መሆን ይቅደም!

ህልምህን ስታገኘው በህልምህ ውስጥ ለመኖር ፍቀድ።
„አስተዋይ መልካም ምክርን ገንዘቡ ያደርጋል“
(ምሳሌ ምዕራፍ ፩ ቁጥር ፭)
ከሥርጉተ ሥላሴ 11.07.2018
(ከጭምቷ ሲዊዘርላንድ)



  • ·       ጠብታ።

የሚገርሙኝ ነገሮች እጀግ በራካታ ናቸው ዛሬ ጥዋት ዩቱብ ያቀረብልኝ የዓለም አቀፍ ጋዜጠኛው የአቶ አለምነህ ዋሴ ዶር ለማ መgርሳ ለጨፌ ኦሮምያ ጉባኤ ያደረጉትን ንግግር መሰረት ያደረገ ነበር። „የያዙት ወርቅ ከመዳብ ቁጥር“ ነው እንዲሉ ያገኘነውን ወርቅ አያያዝ እንወቅበት የሚል ሁለንትና ዕድምታ አለው።

እኔ ደግሞ የቀደመውን ብሂል ገልበጥ ላድርግ እና የያዙት ወርቅ ከመዳብ ሳይሆን ከብረትም አንሷል ባይ ነኝ። አዎን ዘመናይነቱ፤ ቅልጣኑ፤ የኬክ ቁረሱልኝ አቃቂሩ ስለሚያቅለሸልሸኝ። የትም ዓለም በዚህ በ100 ቀን ታይቶ የማያውቀውን ትንግርት ነው አላዛሯ ኢትዮጵያ እያስተናገደች ያለችው፤ ዕውን አላዛሯ ኢትዮጵያ ናት ይህን ሁሉ የተግባር ዕንቁ በመሰብሳብ ላይ ያላቸው ያሰኛል?

እኔ የጠበቅኩት ነው። ከመጀመሪያውም ጀምሬ የተጋሁበት ነው። እንዲያውም ይህ በግራ በቀኝ ውጥረት እና የሰላም ህውከት እዬተዋከበ የተከወነ ሲሆን የተረጋጋ ሁኔታ ቢገጥመው ምን ሊሆን እንደሚችል ሳስበው እራሱ ደረጃም፤ ልክም ለማውጣት ይቸግረኛል። ህውከቱን የወያኔ ሃርነት ትግራይ በፊታውራሪነት ያልታደለ በሉትና፤ ሌሎቹ ደግሞ የቤተመንግሥቱ ወንበር ቀረብን ያሉ ናቸው። ለውጡን ሊደግፉ ሲገባ ለውጡ ተቀልብሶ ለእነሱ የቀይ ምንጣፍ አሸሼ ገዳሜ እንዲውል ነበር ያለሙት። መከራው ይሄው ነበር። ቢሰጣቸው እኮ ለግማሽ ቀን አይችሉትም። ምክንያቱም ትንፋሻቸው ያጠረ፤ ዓይናቸው የጠበበ፤ ትእግስት ያልፈጠራላቸው፤ ሃሳብ ማፍለቅ እርማቸው የሆነ ስለሆኑ …
  • ·       ሰናይት ስትመጣ።

የሰው ልጅ ከሚያስበውም፤ ከሚያልመው ውጪ በሆነ ሁኔታ በዚህ ሁሉ ወጀብ ውስጥ የዚህ መሰል ፍሰሃ እና ሰናይ ባለቤት እንደሆን ዕድሉ ሲገጥመው ኢትዮጵያዊው ሰው በአልክሆልም አይደለም መቀበል ያለበት፤ በሱባዬ በፆም በጸሎት እንጂ። ተደሞ እጅግ ያስፈልገናል። 

ጥሞና እጅግ ያስፈልገናል። ለዚህ ነው እዮባዊነት በእጅጉ ያስፈልገኛል ብዬ የጻፍኩት። ሁሉም ተሞከረ፤ ስብሳባ አለበት በታበለበት ቦታ ሁሉ የአካባቢን ሰው በተናጠል በማነሳሳት ህውከትን እልቂትን መፈናቀልን ተስተናገደ ትግራይን ሳይነካ። የትግራይ ልጆች ሞኞች አይደሉም፤ አካባቢያቸውን በብጥብጥ አንኩረው ርካሽ ትርፍ ለመዛቅ የሚያስቡ አይደሉም። ሊሂቃኑ በታላቋ ትግራይ ህልም በትግራይ የውስጥ ሰላም እና መረጋጋት፤ ተነጥላ መበልጸጓን ትግራይን ይስማማሉ። ታታሪዎቻቸውም እንዲሁ። 

ሁሎችም በተመሰጠረ የሥነ - ልቦና የበላይነት ትግራይ ከፍ ብላ እንድተዘልቅ ይፈቅዳሉ። ስለዚህ ለወረት ብለው ሰው አሰናድተው የፎቶ ቴንብር አያስለጥፉም በዬስብሰባው። መሳቂያ ለመሆን አይፈቅዱትም።
የሌላው ፖለቲካኛ፤ ሊሂቅ፤ ትጉሃን ደግሞ ሌላ ነው ስሜቱ ሌላ ነው የሚበጠብጠው የሚያነኩረው ነገር። አንድ ሰው ስለሚናገረው፤ ስለሚያውጀው፤ ስለሚዘነቁለው ነገር አካባቢውም አብሮ እንደሚነሳ ፈጽሞ አያውቀውም። እርግጥ ነው አንዳንድ አካባቢዎች ዕድለኞች ናቸው።

 ከሞቀው ዘነቅ ይሉና የድል አጥቢያ አርበኝነቱን የክብር ልዕልና ይወስዳሉ። ሳይሞቃቸው ሳይቀዘቅዛቸው 27 ዓመት ሙሉ ትራሳቸወንኢ ከፍ አድርገው ከራርመው አሁን ደግሞ ባለቀ ሰዓት ዘራፍ ቡሉ፤ ሲባሉ ዛራፍ ሲሉ ተደምጠዋል። መቼም ይሄ የጠቅላይ ሚር ቢሮ ሳይረዳው አይቀርም። ሌሎች ደግሞ አሉ እንደ ጎንደር ያሉ በዬዘመኑ በጥርስ የተያዙ አካባቢዎች … በስክነት ውስጥ ያለውን ህዝባዊ ተደሞ ማድመጥ ተስኖ አሁንም በግለት ውስጥ የከተሙ ሚዛነ ዝበት አና ሰሊበት። „እንደ ዕድል ማን ይበድል“ ነው። ነገር ግን ሙሉው የጎንደር ህዝብ ሰናይትን በጸሎት መቀበሉ ተደምጧል።

ከዛ የሚወጡ ልጆች ግን ትንሽ ጥንቃቄ ብሎ አልሠራላቸውም። እርግጥ ነው ሁላችንም አብሮ የሚያድግ ነገር አለብኝ። የመብት መጣስን አሻፈረኝ የሚል የፖለቲካ ዝንባሌ አለብን ይህ ይታወቃል። ያ የፖለቲካ ዝንባሌ ግን የሥልጣን ጉዳይ ሆኖ በዕድሜዬ አይቼም ሰምቼም አላውቅም። እኔ አሁን ከዚህ አይደለም ለጋህዱ ዓለም ጉዳይ ኮሜቴ ውስጥ፤ ፓርቲ ውስጥ ልዶል ቀርቶ እንደዛ አፈር ግጬ ላደራጀኋዋት የዙሪኳ እመቤቴ እንኳን ከሎሌነት በስተቀር አንድም ቀን የሰባካ ጉባኤ አባል መሪ ለመሆን አልፈቀድከትም። አያምረኝም። ምን ሲያደርግልኝ ሥም እና ዝና። 

እንዲያውም ከእኔ ይልቅ የሌሎችን መልካም ሥራ ሲሰሩ ጎሽ በማለት ራስን ከማጉላት ሌላውን አጉልቶ አድንቆ ማውጣት ነው የሚቀደምን ሁላችንም። አሁን አርበኛ አንዱአለም አራጌ ይገርመኛል። ስለ እሱ ሳይሆን ስሌላው ገናነት ነው የሚተጋው … ይህ ትውፊታችን ነው። አሁን ግን ያን የጣሰ ነገር ነው እያዬሁ ያለሁት … እኛ ስለሽግግር መንግሥት ምን ይዶለናል? ምን አገባን? ለዛውም  አብይ መንፈስ የተሻለ ህልም። ይሄ እብደት መሆን አለበት። አዎን ….  በቅንጅት ዘመን እኮ አንደዛ  ያን ሁሉ መስዋዕትነት ጎንደር ከፍሎ አንድ ሥመጥር መሪ አልነበረውም። በደርግ ጊዜም አንድም የፖለቲ ቢሮ አባል የነበረ የለም። አሁን እንዲሁ ነው …

የኤርትራና የኢትዮጵያ ግንኙነት አትራፊው ለዛ መከረኛ ባድማ ለጎንደር እንጂ ለሌላ አልነበረም፤ ትግራዮችም አፋሮችም የቀረባቸው የለም። ሲቀጠቀጥ የኖረው ጎንደር ነው።  አሁን „ኢሳያስ ኢሳያስ ነው“  የሚለው ጹሑፍ ማንነን ለማሳሳት ታሰቦ እንደ ተፃፈ ይታወቃል። „ሥር ነቀል ለውጥም“ „የአኖሌም“ ጥያቄ እንዲሁ። ይህ የጎንደር የህዝቡ ጥያቄ አይደለም። የአማራ ተጋድሎን ያነሳቸውን መሰረታዊ ነጥቦች መመርመር እና ከዛ መነሳት ይጠይቃል። ህሊና ተብዬው አብሮ ከተኖረ።

የተጋድሎው ጥያቄ የአማራነት ህልውናዬ ይጠበቅ ደንበሬ ተከዜ ነው፤ ሱዳን የግራ ቀኝ ደንበሬ ነው፤ የተዛባ የአማራር ሂደት ይስተካካል በመሪዎቼ ልምራ ይሄው ነው። አማራነት ይከበር ነው። ይሄው ነው። አሁን በስተጀርባ በታቀፉ የፖለቲካ ስሜቶች እዬተነሳሱ የህዝቡን መሠረታዊ ጥያቄ ተቀልብሶ ሌላ አፈንጋጭ መልክ እንዲይዝ እዬተደረገ ነው። ስለምን? የያዙት ወርቅ ከብረት በታች ስለሆነ።

አንድ ድርጀት፤ ተቋም፤ ግለሰብ የሚፈተሸው የሚመዘነው የሚለካው በዛ ልክ ነው። እስኪ ሚሊዮን ኢትዮጵውያን የደገፉትን መንፈስ በሆነ ባልሆነ እዬሰነጣጠቁ፤ እዬተረተሩ አቅጣጫ መሳት ምን ሊባል ይሆን ከቶ? ይህን ለማረቅ፤ ይህን ለማስታረቅ፤ ይህን ለማስተካክል ደግሞ አይቻልም። ምክንያቱም ሞጋቼች የተገለልን ነን እና።

ቀድሞ ነገር ማን የትኛው ሊሂቅ ነው የአንዷን ቀን የአብይን ፍሬ አስብሎ ዓይናችን ከሰራው አድርጎ አይተን የምናውቀው? አሁን እኮ ችግኝ ሳይሆን ሰብል እኮ ነው እያዬን ያለነው። የፖለቲካ ሊሂቃን ስለሚባሉት አናዋቃቸውም።

በዚህ በስደት አገር በግዞት አስረው ያስቀመጡን፤ ሁለመናችን እስከ መክሊታችን ግዞት አደርገው የኖሩት የነፃነት ሃይል በማለት ራሳቸውን የሰዬሙት አንዲት ቀን ስልጣን ቢኖራቸው፤ አንዲት ቀን ሁኔታው ቢፈቅድላቸው ሥርጉተ ሥላሴ በህይወት ትኖራለችን? አይመሰላችሁ አትኖርም። ያ የመከራ፤ የስጋት፤ የሰቀቀን፤ የተስፋ ማጣት ጉም ነው የተገፈፈው። ያ የጭንቅ ዘመን ነው የታጠፈው።

እኔ ሥርጉተ ሥላሴ የማላውቀው አገር አይናፈቀኝም። የማውቀው የለማ ገዱ መንፈስ ሲሰኘኝ እዬወቃሁት፤ ሲያሻኝ እዬወቀስኩት፤ ሲያሻኝ እዬፈተንኩት ጥርት ብሎ በነጠረ መስመር እንዲቀጥል ነው የምተጋው። ምኞቴም ህልሜም ይሄው ነው። ለአማራ ደግሞ  ከኦህዴድ የበለጠ አዛኝም ደጋፊም የፖለቲካ ድርጅት የለም። 

እራሱ የአማራ ድርጅት የት ነው ያላችሁት? የት ነው የወደቃችሁት ብሎን ጠይቆን አያውቅም? ስለምን በ66ቱ ሴራ የተሸበለለ ስለሆነ … ይህ ደግሞ እኔ ገልምቶኛል … ስለ አማራ ከሆነ እዛ ተሰደደ፤ ተሰቃዬ፤ ተፈናቀለ ሳይሆን ከቅርቡ ስላለነው፤ ስለተሰደደነው፤ ስለተፈናቀልነው፤ ስለተገለልነው መታገል ይጀመር መጀመሪያ … አሻግሮ ጣሪያ ለጣሪያ ከሚኳትን …

እርግጥ ነው ከምንም መሻሉን ላልፈው አልችልም፤ እነ ጭልፊት አሁንም ማንዣበባቸው አይቀሬ ነው የአማራ ጠራጊ እና ሎሌ ስለሚያስፈልጋቸው …. በተጨማሪም ዓለም ዐቀፉን ማህበረሰብ ለማሳመን የሄደበትን መንገድም አደንቃለሁኝ። ግን ሁሉንም ማድረግ ይቻል ነበር ብልህነቱ ቢኖር። ይሄው ባለቅኔው ጠ/ሚር በ100 ቀን አፍሪካን ሰላሟን - ጤነቷን ሁሉ ወደ ተፈጥሮ ለመመለስ ስኬት ላይ ናቸው … ለዛውም በዚህ ዲያቢሎስ በከተመበት የመከራ ዘመን ዓለም ታስፈራኛለች።
  • ·       እም።

እርግጥ ነው ረቂቅ ነው። እርግጥ ነው ስውር ነው። ግን የነበረው መሰናዶ ሰው ከሚችለው በላይ የገዘፈ መከራ የኢትዮጵያ እናቶችን ይጠብቃል። የኢትዮጵያ እናቶች ስል እኔ በፖለቲካ አቋም አይደለም፤ በፍጹም። እናቶች ላይ ምንም የፖለቲካ አቋም የለኝም። ምክንያቱም በዛ ውስጥ የሞገደኛዋ ሥርጉተ ሥላሴ እናትም አለችና።

እኔ እኮ ሞገደኛ ነኝ። ምንም ነገር የማይገዛኝ፤ የማያታልለኛ፤ ስብር የማይደርገኝ። ግን ዕውነት እግር አውጥታ ከቤቴ ከደጄ ስትመጣልኝ ግን እልል ብዬ ለመቀበል ደግሞ ቁጥር አንድ እኔ ነኝ። „ጣና ኬኛ!“ ሲመጣ ሥርጉተ ሥላሴ ለማውያን ሆነች ካለምንም ቅድመ ሁኔታ፤ ከእለተ ሰንበት ጀምሮ ሥርጉተ ሥላሴ ደግሞ ያን ቡቡ ልባቸውን ሳይሰስቱ ያሰዩን የፕ/ ኢሳያስ አፈወርቂን በተመስጦ በጥሞና ተመልክታ ሥርጉተ ሥላሴ ኢሳያሳዊ ሆነች። ለማውያን + ኢሳያሳውያን= ሰዋውያን ይህም ማለት እኔዊነት ተሆነ ማለት ነው። ተፈጥሯዊነት ተሆነ ማለት ነው። ተፈጥሯዊነትም እኔዎነት ነው። ማለት ሥርጉታውያዊነት።

ቀደም ባለው ጊዜ በለማ፤ በገዱ፤ በአብይ፤ በአንባቸው መንፈስ፤ በካቢኔው ላይም  ኤረትራ እጇን ትሰበስባለች ብዬ አላስብም ነበር። ነገረ ኤርትራን የፖለቲካ ሂደቱን በሚመለከት ያደኩበት ፖለቲካ ስለነበር አስተርጓሚ አያሻኝም፤ ግን ሁሉ ለተዘጋባቸው የለውጥ ፈላጊዎች አንድ ፋሻ ማቅረብ ለእኔ ዋጋ ነበረው። ይህንንም አመስግናለሁኝ። ነገር ግን በኢትዮጵያ ፖለቲካ የኤርትራ ጥገኝነትን ትናንትም፤ ዛሬም፤ ወደፊትም አልደግፈውም፤ እነሱ አገር ናቸው፤ ሉዑላዊ፤ ስለዚህ በፖለቲካ ጉዳያችን ላይ ጣልቃ ሊገቡብን አልፈቅድላቸውም፤ እኛም እንዲሁ።

የተመኘሁት የሁለቱ አገሮች የእኩልዮሽ ግንኙነት እንዲህ በጠራ መሥመር ሲጀመር ደግሞ የበለጠውን ከእኔ በላይ የተደሰተ የለም። ሌላው በተዘጋ በር ነው ደገፍኩ ምንትሶ ቅብጥርሶ የሚለው። የሥርጉትሻ ግን ስትደግፍም ስትቃወምም በግልጥነት ነው። ከእኔ ጋር የሚስማማው እውነት ብቻ ነው። ትዳሬ ዕውነት ብቻ ነው።

እኔ የኤርትራ ልዑክ ቡድን ኢትዮጵያ ሲገባ የተሰማኝን ያህል የተሰማው ኢትዮጵያዊ ዜጋ ከስንት አንድ ነው። እኔ ያን ያህል መጎዳቴን አላውቀውም ነበር። ሙሉ ዝግጅቱን በተለመደው ዕንባዬን እዬለቀቅኩ ነበር የተከታተልኩት። አሁን በድንገት ኤርትራ ላይ ዱብ ሲሉ ጠ/ ሚር አብይ አህመድ ይገርማችኋዋል እንደ ቀደመው ቢሆን ስጋቴ፤ ጭንቀቴ፤ ጥርጣሬዬ መከራዬን ያበላኝ ነበር። ቅንጣት ታህል ጥርጣሬ አልነበረኝም በሰላም ስለመመለሳቸው። ከውስጤ ነው ያመንኳቸው የኤርትራውን ካቢኔ።

ከውስጤ ነው የተቀበልኳቸው። እንዲያውም ራህብ ናፍቆትም እንዳለባቸው ነው የተረዳሁት። ታውቃላችሁን አንድም ቀን ናፍቃኝ የማታውቀው ኤርትራ ሁሉ ናፈቀችኝ። ቢያንስ ወድሜ የተሰዋበትን የአፋ ቤት በርሃ ሄጄ ማዬት እፈልጋለሁኝ። አባቴ አበይ ብልህ ነበር። ሄዶ አይቶታል ወንድሜን። ምንአልባት የመጀመሪያውም የመጨረሻውም አባት ሳይሆን አይቀርም ይህን እርምጃ ሲወስድ።

ፍርሃቴ ልክ የለውም። የአዲስ አባባው ሰልፍ ሲዘጋጅ በቂ መሰናዶ አልተደረገበትም፤ ሰለባ ይሆናል የአዲስ አባባ ህዝብ ብዬ ጽፌ ነበር። ቀድሜ። የሆነውም ያ ነው …. ጭንቀታም ነኝ ፈሪ ነኝ። በዛ ላይ ይህቺ ዓለም በጎ የሚያስቡ ሰዎች አይበረክቱባትም። መልካም ሰው ለሁሉም ያስፈልጋዋል። ለክፉው ሰው ራሱ የመልካም ሰው መኖር ህሊናውን እንዲጠይቅ ያደርገዋል፤ የፖለቲካ ሊሂቅ ሆኖ እንዲህ ሆኖ የተፈጠረ መልካም ሰው ዕድሜ ከሠረኝ አይቼ አላውቅም። ማለት በጠቅላይ ሚኒስተርነት ደረጃ።

የቀደሙት ሁለት ጠቅላይ ሚኒስተሮች ጓድ ፍቅረስላሴ ወግደረስ እና አቶ ታምራት ላይኔ ከአቅማቸው በላይ የሆኑ የመልካምነት ዝልቅ ሚስጢር ሜሮናዊ መንፈሳቸው ዝለቅ ብለው የሚገኙባቸው ጠ/ ሚር ሲመጡ ሁሉ ነገር አጨልመው ነበር የተመለከቱት። 

ሌላው ይቅር ቅንነታቸውን በፖለቲካ አስቤ ሊፈትሹት አልፈቀዱም። ንጽህናቸውን የመተርጎም አቅም አልነባራቸውም። ተስፋ የለውም ነበር አሉት። እንዲህ ዓይነት ኩሩድ መንፈስ ነው ኢትዮጵያን ሲያምሳት የኖረው። ውድድሩ ከእነሱ በከንቱነት ከተደመደመው ዘመን ጋር ነው ያዋደዱት። መፍትሄ የለሽ ጉዞ አድርገው ነበር የገለጹት። አቶ ጁነዲን ሳዶ እራሱ የሰጡት ምስክርነት የሚያስቅ ነበር። የአቶ ኤርምያስ ለገሰ አበደ የሚለው ቃል ብቻ ይገልጸዋል።

ምንድነው ይሄ? ሰዉ ከግል ኢጎ ወጥቶ ኢትዮጵያን የሚያድን መስመር ስለመምጣቱ ሊያሰተውል አልቻለም። ምን ያደርጋል አሁን በቀደመው መልክ ሰው ከሥራ ቢፈናቀል፤ ሰው ለስደት ቢዳረግ፤ ሰው ተወቃሽ ቢሆን ምንድነው ለነገ ለትወልዱ ጠቃሚው ነገር? የሚጠቅመው የለም። በዚህ ውስጥ ተጠቃሚ አለ ቢባል በቀል ብቻ ነው። 

አሁንም ማስር፤ አሁንም መግደል፤ አሁን ሰውን በማሰቃዬት ደስታ የሚያገኙት እንደ ሰው በሰው ደረጃ ሊገመገሙ አይገባቸውም። ሰው ከጭካኔ ጋር መኖር ሲፈቅድ እኮ እንሰሳዊ ተፈጥሮን ተላብሷል። ከሰው ማህበር ወጥቷል ማለት ነው። ስለዚህ ወያኔ ሃርነት ትግራይ ያደረጉት፤ የሚያደርጉት እያሳዘነን አሁን ደግሞ በዛ መልክ በቀልን አይዞህ እንበለው ከሰው ማህበር የሚወጣ ፀላዬ ሰናያዊ መንፈስ ነው።

ወያኔ እኮ ሥርዓት ነው 100 ሚሊዮን ህዝብ ልሰደድ ቢል አይችልም፤ ጫካ ገብቼ ልታገል ቢልም አይችልም። የግድ በዛ ሥርዓት ውስጥ መኖርን ማኖር አለበት። መኖርን ለማኖር ፈተናውን ለመወጣት ከሚኬድባቸው አስገዳጅ መንገዶች አንዱ መማር ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ እድሉን ያላገኘው ካድሬ መሆን ነው። 

እና 7 ሚሊዮን ካድሬ አስረህ፤ አንገላተህ፤ ከሥራ አባረህ ይሆናልን? ሰዋዊነት አይደለም ይሄ … ቢሆን ያው ቤተሰብ ነው የሚበተነው። እናት ናት ደግማ የምተጎሳቆለው። የዕውቀት፤ የዕሴት ተከታታይነትም ይጠፋል …. ያን ለሺህ ዘመናት ኖርንበታል …

እህቴ ስታጫውተኝ ነበር ባለፈው ሰንበት ላይ በስልክ እኔ ስሰወር የደረሰባቸውን እንግልት እና መከራ … ስተነግረኛ ጠበለ ፃዲቅ ተጠርተን ከ እናችን ጋር ስንሄድ ማህል ፖስታ ቤተ ላይ „ግን የት እዬሄድን ነው ተባብልን ሦስታችንም ተጠያዬቅን፤ ሦስታችንም እኔ እንጃ እኔ እንጃ ተባብለን ወደ ቤታችን ተመለስን“ አለችኝ። ይህን ያህል ሦስቱም ከመንፈሳቸው ጋር አልበሩም እህቶቼም እናቴም … በኋዋላ ደውላ ስተወቅሰን ጠሪያችን ነበር ያስታወስነው አለችኝ።

  … አያችሁ ቁመው ብቻ ነበር የሚሄዱት። ከዛን ጊዜ ጀምሮ ብዙ ነገር እንደሚረሱ ጨምራ ሁሉ አረዳችኝ።  ይሄ ይቀጥልን? እንዴት ጨካኞች ነን? ምንም ይሁን ምን? ማን ይሁን ማን? ሰላምን ካላወከ በስተቀር ሰላሙ ሊጠበቅለት ይገባል፤ ጥፋት ካለ በአግባቡ ሥርዓት ሲፈጠር ህግ ይጠይቀው፤ ያ የእኛ ጉዳይ የኛም የቤት ሥራም አይደለም … መንግሥት ካለ ህግ አስከባሪ ድርጅቶች ተቋማት ሁሉ ሃላፊነታቸውን በአግባቡ ይወጣሉ። እንደ አሁን ለአፍ ማሟቂያ የሆነው የሰብዕዊ መብት ድርጅትም በትክክለኛ ሰዎች ይመራል። የስቢክስ ድርጀቶች በአውሬዊ መንፈሶች ሳይሆን በሰዋዊ መንፈሶች ይዋቀራሉ።

ስለዚህ ቀልብን ሰብሰብ አድርጎ ይህን ትንግርታዊ የምህረት ዘመን፤ ለሁላችንም የሚበጅ፤ ሁላችንም እንደ ባህሪያችን የሚያስተናግደውን ቅናዊ መንፈስ እጃችን - ህሊናችን - ዘርግተን፤  በውነቱ እራሳችንም አጽድተን ልንቀበለው ግድ ይላል። እንኳን መጣህልን ልነለው ይገባል። ልንሳሳለት ልንከባከበው ይገባል ሰው ከሆን።

 … ከሰማይ መላዕክታን ቢወርዱ ከዚህ የበለጠ ሲሳይ አላዛሯ ኢትዮጵያ ዕድሉን አታገኝም … በፍጹም። መላዕክታን እኮ ሲቆጡ ሰይፍ ነው የሚመዙት፤ ብስጬዎችም ናቸው። አብይ ተበሳጭቶ አይተነው እናውቃለን? እኔ እኮ ሎሌው ብሆን ሁሉ ቅጭጭ አይለኝም። በማግለል፤ በመግደል፤ በቀል በማወራረድ የሚገኝ ትርፍ ቢኖር ሃጢያት እና ገሃነም ብቻ ነው። ገዳዮችን፤ የገዳዮችን መንፈስ እንዴት ነው ያያዘው፤ ስለዛ ማህብረሰብ ማነው ትጉሃኑ … አብይ አይደለንም?
  • ·       ንነት በውነት።

ቅን ስትሆኑ አጀብ ጭብጫባ ልታጡ ትችላላችሁ ግን ህሊናችሁ እንዳመራበት ተውቦ ይኖራል። ዕውነት ቋንቋ፤ ዘር፤ ሃይማኖት፤ ደንበር፤ ብሄር፤ ቀለም፤ የፖለቲካ ድርጅት የላትም። ዕውነት ለሰው ልጆች የተሰጠችን ሚዛን ናት። ስለሆነም ዕውነትን የተጠጋ ሁልጊዜም አሸናፊ ነው። ቀኑ ሊረዝም ሁኔታው ሊመሰቃቀል ይችላል ግን አሸናፊነት አይቀሬ ነው። ሲደገፍም ሲቃውም ዕዝል ከሌላ የጠራው ዕውነት ከተፈለገው ቦታ ያደርሳል። በቀደመው ጊዜ የኢትዮጵያን ሚዲያ አዳምጭው አላውቅም ነበር ነጠል ብለው ካሉት ትምህርት ነክ የግል ዝግጅቶች ወይንም የጥበብ ሥራዎች በስተቀር።

አሁን ከእኔ ዕውነት ጋር ስምረት ስላለው ቅቤ ጠባሽ የነበረውን የ ኢትዮጵያ ቴሌቪዥንን አዳምጣለሁን በመደበኛ። ሸርም አደርገዋለሁኝ። ሌላ ሚዲያ አዳምጬ አላውቅም። አሁንም እንዲያውም የፖለቲካ ተንታኝ አያስፈልገንም። የጠቅላይ ሚኒስትሩን መንፈስ ለመተንትን ከዬት ይመጣል ቀድመን መተርጎን ስለተሳነን፤ ከልጅነት ጀምሮ አደንቀው የነበረው ዕንቁ ጋዜጠኛ ነበር አቶ ነጋሽ መሃመድ ነገር ግን የአብይ መንፈስ ሲመጣ „ተለጠጠ“ ነበር ያለው። 

ያወያያቸውም ነፍሶች የአብይን መንፈስ የተጻረሩ የነበሩ ናቸው። ስላቅም ነበረበት። አሁን እሱንም ከዛች ዕለት ጀምሬ አዳምጬው አላውቅም። ምን ያን ያህል ሊያስኬደው እንደቻለ ለእኔ ግልጽ ቢሆንም ሌላው እንደ አልባሌ አይቶት ሊሆን ይቻላል። ነገ የሰላም ኖቤል ተሻላሚ ሲሆኑ ምን እንደሚዘግብ እሱን ያዬው ሰው። ሰው ሁሉ ነው ሾልኮ የቀረው። ከግል ስሜቱ ጋር እዬቆረኛ የአላዛሯ ኢትዮጵያን መከራ የሳት መጫሪያ ገል ያህል ክብር ሊሰጠው አልቻለም ነበር የባለቅኔውን ጠ/ ሚር ጥልቅ ስንዱ አቅም።

አሜሪካን አገር ቤተሰቦቼ ሲነግሩኝ የጠ/ ሚር አሜኑን ቃል ሳይሰሙ ማደር የማይችሉ መሆኑን ነው የነገሩኝ። የራሴ እህት የነገረችኝ ይህንኑ ነው። አልችልም ነው ያለችኝ። በህይወቷ የፖለቲካ ስብሰባ፤ ሰላማዊ ሰልፍ፤ ኮንሰርት ተሳትፋ አታውቅም፤ የቤተሰብ ሰርግ ራሱ ትሄዳለች ግን ወጥታ ተወዛውዛ አታውቅም፤ ለዛውም ቤታችን የደስታ ቤት ስለሆነ እናታችን ነፃነቱን ስለምትሰጣች ከእኔ በስተቀር ሁሎችም ዘፋኞች ናቸው፤  አብይ ኦህዩ ከመጣ እገኝለሁኝ ሁሉ ብላኛለች።

እኔ እንኳን በምገኝበት ስብበሰባ ተገኝተው አያውቁም አገር ቤት እያለሁኝ። አንድ ጊዜ አስታውሳለሁኝ የፌድራሊዝም አወቃቀር ማብራሪያ ጎንደር ከተማ ተመድቤ ከተፈጠርኩበት ቀበሌ ምድብ ደረሰኝ እና እኔ ቀድሜ መግባት ነው የምወደው በህይወቴ ሰዓት አሳልፌ አላውቅም። እና ስበሰባው ከተጀመረ እናቴ ከጓደኛዋ ጋር ዘንከት እያለች ስትገባ ቀና ብላ ስታይ እኔ ነኝ መድረክ ላይ ነበርኩኝ። አንገቷን እንደ ደፋች ነበር ስበሰባው የተጠናቀቀው። ለመጀመሪያ ጊዜ እናቴ ተገኝታ አዳምጣኛለች። ብነግራት አትመጣም ነበር።

ከዛ ሰኞ ማክሰኞ፤ አሞ ከሞ እዬተጫወትኩበት ካደኩበት ሰፈር ነበር ሃላፊ የነበርኩት፤ ግን እዛ ስብበሳ ላይ ከዬት የመጣች ናት ብሎ ሰው ሁሉ ሲጠያዬቅ እንደ ነበር ሁሉ በኋዋላ መረጃው ደረስኝ። ምን ለማለት ነው እኔም እራሴ እዛ ተወልጄ ማደጌ ብዙም ሰው አይውቅም። የተከደነ አሰተዳደግ ስለነበረኝ። እንኳንስ እህት ወንድሞቼ። አሁን ግን ተሰልፈዋል ሁሉችም የአዲሱ ፈርሃ እንግዚአብሄር መንፈስ ትጉሃን ነን ብለው። ይህን ያደረገው ሰላም ፍቅር ቅንነት ፈጣሪን የመፈለግ እዮራዊ ታምር ነው።
  • ·       ነ ፎንጫሬ።

… ከዚህ እያፈነገጡ ለመድረክ የበቁ ሰዎች የሚያቀርቡትን ፈንጋጣ እይታ የኢትዮጵያ መንግሥት ሆነ ሚዲያ ከቁጥር ባያገባው ደስ ይለኛል፤ ጭፍጫፊ ነገር ነው … አሁን ቄሌም በተፈጠረው ነገር የወለጋ ህዝብ ሊወቀስበት አይገባም። ፊት ለፊት የወጡ ታታሪ፤ ሊሂቃን፤ ጋዜጠኛ እዬተባለ በሚቀርበው የሥም እርከን ላይ ያሉት የሚፈጥሩትን ነገር ከህዝብ ጋር ማነካካት አይገባም። ስለምን? ጎንደርም የዚህ ሰለባ ስለሆነች… አሁንም ከዛ የተፈጠሩ ሚዲያ እንደ እኔ ያላገዳቸው ወገኖቼ ጥንቃቄ ሊደረግ እንደሚገባው ማሰወቅ አለባቸው። በቃው የጎንደር ህዝብ። ሰላሙን ባገኘበት ዘመን አይወኩት። ጥያቄውን ህግ ይፈታዋል። እንኳንስ የጎንደር የ ኤርትራ ተፈታ አይደል።

የትግራይን ህዝብ እንዲህ ሙሉ ለሙሉ በጠላትነት እንዲፈረጅ ያደረጉት ሊሂቃኑ ናቸው። ትግራይ የፖለቲካ ሊሂቅ አልወጣባትም። የትግራይን ልጆች በውንዥብር እንዲህ ባልተገባው ሁኔታ ሥነ - ልቦናው ለጥጠው አፈራቀው ብቻውን ደሴት ላይ እንዲቀመጥ ያደረጉት ሊሂቃኑ ናቸው። በተለዬ እንክብካቤ እና አያያዝ ላይ አንጠልጥለው። 

ተተኪ ሊሂቃንም የተከተሉት ያነን መስመር ነው። ትግራይ አንድ የመዳኛ መስቀል አላት ደጉ አቶ ገብረምድህን አርያ የሚባሉ ፐርዝ ነው የሚኖሩት። እኒህን የህዝብ ወዳጅ የኢትዮጵያ መንግሥት በቀጥታ ሹመት ፕሬዚዳንት አድርጎ ቢሾማቸው ትግራይን በትክከለኛዋ ሰብዕናዋ፤ ትውፊቷ፤ ዕሴቷ ለማማጣት ፋታ አይወስድባቸውም። አሁን የኦሮሞ መንፈስ እንዲህ ኢትዮጵያን የምህረት የይቅርታ ያደረጉት ሁለት ነፍሶች ናቸው ዶር ለማ መገርሳ እና ዶር አብይ አህመድ። ለትግራይም እኔ እመመኛለት እንዲህ ዓይነት ቅዱሳን እንዲፈልቁባት እና የምህረት ድልድይ እንዲዘረጋ ነው። ለጎንደሮችም እንዲሁ ነው። 

ጎንደሮች መሪ አላቸው ኮ/ ደመቀ ዘውዱ የሚባል እሱን ማደመጥ አለባቸው። ጎንደር መፈረጅ ካለባት ኮነሬል ደመቀ በሚሰጡት ዕይታ እንጂ በሌሎች አይደለም። የ አማራ አብዮት የተነሳው በእሱ ምክንያት ነው። „መፍንቅለ መንግሥት“ የጎንደር አጀንዳ አይደለም። 

ውጪ አገር እኮ ከፖለቲካ ጋር ንክኪ የሌላቸው ጎንደሬዎች ናቸው ለውጡን በጸሎት ሁሉ እዬደገፉት ያለ። የ ኢትዮጵያ መንግሥትም ጎንደርን መተርጎም የሚገባው ክድን ብለው መኖር የሚፈልጉትን መንፈስ እንጂ የሰማይ መና የሚሹትን፤ ያለኖሩበትን የሚናፍቁትን መሆን አይገባም። እኔ ከአብይ መንፈስ ሌላ የሚናፈቀኝ አንድም መንፈስ የለኝም። 

ከዚህ መንፈስ ውጪ ምንም ዓይነት ውይይት ማደምጥን አልፈቅድም። ቅባቅዱሴ ስለሆነ። ከሳተናው ከዘሃበሻ በስተቀር ሌላ ሚዲያ ለመግባት አልፈቅድም። እርግጥ ነው ሰንብት ላይ ያው በፍላጎቱ ውስጥ የዘለቀውን ወዲህ ወዲያ የማይለውን ኢትዮ ሚዲያን እከታተለሁኝ። የማይጥመው ሲኖር አይለጥፍም ስለሞላ አይሞላም ስለጎደለ አይጎድልም ኢትዮ ሚደያ ምንም ይሁን ይሁን እኔ እንዲህ አይነት ቋሚ መንፈስ ግጥሜ ነው። ጋዜጠኛ አለምነህ ዋሴንም እምወደውም ለዚህ ነው። የሰው - የፖለቲካ - የዘር ልዩነት ሳይኖር የተደነቀበትን፤ ያዘነበት እንቅጩን ይናገራል ከልብ ከውስጥ በሚገባ በማይረሳ ቅላፄ።

የሆነ ሆኖ ፈንጋጣዋ እና ሞገደኛው ሥርጉተ ሥላሴ „ብሄራዊ መግባባት፤ የሽግግር መንግሥት፤ ሥርነቀል ለውጥ“ የሚባሉት ሁሉ ከአብይ መንፈስ ታች እንጂ ላዕላዊ አቅም የላቸውም። አፍሪካ ወደ አንድ እዬመጣች እኛ አልተግባባነም ራሱን ያላግባባ የፖለቲካ ድርጅት ሊሂቁ ሁሉ ራሱን ይጠይቅ። ቀን ሲገናባ ሌሊት ሲያፈርስ የሚወልበትን የሴራ ክምር ይናድ።

ሁሉንም የፖለቲካ ሊሂቅ እና ብቃት አሳምሬ አውቀዋለሁኝ ከጥቂቶች በስተቀር በአካልም የቆዩትን በአንድም በሌላ አውቃቸዋለሁኝ። የቴሎፎኑ ጽ/ ቤት እኮ ብትን አፈር አጥቶ እንደ ለመደበት ፉከራው፤ ቀረርቶው ሞገድ ላይ የጉም ሽንት በመሆኑ ውህደት ሲባል እዬሰማን ነው። ነገ ደግሞ ውጠት ይኖራል። ወይ ደግሞ ፍርሰት ብትነት ክፍለት እንደ ተለመደው። ላይ ሳይሆኑ መኖር የማይችሉ እንደገናም ሥራ ለመሥራት ያልፈቀዱ ፋውል መንፈሶች ናቸው አገር ምድሩን ሲያውኩት፤ ሲያናክሱን የኖሩት።
ድርጅት የሚበጠበበጥ ስኳሽ አይደለም። 

ከሞቀ እዬተሄደ እዬተዶለ እንደ ንጉሥ ዙፋን ድፉልኝ ነው የሚታዬው። አንድ ብሎ ደጋፊ አሰባስቦ ሥርዓትን ተከትሎ ተመዝግቦ የለም። ሥራ የለም ሥም ካለሥራ ቆልለን ዘመናት ተገፉ። … ይህን ትናንትም አይተናል ዛሬም ዓመት ድገሙን ነው። 

ነገ ደግሞ ተከፈለ - ተሰነጠቀ - ተበጠሰ  -ተቀጠለ ይደመጣል።  የኢትዮጵያ እናቶችም ለግብር አቅርቦት ማን ብሏቸው፤ …. አንድ በሽተኛ መንፈስ ከኖረ በዬሄደበት ሁሉ እንዳወከ፤ እንዳናከሰ ነው የሚኖረው …. እፉኝት ይሄው ነው። ሲረገዝ አባቱን ሲወለድ እናቱን ይገድል እና እራሱን እያበራከተ የሚኖር … ይህን ከሥረ መሰረቱ ለማጥናት ያቃታቸው አቅመ ቢሶች ናቸው „የሽግግር መንግሥት፤ ብሄራዊ መግባባት፤ ሥርነቀል ለውጥ“ እያሉ የሚነስቱን …. እግዚአብሄር ይቅር ይባላቸው … ተተኪው ደግሞ አቤቶ የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ ይሆናል እሺ ካለ ይዋጣል፤ እንብኝ ካለ ደግሞ ይተረተራል ቅራሪ አሰኝቶት ተዘንቋል እና … ከዲሪቶ መንፈስ ጋር …
  
ጎንደር ግን ከአብይ መንፈስ በበላይ ምንም ነገር እንደማይጠብቅ በሚሠራበት መሥመር ይሠራበታል … ጎጃም ከተከተለኝ ደስታውን አለለችውም፤፡ ጎጃም የታምር ቅኔ ስለሆነ …

ይህ ዘመን ኢትዮጵያ ላይ አዲስ ጸሐይ የወጣበት፤ መጪውን ዘመን በአክብሮት በልቅና - በፍለቅና - በሳቅና - በሐሤት የምንነሳበት አዲስ ዓመት ነው የዘንድሮው ቅዱስ ዮሖንስ። እንደ እኔ እንደ ሥርጉተ ሥላሴ የምርጫ ዘመኑ ሁሉ እንዲራዘም እጸልያለሁኝ። ሌላ መሪ እንዲቀመጥ አልሻም! ማህተም አለበት። እቴጌ ኤርትራም ትፈርመበታለች። የኤርትራ ህዝብም ካለ ድምጸ ታዕቅቦ ያትምበታል። ይሄው ነው። 

አብዩ ነብዬ! አብዩ አሜኑ! አብዩ ሜሮኑን ኤልሻዳይ ይጠብቅልን አሜን! ይሁንልን! ይደረግልን! አሜን አሜን በሉ … ለአሜኑ መንፈስ።
  • ·       ጽሑፌ መነሻ እንደ መከወኛ።

አዝናለሁኝ ዓለም ዓቀፉን ጋዜጠኛ አለምነህ ዋሴን የሚያስተናግድ ሰፊ ሚዲያ ባለመኖሩ። የጠ/ ሚር ቢሮ ይህን ቢያስበብት መልካም ነው። ይህን የመሰለ ዕንቁ ጋዜጠኛ እንዲህ ባሊህ ባይ አጥቷልና። የሚገርመኝ ጋዜጠኛ ነው። ጸጋው፤ ድምጹ፤ ተጽዕኖ ፈጣሪነቱን ይደንቀኛል።

የሞገደኛዋን የሥርጉተ ሥላሴ ልብ የገዛ እና የመራ … ምክንያቱም ጓዘ ቀላል ስለሆነ ነው፤ ብዙ ዝግጅቶችን በበጸጋዬ ራዲዮ አስተናግጄዋለሁኝ።
ጋዜጠኛው … ጥግ ያደረገው ሃይማኖት፤ ፖለቲካ መስመር፤ ዘር፤ ቀለም ስሌለ ነፃነት የሚለውን ንጽህና በመኖሩ ውስጥ አቆምሶ የሚኖር የትውልድ ፈርጥ ነው - ለእኔ። አጀንዳው አላዛሯ ኢትዮጵያ ብቻ ናት። 

ብታጋላብጡት፤ ብታበጥሩት፤ ብታንተረትሩት ያችው የእናቱ ድምቀት ነው ጉዳዩ። በምንም በማንም መጠለል የማይፈቅድ፤ በራሱ ሰብዕና ውስጥ ዘልቆ ለመኖር የቆረጠ እና የወሰነ። ይባረክ! ኢትዮጵያ ጋዜጠኛ አለኝ ብትል እጅግ በቁጥር ካነሱት አንዱ እሱ ነው። ለዛውም ቢበልጥ ነው። ዩቱቡ ላይ የራሱ ፎቶ ከፍ ሲል የአባበ ቢቂላ ፎቶ በቃ። ሰብዕና እንዲህ ነው። ስለሰው እኩል ግንዛቤ ሲኖርም እንዲህ ነው። አሳዳጊውን ይባርከው። አሜን!

ኢትዮጵያዊነት ፈተናን አሸንፎ የተፈጠረ ሚስጢር።

የኔዎቹ ቅኖቹ ተባረኩ!

መሸቢያ ጊዜ!

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።