ክፍል አራት ርትህ።
ርትህ።
ክፍል አራት።
ከሥርጉተ © ሥላሴ 01.06.2018
(ከመንኩሲያዋ ሲዊዘርላንድ።)
„የሚምሩ ብብፁዓን ናቸው ይማራሉ እና“
(የማቴወስ ወንጌል ምዕራፍ ፭ ቁጥር ፯)
- · መነሻ።
ጠ/ሚ ዶ/ር አብይ አህመድ ከአፋር ህዝብ ጋር ያደረጉት ሙሉ ውይይት PM Dr Abiy Ahmed discusses with the people of Afar
- · የወግ ገበታ።
ውዶቼ ቀደም ሲል የነሳኋዋቸው ከክፍል አንድ እስከ ሦስት ድረስ ለመነሻ መዳረሻ የሚሆኑትን ብቻ ስለነበር ሊንኩ አለጠፍኩትም ነበር። አሁን በዚህ በክፍል አራት የምናዬው ጠ/ ሚር አብይ አህመድ ሠመራ በነበረው ጉባኤ ላይ የሰጡትን መልስ አስኳል ጉዳዮችን ማዬት ስለሚያስፈልግ ነው። በዚህ ክፍል እስከ መግቢያዋ ላይ ያለችውን ጥላቻን ብቻን ማዬት ብንችል ብያለሁኝ አሁን። እንዳይበዛ እንዲሁም አሰልቺም እንዳይሆን።
„ሰው ጠልተህ መተኛት አትችልም። ሌሊቱን ሰውዬው በሌለበት ስትቃጠል ነው የምታድረው። እሱ አያይህም። ያለህበትን ሁኔታ አያውቅም። አንተ ግን ስትቃጠል ታድራለህ። ከዚህ ውጪ መወጣት አለበት። ሰውን ለመጥላት መሮጥ ነገርን ለማሰብ አዕምሮአችን ማበላሸት የለብንም! ጊዜያችን ማጥፋት የለብንም! እኛ ምን እንደርጋለን? ሰው እንወዳለን! ሰው እናቀርባለን! እስከተቻለን ድረስ ሰውን እንረዳለን። ነገር ግን የሚጠሉን ሰዎች እንደሚኖሩ እናውቃለን። ዓለም እንዲህ ስለሆነች። ሰዎች ሲጠሉህ አንተም ቁልቁል ተመልሰህ ጥላቻ ውስጥ ከገባህ በእነሱ ሜዳ ውስጥ ገብተህ እዬተጫወትክ ነው ማለት ነው። የጦር ሜዳውን እንቀይር እምንለው ለዚህ ነው።“
ከዶር አብይ አህመድ የተወሰደ።
- · ጥላቻ።
ይህን መከራ ተሸክሞ አላዛሯን ኢትዮጵያ ለመታደግ ከባዱ ፈተና ነው። ሁላችንንም የሚፈትን እከሌ ተከሌ ሳይባል፤ ከሊቅ አስከ ደቂቅ ድፍረቱን ለማምጣት መርጋችን ነው። ጥላቻ ነው ቂምን፤ በቀልን፤ ቁርሾን፤ ቋሳን፤ ግለኝነትን፤ ዓይነ ጠባብነትን፤ ስስታምነትን፤ ስግብግብነትን፤ መግደልን፤ ማሰቃዬትን፤ ማሳደድን፤ ሴራን፤ ተንኮልን፤ ሸርን፤ ማግለልን፤ ማስገለልን፤ ማስጠላትን የሚያበረታታው።
ጥላቻ መንቀል እንዲቻል ራስን ማሸነፍ ካልተቻለ በዓዋጅ የሚመጣ አይደለም። ስሜትን መመዘን፤ መግራት የሚችለው ከጥላቻ የጸዳ ህሊና እንዲኖር ባለቤቱ ሲፈቀድ ብቻ ነው። በዚህ በተኖረበት የ43 ዓመት የድምጽ አላባዎቹ የኢትዮጵያ እናቶች መከራ መሰረታዊ ጉዳይ የፍቅር ረቂቅ ተፈፍጥሯዊ ችሎት ያለረታቸው ተባይ ስሜቶች የፈጠሩት ጦርነት ነው።
ጥላቻ ሃጢያት ብቻ አይመስለኝ - ለእኔ። እኔ ሰው የተፈጠረበትን አምክንዮ ለመግደል የተነሳ እርግማን ነው። ሰው ጥላቻን በቀረበ ቁጥር እና ከጥላቻ በራቀ ቁጥር በስብዕናው አፈጣጠር እና ተልዕኮ ላይ የሰማይ እና የምድር ያህል ልዩነት አለው። ምክንያቱም ሰው የመሆነን መሰረታዊ ምርቃት እዬገደለ በሬሳው ላይ መኖር መፍቀድ እና ሰው ለመሆን የተሰጠውን ምርቃት እዬተመገቡ ለመኖር መፍቀድ የማይገናኙ መንገዶች ስለሆኑ።
ጥላቻ መጀመሪያ የሚመለምለው የራስን ስብዕና ነው። ጥላቻ እንደ ተፈጥሮው የያዘ ሰብዕና በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ከዚህ ማእቀፍ ለመውጣት አቅም ያንሰዋል። ደካማ ነው። እጅግ ፈሪ ነው። በጣምም ተጠራጣሪ ነው። እንደራሱ ስለሚመስለው።
አልኮህል ጠጪዎች አልኮህል ካልቀመሱ ደማቸው ለመዘዋወር አቅም እንዲሚያንሳቸው ሁሉ ማለት ነው።
አንድን ነገር አጥብቆ እና አክሮ በጠሉት ቁጥር በዛ ውስጥ ያሉ መልካም ነገሮችን እንኳን ለማዬት አቅም ያንሳል። ወይንም በዛ አዬር ውስጥ ያሉ ቤተኞችን እንክራዳድ ከስንዴ ነጥሎ ለማዬት ይችግራል። ስለምን? ጥላቻ ዓይን ሳይሆን የህሊና ሚዛናዊ ዓይንን ስለሚያውር። ለምሳሌ አንድ መስታውትን ሙሉውን በጥቁር ቀለም ብንቀባው እራሳችን ሊያሳዬን አይችልም። እኔ እማዝነው ስለማያወቁት ሰው መከራን ስለሚያሳድሙ ሰዎች ብቻ ሳይሆን የማያውቁትን ሰዎች ሥምም ሳያውቁት ለሚጠሉትም ጭምር ነው። የኢትዮጵያ ፖለቲካ ዶግማው ይሄው ነው።
- ተዛነፍ።
ሌሎች መልካም ሰዎች ለምሳሌ እነ ሐሃሀዎች እንበል፤ ለእነ ጸፀዎች ጥሩ አቀራረብ ቢኖራቸው፤ እነ ሠሰዎች በእና ጸፀ ጥሩ ዕድል ድብን ብለው ይቃጠላሉ። ስለምን? እነ ጸፀዎችን ሰሠዎችን የመጥላት አድማ ውስጥ ሐሃሀዎች አባል መሆን ስለማይፈቅዱ። በጥላቻው የጽዋ ማህበር ስላልተደመሩላቸው። አሁን ምን አለበት ሐሃሐዎች ጸፀዎችን ቢረዱ። ሰሠዎች እርዱ ደግፉ አልተባሉም እኮ። ሐሃሀዎች እናመሰግናለን ጸፀዎች ቢሉ እንኳን ቃሉ ምንም የለበትም፤ ግን ለጥላቻ የተፈጠሩ ዕብኖች ይታመማሉ። አንዲት ቃል ስለወጣች። ይሄ ነው የድምጽ አልባ እናቶች መከራ ሲያመርት የኖረው ፍዳቸው። ልጆቻቸው በስደቱ መከራ ቀንበር አለበቃቸው ብሎ ሲሳዱዱ ራሳውን አጥፍተው እንዲሞቱ ሁሉ ሲፈረድባቸው የተኖረው።
እነዚያ ሰሠዎች ለሌሎች መልካም ሊሆኑ ይቻላሉ፤ ግን የማይመቻቸው በእነሱ የጠላትነት ዝርዝር ውስጥ የገባው ፍጥረት በዬሄደበት ተወግዞ፤ ተገሎ እንዲኖር ነው የሚሹት። መልካሞችም ሐሃሀዎች የእኛ እንጂ የሌላ መሆን የለባቸውም ባዬችም ናቸው። ስንጠላ ጥሉ፤ ከወደድነው ጋር ደግሞ ተዳበሉ ነው። ይህ እንግዲህ በፈጣሪ የሰው አፈጣጠር ላይ የኮፒ ራይት ባለቤቶች እኛ ነን ነው። ይህ እንግዲህ ሰው ሮቦት ሆነህ ኑር ነው። ሰሞኑን እንዳዬናት ሶፍያ ማለት ነው። ሰው ሰውን እፈጥራለሁ ብሎ ፍዳውን ያዬበት መረጃ አይዋ ዩቱብ አምጥቶ አይቸዋለሁኝ። እነሱም የትም ኑሮ የ እኛ ልብ የተገጠመላችሁ ግብዞች ሁኑ ነው የፍርደ ገምድሉ ብይን።
ስለምን? የጥላቻ አባል ለማሰባሰብ ትጉህና ታታሪ መሆን እንደሚያስፍልግ አይታወቅም። ጥላቻ በቀላሉ ማስተላለፍ የሚቻል መረብ ነው። አቋራጭም መንገድም ነው። አሁን በመደመር ፖለቲካ ያለው ፈተና ይሄው ነው። በሴራ ተቦክቶ የተጋገረው የኢትዮጵያ ፖለቲካ በምን አቅሙ እና ችሎቱ ከዚህ ብክል ሰይጣናዊ መንፈስ ጋራ ራሱን አፋቶ በጸዳ ጎዳና መንገዱን እንደሚመራ መዳህኒተአለም ብቻ ነው የሚያውቀው።
- · ማጣሪያ።
ሁሉም ከነ ጓዙ ስለሚደመር ማጣሪያ፤ ማንዘርዘሪያው ለእኔ የሚታዬኝ አንዱ ስሌላው ስለሚሰጠው ምስክርነት ራሱ የተመሰከረለት ሰው ወይንም የተመሰከረበት ሰው በአካል ፊት ለፊት የሚጠዬቅበት ሁኔታ ካልተፈጠረ አሁንም መተላላለቅ ነው የሚሆነው። ሴረኞች አቅማቸው ይሄው ብቻ ነው። አዬር ላይ ብከክላቸውን አረም መዝራት። የፈለገ ዓይነት ታዋቂ ይሁን ገመናው የ አደባባይ ሲሳይ ከሆነ ሌላው ያፍራል። በስተቀር አሁንም የሞተልሽ ቀርቶ የገደለሽ በላ ነው የሚሆነው እንደ ድንቁ የአማራ ተጋድሎ፤ እንደ ሚደያ አልባዋ ጎንደርሻ።
አንዱ ቤተኛ ሌላው እዳሪ ይጣላል። እንዲያውም ንጹሃን፣ ቅዱሶች ተገፊዎች፤ ተጋላዮች፤ እንደ ለመደባቸው በጨለማ ውስጥ እንዲኖሩ ከቀደመው በባሳ ሁኔታ ተሳቀው እና ተሸማቀው እንዲኖሮ ሊገደዱ ይችላሉ። ልክ እንደ አማራ የህልውና ተጋድሎ።
የጥሩ ሰዎች ስደቱ ቀላል በሆነ ቋንቋ አልገልጸውም። ንጹሃን መፈጣራቸው ለፈታና ነው። ሲሳደዱ ነው የሚኖሩት። አሁን በዚህ የመደመር ፖለቲካ ሁሉም ከነገመናው ለመከተም ስለሆነ ሩጫው እና ሽሚያው „እኔም ተደምሬያለሁ“ የሚለው። ከመደመሩ በፊት ግን የዕምሮ ሳውና መግባት እንዳለበት አያውቀውም።
እያንዳንዷ የብዕር ጠብታ፤ የቃል ጠብታ በጽኑ ከዚህ ውስብስቡ ስብዕና መንጦላዊት መንፈስ ጋር የተገነባ ነው። ስሌሎች ክፉነት ለመግለጽ ራስም ከክፉነት ምን ያህል ተጽዳድቷል የሚለው ነገር አይነሳም። ስንቱ አቅም ነው እንዲህ ባክኖ፤ በኖ፤ ተኖ የቀረው። ስንት ደግ ሰዎች ናቸው አልባሌ ሆነው የቀሩት። ስንት የሃብት ሃብት የሆኑ መንፈሶች ናቸው ባልሂ ባይ አጥተው የቀሩት።
እኔ የሚደመሩት የፖለቲካ ድርጅቶች ሁሉ መጀመሪያ የህሊና ማጽጃ ላውንደሪ መክፈት አለባቸው። እስከ ደጋፊዎቻቸው እስከ አባሎቻቸው እስከ አድናቂዎቻቸው ድረስ።
ስለሆነም ጥላቻ ክፉ ነገር መሆኑን ጠ/ ሚር አብይ አህመድ ዛሬ ሳይሆን በቀደሙ አገላለፆች ሁሉ ሲናገሩ፤ ሲመክሩ ነበሩ። ልዩነቱ ብሄራዊ አቅም መንፈሳቸው ማግኘቱ ብቻ ነው። እኔ እንደ ሥርጉተ ሥላሴ ትቢያ ላይ ናት ብለው ካልተዉት በስተቀር የዚህ የመደመር ፖለቲካ እና ዕጣ ፈንታውን አያያዝ በሚመለከት ግልጽ የጠራ የመስምር ንድፍ ሊኖረው ይገባል።
በወል ከታታሪዎች፤ ከካድሬዎች፤ ከተፎካካሪ ፓርቲዎችም፤ ከራሱ የግንባሩ ሰዎች ጋር በውል በምህላ ላይመለሱበት በአጀንዳ ሊወያዩበት ካልተቻለ አሁን የሳቸው ንዑድ መንፈስ ታጥቦ ጭቃ ነው የሚሆነው። ያሰፈሰፉ ተባይ መንፈሶች ሁሉ ጠልፈው እዛው ረግረግ ውስጥ ከዘፈቋቸው፤ ተስፋ ወደ መቃብር ነው። ተስፋው የሚሊዮን ነው። የእኛ ብቻም አይደለም ሉላዊም ነው። በትዝብት እና በጥንቃቄ የሚከታታሉት ብዙ የሉላዊ ሰዎች አሉ እና። መሪዎችም።
የተኖረበት የሚገለማ መራራ ዘመን ከባድ ነው። አምላክ የሰጠው መክሊት በግዞት የኖረበትን ዘመን በቃህ ለማለት ከሴራው ፓለቲካ ጋር በህሊናዊ የውህደት መንፈስ ለመቀጠል ፈተና ነው። ለአንዲት አዳራሻዊ ስብሰባ እንኳን ስንት ነገር ነው የሚደመጠው?
እኔ እምጮኸው ለድምጽ አልባዎቹ ንጹሃን ነው። በዚህም በተቋጠረ ቂም ለቀጣዩም እንሱ ተጠያቂ እና ተገፊ እንዳይሆኑ ስጋቱ አለኝ - በገዘፈ ሁኔታ።
- · ምስክር ተመሳካሪ አመሳካሪ።
ስለዚህ ስለ ማንኛውም ሰው ምስክሩ ተግባሩ፤ መንፈሱ፤ ነፍሱ ቢሆን የተሻለ ይሆናል። ርትህ ለዚህ ጊዜ ነፍስም፤ ትውልድም መንፈስም ለማዳን ዘብአደር መሆን አለባት።
የጥላቻ ፊታውራሪ ስለፍቅር ብትገልጽላት አይገባውም። ልሁንም ቢልም አያምርበትም። በፍቅር ተፈጥሮ ለመኖር ሲወስን ራስን ማሸነፍ ግድ ነው። ተዚህ በስደቱ የመከራ ጥቁር ዘመን እኔን ሲያሳድድ የነበረ አሁን አገር ገብቶ ለፍትህ እና ለርትህ ጠበቃ ይሆናል የሚል እኔ ቅንጣት ታክል እምነትም ተስፋም የለኝም። ስደት እርግማን ነው። እርግማኑን ውሃ ባዘለ ተራራ ያሸከመኝ መንፈስ የነገ የብሩህ ተስፋ ተባባሪ እና ሥራ አስኪያጅ ይሆናል ብዬ አላስበውም።
- · መቆለል።
መጀመሪያ የፖለቲካ መሪዎች ከተጠቀለሉበት የመረዝ አዟሪት ራሳቸውን ማውጣት አለባቸው። እራሳቸውን በራሳቸው ማዳን ይጠበቅባቸዋል። ላናባከኑት የትውልድ ነፍስም በግልጽ ቋንቋ ይቅርታ ሊጠይቁበት ይገባል።
ማሳደድ የማይታክታቸውን የካድሬዎቻቸውን መንፈስ ለመግራት ይድፈሩት። እነሱም ከራሳቸው ከተጠናወታቸው የምናብ ተራራ ወርደው በሁለት እግራቸው ሰው መሆናቸውን ያረጋግጡ። ሰው ሰው ሆኖ የተፈጠረው እንጂ ዘውድ ደፍቶ አልተፈጠረም። ንጉሥ ሆይ! እዬተባሉ እንዲኖሩ ያደረጉትን ትብትብ ቅብ የመኖር ሳንክ ጋር ይፋቱ።
እኔ እንደ አንቺ፤ እንደ አንተ፤ እንደ ሁላችንም ሰው ነኝ። ከአንቺ ከአንተ ከእናንት ከሁላችሁም የምበልጥበት ምንም ነገር የለኝም።
ህዝብ የሚሰጠኝ ክብር እንጂ እኔ የቆለልኩት ክብር ቁልል አመድ ነው ብለው አምነው ይቀበሉ። አሁን አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ሁልጊዜ ያልተገባኝን አትስጡኝ እያሉ ሲማጸኑ አዳምጣቸዋለሁኝ። ስለዚህም እሳቸው ባይፈልጉትም እኔ ግን እንዳከብራቸው ተገድጃለሁኝ። ዶር አብይም አህመድም ቢሆን ፕሮፌሰርነት ዶር.ርነት ሰው ከመሆን በላይ አይደለም።
ሁላችንም ጃኬታችን አውልቀን መሬት እንርገጥ ስላሉ አክብራቸዋለሁኝ። ከአረብ ኢምሬቶች ጉዞ በኋዋላ በተገኙበት የህዝብ ስብሰባ ላይ „ሳለገኛችሁ እቀራለሁ ብዬ፤ ታመልጡኛለችሁ ብዬ አስቤ ነበር እግዚአብሄር ያክብርልኝ“ ሲሉ ከልቤ ጠብ ነው ያለችው። መሪ እንዲህ ራሱን ተራ እና ቀላል ሲያደርግ ነው መከበር፤ መደመጥ የሚገኘው። ከዚህ በላይ ፈጣሪም የተመኘውን ሁሉ የሚባርክለት።
🎆🌌🌌🌌🌌🌌🌌🎆
በፍቅር የተፈጥሮ መርህ ለመኖር ስትቆርጥ አንተ ራስህን ያሸነፍክ ጀግና ነህ!
🎆🌌🌌🌌🌌🌌🌌🎆
ወዶቼ ይቀጥላል …
ኑሩልኝ እስተዘላለሙ!
መሸበያ ጊዜ!
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ