ጠ/ ሚር ዶር አብይ ለልዩ ሃይሉ ትህትና መቀለባቸውን እደግፈዋለሁ።

መጋጋል
„እግዚአብሄር የእውነት ዳኛ ነው፤
ሃይለኛም ታጋሽም ነው። ሁልጊዜ አይቆጣም“
ከሥርጉተ© ሥላሴ
 13.10.2018
ከጭምቷ ሲዊዘርላንድ።



በሰሞናቱ የልዩ ሃይል አመጥ ጉዳይ የሁለገብ ሊቀ ሊቃውነቱ ሻለቃ ዳዊት የሰጡትን ቃለ ምልልስ አዳመጥኩት። ያው ሙያዊ ነው። እሳቸው ሉላዊ ዕውቀትም፤ ልዩ ተመክሮም ያላቸው ሊሂቅ እጬጌም ናቸው። በሌላ በኩል መጀመሪያ ላይ ከምንም ያልቆጠሩት ሁሉ አሁን ውይይቱ ሦስት ቀን ነበር ሲባል ማጋጋሉን ተያይዘውታል።

መጀመሪያ ላይ ነው ጠረኑ ትክክል አለመሆኑን በርቀት ማዬት፤ ጠንከር ያለ ማሳሰቢያ ለመንግስት መስጠት። ቀደም ብሎ ጉዳዩን ማጥናት፤ መተንተን እና መረጃውን ከተለያዬ አቅጣጫ የመገምገም ምህንድስና ሊደረግበት ነበር የሚጋባው።

ቀድሞ ነገር እንደዚህ ያለ ነገር ሲደመጥም ወዲያው ማብራሪያ መስጠትም የተገባ አይደለም። ችኮላ አያስፈልገውም። ተደሞ ያስፈልገዋል። ርጋታ እና ስክነትም ይጠይቃል። አሳድሮ አገላብጦ አይቶ ከስሜት ጋር ሳይስጠጉ፤ በራስ ፍላጎት ሳይቸነክሩ የጭብጡን ማንነት ብቻ በራሱ ማንነት ራሱን አስችሎ መመርመር ነበር የሚገባው።

የሆነ ሆኖ እኔ አስተያዬቴን ዛሬ ልሰጥ የፈልግኩበት ምክንያት ሻለቃ ዳዊት ወ/ጊዮወርጊስ ዕይታ ጠ/ ሚር አብይ አህመድ የወሰዱት እርምጃ ትክክል አይደለም የሚሉትን ነው። እሳቸው ዘመን ጠገብ ባለሙያ ስለሆኑ እሳቸውን አሻቅቤ መተቸት አልችልም። ክህሎቱም ተመክሮውም ብልጹግ ነው በሲቢሉም ሆነ በወታደራዊ። መሬት ላይም ሰርተውበታል። ነገር ግን እኔ እንደ ሰው ጠ/ ሚር አብይ አህመድ የወሰዱት እርምጃ ትክክል ነው ብዬ ነው እማስበው

ጠ/ ሚር አብይ አህመድ እያስተማሩ ያሉት የሃሳብ አቅም ከባዱን ተራራ ንዶ፤ ደልድሎ፤ ሸካራውን ለግቶ እና ሰባራ ሰንጣራውን ጠርቦ አስፓልት ያደርጋል ባይ ናቸው። እሳቸውን ለማግኘት የሚፈቅድ ሁሉ ቢያገኛቸው ይፈቅዳሉ። እንዲያውም ጥሎባቸው ነው እንጂ ካለ አጃቢ ቢሄዱ ሁሉ ይሻሉ። 

ቤተሰብዕዊ ሰብዕና ነው ያላቸው የተለዩ መሪ ናቸው። ይህን ከቀደሙት መ/ቤታቸው አብረው የሠሩት ሁሉ የሚናገሩት ወላዊ ዕድምታ ነው። ሰብዕናቸው አብሯቸው ነው ያለው። የተለወጠው የሃላፊነት መስመሩ ብቻ ነው። ስለሆነም ሰብዕናቸውን እና አዲሱን የሃላፊነት ማንነት በሚያጣጥም መልኩ ነው እየሠሩ ያለው። መነሻው አይጠፋቸውም፤ ያ ህውከት ቀጥሎ በአጭሩ ተጨንግፎ እንዲቀር የሚሻው ሃይል ፍላጎት ስለሆኑ አሳምረው ያውቁታል።

ለተቆጣ፤ ለተበሳጨ፤ ሌላ እሳት እንዲጭር ለሄደ፤ ሌላ ገፊ ሃይል ላለው ባለመሳሪያ እሳቸውም እሳት ለብሰው እሳት ጎርሰው ቢጠብቁ የሚነደውን ነገር ማሰብ ያስፈልጋል። ግዙፉ ችግር ስላልሆነ፤ ስላልተከሰተ ብቻ አሁን በሰላም መጠናቀቁን እንደ ሃላፊነት ዘገምተኝነት አድርጎ መውስድ የተገባ አይደለም።

አብይ አብይ ናቸው፤ መለስም መለስ ናቸው። መንጌ መንጌ ናቸው። ሃይለማርያም ሃይለማርያም ናቸው። በአብይ መንፈስ ውስጥ ራሱ አብይ በነፍሱ ነው ያለው። የህይወቱ መርሆወች አሉት። የድርጅቱ የመንግሥት መርሆዎች የቀደሙም አሉ። 

ሌላም ልዩ ጫና የሀምሌው ዝምታ እደታመቀ አለ። አዲሶች ህዝብ የሻታቸው መንገዶችም አሉ። ይህም ቢሆኑ ነባሩን ሰብዕና እንዲሸጡ እና እንዲለወጡ የሚፈልጉ አይደሉም ዶር አብይ አህመድ። እንዲያውም ይህ እርግጠኛ የሚያደርገኝ ነገር ሲስተጓጎል ነው እኔ አብዩን ፍለጋ ላይ ነኝ የምለው፤ ደፍሬም እንዴህ ያለ መዝረክርክ ማዬት አልሻም የምለውም፤ አልጠብቅምም የምለው።

ዶር አብይ አህመድ እኮ በፍጹም ሁኔታ መንፈሳቸው የተደራጀ ነው። አቅል አላቸው። ነገሮችን ሸፍን ለማድረግ የሚሄዱበትም ሁኔታ አደባቸው ጥልቅ ስለመሆኑ ያሳያል እንጂ እዬዋሸን ነው እንደሚሉት አይደለም። እርግጥ ነው ቀለል አድርጎ ማዬት ዋጋ ያስከፍላል።

በሌላ በኩል ገለጥለጥ ቢያደርጉት ደግሞ ሌላም ስምምነት መጣስ ይሆናል። እኛ የማናውቀው፤ ወደፊትም ልናውቀው የማይፈቅድልን መከራ ተሸከምው ያሉ ሙሴ ናቸው። በህዝብ ዘንድ ሙሉ ተቀባይነት ማግኘታቸው አልተወደደላቸውም።

የሆነ ሆኖ ያ እሳት ለብሶ እሳት ጎርሶ የመጣን የሠራዊት ሃይል አያድርገው እና ሁሉም ሲመለስ ምላጩን ቢስብ ምን ይጠቀሙ ነበር ዶር አብይ አህመድ። የፈሰሰ ያልተፈስ ይሆን ነበር። እንኳንም አላደረገው እንጂ ቢያደርገው ኖሮ የተበሳጨን ሃይል እንዴት እንደዛ አስተናገደ አብይ አልደፈረም ብሎ ታበዬ አንባገነን ሆነ ወዘተ ወዘተ መከራ ነበር። ደርሶ ስላላዬነው ግብረ ምላሹን ፈራጁ፤ ዳኛው በዛበት።

 ሌላው እኔ ብሎ ቢያስበው ተቆጥቶ ሲሄድ፤ ተቆጥቶ የሚቀበለው ወይንስ በትህትና አክብሮ ቁጣውን የሚያዳምጠው ነው የፈቀደው? ሁላችንም ቁጣችን ካራገፍን በኋዋላ ብናስበው ቁጣችን በማንኛውም መስፈርት ትክክል አለመሆኑን እንረዳለን።

 እኔ እናቴ እብዬ የሚደንቅ ሰብዕና ነው ያላት። የፈለገ ሰው ያስከፋት፤ ይቆጣ፤ ሳያስከፋት፤ ሳይቆጣ በነበረው የቀደመ አያያዝ ነው የምታስተናገደው እናም በሁሉም ዘንድ ተወዳጅ ናት።

አሁን እኔ ለደህንነቷ ስል እጅግ አስከፍቻታለሁኝ መንኩሳ እንኳን ለዚህ አበቃሽ አላልኳትም፤  ግን በማናቸውም ጊዜ ድምጤን ብትሰማ ስለምን ጠፋሽ ብላ አትጠይቀኝም፤ ደህንነቴን በትህትና ጠይቃ ሻማ አብርታ አምላኳን ከማመስገን በስተቀር። 

እንዲህ ዓይነት ሰብዕን ዘመኑ ሁሉ ውስጡ ሰላም የሰፈነበት ይሆናል። እናቴ በጣም ውስጧ ሰላም አላት። እምትጸጸትበት ነገር የለባትም። እኔን አስሮ ያሰቃዬኝን በሞቴ አፈር ስሆን ብላ አግብታ መግባ ጥብቅ ወዳጁ ትሆናለች። እኛ እንዲያውም አስጠቂ ነው የምንላት።

የአብዩ ለስላሳ እናታዊ መንፈስ ድብልቅልቅ ሊያደርግ እሳት ለብሶ እሳት ጎርሶ የመጣውን፤ እንዳላወቀ አድርጎ አባብሎ፤ አቆላምጦ፤ ቁጣውን አብርዶ፤ አገርን መታደግ በዘመናችን ያላዬነው እጅግ ድንግል ጥበብ ነው።

ሌላው ቀርቶ ሁሉም ቤተ መንግሥቱን ከለቀቀ በኋዋላ አንድ ጊዜ ሩምታ ቢተኩስ እንኳን እድምታው ከባድ ነበር የሚሆነው። ይደርሳል እኮ ቁጣውም፤ ምርምራውም፤ እርምጃውም። ላለቀ ቀን። ላልጠፋ ትህትና ጥቂት ታግሶ ብዙ ማዳን እኮ የታላቅ መሪ ጥብብ ነው። ጠ/ ሚር አብይ አህመድን ኢትዮጰያ በ100 ዓመትም አታገኛቸውም።

እኔ በዚህ ውስጥ ያዬሁት ጥበብ እሳት ውስጥ ውሃ አፍልቆ እሳቱ ከሚያደርሰው አደጋ መታደግን ነው። ልብ ላላቸው ፍጡራን አብይ እዮራዊ ስጦታ ነው። ቁጣ ምን ያድርጋል? ክፉ ቃልስ ለማን ይጠቅማል? ለዛውም በመሪ ደረጃ። ወጣቶቹ ከበረዱ በሆዋላ ሁሉ ይደርሳል። ዘና እያደረጉ መምራት፤ መቅጠት፤ መቆንጠጥ።  

በዚህ ውስጥ የሚታዬው ዶር አብዩን ለማሳጣት ያለው የተደራጀ ጉዳይን ልብ ማለትም ያስፈልጋል። አብሮ የሚቆመው ቀን አብሮ ሲገነባ ይወላል ሌሊት አይተኛም ሲንድ ያድራል። አብዩ ግን በሰላም ተኝቶ፤ በጤናው ተነስቶ ለቀጣዩ ቀን በሙሉ አቅም ይተጋል። እናቱን በቅንነት ሊያገለግል አሰበ ግን ቅኖች አነሱ። ሴረኞች ራስ እግሩ ሆኑ - በረከቱ።

በሌላ በኩል አስተምህሮቱ እሳቸው ቀጠሉም አልቀጠሉም፤ ከዚህ በሰርክ ከሚቃጣባቸው የሞት አደጋም ተረፉም አልተረፉም ቀጣይ መሪዎችን እያስተማሩ ነው። ራሱ በአጠገባቸው ያሰፈሰፉትን በስውር የሚታገሏቸውን የኢጎ ፈረሰኞችንም እግረ መንገዳቸውንም እያስተማሩ ነው። 

ሌላው ቀርቶ እኔን አታምስግኑኝ እኔን የሚተካኝን አመስግኑ በማለት ከአሜሪካ ታሪክ ጋር እያወደዱ የሚገልጹት አመክንዮ አለ።
አሁን እሳቸው የሚያደርጓቸውን አብነቶች የተከተሉ እንዳሉ አስተውላለሁኝ። ለቡራዩ ምንዱባን ደም ሲለግሱ ሊሂቃንን ተመልክቻለሁኝ። ሌላው ታታሪም ባለቤቱን መድረክ ላይ በተከታታይ ይዞ ሲታደም ተመልክቻለሁኝ። ሌላውም ጋብቻውን ህጋዊ ሲያደርግ። 

ይህ ደግሞ ከብቁ መሪ የሚጠበቅ አንድ የብቃት ልክ ነው። ሮል ሞዴል መሆን። እሺ ሳይተኩስም ይመለሱ እንበል ወጣቶቹ፤ ትህትና ባይመገቡ ኖሮ ምላጩን እንደሳሉ ቢመለሱ ኖሮ ምን ሊፈጠር ይችል ነበር? መንገድ ላይ ያገኙትን ሁሉ እያጨዱት ድብልቅልቅ ቢያደርጉስ ኖሮ? ይህም አደጋው እጅግ የሰፋ ነበር የሚሆነው። የሚያስከትለውም ጥፋት እንዲሁም።

በሌላ በኩል በህሊና ውስጥ እኔ እንደ ዜጋ አልታይም የማለትም ሥነ - ልቦናዊ ጫናም ይፈጥራል። ዶር አብይ እኮ የአገር መሪ እንጂ የጨበራ ተዝካር አጋፋሪ አይደሉም። የአገር መሪ ማለት ደግሞ ሲያስፈልግ እናት፤ ሲያስፈልግ አባት፤ ሲያስፍለግ መምህር፤ ሲስፈልግ የኔታ፤ ሲያስፈልግ ቀጪ፤ ሲያስፈልግ መካሪ፤ ሲያስፈልግ ደግሞ ቅኔ መሆን ማለት ነው። 

ሁሉንም በጊዜው በሁኔታው ልክ መጥኑ አመዛዝኖ መከወን ማለት ነው መሪነት። የተገናኙት እኮ ጦር ሜዳ ላይ አይደለም ቤተ መንግሥታቸው ውስጥ ነው። ቦታውም፤ ሁኔታውም፤ ጊዜውም፤ ተጨባጩም ወሳኝ ነው። ሰው ማለት አጋጣሚዎችን በማስተዋል መግራት መቻል ማለት ነው።

ወደ አንተ የሚገሰገስን እባብ ዞር ብላህ ታሳለፈዋለህ እንጂ ሄደህ አትጠመጠምበትም። ለዚህ ነው አቦ/ እሞ „የሚያልፍ ዝናብ አይምታህ“ የሚሉት። ሙሴነት ስልት ጥበብ ያስፈልገዋል። ለዛውም የኢትዮጵያ ፖለቲካ ሴራ እና ምቀኝነት የከተመበት ነው። ሰነፍ ቢሆኑ ይህ ሁሉ መከራ ባልደረሰ ነበር። ኢትዮጵያም እኛም ባንታደል ነው ይህን ሁሉ አሳር የሚያዩት።

እሳቸውማ በ20 ዓመትም የማናገኘውን ደስታ እስኪበቃን ድረስ በ100 ቀናት ወስጥ አስከስክሰውናል። ኤርትራን ራሷን ታድገዋታል፤ ለኤርትራ ዶር አብይ አህመድ የምሥራች ብሄራዊ ቀኗ ናቸው - ቅንነቱን ከሸመተች። አደራውን ቅርጥም አድርጋ ከባለጊዜ ጋር ካልበላችስ። ግን እትጌ ኤርትራ የአዳራ አያያዟ እንዴት ነው? አደራን ታወጣለችን?

 ባለፈው ጊዜ የጀርመን ልዑክ ወደ ኤርትራ አቅንተው ነበር አሁን የጣሊያኑ እዛ ናቸው፤ በሌላ በኩል የተባባሩት መንግሥታትንም በቅርብ ቀናት ልትቀላቀል መሆኗ ተደምጧል፤ ሽልማትም አግኝታለች እትጌ ኤርትራ።  አሮን በትር ናቸው ለእኔ ዶር አብይ አህመድ ማለት። የረገጡት ሁሉ ለምለም ነው። ግን የሴራ መዥገር ነው አግቶ እዬተከታተለ እያደረቀ ያለው። በሙሉ አቅማቸው ልክም እንዳይነቀሳቀሱ የሐምሌው ዝምታ ተጭኗቸዋል።

የራስ ተሰማ ናደው ሴራ ሌጋሲ ነው እዬፈተናቸው ያለውም አቅማቸው ብቃታቸው የማይደፈር እና የማይሰፈር በመሆኑ ነው። የሆነው ሁሉ ከእግዚአብሄር ስለሆነ አንድዬ ከተወረወረው ቀስት ሁሉ ይታደጋቸዋል ብዬ አስባለሁኝ። 

ሥጦታነታቸው የሰማይ የእዮር ነው ለእኔ። ቅብዕውም እንዲሁ። አሁን እሳቸውን አጥፍቶ ቅብዕ እንጠቃለሁ የሚለውም ሁሉ ልክ እንደ ራስ ተሰማ ናደው አይሰነብትባትም፤ ይቀዘፋል። ራስ ተሰማ ናደው አሴሩ ግን አልሰነበቱባትም ምድሪቱን።
 
በዘመነ ደረግ የእነ ጄኒራል ታሪኩ የግፍ ህልፈት እኮ በመስል ሁኔታ ነው የተፈጸመው። አብራጅ፤ አቀዝቃዥ የመሪነት ጥበብ ጠፍቶ። ለዛውም ያነ ጦር ግንባር ላይ ነው። የሁለት ልጆች እናታቸው „ቋሳ“ በሚል ዕርስ ይመስለኛል ካልተሳሳትኩኝ ታሪኩን ጽፈውት አንብቤዋለሁኝ። 

ከዛም በኋዋላ ነው የኢትዮጵያ ሠራዊት ህሊናው ትጥቁን ፈቶ መንፈሱን በደርግ ላይ ያሸፈተው። ጥንቃቄ ያስፈልገው ነበር ለሁኔታው ከግብታዊነት ይልቅ እርጋታን ስክነትን ይጠይቅ ነበር። „ከአያያዝ ይቀደዳል ከአነጋገር ይፈረዳል“ እንዲሉ።

ይደርሰል እኮ እርምጃው፤ ቅጣቱ፤ ክትትሉ፤ ምርመራው። ለነገሩ ተባባሪዎችን የላይኞች መኮነኖች ቁንጮዎቹ አሁን አይነኩም የታችኛው ነው መከራውን የሚያዬው። 

ይህም ሆኖ እንደዛም አድርገው በሥርዓት ትንሽም ወታደራዊ ቅጣቱን አብረው ራሳቸው እንዳጠፉ ሁሉ አብረው ተቀጥተው ፈገግታቸውንም በገፍ ለግሰው፤ በትህትና የሳቢያ ብሶታቸውን አዳምጠው፤ ቤተ መንግሥቱም የእናንተ ነው፤ ነገ አንዳችሁ ትመጡበታላችሁ ብለው ቤት ለእንግዳ ብለው እንደ እናት የተቆጣን ልጅ በአክብሮት መሸኘት የተገባ ነው ባይ ነኝ እኔ። 

ትህትና ግትርነትን ይገራል፤ አክብሮት ማንአህሎኝነትን ይጠርባል፤ ደግነት ደግሞ ጭካኔን ይሞርዳል። ስክነት የቁጣ መንፈስን ይገራል። ሴራ እኮ ነው አሁን አድብ ነስቶት እዬተቁነጠነጠ አገር እንዲፈታ እያደረገ ያለው።

ወጣቶቹም ልጆቻቸው እንደ ገናም ባለደረቦቻቸውም ናቸው። ዶር አብይ አህመድ ለሌሎች ያደረጉትን ነገር ማደረግ ግድ ይላቸዋል። ወታደር ቢሆንም ሰዎች ናቸው። ትህትና ይርባቸዋል። ለሌላው የተሰጠው ፍቅር ይናፍቃቸዋል። ቁጣቸውን የሚያበርድ መሪን ይመኛሉ።

ሥርዓት ጥሰሀ መጥተሃል እና እኔም ሥርዓት መጣስህን ልማርበት ማለት ነበር ሳያነጋግሯቸው ቢመልሳቸው ኖሮ። በወጣቶቹ ጀርባ ደግሞ መከራኛዎቹ የኢትዮጵያ እናቶችም አሉ። የወጣቶቹ ፍቅረኞችም ይኖራሉ። እንዲያውም ወታደር የፍቅር ጌታ ነው ለቤተሰቡ። ለትዳሩ ክብር ወደር አያበጅለትም ለሠራዊቱ አባላት በቀደመው ጊዜ የአሁነን አላውቅም።

ዶር አብይ አህመድ ልቅጣ ቢሉ ሳያነጋግሯቸው ቢመለሱ የሚከፉ እናቶች፤ የሚከፉ እጮኛዎችም፤ ተስፋ የሚቆርጡ ሚስቶችም ሊኖሩ ይችላሉ። እኔም እንደ ሰው በውነቱ ይከፋኛል። ሰውኛ ጠረን እፈልጋለሁኝ ከአንድ መሪ ከአንድ ሙሴ። ለዚህ ነው መሽቶ ሲነጋ የአብዩን ዜና እማስሰው። ሌሊት ሁሉ ተነስቼ ቼክ አደርጋለሁኝ። ልቤ ራሱ ይመተብኛል። 

ከዚህ ቀደም እኮ ተከድነው የቀሩ ሙከራዎች ነበሩ እሳቸውን ለማስወገድ። እንዲያውም እሳቸው ሁልጊዜም ሊያጠቋቸው ካሰቡት ጋር አቅልለው አይተው አሁን አብረው በቅንነት በትህትና አብረው እዬሠሩ ያሉ ይመስለኛል። እንጂ ታማኝነት እማ ሰኔ 16 እኮ አከተመ። 

ባለቅኔው መሪ ዶር አብይ አህመድ ብዙ ነገር አይጣፋቸውም፤ ያውቃሉ። ብልህ ናቸው። ማስተዋላቸው ወደር የለሽ ነው። በማፈርስ ላይ የሚገነባ ዴሞክራሲ እርባና እንደሌለው ያውቃሉ። ማቆሚያም እንደሌለው ጠንቅቀው ይረዳሉ። 

አሁን ችግሩ የሳቸውን መሻት የሚረዳቸው አለማግኘታቸው ነው። አሁን በዚህ አያያዝ አስቸኳይ ጊዜ ቢታወጅ ጎሽ ነው እኔ እምለው። ምክንያቱም መብቱን ያላወቀ ግዴታውን ሊቀማ ይገባዋል እና።

ክብር የሰጠኸው ክብሩን መሬት ለመሬት ሲጎትተው ይገኛል፤ ስለሆነም መከበሩን ያለወቀበት ይረሳል። አሁን እኔ ሺህ ሚሊዮን ጊዜ ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ ቢሉ አቶ በቀለ ገርባ ከልቤ አይጠጉም። ቁስለቴን እማውቀው እኔ ብቻ ነኝ እና። 

ስለዚህ ወጣቶቹን አክብሮ የሸኘውን መንፈስ አክብሮ መነሳት የእያንዳንዱ የሠራዊቱ አባል የህሊና ኪዳን ሊሆን ይገባል።
ይቅርታ መጠያቃቸውን አዳምጫለሁኝ። ያ ፌክ ነው፤ በድርጅታዊ ሥራ የተፈጸመ ነው። 

ይልቅ ተሳታፊዎችም ሆኑ ውጭ ያሉት የሠራዊት አባላት ህሊና ካላቸው ይህን የአክብሮት አያያዝ ያሰተዋሉ ልብ ያላቸው የሠራዊቱ አባላት አካላት፤ ከፍተኛ መኮነንኖች እኔም በዚህ ክብር ውስጥ አለሁኝ ብለው ማሰብ ይኖርባቸዋል። አብይ ማለት የእኔም ነው፤ ላግዛው፤ ልረዳው የምችለውን ሁሉ ነገር ላደርግለት ይገባል ብሎ ከራስ ጋር መክሮ የአብይን ቅን መንፈስ ለማስቀጠል መትጋት ይጠበቅባቸዋል። 

ዶር አብዩ የዛሬ ሰው፤ ዶር አብዩ ዕለታዊ ሰው፤ ዶር አብዩ ለራሱ ስሜት ብቻ የቆሙ አይደለም የልጅ ልጅ እጣውን፤ ትውልድን ያሰበ ሸልማት ነው። ቢታወቅበት። ስለሆነም የሰራዊቱ አባላት / አካላት የነገን የልጆቻቸውን፤ የልጅ ልጆቻቸውን ህይወት ዛሬ ለማደራጀት ከተነሱት መሪያቸው ጎን መሰለፍ ይጠብቅባቸዋል።

ክብርን ፍቅርን ሰጥተው ማደመጣቸው፤ ዶር አብይ አህመድ የሠሩት እጹብ ድንቅ ተግባር ነው። የኢትዮጵያ ሠራዊት አባላትም የሰው ልጅ ናቸው፤ እንደ ሰው ርህርህና፤ መደመጥን፤ መቀረብን፤ መከበርን ይናፍቃቸዋል። ስለዚህ ይህን አብዩ ሰጥቷቸዋል። ከሚሰሙት ከሚያዳምጡት በላይ አብይ ማለትን አዬት - ተረጎሙት - አጣጣሙት። አጣመው የላኳቸውንም ልብ ካላቸው ይቀጡበታል።

ይህ ታላቅ የዘመን ልዩ መክሊት ነው። እያንዳንዱ የሰራዊቱ አባላት በግልም በወልም ይህን መሰል የሙሴን ልዩ አትኩሮት ሽልማቱን እንደሜዳልያ አይተው ለበጥባጮች፤ ለአዋኪዎች፤ ለሰላም ነሺዎች ስንቅ ሳይሆኑ ራሳቸውን ገዝተው፤ ራሳቸውን ተቆጣጥረው፤ ራሳቸውን ገርተው ከአብይ መንፈስ ጎን መቆም ይኖርባቸዋል።

ነገም ከእነሱ ውስጥ በጥረቱ መሪ ሊሆን የሚችል ይኖራል። ጠ/ ሚር አብይ አህመድ የማይጸጽታቸውን ነገር አድርገዋል ብዬ እኔ አምናለሁኝ። ሥልጣንም ህይወትም ያልፋል ትህትና እና ደግነት ግን ትውልድን በተግባር በቋሚነት ይቀርፃል። የሚገርመው ይህን እያዩ የማይማሩ ሊሂቃን ናቸው።

ዶር አብይ አህመድም ያስተማሯቸው ትህትናን ነው፤ እኔ ደግሞ የዶር አብይ አህመድ ሰውኛ ጠረናቸው ክፍሌ ነው። እኔ ቁጡ አለቃ አልወድም። እኔ ክልፍል አለቃ አልወድም። እኔ ቁንጥንጥ አለቃ ግጥሜ አይደለም፤ እኔ እርጋታ የነሳው አለቃ አልወድም፤ እኔ የታበዬ አለቃ አልወድም። እግዚአብሄር ይመስገን ከአንድ ወቅት በሰተቀር የአለቃ ፈተና ገጥሞኝ አያውቅም።

አገር ሊመሩ የሚችሉ ብቆዎች ጋር ነበር ዕድል የሰጠኝ እና ብዙ የእውቀት ነገር ገብይቸበታለሁኝ። መኖሬን ያሳማረው እኔን ለመቅረጽ አለቆቼ የደከሙበት፤ ያፈሰሱት ጊዜ እና መንፈስ ልዩ ነው የነበረው። እኔ አሁም ሥራ ዓለም ይሁን፤ ስብሰባ ይሁን፤ ሃላፊነት ይሁን በሙያዬ በአደራጅነቴ የማፍርበት አንዳችም ነገር የለብኝም እድሜ ለእነ ጓድ ገብረመድህን በረጋ።

ሙያየን እንድናፍቀው ብቻ ሳይሆን በማይቻል ሁኔታ ራሴን አደራጅቼ ኑሮዬን አሳምሬው፤ ወድጄው እንደኖር አድርገውኛል። አሁን ይህን መሰል ጠረን አገሬ ስላገኘች ደስታኛ ነኝ ካስቀጠሏቸው የኢጎ ፈረሰኞች። እያንዳንዷ ደቂቃ ከአብይ መንፈስ አገር ለሚሠራ ሁሉ ተቋም ነው። ብዙ ያልተገለጡ ያልተጻፉ ነገሮች አሉ። ዕውቀትን በማሻገር እራሱ ቀደሚው ሙሴ ናቸው።

ብዙ ስለለመድን አይጉደልብን ስለምንል ብቻ ነው ሙግት የሚበዛው እንጂ አብዩ ነፍሱ የጽድቅ ናት።  እርግጥ ነው እንደ አጀማመሩ ለመቀጠል ፈተና ውስጥ መሆኑን እኔ በሚገባ አውቃለሁኝ። ቅኖቹ አነሱ።

ያልደረሰ ያላዬነው መከራ ናፍቆን ካልሆነ በስተቀር ዶር አብይ አህመድ ያደረጉት ጥበብ ጠገብ ቅኔ ነው። የተቀናቃኝ መንፈሶችንም ቅስም በድርቡ እንኩት ያደረገ ልቅና ነው። አንድ ሙሴ ማለት የወታደር አዛዥ ጄኒራል ማለት አይደለም። ከዛ ሳይደርሱ በሜጫ ከሚሉት የተለዩ ስለመሆናቸውን መሬት ላይ እያስመሰከሩ ነው።

ባልታቀደ ሁኔታ ማዕበል በሃይለኛ ወጀብ ታግዞ መርከቧን ሊያስምጥ ሲል ጥሩ ካፒቴን ሆነው የጥቅምትን ግርግር እሻገረውናል። ነገ ለራሱ ፈጣሪው አለው። ቅብዕውም እዬራዊ ነው፤ የተቃጣው ሁሉ እዬከሸፈ ነው። አሁን የመንፈስ ባለ ኩዴታዎች ገማናቸው እንዳይገለጥ ቀጣዩ አዲሱ ሰንሰለት በአንገት እንዲጠለቅ የሚሆነው በውጭ ጉዞ ላይ ነው፤ ይህንንም ጥቅምት መጨረሻ ላይ ተረገጡን እምናዬው ይሆናል።

ትዕግስት ካሰቡት የምታደርስ ሰጋር በቅሎ ናት!

የኔዎቹ ኑሩልኝ፤

መሸቢያ ጊዜ።  

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።