የአዲሱ ለውጥ ትሩፋት።

መንትዮሾቹ የተግባር ልዕልቶች በደግነት
     ማዕዶት!
„የፃድቃን መንገድ ግን እንደ ንጋት ብርሃን ነው፤
ሙሉቀን እስኪሆን ድረስ እዬተጨመረ ይበራል።“
መጽሐፈ ምሳሌ ምዕራፍ ፬ ቁጥር ፲፰
ከሥርጉተ©ሥላሴ
30.08.2018
ከጭምቷ ሲዊዘርላንድ።


አዲሱ ለውጡ አደጋ ያመጣል የሚሉት የአባ ቆስቁስ የአቶ በረከትን የኑዛዜ መስቃ እንዲህ መናነቱን ተግባር ቁሞ ይመሰክራል። የአባ ቆስቁስ የአቶ በረከት ስምዖን ሙገት ቁሞቀርም መሆኑ እንዲህ ይታያል።

ይህ ተግባር አላዛሯ ኢትዮጵያ የተፈጠረችበትን የደግነትን፤ የቸርነት ትውፊቷን አህዱ ብላ መጀመሯን ያሳያል። ሲጀመር ጀምሮ ለውጡ ሰውኛ እና ተፈጥሮኛ ነው በማለት ነበር ስሞግት የባጀሁት። አዲሱ የኢትዮጵያ መንገድ ይሄውና ዛሬም የበጎ ምግባርን ተግባር ተስፋን ሰንቆልናል ...

ይህ ድርጀት መቄዶኒያ በራስ አነሳሽነት ከመንገድ ላይ የወደቁ አቅመ ደካሞችን በራስ ጊዜ፤ ጉልበት እና አቅም የተጀመረ ነው። መስራቹ ቅዱስ ብቻቸውን የጀመሩት ተቋም ዛሬ እንዲህ አፍርቶ ለወግ ለማዕረግ በቅቶ ለዚህ ቀን በቅቷል። 

ቤተ መንግሥትም እንዲህ እንሆ ታደመበት። ወይ ጊዜ እንዲህ ትክሳለህ! ሁለት ዳጋጋውያን አንስቶች እራሳቸው ደካሞችን በማስተናገድ የተሰለፉበት ይህ የቸርነት መንገድ አዲሱ የለውጥ መንፈስ እንዲህ ቅንድስና፤ ብጽዕና ያለው መሆኑን ያመላክታል።

ይህ የቸርነት ጉዞ ትንሽ ራቅ አድርጌ የዛሬ አምስት ዓመት የት ትደረስ ይሆን ብዬ ስጠይቀው „አይተሽ ፍረጂ ብሎኛል።“ እናንተም አይታችሁ ፍረዱት ልበል በተሰጠኝ መልስ መሰረትነት። 

የኔ ውዶች የጹሁፌ ታዳሚዎች ትንሽ ገፋ አድርገሽ ወደ 10 ዓመትስ ስለምን አለወሰድሽውም ትሉኝ ይሆናል። 10 ዓመቱ ረዘመብኝ እና ነው በእኩሌታው ባሳለው ይሻላል እንዳይርቅብኝ ብዬ ነው። ቸርነት ቅርብ ሆኖ እዬታዬ ስለምን ዘለግስ አድርጌ ላቆዬው?

ሰንበት ላይ ጠ/ ሚር አብይ አህመድ እና የአዲስ አባባ ምክትል ከንቲባ አቶ ታከለ ኡማ እስከ ቲማቸው ድረስ የእሙሃይ አዱኛ ማዕደኛ ሆነው ነበር፤ ቀን እኩል ላይ ደግሞ አቅማቸው ዝቀተኛ የሆኑ ቤተሰቦች ላላቸው ልጆች ተስፋን የሰነቀ መልካምነትን ያበራ፤ አይዟችሁን ያሰበለ ህልም የሚመስል ግን ዕውን የሆነ ተግባር ተከወነ።

ዛሬ ደግሞ ደርባባዋ ቀዳማይ እምቤት ወ/ሮ ዝናሽ ታያቸው እና የአዲስ አባባ ም/ከንቲባ ክብርት ወ/ሮ  ዳግማዊት ሞገስ በጋራ በደግነት መንትዮሹ በተግባር ማዕዶት፤ በርህርህና፤ በቸርነት ሲታትሩ ለተመለከተ ልባቸው አንድ፤ ህሊናቸው አህቲ ስለመልካምነት ሆነው አገኘኋዋቸው።

ይህ ነው እንግዲህ የአዲሱ ለውጥ ትሩፋት፤ ረድኤት፤ ተስፋ፤ ራዕይ ሲሆን፤ ነገን በተስፋ ቅኝት እንጠበቀው ዘንድ ለቅኖች ማህንዲሳችን ሆነ ማለት የምንችለው። ያው እኔ የምጽፈው ለቅኖች ብቻ ነው። ቅኖች ብቻ ናቸው ሥርጉተን ሊረዷት የሚችሉት። ፈንገጥ ያለውን ጠባዮዋ ሆነ ፈንጋጣ ሙግቷ ግጥማቸው የሚሆነው … ለቅኖች ብቻ ነው።  

መቼም ይህን መቃዎም፤ ይህን ማውገዝ፤ ይህን ለመገደብ መጣር ሳጥናዔላዊነት ነው። ይህን አለማገዝ፤ ይህን እንዲቀጠል አለመርዳት፤ ይህን አለመበረታትም ያው ሳጥናኤልነት ነው። ሰው ሰውኛውን መደገፍ ከተሳናው ከሰው ደረጃነት መውጣት ነው። 

ሰው ስለመሆን የሚፈትን ዘመን ቢኖር ዘንድሮ ነው። ሰው ሁሉ ጉዱ ፈላበት … ገሃዱ ዓለም እና መንፈሳዊ ዓለምም ተፋጠጡ። ተመስገን። የሎሬቱ ዘመን፤ መባቻ ያልኳችሁም ይህን ነው … ጠረኑ ነፍስ ሆኖ፤ ነፍስ ሰጥቶ ነፍስን ይታደጋል። ተመስገን!

ነፍስ ያለው ፍጡር ይህን የርህርህና መንገድ አለሁህ ሊለው ይገባል። ቢያንስ በጸሎት ሊያግዘው ይገባል። ቢያንስ ሲያው አምላኩን ማመስገን ይኖርበታል። ቤተ- መንግሥት እንዲህ ባለቤት ለሌላቸው ነፍሶች እኔም አለሁላችሁ ከማለት በላይ ለእኔ ለነፍሴ ሐሴት የሚሰጠው ምንም ነገር የለም። ዛሬ በሙሉ ዕድሜ ላይ ነኝ። እንዲህ ችግረኛን ቤተ መንግሥት በይፋ  በአደባባይ አጀንዳው ሲያደርግ ያዬሁት ግን በዘመነ አሜኑ አብዩ ነው … ተመስገን። እንኳንም በህይወት ኖርኩኝ።

ሌላው የገሃዱ ዓለም ትርምስ ለእኔ ምናምንቴ ነው። በቃ ሰው መሆን እንዲህ በርህርህና በመሆን ሲበለጽግ፤ ለባለቤት አልቦሾቹ አለንላችሁ ሲል፤ ዝቅተኛውን የማህበርሰብ ክፍል አደግድጎ ሲያገለግል ከዚህ በላይ እርካታ የለም።

ብዙ ጊዜ አነሳዋለሁኝ አያቶቼ ጥር ሥላሴን እንዲህ ነበር ድንኳን ጥለው ፍሪዳ አርደው ነዳይን ገናን የሚያገድፏቸው የነበረው። ሸንበቆ ተሰነጥቆ፤ ተቆራርጦ እንደ ቢላዋ ይሆናል፤ አዋዜው፤ ጠላው ተሰናድቶ ታላላቆቹ ዓራት ዓይናማ የጎንደር ሊቃውነታት አደግድገው ነዳያን በቁርጥ፤ በጥብስ ተጎንበስው ሲያገለግሉ እያዬሁ ነበር ያደግኩት።

አሁን በምልስት ያ የጎንደሩ የደብርብርሃን ሥላሴ መልካምነት ነው ዛሬ ያዬሁት። ይሄ ነው ሰው መሆን ማለት። ይሄ ነው መሪነት ማለት። ይሄ ነው ሃላፊነት መወስድ ማለት። ይህ ነው አገልጋይነት ማለት። ዜግነት እንዲህ ሲሆን ነው አገር አለኝ ብሎ ማወጅ የሚችለው።

ይህ እንግዲህ የአዲሱን ትውልድ የሞራል ቀረፃ በሚመለከት በራሱ ጊዜ ማዬት ማመን እንዲሉ ያደርገዋል። ልጆች ከሚሰሙት ይልቅ በሚያዩት ነገር ይሳባሉ፤ ይለወጣሉም።

እጅግ የማከብራችሁ ሁለታችሁም የተግባር ልዕልቶቼ ክብርት ቀዳማይት እምቤት ወ/ሮ ዝናሽ ታያቸው፤ ክብርት ወ/ሮ ዳግማዊት ሞገስ ፈጣሪ አምላክ ያኑራችሁ! ከዚህ የበለጠውን ነገር ትከውኑ ዘንድ ድንግልዬ ትርዳልኝ። አሜን!

አቤት ስንት ደስታ ነው ዘንድሮ ያገኘነው - ቅኖች። ብቻ መጨረሻውን ያሳምርለን። አሜን በሉ! ይሁን በሉ! ይደረግልን ይቀጥልንን በሉ የኔ ቅኖች ውዶቼ የጹሑፉ ታዳሚዎች።

Ethiopia: ቀዳማዊት እመቤት ወይዘሮ ዝናሽ እና ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ በመቄዶኒያ ተገኝተው አረጋዊያኑንና የአእምሮ ህሙማኑን ምሳ መገቡ

ሴቶች የርህርህና ጥበቦች ናቸው!

የኔዎቹ ኑሩልኝ።

ማለፊያ ጊዜ። 

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።