ኮ/ ጎሹ ወልዴ ለአላዛሯ ኢትዮጵያ በምድሯ ሲገኙ ምርቃት ናቸው።

ኮ/ ጎሹ ወልዴ ለአላዛሯ ኢትዮጵያ
በምድሯ ሲገኙ እዮራዊ ምርቃት ናቸው።

„ጥበብስ በቀደሙ ሰዎች ዘንድ ተመረመረች።“
 መጽሐፈ ምሳሌ ፴፱ ቁጥር ፩
ከሥርጉተ©ሥላሴ
 30.102018
ከጨምቷ ሲዊዘርላንድ።



መልካም ነገር ኮ/ጎሹ ወልዴ አገር ቤት ገብተዋል። እንግዲህ በሳቸው ጥልቅ የማስተዋል አቅም የመጠቀም የጠ/ሚር አብይ ለማ ካቪኔ ጉዳይ ይሆናል። እጅግ ለረጅም ጊዜ፤ በተደጋጋሚ ጊዜም እንደምገልጠው ኮነሬሉ የተከደኑ የአገር ሲሳይ መሆናቸውን ነው። 

እሳቸው የጠ/ሚር አብይ አማካሪ ከሆኑ ብዙ ነገር እንደሚቃለል ተስፋ አደርጋለሁኝ። የተወጣጠረው መተንፈስ የታሳነው አዬር ንጹህ አዬር ያገኛል። ኮነሬል ጎሹ ወልዴ ለአላዛሯ ኢትዮጵያ እዮራዊ ምርቃት ናቸውና

 ምርቃትን መጠቀም ደግሞ የዘመኑ መሪዎች ልባምነት ልብ ብርሃንነት  ይወስነዋል። አላዛሯ ኢትዮጵያ ከልቡ በሳል የሆነ፤ ልበ ሙሉ፤ ጨዋ ምርቁን የዋጠ፤ አማካሪ ያስፈልጋታል። ለዚህ ደግሞ ኮነሬል ጎሹ ወልዴ አብዝቶ የሰጣቸው የማድረግም፤ የመሆንም፤ የመቻልም፤ የመታገስም ባለሙሉ አቅመኛ ናቸው። እኛዊነትን ማግኘት የሚቻለበት አምክንዮ የውስጣቸው ማህተም ነው። ብሩህ ህሊናቸው እና ቅን አመለካከታቸው በራሱ አንድ ትውልድ ይገነባል።

እኒህን የአላዛሯ ኢትዮጵያ አንጡራ ሃብት ኢትዮጵያ በ100 ዓመት ከማታገኛቸው ልዑቃን አንዱ ናቸው። ክውን፤ ሽክፍ፤ ጠፈፍ ያሉ ብርቱ እና ጠንካራ አብነትም መሆን የሚችሉ ደርባባ የፖለቲካ ሊሂቅ ናቸው።

በወታደራዊው መስክ ሆነ በሲቢሉ በነበራቸው የተባ የተግባር ቆይታ፤ በስደትም አገር ቢሆን ክውን ያሉ ድምጣቸው ተሰምቶ የማይታወቅ የአገር ባለውለታ እና ተምሳሌት ናቸው። ስለሆነም እሳቸው የለውጡ አካልነታቸውን ከተበሰረ መዋለ ዕድሜያቸውን ከልጅነት እስከ ዕውቅት ያፈሩት በሳል የዳበረ ተመክሮ ድርጊት ላይ እንዲያውሉት ምቹ ሁኔታ ቢፈጠረላቸው እንጠቀማለን እንጂ አንጎዳም።

የአሁን የዬአካባቢው ገጭ ገው እንደ ተጠበቀ ሆኖ ኢትዮጵያ ዛሬ በምታራምደው ዝርግ ፖለቲካ ኮነሬል ጎሹ ወልዴ ሁነኛ ጉልበት ሆነው ያገለግላሉ ብዬም አስባለሁኝ። አሁን ኢትዮጵያ የራሷ ችግር ሊውጣት ተቀርባ ደግሞ ሌላ ተራማጅ እርምጃ እውስዳለሁ ማለቷን እያዳመጥን ነው። ከኦብነግ ጋር ያለውን ስምምነት ራሱ ጊዜ ቢሰጠው እና አደብ ቢመረመር በትእግስት ብታዬው ይመረጣል።

አሁን የተመደቡት አቶ ሙስጠፋ ዑመር/ መሐመድ ሥራ የጀመሩት በፈረሰው ጅጅጋ ላይ ነው። የሰውን ህሊና ለመለወጥ ተከታታይ ተግባራትን ይጠይቃል፤ የተጀመሩ ጉዳዮች መሰረት ሳይይዝ ለሌላ ቻሌንጅ የሚያደርግ ችግር ደርቦ መወጠር በውነቱ ለእኔ የፖለቲካ አማካሪ እጥረት ይመስለኛል። 

ሁሉ ነገር ቀስ እዬተባለ ይደረሰባታል። 40 ዓመት የኖረች አንዲት ዓይኗ የተሸፈነች ሴት አንድ ቀን እደሪ ብትባል እንደምን ብዬ እንዳለችው የተያዘ የተረዘዘው ሁሉ ጥድፊያ በጥድፊያ ሆነ። ምን ያስችኩላል?ይህን ያህል በአፍንጫ ይውጣ የሚሰኝ የሚጣድፍ ነገር የለም። ቀኖቹም ወራቶቹም ዓመታቱም የነበሩ ናቸው። ነገም ቀን አለ፤ ነገም ወር አለ፤ ነገም አዲስ ዓመት አለ ስለዚህ ተግ ማለትን ይጠይቃል።

ሌላው ሰሞኑን እንደ አዲስ የምሥራች የተሰማው አፍሪካውያን ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡበት የቪዛ ሁኔታ አዲስ ስልት የኢትዮጵያ መንግሥት እንደሚከተል ተደምጧል። ይህ የፓን አፍሪካኒዝም አህዱ ቢሆንም ኢትዮጵያ ይህን ለማስተናገድ ጥገናዊ ለውጧ እራሱ ያልጠና ስለሆነ መዘግዬት አለበት የሚል ጽኑ አቋም ነው ያለኝ። ጎንደሮች ይህን „ራስ ሳይጠና ጉተና“ ይሉታል።

የለማ አብይ መንግሥት ይህን ተከትሎ ሊመጡ የሚችሉ ችግሮችን ለመቋቋም የሚችልበት ሁኔታ ላይ እንዳልሆነ ይታወቃል። ራሱም ያውቃል። ሰከን ይበል - በትሁት መንፈስ። ለዚህ ነው „ሁሉ ተፈቅዶልኛል ሁሉ ግን አይጠቅምም“ የሚለው ቃለ ወንጌል። ጊዜ አቅም ሁኔታ ወቅት እና ቦታ የሚፈቅዱት እና የማይፈቅዱት ጉዳዮች አሉ።

 ከ2 ሚሊዮን በላይ ተፈናቃይ ያለባት አገር፤ አሁንም መፈናቀሉ ቀጥሎ ሌላ ካሳስትሮፍ መከራ ደግሞ እቀባለላሁ ብሎ መሰናዳት በውነቱ የልባም አማካሪ እጥረት ወይንም ድርቀት ነው። በዚህ ዘርፍ ጥሩ መባልን ከሆነ የተፈለገው ሳንባል ይቅር። ለሱማሌ ሰላም፤ ለደቡብ ሱዳን እና ለኤርትራ ስደተኞች ኢትዮጵያ የምትችለውን እያደረገች ነው። ያ ከበቂ በላይ ነው። ስለሆነም ጉዳዩ በይደር ሊቀጠር ይገባል ባይ ነኝ። በማስተዋልም ሊመራ፤ በ አደብም ሊመረመር ይገባል።

አላዛሯ ኢትዮጵያ ከውጭ የነበሩ የፖለቲካ ተፎካካሪ/ ተቀናቃኝ/ ተቃዋሚ ድርጅቶችን ወደ አገር በገፍ አስገብታለች። ለዚያ የሚሆን የህሊና መስናዶ እንኳን ለእኔ አሟልታለች ብዬ አላስብም። እነሱ የሚገኙበት ወርክ ሾፕ እንኳን የተካሄደ አይመስለኝም። ያ በዝርግ ፖለቲካ ሁሉም በፈለገው እና ባሻው መልክ ነው ትትርናውን መቀጠሉን አይተናል። ቢያንስ ወጥ የሆነ በወል ሊያስማማ የሚችል መንፈስን በተወሰነ ደረጃ ሊያቀራርብ የሚችል ምንም ሰነድ አልተደመጠም። ህግም ያስፈልጋል። 

የውጩ ዓለም እና የአገር ውስጡ ፖለቲካ ፍላጎቱ ራዕዩ ተመሳሳይ ቢሆንም፤ ተጨባጩ እና አዲሱ ታዳጊ ትውልድ አገር ያለው የመንፈስ አቅም ጋር አመጣጥኖ የመጓዝ የወልዮሽ የሆነ ወጥ መግባቢያ ሰነድ አስፈላጊ ነበር። ሰሚናርም በእጅጉ ያስፈልግ ነበር። መሰናዶው ስስ ነበር። በዬዕለቱ ሞት እና ግጭት፤ ጦርነት እና መፈናቀል ተስፋ ማጣት መሰረታቸው የዛ የዝርግ ፖለቲካ ጦስ ነው። ችግሩን አባባሰው የዝርግ ፖለቲካው ዘይቤ።

በሌላ በኩል ከተፎካከሪ/ ተቀናቃኝ/ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ምክክሩም ውሉም በጓዳ ነው የተከወነው። በራስ ውስጥ በግንባሩ ያሉ የገረዘዙ አመክንዮችም አሉም። ወጣ ገብ የሆነ። በጠቅላላ በውጭም በፖለቲካ ንቁ ተሳትፎ ሲያደርጉ የነበሩ የግል ታጋዮችንም በሚመለከት እንዲሁ አገር ገብተዋል፤ እነሱም ከህዝብ ጋር እንዲገናኙ ከማድርግ በስተቀር ሊመሩበት ስለሚገባ የተነደፈ የተዘጋጀ ነገር አልተደመጠም። ይህ ተስፋውን ወደ ስጋት ለመለወጥ ራሱን የቻለ አስተዋፆ አድርጓል። የተሸመተው የህዝብ ፍቅርም አይሆኑ ሆኗል። ቅኖች ጥቂት ናቸው፤ ለማገዝ ለመርዳት የሚታትሩትም እንዲሁ።

የኤርትራ እና የኢትዮጵያ ግንኙነት በሚመለከት ከላይ ቢጀመርም በገፍ ወደ ኢትዮጵያ ስለሚገቡት ኤርትራውያን ጉዳይ ባሊህ ባይ የሌለው ጉዳይ ነው። በሥነ - ልቦና ለማቀራረብ ሊሰሩ የሚገባቸው ጉዳዮች ያው በዝርግ ፖለቲካ በልቅነት ቀጥሏል። ኤርትራ ላይ እንዲህ ዓይነት ቀልድ የለም ብዬ ነው እማስበው። መግቢያው ሰፊ ቢሆንም እንቅስቃሴው እና መውጫው ግን ማጣሪያ ያለበት ነው። እነሱ ጥንቁቅ ናቸው። ዕድሜ ጠገብም የፖለቲካ ልምዳቸው እና ክህሎታቸው ለሀገር ልዑላዊነት ለማዋል ዝግጅታቸው ድርጁ ነው።

በሌላ በኩል ታስረው፤ መከራ አይተው፤ ተሰቃይተው የተፈቱ እስረኞች ጉዳይም በሚመለከት በገፍ ተፈቱ ከዛ በሆዋላ አንድ ድርጁ የሆነ ተግባር አልተከወነም። በሥነ - ልቦና ላይ የደረሰው ቁስለት፤ በአካል ላይ የደረሰው ጉድለት፤ በመንፈስ ላይ የደረሰው ድቀት በቃ እንደ አልባሌ ነገር ታይቶ አጀንዳ ሳይሆን ነው የቀረው። እነዚህ  የነፃነት አርበኞች ቤተሰብ አላቸው፤ ልጆች አላቸው ስለዚህም ህይወት ያለው ነፍስ ያለው አቅርቦት ሲደረግላቸው ማዬትን ይናፍቃሉ። 

እነዚህ የነፃነት አርበኞች አንድ ቀን እስር ቤት ካልቆዬ ጋር መመጣን ቀርቶ አላችሁን ሊባሉ አለመቻላቸው እጅግ አስደንጋጭ ነገር ነው - ለእኔ እንደ ሥርጉተ ሥላሴ። ከእንግዲህ ልጅ መውለድ የማይችሉ ሁሉ አሉ። እነዚህ ምንዱባን አልነበሩም ከፍ ያለ ክብር እና ሞገስ የተሰጣቸው።
  
ይህ ሁሉ ሰብሰብ ሲል እኔ ጠ/ሚሩ ብቁ፤ ልባም፤ ክህሎት ያለው፤ ሚዛናዊ የሆነ አማካሪ አላቸው ብዬ አላስብም። ስለዚህም ነው ምርጫዬ ወደ ቅኑ ኮ/ጎሹ ወልዴ ዝንባሌ እንዲኖረኝ ያደረገው።

ክፍተቶች በሰፉ ቁጥር ተጨማሪ አቅምን ይጠይቃሉ፤ ክፍተቶች በጠበቡ ቁጥር ግን አቅምን ይቀንሳሉ። ክፍተቶችን እዬሞሉ ለመሄድ ደግሞ ብቁ አማካሪ ጠ/ሚር አብይ አህመድ ያስፈልጋቸዋል። ኮ/ጎሹ ወልዴ ቅንነቱ አላቸው፤ ደግነቱ አላቸው። ዕውቀቱ አላቸው። ለማድመጥም ፈቃደኛ ናቸው። ከሁሉ በላይ ችግርን የመቻል ተፈጥሯቸው ድንቅ ነው። ሰውን ያከብራሉ። ሥልጣን ለቀቅኩኝ ብለው እንኳን ከኢትዮጵያዊ ሞራላዊ ዕሴት ዝንፍ ሲሉ አልተደመጡም። 

ኮነሬል ጎሹ ወልዴ በዕድሜም፤ በልምድም፤ በዕውቀትም በዲፕሎማሲያዊ ተግባራትም አንቱ ስለሆኑ ለዚህ ለጋ የለወጥ ዕንቡጥ ሂደት እጅግ አስፈላጊ እና ወሳኝም ሚና ይጫወታሉ ብዬ አስባለሁኝ። እኔ እሚያሳሳኝ ቅንነታቸው ነው። የፖለቲካ ሊሂቅ ሆኖ ቅን ሰው ማግኘት ዳገት ነው። 

አጋጣሚውን፤ ሁኔታው ስላልፈቀደ ነው እንጂ እኒህ ቅን ግልጽ እና ብቁ ኮነሬል ብዙ እጅግ ከፍ ያለ በሳል ተመክሮ ነው ያላቸው። ሙሉ ብቻ ሳይሆን ንብርብር ክህሎትም አላቸው። እግዚአብሄር የሚመሰገነው ሌላው ቁም ነገር ደግሞ ፕሬዚዳንት ወ/ሮ ሳህለወርቅ ዘውዴም የዲፕሎማሲያዊ አቅማቸው ልዑቅ መሆን ከወጣቱ መሪዎች ጋር ይህ ሲዋህድ አላዛሯ ኢትዮጵያ ዳግሚያ ትንሳኤዋን ተስፋ ማድረግ ይቻላል የሚል ሙሉ ዕምነት አለኝ።

በመጨረሻ እጅግ ለማከብራቸው፤ ለምሳሳላቸው ለኮ/ጎሹ ወልዴ እንኳን ለአገረዎት መሬት አበቃዎት እያልኩኝ ረጅም ዕድሜ እመኛለሁኝ። በተጨማሪም ቲም ለማ ዕድሉን እንዲያውቅበትም እንደ ተለመደው ሁሉ ዛሬም አበክሬ የምገልጸው ኮ/ጎሹ ወልድ የጠ/ሚር አብይ አህመድ አማካሪ ሆነው እንዲመደቡ ነው። በዚህ ኢትዮጵያዊነት ያተርፋል፤ በዚህ ተስፋ ያተርፋል። በዚህ ኢትዮጵያ ታታርፋላች፤ በዚህ ትወልድ ከብክነት ይድናል።

ችግራችን ልቅ - ፍላጎታችን ልቅ - ምኞታችን ልቅ - ህልማችን ልቅ - የመሆኑን ያህል ከምናመሰግነው የምናጣውረው ይበርክታል። ከምናበረታታው ይልቅ ስንጥቆችን እያሸተትን ማስፋት ይቃናናል፤ ይህስ ባይሆን ኑሮ ይህስ ዕድል ባይገኝ ኖሮ ብለን አናስበውም። ለውጡ ጥገናዊ ለውጥ መሆኑ እዬታወቃ ስለምን አብዮት አላዬንም፤ ስለምንስ ሥር - ነቀል ለውጥ አልመጣም ብለን የትናንት ላይበቃ ዛሬም እዛው ላይ እንዳክራለን። ኢህአዴግ ሥርነቀል ለውጥ ላማጣ የምለው ራሱን በራሱ ሊከስም ነውን? ተበጥብጦ አይጋት ነገር የሚሰማው ነገር እኮ የጉድ ነው። 

የሆነ ሆኖ ጠ/ሚር ቢሮ የሚችለውን እያደረገ ነው። ሰው የሚችለው ብቻ ነው የሚችለው። ከሚችለው በላይ ከሆነ ያ ሰው ይፈነዳል። ከዛ በላይ ሦስት ጊዜ ግድያ አራት ጊዜ መፈንቀለ መንግሥት ሌላም አለ የሐምሌው ዝምታ። ወያኔን ያህል ጠጣር የፖለቲካ ድርጅት ተሸክሞ፤ አቦይ ስብሃትን ሳጅን በረከትን ያህል የሴራ ቦንዳ ተሸክሞ ይህን ያህል መራመድ ረመጥ ላይ ጎጆ ቀልሶ የመኖር ያህል ነው። ከበሮ በሰው እጅ ነው ነገሩ ...  

የ50 ዓመት ችግር በ7 ወር ቀርቶ በ10 /20 ዓመት መጨረስ ከተቻለ ዕድለኞች ነን። እግዚአብሄርም ምርቃቱን የሚያሰቀጥለው የተገኘውን ዕድል ተመስገን ስንል ብቻ ይሆናል። በስተቀር ምርቃት እኛን ቆሞ አይጠብቅም። ምርቃት የኩሬ ውሃ አይደለም ካልተጠቀምነበት ቀልጦ ይፈሳል። ወይንም ምርቃቱ ይነሳል።
ተጨማሪ ሊንኮች እንሆዎ ... 

https://sergute.blogspot.com/2018/06/blog-post_42.html

ትውልድ የማይተካቸው ኮ/ ጎሹ ወልዴ ቃላቸውን አተሙ!

ረቡዕ ፣20 ጁን 2018

ኮ/ጎሹ ወልዴ ለ አብይ ካቢኔ አማከሪ ቢሆኑ? ሐሙስ 11 ኦክቶበር 2018

ማስተዋል የተሰጠን ልንጠቀምበት እንጂ ተንተርስነው ልንተኛ አይደለም።
የኔዎቹ ኑሩልኝ።

መሸቢያ ጊዜ። 

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።