ኮ/ ጎሹ ወልዴ ለአብይ ሌጋሲ አማካሪ ቢሆኑ?
ቅጥልጥልጥልጥል።
የድንገቴ ደረሽነት ዘላቂ ጠያቂ ነው ፍትህነት።
„ነፍሴ እጅግ ታወከች፤ አንተም አቤቱ እስከ መቼ ድረስ ነው?“
መዝሙር ፮ ቁጥር ፫
ከሥርጉተ©ሥላሴ
11.10.2018
ከጭምቷ ሲወዘርላንድ።
ለኢትዮጵያ እኒህ የምርጥ ምርጥ ዕንቁ ዜጋ አሁኑኑ ያስፈልጓታል!
ትንሽ ነገር ማለትን ፈለግኩኝ። ትናንት ተፈጠረ ስለተባለው ጉዳይ የእኔ ምልከታ ደግሞ ትንሽ ለዬት ይላል። ትንሽ ወደ ኋዋላ ልመለስ የ2010 መባቻ መስከረም ገፋ አድርጎ ወራት ሲከታተሉ የድንገቴው ሁኔታ ሱናሜ ነበር። ይህን ሱናሜ በእርጋታ በማስተናገድ እረገድ የቀደመው ኦህዴድ/ ኦዴፓ ይዞት የተነሳውን ዓላማ ለማሳካት ሰማይ እና መሬት ቢደባለቅ አለቅም ብሎ ሞጥሮ ከገዱ መንፈስ ጋር ሲታገል ነበር።
በሱማሌ ክልል ወደ አንድ ሚሊዮን ህዝብ መፈናቀል፤ ቀጥሎም ሙያሌ አካባቢ 50 ሺህ ዜጎች መፈናቀል ብቻ ሳይሆን ወደ ኬንያ በርካቶቹ መሰደድ በሚመለከት የሚችለውን በማድረግ በተረጋጋ መንፈስ የቁልፍ ቦታ ባለቤትነት ላይ ትጋቱ የኦህዴድ እንደ ባህል መወሰድ የሚችል ይመስለኛል እኔ የታዘብኩት እንደዛ ነውና። ነገሮችን ተረጋግቶ መመልከት።
አሁን ጠቅላይ ሚኒስተር አብይ አህመድ ወደ ሥልጣን ከመጡባት ማግሥት ጀምሮም መፈናቀሉ፤ ሞቱ፤ ሳቦታጁ በእጥፍ ቀጥሏል። እሳቸው ደግሞ በነበረው ሙቀት ልክ ተረጋግተው የሚችሉትን እዬከወኑ ነው። ይህ መረጋጋት የዶር ለማ መገርሳ፤ የዶር አብይ አህመድ፤ የአቶ ደመቀ መኮነን፤ የዶር ገዱ አንዳርጋቸው የመንፈስ አቅም ይመስለኛል።
ዶር አብይ አህመድ አይደናገጡም። አይርበተበቱም። ይህ መልካም ነገር የሚያሳዬው በራስ የመተማመን አቅም ነው። ነገር ግን በራስ መተማመኑ ካልተመጣጠነ ቸለልተኝነት ፈጥሮ አደጋ ሊያስከትል ይችላል። ምን ማለት ነው ይሄ? በራስ መተማመኑ ከኢትዮጵያ የሴራ የሸር የአድማ የምቀኝነት የቅናት በሽታ መከዘን ጋር የተመጣጠነ አይደለም።
ሴራ ሌጋሲው ለሆነው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ልስሉሱ የአብይ ሌጋሲ አካሄድ ግጥሙ ሊሆን ባለመቻሉ ነው ይህ ሁሉ ቀውስ እዬታዬ ያለው። አንድ ቀን የሌላ አገር ኢንባሲዎች ኢትዮጵያን ለቀው ሊሄዱ ይችላሉ፤ ይህም ብቻ አይደለም የአፍሪካ ህብረቱም ቦታው ይቀዬር ሊባል ይችላል። ይህ ግነት ሊመስል ይችላል። አይደለም። ሶርያ እኮ ኢትዮጵያ ሁናለች። የተደራጀ አሉታዊ ሃይል ኢትዮጵያም ምስቅልቅል እያደረጋት ነው። በዛ ላይ ድህነቱ አለ።
ከመንግሥት አቅም እና ቁጥጥር በላይ የሆኑ ሥርዓተ አልበኝነቶች ከቃላት አጠቃቀም ጀምሮ እዬታዬ ነው። ኦነግ እኮ እኔም መንግሥት ነኝ እያለን ነው። መቀሌ ከመጋቢት 24 ቀን ጀምሮ ለማንም ለምንም በማንም ተዳድሮ አያውቅም፤ ቤንሻንጉል አፋር ጋንቤላ መታበዩ ያን ያህል የተንጠራራ ነው።
እያንዳንዷ ዲቂቃ በሸር በምቀኝነት በሴራ በአድማ በቅናት የበከተ ነው። ትግሉ ከዚህም መሰል እኩይ ተግባር ጭምር ጋርም ነው። ይህም ብቻ አይደለም ወንጀለኞች፤ ገዳዮች፤ ዘራፊዎች፤ አረመኔዎች፤ ሴረኞች ምንም እርምጃ ሳይወሰድባቸው በዛው በነበረው ልክ፤ መዋቅራቸው፤ መረባቸው እንዳለ ሆኖ በቸለልተኛው የአብይ ሌጋሲ ንድት ላይ ተግተው እዬባተሉ ነው፤ ነባሩ መዋቅር አልፈረሰም፤ ጥገናዊ ለውጥ እንኳን አልተደረገም። አውራ ሆኖ በወጣው ኦዴፓ በኦነግ ምክንያት ብቻ ሳይሆን ቀደም ባሉት ጊዚያቶች ጠራጠሮ ነገር መኖሩን በርቀት ጠረኑን ያስተዋልን ነበርን።
ራሱ አውራው ፓርቲው ኦዴፓ ራሱን የሚታገል ከሆነ፤ ለሚመራው ለውጥ የጀርባ አጥንት የመሆን አቅም ካነሰው፤ ቅንነቱ ከተላጣ፤ ታዛዥነቱ ፍቅፍቅ ከሆነ አደጋው ሰፊ ነው። የሰው ለውጥ በዬጊዜው ሲያደርግ እመለከታለሁኝ ይህ ሳይሆን የእኔ ብሎ ለውጡን የመቀበል ጉልበታም አቅም መፍጠር ነው የተሻለው መንገድ። ለምን? ቅናት።
አብዩ በአጭር ጊዜ ውስጥ ያን ያህል ፍቅርን በገፍ ያገኛል ተብሎ አልተገመተም ነበር። አሁን ሁሉንም ሎድ ተሻከሚው አማራ ክልል ነው። ፍጹም በሚደንቅ ሁኔታ የአብይ መንፈስም በነፍስ ወከፍ የያንዳንዱ ቤተስብ አባል ሆኗል። ይህ ቅንነት የመኖር ብቻ የከወነው አመክንዮ ነው።
ለቅኖች መልካሞች ቅርቡ ናቸው። ከሁሉ በላይ መልካም ዕድሉ ለአገር ይበጃል ብሎ የማሰብ ሥልጣኔም ነው ብዬ ነው እኔ እማምነው። ህብረ ብሄር ተፎካካሪ ፓርቲዎች ያላቸው ተስፋም፤ መንፈሳቸውን ያስጠጋውም የአማራ ህዝብ ብቻ ነው። ውሃ ልክነት ማለት ይህ ነው።
ሌላው የዓመቱ የሥራ አፈጻጸም ስንፍና የዘገበው የሰሞኑ ዜና ገላጮቹ እነማን እንደ ነበሩ ተረድተናል። ገላጮቹ ቅኖች ሊሆኑ ይችላሉ ግን አንድ ስዕል ማዬት ይቻላል ከላይ እስከታች ያለው መዋቅር እንዴት እንደ ተዋቀረ። ገዳዩ - አሳሪው - ፈራጁ - መርማሪው - ደብዳቢው አንድ አይነት ሆኖ የሰብዕዊ ጉዳይ ኮሚሽነሩ ደግሞ እዛው ቤት ነው፤ የሚገረመው እስከ ታች መሰሉ ነው የተዋቀረው አሁን ቤንሻንጉል ላይ እነ „ጓድ አትክልቲ“ናቸው።
በዚህ ሁኔታ ማዕከላዊ መንግሥትን የህዝብን ደህንነት ሰላም መረጋጋት በመፍጠር ላይ ያለው ከአንድ ቦታ አንስቶ ወደ ሌላ ቢወሰድ የሃላፊነት ሽፍት ቢደረግ እንኳን እስከ ታች እስከ አለወረደ ድረስ አደጋው ሰፊ ነው። አሁን የኢትዮጵያን የጸጥታ አካላት የሚመሩ መኮንኖችን ከጠ/ ሚሩ ጋር ወይይት አደርገዋል። ገለፃው እጅግ ከባድ ነበር። እኔ አልገባኝ ብሎ ካናዳ ከሚኖረው ፖለቲካ ሳይንስ ካጠናው ወንድሜም ጓዴም ጋር ተወያይቸበታለሁኝ።
የዛን ጉባኤ መንፈስ ወደ ታች ለማወርድ ቀላል አድርጎ ለማስረዳት የተሄደበት መንገድ ምን ያህል ነው? ለመሆኑ የበታቾቻቸውን የሠራዊቱ የበላይ መኮነኖች ደረጃ በደረጃ የለውጡን መንፈስ አስረድተዋቸዋል ወይ? አልሰማነም። ከፍተኛ መኮነንኖች ሠራዊቱን ለመሰብሰብ ራሱ ድፈርቱም አይኖራቸውም። ምክንያቱም በሙስና ጭምልቅልቅ ያሉ ስለሆኑ። ሙስናው የገንዘብ ብቻ አይደለም የሴሰኝነት፤ የስልጣን ብልግና፤ የስንፍና ወዘተ ….
ያ ብቻ አይደለም ራሱ ህዝቡ ዘንድ እንዴት መንፈሱን ጤናም የሆነ ግንኙነት ሊፈጠር እንደሚችል ሁሉ አልተሠራበትም። እኔ አንድ ጊዜ ፋቲክ ራሱ አስፈሪ ነው ብዬ ሁሉ ጽፌ ነበር። ልጆች ፋቲክን ሲዩ እንደሚበረገጉ እና በሥነ - ልቦናቸው ላይ ጫና ሊፈጠር እንደሚችል ነበር የጻፍኩት። ፋቲኩ ልብሱ አስፈሪ ከሆነ ጭካኔያዊ ሰብዕናው ሲታሰብ ከዚህ ከለማ አብይ ሰዋዊ ተፈጥሯዊ አዲስ ፍልስፍና ጋር ለማገናኘት ጥረት አልተደረገም። ላይ ብቻ ተንጠልጥሎ ነው የቀረው።
ሁሉን ነገር አንድ ሰው ሊፈጽመው አይችልም። አሁን እንደማዬው ተወጣው አይነት የዝብሪት ቤት ነው ሆኖ ያለው። ከጎን የተሰለፈው ሰው ጥቂት እንደ ሆነ ነው እኔ እምረዳው። ተፎካካሪ ፓርቲዎችም ጤነኞች ቁጭ ብለው ሳይመዘገቡ ቀለብተኛ ከሚሆኑ እስኪ ትንሽ ሥራ ይጀምሩ። የእረፍት ጊዜው የሃኒ ሙኑ ክ/ ጊዜ ቢያበቃና ህሊናን ወደ በጎነት በመለወጥ ተግባር ቢተጉ ምን አለበት?
አሁን የትናንቱ ጉዳይ ለእኔ የኩዴታ ክብሪት ነው። የወታደራዊ ኩዴታ የሙከራ ሪህርሳል ነው ለእኔ የሚሰጠው ትርጉም። እስኪ ሂዱና ሞክሩት ዓይነት የበላይ አዛዦቹ የፈቀዱት ነው። የ66ቱ አብዮት እኮ በዚህ መልክ ተከውኖ የተካሄደ ነው።
አመጽ በወታደራዊ ቤት እዝ ሰንሰለት ተጥሶ ያ ሁሉ ዲስፕሊን ተረግጦ ገፊ ሃይል ከሌለው በግብታዊነት ተከወነ ለማለት እኔ አልችልም። ታቅዶ የተከወነ ነው ብዬ ነው የማስበው። መረጃውም ቢሆን አልደረሰም ሊባል አይችልም መረጃው ደርሶ ግን የማስደንገጥ ተግባር መከወን የፈለገ ሃይል አለ ብዬ ነው የማስበው። አዘዦቻቸው ሊጠዬቁ ይገባል። መረጃው የታፈነበት አንድ አካል እንዳለ እረዳለሁኝ። እዛውም አገር ውስጥ ጠ/ ሚሩ እያሉም እንዴት ኩዴታ ማድረግ እንደሚቻል ልምምድ ነው ፑሽአፑ።
እኔ የገረመኝ እንደ ሁልጊዜው ዶር አብይ አህመድ ቀለል አድርገው መግለጻቸው ነው። ይህም ብቻ ሳይሆን ያሰተነገዱበት መንገድ ራሱ እንደ ሲቢሉ አያያዝ ነው። እኔ እንዲያውም እዬገረመኝ ያለው በዚህ እጅግ ትሁት የሰብዕብና ሁኔታ እንዴት በወታደራዊ ቤት እንደኖሩ ነው።
ምንም እኮ ወታደራዊ ቤት ድርሽ ያሉ አይመስሉም። እኔ እንደሚገባኝ ይህ ጉዳይ ተቀጣጣይ መልዕክት ይዞ የተነሳ ግዳጁንም የፈጸመ ይመስለኛል። ለቀሪ የጸጥታ ክፍሉ አዲስ ድንጋጌ ጽፏል። የማይቻል የለም የሚል። ለእኔ ይህ ልዩ አመጽ አነሳሽ ደወል ነው። ለእኔ አለርም ነው። ለእኔ ጠረኑ የኩዴታ ጠርን ነው።
ሳቢያው የኑሮ መጎሳቆል ይሁን እንጂ ምክንያታዊ ንቅናቄው ግን የለውጥ አካል የመሆን ሩበኝ ፈሊጥ ነው። ቀደም ሲል በተለያዩ አካላት ለሠራዊቱ ጥሪ ሲያቀርቡለት ነበር። ያን ጊዜ ጥሪውን አልተቀበለም ሰራዊቱ አሁን ግን ያን ድምጽ ያዳመጠ ይመስላል።
በሌላ በኩል በተደጋጋሚ የገለጽኩት ጉዳይ ነበር። አንድ ግድያ ሲፈጸም ሌላ ቃጠሎ እንደሚኖር። ከድንገተኛ ክስተቱ በፊትም በኋዋላም እሳት ቃጠሎ አለ። የሰኔ 16 የኩዴታ ጉዳይ መርካቶ መስጊድ አካባቢ ቃጠሎ ነበር፤ የሐምሌ 19 የቆመስ እንጂነር ስመኘው ህልፈት ተከትሎ በተከታታይ አዲስ አባባ ሁለት ቦታ ላይ ቃጠሎ ነበር፤ የጅጅጋው የቤተ መቅደስ ሰማዕትነትም ከቃጠሎ ጋር ድንኳን የጣለ ነበር።
አሁን ደግሞ ልዩ ሃይል ወደ አዋሳ ከመመለሱ በፊት ጠ/ ሚሩ ጋር መነጋገር እንፈልጋለን በሚል በተወሰደው ንቅናቄ አዋሳ ላይ ሌላ ቃጠሎ ነበር፤ እዛው አወሳ ላይ አንድ ባለሃብትም ልክ እንደ ቆሞስ እንጂነር ስመኘው በቤታቸው ውስጥ እንደተገደሉ ዜና ተዘግቧል፤ ነገ ደግሞ ሌላ ቃጠሎ፤ ከቃጠሎው ፊት እና ኋላ ደግሞ ሌላ ግድያ ይሁን ፍንገጣ አለ። ቅጥልጥልጥልጥል ያለ ነገር ነው እኔ የማዬው። አሁንም ሌላ ቅጥልጥል ይኖራል።
የሚገርመው ትግራይ ላይ ኮሽ የምትል ነገር አለመኖሩ ነው። ትግራይ በሰላማዊ ደስታዋ ህይወቷን ታጣጥማለች። ወንጀለኞቿንም እቅፍ ድግፍ አድርጋ ዋሻ ሆና ትንከባከባለች። አገር ቢነድ ምን ሲገዳት፤ ብቻ ከሷ አይድረስ። አሁን የአቶ ሞላ አስገዶም ሠራዊት ከህዝብ ጋር ከመቀላቀሉ በፊት ስልጠና ላይ ታስከትመዋለች። ቀልድ የለም። አንድ የወል ቋንቋ አለ መሬትን ንብረትህን ሰላምህን ልማትህን አታውክ የሚል። ልባሞች ናቸው እነሱ እቴ። እነ አቶ ዳውድ ኢብሳ ግን ቤንዚን እና ክብሪት ይዘው ይገሰግሳሉ … አሁንም ህዝብን ለማሳጨድ።
ወደ ቀደመው ነገር ምልስት ሳደርግ ይህን ቅጥልጥል ነገር የሚነግረን በውል የተደራጀ ከትግራይ በስተቀር በዬአካባቢው እንዲህ ዓይነት የማስደንገጥ ተግባራትን የሚከውን ሃይል መኖሩን ነው። አሁን የአዋሳው የኢህአዴግ ጉባኤ በአዲስ ጉልበት በአዲስ መንፈስ ተነሳሁ ብሎ አዋሳ ላይ ባወጀ ማግስት ነው ይህ የትናንቱ የቤተ መንግሥት ግልጥ ግርግር የተከሰተው። አትፎክሩ ነው ዕድምታው።
ከቃጠሎው በተጨማሪ አንድ ባለሃብት በቤታቸው ውስጥ ሞተው የተገኙት ደግሞ አዋሳ ላይ ነው፤ ወደ አውደ መኖሪያው ወደ አዋሳ ሊሄድ የነበረው ልዩ ሃይል ደግሞ በተሟላ ትጥቅ ቤተ መንግሥት ድረስ ሄዶ አስገድዶ ጠ/ ሚሩ የማግኘት እርምጃ ወስዷል።
እርግጥ ነው በሰላም ውይይቱ ተጠናቋል። በዚህ ወስጥ ያሉ ያልተፈቱ ቁልፍልፍ ያሉ ጉዳዮች ግን የጠ/ ሚር አብይ አህመድ ጽ/ ቤት ሆነ የኢትዮጵያን ደህንነት እንዲጠብቅ ሃላፊነት የተሰጠው አካል እንዲህ በመሰለ ገርነት እንዲህ በመሰለ ዝርክርክነት ነገሮችን አቃሎ በማዬት እንዲህ በመሰለ ነገሮችን ሳያያዙ ምክንያታቸውን በሳቢያ ብቻ ጠቀላሎ ማሸግ እና አስታግሻለሁ የሚለው ነገር ለመንግስት የሚበጅ አይደለም።
ለኢትዮጵያ ህዝብ የሰላም ዋስትና የሚሰጥ አይደለም። በዚህ ዙሪያ ቀጣይ እርምጃዎች ሊወሰዱ ይገባል። አሁን እኮ በዬቦታው ቀዳዳው እዬበዛ ነው። ለነገሩ ስንቱ ተወትፎ ይዘለቃል?
ለውጥ ያመጡት የኦሮሞ እና የአማራ ንቅናቄዎች ናቸው፤ በዚህ ውስጥ ሠራዊቱ የለበትም። የሠራዊቱ ድርሻ አለመኖር በለውጡ ውስጥ የሥነ - ልቦና ጫና ይፈጥራል ብዬም አስባለሁኝ። ልክ ዛርማ እንደተፈጠረው ማለት ነው፤ ከዚህ ጋር በተያዬዘ ፋቲክ ካስፈሪነት ወደ ቤተሰባዊነቱን የሚያጠነክሩ ተግባር አልተከወነም። ሠራዊቱን በሚመለከት ምንም የተከወነ ነገር የለም።
ሚዲያዎችም የዕውቅ ሰዎችን ፎቶ እና ኑሮ ከመዘገብ ውጪ ሌላ ተግባር የላቸውም። ለእኔ የሚታዬኝ የአብይ መንፈስ ብቻውን መለመላውን እንደ ቆመ ለምለም የገነት ዛፍ ነው።
ቅን የሆነ አጋዢ፤ ረዳት ፈጽሞ አላገኘም። የማይቀና ሊሂቅም ለማግኘት ዳገት የሆነበት ይመስላል። እያንዳንዱ ተደምሪአለሁ ሲል ከእኔ ምን ይጠበቃል በሚለው ላይ ገና አልጀመረበትም። እንዲያውም ህውከትን ውስጥ ለውስጥ በማደራጀት ከመፍቻነት ችግር ፈጣሪነት ነው እዬታዬ ያለው፤ በውነቱ የሠራዊቱ መኮንን መሪዎች ራሳቸው ሊጠዬቁ ይገባል። ሊገመገሙ ይገባል። ህዝቡ ለፋቲክ ያለው አመለካከት አልተለወጠም። አልተሰራበትማ። እንዴትስ ይለወጥ?
የቆሞስ ኢንጂነር ስመኘው በቀለ አሟሟት እና የቀበር ሥርዕት እገዳ፤ የሰኔ 16 የኩዴታ ሙከራ እና የውጤት ዕድምታ፤ የ1000ዎች አዲስ አበቤዎች አፈሳ እና አበሳ፤ የትናንት የቡራዩ ጭፍጨፋ እና ያን የተቃወሙ ንጹሃን አስፓልት ላይ መረሸን ፍርሃትን ቢያነግስ እንጂ መረጋጋትን ሊፈጥር አይችልም። ፋቲክንም ወገኔ ብሎ፤ ፋቲክን የእኔ ብሎ፤ ፋቲክን ቤተሰቤ ብሎ ለመቀበል የሚያስችል አይደለም። መሃል ላይ የተቋረጠ ነገር አለ። ክፈተቱ ብዙ ነው።
ሚሊዮኖች ተደመሩ እና ለሚደመሩት ሥነ ምግባር ራሱ የተሰናዳ ሰሚናር እንኳን የለም። በምን ያህል መጠን እና ልክ የመደመርን ፍልስፍና ለህሊና እጣቦሽ ለማዋል መሰናዶው አልታዬም። ቃሉ ሳይፈስ ውስጥ መሆን የሚችለው ተከታታይ ተግባር በተቋም ደረጃ ሲከወንበት ነው።
ሌላው በአቶ ደመቀ መኮነን ዙሪያ የነበረው ራስን የማግለል ሁኔታ እኔ ብዙ ጽፌበታለሁኝ። ተሽብልሎ ሊታይ የማይጋበው ጉዳይ ስለነበር። ትናንት ታዬ የሚባለው ነገርም ግነቱን ዝቅ አድርጌ አንዱ በጥፊ ቢመታቸውስ? ክብርን ማውረድ ነው የሚፈለገው። ሥልጣን ማስለቀቅ ካልተቻለ።
ያ ሁሉ የልዩ ሃይል መሳሪያ ፈቶም ቢገባ እንኳን አንድን ነፍስ ሲጥ ለማድረግ ምን ይሳነዋል? የሚበጀው የፎቶ ግርሻ ሳይሆን የተግባር ቁርጠኝነት ነው።
እኔ እንደ ሥርጉተ ለጠ/ ሚር አብይ አህመድ ካቢኔ ኮነሬል ጎሹ ወልዴ በአማካሪነት ቢመደቡ ብልህነታቸው፤ ቅንነታቸው፤ ታማኝነታቸው፤ ተመክሯቸው ዘመን አይተካቸውም። ለኢትዮጵያ እኒህ የምርጥ ምርጥ ዕንቁ ዜጋ አሁኑኑ ያስፈልጓታል። እኔ ከልጅነት ጀምሮ አብሮ አደጋቸው ስለሳቸው እያስጠኑኝ ነው ያሳደጉኝ።
የኢትዮጵያ መሪ ብዬ እንድቀበላቸው ተኮትኩቼ ነው ያደግኩት። ታሪካቸውን ሳጠናው ድርብ ጭንቅላት ከሚባሉት ወገን ሆነው ነው ያገኘሁዋቸው። ለሁላችንም እኩል ናቸው። አብዛኛው ደግሞ ይስማማባቸዋል። ለዚህ ላልተረጋጋው የኢትዮጵያ ፓለቲካ ባላ እና ወጋጋራ ሆነው ይህን ለውጥ ከግቡ ያደርሱታል ብዬ አስባለሁኝ። መሸጋጋሪያ ድልድዩ ኮ/ ጎሹ ወልዴ ቅናዊ እሳቤ መሆኑን አምንበታለሁኝ። ሰሚ ከተገኜ።
ከሁሉ በላይ የሥልጣን ሱሰኛ አይደሉም፤ ይህ ሁሉ ሴራ ያው አራት እግር ፍለጋ ነው። ኮ/ ጎሹ ወልዴ ግን ያደራጁትን ፓርቲ መድህን ራሱ በፈቃዳቸው ሲለቁ የተኳቸው ወጣት ሁለት ረዳት ፕሮፌሰሮች መሪዎች ስብዕናቸው ዕጹብ ነበር። አንድ ሁለት ጊዜ አግኝቻቸው ነበር። ይህ ያሳዬኝ በልጅነት ያጠነኋዋቸው ኮ/ ጎሹ ወልዴ ስብዕና ሰውን በመፍጠር፤ ሰብዕናን በመቅረጽ ረገድ ልዩ ክህሎትም እንዳላቸው ነበር የተረዳሁት። በዛ ላይ ለአብይ ሌጋሲ ቅርበት ፍጹም ድንግል ናቸው።
ቂመኛ አይደሉም። ቁርሾኛ አይደሉም። በምዕራባውያን ዘንድም እጅግ የተከበሩ ናቸው። ለኢትዮጵያ ታቦት የመፍትሄ ቁልፍ ናቸው።
ሌላው ባለቤት አልቦሽ ለሆነው የህዝብ መፈናቀል በሚመለከትም በማህበራዊ ኑሮ፤ በፖለቲካ ጥልቅ አስተሳሰብ ያላቸው እዛው ያሉት ዶር ካሳ ከበደ ተመክሯቸውን የሚያጋሩበት ሁኔታ ቢፈጠር ለውጡ ከተቃጣባት ሁለገብ አደጋ ይድናል የሚል ዕሳቤ አለኝ።
ይህ ለውጥ ሰኔ 16፤ ሐምሌ 19፤ ከስሜን አሜሪካ መልስ ታፍኖ የቀረው የመንፈስ ንጥቄያ ወይንም የመንፈስ ኩዴታ አመክንዮ፤ የጅጅጋው ቀወስ፤ ከአዋሳ መልስ ፈተናዎቹ ቢገለጡም ባይገለጡም፤ ቢቃለሉም ቢጣጣሉም የኢትዮጵያ መንግሥት አደጋ ውስጥ እንዳለ እዬታዬ ነው። ሌላው የተቀበረ ፈንጅ ጋንቤላ እና አፋር ላይም አለ።
በሁለቱም ክልሎች ውጭ ከተመለሱት የፖለቲካ መሪዎች እና አክቲቢስቶች ጋር ተገናኝቶ የሱማሌ ችግር በተፈታበት መልክ የአመራር ለውጥ ካልተከወነ የተማቀ አዬር፤ የተቀበረ ፈንጅ አለበት። ጋንቤላ የታሰረበት ዕንቁ ሊሂቅም አሉ እሳቸውም ካለምንም ቅድመ ሁኔታ መፈታት ይኖርባቸዋል።
ስለዚህ በሁሉም ዘርፍ ቆፍጠን ያለ ጠንከር ያለ አመራር ይጠይቅ ይመስለኛል። አልታወቀበትም ዴሞክራሲ፤ ነፃነት የሚባለው ነገር እንዲሁ ፈሶ እንዲቀር ነው የሚታዬው ህግ አልቦሽነት። በሁሉም ቦታ ሥርዓተ አልበኝነት ነው የሚታዬው። አንድ የሚሊተሪ አካል ከነ ትጥቁ ቤተ - መንግሥት ድረስ መሄድ? ምን ሲባል ታሰበ? ምን ሲባልስ ታቀደ? ከባድ ነው።
ሌላው ኦነግን በሚመለከት ዶር አብይ አህመድ አቃለው ተመልክተውታል። አዬ የሳቸው ነገር? መቼም የአገር መሪ ሆኖ ይህን ያህል በነገሮች አለመደነቅ፤ በሚገጥሙ ነገሮች አለመብሰልሰል መቼም መታደል ነው። አሁን አሁን ሲዊዞችን እዬመሰሉኝ ነው። ሲዊዞች እንዲህ ናቸው። የሚደነቁበት፤ የሚገረሙበት ነገር የለም። ብቻ የዶር አብዩን አርገታቸውን፤ ስክነታቸውን፤ ትእግስታቸውን፤ ቻይነታቸው፤ ቀናነታቸውን የሚጠቀሙበትን ለስላሳ ቃላት እጅግ አድርጌ እውደዋለሁኝ።
ግን ለግራ ፖለቲካ አራማጆች ሴራ አይሆንም። አሁን እኮ አቶ ዳውድ ኢብሳ ልክ እንዳ ኬኒያው መንግሥት መሪ ነኝ እያሉ ነው። በመሪ ደረጃ እዩኝ እያሉ ነው። በመሪ ደረጃ እንደራደር እያሉ ነው? ማንን ተማምነው? ማን በሰተጀርባ አለላቸው?
ድርድሩ የሁለት አገሮች የሚያደርጉት እንጂ በአንድ አገር ውስጥ እንደ አንድ የተፎካካሪ ፓርቲ የሚታይ አይደለም። ልክ እንደ ደቡብ ሱዳን እና ሰሜን ሱዳን ዓይነት ነው ባይ ናቸው። አደጋው ደግሞ የኢትዮጵያ ብቻ አይደለም፡ OMN ኬኒያ ላይ ጣቢያው በስዋልህኛ፤ በሱማልኛ እና በኦሮምኛ ቋንቋ ነው መጀመር የተተለመው፤ ይህም ምክንያታዊ ነው።
አቶ ጃዋር ኬኒያ በነበርኩበት ጊዜ ኬኒያዎች ምሩን ብለው አሉን ሲል አዳምጨዋለሁኝ። በራሱ በኢትዮጵያ መሬት ላይ ኢትዮጵያን የማፈረስ ይፋዊ እንቅስቃሴ እያለ እንደዛ አቃሎ ማዬት የሚገባ አይመስለኝም። ጫካ ቢገቡስ አቶ ዳውድ ኢብሳ? ከእጅ ቢያመልጡስ? አያዋጣውም እያሉት ነው መንግሥታቸውን አቶ ዳውድ ኢብሳ። ከጅምሩም የድርድሩ የእርምጃ አወሳሰዱ ጥብብ መጉደሉ ብቻ ሳይሆን የሚታዬኝ ሌላም ሸንቁር እንዳለበት ነው።
አገር በተመለደው ሁኔታ የሚቀጥለው ህግ ሲከበር ብቻ ነው። ህግ ሲጣስ በተለመደው መምራትም፤ ማስተዳደርም ያቅታል። ሲከር ይበጠሳል ሲሞላም ይፈሳል። አሁን ያለው ጭፍጫፊ ነገር ነው። ዋናው ግንዱ አመጽ ከቀጠለ ግን መከራው እጅግ ሰፊ ነው። ዶሮ ከእንቁላል ነው የሚፈጠረው።
የዛሬው ቸለልተኝነት፤ የዛሬው አቅሎ ማዬት ከእጅ አያመልጥም መባሉ ሰፊ አደጋ ነው ያለው። ቀን የማይሰጠው ነገር ኮ/ ጎሹ ወልዴን አገር ማስገባት እና የምክር አገልግሎት ተግባር እንዲጀመሩ መደረግ በጣም እጅግ አስፈላጊው ጉዳይ ነው። ይህን ደፋር እርምጃ መውሰድ ካልተቻለ መጪው ጊዜ ይከብዳል። በዬ4 ዓመቱ ደግሞ ከበድ ያሉ ነገሮች ይከሰታሉ። ከማርቆስ ወደ ሉቋስ ሽግግሩም አለ።
ለእኔ ትናንት የአመጽ መባቻ ነበር። ይህ የአመጽ መባቻ ለመሰንበቻ እንዳይሆን ፈጽሞ እንዳይደገም ለማሰናባቻ ለማድረግ ጠንካራ አመራር ከቁርጠኛ ውሳኔ ጋር ይጠይቃል። ነገ የዩንቨርስቲ ተማሪዎች፤ የመንግሥት ሠራተኞች ይህን የሚሊተሪ አመጽ ሊቀላለቀሉት ይችላሉ።
በዛ ላይ የማህበራዊ ሚዲያ ሞገድ አለ። ማህበራዊ ሚዲያ እኮ መንግሥት ነኝ ከሚለው በላይ አቅምም ጉልበት አለው። አሁን እኮ ሉላዊ የመንግሥት አካላት ሳይቀር የቢሮ ሥራ እርግፍ ብሎ ቀርቶ ጽ/ ቤቱ ማህበራዊ ሚዲያ ሆኗል።
እኔ ባይገርማችሁ የጥቅምቱ የጀርመን ጉዞ ሁሉ ያሳስበኛል። እዛው ተሁኖ ይህ ከተከሰተ እንደ ማለት … የትናንቱ እኮ ትልቁ መንፈስ የመነቃነቅ ሁኔታ የታዬበት ነው። ለራሱ ለኢህአዴግ እንደ ግንባር በአውራ ፓርቲነት ለመቀጠልም ላራባ ነው …
የመረጋጋት ብሄራዊ ተስፋ ከሰኔ 16/ ከሐምሌ 19 ጀምሮ በስጋት ተተክቷል። እኔ ያዬሁት ህልምም አለ ባዶ ወንበር ነው ያዬሁት። ሰማይም እንጅባራ ላይ መሬትም ከመቀሌ እሰከ ደቡብ የንጠት ምልክት ታይቷል። በአንድ በኩል ፊትን ወደ ፈጣሪ መልሶ፤ በሌላ በኩል ግን አካባቢንም ማጥናት የሚያስፈልግ ይመስለኛል።
አንድ ያልታወቀ ሃይል አለ። አንድ ሽብር ፈጣሪ ሃይል አለ። ይህን ሥራዬ ብሎ የኢትዮጵያ መንግሥት መከታተል አለበት። ሥሩን አግኝቶ በቁጥጥር ሥር መዋል አለበት፤ ሌላም ለጋ የሆነ የሴራ መረብም አለ ይህም ሌላው መከራ ነው። ምን አልባት የቤት ውስጥ የመቀመጥ አድማም ሊያስተባባር ይችላል፤ እንደገና ደግሞ ከኤርትራም ወደ ኢትዮጵያ በገፍ የሚገቡትም ቢሆኑ ፍተሻ ያሰፈልገዋል። ዝንቅንቅ ቅይጥይጥ ያለ ሁኔታ ነው ያለው።
በመጨረሻ የምለው በአብይ ሌጋሲ ዝርግ የፖለቲካ ትሁት አያያዝ የ50 ዓመቱን የሴራ ግንብ ለመናድ አይቻለውም። የአብይ ሌጋሲ ሌላ ስልት እና ዘይቤ መከተል ያለበት ይመስለኛል። ይህ የለውጥ ተስፋ ለማክሰል ቅኖች ጥቂት ቢሆኑ ነው ይህን ያህል የሺዎች መፈናቀል፤ እሮሮ፤ ስጋት፤ ጭፍጨፋ፤ የሥራ መጓተት እዬታዬ ያለው።
ቸለልታ ዋጋ ሲያስከፍል የተፈጠሩበትን ቀን አስረግሞ ነው!
የኔዎቹ ኑሩልኝ።
መሸቢያ ጊዜ።
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ