ለቀንበጥ ብሎግ ውዶቼ እንኳን አደረሳችሁ! መልካም አውድዓመት!



ይድረስ ለቀንብጥ ብሎግ ታማኝ ታዳሚዎቼ በሙሉ።

ከሥርጉተ ሥላሴ የቀንበጥ ብሎግና የፍቅራዊነት ዩቱብ አዘጋጅ።
„ልባችሁ የቀና ሁላችሁም እልል በሉ።“ 
መዝሙረ ዳዊት ምዕራፍ ፴፩ ቁጥር ፲፩

ናፍቆቶቼ ሆይ!

በቅድሚያ ዘመኑ ለተለወጠበት ምክንያታዊ መስዋዕትነትን ለከፈሉ ወገኖቻችን የህሊና ጸሎት በዬቤታችን እናደርስ ዘንድ እለምናችሁ አለሁኝ፤ ለሰኔ 16 ሰማዕታትንም አስበን። በዚህ እንስማማ።

ቄሮ እና የአማራ የህልውና የማንነት ተጋድሎ ላደረጉት የሰፋ እና የደረጀ የተጋድሎ አውራነት፤ ለፍሬም መብቃት ሁሉ ምስጋና ይገባቸዋል። ለዚህ ተጋድሎ ግንባራቸውን ለባሩድ ለተሰዉት ነፍሳቸውን አርያም ገነት ያግባልን፤ አካላቸው ለጎደሉትም መጽናናቱን ይስጥልኝ። ቤተሰቦቻቸውንም ይጠብቅልን፤ አሜን!

ጤና ይስጥልኝ እጅግ የማከብራችሁ እና ሙሉ መንፈሴን ለምልገሳችሁ የኔዎቹ፤ የብቻዬ የቀንበጥ ብሎግ ታዳሚዎች ሚስጢረኞቼ። እንዴት አላችሁልኝ? እንኳን ለዘመን መለወጫ ለ2011 ለቅዱስ ዮሖንስ ዋዜማ ዕለት አደረሳችሁ አደረስን።

እንቡጢጣ መረጃ ስለ ጎንደር አለችኝ።

እንዲህ አንድ የተለዬ ባህል አለው - ጎንደር። እርግጥ ከቤተሰብ ቤተሰብ ይለያያል አፈጸጻሙ። ለጎንደር ዋዜማው ፍጹም የተለዬ ግርማ ሞገስ አለው። እንዲያውም ዕለቱ የልጆች ሲሆን ዋዜማው ምሽት ላይ  የአዋቂዎች ነው ብል ያምርብኛል።

ዋዜማው ምሽት ላይ ጉዝጓዙ ግጥም ብሎ ይጎዘጎዛል። በጉዝጓዙ ልክ አድዮ አለበት። ከዛ ቤተሰብ ክብ ሠርቶ አዲሱን ልብ ለብሶ፤ ያልገዛውም ጸዳ ያለውን መርጦ በረድፍ በረድፉ እንደ ዕድሜ ደረጃ ይቀመጣል። 

ለቤተሰቡ ልዩ ሆና የምትወደድ የቅርብ ሰው ጎረቤት ልትሆን ትችላለች፤ አበልጅ ልትሆን ትችላለች፤ ጓደኛ ልትሆን ትችላለች፤ ምራት ልትሆን ትችላለች ልጅም ልትሆን ትቻላለች ብቻ የፍቅራዊነት መባቻ የሆነች አንዲት ልበ ንጹህ ቡና ታሰናዳለች።

በጉ ይጮሃል፤ ዶሮው ታስሮ ይጮኻል ሁሉ መሰናዶ ተጠናቋል። ጎንደር የሚቆላው ቆሎ የቡሌ ማሽላ አባባ ቆሎ ሽንበራ ስንዴ ገብስ የተለጠለጠ ንጉ በስኳር ተንቦልቡሎ ተዘጋጅቶ ህብስት ዳቦ የጎንደር ድፎ በልዩ ሁኔታ በውሃ እንፍላሎት ነው የሚጋገረው፤ በመደበኛም ሊሆን ይችላል ብቻ ምን አላፈችሁ አውዱ አልባብ ባልባብ ይሆናል። አቤት ደስ ሲል።

ነጭ ሪያኑ፤ ጠጅ እሳሩ፤ በኩቡካው፤ ዝንቅንቁ የተቀላቀለበት እና በተጨማሪም ሰንደል ይጨሳል። እና ለእኔ ዛሬ ነው ቅዱስ ዮሖንሴ። አንድ ዕውነት ብነግራችሁ ግን ዘንድሮ ብቻ ነው እኔ ዓውደ ዓመቴ ብዬ በሙሉ መሰናዶ የተዘጋጀሁት፤ በስደት ዘመኔ ሁሉ በተለዬ እሚከበረው ዘንድሮ ብቻ ነው። ዛሬ ያለብኝ ሥራ እንዲህ እንዳይመስላችሁ። 

እንደዚህ ዘመን በሥነ - ልቦና ያሸነፍኩበት ዘመን የለም። ስለዚህም ዲል ብሎ ይከበራል። አብይ ኬኛ! መመረጡ የሚሊዮኖች ድምጽ መሆኑ ብቻ ሳይሆን ይኸው ሰናይን በስፋት ዘርግቷል ስኬቱም ተፈትኗል። 

ድርብ ጭንቅላት ያለው፤ ብሄራዊ ቀን የሚያስወስን፤ ኢትዮጵዊው ማርቲን ኪንግ ሉተር፤ የአፍሪካ መሪ ብዬ ጽፌ ነበር አብይ ኬኛ ማጠቃለያውን ክፍል 6 እዩት ለእኛ ብቻ ሳይሆን እንዲረዱን እምነት ለጣልኩባቸው ይህንኑ ነበር የገለጽኩላቸው፤ ለሴቶች የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ፈላስፋችን ነው ብዬ መስክሬያለሁኝ፤ ደግሞም ዕውነት ነው መጋቢት 24 ቀን 2010 ትመስክር።

አሁን በቅርቡ የመልሱን ዕውቅና ደረጃ ከፍ ብሎ አዳምጫለሁኝ። ዕውቅናው እስከዚህ ድረስ የዘለቀ ስለነበር፤ ያልኩት ባልኩት ልክ ሆኖ ስለተገኘ መታመንንም አፍሼበታለሁኝ።

ስለሆነም ዘንድሮ ቅዱስ የሖንስ በተለያዬ መስተንግዶ፤ ሆኖ በማያውቅ መልኩ ባልተደመደ ሁኔታ በፍሰሃ ይከበራል። በዚህ አጋጣሚ ግን ለረዳኝ ለተባባረኝ - ላገዘኝ - ሃሳቤን ላለፈነው፤ ፍጹም ርጉና ቅኑ የሳተናው ድህረ ገጽ ለጥ ብዬ የጸጋ ስግደት እሰግድለታለሁኝ። የሚዲያ ነፃነት ኢትዮጵያ ያላት ከሱ መንፈስ ውስጥ ብቻ ነውና። በተጨማሪም የልቤን ያደረስ ማርከሻ ድህረ ገጽ ነው። ኦ 2010!  የሳቅ የፈግግታ ዓመት አዲስ ዓመት አጨልን አሳቀፈን …. ተመስገን።

ውዶቼ ሆይ!

ላደረጋችሁልኝ ልግልጸው የማልችልው ልዩ አትኩሮት እና ሊገለጽ ለማይችለው የታዳሚነት ነፍስ የሆነ ተሳፎ እጅግ አድርጌ አመስግናችሁ አለሁኝ።

በዚህ የስከንት ጉዞ የታዳሚ እና የብራን የመንፈስ ሃዲድ መሠረቱ ቅንነት መሆኑን ስላማምን ቅኖችን ያበራክትልን እላለሁኝ። ቅኖች ብቻ መከራችን ያሻግሩናል … ሸፍጥና ሸር ደግሞ ገድሎናል ወደፊትም አይምረንም። ብዙ ፈተና አለብን እንዳትረሱት እንዳትዘናጉም። 

ክብሮች ሆይ!

ቅንነት ከመልካምነቱ ያለፍ አቅም ፈጣሪ ብቻ ሳይሆን ትውልድን በስክነት ለመገንባት አውታሩ ነው። ቅኖች ከበረከቱ ብቻ ነው አላዛሯ ኢትዮጵያ በቀጠናው ይሁን በአገር ውስጥ ላለባት እናታዊ ሁለንትና ድርሻ ብቃቷን በጥራት አስተጋብራ እንደ አገር እንደ ህዝብ መቀጠል እና ማስቀጠል የምትችለው።

ክብረቶቼ ሆይ!

ተከድነው የሚንተከተኩ የማናቸዋም የክፉ ነገር ሥሮች መስረታቸው የቅንነትን መርህ የመግደፍ ጉዳይ ነው። ቅንነት ብቻ ነው አባጣ ጎባጣውን፤ ኮረኮንቹን፤ ዳገት ቁልቁለቱን ልጎ እና አስተካክሎ መርሃዊ ጉዟችን የሚያቃልልልን። 

ቅንነት ለብሩህ ተስፋ ሆነ ለፍቅራዊነት ማሃንዲስ ነው ለግልም ይሁን ለማህበራዊ ኑሯችንም። ቅንነት ወሳኝ ነው በሴራ ለተከዘነው የፖለቲካው መስክ ጉዞም። ቅንነት የመፍትሄ አምንጪም ነው። ቅንነት ጠቀሜታው ውቅያኖስ ነው። ችግሩ ቅኖች ጥቂት መሆናችሁ ነው።

አዱኛዎቼ ሆይ!

ፍቅርን ብቻ ሳይሆን ቅንነትም እንደ ጦር ነው የሚፈራው። መልካም ነገሮችን አንደፍራቸውም። ይልቁንም ድፍረታችን እና ድል አድራጊነታችን የሚወራረደው በሽፍጥ እና በተንኮል በተመሙ ስንስካሳራዊ ቅብጥርሶች ምንትሶች ነው። ግራጫነታችን ልክ የለውም። ግልፆችም አይደለነም - ለቅንነት። ራሳችን ስለማናምነው ትናንት ያልነውን ደግመን ማለት አቅሙም ሞራሉም ያነሰናል። 

ቅንነትን አሾፈንበት በመኖራችን ትውልዱ 50 ዓመት ሙሉ ሲባክን ኗሯል፤ ፕሮፓጋንዳ ተስፋን አያሳካም። አንዲት መልካም ዛፍ ለግለግ ብላ ከወጣች ያችን ከትክቶ ለማፍለስ ርብርቡን ከ2010 በላይ ያዬንበት ዘመን የለም። በአብይ መንፈስ ላይ የተሳላው ጎራዴ እና የተሰነቀው ሸፍጥን ታድምንብታል። ቀድሞ ነገር „ደምህ ደሜ ነው“ የጎንደር ቅኔ ከዚህ ይደርሳል ተብሎ አልታሰብም ነበር።

ጣና ኬኛን የወለደው እኮ ያ ቅንነት ነው። የጎንደሬዎች ሥረ - መሠረት የጎጃሜዎች ጣና ዘገሊላ ሆነና የዘመናት የቆም ቁርሾ ለመናድ መንገድ ተጀመረ። ነገር ግን ተጋፋ ተዘመተበት። ቸርነቱ የማያልቅበት አማኑኤል ከሃሳብ በላይ ሆኖ ሁሉንም በልባምነት ከወነው ለሁሉም ዛሬ ሀሤቱ ደረሰው። ሳቁ የሁሉም ሆነ። መከራው ዕለት ግን ጥቂቶች ብቻ ነበሩ።

የቀረ መኖሩ ጠፍቶኝ አይደለም። የ50 ዓመት ችግር በእፍታ አይወገድም። ክንፍ አለን ያሉትም ከዚህ የተግባር አውራ እርምጃ ከጫፉ መድረስ አያችሉም። ራሳቸውን ማሸነፍ ተስኗቸው ያሉበትን ደረጃ እንደ ትናንቱ እያየን ነው። ዘመንም ጊዜም አያስተምራቸውምና ዕብለት ብቻ፤ ኩሸት ብቻ፤ ማስመሰል ብቻ፤ መሸፈጥ ብቻ።

የሆነ ሆኖ ትግል ድል የሂደት ውጤት ነው። ተጋድሎችን በቅንነት ከተጋንለት ይሳካል። የሴራውን መረብ እዬበጣጠስን ቅኖች ያሰቡት ከግብ እንዲደርስ እንተጋለን። 

አብሶ የ አማራ ይህልውና የምንነት ተጋድሎ መስዋዕትነትም መረማመጃ እንዳይሆን እንታትራለን። በድፈረት ስለ ዕውነት ዘብ እንቆማለን። ዕውነት የቀን ብቻ አይደለችም። ዕውነት የተፈጥሯዋ ናት እና።  

ትህትናዎቼ ሆይ!

ዛሬ አዲሱን ዓመት በፍቅር ለማሰለፍ በርካታ ወገኖች አገር እንደገቡ እናውቃለን። ይህ ቀን እንዲመጣ የሚያደርገው ቁልፉ ጉዳይ ግን ስንት አሳር እንደ ነበረበት እናንትም ታውቁታላችሁ። የተቃለለ የትም አይደርስም የተባለ፤ የወያኔ አጀንዳ ነው ተብሎ የተጣጣለ እንደ ማበሻ ጨርቅ የትም እንዲወረውር የተዘመተብት ነበር። 

ነገር ግን ዛሬ ለሁሉም የሚበቃ ብርሃን እንሆ ሆነ። ከዚህ ውጪ መኖር ከባህር የወጣ አሳ ስለሚያድርግ ብቻ ባለመሆን ውስጥ መቀበል ግድ ሆነ። ይህ ዕውነት ነው።  

አይዞሽ ባዮቼ ሆይ!

ይህ ጉዞ ቅኖች ባይረባረቡበት ኖሮ በለመድነው ሁኔታ 2011 ቆዝምን እንቀበለው ነበር። አቅመ ቢሱ አቅም እንደሌለው ለዛሬ ብቻ ሳይሆን ለማግስትም ልኩን አውቆ መራመድ ይኖርበታል። ዛሬ ትንሳኤው ከሁሉም በላይ ለኢትዮጵያ እናቶች ነው። ይህ እንዳይሳካ ነበር አሉታዊው ትጋት የነበረው። 

አብዛኞቹ የታሰሩ፤ ሞት የተፈረደባቸው፤ የዕድሜ ልክ እስራት የተበዬነባቸው ሁሉ ለውጡን ሳይደግፉ ግን ነፃ የወጡበት ዘመን ነው፤ ለቀሪዎቹም የካቴና ቤተኞችም መትጋት ይኖርብናል። 

የነጻነት አዬር እዬተነፈሱ የሽግግር መንግሥት እያሉ የተሰበሰበን መንፈስን ይበትናሉ። መሪነት ጩኽት ገበርዲን እና ሱፍ አይደለም። 7 ቀን ሌት እና ቀን በጥበብ መሥራት፤ ያሉትን ሆኖ መገኘት፤ ፍቅርን ርህርህናን በ እኩልነት መመገብ ሃሳብ ማፍለቅ ነው መሪነት ማለት። 

ሌላው ቀርቶ የአላዛሯ ኢትዮጵያ አዬር ነፃነት የሚባለውን ያወቀበት ዘመን ነው። ሰንደቅዓላማችን ከፍ ብሎ በዬአደባባዩ አዲስ ዘመንን ለመቀበል በኩራት የተውለበለበት ዳግሞያዊ የአድዋ ድል መባቻ ላይ ነን። ይህን የደፈረው ደግሞ የጎንደር ጎጃም የአማራ የማንነት ይህልውና ሞጋዳዊ ምክንያታዊ አብዮት ነው። የትኛውም ዲሞ ላይ ተከስቶ አያውቅም ይህን መሰል የነፃነት ሙሉ ተጋድሎ። 

ገና አዲሱ መንገድ ሲወጠን „መባቻ“ የሚል ጹሑፍ ጽፌ ነበር። እነሆ መባቻው መሰንበቻም እዬሆነልን ነው። ተመስገን! የአብዩን ቅን መንፈስ ታገሪዎችን ያሰንብትልን። አሜን።

ስጋቴ በርካታ ነው አብዩን ሴረኞች መንገዱን እንዳይስትቱ ጉልበታቸውን እንደ ቄጤማ ያሰደርግልንም ሃሳባቸውንም ያምክንልን። አሜን በሉ! ይሁንልን በሉ! ይደረግልን በሉ። 

እውነት ለመናገር የራስ ተሰማ ናደው ሴራ ገና ከሩቁ እዬሸተተኝ ነው ስል ነው የባጀሁትም አሁንም ያ መንፈስ አያንቀላፋም። ለአድመኞች መዛል አያስፈልግም።

አጽናኞቼ ሆይ!

የሃይማኖት እሰጣ ገባዎች ውል ያለው ተግባር የተከወነበት ዘመን ነው። በፖለቲካ አቅም ደርጅት ተፎካካሪ ይባሉ ተቀናቃኝ ፓርቲዎች መሪ አልነበራቸውም፤ ቁጭ ብሎ የሚደራደራቸው ከእነሱ በሃሳብ የቀደመ እና የላቅ የሚያደራድራቸው መንገድ ቀያሽ መሃንዲስ አልነበረም፤ ኢትዮጵያ ሙሴ አልነበራትም።

ዛሬ ግን አንገታችን የማንደፋበት፤ የማናፍርበት ጠ/ ሚር አለን ብለን አፋችን ሞልተን የምንናገርበት፤ ሙሉ ስብዕና ያለው። ሙሉ የሞራል አቅም ያለው፤ ኢትዮጵያ አገራችን መንግሥት አላት ብለን ደፍርን የምንናገርበት ዘመን ላይ ነን። ለዛውም እረሙኝ ቆንጥጡኝ የሚል። እሱ ፈቅዶ ዝቅ ብሎልን እኛ በፍቅራችን ፈቅደን ከፍ ያደረግነው።

ቀጣይ ሙግቶች እንደ ተጠበቁ ሆነው። መቼም ሃያሲ ያዬውን ነገር አያሳድረውም። ድል ማለት ለውጥ ማለት መቀጠል መቻል ማለት ነው። ለመቀጠል ደግሞ አረም እንዲበቅል መፍቀድ የለብንም።
ዛሬ አድማጭ ነፍስ ያለው ማግኘትም አንድ ትልቅ ነገር ነው። 

አንዱ ባይመቸን ለሌላው አቤት የምንለበት አማራጮች ሁሉ አለን። ዛሬ ኢትዮጵያ እንደ ቀደመው የመሪ ደሃ አይደለችም። ቅን የሆኑ መሪዎች ለዛውም በኢህአዴግ በግንባሩ ውስጥ ባላሰብነው፤ ባልጠብቀነው ታምር ልንለው በምንደፍረው ዕውነት ውስጥ ኢትዮጵያ መሬት ላይ ተፈጥረውልናል። ተመስገን!

መኩሪያዎቼ ሆይ!

ያን ያሳለፍነውን ድቅድቅ ጨለማ አልፈን ዛሬ አንድ ጠ/ ሚር በደካሞች ጎጆ ተገኝቶ ማዕደኛ የሆነበት፤ ስደት ላይ ብጹዕና የሃይማኖት አባቶቻችን ጨምሮ ወገኖቹን በሚጓዝበት የሰማይ አውቶብ ካለምንም ቅደመ ሁኔታ አብሮ አሳፍሮ ከብክቦ ይዞ ወደ አገሩ የሚመለስበት፤ ጠያቂ ያጡ ደካሞችን አጋሩ አካሉ ቀዳማይ እምቤት ወ/ሮ ዝናሽ ታያቸው ጉንብስ ቀና ብለው የሚያስተናግዱበት፤

ከዚህም አልፎ ወላጅ አልባ ዕድለኛ ልጅን በግል ተርክቦ ለማሳደግ ቤተ መንግሥት የቆረጠበት እና የወሰነበት፤ ከዶሮም ባነስ ሁኔታ የምትኖር ልጃችን አብሥራ ማሬ ደማችን  -የመንፈስ ክፍያችን ችግር አደባባይ ወጥቶ ተሰምቶ ተደምጦ ሳይቀር፤ ቅዱሳን የተረባረቡት እና በደቂቃ በቅስፈት በአቶ ማይክል ወልፍ ኑሮዋ ህይወቷ ተለውጦ፤ በተስፋ ውስጥ እሷ ስቃ እንድንይበት የሆንበት ዘመን ነው። ዓውደ ዓመት እንዲህ ተስፋ ተጀምሮ እያዩ ከሆነ አውድዓመት ሊባል ይችላል።

ተስፋዎቼ ሆይ!

ለረጅም ጊዜ ከአዲስ አባባ ኗሪዎች በስተቀር በሁሉም ክልሎች ህዝብ ከመሪው ጋር ፊት ለፊት ሆኖ ከማህል እስከ ጠረፍ የናፈቀን የወገኖቻችን ሃሳብ የተጋራንበት፤ ምን እንደሚሰማቸው - እንዴትስ እንደሚኖሩ ያዳመጥንበት፤ እኛን እራሳችን ውስጣችን እንድናይ የሞገትንበት መልካም ዘመን ላይ እንገኛልን።

በአንጻሩ ሰው ሰራሽ በሆኑ ችግሮች ሚሊዮኖች የተፈናቀሉበት፤ ህይወታቸው የተቀዘፈበት፤ ኑሯቸው የተመሰቃቀለበትም አሳዛኝ ገጠሞኞችም አሳልፈናል።

መጪው ዘመን ቀላል የማይበሉ መስናክሎች፤ ድርብ ሴራዎች ሊኖሩ ቢችሉም ቅንነትን ዕውነት ከመገብነው ግን አይደለም ለኢትዮጵያ ለአፍሪካ የተስፋ ምድር የመሆናችን ሚስጢር ይጀመራል።

ዋርካዎቼ ሆይ!

ዘንድሮን ለዬት የሚያደርገው ያለመድንብን ለመልካምነት ዕውቅና በመስጠት እና በማመስገን እረገድ ዳታ ያለበዛንበት፤ እንኳን ደህና መጣህልኝ እቅፍን፤ እንኳን ተፈታህልኝ ውስጥን በመስጠት እና በመቀበል፤ መኖራችን ፈገግታት በመሸለመም ዘንድሮ አዲስ የታሪክ ዘመን እንድንጀምር ሽግግር ላይ የሆንበት የሳቅ ዘመናችን ነበር።

ሳቅም ብቻ ሳይሆን ዕንባም በወልዮሽ ያነባንበት የሲቃ ዘመንም ነበር። ብቻ ዘመኑ ጥሩነቱ አምዝኖ የበለጠ ጥሩ ይሆን ዘንድ ቅንነት እንሰንቅ ዘንድ መልካምነትን - ቸርነትን - ይቅርታን - ምህረትን የቀማመስንበት ተስፋን ለመጀመር የተሰናዳንበት ጊዜ ነው። ዘመነ ሎሬት ያልኩትም ለዚህ ነበር።  

መተማማኛዎቼ ሆይ!

በዚህ ሁሉ ሂደት አብረን ለመሆን መፍቀዳችሁ በሌላችሁ ጊዜ ውስጣችሁን በቅንነት፤ መንፈሳችሁን በልግስና፤ ልባችሁን በንጽህና ለእኔ ብዕር ምርት እና ብራና አስገብራችሁ ከግንቦት 1 እንደ ፈረንጆች አቆጣጠር እስከ መስከረም 10 ቀን አብራችሁኝ ለቆያችሁ፤ አብራችሁኝ ለሆነችሁ፤ ለደገፋችሁኝ - ላጽናናችሁኝ - አይዞሽ እኛ አለንልሽ ላላችሁኝ በመላ ዓለም ለምትገኙ የቀንበጥ ታዳሚዎች ሁሉ፤
በተጨማሪም ቀደም ሲልም በሳተናው ብራና ሙሉ ታዳሚዬ ለነበራችሁት ሁሉ መጪው ዘመን የደስታ - የፍስሃ - የጤና -የሰናይ - የሐሴት - የመቻቻል  - በጸና ቋሚ ስብዕና አብረን የምንዘልቅበት ይሆን ዘንድ ከልብ እመኛለሁኝ።

በፍጹም ፍቅራዊነት እና እኛዊነት እንቁጣጣሽ ይላል የውስጥ መስመራችሁ ታዛዣችሁ ቀንበጥ ብሎግ እንዲህ ይላል ...


ርህርህናው የጠለቀ
አክብሮቱ የላቀ
ሙግቱ የሞቀ
ፍቅሩ የፈለቀ
ቀረቤታው የደመቀ
ዕብለትን የሰለቀ
ነፃነት የሰነቀ
ጥበብን ያጸደቀ
የቅኖች ታዛዥ - የቅኖች ብራና የናንተው ቀነበጥ ብሎግ እንኳን አደረሳችሁ ይላል፤

የማከብራችሁ ሆይ!

ቀንበጥ የክት እና የዘወትር ታዳሚ የለውም። ለቀንበጥ ሁሉም የጥበቡ ጉልልት - የትውፊቱ መስረት - የእኛዊነት ልባዊነቱ፤ የእኩልነት ህይወቱ የታሪኩ ክፍለ አካል ውስጡ ነው።

እኔ ሎሌያችሁ ካለመጻፍ ምንም ነኝ። ካለእናንተም ትቢያ ነኝ። አኩርታችሁኛል። አብሶ የተሳታፊዎችን መኖሪያ ሳይ ግርም ይለኛል። አሁን እኔ ፖላንድ ኢትዮጵያዊ ለዛው አንባቢ ይኖራል ብዬ አላስብም ነበር። ፊሊፒን ራሱ ብቻ ኑሩልኝ። እንበርታ።


                            ቅንነትን እናበረታታ!                          
                        ዕውነት የተፈጥሮዋ ናት!                          

                የምንግዜም አክባሪያችሁ - ኑሩልኝ ሥርጉትሻ።        

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።