ጠንቃቃ መሆን ያተርፋል እንጂ አያከስርም።
ሞት የፖለቲካ አቋም የለውም።
„እግርህንም ወደ ፍቅር አንድነት ጎዳና አቅና፣
የእግዚአብሔር ዓይኖች ወዳጆቹን ይመለከታሉና፤
ጆሮውም ልመናቸውን ይሰማልና
ፍቅርን ፈልጋት ተከተላት።“
(መጽሐፈ መቃብያ ምዕራፍ ፳፪ ቁጥር ፰)
ከሥርጉተ©ሥላሴ
26.07.2018
(ከገዳማዊቷ ሲዊዘርላንድ።)
በቃችሁ ቢለን ይህን የድንገተኛ ህውከት ቢያስታግስልን ምን አለ ፈጣሪ? ዛሬም አዲስ መርዶ አዬሁኝ። የአባይ ግድቡ የሙያው ማህንዲስ ከመኪናቸው ውስጥ ህይወታቸው አልፎ ተገኜ ይላል ክፉው ዜና። ዜናው ያገኘሁት ከአማራ ሚዲያ ነው።
እኔ የአባይ ግድብን ጉዳይ በገለልተኝነት ነበር እምከታተለው። አልተቃውምኩትም አልደገፍኩትም። ምክንያቱም በማህል ያለው የፖለቲካ ጨዋታ ቀልቤን ሚዛናዊ አድርጎ አንዱን ሊያስወስነኝ ስላልቻል።
ይህ ፕሮጀክት በጣም በዙ ኢትዮጵውያን ልባቸውን የሰጡት ብቻ ሳይሆን ህይወታቸውን ለመገበር የተሰለፉበት ነበር፤ ይህም ብቻ ሳይሆን በበዛ ተስፋ ፍንድቅድቅ የሚሉም ባለሙያዎችን አዳምጣለሁኝ። እኔ ደግሞ ሳይሞቀኝም ሳይቀዝቅዘኝም ነው የኖርኩት።
የመንፈስ ነፃነት ነው ለእኔ ገዢዬ። ቁስ ብፈልግ ሲዊዝ ተቀብሬ አልቅመጠም ነበር። የተሻሉ ዕድሎች ስለነበሩኝ። ጉዳዬ ሰው በመንፈሱ ነፃ መሆን አለበት ነው። አሁንም ይህን አዲስ ለውጥ እምደግፈው የመንፈስ ነፃነት ያስፍናል የሚል ተስፋ ስላለኝ ነው። ጭንቅላት የተቆለፈበት ገነት ለእኔ ገሃነም ነው የፈለገ ዓይነት የኑሮ ደረጃ ይኑረው ...መንፈሴን ለመቆጣጠር ገና አንዲት ስንዝር እራመዳለሁ የሚል ማንኛውም ሰው ዕድል የለውም ከእኔ ጋር የመቀጠል። ምክንያቱም የራሱ መንፈስ አለውና ... መንፈስን በቅኝት ከመስጠት፤ ከመፍቀድ ሞት በስንት ጣዕሙ ...
የተስፋው መጠን የተንጠራራ ነበር በአባይ ግድብ ላይ።
አንድ ጊዜ ኢትዮጵያ ውስጥ የፈጣራ ወጣቶችን የሚያበረታት ድርጅት „አንበሶች“ የሚል ይመስለኛል ልዩ ዝግጅት ነበር። እርእሱን እርግጠኛ አይደለሁኝም፤ ብቻ ወጣቶቹ አማራችን ከገብያተኛ ጋር በቀጥታ የሚገናኝ መስመር መዘርጋት፤ የማገዶን ፍጆታ የመቀነስ ቀላል አቀራረብ ያከተቱ የተለያዩ ኑሮን የሚያአቀሉ ፈጣራዎችን ይዘው ነበር የቀረቡት።
እሳት የላሱ ከ18 እስከ 25 ዕድሜ ያላቸው በእኔ ግምት በግል እና በጋራ የራሳቸውን ፕሮጀክት እያቀረቡ ባለሃብቶች ከተመቻቸውን ፓተንት ጋር አብረው ለመሥራት ይደራደራሉ፤ ጀርመንም አለ እንዲህ ዓይነት ፕሮግራም እና የማገዶ ፍጆታን በማቃለል ለቀረበው አዲስ ፓተንት የተሰጠው መልስ "አባይ ግድብ በቅርቡ ስለሚጠናቀቀ ይህ ፓተንት ዘላቂ ሊሆን አይችልም ስለዚህ አብረን ለመሥራት አንፈቀደውም" የሚል ዕድምታ ነበረው።
እንዲያውም ፓተንት አቅራቢ ወጣቶችን በከንቱ ደከማችሁ ዓይነት ነበር፤ አሁን ያን መልስ የሰጡት ዲታዎች ይህን ሲሰሙ ምን ሊሉ ይችሉ ይሆን አልኩኝ የሰሞናቱን መረጃ ስሰማ … ምክንያቱም ግድቡ በተንጠራራ ተስፋ ይጠበቅ ስለነበር። ሁሉም በጉጉት ሲጠብቁት ስለነበረ ሥርጉተን ሳይጨምር፤
አባይሻ።
በብዕሬ አባይን በሚመለከት አንድ ልበ ወለድ ድርሰት ላይ ጽፌው ነበር። ግብጽ የሚኖሩ ኢትዮጵውያን የስደት ኑሮ እና የማህበራዊ ኑሮ ትስስራቸውን የተመለከተ ነበር ድርሰቴ። አጭር ድርሰት ነበር፤ ለህትምት አልበቃም። ራዲዮ ላይ ግን በ2006 ተርኬዋለሁኝ። በአባይ ማንነት ላይ ልጻፍ እንጂ በዚህ በሄሮድስ መለስ ዜናዊ የፖለቲካ ማዕቀፍ የአባይ ግድብ ትውና ግነትም፤ አቃሎ ማዬትም ውስጥ አልነበርኩኝም። ዜናውም አይሰበኝም ነበር ... የፖለቲካ አጋፋሪ ዜናዎችን ቀልቤ አይፈቅዳቸውም። በትክለኛው መንገድ ሲሆን ነው ...
ምክንያቱም ከዛ የቀደሙ መሪዎች በጣም ዘለግ ባለው ዘመን በመካከለኛው ዘመን ሁሉ በዚህ አባይ ነክ ጉዳይ ቀደምት መሪዎች የራሳቸውን አሻራ አሳርፈዋል። እንደገናም ያ ፕሮጀክት የተቃደበት ሁኔታ በራሱ ሌላ ጭብጣዊ ግብረ ምላሽም ነበረው።
እርግጥ ነው አባይ የማንነታችን መገለጫም ብቻ ሳይሆን አንባሳደራችንም ነው። በሌላ በኩልም የጉርብትናውም ቀለም የሚንጥም ፖለቲካም ነው ነገረ አባይ። አባይ የአንድ ብቻ ሳይሆን የበርካታ ሚስጢራት ማዕከላዊ ተቋም ነው።
የዛ ሊቀ ሊቃውንት ሳናውቅበት፤ ዕውቅናም ሳንሰጠው የቀረነው፤ የሲዊዲን ኢትዮጵውያን ብቻ የክብር ቅርስ የሆነው የቅኔው ልዑል የጎመራው „እናትክን በልልኝ“ ሚስጢርም አባይን በውል ከሰብዕና በላይ አድርጎ ይገልጠዋል። አባይ ሁለመናችን ነውና።
የሆነ ሆኖ አንድ መረጃ ከሰሞናቱ ወጥቶ ነበር „በዚህ ከቀጠለ እስከ 10 ዓመትም አያልቅም“ የሚል … ፍጥነቱን - ጥራቱን - አደረጃጃቱን - አወቃቀሩን - በጀቱንም አቅደን ማስኬድ ካልቻልን ከተስፋችን ጋር ለመገናኘት አቅም ያንሰናል ማለት ነው ትርጉሙ እንደ እኔ።
ስለዚህም ትጋት የጎደለውን በአቅም አጎልብቶ ለማጣደፍ ሌላ ተጋድሎ እንዳለበት አመላካች ነበር አገላለጹ እኔን ሲገባኝ። ያው ውበትም እንደ አካባቢው ይተረጎማል፤ ስንኝም እንደገባው ልክ ይብራራል። አብሶ በዚህ ዘመን ከስሜት ጋር በማጠጋጋት ነው ትርጓሜው ሁሉ። ዕውነት በተፈጥሯዋ ልክ አትመዘንም። … ቅንነትም እንዲሁ ...
አመከንዮ የሚቀረበው ወይንም የሚገፈተረው … በስሜት ዘሃ ዝርዝር ነው …
የሆነ ሆኖ በዚህ ግልጥ መረጃ ማግስት ኢንጂነር ስመኘው በቀለ አብዮት አደባባይ ላይ ሞተው ተገኝተዋል።
መቼም ሞት አዲስ ካልሆነ በሰተቀር ከ4 ዓመት በፊት ፕ/ እምሩ ስዩም ከታክሲ ውስጥ ሙተው ተገኝተዋል መሃል አዲስ አባባ ላይ። ለዚህም ነው ጀግናዬ አርበኛ ሃይለመድህን አበራ በዝምታው ውስጥ፤ በጨዋነቱ ውስጥ ሌላ ህውከት ሳያስከትል፤ ወገኖቹን ሳያስከፋ፤ በኢትዮጵያ ንብረት ላይ ምንም ነገር ሳያቄም፤ ኢትዮጵያ አገሩን ከሌላ ህዝብ ጋር ደም ሳያቃባ ግን መከፋቱን ለመግለጽ ጣሊያን ሮም ማረፍ የነበረበትን አውሮፕላን ሲዊዘርላንድ ያሳረፈው።
ከዚህም ሌላ ጸሐፊ እና የፖለቲካ ሰው አቶ አሳፋ ጫቦም፤ ለማግስት በቀጠሩት ጹሁፍ ላይ ሳይደርሱ እንደ ወጡ የቀሩበት ምክንያት በዚህ የሴራ ስሌትና ስኬትም ነው። ከሳቸው በፊት በአሜሪካ ወደር የለሹ ጸሐፊ አቶ ሙሉጌታ ሉሌንም በድንገተኛ ሞት አጥቷል የኢትዮጵያ ህዝብ። እነዚህ ሁሉ ሲመረመሩ የሴራ ፓለቲካ ምክንያቶች ናቸው።
ሰው ስለምን ይገደላል? ሚስጢር እንዳይወጣ ነው አይደል? ግን ሚስጢሩ እንዳይወጣ እኮ በሌላ መልክ ማድረግ ይቻላል። በግል ቁጭ አድርጎ ሳያስፈራሩ ጠቀሜታው እና ጉዳቱን መግለጽ፤ ማሳመን፤ የሚስጢሩን ባለቤት ማግባባት።
አብሶ ሚስጢሩ ቢወጣም ባይወጣም አሁን ላለው የመቻቻል ፖለቲካ ብዙም ጠቃሚ አልነበረም፤ በሴራ በበቀል የተሰናዳው የሞት መርዶ አሳዛኝ ነው። … ምክንያቱም እጅግ የከፉ እጅም የሚሰቀጥጡ መከራዎች አሁን እዛው መሬት ላይ ስላለ …
ይህን ያክል ዘመን የቆዬ ነገር እንዴት በአንድ ጀንበር ህይወትን ቀጠፈ? ነገስ ተረኛው ማን ይሆን? አገር የገቡትም፤ ገና ሊገቡ ያሰቡትም የተፎካካሪ ፓርቲ ቁልፍ መሪዎች ጥንቃቄ ማድረግ አለባቸውም።
መኖራቸው ስለሆነ ቀዳሚውና ጠቃሚው ነገር። አላስፈላጊ መስዋዕትነት ከመቀበል ተግ ማለት ይመረጣል። መወሰን ቀላል ነው፤ ችግሩ በወሰኑት ልክ ዓለማን ለመፈጸም እና ለማስፈጸም ያለው ቅንነት በሁሉም ዘንድ አለ ወይ? ይህ የሚከፋቸው የማይማቻቸው ደግሞ ይኖራሉና? ዝንቆች ነን።
በኢትዮጵያ የ27 ዓመት እምስ ፖለቲካ አንዱ በዳይ፤ ሌላው ተባዳይ ነበር። አንዱ አጥቂ ሌላው ተጠቂም ነው። አንዱ ቤተኛ ሌላው ባይታዋር ነበር። አንዱ ተገፊ ሌላው ሹመኛ ነበር። ግን ያን በደል እንዳይቀጥል ለመድረግ የሚቻለው በመቻል ውስጥ ሴራዎችን፤ ግድያዎችን ማስቆም ሲቻል ብቻ ነው። ይህን ለሚፈጽሙትም በህግ አግባብ ለፍርድ ማቅረብ ሲቻል ነው። ዳታ በበዛ ቁጥር ሞት በዬቀኑ በር እያንኳኳ ከች ማለቱ አይቀሬ ነው።
ሰው ጠንቃቃ መሆን ስለሚያነሰው ነው እንጂ ከዚህ ውይይት መልስ ሌላ አደጋ መኖሩን መጠርጠር ይገባ ነበር። ራስን መጠበቅ። ለነገሩ አዲስ አበባም ባይሆን የትም ቦታ አያመልጡም ነበር ሟቹ ኢንጂነር ስመኛው በቀለ። እዚህ እራሱ ያለው አደን እንኮን እጅግ ከባድ ነው።
የበለጠ ከቀደመው ከሯል ማለት እችላለሁኝ። ዘግቶ ለመቀመጥ እንኳን አይቻልም። እንኳንስ ኢትዮጵያ … አዋኪው አሳዋኪው ማን እንደሆን አይታወቅም። ከደሙ ንጹህ የሚሆን አለ ለማለት እኔ በግል ህይወቴ ነገ ስለሚከሰተው ነገር መጠቆም አልችልም። ምክንያቱም ሁሉም የእውነት ደፋር ሳይሆን ፈሪ ስለሆነ። ራሱን እዬፈራ በሚኖር ፖለቲካ እና ፖለቲከኛ ደግሞ ይህ አይቀሬ ነው ሞት የሁላችንን ቤት መጎብኝቱ ...
በማንኛውም ሁኔታ ልብ ጥሎ የሚያስኬድ ነገር የለም። አሁን እንደሚሰማው እኮ አዲስ አባባ ላይ ብዙ መሳሪያ ተገኜ ነው የሚባለው። ስለዚህ እርግጠኛ የሚያደርግ የደህንነት ሁኔታ የለም ማለት ነው። በተለይ ታዋቂ ለሆኑ ሰዎች።
አብሶ እንደ ወጣት ተመስገን ደሰላኝ ላሉ ደፋር ጋዜጠኞች እጅግ ከባድ ነው። አሁን ደግሞ አርበኛ ዘመነ ካሴ አገሬን እገባለሁኝ እንዳለም ቃለ ምልልሱ አዳምጫለሁኝ። ከባድ ነው። ደመ ከልብ መሆን ነው። ማን ፈጸመው ለማለት የሚከብዱ ነገሮች ስለአሉ።
ምክንያቱም በዚህ በእኛ ፖለቲካ መውቀስ፤ መተቸት፤ መሞገት አልተለመደም እና። አንዱን የፖለቲካ ድርጅት ሲተች በእኔም ውስጥ ይሄ አለና ላስተካል አይልም ሌልኛው። ከእኔ ከመድረሱ በፊት ልጉረደው፤ በአጭሩ ላስቀረው ነው፤ ማህበራዊ መሰረቱን ላሳጣው ነው። ልጨረሰውም ነው። ግን ሊያስፈሩ የሚገቡት ዝም ያሉት እንጂ የሚናገሩት ሊሆኑ አይገባም ነበር።
የሆነ ሆኖ ጠንቃቃ መሆን ያተርፋል እንጂ አያከስርም። በሌላም በኩል ኮ/ ደመቀ ዘውዴም ቢሆኑ የቀደመው አደባቸው እና ትእግስታቸው ብቻ ነው ህይወታቸውን ሊያስቀጥለው የሚችለው። ሌሎችም የነፃነት አርበኞችም እንዲሁ …
ምክንያቱም የነበረው የቁርሾ እርሾም እንዲቀጥል የሚፈልጉ ዲያቢሎሳዊ እሳቤዎችም ስላሉ። ይቅር ማለትን ማጽናት ሞት የሚሆንባቸው ይኖራሉ። ይቅርታ እኮ ከገነት በላይ ነበር። ለነገሩ ብዙው የ66ቱ ሊሂቃናት እኮ ከሃይማኖታዊ ዶግማ ጋር እንብዛም ናቸው። ይህ እንዳይሰምር አሁንም እናቶች ሚስቶች እህቶች በስጋት እንዲናጡ ማድርግ የሚሹ ይኖራሉ … ከፈጣሪም በታች ጠንቃቃ መሆን ይበጃል።
ከሁሉ በላይ ግን መጸለይ በብርታት፤ መስገድ በጽናት፤ መጾም በትእግስት ያስልጋል። ምክንያቱም ትውልድን ማትረፍ ስላለብን። ያጣፈውን ስንወቅስ እኛ የዛ ጥፋት አጋፋሪ በመሆን ቂም ቋጥረን መሆን አይኖርበትም። ንጽህና ከሌለን እግዚአብሄርም ይሸሸናል። ወቀሳችን - ነቀሳችን - ትችታችን ለአላዛሯ ኢትዮጵያ ነፍስ መዳን ብቻ ሊሆን ይገባል። ከራስ ስሜት መውጣት …
ነገም ሌላም ሞት አደጋ ይኖራል። በተለያዬ ሁኔታ ይህን ደጋግሜ ጽፌዋለሁኝ። እኔ ፈሪ ነኝ እያልኩኝ። የተሸነፈ ሃይል ሁልጊዜም መሸነፉን የሚቀበለው በዚህ መልክ ስለሆነ፤ እግዚአብሔርን በማስከፋት ስለሆነ …
ሞት አይቀርም፤ ማንም አይቀርበትም፤ ሞት ታቅዶም አይደለም የሚመጣው። ግን ከእግዚአብሔር በታች መጠንቀቅ ያስፈልጋል። አብሶ እጅግ የነፍስ የሆነ መረጃ በአጋጣሚ በወግ ምክንያት ከወጣ፤ ነፍስን መጠበቅ ያስፈልግ ነበር።
የትዳር አጋሮች በተለይ ሚስቶች በዚህ በኩል ጉልበታም ምክራችሁን ለትዳር አጋራችሁ ማድረግ የተገባ ነው። ተው ማለት። ተጠንቀቅ ማለት። ባሎችም ማድመጥ። ዛሬ ይህ ማህብራዊ ሚዲያ ሞገዱ መከራ ሆኗል።
አይታችሁዋል „ወርቅ ናችሁ ይሉናል“ የሚለው መረጃ እንዴት ምድርን ቀውጢ እንዳደረገው፤ እንደ ወገን ቢታይ ግን ወርቅ ቢባል ወገነህ ምን ይቀርበሃል። ሥጋህ ደምህ አይደለምን? ኢትዮጵያዊ ነኝ ካልክ ማለት ነው … ግሪኩ፤ ግብጹ፤ ካናዳዊ አልነበረም ወርቅ የተባለው፤ በጋብቻውም፤ በአበልጅነቱም፤ በሰንበቴው፤ በእድሩ የምታገኘው በሁሉም ያንተው አምሳያ ነው። ግን አደብ የለም …
ችግር ሊሆን የሚገባው ወርቅ ነኝ ብሎ ሲንጣራራ እንጂ በጨዋታ ማህል በተነሳ ወግ ያን ያህል የሚያደባልቅ፤ ውርጅብኝ የሚያመጣ፤ አንቺና አንተ የሚያስብል አልነበረም።
አሁን መጣር የሚገባን በመንፈሳዊ ግንባታ ላይ መሆን አለብን። ተመርዘናል። ቅይጥ ሆነናል። እምንጠላውን ነገር እኛው እራሳችን ስንፈጸመው አይታወቀነም። ፍላጎታችን ግራጫማ ነው።
ስለምን? አዎንታዊነትን የሚሰብክ አንድም ተቋም የለንም? አዎንታዊነት አጀንዳችንም አይደለም። አዎን ስንፈቅደው አይንም ካልፈቀድነው ሰው አይደለንም። በሰውነት ውስጥ ሰውነትን ራሱን ቁጭ አደርገው የሚሞግቱ አመክንዮዎች አሉና። እንደ ሰው ሰው ሲሞት ልናዝን ይገባል። ሞት የፖለቲካ አቋም የለውም እና።
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ