እስኪነጋ...

እስኪነጋ ...
“ከአፌ ቃልም ቃል ፈቀቅ አትበል።
 አትተዋት ትደግፍህማለች፤
 ውደዳት ትጠብቅህምአለች።”
 መጽሐፈ ምሳሌ ምዕራፍ ቁጥር

ከጸሐፊ መስፍን©ማሞ ተሰማ
(Mesfin© Mamo Tessema)



ሠላም ለናንተ ይሁን!

አዎን እናምናለን። አዎን እየነጋ ነው። የህሃትና ህውሃታውያን ዘመነ ፅልመት እየተገፈፈ ነው። በኢትዮጵያ ሠማይ ሥር የብሩህ ቀን አጥቢያ ፍካት ይታያል። ያለጥርጥር ይነጋል። አዲስም ቀን ይሆናል። ግን ገና አልነጋም። መቼ ይነጋል? ብላችሁ አትቸኩሉ። ንጋትም ተፈጥሯዊ ዑደቱን ያጠናቅቅ ዘንድ ግድ አለውና። ንጋቱ በህወሃትና ህወሃታውያን ፅልመት እንዳይጋረድ ግድ ነውና።

ህወሃታውያን እነማን ናቸው? ህወሃታውያን ማለት እነ ጃዋራውያን እነ ፀጋዬ አራርሳውያን መሰሎቻቸውና ወዘተርፈዎች ሁሉ ናቸው፤ የበቀልና የቂም በቀል የጥላቻና የጎጠኝነት ታንቡረኞች። ህወሃትና ህወሃታውያንም የኢትዮጵያን ዘመነ ፅልመት ናፋቂዎች ናቸውና።

እንዲነጋ፤ የህወሃትና ህውሃታውያን መጋዝ ጥርሳቸው ሊረግፍ ግድ ነው። እብሪተኛው ጉልበታቸው ሊፈስ ግድ ነው። ለ27 ዓመት እንደ መንግሥት የረጩት መርዛቸው ሁሉ ሊመክን ግድ ነው። የታበዬ ልባቸው ሊሟሽሽ ግድ ነው። በዝርፊያ የደለበው የባንክ ደብተራቸው ይቀደድ ዘንድ ግድ ነው።

እንዲነጋ፤ መከላከያ ፖሊስና ደህንነት በለውጡ ህግ ሊገዙና ሊደራጁ ግድ ነው። የሀገር እንጂ የጎጥ አገልጋይና ታዛዥ አይሆኑ ዘንድ ግድ ነው። ፍርድ ቤቶችና የህግ ተቋማት በለውጡ ራዕይ በህግና ፍትህ አርማታ ላይ ብቻ ይታነፁ ዘንድ ግድ ነው።

እንዲነጋ፤ ዴሞክራሲያዊ መብቶች ሳይሸራረፉ በህግ ማዕቀፍ ይከበሩ በዜጎችም ያለ ስጋት ይተገበሩ ዘንድ ግድ ነው። እንዲነጋ፤ በኢትዮጵያ ሠማይ ሥር ነፃነትና ፍትህ መብትና እኩልነት ጠያቂ ዜጎች መኖሪያቸው ጨለማ ቤቶች ምሳና ራታቸው ሰቅጣጭ ቶርቸር ውርደትና ሞት መሆኑ በርግጠኝነት ማብቃት አለበት።

እንዲነጋ፤ የኢትዮጵያ ልጆች በኢትዮጵያ ምድር ሁሉ የመኖር ተፈጥሯዊ መብታቸው በህግ ማዕቀፍ ሊረጋገጥ ያለ ሥጋትም በዜጎች ሊተገበር ግድ ይላል። እንዲነጋ፤ ኢትዮጵያ ልጆቿን የምታሳድድና የምታባርር መሆኗ ቀርቶ የምታቅፍና የምታኖር መሆን መቻሏ ግድ ነው።

አዎ! በኢትዮጵያ መንጋቱን አዲስም ቀን መጥባቱን ለማብሰር - በኢትዮጵያ ሠማይ ሥር በኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ነፃ ፈቃድና ነፃ ምርጫ የተመረጠ መንግሥት ቤተ መንግሥቱን ይረከብ ዘንድ ግድ ይላል። እነሆም በዚያን ቀን የአዲሲቷ ኢትዮጵያ ንጋት ይፋ ይሆናል!!! እነሆ ያኔ ፅልመቱ ያለ ርዝራዥ ተገፎ ይነጋልና፤ ኢትዮጵያና ህዝቧም አዲስ ዘመን ይጀምራሉና!

እንግዲህ ይህ እስኪሆን ኢትዮጵያውያን እንቅልፍ አይኖረንም። እረፍትም አንመኝም። የጨለማውን ዘመን ትብትብ የፖለቲካ ሠንሠለት እስክንበጣጥስ፤ የተዘረፈውን ሀገራዊ ሀብት እስክናስመልስ፤ በየጎጣቸው ድንኳን ሥር የተደበቁትን ጥፍር ነቃዮችንና የተደራጁ ሌቦችን መንጥረን በአደባባይ ችሎት እስክናቆምና እስክንፋረድ፤ በየጎጡ የታመሰውንና የታመመውን ማህበረሰብ እስክናክም ከቶም ደከመን አንልም። ጨለማው ዘመን እንዳይመለስ ከቶም እንቅልፍ አይኖረንም።

አዎን እናውቃለን፤ እስኪነጋ ሃሳዊ መሲሆች ይበዛሉ። በኢትዮጵያ ሥም እየተገዘቱ የአዞ እንባ የሚያነቡ የአሳማ ጩኸት የሚጮኹም ይበረክታሉ። እንደ ልበ ሙቅ የጅብ መንጋ ከየጎሬያቸው ተጠራርተው እየተፈራገጡ የሚያቅራሩ፤ እንደ ጃርትም በየጎጡና በየቀበሌው የሚርገፈገፉ ይነሳሉ። የጨለማውን ዘመን የደም ጥርሳቸውን እያፋጩና የደም ጥፍሮቻቸውን እያንጨፈረሩ ይወራጫሉም።

አዎን እስኪነጋ ደናቁርትና ዘመን ያለፈባቸው ፖለቲከኞች ይበዛሉ፤ <ትንቢተኞች> ይፈላሉ፤ ጃኬት ገልባጮች ቦታ ይይዛሉ። አብይንና መንግሥቱን ተቺዎችና አቃቂረኞች የበዙበትን ያህል ጭፍን አምላኪዎችም እንደፈሉ እናውቃለን።  አዎ፤ እስኪነጋ ይህ ሁሉ በኢትዮጵያ ሠማይ ሥር ይሆን ዘንድ እናውቃለን። አስቀድሞ ጠቢቡ እንደተናገረው እነሆ ይህ ሁሉ ሲነጋ ከንቱ ነው። አዎ፤ መንጋቱ ከቶም አይቀሬ ነውና ይነጋል!!

እስከዛው፤ በደማችንና በሞታችን፤ በእስራችንና በስደታችን ባላባራውም ተጋድሏችን በአብይ ፆም መውጫ በአብያዊ በዓለ ሲመት በታወጀው ኢትዮጵያዊነት ያገኘነውን አብይ ስጦታ እስኪነጋ ድረስ ይዘነው እንዘልቃለን። የትግላችን ፍሬ የሆነውን አብያዊውን መንግሥት የደገፍነውና የምንደግፈው - ሰውና ኢትዮጵያዊ ስለሆንን ብቻ ነው!! ለዚህም ነው እስኪነጋ ተደጋግፈን አብረነው የምንጓዘው።

„Ethiopia:/ አብይ አስደማሚ ንግግር አደረገ

 የኢትዮጵያ የፖለቲካ ለውጥ በሚል“


ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ህዝቧን ይባርክ! አሜን!
ህዳር 2011 ዓ/ም (ኖምበር 2018)

ሲድኒ አውስትራልያ 

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።