ለውጥን ማስቀጠል በህግ የበላይነት እና በተጠያቂነት!

ብልህነትን ከብልሆች ብቻ ሳይሆን ከሞኝዎችም መማር ይገባል።
„ከቀረውም ብርና ወርቅ አንተ እና ወንድሞችህ ለማድረግ ደስ
የሚያሰኛችሁን ነገር እንደ አምላከችሁ ፈቀድ አድርጉ።“
መጽሐፈ ዕዝራ ምዕራፍ ፯  ቁጥር ፲፱
ከሥርጉተ©ሥላሴ
23.90.2018
ከጭምቷ ሲዊዘርላንድ

የሰርክ ዕጣ ለቅሶ!ማን አብሶ?

እንዴት አለችሁ አዱኛዎቼ። ደህና ናችሁ ወይ? አንድ ዜና ሰማሁኝ ዕውነት ከሆነ ወርቅ እርምጃ ነው። የጠ/ሚር አብይ አህመድ የስሜን አሜሪካ ጉዞ መሰረዝ ጉዳይ የልቤ የሚባልለት ነው። 

በዚህ ስሌት የስሜን አሜሬካው የቀደመው ከሀምሌ 19 ጀምሮ የነበረው ጉዞም ተሰርዞ ቢሆን ለእኔ ምቾት የሚሰጠኝ ነበር። እኔ ተደሞዊ ነገር ነው ግጥሜ። ደመቅ ያለ ነገር አይወድልኝም። ብልጭልጩም እንዲሁ ... 

ሌላው የሰኔ 16 የድጋፍ ስልፍም ወቅቱን ያልጠበቀ በፍርክርክ ትልም ዜጎቻችን ለመሰዋዕትን የቀለበ ነበር፤ ይህንንም ተቃውሜ ጽፌ ነበር። እንዲቀርም ተማጽኜ ነበር። በውስጡ ያልተደፈሩ ሽንቁር - ድፍርስ - የጎርፍ ክምሮች ነበሩቡት። ለአዲስ አባባ የበቀል ጥሪት ማከማቻም ነበር። ይሄው ድሃው ዋጋ እዬከፈለበት ነው። አስከፋዩ ደግሞ የቀናው፤ የተቃጠለው ወገን መሆኑ ነው የሚያቆስለው።

ለዚህ ነው ወዮ አዲስ ስል የባጀሁት። ሌላው ይህ አቀባባል ምንትሶ ቅብጥርሶም የሃይል አሰላለፉን መስመር ቀያሽ ስለነበር አስፈላጊ አልነበረም። ፍንትው ያለ መረጃ ይሰጥ ነበር።በዚህም ሆነ በዚያም፤ እንዲህም ሆነ እንዲያ መስዋዕት ከፋዩ ደሃው ነው። ሊሂቃኑ እማ ምን ሲነካቸው ነው።

የሆነ ሆኖ ደስታን ቆጥቦ መያዝ ቀጣዩን ጉዞ የስኬት ዘውድ ይደፋለታል። ከመዋለ ንዋይ ይልቅ ደስታን በቅጡ ቆጥቡ መያዝ ከብዙ ነገር ይታደጋል። ነፍስ ሆኖ ነፍስ ይሰጣል። ሁሉንም ቀስ አድርጎ መያዝ መልካም ነው። እኔ አስከ አሁን ድረስ ለቤተሰቦቼ አልደወልኩም። ነገን ስላማላወቀው። ለዚህች መከራ እናት አዛኝ ዋቢ አግንታለች ብዬ የመሰከርኩት ድርቀት ታውጆበታል። አሁን ድምጽ አልባዎቹ  የኢትዮጵያ እናቶች ያለቅሳሉ። ዕንባቸውም እዮርን ያንኳኳል። 

የሆነው እና የሚሆነው ደግሞ የልብን ግድግዳ የሰነጥቃል። በነገራችን ላይ የነፃነት ትግል እንዲህ ችርስ የበዛበት ሠርግ እና መልስ ሲሆን ታሪክ ያሰተናገደው በሰሞናቱ ትዕይንት ነው። ልትታገል ስትቆርጥ ለከበሮ ባርኖስ አይደለም። 

አብሶ የነፃነት ጥማተኛውን ድምጽ አደራ የተሸከመ፤ ለዓይ አፋርነት ሁለመናን ማሳገዛት ተገቢ ነበር። ውዶቼ፣ ---ታውቃላችሁ ዕውነት ዓይን አፋር እና የቤት ልጅ መሆኑን?

ወደ ቀደመው ነገር ምልሰት ሳደረግ በዶር አብይ አህመድ ልቅና ወስጣቸው የተቀበለ የፖለቲካ ድርጀት መሪ ከሆኑት ውስጥ እኔ ዶር ነገደ ጎበዜ ብቻ ናቸው ብዬ ነው እማምነው። እሰቡት ከፖለቲካ ድርጅት ሊቀመናብርት ነው ያልኩት። ከዛ ውጪ ሥልጣን የማይሹ ቅኖች ሊቀ - ሊቃውንታት በድጋፍ ሆነ በተቃውሞ መቆማቸው ተፈጥራዊ ነው።

የሆነ ሆኖ እጅግ የተደሰትኩበት ዕውነት ከሆነ የሰሜን አሜሪካው ጉዞ ነው። አዎን! አሁን አሰፍስፈው የሚጠብቁ ሥር - የሠደዱ፤ እርር ኮምትር ያሉ፤ አቅም ያነሳቸው በተለመደው ትርምስ ኢትዮጵያ እንድትጓዝ የሚሹ መኖራቸው ከቅንነት በላይ አለመሆናቸው መልካም ነው። ልብ ተሸምቷል ማለት ነው። 

አስቸጋሪ ያደረገው የአብይ ሌጋሲ በሩ የለሽ እልፍኝ መሆኑ ነው። ይጠፋዋል ባልልም የአማካሪ መረጣው ላይ ግን ለእኔ ምቾት የማይሰጠኝ ጉዳይ ነው። የራስ ተሰማ ናደው ጠረን ይሸተኛል እያልኩኝ ዘለግ አድርጌ ጽፈያለሁኝ። ያ ደግሞ እጅግ አደገኛ ዘማናዊ የአድማ ድንኳን ነው።

አሁን እንኳን የአብይ ሌጋሲ ገና በለጋው የሚወሰደው እርምጃ እና እውነትን ለመድፈር ያለው አቅሙ ወና መሆን የነገውን ቅናዊ መንገድ ጎድጓዳ ወይንም ዝርግ ያደርገዋል። ታሪኩ ግራጫ እንዲሆን ያደርገዋል። ነፍስ አንድም ነፍስ ነፍስ ናት የፈጣሪው ፈቃድ ናት። 

ካለፈጣሪ ፈቃድ ነፍስ ከጠፋ ትግሉ ከእዮር ጋር ይሆናል። ለአደመኞችም መመቸት ነው። ለምቀኞችም መመቸት ነው። ለቅናቶኞችም መመቸት ነው።፡"አብዩም ይሄው አስገደለ" ለእኔ የሰማይ መብረቅ ያህል መርዶ ነበር። ለዛውም ለ እጩ ጠ/ ሚር ራሱን ላጨ አሸባሪ አድማ እና ሽብር ፍንደቃ ትእቢት ሲባል። ማዘን የውሰጤን ቁስለት አይገልጠውም። ተበደልውም በራህብ ይለቁ ነው ጉዳዩ ... ሚዛን የት ነህ ያሰኛል።

ከሌላው አብዩ መሻሉ በሰብዕናው ተፈጠሯዊነትን ማከብር ሆኖ ሳይ ያልበደሉ ንጹሃን መቀጠፍ በፈጣሪ ዘመንድም ሃጢያቱን ግዙፍ ያደርገዋል። ለሌላው የሚሰጠው ትእግስት ሌላውም የዛች አገር ዜጋ ነው። መሪ ወላጅ ነው። ይህን ሳያዩ ነፍሳቸውን አብይ የ እኔ ብለው የተሰወቱ ፈጣሪ ምን ያህል ይወዳቸዋል፤ ወላጆቻቸውም ለዚህ ልጆቻቸው መሰዋታች ምን ያህል ያቃጥላቸው? 

„ለውጥን በደም ስለማስጠበቅ“ የተነሳው እራሱ ለእኔ ምቾት አይሰጠኘም። ለዛውም በ አብዩ አንደበት፤ ይህን ተናግሮ አብዩ እንቅልፍ ወስዶት ካደረ መቼም ይገርመኛል? በደም ማሸነፍ ዕዳ ነው። አደራንም መብላት ነው። ግዛኝ ...ንዳኝ ... ቆንጥጠን ...  በሃሳብህ ሞግተህ እንድታሸንፈኝ እሻለሁኝ፤ እለቃልሃለሁ ብለህ ለከፈትከው በር …? ህም! ስንት ጊዜ ኢትዮጵያ ታምጥ?

ለዛውም ካለደም ብዙ ነገሮችን በጥንቃቄ መመራት የሚቻልበት ሁኔታ ሳይጠነዝል፤ ሚሊዮን ድጋፍ ተንተርሰህ ተኝተህበት ካለሆነ በስተቀር … ዕድሉ ሰፊ ድልዳል ነበረው… በ አብይ አክቲቢዘም ላይ እኮ ሳይከፈለን የተሰለፍን ሠራዊቶች እያለን፤ ምን ወደ ጉልበት ያስኬዳል። እርግ ይህ ፍቅር ስለመቀጠሉ የሰሞናቱ ሃላፊነት የጎደለው፤ ተጠያቂነትን የፈራ ትዕይንት ነገን ይዳኛው።

የአብይ ሌጋሲ የእሱ ጥረት ብቻ አድርጎ ሊመለከተው ይችል ይሆናል፤ ወይንም ወገኖቼ ብሎ የሚሳሳላቸው ሊመስለው ይችል ይሆናል፤ ማንም ባልነበረበት ቀን እና ሌት በግራ በቀኝ ይጨፈጨፍ፤ ይወገዝ በነበረበት ብዙ ተተግቶበታል በሚታይም በማይታይም ሁኔታ … ያን ድካም ከንቱ አድርጎ ማፈሰስ ከሃጢያት በላይ ነው። ወንጀልም ነው። 

የደከሙት ቅኖች በዬትኛውም ተቋም የደላቸው አልነበሩም። ወደፊትም ዕውነትን በወገኑ ቁጥር የደገፉት መንፈስ እራሱ እንደሚያሳዳቸው ይታወቃል። ይህም ተመክሮ እያለ ነበር ያን ያህል አቅም የፈሰሰው … ዋጋ ይውጣለት፤ ይተመን ቢባል ከሚገመተው በላይ ነው። 

የደገፍን ወገን ማሰር እና ማፈን ይቅር የማይባል ወደል ግድፈት ነው ለአብይ ሌጋሲ። ይህ የሆነው ከአማካሪ ክርታስነት የመነጨ ነው … ልክ እንደ የሰኔ 16 ሰልፍ ፈቀድ እና የአሜሪካ ጉዞው ቅንብር ልልነት፤ በሌላ በኩልም … አንዱን በመንፈስ ማቅረብ ሌላውን ማራቅ … ከ እናት ከሆነ መሪ አይጠበቅም። ጠ/ ሚር አብይ አህመድ በታሠሩ ንጹሃን ሆነ፤ አደባባይ ላይ ስለሚሰዉት ንጹሃን ማፈር አለባቸው፤ ዶር ለማ መገርሳም ቢሆኑ ...ወደ ተነሰቡት ንጽህና ቢመለሱ መልካም ነው። ሰው እነሱን ለመሆን እየታገል እዬታዬ እንዴት አልሆነ ገደል ውስጥ ሄደው ይቀረቀራሉ።  

አሁን እማያቸው ጠ/ ሚሩን መስሎ ለመታዬት ያሉ ሂደቶች የሚጠቁሙት መሠረታዊ አመክንዮዎች የሚያሳዩት የተበለጥን አይነት ጉዳይ ስለመሆኑ በአንድም በሌላም መልዕክት ይልካሉ። 

ሌላው ... በተያየዘ ሁኔታ፤ ትናንት ያልሆኑ ነገሮች፤ ትናንት ያልተለመዱ ነገሮች ዛሬ ላይ አያለሁኝ። ኮፒ ተደርገው። መልካሙን ኮፒ ማድረግ ጥሩ ነው። ግን ከውስጥህ ካልሆነ በጥድፊያ ይደርቃል። ጤዛ ነው አይቀጥልም። አንድ ዋሾ አንድ ቀን የተናገረውን አይደገመውም። ስለምን ቢባል ውሸት ስለሚረሳ።

ርህርህና፤ አክብሮት፤ ልስላሴ፤ ፍካት፤ ታጋሽነት፤ ውስጥነት፤ አቅራቢነት፤ አቃፊነት፤ እኛዊነት ወዘተ ከውስጥህ ከኖረ አትቸገረም፤ በቅዝቃዜም በሙቀትም፤ በደጋም በወይና ደጋም፤ በቆላም በበጋም።

ምክንያቱም የአንተ መግለጫ ስለሆነ። መምሰል ከሆነ ግን ትረሳዋለህ። ሌላ ምሳሌ ላንሳ ሰዎችን ሲያዩ ጸልዬው የሚመገቡ ሰዎች ይኖራሉ፤ በሌላ ቀን ስታገኟቸው ሳይጸልዩ ሲመገቡ ታያላችሁ። ምን ማለት ነው ይሄ ያ ተለምዶ ቀድሞውንም አልነበራቸውም ማለት ነው።

በኢትዮጵያ ፖለቲካም እንዲሁ ነው አንድነት በለው፤ አብሮነት በለው፤ አክብሮት በለው፤ ታማኝነት በለው ሁሉም በሆንከው ልክ ነው ከአንተ ጋር የሚኖረው። እሆናለሁ ብለህ ትሞክረው ይሆናል ግን አይዘልቅም። ስለምን? ያንተ ስላልሆነ ስለምትረሳው። 

የእሱነት ውስጥ ከሆነ ግን በፈለገው ሁኔታ ቢዳብር፤ ቢለመለም፤ ቢያሰብል እንጂ ደርቆ ወይ ተሰብሮ፤ ወይ ተቀንጥሶ፤ ወይ ጭራሽ ተረሺ ሆኖ አይታይም። ስለምን? የውስጥ ስለሆነ፤ ኮፒ ስላልሆነ። ፃዕዳ እና ኦርጅናልም ስለሆነ።

ምልከቶች መንገድ ጠራጊዎች ናቸው። ምልክቶች መንገድ ጠራጊዎች ብቻ ሳይሆን ብርሃንም ናቸው። እነዛን ምልክቶች ተከትሎ ሲኬድ መስታውት ይገኛል። መስታወቱ ዕውነትን ይገልጣል። 

በዕውነት ወስጥ ያሉ ማናቸውም አምክንዮች ብርሃን ሲያገኙ ግርዶሹ ተገልጦ እውነተኛ ማንነታቸውን ማዬት ይቻላል። ብልህነት ከብልሆች ብቻ ሳይሆን ሞኞቹ ገልበጠው መሆንን ሲተውኑ ለብልሁ ምን ያህል ባለመሆን ውስጥ መሆን ሲጋርድ እንደሚከፋ፤ እንደማያምር፤ ብልሹ እንደሚያደርግ፤ ተለጣፊና ግዑዝ እንደሚያደርግ ስለሚያዩት የበለጠ ብልህነታቸው ነጥሮ ተፈጥሯዊ እንዲሆን ያደርግላቸዋል ማለት ነው።

የሞኞቹ ጉዞ ግርድፍድፍና ወይንም ሽርክትና ለብልሆዎች የተላጋ፤ የተጠረበ፤ የተስተካከለ ሰብዕና እንዲላበሱ ያደርጋቸዋል፤ ብልህነት የሞኞችን መንገድ እገለብጣለሁ ካለ ግን የተገለበጠ የተቃጠለ ካርቦን ዕጣ ይገጥመዋል።

ሌላ እንደመከወኛ አንድ ምሳሌ ላንሳ። አንድ በዳይ በበደለው ጉዳይ ላይ አሸናፊ ሊመስለው ይችላል። ነገር ግን በመሸነፉ ነው መበደልን መፍትሄ ስለማደርጉ አይረዳውም።

ብልሁ ተበዳይ ግን በዳዩ ራሱን እንዲያብት የሚፈቅደው ያነን በደል ባለመድገም መሆኑን ጠንቅቆ ያውቃዋል። ስለዚህ ከክፉ ነገር ይልቅ አለመበደልም፤ መደልም አትራፊነታቸው ጣምራ ስለመሆኑ ይረዳዋል።

በዳይ በበደለው ልክ ከራሱ ሲሸሽ፤ ተበዳይ ደግሞ በተበደለው ልክ ራሱን እዬቀረበ ወደ ተፈጥሮው እዬዘነበለ ወንድ ከሆነ የራሱ ጌታ፤ ሴት ከሆነች የራሷ ልዕልት ያደርጋታል።

ነገን የሚፈራ ሰው ብቻ ነው የሚበድል። ነገን የሚደፍር ሰው አይበድልም። ስለምን? ነገ የራሱን ዕውነት ይዞ ስለሚዳኝ። ከጋሞ ተጎጂ ህዝብ እና አበው፤ ከጋሞ ወጣቶች ነገን የማድመጥ ብቃት እና ልቅና ይህ ዘመን የተማረው ታላቅ ተቋም የኢትዮጵያ ትውፊት እና ትሩፋት ሆኖ ይቀጥላል። 

ሌላውን ከመበደል፤ መደል ይሻላል - ለእኔ።

የኔዎቹ ኑሩልኝ።

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።