ዓይነ ጠባብነት?

ወጣቶች እንደ 66ቱ ዘመን ዓይነ ጠባቦች መሆን አይገባቸውም።
ክፍል አንድ።
ከሥርጉተ ሥላሴ 29.06.2018
(ከገዳማዊቷ ሲዊዘርላንድ)
„የጆሮ ጠቢብ ቃል እንደ ጣፋጭ መብል ነው።“
(መጽሐፈ ምሳሌ ምዕራፍ ፲፷ ቁጥር ፰)


  • ·      እፍታ


ዛሬ ነው ከብራና ሳተናው የገባሁት። ትናንትና በተከታታይ የጻፍኳቸው የሰቆቃው አማራ ጉዳይ እና የእውነት ጠበቃ ማጣት በሚመለከት ስጽፍ ስለዋልኩኝ ጊዜ አልነበረኝም።

  • ·       ወጣትነት እና መልካምነት ስለምን አይጣጣሙም?

እኔ ወጣቶች ስለምን መልካም ነገርን ሊወርሱ እንደማይፈቅዱ ይጨንቀኛል። መልካም ነገር ዛሬ ላይ ካለወረሱ እንሱም ነገ መልካም ነገርን የሚፈራ ትውልድን ነው የሚተኩት። ቢያንስ ስለምን በመልካም ነገሮች ላይ ሚድያዎችም አትኩሮት ሊያደርጉ እንደማይፈልጉም አሁንም እኔ ይጨንቀኛል። የ66ቱ ዘመን እኮ እከሌ ተከሌ የለበትም። በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ከሴራ ጋር የተጋባ ነበር ንድፈ - ሃሳቡ። የጸዳ ተግባር ለመሸከም ሆነ ለመከወን ራሱ ንድፈ ሃሳቡ አይስችለውም። ለበጎ ነገር በሩ የተከረቸመ ነው። ለዚህም ነው ለዘመኑ ያልመጠኑ ቡቃያዎች ሳይበቅሉ በክፉዎች አረም ተውጠው ወይንም ደግሞ ከሰመው የቀሩት። ገና በለጋቸው ተባብሮ መቅበር ለምዶብናል። 

እራስ እግሩ ማለት እስኪያስችል ድርስ ሸር ነው የሶሻሊዝም ንድፈ ሃሳብ። በመልካም ነገሮች ውስጥ የሚጠቀለለው የሸር መርዝ ነው። ሴራ ነው ድር እና ማጉ የሸማችን ዕጣ ፈንታ።  አሁን አንድ ሱዳን ላይ ያለ አጋርህ፤ ወንድምህ እንደ አንተ የተሰደደ ከልታማ ታማሚ ለህክምና የውጪ ዕድል ቢያገኝ ማሰናከል ከቶ ምን ይባል ይሆን? አንተ አትከፍልበት፤ አንተ ስፖንሰር አይደለህ። 

ሌላ በጎ አድራጊ ደርጅት ሊከወነው ሲያስብ በወገንህ አሲረህ ግን ወገንህ እንዲሞት ትፈርድበታለህ። ሲሞት ደግሞ ሳጥን ተሸካሚ ትሆናለህ። በሴራ፤ በሸር ጉዞውን እንዳይሳካ ሁሉ የተደረገበት ሰው እኔ አውቃለሁኝ። ቀደም ባሉት ዓመታት ወደ ኢትዮጵያ ተመልሷል፤ ምንም እንኳን በምን ሁኔታ አሁን እንዳለ ባላውቅም። ሱዳን እያለ የሆነውን ሁሉ ሲያጨውተኝ አዝን ነበር። ቢያንስ ስደት ለዛውም አፍሪካ ላይ ያለ ስደተኛ ስለምን በፖለቲካ አስተሳሰቡ ምክንያት ሞት ይፈረድበታል። እንደ ነገረኝ ሞቼ ነበር ነው ያለኝ።

  • ·       ሴራ እና ባለድልነት፤

በቃ ሴራ ነው ትልቁ የአስተሳሰብ ልቅና፤ ልዩ ፍልስፍና፤ የህሊና ብልጽግና እና ጻድቃንነት። ይህ እኮ ተኖረበት በዬሥርቻው ያለውን አቅም መቃብር ሲፈረድበት። አቅምን ሲቀነቅን የኖረው በዚህው የሴራ ፍልስፍና ነው። ሁለመናችን የሴራ አማልኮኛ ነው። ይህም በመሆኑ ለሴራ ፖለቲካ የኢትዮጵያ እናቶች ድፍን 43 ዓመት ሙሉ ማህጸናቸውን ሲገብሩ ኖረዋል። ተሰደንም ልጆቻቸው ሰላማችን ታውኮ፤ ኑሯችን ብቄት አልባ ሆኖ ከስሎ ቀርቷል።

በጣም የሚደንቀኝ እና የሚገርመኝ ጀርመኖች እንዴት ይህንን ፈተና ተሻገረው የዓለም የሁለመና የጀርባ አጥንት እንደሆኑ ነው። ሁልጊዜም እማነሳው እምጽፈው ይሄው ነው። ጀርመኖች ለዚህ ዛሬ ላለው ሉላዊነት የመቻቻል እንብርት የሆኑት በዚህው የሶሻሊዝም የሴራ ድር እና ማግ ፖለቲካ ትብትብ እግር ብረት ዝልቅና ጥልቅ የማያዳግም እርምጃ በመውሰዳቸው ነው። 

የሶሻሊዝም ፍልስፍና መሰረቱ፤ ላዕላይ እና ታህታይ መዋቅሩ በሴራ የተገነባ ነው።
ለዚህ ነው ከሴራ ጋር ንክኪ የሌላቸው ሰዎች ቅንነትን ይዘው ፖለቲካውን ይቀላቀሉና እና ህዝብ ሆ! ብሎ መደገፍ ሲጀምር ዓይናችን ጉርሽጥ ይሆናል፤ ስለዚህም ተስብረው፤ በቀንበጥነታቸው ከስለው እንዲቀሩ ይደረጋሉ።

አቅማቸውም አፍሮ አንገቱን ቀርቅሮ በተዘጋ ግን አፍ ባለው መቃብር ኑሮውን ያደርጋል። ና // ነይ እስኪለው // እስኪላት ድረስ። ምክንያቱም ሴራ እና ሴረኛ አምራቹ ሶሻሊዝም ቅኖችን „እንኳን ደህና መጣህ“ የማለት አቅም የላቸውም። የሚበልጥ አቅምን ከመቀበል ጦርነት ገብቶ መዋጋት የሴረኞች የደቦ ውልአደር ነው።
  • ·       ፈርጥ እና የበራ ልቦና ፈተናው።

ለዚህም ነው እነ ኦቦ ለማ መግርሳ፤ ዶር አብይ አህመድ፤ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው፤ ዶር አንባቸው መኮነን ወደ ፊት ሲመጡ ያን ያክል በደቦ አክስሎ አመድ ለማድረግ የሴራ ፖለቲካ ማህበርተኛው ሁሉ ጦርነት የከፈቱባቸው። ተው፤ ሃግ የሚል ጠፍቶ ለወያኔ ሃርነት ማንፌስቶ ሴራ ድልዳል በቂ የዝግጅት ጊዜ እርፍት የተሰጠው።

ሌላው ቀርቶ እንዚህ አራት ነፍሶች በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ በወያኔ የሴራ ፖለቲካ ለጠፋው ጥፋት ሁሉ ራሳቸውን ተጠያቂ እያደረጉ፤ ራሳቸውን በደለኛ እያደረጉ፤ ተዋርደናል እያሉ ይህን እንኳን የትግራይ ልጆች አጀንዳቸው አድርገው ትውልዱን ሊነቅል ከተነሳው ክፉ ሃሳብ ጋር ፊት ለፊት መዋጋት ተስኗቸው ዳር ላይ ቆመው ይመለከታሉ። ይህ እኮ ሆኖ አያውቅም ድፍን አለም የሚያውቀውን የ ኢትዮጵያ ህዝብ በደል እኛም ተጠያቂ ነን ይላሉ ደጎቹ … የሚገርሙ ፍጡራን። ውይይት ላይም ህዝባቸውን የሚገሩት በዚህ መንፈስ ነው። ቂም ማውረስ አረም መብላት ስለሆነ። በቀል ማውረስ ሙጫ መዋጥ ስለሆነ።

ይህ መንገድ ከምንም እና ከማንም በላይ ለትግራይ ህዝብ የነፍስ አባት ነበር። ቁጭ ብለው መከረው፤ ዘክረው፤ ከክፉ አስተሳሰቦች ጋር ላይመለሱበት ወስነው ከመልካም ነገር ጋር ቤተኛ መሆን ሲገባቸው እነሆ እያንዳንዱን ደቂቃ እያቃጠሉት ነው። ባለፈም የሴራው ግንባር ቀደም ተባባሪ የሆኑም አሉ። ለትውልዱ እውነት ለመናገር የወያኔ ማንፌስቶ መርዝ ነው። ነፃነት አመጣ ለሚባለው ለእነሱ ከሆነ አዝለውት ይዙሩ።

ቀድሞ ነገርም ከመሠረቱ ኢትዮጵያ ብሎ አልተነሳም፤ የተነሳውም ለታላቋ ትግራይ ብቻ ነው። አሁንም ኢትዮጵያ ትንሳኤ ሲመጣ ነው ይህ ሁሉ ሞት፤ መፈናቀል፤ መታረድ፤ ቃጠሎ እዬተደመጠ ያለው። ሰው እንኳን ይሁን ብሎ ቢቀበለው የእዮርን ማናቸውም ቁጣ ግን መገደብ ማስቀረት አይቻልም ለእነ ተጋሩ። ለሃጣን የመጣ ለፃድቃን እንዳይሆን ብቻ። ችግሩ ዙሮ ተመልሶ ከሰማይም ይምጣ ከምድር የኢትዮጵያ እናቶች እንባ መጨመሪያ ነው የሚሆነው። ሰቆቃው የህፃናት የፍዳ ማምረቻ ካንፓኒ ነው የሚሆነው። የአሁኑ የመላ ኢትዮጵያ የዕልፍ ዕላፋት ዕንባ ነገ ዋጋውን መላሹ እዮር ብቻ ነው። … ቢያንስ አማንያን ወደ ልቦናቸው ተመልሰው አቁርልን ለማለት አለመደፈር ከውስጤ የማዝንበት ጉዳይ ነው።

  • ·       ከሴራ ጋር ለመፋታት ጸሎት።

ዋናው ከማንኛውም ኢትዮጵያዊ ዜጋ፤ ሃይማኖት ያለውም የሌለውም ቢሆን ልዑል እግዚአብሄር ከሴራ ጋር እንዲያፋታን፤  አዕምሯችን እንዲያጥብልን መጸለይ አለብን። ሁሉም ተበክሏል። አሁን ዛሬ ሳተናው ብራና ላይ የኢሳቱ ጋዜጣኛ አቶ መሳይ መኮነን የመደመር ፖለቲካ አስፈርቶታል።ከዚህ አንዳንዶች ባይደመሩስ?“ (መሳይ መኮነን)
„አንዳንዶችስ ባይደመሩ ይለናል?“ ቀደሞ ነገር ከወያኔ ሃርነት ማንፌሰቶ ዶግማ ጋር ማን ያልተጋባ ማን ያልተዋለደ ኖሮ ነውና? በርሃ ድረስ እኮ ይሆናሉ ተብለው ተረድተዋል። ሻብያ ሁለመናውን ሰጥቷቸዋል። ኦንግም እንዲሁ አብሮ አሸሼ ገዳሜ ብሏል። ውጭ ይኖሩ የነበሩት ሙሁራንም ቀደምቶቹ ሲባረሩ ስለምን ይጭነቅህ ሄሮድስ መለስ ዜናዊዬ እኛ እያለልንህ በማለት ዬሴረኛውን የናዚ ፖለቲካ ጥቃት በማውጣት ማገር ወጋግራ እንሆንልሃለን ብለው ሄደዋል። 

በቃኝ እያለ የወጣው ሁሉ በዛ ማንፌስቶ ማዕቀፍ ውስጥ ነው የነበረው። ዘመን የማይተካው ጋዜጠኛ ሙሉጌታ ሉሌ በጮኽበት ዘመን ማን አዳመጠው? ለነገሩ በኋዋላም ሞቱን በሞቶ ገዝቶ አልፏል። ያው በሴራ ፖለቲካ። ጓዳችን ተብሎም እንደ ሌሎቹ ለመግለጫ ክብር እንኳን አልታደለም። ከቶ አማራነቱ ይሆን?
እነኝህ የወያኔ እረዳት የነበሩ ወገኖቻችን ሁሉ በቃን አይተነዋል ሲሉ ጋዜጠኛ መሳይ መኮነን ጨምሮ ምንም ቅድመ ሁኔታ አልነበረም። መጣን ሲሉ፣ ልንደምር ነው ማለታቸው ነበር ቁም ነገሩ። አይደለም ወይ? ተደመሩ ተባለ። ተደመሩ።

እንዲያውም ቀድሞ ሲታገላቸው ከነበረው ማህበረሰብ ከፍ ብለው ባንዴራ ሆነው ተሞገሱ፤ ተከበሩ፤ ተደነቁ፤ ተጨበጨባላቸው። አብረው ከነበሩት በጎች ይልቅ ጠፍታ የተገኘችው ይበልጥ ተከበረች ስለሚል ወንጌሉ። በመሃል ሁሉንም ጥሶ ኢሳት መጣ። አቀባባሉ አዝጋሚ ቢሆንም በታሪክ አጋጣሚ ከፍ አለና የሁሉን አደብ ሆነ ቀልብ ገዛ።

ነገር ግን ኢሳት እንደሚያብጠለጥለው የወያኔ ሃርነት ትግራይ የሚዲያ ማህበር እሱም ከዛ በአቋም አይለይም። የተወሰነው ሲያቀርብ፤ የተወሰነውን ሲያገል ነው የኖረው። ከምንም የማይሻል ነገር ስሌለ ሁሉም እንዳሻው ብሎት ኖረ። ድርጅቱ በምን ላይ እንደሚሠራ፤ ምን እንደሚያቅፍ፤ ማንን እንደሚያገል፤ ማንን ከተገለገለበት በኋዋላ እንደ አሮጌ አካፋ እና ዶማ ወርውሮ እንደሚጥል እያንዳንዷ ቅንጣት ነገር ማስተዋል ላለው ሰው ያዬዋል።

ይህም ሆኖ እዬታወቀ „አንድ ዓይን ቢኖራት እሱንም በዘነዘና“ እንዳይሆን ቢያንስ በመንፈስ ብዙው ሰው ይኑርልን መኖሩ አይከፋም ይላል። ያው በዛ ውስጥም በሰብዕና ሙሉ የሆኑ ሰዎች ስላሉበት እነሱ እያሉ ስለሚባል። ነገር ግን በዚህ በጎሽ ልብ መደመርን እቀላለቀላለሁ ቢል ግን ይከስማል።
  • ·       ልብን ማጽዳት የሚዲያ ዶግማው ሊሆን ይገባል።

መደምር ከቆሻሻ ጋር መደመር አይደለም ግን የቆሻሻን ርዝማኔን ለማሳጠር አቅም በተደራጀ ሁኔታ ይፈጥራል። የመደመር ፍልስፍና ለእኔ የማጣሪያ ወንፊት ወይንም ፊልተር ማለት ነው። መጀመሪያ በግርድፉ ትደመራለህ፤ ዓይኑ ሰፋፊ የሆነ እንኳን ወንፊት አይኖርህም። እንደ አለ መቀላቀል ነው። መቼም መቀላቀል መዋህድ ማለት አይደለም። ፌስታ የአደባባይ ትርኢት፤ ቲያትር ቤት፤ ሲኒማ ቤት እንደምንገኘው ማለት ነው። ቤተ -አምልኮም ቅልቅቅልም ነው። ቅልቅል ነው የምለው የቤተ አምልኮውን ዶግማ የሚደፈሩ ህግ ተላላፊዎችም አብረው ስለሚደመሩ። ሌቦችም - ዘራፊዎችም - ቅንዝረኞችም - ዋሾችም ቀናተኞችም - የኢጎ አርበኞችም - አላቢላዎችም - ቀልበጡሊዎችም አብረው ተደምረው ነው የሚገኙት።

ጥራቱ ወንፊቱ ያለው የቤተ አምልኮው ምድር ሳይሆን ላይ ሰማይ ቤት ነው። ምስክሩ ደግሞ ህይወታቸው ነው። ህይወታቸው መምህር ነው የጠሩት የነጠሩት። ስለዚህም በምድራዊ ዓለሙም ሂሳብ ቢሆን ማህበረሰቡ ነጥሎ እንደ አብነት ያያቸዋል። ሰላማዊ ሰልፍን ስንወስድ እንደ ተልዕኮ ተመሳሳይ ፍላጎት ያላቸውን ቢያሳትፍም አብረው የሚተሙም ተቃራኒ መንፈሶች ይኖራሉ። ራሱ ትዕይንቱን ለማታደምም በገለልተኝነት አቋም የሚኖሩም አባልተኞች አሉ። እነሱም በመደመር ስሌት ነው ተደምረው ላዛች ቀን የቁጥር ቁጥረኛ የሚሆኑት። መደመር ቁጥር ነው።

አንድ ቁጥር ከአንድ ሲደመር ሁለት ይሆናል፤፡ ቁጥሩ እንደ ሳይዙ መጠኑ ከፍም - ደጎስም - ደመቀም ቢል ያው ነው። በቀለም ቢለያይም ተደማሪው አንድ እና አንድ ይሆናል ሁለት ነው። አንዱ ቀይ እና ትንሽ ስለሆነ፤ ሌላው ሰማያዊ እና መሃከለኛ ስለሆነ፤ ሌላው አረንጓዴና ትልቅ ለግላጋ ስለሆነ በይሆናል ላይ ያው ውጤቱ ሁለት ነው። በቀዩም በሰማያዊውም በአረንጓዴውም፤ በትንሹም በማሃለኛውም በትልቁም መጠን ውጤቱ ያው ነው መደመር ነው። 

ወፍራም፤ ቀጭን፤ ሰላላ፤ መላላ፤ ጉልህ፤ እረጅም፤ አጭር፤ ኮሳሳ አንድ ከመሰሉ አይደለም ከማይመስለው በቁመትም በስፋትም አንድ ጋር ሲደመሩ ሁለት ነው ውጤቱ።

አንደኛው ፍልስፍና ሲሆን ሲሆነ ሁለተኛው ቀመር ነው። ትንሾች ራሳቸው ሳይዛቸው የተለያዩ ብቻ ሳይሆን ቀለማቸውም እንዲሁ ሊሆን ይችላል። ቀይ ቀለሞችም እንዲሁ ዘረ ቀይ ናቸው ግን ዞጋቸው ይለያያል። አንድ ሰው ሲደምር ሌላ ሰው ይሆናል ሁለት ሰው።  
  • ·       ነገር በዓይን ይገባል እንዲሉ።

መጠን 11/ 1+1= 2  ቀለም ንጹህ ቀይ
መጠን 14/ 1+1= 2  ቀለም ወይንማ ቀይ
መጠን 9/             1+1= 2  ቀለም    ቡኒማ ቀይ
 መጠን 16/ 1+1= 2 ቀለም ሰማያዊ
መጠን 26/ 1+1= 2 ቀለም አረንጓዴ

በትንሹ ሳይዝም ተፃፈ፤ በትልቁ ሳይዝም ተፃፈ አንድ ሲደምር አንድ ይሆናል ሁለት ነው። ስለዚህ በዚህ ዶግማ ውስጥ የመጨመር እንጂ የመቀነስ ፖለቲካ አፈር ለብሷል። ይህቺ ሁለት ሰላም + ፍቅር፤ ነፃነት + ዴሞክራሲ + ፍትህ + ይቅርታ + ተደምረው = አዲስ ኢትዮጵያዊ ትውልድ። ኢትዮጵያ + ኤርትራ + ጁቡቲ + ሱዳን + ሱማሌያ =  አፍሪካ ቀንድ አገሮች። አፍሪካ ቀንድ አገሮች + መካከለኛው አፍሪካ + ስሜን +ደቡብ +ምዕራፍ  አፍረካ ሲደመሩ ይሆናሉ ፓን አፍሪካን ዳግም ውልደት። የፓን አፍሪካ ዳግም ውልደት + 7 አህጉር= ሉላዊነት።
  • ·       የመደመር አይዲዎለጂ

በጣም የሰፋ እና የገዘፈ አይዲዎሎጂ ነው። እንደ ለመደብን በቁንጽል እንደ ፋሲካ ስጋ እዬዘለዘለን እምንሸነሽነው ቲዎሪ አይደለም መደመር። ያ በግብታዊነት ስንጋልብበት የነበረው የሴራ ፖለቲካ በመነጠል፤ በመቀነስ፤ በማግለል፤ በመሰንጠቅ፤ በመትርትር፤ በማድማት፤ በማደም፤ በመካፈል፤ በጥላቻ ማነስ ብቻ ነው ትርፉ።

እንደ ሚዲያ እንደ ጋዜጠኛም ለዚህ አደብ ገዝቶ ልብ እንዳመጣ መንተክተክ ሳይሆን ፍልስፍናው ካልገባን አርፎ ዜና እያነበቡ መቀመጥ ይሻላል። በሌላ በኩል በአንዱ መክሊት ሌላ ተደራቢ ታክሎት በሥጋ ቋጠሮ ተሰልቶ ባል እና ሚስት ተደምረው ጋዜጠኛ፤ ወንድም እና ወንድም ተደምረው ጋዜጠኛ እንደሚባለው … ከእንግዲህ ዋጋ ያለው አይሆንም … ለተወሰነ ጊዜ ይቻል ይሆናል፤ አሁንም ሽግግር ላይ ስላለን አገር ቤትም በዚህው መስምር ወዲህና ወዲያ ጅዋጅዊት እንዳለ ይታያል። ነገር ግን አይቀጥልም። በሁሉም መስክ የማያዳግሙ የጸኑ የሞራል ልዕልና ኢትዮጵያ ውስጥ ያለጥርጥር ይገነባል። ዶር አሜኑ አብይ አህመድ በህይወት ከኖሩልን።
  • ·       ቁንጥንጥ

ይህን ወጋ ጠቀም የሚል ዘለበት እያንዛላላዘሉ ከማመስ እና ከማተራመስ … አብሶ ወጣቱን ከማፈረስ ፖለቲካ ራሱን ማውጣት ይገባዋል ኢሳት በነፍሱ። ኤርትራን መጠጊያ ስትደረግ በምቾት አልነበረም። በፍጹም ሁኔታ እያመመን ግን ለአንድ ቁስለኛ አርበኛ ህክምና ከሰጠች፤ ለአንድ ለከፋው ነፍስ መጠለያ ከሆነች ከዚህ በላይ ቅድስና የለም፤ „ሂዱ ሞክሩን ፈትኑን“ ከተባለም ምርጫ የላቸውም በማለት ነበር ድጋፉ ሲጎርፍ የነበረው እንጂ በፖለቲካ አስቤ በምንም መስፈርት የሚሆን ነገር አልነበረም። ለእኛ ሲሆን ማር የአዘንብ ለሌላው ሲሆን ደግሞ ሊጎመዝዘን አይገባም። ያም በመደመር ፖለቲካ የተከወነ ነበር። ተጠቃሚው ያውቀዋል ፈስስ እና ፈስስ ያለው።

ይሄው ኤርትራ በጅ አትልም ብሎ ጋዜጠኛ መሳይ መኮነን በሞገተ ማግስት ማህል ላይ ደግሞ „አንዳርጋች በመፈታቱ ልቤ ለ አብይ ቀና“ ሆነ ሲል አንድ ጹሁፍም ጽፏል ስለባድመ ሲጻፍም አርበኛው ተፈቶ ለንደን ላይ ከቤተሰቡ ጋር ነበር። የሆነ ሆኖ ኤርትራ ውሳኔው እሺ አትልም በድፍረት እና በእርግጠኝነት የተባለቸው አርትራ ክብር ፍቅር ሰላም ተለገሰች። „የመጀመሪያው የሹመት ንግግር መተማማኛችን ምንድነው“ ሲባል ትጥቅ ትግል ትተን ሰላማያዊ ትግልን ተቀብለናል ተባል፤ አልፎ ተርፎ የድጋፍ ሰልፉም ዕንባውም ደረት ምታቱም እየተንከተከትን ተመክተናል፤ በተለመደው የለቀማ ፖለቲካም ሚዲያ ላይም ፊታውራሪ ተሁኗል። የሚዲያ ሙሽርነቱም በወረፋ መሆኑን ተመልክተናል። መደመር ማለት እኮ ይሄው ነው። 

መደመሩ የክት እና የዘወትር የለውም። ለዛውም አሁን በተቃራኒ መቆም ለማይሰለቸው ኢሳትና ታዋቂዎቹ። ነገ ደግሞ ተንበርክኮ ጉልበት መሳም ይጠበቃል። ገና ብቅ ሲል ክትከታ የጀመረው ኢሳት እና ጋዜጠኞቹ ናቸው። ነቃፊ ጹሁፎች ብቻ ነው እዬተለቀሙ ፕሮዎች እንዲለጠፉ የተገደዱትም እነሱው ናቸው። አሁን ደግሞ ያ ጉሽ ጠርቶ፤ ጉሙ ተገፎ ሁሉም ደሃ ብንሆንም ኑልን ፍቅር ያጠገበናል፤ ያኖረናል ሲባል ደንበር ይለይ፤ ክትር ይዘጋጅ፤ አያስኬድም። ይሄ በእናትተው የሰብሰባ ዕልፍኝ።

ለነገሩ ዜመኛ እኮ ሁልጊዜም ላለው ማገልገሉ የተለመደ ነው። አንዱ ንጉሥ ውርዶ ሌላው ሲመጣ ያንኑ ነው የሚያወድስው። ይህ የወል ባህሪ ነው። ከንፍሮ የሚያወጣቸው የሃቅ ታታሪዎች ከኖሩም መከራቸው የቀራንዮ ነው።

እዚህ ላይ በደርግ ጊዜ ነፍሱን ይማረው እና ዜመኛው አርቲስት አቶ ይርጋ ዱባለ ለሸንጎ ለብሄራዊ የፓርላማ አባልነት ተውዳድሮ ነበር። እናቴ „እናንተ ስትወርዱ ደግሞ ሌላውን አሞግሶ የዛሬውን ነቅሶ ያዜማል ያን ጊዜ እናንተን ያዬ“ ነበር ያለችኝ። እናቴ ብልህ ፖለቲከኛ ናት። ያው እሷ የሁመራ አራሽ ስለነበረች እኔ  የአሠፓ ሠራተኛ መሆኔ ብዙም አይደላትም ነበር። 

ብቻ መተሳሰባችን እና የነበረን የሥራ ህብረታችን ብቻ ነበር የምትውደው። በደጉ ዘመን እንዲህ አልነበረም የምትለው ነገር ሁሉ ነበራት፤ አንዳንድ ነገር ወደድ ሲል። እኔም ሳማርር ሳልማር ቀረሁኝ ስል … መንግሥትሽን ጠይቂ ትለኝም ነበር … ትዳሬ ባይፈርስ፤ መሬቴ ባይወረስ፤ ንብረቴ ባይወሰድ እስከ ተፈለገው ድረስ ትማሪ ነበር ነው … አባባ ኢዲዩ ሆነው ጫካ ስለገቡባት … ለነገሩ ዛሬም ያው ነው የኢትዮጵያ እናት የኔው ስደት ግዞት ነው … በዚህ ወያኔ በዚህ የግንቦት 7 ካድሬዎች ያሳድዱኛል።
  • ·       ድንበር የለሹ የመደመር ፍልስፍና።

በመታከል፤ በመጨመር ውስጥ ድንበር አያስፈልግም። መታከል ማለት አሁን ኢትዮጵያ ከሞት አፋፋ የተረፈችበት ወቅት ነው። „ገንቢውም ተገንቢውም የፈረሰበት ዘመን ላይ ነበርን“ ያሉ አንድ የሰሞኑን ቅኔኛ አዳምጫለሁኝ። ትውልድ እዬፈረሰ ነው የነበረው። ፍርሻው ደግሞ ጥላቻን፤ ቂም፤ በቀል ጸንሶ ነበር። ያ እጅግ አደገኛ ጉዞ ነበር።

ሃዘን ቤት ሃዘን ደረሰ ሲባል አደጋ ሲኖር ምንም ጊዜ የለም ለማማረጥ። አደጋ ጊዜ ያለ አገር መከራን አብሮ እቅፍቅፍ ብሎ ማሳለፍ አለበት። አሁንም እኮ መከራው አላለቀም፤ ነገ ቀርቶ በዚህች ቅጽበት ምን ሊፈጠር እንደሚችል አይታወቅም። ቦንቡ፤ መትረዬሱ፤ አዬር መቃዋሚያው ቀድሞ የተደራጀው የሳቦታጅ መረብ ያለው በጉልበተኛው የወያኔ ሃርነት ትግራይ እጅ ነው። እሁድ ባህርዳር ላይ የድጋፍ ሰልፍ አለ አሁንም እኔ እንደ ተለመደው ስጋት ላይ ነኝ። ቀኑ ጥሩ ነው ሦስተኛ ወሩን የትንፋሽ ማጠር አየር ካገኜ ግን… መሰናዶው ማን ከማን ሊለይ እንደሚችል አይታወቅም። እርግታ ስክነት ፖለቲካዊ አመራር ቢያገኙ ምርጫዬ ነው … ለዛውም ለሳጅን በረከት ጋንታ ፌስታነት …
  • ·       መታከል።

የሆነ ሆኖ በመታከል ሲታከል በዚህ ውስጥ ነጭ ለባሽ ተለይቶ አይሆንም። መደመሩ ጨርቅ ለባሾችንም ይጨምራል። ብረት መዝጊያ ዘመድ ያለውን ብቻም አይደለም የለም። ዘመድ አልቦሹ እንደ ባተሌዋ ዓይነት ሥርጉተ ሥላሴ ዕጣ ነፍሳትን ሁሉ ነው የሚያጠቃላልው። የፖለቲካ ማንፌስቶ ማህበርተኛም ማህበርተኛ ያልሆነውንም፤ ጤናው ሙሉ የሆነወም ያጣውም፤ አካሉ የተጎዳውም ሙሉ አካለኛውንም፤ ያለውንም የሌለውም፤ ህፃኑም ሽማግሌውም፤ ፅንሱም ለመጸነስ ሃሳብ ያለውም፤ ታዋቂ ባለቀይ ምንጣፉም፤ ተርታው የእኔ ቢጤም ትቢያ ላይ ያለውንም፤ የፆታ፤ የዕምነት፤ የብሄር ብሄራሰብ ልዩነት የለውም፤ የቦታ የሁኔታ ልዩነት የለውም። የተማረ ያልተማረ የለውም። እግሊዘኛ ቋንቋ ተናጋሪ አልተናግሮም አብረው ነው የሚደመሩት።

  • ·       ርደት።

እንግዲህ ጋዜጠኛ መሳይ መኮነን የአሁኑ መደመር ያስፈራው እዚህም ውጪ አገርም ሆነ አገር ቤትም ግንቦት 7 ያገለላቸውን፤ የገፋቸውን፤ አንያችሁ ያላቸውን፤ ያሳደዳቸውን፤ ማህበራዊ መሰረታቸውን አይሆኑ ያደረጋቸውን ማህበረሰቦች፤ ግለሰቦች፤ የፖለቲካ ድርጅቶች፤ ታዋቂ ግለሰቦች ሁሉ የጠ/ ሚር አሜኑ ካቢኔም ያግል ነው ቁምነገሩ፤ ፍሬ ነገሩ። እናትዬ ይህማ ተኖሮሮበታል።
የሥርጉተ ሥላሴን ጹሑፍ ያተመ ውግዘ ተርዮስ፤ ሊንኩን የለጠፈ ውግዘ  ተአርዮስነቱ። ጉግልን ሸር ማድረግ እንኳን ዕቀባ አለበት። ብቻ መሬት ላይ ይህ የሴራ መረብ የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ ያበቃ ያከተመ ጉዳይ ነው። ሞተ ተቀበረ አግላይ የፖለቲካ ባህል። ቀብሩን አብረን አበሠርን ለዚህ ነው ሽንጣችን ገትረን ስንሞግት የባጀነው።

ሰዉ ዛሬ በሚያደርገው ነገር ብቻ ነው የሚፈረጀው፤ የነገን እንርሳ ነው የመደመር አይዲዎሎጂ … ሁሉም ነገር ወርቅም ቢሆን ከሰው በታች ነው። ሰውነታችን ይበልጣል ነው። ይህን ደግሞ ለወረቀት አምላኪዎች ሁሉ ሁሉም ነገር ከንቱ ስለመሆኑ ከሁሉ የሚበልጠው ሰው መሆን መቻል ስለመሆኑ እንደ ሃይማኖት የያዙ ቅዱስ ሰው ናቸው ዶር አሜኑ አብይ አህመድ ማለት። ደንበር አይሰሩለትም ለተፈጥሮው …  

Ethiopia Dr abiy ahmed በመጀመሪያ ካፖርትህን አዉልቅ


በኢትዮጵያ በአነሰም በበዘም በደለመ፤ ጠቀመ ትልቅ ሃላፊነት ላይ የነበረ በምስጋና እና በሽልማት እኮ ነው የተሰናበተው። ወደፊት ሴረኞች በዚኸው ቀጥለው የትግራዩ መንግሥት እና የአዲስ አበባው ፌድራል መንግሥት ቀዝቃው ጦርነት ውስጥ ስላሉ የትግራዩ መንግሥት ቢሸነፍ ተጣርቶ ህግ እና ፍትህ ብቻ መልስ ይሰጥበታል። ከቂማዊ ፖለቲካ በጸዳ መልኩ። በዝንቅ መንፈስ የተቀላቀለውም ሆነ ሊቀላለቀል የሚፈልገው ጥራቱን ራሱን አምጦ ማምጣት ካልቻለ እዬሾለከ ነው የሚቀረው። ዘመኑ ሰብዕና በሙሉነት ተደላለድሎ መሬት መርገጥ መቻል ስለሆነ።
  • ·       ርትህና መንፈሱ።

በፍትህ ሥርዓት መሪነት ከሆነ ቂም አያቋጠርም። ለጥፋቱ ተገቢውን ቅጣት የሚሰጠው ህጉ ድንጋጌው ብቻ ይሆናል። ቅጣቱን የሚሰጠው ህግ መንግሥቱ ነው። ቀድሞ ነገር ራሱ ወያኔ ሃርነት ትግራይ ለራሱ ዘመነ መንግሥት ቀጣይነት ቢሆነም ከህግ በላይ ሆኖ ለመኖር ዘመኑ አልቆበታል። የተወሰኑ ሰዎች በዚህ ህዝባዊ የፍቅር እና የምህረት ቀን የትግራይ ልጆችም ደስተኛ እንዳልነበሩ ሲጽፉ ዩቱብ ላይ አነባለሁኝ። ተው እንጂ አባይ ሚዲያ ዶር አብይ አህመድ ላይ በነበረው የደህንነት ጫና ሠራዊቱ ከሁለት ተከፍሎ እንደ ነበር መረጃ ሰጥቶናል። እኔም የእሱን መረጃ አምኜ በተደጋጋሚ አምስግኜ ጽፌያለሁኝ ለዶር አብይ አህመድን ተገን ለሆኑ የወያኔ ሃርነት የሠራዊቱ አባላት።

ቢያንስ አምነት ሃይማኖት አለኝ የሚሉ አዲስ አባባ ተወልደው ያደጉ የትግራይ ልጆች ለውጡን ባለመቃወም መንፈሳቸው በገለልተኝነት የነበሩ ሊኖሩ ይቻላሉ ብሎ ማሰብ ጤነኝነት ነው። መደመሩ እነሱንም የሚያካትት ስለሆነ። የኪነ- ጥበብ ሰውማ ቅርንጫፍ ነው። ግንዶቹ መሥራቾቹ እኮ አሉ በነፍሳቸው አገር ውስጥም ውጪ አገርም። እነ ዶር አረጋይ በርሄ እነ አቶ ገብሩ አስራት እኮ ተደማሪዎች ናቸው የወልቃይት እና የጠገዴ ደም ፈሶ። በመደመር ውስጥ ሁሉም መኖሩ ግድ ነው። የወያኔ ሃርነት ትግራይ የሠራዊት ዋና ኢታ ማጆር ሹም አዛዡ እኮ በክብር ነው የተሸኙት።
  • ·       በክፋት መቅናት ሰውነትን ይዳፈራል።  

በክፋት፤ በተንኮል፤ በሸር ፤ በሴራ ፤ በሚዛን አልቦሽንት መቅናት አይገባም። ክፋት ሰውነትንም ይዳፈራል። እናንተ አትሁኑ ግን ሌላው ሲያደርገው አትቅኑበት። ጎንደር ስስታም ሰውን ዓይነ ጠባብ ይለዋል። ስስታምነት የእህል ብቻ አይደለም። ለሌለው በሚሰጠው ክብር እና ሞገስን በጠናና ማዬት፤ ማጣጣል ያው ዓይነ ጠባብነት ነው። ዓይነ ጠባብ አትሁኑ። 

ልቦናችን፤ ሆዳችን ብቻ ሳይሆን ዓይናችንም ይስፋ። አሁን እነዚህ የተጠቀሱት የምናውቃቸው ወያኔ ሃርነትን ትግራይ አባላት ከፍ ባለ ኢ- ሞራላዊ ሁኔታ ሲያደገድጉ የነበሩት ለኢሳት አቀባበል ቢያደርጉ ቦሌ ላይ ዋና ተቀባዩ አቶ ሠራዊት ፍቅሬ ቢሆን መጋረጃ ልትሉ ነውን ኢሳቶች? አቶ አርከበ እንቁባይ ቢሆኑስ? በቃ ቦሌ ላይ ግንቦት 7 ሲገባ ዶር ደብረጽዮን እንዲሆኑ ቢደረጉስ? ወይንም አቶ ልደቱ አያሌው ጋር ጎን ለጎን ለግንቦት 7 ውክል አካል ወንበር ቢዘጋጅ ምን ልትሆኑ ይሆን? ባለፈው ጊዜ ከግንቦት 7 ጋር VOA ከኢዴፓ ጋር ቃለ ምልልስ ነበረው። እና ተቆርጦ ነበር ተልጥፎ  ያዬሁት። መቻል አለብን። መስፋት ያሰፈልጋል። ጥብቆነትን 21ኛው ምዕተ ዓመት ተፍቶታል። አሁን እኮ በ አንድ የመረጃ መረብ ተጋብታ ወልዳ ከብዳለች።
  • ·       ወልደግራው ነፍስ።

ይህ ማለት በዚህ የመደመር ፖለቲካ ምን እና ምን ሊሆኑ ይሆን ያሰኛል? ነፍሳቸውን ይማረው እና ኢንጂነር ሃይሉ ሻውልስ በህይወት ቢኖሩስ? እራስን በሁሉም ዘርፍ ማስናዳት ያስፈልጋል። የማይደገፍ የፖለቲካ ድርጅት ቢኖርም ግን ሃሳቡን ስትጠላው ስብዕናውን ደምረህ ከሆነ ከባድ ፈተና ነው። የፈጣሪ ፍጡር ስለሆነ የፈጣሪ ሥራን መዳፈር ይሆናል፤፡ ስትጸልይ ፖለቲካውን የማትወድለትን ጨምረህም እንዲኖር፤ ልቡን እንዲ መልሰው ወደ መልካም ነገር አብረህ ጸሎት እማታደርስለት ከሆነ ከእንሰሳ ምን ይለዬናል? ሁሉም የኢትዮጵያ ሃብት ነው እሾኽ አሜኬላ አይንካው፤ ካላልክ ምን ስውነት አለና። ይህን መድፈር ከተሰናህ ባትስበው ይሻላል ይህን የአብይን መንፈስ የመደመርን አይዲዎሎጂ።

ለጨካኞች፤ ለክፉዎች፤ ለአረመኔዎች ፍርድ ሰጩ ደግሞ አማኑኤል አለ። ለእሱ መስጠት። ልብን ከበቀል፤ ከቂም፤ ከሸር፤ ከሴራ፤ ከተንኮል ማጽዳት በእጅጉ ያስፈልገናል ከሊቅ አስከ ደቂቅ። በሥም ልዋጭ የፖለቲካ ድርጅት ምሥረታ እና ፍርስት ስንት ነገር እንዳፈረስን በስንት እናቶች ማህጸን እንደተጫወትን በምልሰት ራስን መውቀስ በአግባቡ ይገባል። ንሰሓ መግባት። ሃይማኖቱ ከኖረ። ደብቀን ለያዝነው የወንበር ግብግብ ነው የኢትዮጵያ እናቶች 43 ዓመት ለሥልጣን ሱሰኞች ማህጸናቸውን በቦንብ ሲያስጨፈጭፉ የኖሩት። 

ያ ሳይጎረብጥ አሁንም የሴራ ቡድን አደራጅቶ በዛው መንገድ መጪ ማለት የጎንዱ ተክልዬ እባክህ አንድ በል ያሰኛል። ሰው ስንት ጊዜ ደጋፊውን እያሰለፈ ሃሳብን በፋስ ይፈስፍሳል?   

ቀደም ብዬ ጽፌዎአለሁኝ ኤርትራን በውስጣቸው እንደ ነበረች በሚመለከት አሁን በእራት ግብዣው እንዳደምጥኩት ለካንስ „የሦስት ማዕዘን“ ድርሰት ላይ ተሳትፈዋል ዶር አብይ አህመድ። ኢሳት ለፖለቲካ ሸቀጥ፤ በደፕሎማሲ ቅርቅራ ለማስገባት ይላል እሳቸው ደግሞ የአንድ ደም እና ሥጋ ልጆች መለያዬት የለብን ናፍቆታችን ቢያንስ ይለፍለት ባይ ናቸው። ኢሳት ከቴዲ አፍሮ ወሰደዱት ይላል ኢትዮጵያዊነትን እሳቸው የሰለጠኑት አገረች ወላጆቻችን በጉልበታችን ገነቡት ይሉናል። አቶ ሃብታሙ አያሌው ኢትዮጵያዊነትን ከቴዲ አፍሮ እና ከጥላሁን ወሰዱት ይለናል እሳቸው ደግሞ ስለ ዓለም ጥቁሮች እንዲህ ይሉናል።

Ethiopia Dr abiy የሰዉ ልጆች ልዩ ብቃት ክፍል አንድ


ይህም ብቻ አይደለም አቶ ሃብታሙ አያሌው የወያኔ ሃርነት ትግራይ ካድሬ በነበረበት ጊዜ የሳቸው ቋጠሮ ይህን ይመስል ነበር በጥቂቱ ትርጉሙን ጀምሬው አልጨረስኩትም ወደ ሁለት ወር ሆነው ክፍዬ ነው ያቀረብኩት

„… እናቴን የአንቺን ሥም ዝናር ድግ አድርጌ
አንችን አደግድጌ
አንችን አንችን እሚሉ
ሲሆንም ሳይሆንም
ሲሞላም ሰይሞላም
ሁሉን እንደ ሁሉ ስላንቺ ሚችሉ
ከጉያሽ ሚውሉ ልጆች ልሰራልሽ ከመባከን ሌላ
ፍቅር ልዘራብሽ ከመኳተን ሌላ
ለዘጻዕት ጉዞሽ ከመሰጠት ሌላ

አንቺም ታውቂያወለሽ የለኝም ሌላ ቃል ከትንሳኤሽ ኋዋላ
ውዴ ታውቂዋለሽ ውዴ ታውቂኝ አለሽ
በመከራሽም ቀን አብረን ተኗኑረናል
ዛሬ ሳይሆን ትናንት አሁን ሳይሆን ድሮ
ያኔ ምንም ሳልሆን ምኔም ተቀይሮ“

አሁን አማረብኝ ባይል አቶ አሃብታሙ አያሌው ጥሩ ነው። ልኩን ቢያውቅ። ጎንደር የ2009 በእለ ደመራ ተጋድሎ ሌቦቹ ሊቀሙት በኮፒ ራይት ሲናጥ አስተውሎቱን የገለጸበት „አንከባባር!“ ነበር። በዛው በመስቀል ደመራው ውድድርም አሸናፊው ቡድን ሽልማቱን ቤቱ ድረስ ሄዶ ለጀግናው ቤተሰብ አበርክቷል። ሌላው ምን አገባህ በተጋድሎዬ የተጋድሎ መሪ አለው የሚል የታሪክ ዱላ ለዘራፊዎች ልኮላቸዋል። እኔም አቶ ሃብታሙ አያሌውን በዚኸው አጋጣሚ „እንከባባር!“ ልለው እፈልጋለሁ - በአጽህኖት።

የሆነ ሆኖ የክት እና የዘወትር የዓለም ዜጋ እንዳይኖር ነው አምንስቲም ሂዩማን ራይትም፤ የቀይ መስቀልም ድርጅቶች የተቋቋሙት። እራሱ የተባበሩት መንግሥታት ዓላማ እኮ ይሄው ነው። ስለዚህ ይህን የ አብዩ መልካም መንፈስ እግሩ ሥር ወድቆ ነው የዓለም ህዝብ እንኳን ደህና መጣህ የሚለው። ለዛውም አፍሪካ ላይ። ቆዩ ሽልማቱን ታዩታላችሁ። የኤርትራ ህዝብ እራሱ ናፍቆትህን ያሻህን ያህል ውሰድ ግዛን ንዳን ነው የሚለው ፍቅር አትራፊ ነዋ። የሚደፍረው ካገኘ። ማጠቃለያው ቀጣይ ነው …

አዶናይ ሆይ ሁሉ ይቻልሃልና ልቦና ስጠን!
ኢትዮጵያዊነት ከመፈጠሩ በፊት ፈተናን አሸንፎ የተፈጠረ ሚስጢር!

የኔዎቹ ቅኖቹ ከጥቂት ሰ ዓት በኋዋላ ደግሞ ማጠቃለያውን ይዤ ከች እኔ ሎሌያችሁ።  ኑሩልኝ። 

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።