የሃይማኖት ተቋማት የህዝብ ሰቆቃ አጀንዳቸው አይደለም።

ሃይማኖት ምንድን ነው?
„ልጄ የበደልከው በደል የሳትከው ነገር አንዳለ እወቅ
 ከዚህ በኋዋላ ዳግመኛ አትበድል ስለ ቀደመው
ሃጢያትህ ንስሓ ገብተህ ተቀመጥ።“
መጽሐፈ ሲራክ ምዕራፍ ፳፩ ቁጥር ፩

ከሥርጉተ© ሥላሴ
02.10.2018
ከጭምቷ ሲዊዘርላንድ።


እኔ ውዶቼ ስለ ሃይማኖት ፍልስፍና ልናገር አይደለም። ይህ ጸጋ የአቨው የሃይማኖት ሊቃውንት መክሊት ነው። ሃይማኖት ማለት ምንድን ነው ብዬ የምጠይቀው ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የሃይማኖት ተቋማት ከንፈር ከመምጠጥ በስተቀር በዚህ የመከራ ቀን ከህዝብ ጎን ሊቆሙ አለመቻላቸው ሃይማኖት አለ ኢትዮጵያ ውስጥ ለማለት ከበደኝ።



የእውነት ከበደኝ ሃይማኖት አለኝ ለማለትም። የእውነት ይጭነቃል። ጂጂጋ ላይ ያን ያህል ሐዋርያት ሲታረዱ፤ አድባራት ሲነዱ፤ ምዕማናን ያን ያህል መከራን ሲቀበሉ አንድም ልዑክ  ከቅዱስ ሲኖዶስ ተልኮ ሄዶ ቦታውን እስከ አሁን ድረስ አላዬም። ለመሆኑ ፕትርክና ምንድን ነው? ምዕመናን እቦታው ድረስ ሄዶ ካላጽናን? ዓምት ሙሉ መፈናቀል?  ዓመት ሙሉ በሰው ሰራሽ ችግር እንዲህ ፍዳ መክፈል። ተቆጭ የለ። መካሪ የለ። የሚገስጽ የለ። ግርጫማ ጸጉር ያለው የለ። የሚፈራ የለ።



በሃይማኖታዊ ተቋማት ለተጎዱት አንዳችም ነገር አልተደረገም። ማውገዙን እማ እኛ ድሆችም እናወግዘው የለ። በቃ ሚዲያ ላይ ወጥቶ መናገር የሃይማኖት አባትነት ያሰጣልን?


ሃይማኖት ለዚህ መከራ ቅርብ ካልሆነ ማን ሊሆን ነው? በዬቦታው ለቅሶ ነው። በዬቦታው ዋይታ ነው። የመንግሥት መሪዎችን አይገስፁ የሚቆጣቸው የለ፤ የሃይማኖት አባቶች ቸልተኞች እና ግድየለሾች። ለነገሩ የራሰቸው ገማና ከሆነስ?



ሌላው ቀርቶ ቡራዩ ላይ እስከ 15 ሺህ ተፈናቀለ የተባለውን መንግሥት አውርዶ 3ሺህ ሲያደርገው ቀሪዎቹ ዜጎች አይደላችሁም ሲባሉ የዬትኛውም የሃይማኖት መሪ ወጥቶ መንግሥትን አልሞገተም? እነዛ ቁጥራቸው የተሰረዙት እኮ ከበዳላቸው በላይ ዜጋ አይደላችሁም ሲባሉ ይህ የማያርመጠምጠው የሃይማኖት አባት ምን ይባል ማንስ ይባል? ዕምነት እንዲህ ነው ወይ?


ይህን ነው ከልዑል እግዚአብሄር/ ከአላህ የተቀባላችሁት አደራ? ሥልጣነ የሃይማኖት አባትነት እንዲህ ገዴለሽ እንዲኮን ነውን?  ለመሆኑ የሃይማኖት መሬዎች ሊቃውንታት እንቅልፍ ተኝታችሁ ታድራለችሁን? ለመሆኑ የምትመገቡት ምግብ፤ የምትጠጡት ውሃ ከጉሮሯችሁ ይወርዳልን?


የመስቀል ደመራስ ለሰማዕታቱ ጸሎት ሳይደረግ እንዴት ተጀመረ? አያሳፍርም? ይህ ውርዴት የቤተክርስትያነት የመስጊዶች አይደለምን? በውነት የአውሮፓውያኑ ችቦ ርችት ለ2011 መስቀል ደመራ የሚያስተኩስ ነበርን? እሬሳው እንኳን በዬጥሻው የወደቀው አልተነሳም እኮ? ወድቆ በዬመንገዱ የቀረውስ?


ሁሉም ሃይማኖቶች ስለምን አንድ ላይ ሆነው አንድ የተደራጀ የችግር ጊዜ ደራሽ ቋሚ አካል አይፈጥሩም? ለምን መጠለያ በጋራ ሆነው አይሰሩም? ለምን ስንቅ አያቀርቡም? ስለምንስ እዛው አፍንጫቸው ላይ በግላቸው ርዳታ የሚያደርጉ ቅኖች ላይ ማዕቀብ ሲጣል ስለምን ወጥተው መንግሥትን እራሱን አይሞግቱም። ሞትም ከሆነ፤ እስራትም ከሆነ መቀበል ነው? እነሱ በድርጊት ያላስከበሩትን ሃይማኖት ማን ያክበርላቸው?አሁን ደግሞ ነቀምት ከቤንሻንጉል ጉምዝ የተፈናቀሉት ከ50 ሺህ በላይ ኢትዮጵያዊ ወገን ሜዳ ላይ ወድቋል። ወሎ አፋር ይቀጥላል … ችግሩ ትግራይን አይነካም...ለነገሩ ይህም አንድ ነገር ነው።  



አሁን ደግሞ የፖለቲካ ሊቃንት ሁሉ ተሰባስበው አዋሳ ሲመክሩ ሌላ ማዕት ደግሞ ይዘንባል። አሸባሪዎች ትእዛዝ ከሰጡ ደግሞ እንደ እሬቻው በዕል በሰላም ይጠናቃቃል። ትዕዛዝ የሚሰጠው እኮ ማሃል አዲስ አበባ ላይ ነው። ምን ጫካ ያስኬዳቸዋል? ሆቴል እዬተከፈለላቸው፤ ጠባቂ ተመድቦላቸው እዬተዘባነኑ ነው ይህን ሁሉ ቲያትር የሚሠሩት።  የሰው ደም የጠማቸው፤ የ ሰው ዕንባ የሚያስጨፍራቸው ክፉዎች። 


ለመሆኑ ምንድን ነው ሃይማኖት? ለዚህ ያልሆነ ሃይማኖት ምን ያደርግልናል? ስለምንድነው የዕምነት የሃይማኖት ተቋማት ችግሩ የእኛ ነው ብለው ለተደራጀ እርዳታ የማይተጉት። ስለምን?



ለምን ሃይማኖት ተፈጠረ? ለመጨካከን ነውን ሃይማኖት የተፈጠረው? ሥጋን የራስን ዞግ ወዶ የወገን ሰቆቃን እንዳላዩ ለማለፍ ነውን ሃይማኖት የተሰጠው? ጸሎት ድርሳን ድዋ ቅዳሴ ዝማሬ ለማድረግ ብቻ ነውን? እውነት ያሳፍረኛል። ኢትዮጵያዊ ዜግነቴ እያሳፈረኝ ነው? የተዋህዶ ልጅነቴም እምነቴም እንዲሁ።



አንድ መጠለያ፤ አንድ ቋሚ መጋዝን፤ አንድ በዚህ ሃሳብ ዙሪያ ነፍስ ያለው ተግባር መከወን የማይችል የዕምነት ተቋም ለሥጋ እንጂ ለመንፈስ ተፈጠረ ለማለት አያቻልም። እናት አላባዎች፤ አባት አልባዎች፤ ሚስት አልባዎች፤ ባል አልባዎች፤ ጧሪ ቀባሪ አልባዎች፤ ልጅ አልባዎች፤ ጤና አልባዎች፤ ትዳር አልባዎች ሺዎች ናቸው። እነዚህ በአገራቸው መሬት በድህነት መኖር ተከልክለው ፍዳቸውን እዬከፈሉ ነው።


ለዚህ የጨለማ ቀን አጀንዳ የሌለው ክርስትና እስልምና ምን ይባል? ምን ሥም ይሰጣቸው ኢትዮጵያ ውስጥ ለሚገኙ የሃይማኖት ተቋማት እስልምና ሆነ ክርስትና? ተፈናቃዩ ስንት ሚሊዮን ደረሰ? ሟቹስ ስንት ነው? አካሉ የጎደለውስ ምን ያህል ነው? ለመሆኑ ቁጥሩስ በትክክል ይታወቃልን የአገር አልባ ምንዱባን። አገር የሌለው ዜጋስ እንዴት ሃይማኖት ሊኖረው ይችላል? ካለሰው ሃይማኖት አለን? ካለሰው መስጊድስ ቤተ እግዚአብሄርስ ይኖራልን?



ይፈሩ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የሃይማኖት ተቋማት በሙሉ። ይህን ማስተባበር እንዴት ያቅታል? ይህን ማደራጀት እንዴት ይሳናል? በሞት ላይ ሆኖ እልልታ? በሞት ላይ ሆኖ ኩልልልታ …. እጅግ ይሰቀጥጣል? እጅግ ይጎመዝዛል ….



 ኢትዮጵያ እኮ በቀዝቃዛ ጦርነት ውስጥ እዬተማሰች ነው ያለችው። አላዛሯ ኢትዮጵያ በእጅ በተሰራ መከራ እዬነደደች ነው ያለችው። ቢያንስ በዚህ ጊዜ ይህን ችግር የሃይማኖት ተቋማት ሃላፊነት ወስደው ስለምን አይተጉበትም?
እውነት ብናገር ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የሃይማኖት ተቋማት የተሰጣቸውን መክሊት እዬጠቀጠቁት ነው። በዚህ ወቅት ይህ መከራ አጀንዳቸው ያልሆነ ለመቼ ሊሆኑ ነው። ያሳፍራል።



ይህ እኮ የአንድ አካል ብቻ ችግር አይደለም። በዚህ የጭንቅ ጊዜ ቤተክርስትያናት መስኪዶች ወደ ተቸገሩ ወጎኖች መገስገስ አለባቸው። ሐዋርያነት ተግባር እኮ ይህው ነው። እነሱ እኮ እዬተፈተኑበት ነው …


ይህ ፈተና የመጣው ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ተቋማት ሁሉ ይፈተኑበት ዘንድ ነው።  የአማኑኤል/ የአላህ የመጨረሻ ቁጣ የመጣ እንደሆን ተራፊ የለም እሳቱ
 በሁሉም ጎጆ ይነዳል …. ይብቃኝ ….

በቃችሁ ይበለን አምላካችን። አሜን!
ውዶቼ ኑሩልኝ።

በጸሎት እንትጋ። 

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።