ሳተናው ድህረገጽ የ2010 ምርጤ ነው።

ምርጤ!

                              "ጥበብ በቀደሙ ሰዎች ሁሉ ዘንድ ተመረመረች።
                               በሃይማኖት ስማቸውን ላስጠሩም ሰዎች ትንቢትን
                                 ታስተምራለች፤ ወደ ነብያትም ምሳሌ ታገባለች።
                                   የተሠወረውንም ምሳሌ ትመረመራለች፤
                                     ንባቡንም ወደ ትርጓሜ ትመልሳለች።“
                                 መጽሐፈ ሲራክ ምዕራፍ ፴፱ ከቁጥር ፩ እስከ ፫

ከሥርጉተ©ሥላሴ
09.09.2010
ከጭምቷ ሲዊዘርላድ። 


የሳተናነት ማር ወለላ
አዎንታዊነትን ሲያበላ
የቅንነት ነፃነት ገላ
የቤተ አብርኃም ፍሬ ዘለላ
የጥሪት ቅኔ ፈርጣዊ ዛላ።

የሁለመና ህብረ ዜማ ረቂቅ
የሁለንትና ነባባተ ብርቅ
የተግባር አናባቢ ንዑድ ድንቅ
ሳተናው አንደስምህ ወርቅ!

ሳተናው ድህረ ገጽ ለቀንበጥ ብሎግ የ2010 የዓመቱ ምርጥ ሚዲያ ነው። ምርጥነቱ ቅንነቱ፤ አሳታፊነቱ፤ አቃፊነቱ እና ሚዛናዊነቱ ልዩ ጣዕም ያለው፤ እውነት የፈለቀበት ከመሆኑ ላይ ነው።

ሳተናው ድህረገጽ የሃሳብ ሙግቶችን ያለ ተዕቅቦ የሚስተናግድ  ለኢትዮጵያ የሚዲያ ህይወት እና ታሪክ አዲስ በር የከፈተ ልዩ የሚዲያ ነፃነት ምዕራፋችን ነው።

ሳተናው ደፋር ነው። ድፍረቱ ሰውነትን በመቀበል እረገድ ነው። እኔ እንደ እሱ ሰውነት የሚቀብል ሚዲያ አይቼም፤ አድምጬም አላውቅም። ሁሉ በተመሠረተብት ማንነቱ ወይንም ዞጉ ላይ የተመሠረተ ነው። ሳተናው ድህረ ገጽ ለጥብብ ያለው ክብር እና ልዕልናዊ እሳቤም ብጡል ነው።

ሳተናው ድህረ ገጽ ፍጥነቱ ከነፃነት ወዳድነቱ መፍለቁ ብቻ ሳይሆን ወገናዊነቱ ዕውነትም በመሆኑ ጭምር ነው። ነፃነት እምለው እኔ ይህን ነው። የነፃነት ድምጽ ሚዲያ እምለውም ሳተናውን ብቻ ነው።

ለሳተናው ጀግና በተግባሩ እንጂ በወረቀት አምልኮት አይደለም የሚለካው። ስለዚህ ንፋስ በነፈሰ ቁጥር ዘንብል ቀና የማይል፤ የቁርጥ ቀን የእውነት አርበኛ ሚዲያ ነው።

አብነትነቱ ለኤሌትሮኒክስ ሚዲያም፤ ለግሉ ዘርፍም ሆነ ለመንግሥትም ዘርፍም ጭምር ነው። ማለትም ለብራና ብቻ አይደለም አርያነቱ።

ከ2006 እኢአ የአማራ ማንነት የህለውና ተጋድሎ መፈጠር ጀምሮ በዬደቂቃው ፈተና መወድቅ እንደ ባህል የተወሰደ የሚዲያ የወል መለያ ሆኖ ባጅቷል በውጩ ዓለም።

አብሶ 2010 ፈተናው ዝልቅና ጥልቅ ነበር። ይህን ፈተና በድል እና በአሸናፊነት የተቀዳጀው ደግሞ ሳተናው/ ዘሃበሻ ብራና ብቻ ናቸው።

ሳተናው ብራና የተለዬ የሚአደርገው ማንም ባልነበረበት ሰዓት፤ ማንም ባልገመተው ሁኔታ፤ ምንም ባሊህ ባይ በሌለበት ወቅት፤ አንደበት አብይ ሆኖ በትጋት ሠርቷል። ሳተናው በአብይ አክቲቢዝም ላይ ሲተጋ ያን - ይህን የዝና ግነት አገኛለሁ ወይንም የክብር ሊሻን ይሰጠኛል ብሎ አልነበረም። 

ሳተናው ሚዲያ የድል አጥቢያ አርበኛም አይደለም! እንደ ሽንብራ ቂጣ አይገላበጥም። በ እምነቱ ውስጥ ሲዘልቅ እና ሲጸና ነው የማዬው።

ከውስጡ የአላዛሯ ኢትዮጵያ የችግሯ ቁልፍ ነው ብሎ ነበር በተገፊው እና በተገላዩ አብይ አክቲቢዝም ላይ በስፋት የተጋው። ቀድሞ ነገር የአብይ መንፈስ ከዚህ ይደርሳልም እንዲህም ይሆናል ብሎ ያለመው አልነበረም ካለሳተናው በስተቀር። ትጋቱን ለማጨናጎል ብዙ ተደክሟል። ግን በመከራው፤ በወጀቡ ጊዜ በጽናት ሁሉንም ጨቀጨቅ እና መሰናክል ተሻግሮ ለቀን አብቅቷል። ዛሬ አብይ ኬኛ! የሁሉም ነው የሚሊዮኖች ኤርትራንም ኬኒያን በድርቡ እክሎ።  

ልብ ያላቸው፤ ማስተዋል የተሰጣቸው ልበ ብርኃኖች ይህን አያጡትም። ያን አድካሚ ወቅት፤ ያን አጣዳፊ ወቅት፤ ያን በዬቀኑ በአዳዲስ ጉዳዮች የተዋጥንበት ወቅት በትጋት - በታታሪነት - በፍጹም ወገናዊነት እና በብቁ ሁኔታ የተወጣው ሳተናው የቀንበጥ ብሎግ የዓመቱ ምርጥ ድህረ ገጽ አድርጌ ስመርጠው ውስጤ በሰናይ ተሞልቶ ነው።

በአዎንታዊነት እና በርጋታ የሰከነው አዘጋጁ ብዙ የማይናገር፤ ልታይ ልታይ የማይል፤ ግን ብዙ የሚሠራ፤ ደከመኝ፤ ሰለቸኝ፤ በዛብኝ የማይል ሌት እና ቀን ስለ እናት አገሩ ከውስጡ ሆኖ የተገኘ የተግባር ልዑል ነው። ኢትዮጵያዊነት እማዬው በ እሱ ውስጥ ነው። የብሄራዊ ሰንድቅን አውነተኛ ፍቅርም የማገኘው ከእሱ ዘንድ ነው። 

በብዙ ነገሮች፤ በብዙ ሁኔታዎች ፈተንኩት ግን አለፈ። ማለፍ በሥነ - ልቦና አቅሙ ረቂቅ ስለሆነ ለሳተናው አዘጋጅ ባይታዬውም እኔ ግን በርቀት ሆኜ፤ ከገዳማዊ ህይወቴ ውስጥ ሆኜ በተደሞ ስከታተለው እጅግ የልቤ የሚባል ለእናቱ እናት የሆነ ወንድማችን ነው።  እናት ነው። ይኑርልን!

ከሁሉ በላይ ዘመኑ የእናት ስለሆነ፤ ዘመኑ በመንፈስ ልዕልና ደረጃ የሴቶች ስለሆነ ለእኔ ልዩዬ ነው። ሳተናው ኬኛ!

ሳተናው ድህረ ገጽ ሁለገብ፤ ሚዛናዊ እርምጃው እና ተግባር ላይ መገኘቱ እናት ኢትዮጵያ ይህም አላት እንድል አስችሎኛል። ኃላፊነት የሚሰማው ለቅናዊ እና አዎንታዊነት አግልሎት የተፈጠረ ወንድማችን ነው። ሳተናው ተስፋ የመሆን አቅሙ በመሆን እንጂ በማስመስል አይደለም።

ባሳለፍኩባቸው የስደት ዘመኖች ሁሉ ኢትዮጵያዊነት ሥሙ እንጂ ምግባሩ፤ ፍልስፍናው፤ ሞራሉ ለማዬት ውስጡን አግኝቼ ከውስጡ ጋር ታድሜ ለማውጋት አልታድልኩም ነበር። ብዙ ነገሩ ፌክ ነው። 

የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ስለተውለበለበ/ ወይንም ስለሚያውለበለብ ወይንም ስለሚለበስ በግል ይሁን በድርጀት ኢትዮጵያዊነት የሚፃረር ጥቁር የድንጋይ ጣዖት የለበትም ማለት አይቻልም። ነፍጠኝነትን ማን ከውስጡ ሲያስቀርብ፤ አሁንም የጭንቅ ሆኖ ነው ... 

ኢትዮጵያዊነት የእዳሪም - የቤትም ሰው ሳይኖር ዜጋን በእኩል መንፈስ ማቅረብ፤ መቀበል ቢያንስ ሰው ነህ / ሰው ነሽ ማለት መቻል ነው። ይህን ደግሞ አላዬንም አልኖርነበትም።

ያን ለማድረግ እና ለማስደረግ ደግሞ የሚታዬው ሁሉ ወርቅ አለመሆኑን ዘመን ቁጭ አድርጎ አስተምሮኛል። በዞግም ቢመጣ መሰሉ ነው። ዞጉን ስለጠራ የሚመሰለውን ዞግ በቅንነት ለመቀበል፤ ለማቀፍ፤ ለመርዳት ያለው ፈቃደኝነት ዜሮ ነው።

እኔ የምናገረው የውጪ አገሩን የኖርኩበትን ህይወት ነው። የአገር ውስጡን አላውቀውም። ኢትዮጵያዊነት ስለሚባለውም ሆነ ዞግ ስለሚባለውም።

ብቻ ለሀሉም ማስተጋሻ፤ ለሁሉም ማባባያ፤ ለሁለም የአብራኃሙ ቤት ሳተናው መሆኑን በረጅም ጊዜ አጥንቼ፤ አውጥቼ አውርጄ የደረስኩበት የውሳኔ ሃሳብ ነው።

ለዚህ ለፖለቲካ ፍጆታ ያለው የቅብ ብርቅርቅ ሳይሆን ለቀጣዩ ማግስት የሚረዳው ሰው ነኝ ባለው ውስጥ ሆኖ ስለሰው መገኘቱ ነው ጠቃሚው ፋይዳ ያለው ነገር።

ይህን አንግዲህ ሳተናው ድህረ ገጽ አሟልቷል። ስለሆነም 100%  የዓመቱ ምርጥ ድህረ ገጽ እንዲሆን በቀንበጥ ብሎጌ ስመረጠው ደስ ብሎኝ አኩርቶኝም ነው። ተስፋዬም ነው። 

በአብይ አክቲቢዝም ላይ ይህ ቀን እንዲመጣ አይደለም ሌላው OBN አልሠራም። የሳተናው ትጋቱ ዲካ አልነበረውም። ፌስ ቡክ ያሉትን መልካም ዕይታዎች ሁሉ ይለጥፍ ነበር። ያ ደግሞ እንደ እኔ ላለ ፌስ ቡክ ለማይሳተፍ ሰው እጅግ ጠቃሚ መረጃ ነበር። አንድ ጊዜ "ኢትዮጵያ ከጅብ ቆዳ የተሠራች ከበሮ አይደለችም" የሚል እኔ  ያላዬሁትን ለጥፎት አንብቤአለሁ። አገላለጹ የጠ/ ሚር አብይ አህመድ ነበር። 

የማከብረው እና እጅግም የምሳሳለት ሳተናው የፈለገው ሥራ ቢደራረብበት የአብይን መንፈስ የሚገልጹ ማናቸውንም መረጃዎች ለመለጠፍ ፋታ አይወስድም ነበር። ከብርኃን የፈጠነ እርምጃ ነበረው።

ይህ ቀን እንዲመጣ ነበር ድካሙ። ዛሬ ፍልቅልቅ ብለው ከረባታቸውን እና ገበርዲናቸውን ሽክ አድርገው፤ በአጀብ እና በእልልታ ጉሮ ወሸባዬ እዬተባለላቸው ወደ ባዕታቸው የገሰገሱት ሁሉ በሳተናው መንፈስ ውስጥ የነበረው የቅንነት አዎንታዊነት ያስገኘው የጥንካሬ ጥረት ስለመሆኑ ልብ ሊሉት ይገባል። 

ያን ጊዜ አብይ መንፈሱን አይዞህ - በርታልን - ጠንክርልን ማለት ይገባ ነበር። በዛ ባረጋ - ባልሰከነ በዶፋማው ወቅት ያን ዕንቡጥ ተስፋ መደገፍ፤ ከጎኑ መቆም በመንፈስ ደረጃ የዜግነት ድርሻ ነበር። 

እኛ ቀና ያለውን አከርካሪ በመስበር ስንጎምድ፤ ዕድላችን ስናሾልክ እንደኖርን ይታወቃል። ያ እንዲሆን ነበር የአሉታው ዘማቻዊ ትጋቱ። ተስፋን በባዶ እጅ በተነፋ ወና ፉኛ ...መጠበቅ ብቻ። ዕድሜ ልክ።

ሙሉ አቅም በሙሉ ክህሎት መዳፋችን ላይ ተገኝቶ እሱ ባክኖ ወይንም ፈንድቶ እንዲቀር ነበር ትጋቱ። ምንም የሌለን ያለውን ደግሞ ሽንጣችን ገትረን አከርካሪ ለመስበር ይሉኝታ የሌለን - ጉዶች። 

ስለሆነም ሚዲያቸው እና ካድሬዎቻቸው በቀበረቱ ጉድጓድ እዬተገባ ነበር የአብይ መንፈስን አቧራ በማረገፍ ልዕናውን ለማስከበር ወርቅነቱን ለማንጠር ሰፊ ተግባር ሌት እና ቀን የተሠራው።  

እናም ሳተናው ድህረ ገጽ የአሰበው ሆኖለታል። እኔ ነኝ ያለውን ብቸኛ ነኝ ያለውን ሁሉ በልበሙሉነት አሸንፏል። ስለሆነም እንኳን ደስ አለህ ልለው እሻለሁኝ።

ሳተናው ድህረ ገጽ ሁላችንም የሚያስማማን የሁሉ ቤት የሆነ አንድ  ለእናቱ የእናት ብቸኛ ጓዳችን ነው። 

ሲከፋን ዘው እንዳሻችን የምንልበት፤ ጨርቅ ለባሽ ተብለን የማንገፈተርበት። ልብ የመንፈስ አዳራሻችን - ሳተናው ብቻ! የህሊናም ማረፊያችን - ሳተናው ብቻ! እንዳሻን የምንሆንበት የጥበብ የነፃነት ማዕዶት እልፍኛችንም - ሳተናው ብቻ። ተመስገን እንኳንም አንድ ለእናቱ እሱ ኖረልን።  

በተረፈ ለሳተናው ድህረ ገጽ መጪው 2011 ዘመን የፍሰኃ፤ የሐሴት የሰናይ፤ የብሥራት፤ የበለጠ የስኬት እንዲሆንልት ከልብ እመኛለሁኝ።

መልካምነቱ፤ ደግነቱ፤ መካሪነቱ፤ ትጋቱ ለሁሉም የእኩል መንፈስ ማረፊያነቱንም እንዲቀጥልበት በትህትና አሳስበዋለሁኝ።

የኔዎቹ ተግባሩን ለመለካት በምልስት በአብይ አክቲቢዝም ላይ ከጣና ኬኛ ጀምሮ ፈቅዶ ፖስት ያደረጋቸውን ተግባራት አርኬቡ ላይ ገብቶ ማረጋገጥ ይቻላል።

 በዛውም አዲሱን ለውጥ ተፃረው ግን ነፃነት እንሰጣችሁአለን የሚሉትንም ቤተ የምሾ - የራሮት ድንኳነኞችንም መንፈስ ምን ይመስል እንደ ነበር ዝገቱን ሆነ ምርተቱን በምልሰት ማገናዘብ ትችላላችሁ።

ፈጣሪ የቀባው መንፈስ ኢትዮጵያ አድሎታል። ይህን እንዳይነሳንም አብዝተን እንጽልያለን። እንተጋለንም። እንኳን ለዚህ አበቃን! አምላካችን ልዑል እግዚአብሄር። ተመስገን አይልቅበትም። 

         የማክበርህ ሳተናው እንኳን ለ2011 በሰላም ደረስክልን።   

                        እንቁጣጣሽ። ኑርልን አክባሪህ።

ኢትዮጵያዊነት ከመፈጠሩ በፊት ፈተናን አሸንፎ የተፈጠረ ሚስጢር።
የኔዎቹ ቅኖቹ፤ ውዶቼ፤ ክብረቶቼ ኑሩልኝ።

መሸቢያ ጊዜ። 

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።