ሥርዓት አልበኝነት ክብር ሳይሆን ውርዴትም ውርዴም ነው።

ጨካኝነት ወደ እንሰሳነት የመቀዬር ዋዜማ ነው።
„ከቀና ህግ ወጥተን ሳትነ የክርስቶስ ብርሃን ረድኤቱ
አልተገለጠልንም፤ ክርስቶስም ለኛ አልተወለደልንም።“
መጽሐፈ ጥበብ ምዕራፍ ፭ ቁጥር ፮
ከሥርጉተ©ሥላሴ
29.10.2018
ከጭምቷ ሲዊዘርላንድ።


  •  መቅድም። 

በምንም ሁኔታ ጭካኔ ዓይን ሊሰጠው አይገባም። በምንም መስፈረት አረመኔነትን ዝም ልንለው አይገባም። ወንጀልን ወንጀል ስለመሆኑ ልናወግዘው እንጂ ልንከባከበው ወይንም ግርዶሽ ልንሰራበት አይገባም። 

ሰባዊነት ነው ሰውን 'ሰው' የሚአሰኘው። የሚያደርገውም። ርህርህና ነው ሰው የሚያሰኘው። አዘኔታ ነው ሰው የሚያሰኛው። የሰው ልጅ ከርህርህና፤  ከአዘኔታ ወጥቶ ጭካኔ መሪው ካደረገ ያ ሰው ወደ እንሰሳነት ተለወጧል ማለት ነው። 

ከአዕምሮውም የጎደለ ነገር አለ ማለት ነው። እንደ ሰው ማሰብ ከልተቻለ ወደ እንሰሳነት የመለወጥ መለያነት ነው። 

ሰው መሆን ማለት እኮ ከእንሰሳ ዓለም መለዬት ማለት ነው።
በሌላ በኩል እናት የምትባል ልዩ ፍጥረት አለች። ሁልጊዜ እናት ልጇ ጎልማሳ ሆነ አዛውንት ልጇ ለእሷ ሁልጊዜ እምታዬው ልክ እንደ ህጻን ነው። እናት አብሶ የአላዛሯ ኢትዮጵያ እናት ባላባራ የዘመናት ጦርነት የልጅ ብርንዶ አቅራቢ ናት። መፍትሄ ለሌለው ማናቸውም በትረ ስልጣን ልጇኝ ስትገብር ኖራለች የኢትዮጵያ እናት።
  • እናት

የኢትዮጵያ እናት እንጨት ለቅማ ሽጣ፤ ኩበት ለቅማ ሽጣ፤ እንጀራ ጋግራ ሽጣ፤ በቀን ሰራተኝነት ተቅጣራ ላቧን አንጠፍጥፋ፤ የሰው ፊት ገርፏት ወጥታ ወርዳ፤ የረባ ልብስ ሳይኖራት፤ የረባ የለማ የጣመ ሳትመገብ፤ አንጀቷን አስራ፤ ሙሉ ቀን ስትባትል ውላ ስትባትል አድራ፤ ዓመት ይዞ እስከ አመት በታከተ እድል ፍዳዋን ስትከፈል ኖራ ነው ልጅ አርግዛ ወልዳ እምታሳድገው።

አሳድጋ ተስፋ አድርጋ ደግሞ ቀመኛ መጥቶ ያስርበታል፤ ይገደልባታል፤ አካሉን ያጎድልባታል፤ ያሰድድባታል። ይህ በዬዘመኑ በነበሩ መንግሥታት የታዬ ነው። አገር ደንበር ተደፈረ ሲባል ደግሞ እንባዋን እያዘራች ገመዷን ታጥቃ፤ ኮሶ ቆርጥማ ልጇን አንጀቷ ቁርጥ እያለ ከአገር በላይ የለም ብላ አሳድጋ ለሞት ትልካለች።

ነፃ አውጣለሁ የሚለውም ሆነ የፖለቲካ ድርጅት ነኝ ባዩም ሲመጣ እንዲሁ ጥሬ ቆርጥማ ያሳደገችውን፤ መቼ ደርሶልኝ፤ መቼ ደርሳልኝ ያለቻትን ግብር አዘውትራ ታቀረባለች። ቀን ይዞ ቀን፤ ወራት ይዞ ወራት፤ ዓመት ይዞ ዓመት ይኸው ነው። አሁን የሚገረመው ይህ ደግሞ ረብ አለ ሲባል ህዝቡ ራሱ ወደ እንሰሳ ተቀይሮ ያርዳል፤ ያንጠለጥላል፤ ይሰቅላል፤ ፍርድ ይሰጣል በተራው …
  • ገማናችን ተትረፈረፈ ... 


ነፃነቱም ሲታጣ መከራ፤ ነፃነቱም ሲገኝ መከራ ሆነ። ስለምን ይጸለይ፤ ስለምን አቤት ይባል። እንዴት የሰው ልጅ የሰው ልጅን በዱላ ደብድቦ ይገድላል? እጅግ ያሳፍራል። እጅግም ያሳዝናል። መግደል ጭካኔ አረመኔነት እንሳሳነት ነው። የሚገርመው ተው የሚል አዛውንት መጥፋቱ ነው። ግራጫ የመከነበት ዘመን። እግዚኦ!

እንዴት በዚህ ዘመን በስንት ፍዳ የተማሩ ልጆቹን ራሱ ደብድቦ የራሱን ልጆች ይገድላል? ወደ ዬት ይሆን ጉዞው? ማብቂያውስ የት ላይ ነው? ይሰቀጥጣል። ይመራል። ሃፍረቱም የሁላችን ነው። አንገት መድፋቱም የሁላችንም ነው። መልመድ እስክችል ድረስ ነው ጸጥ ያልኩት። ይህ እንሳሳዊ ዘመን እንዴት ይለመዳል? መቼ ነው የትስ ነው ማቆሚያው?
ለነገሩ ባለፈው ጊዜ አንድ ጹሑፍ ጽፌ ነበር። 

እርእሱን አላስተውሰውም። እንደ አቶ ጀዋር መሃመድ ጨካኝ ሁኑ የሚል ስብከት ከገጣሚ ሄኖክ የሺጥላ አዳምጬ አዝኜ ጽፌ ነበር። 
ሰው አብነት የሚሆነው ለመልካም ነገር እንጂ ለጭካኔ? እንዲህ አይነት ዶክትሪኖች ምላሻቸው ይኸው ነው። 

አዲስ አፍላ ወጣትን ሰው አድርጎ፤ ሩህሩህ አድርጎ፤ ደግ አድርጎ፤ ሰው አክባሪ አድርጎ ማዘጋጀት ሲገባ ክብር ከጭካኔ ይገኛል እና እንድትከበር ጨካኝ ሁን? በአረመኔነት የሚገኝ ዝና እና ክብር እንዲሁም ተቀባይነት በተጨማሪም ቀይ ምንጣፍ በአፍንጫዬ ይውጣ።

ደግነት ሰውነት ነው፤ ለሰማይም ለምድርም የህሊና ጌታ የሚያደርገው። ይህው አሁን ለምርምር የሄዱ ሁለት ቀንበጦች በአገራቸው መሬት ተደብድበው ተገደሉ። አያ ሆይ በሬ ሆይ አዱኛዬ ሆይ በሚለው በሬውን አክብሮ አልቆ በዜማ እያባበለ በመቻቻል ቅላጼ የሚያርሰው ገበሬ ትውፊቱን ትቶ አምሳያውን በራሱ አምሳል የተፈጠረውን በክርስቶስ አምሳል የተፈጠፈረውን ደብድቦ ተገደሉ ይላል ዘገባው። ሞት ነው። ለዛውም መራራ ሞት። ለታሪክ ለትውፊትም ሞት ነው።

https://www.ethiopianregistrar.com/amharic/archives/59028

ምዕራብ ጎጃም ዕጩ ሁለት ዶክተሮች ተደብድበው ተገደሉ

ወደ ቀደመው ምልስት ሲሆን ባለፈውም ባህርዳር አካባቢ ለአማራ ወጣት ልጅአገረዶች ብቻ ተለይቶ 300.00 ብር እዬተሰጣቸው ለናሙና ሲሰራ የነበረ ነገር ነበር ያም ምልክት ነበር። ደብረታቦር ላይ በጨለማው ዘመን ለ ዓይን መዳህኒት ተብሎ በነፃ የታደለ መዳህኒት ብዙ ነፍሰጡር እህቶችን እንዳሰወረደ አውስትራልያ የምትኖር መንኩሲት ጓደኛዬ ነግራኛለች። መነኩሲት ስል ኑራዋን በዛ የደካች ለማለት ነው። 

እንዳ እኔ እንደ ሥርጉተ ከጤና ጋር የተያያዙ ጉዳዮ አማራ መሬት ላይ ጥናት ማድረግ መቆም ያለበት ጉዳይም ነው። አንድ ጊዜ መምህር አቶ አቻምዬለህ ታምሩ ሲናገር እንደ ሰማሁት እሱ ራሱ ያዬውን እረኛ ሙሽራ ገጠር እንደ ጠፋ ነበር የገለጸው። ከብት የሚያቆም እግረ ተከል እንደተራቆተ ገልፆ ነበር።

የቤተሰብ ማመጣጠን በሚል ሙከራውም ተግባሩም የተሠራው 
አማራ መሬት ላይ ብቻ ነበር። ይህ ደግሞ ሃሰት አይደለም። በሌላ 
በኩል የመጨረሻው ከ ዓለም አገሮች በዓይን በሽታ ተጠቂው ደግሞ አማራ ክልል ነው ድህንቱም እንዲሁ። ብአዴን/ አዴፓ በቀደመው ተግባሩ ሊያፍር ይገባል እንጂ ከዘመነኞች ጋር አብሮ ድርጊቱን 
አልተፈጸም ብሎ መካድ የተገባ አይደለም። እሱም ተባባሪ አራጊ ፈጣሪም ነበር እና። 

ነገረ አማራ ላይ ያለው መላ ያልተገኘለት ሥር ሰደደ ዘመቻ ጥናቱ አልተጀመረም ገናም እንደ ዜጋ ኢትዮጵያዊ በሚለውም ወግን ከልባችንም አልገባም። የዋሆች፤ ገሮች የእኔ ቢጤ ሰዎች ነገሩን 
በለብታ ልናዬው እንችል ይሆናል። ጉዳዩ አማራን የመሰረዝ 
ጉዳይ ነው። ማፍለስ።

ስለሆነም የዛ የኖረ ወደፊትም ሊቀጥል ይችላል የሚለው ስጋትም ጭምር ቁጣ መካተቻ፤ የዛ ቁርሾ መወጣጫ ነው የሆኑት እነዚህ ሁለት የአገር  ወገን ተስፋዎች። ጥንቃቄ በብርቱ ያስፈልጋል። ሰዉ ብስጩ ሆኗል። ሰዉ ቁጡኛ ሆኗል። 

ስለዚህ ጤና ነክ ጥናቶች በግልም ይሁን በድርጅት በክልሉ ማቆም ቀዳሚው ተግባር ነው። አሁንም ደግሜ መናገር አምፈልገው አማራ መሬት ላይ ጤና ነክ ምርምሮች መቆም አለባቸው። እውነት ለመናገር የጤናም አይደሉም። በመረጃ መሳሳት አይደለም ከዛ ከገጠር በሉላዊ ዓለምም የሚገጥም ጉዳይ ነው። 

አሁን ሰሞኑን የትግራይ ወጣቶች የከፍተኛ ተማሪዎች እዛው በክልላቸው እንዲመደቡ የሚጠይቅ ሰላማዊ ሰልፍ አይቻለሁኝ። ይገባል። ይህ ክልል የተሻለ ነው ማለት አይቻልም። ሁሉም ክልል ቋፍ ላይ ነው ያለው። 

ስለዚህ እንደ እኔ በዬክልላቸው ተማሪዎች ቢመደቡ የተሻለ ይመስለኛል። ምክንያቱም የሰው ልጅ እንደ ዶሮ እንኳን ሊታይ የሚችልበት ሁኔታ ላይ አይደለነም። ሰው ሰው የሚሸት ጥረን እዬራቀን ነው። 

ትግራይ ላይ ያሉ ወጣቶች ደግሞ ሊሂቃኖቻቸው የሚሠሩትን በደልም ማጋለጥ አለባቸው። ከተጎዳው የኢትዮጵያ ህዝብ ጎንም መቆም ይጠበቅባቸዋል። ወንጀሎኞችን ሸፍኖ መፍትሄ መጠዬቅ ሰውኛም አይደለም። ችግር ከሌላው ይድረስ ከእኛ ግን ትውር አይበል ይህም ሰውኛ ጠረን አይደለም። ከሁሉ በላይ ግፍን በሚዛን የሚያው የላይኛው ደግሞ አለና።

ከሁሉም በላይ የአማራ ማንነት የህልውና ተጋድሎ ውጤት የሆነው የሜ/ጄ/አሳምነው ጽጌ የክልሉ የጸጥታ ጉዳይ ሃላፊ ሆነው መመዳባቸው ማመስገን፤ እርምጃው መክበር ይኖርበታል። አክብሮት በድርጊት መገለጽ ይገባል። 

ጎደለ ብለን የምንወቅሰውን ያህል በሙላት ባሉ ጉዳዮች ላይ ምስጋናቸው ገቢር ላይ መገኘት ይገባዋል። እሳቸውንም አይዞህ ከጎንህ ነን ማለት የሚቻለው እንዲህ ካለው ሥርዓት አልበኝነት፤ ኢሰብዐዊነት፤ እና አረመኔዊነት ተግባር መቆጠብ ሲቻል ብቻ ነው። 

የምንፈልገውም አልተመደበልንም ተገልሏል ስለንል ቁጣ፤ የምንፈልገው ሰው ሥልጣን ሲይዝ ብጥብጠ ይህ የጤና አይደለም - ለእኔ። ጥርጣሬ ካለ ይዞ እጃቸውን ለመንግሥት ማቅረብ ይቻላል። በሌላ በኩል ጥናት ልናደርግ የሚሉ ሰዎች ሲመጡም ፈቃድ አልመስጠት። አለመሄድ። በቃ። 

በተለይ አሁን አዬሩም ብስጩ ስለሆነ፤ እያንዳንዱ አማራ በክልሉ ለሚኖሩት ማናቸውም ኢትዮጵያዊ ዜጋ ዘብ መቆም ይኖርበታል። ንብረታቸውን መጠበቅ አለበት ከራሱ በላይ። ልጆቻቸውን መጠበቅ አለበት ልክ እንደ ወለዳቸው ልጆች። ሥርዓት ያልፋል ትውልድ ግን ይቀጥላል። 

የሚፈልጋቸው፤ የሚወዳቸው፤ የሚከባራቸው መሪው ብ/ጄ አሳምነው ጽጌ በቦታው ሃላፊነት ተስጥቷቸዋል። በዛ ላይ ለእሱ ሲሉ ነው መከራን የተቀበሉት፤ ይህም ብቻ አይደለም የሚሰጧቸውን አስተያዬቶች ሁሉ ተከታትያለሁ እጅግ የሰከኑ፤ የተረጋጉ፤ የበሰሉ፤ ሊደመጡ የሚፈቀዱ ብቁ የሚያኮሩም ዜጋ ናቸው። ስለዚህም ምደባውም ትክክል ነው። 

ይህን በማድረጉ የኢትዮጵያ መንግሥትም ሆነ የአዴፓ ሪኮምንዴሽንም ሊመሰገን ይገባል። በርቱ ሊባል ይገባል። ጥያቄም ሲመለስ ምስጋናው ቢቀር እንዴት አንዲህ የሚያስወቅስ ተግባር ይፈጸማል?

 የአማራ ሊሂቃን ሲገለሉ ኡኡ እንደምንለው ሁሉ ቦታ ላገኙት ደግሞ ልናግዛቸው ልንረዳቸው ይገባል። ህሊና ይኑር፤ ማንዘርዘሪያም እንዲሁ።

አሁን እሳቸው ም/ጄ/ አሳምነው ጽጌ በተመደቡበት ማግሥት ይህ እንሳሳዊ ጉዳይ መፈጸሙ 20ሺህ የአማራ ተጋድሎ እስረኞችን መከራ መርገጥ ነው። አካላቸው የጎደሉ፤ ጥፍራቸው የወለቁ፤ ለዘር ማይበቁ ሁሉ ወኖችን ፍዳ አላውቅህም እንደ ማለትም ነው። 50 የባህርዳር ነዋሪዎችን፤ 26 የአንባ ጊዮርጊስ ህጻናት ጭፍጨፋን ደመ ከልብ ማድረግ ነው። ሥርዓተ አልበኝነት ክብር ሳይሆን ውርዴትም ውርዴም ነው።

በመጨረሻ በመላ የአማራ ክልል ትናንት 29.10.2018 የተካሄዱ ሰላማዊ ሰልፎች በሰላም መካሄዳቸው ሆነ ካለምንም ወታዳራዊ ወከባ መጠናቀቃቸው አዴፓ ሊመሰገን ይገባዋል። 

ተሰላፊዎችም ሥርዓት ጠብቀው ሂደቱን በሰላም እንዲጠናቃቅ ያደረጉት ተሳትፎም ያስመሰገናል። በፍጹም ሁኔታ የተደራጀ እና ወጥ መንፈስም የነበረው አስመስጋኝ ታሪካዊ፤ ትውፊታውም ነው።

የከፋቸው፤ የተቹ፤ ያጣጣሉ፤ የከሰሱ፤ አልፈው ተርፈው ለመንግሥትም ማሳጣት ያሻቸውን ተከታትያለሁኝ ይህ የሚጠበቅ ነው። ዴሞክራሲ የማይመቸውን አስመችቶ መቀበል፤ ማስተናገድ ስለሆነ ያም ትክክል ነው ላቅራቢው።

ይኬኛውም የበደል መከራ ተከምሮበት ለኖረው አማራም ትክክል ነው ውስጡን ግልጥልጥ አድርጎ ማቅረቡ። መጥፎ ነገር ተከድኖ ሲንተከተክ ብቻ ነው። የ አማራ ህዝብ ንቅቅንቅ ብሎ የወጣው ከፍቶት እንጂ ደልቶት አይደለም። 

ለሰልፍ የሄደው ለሠርግ ሴሪሞኒ፤ ለካባ፤ ለወርቅ ሽልማት፤ ለሃኒ ሙን፤ ለዝና እና ልክብር ለጫጉላ ሽርሽር አይደለም። ደም የገበረበት ተጋደሎ ትሩፋት ውጤቱ ምንም ስለሆነ ብቻ ሳይሆን ነገም መከራው ቀጣይ እንዲሆን ያለው ዝንባሌ እዬታዬ ስለሆነ ነው። የግለቱ ሁኔታም እያዬን ነው።  አልጫ እና ቀይ ወጥ ክትፎ እና ቁርጥ ምርጫው ለተመቸው ነው። በዕንባ 50 ዓመት ሙሉ ለገፋ ለማገዶው የአማራ ህዝብ ግን የተሰማውን ገልጧል። የነበረው የችርስ ሰ ዕት ሳይሆን የ ዕንባ የወልዮሽ ሱባኤ ነበር። ክብር ለእሱ ለአዶናይ ይሁን። ይህን ዕድል ያገኘውም ራሱን ገብሮ ነው።  

እነ አቶ አስራት አብርሃም የመጀመሪያ የጎንደርን አብዮት ሀምሌ 5 ሲፈነዳ የገብያ ግርግር፤ ጎርፍ፤ እዛው ወልቃይት ላይ የማያልፍ ችግር ብለው ያቃለሉት ተጋድሎ ሥርዓት አስለውጦ ከዚህ ደረጃ ደርሷል ነገ ደግሞ ርስት ለባላርስት ይመለሳል። 

ዝርፊያም፤ ሌብነትም፤ ወረራም ነውር ስልሆነ ትውፊትን እንዳይበክል ፍርድ ያገኛል። ጊዜ ሁሉንም መልስ ይሰጠዋል።

ለስራ ሂደው ይህን መሰል አሰቃቂ በደል ለተፈጸመባቸው ወገኖቼ ነፍሳቸውን አርያመ ገነት ፈጣሪዬ ያግባልኝ። ቤተሰቦቻቸውንም ያጽናና አማኑኤል። ይህ የመጨረሻ የጭካኔ፤ የሃዘን መደምደሚያ ይሁንልን። አሜን!

ማስተዋል የተሰጠነን አምላካችን በውስጡ እንኖርበት ዘንድ ዘንድ አቤቱ አማኑኤል ሆይ አቅም ስጠን! አሜን

የኔዎቹ ኑሩልኝ።

መሸቢያ ጊዜ።  

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።