤
ምን ቢከፋሽ ከቶ ዕንባ ብታዘሪ፤
እውነቱን ልንገርሽ የቅንነት ዝረዝር ቶሎ አዘርዝሪ …
የተግባር ውሎውን ለኪዳን ገብሪ።
ጓዳሽን መርምሪ እትብትን አናግሪ፤
በምግባር በወቄት ማግሥትነት ግሪ።
ታሪክሽ ተቀልሞ ተሰጠ ለሠሪ
ሸማውን አልብሽው ለትሩፋት መሪ።
  • ·         እናቴ እትዮጵያ የክብር ጽላት … ህብስት፤

…. መጸሐፍ ሲከድን በዝምታ ማጥ ውስጥ
ብዕር በጨለማ ተስፋን ተቀምቶ፤ በእንብርክኩ ሲያምጥ፤
ዓውራ ቤት መዋሉ፤ ብራና መግለጡን ሲከደን በአፍታ፤
ከቀለም ማህበር ሽው ሊል ሲዳፈን እልልታ ዕልፍኙ ሲፋታ፤
የተውኔት መድረክ በድርቅም ሲመታ፤
ማለት ምን ይበጃል የት ያለህ ቱማታ።
የጥበብ ገበሬው ድርሳኑ ሲዘጋ፤
?ዝክረ ታሪክሽም እያለሽ ሊዛጋ?!
በአጭርም በረጀምም፤ መዳፍሽን ከንጂ እና ሌማቱን ዳስሽ፤
በመከራሽ ሁሉ ከቅርብሽ፣ ከጎንሽ አለሁ የሆነልሽ፤
የኖረው ስለአንቺ በመሆን አብነት ከረቂቅ ሲያትምሽ፤
ቀኑ ጨልሞበት የጥበብ ገበሬ ዕለቱ ሲከደን፤
ሌሊት አልነጋ ሲል ዝክረ ታሪክሽም እንደመሸ ሊቀር?!
ሳይነጋለት ቀርቶ እንደ ዳመነበት ዕለታት ሊቆጥር?!
ታስሯልኝ ያ ትንታግ የሁሉ ፍቅረኛ ያልሆነ ጊዜኛ፤
የመንፈስ የነፍስም የሰናይ ሙሴኛ።
  • ·         ሥጦታ … ለውስጤ ለማከብርህ ለባለግርማው ተዋናይ ታላቅ ሰው ለአርቲሰት ኪሮስ ኃይለሥላሴ ይሁንልኝ። ድንግልዬ ምህረቱን ትላክልህ። „አሜን!“ ለአላዛሯ ኢትዮጵያ ጌጥና ፈርጥ ምህረት ከእዮር ይላክለት። „አሜን!“ አንተ የአገር ዋርካና ቀንድን ቅዱሳኑም አይለዩሀ። „አሜን“  ምህረቱን ቸርነቱ አዶናይ ይላክልህ። „አሜን!“ አንተ የቅኖችም ነህ እና ስለሆነም የማያዳለው የሰማይ እና የምድር ነጉሥ አማኑኤል ብርሃንህን ይስጥህ። „አሜን!“


  • ·         ጣቀሻ። 25.05.2018 እ.አ.አ

አርቲስት ኪሮስ ኃ/ሥላሴ የአይን ብርሃኑን አጣ! Kiros with Seifu Fantahun“

የኔዎቹ እንዴት ሰነበታችሁልኝ? ደህና ናችሁ ወይ? ይህን ዜናውን እንዳደማጥኩኝ ውስጤ ያለኝ ነው የጣፍኩት። እንደዚህ ዓይነት ጉዳይ ሲገጥመኝ የሚለኝን መናገር ብቻ ነው በስሜት። ስለዚህ የቃላት ግድፈት፤ የአገላለጽ ኩሰት፤ የሥንኝ ስብራት ከገጠመው ወጌሻ ሁኑለት፤ ይቅርታችሁን እጠይቃለሁኝ - በትህትና። 

ስለሆነም ጠንካራ ነው ብዬ አላስብም ግን ቢያንስ እግዚአብሄር ይማርህ ማለት ስለሚበጅ ነው። እዚህ ላይ አበክሬ እማስገነዝበው የዓይን ኦፖራሲዎን ከሁሉም በላይ ፈጣሪን መጠዬቅ እና ምልክቱን አለመዝለል ይጠይቃል። ውጪ አገርም ግድፈት ሊኖር እንደሚችል፤ በተጨማሪም የቀን ስብራትም የራሱ የሆነ ተጽዕኖ እንዳለው ከተመክሮዬ መግለጽ እሻለሁኝ። መጸለይ እና የህልምን ምልክት መከተል ይበጃል። 

በህልም የሚገለጥ ነገር ከኖረ ዕውቅና መስጠት የተገባ ይመስለኛል። በተረፈ ልዑል እግዚአብሄር የምህረቱን፤ የቸርነቱን ወሬ ያሰማን። „አሜን!“ አዝኛለሁ በጣም፤ መድረክ ላይ ትውናው ለዬትኛውም ገፀ ባህሪ ግርማውና ሞገሱ የንጉሥ ያህል ነው። እኔ የተለዬ ወጥ መክሊቱ የምለውም ይሄን ነው። በተረፈ አይዞህ የእናት ልጅ እንደ ዳመነ አይቀርም። ለእሱ የሚሳነው የለም።

ኢትዮጵያዊነት ፈተናን አሸንፎ የተፈጠረ ሚስጢር!
„ራዕይ የሌለው መሪ ነጂ እንጂ መሪ ሊሆን አይችልም!“
ከባለቅኔው ጠ/ሚር አብይ አህመድ የዘመንን ፖለቲካ አመራር ቅጥ አስያዥ መርኽ የተወሰደ።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ።

መሸቢያ ጊዜ። 

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።