ሽብልል በሽብልል ቃለ ምልልሱ ከፖለቲካ ሳይንቲስቱ ጋር - በዋልታ።

ሽብልል በሽብልል።
„ስለ ራዕይ ሸለቆ የተደገረ ሸክም።
እናንተ ሁላችሁ ምን ሆናችኋዋል?“
ትንቢተ ኢሳያስ ፳፪ ቁጥር ፩
ከሥርጉተ©ሥላሴ
 14.11.2018
ከጭምቷ ሲወዘርላንድ።

                                                        

·    መነሻ።

ሽብልል የሚለው ቃል አንዲት ሴት የገብስ እንጀራ ካሰኛት በወፍራሙ ትለውሰዋለች፤ ለረጅም ጊዜም ይቆይላታል። አገልግሎቱን ውጤቱን ሳያሳውቅ። እዬገነፈለም አያጨናናቃትም ቀኑ ሲደርስ አቅጥና ከሙገጎ ጋር ታገናኘው እና እንጀራ ይሆናል፤ እሰከዚህ ድርስ ግን ሽብልሉ የዳቦ ይሁን፤ የጠላ አብሽሎ ይሁን የእንጀራ ይሁን መለዬት አያቻልም። ያው ሽብልል ነው። እንደተሸፈነ ተሸብልሎ ይሰነባብታል። ቀኑ ሲደርስ ግን ተቀጥኖ ሲጋጋር የገብስ እንጀራ ይሆናል። 


ሌላው ግምል የሚባል ደግሞ አለ። ግምል ደግሞ የማሽላ ነው። የደበር፤ የወድ አራባ፤ የወዳከር የቡሌ ወይንም የባህር ማሽላ ሊሆን ይችላል። ገምላ አስንብታ ልታጋግር ስታስብ ሴት ባለሙያ አቅጥና ትጋግራዋለች ማለት ነው። የጤፍ የቦካ በሌላ ዕቃ ከኖራትም አብራ አዋህዳ ትጋገረዋለች። የገብስ እና የማሽላ ልወሱ ለብቻ ነው የሚዘጋጀው። እንዲያውም በሰፊ ገበታ ነው የሚቀመጠው። የ ጤፉ ግን በማንኛውም ቡሆዕቃ ይሰናዳል፤ በቅልም በ እንስራም ትልቅ ቤተሰብ ካለም፤ ድግስም ከኖረ በጉርድ በርሚልም ሊሆን ይችላል። የማሽላው እንጀራ ፍርክ ፍርክ የሚል ሲሆን የገብሱ ግን ለስላሳ እና ዘንጣፋ ነው። ግን ማሽላው በግምል ገብሱ በሽብልል መሰንበቱ አይቀሬ ነው።  

 

·       ሥሜ።

https://www.youtube.com/watch?v=9Ck5Y9I42lA Professor Merera Gudina

የኦፌኮ ሊቀመንበር ከሆኑት ከዶ/ መራራ ጉዲና ጋር

 የተደረገ ቃለ መጠይቅ እንድትከታተሉ በአክብሮት እንጋብዛለን

 

ሰኞ ዕለት ይህን ቃለ ምልልስ እያደመጥኩ እያለ ሥሜ ተጠራ። አምላካችሁ አለ ክው አልኩኝ። ደነገጥኩኝ። ምክንያቱም በኢትዮጵያ የመንግሥት ሚዲያ የእኔን ሥም ምን እግር ጣላው ብዬ ነው። ተዚህ በውጭ አገሩ ሚዲያ የተፈራ፤ የማይደፈር ሥም ነውና ሥርጉተ ሥላሴ። ወጣት እያለሁም ዓለማዊ ሥሜም ገናና ነበር።

 

ተግባሬ ትትርናዬ ትጋቴ ሳንክ ቢገጥመውም መሪዎቼ አለቃዎቼ የሁሉም የመምሪያ ሃላፊዎች ብቻ ሳይሆን ጓድ ገ/መድህን በርጋ የመሰለ ጠንካራ ኳች ስለነበረኝ በዘመኑ ለነበረኝ አቅም የድርሻዬን የምወጣበት ሙሉ የተጋድሎ መስክ ነበረኝ። ተቀይሮ ሄዶ እንኳን በእኔ ጉዳይ ላይ አይተኛም ነበር የሙያ አባቴ። የቀረጸኝ ውስጤን በአደራጅነት ሙያ የፈወሰኝ አባቴ። 


ሌሎችም የፖለቲካ ሊሀቃን ቢሆኑም እኔን ለመቅረጽ አይደክማቸውም ነበር። የእነሱ ጥረት ነው የዚህ የስደቱ ወጀብ እና ሰው ሰራሹንም ፈተና እዬጠቀጠኩኝ በመንገድ እና በመርሄ ውስጥ ልብ ሳላስገጥም ከነጠፍሮዬ የምገኘው። በሥርጉተ ሥላሴ ነፍስ ውስጥ የሥርጉተ ሥላሴ መርህ ብቻ ነው ያለው።  

 

„መፈራት“ የምትል ቃል ከላይ ተጠቅሜያለሁኝ፤ መፈራት ስል በሥልጣን አይደለም፤ በሴቶች አቅም ላይ፤ በዜጎች አቅም ላይ፤ በዜጎች የተሳትፎ አድማስ ላይ፤ በሴቶች ችሎታ እና መክሊት ላይ፤ በስደተኛ እህት ላይ ዕቀባ ተጣለ ቢባል የመጀመሪያዋም የመጨረሻውም ሥርጉተ ሥላሴ ብቻ ናት። እንግዲህ ሥርጉተ ሥላሴ ጎንደሬም ናት አማራም ናት። 



ከሁሉ የሚልቀውም ፍልቁ ማንነቷ ደግሞ እንበርቱ ኢትዮጵያዊት ናት። ለኢትዮጵያ እንተጋላለን አዋጬው የዘግነት ፖለቲካ ነው የሚለው ነው እኔኑ ሲታገለኝ የኖረው። አሁን እሱም ነፃ ወጪ ሆኖ አድባሯ ዎህ ብላለች። ተነፈስን። ተመስገን!

 

በተከታታይ ዓመታት ዘሃበሻ አግዞኛል። ስለ ዘሃበሻ ሰዎች ናቸው አድራሻቸውን የሰጡኝ፤ እስኪ ሁሉም ያገደሽ ስለሆነ እነሱን ሞክሪ ተብዬ ነበር የሞከርኩት። አሳኩትም። እርግጥ ነው ዘሃበሻ በርከት ብለው ስለሚሰሩት አንዱ ሲያትምልኝ ሌላው የሚነሳበት ሁኔታ ነበረበት። ሳይወጡ የቀሩ ጹሁፎቼም አሉ። ግን በአብዛኛው ጹሑፌን ዘሃበሻ አውጥቶልኛል። አብሶ በሌላ ሰው ፎቶ ከሆነ ርዕሰ ዕምድ አድርጎ የስክሪን ጌታ ያደርገዋል ነበር ጹሑፌን። ቢያንስ ሥሜ እስክሪን ላይ ውሏል ማለት ነው።

 

ፎቶዬ የያዘ ከሆነ ግን ደረጃውን ጠብቆ እታች ይለጠፋል፤ ከዛ ሁሉ ጹሑፍ ውስጥ አንድም ጊዜ ፎቶዬ እንደ ሌሎች ጸሐፍት ስክሪን ላይ አልዋለም። ስለምን ቢባል ሥርጉተን ሥሟን መለጠፍ በራሱ ሁለተኛው ዓለም ጦርነት ምስጋን ይንሳው። መከራቸውን ያበሏቸዋል። እኔን መንፈሴን ቀብረው፤ መክሊቴን ሁሉ አሳግደው ድል አድርገው ቢሆን ኖሮ ግንቦት 7 ምንኛ እልል ባልኩለት ነበር። ግን ነቀላው ራስንም ነው የነቀለው ለዛውም በህዝብ መንፈስ ውስጥ። የአሁኑ የአገር ቤት አጀብ የሳሙና አረፋ ጤዛ ነው። ለዚህም ኢሳት የሠራው ነው። የሞገድ ውጤት።

 

የሆነ ሆኖ እኔ ዘሃበሻን ደጋግሜ አመስግኜዋለሁኝ ወጀቡን ሁሉ ችሎ 2013/ 2014/ እስከ 2015 ጥቅምት ድረስ አስተናግዶኛል፤ ተከፍሎኝ አልነበረም እምሠራው፤ በራሴ የጊዜ እና የመንፈስ ወጪ ብቻ ነበር። ለዚህ የነፃነት ቀን ብዬ እደክም ነበር። … በዬማህሉ ጫናው ሲበዛበት ጹሑፌን ሲያነሳው እኔ ደግሞ አልጋፈጥም፤ ተወት አድርጌው እቆይና እንደገና አረሳስቼ ስልክላቸው ደግሞ የሚያቅፉኝ የሚያከብሩኝ ባሉበት ዕለት እና ሰዓት ጹሑፌ ከደረሰ ይወጣልኛል። ካልሆነም ዕጣው ይቀራል። ያው ሎተሪ ማለት ነው።

 

ከዘሃበሻ ቀጥሎ አብረውም ቢሠሩም ከሳተናው ጋር ሳተናው / ኢትዮ ሪጅሰተር በድርብ ድፍረት በልዩ አክብሮት አስተናግዶኛል፤ እንዲያውም የእኔን ፎቶ አጉልቶ በማውጣት „መነበብ“ ያለበት እያለ ርዕሰ ዓምድ እያደረገ፤ አሁን እንኳን ከወቅታዊ ሁኔታዎች ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ሲገጥምጡት የእኔ ቀድም ያለ ጹሑፍ እዬለጠፈ ለመንፈስ ጥገት ሆኗል። ሌላው ይገርመኝ የነበረው ፎቶዬን እንዴተት አስተልቆ አምድ ያደርገው እንደ ነበር ነው። ይገርመኝ ነበር። የታምር ያህል ነው የሚገርመኝ። ያው የሎሬቱ መንፈስም ቅኝት ስለሆነ ይመስለኛል ሳተናው። ለጥበብ ሰው ቀናተኛ ዋቢ ይመስለኛል ሳተናው። ለሴቶች አቅምም እንዲሁ።

 

እና አንድ ጊዜም „የሳተናው አምደኛ“ የሚል የክብር ኒሻንም አክሎበት ነበር። ይህን ሳይ ለሚቀርቡኝ ወዳጆቼ አሁን ያስነሱታል ብያቸውም ነበር። አልበረከትም ተነሳ። እሱም የሚኖርበትን ወጀብ፤ ጫና፤ መከራ ተሸክሞ ነበር የተቋረጠውን የመንፈስ ምርቴን ሲያስተናግድልኝ የኖረው። እኔ እንደ እናቴ ነው የማዬው። በቤቱ አልኮራምና።

 

ድብዛዬ ጥፍት ባለበት ጊዜም ለቤተሰቦቼ አለች ብለው እንዲያሰቡ አድርጓቸዋል። አብሶ የእናቴን ህይወት አቆይቶልኛል። ወላጅ እናቴ እብዬ መኖሬን የምታውቀው ዜና የሚያወጣላት በሳተናው ስለነበር። በርከትከት ላሉ የብዕር ሥሜን ለሚያውቁት ቤተሰቦቼንም እረፍት ይሰጥ ነበር። መንፈሱን ሳተናው ያዳነው በዛ በጨለማ ጊዜ የመነኩሲቷን ደካማ እናቴንም ነው። ቀን ያወጣ ብራና ነው ሳተናው/ ኢትዮ ሪጅሰተር። ረቂቅም ነው ዕድምታው። የእናቴን ነፍስ አቆዬልኝ። ሆድ ይመርቅ ብቻ። የመንፈሴ ጉልላትም ነው። 


የእኔን ጉዳይ የሚያትሙ ቀርቶ ሥሜን ተግባሬን የሚያነሱ ሰዎች በእግር በፈረስ ተፈልገው ግንኙነቱን እንዲያቆሙ ይደረጉ ነበር። ይህን ደባ ተሸክሞ የነጻነት ታጋይ መሆን ፍርድን ለሚዛን ልተዎው። የሰውን ጸጋውን መክሊቱን መቅበር ነፃነት መስጠት አይደለም። ለነፃት ታጋይነትም አያበቃም።

 

 ከዚህ ባሻገር ግን ሲያሳድዱኝ ሥሜን የጠራ እኔ የቀረበ ሁሉ እዬታደነ፤ የተሳሳተ መረጃ እዬሰጡ ከምድረ ገጽ መንፈሴን ለማጥፈት ያልተከተ ተግባር ተደራጅተው ፈጽመውብኛል። እስኪ ይነገረን በስደት ውስጥ ሆና 7 መጸሐፍ የጻፈች ሴት፤ በማያቋርጥ ሁኔታ የምትጽፍ ቋሚ የድህረ ገጽ አምደኛ፤ የጸጋዬ ድህረ ገጽ፤ የጸጋዬ ራዲዮ ፕሮግራ በጥምረት የመሰረተች ለዛውም ስደተኛ ካንፕ ውስጥ ሆና፤ በር ሲዛጋ በመስኮት መስኮት ሲዘጋ በጣሪያ ጥረቷን ያልቋረጠች፤ ነፃነት ተኝታ ቀን ሲወጣ ያልፋል ብላ ያልጠበቀች ሴት ናት ሥርጉተ ሥላሴ ማለት፤ ፊት ለፊት ወጥታ የሞገተች፤ የታገለች ናት።

 

 አሁን ደግሞ ቀንበጥ ብሎግን የፈጠረች፤ የዓለምን የሰላም ምልክት የሆነውን የተባባሩት መንግሥታት ጽ/ቤት እና የአውሮፓው ህብርት ፕላኔታችን እያስፈራች ነው ፍቅር እንደ ሂሳብ እንደ ባይወሎጂ በት/ቤት ደረጃ መሰጠት አለበት ብላ የሞገተች፤ አልሆን ሲላት የራሷን ዩቱብ መስራት አነሳሽ የሆኑ የፍቅር ጥልቅነትን የሚገልጹ የቃላት የፖስተር ቻናል ለመጀመሪያ ጊዜ ያሰናዳች፤ በአማርኛም በተወሰነ ደረጃ ዩቱብ ላይ እምትሰራ ሴት ኢትዮጵያዊት እንዲህ ግዞተኛ ሆነ ነው ያለችው።

 

እና ሰኞ ዕለት ሥሜን ጋዜጠኛው ሥሜነህ ባይፈርስ ሲያነሳው ከእስር መፈታቴን አረጋገጥኩኝ። የወያኔ ሃርነት ትግራይ እስር መሬት ላይም እስረኛ ስለነበርኩኝ እዚህ ቢአሳድዱኝ የማውቀውን አውቀዋለሁኝ፤ ፍች የማጣለት እዚህ ውጭ አገር ያለው የስደተኛ አቅምን፤ መንፈስን፤ ህሊናን ለማስር የነበረውን የደቦ ሴራ ነው። አስታዋሽ አንድስም እንኳን በሌለበት ሰዓት እንዲህ ሥሜን ሙሉ የብዕር ሥሜን ማንሳት ከእውነት ታምር የተሰጠ ልዩ ሽልማት ነው ማለት ይቻላል። ለካንስ አገር ቤትም እንዲህ የእኔ የሚባሉ የሃቅ አርበኞች፤ ለማንፌስቶ ሎሌ ያልሆኑ ወገኖች አለን ለማለት እስችሎኛል። እርግጥ ነው ውይይይቱን የዋልታን ይሁን የናሆን  የኤል ቲቪን አንዲሁም የአንድ አፍታን ወድጄው እከታተላለሁኝ። ትህትናቸው የመቻል አቅማቸው አደባቸውን ስለምወደው።  

 

ወደ ቀደመው ምልሰት ሳደርግ እኔ እዚህ ሲዊዘርላንድ በመጣሁበት ዘመን ኢንተግሬሽን ቤተ መጻህፍት አማርኛ መጻህፍት አልነበራቸውም። የእኔ ግን 6ቱም መጸሐፍቶቼ በኢንተግሬሽን ቤተመጻህፍት። የሲዊዝ ብሄራዊ የ ኢንተግሬሽን የቤተ መጻህፍት ጉባኤ ላይ መግለጫ 6 ጊዜ ተሰጥቶባቸው እዛው ላይ ተሽጠዋል። 7ኛውም ቢሆን ወጀቡ ስለበዛብኝ ነው እንጂ እነሱ ካወቁ ያደርጉታል።

 

ሲዊዘርላንድ ውስጥ እንደ አጀማመሬ ጸጋዬ ድህረ ገጽ እና ጸጋዬ ራዲዮ ቢቀጥሉ የብዕር ሆነ የመንፈስ ብድር ስለማልሄድም፤ የማድረግም፤ የመፍጠርም አቅሙ ስለነበረ ዛሬ ሲዊዝ ላይ አንቱ ከሚባሉት በኋዋላ ከተፈጠሩት ሚዲያዎች እኩል የብላቴ ሎሬት ጸጋዬ ገብረመድህን ሥምን የያዘው ግራ ቀኝ ሚዲያ ከሌሎቹ ጋር ተርታ በተሰለፈ።

 

 ለዚህም ነው መከራው የእኔም ብቻ ሳይሆን የብላቴውን ሥም ማዬት ለማይሹት ስል ቀንበጥ ያልኩት አዲሱን ብሎጌን። ይህም በፈተና ነው የተጀመረው። ቀንበጥ ከሁለት ዓመት በፊት ባዶ ሥሙን ተሸክሞ ኑሮ፤ ግንቦት አንድ ላይ ግን በአብዮ አክቲቢዝም ላይ የተሠሩትን ብቻ ላይቼ ማሰቀመጥ፤ ለትውልድ ስለሚያስፈልግ ጀመርኩት እንጂ ለእኔ የነፍስ ማረፊያ ብላቴው ሎሬቱ ነው። 


ግን የእሱን ሥም ማስጠራቴ ገና ስጀምረው በውጥኑ የኦሮሞ ድርጅት አባል ናት ተብዬ ሁሉ ተከስሼበታለሁኝ። የተሰጠው መልስም በእጄም ይገኛል። ለሁሉም ብረት መዝጊያ የሚሆን ዘመድ ያስፈልጋል። ያ ከኖረ የወያኔ አሽከር የነበረውም ባለሙሉ ጌታ ነው። አንቱ ነው፤ ተንታኝ ነው፤ አወያይ ነው። ታዋቂም ነው።

 

የገረመኝ ይህን ሁሉ በደል አደራጅቶ የፈጸመው ግለሰብ ጎንደር መሬት ላይ ተገኝቶ ሸር ጉድ ሲል ነበር። አይታፈረም ወሎም የ እሱን ትንተና አዳምጥ በሎ ከግንቦት 7 ሰው ጠፍቶ መግለጫ ሲሰጥ በጨረፍታ አዬሁት። አላደመጥኩትም። ምን ሊገኝ? ወሎም ፈርዶበት? አብሶ ጎንደር ላይ እንደ እሱ ብሆን ብትንትኑ የሚያወጡ አንበሶች ነበሩ ከቦታው። እሳት የላሱ። መሰናዶውን ከሚመሩት ከቁንጮው ጀምሮ። 


የጎንደር ልጅ ይህን ያክል እዬተሳደደች በመቃብር ውስጥ እንድትኖር ግዞት ተፈርዶባት እንደዛ መዘባነን ባልተገኜ ነበር። ለጎንደር ማተቤን ሳላጥፍ፤ በጽናት፤ በብርዱ በሃሩሩ በጫካ በዱር በገደሉ በካቴነው በስደቱ ሁሉንም ያስተናገደች ልጁ ናት እና ሥርጉትሻ።

 

ይህ ሁሉ ሲሆን መሃያ እዬተከፈለኝ፤ አጃቢ ተመድቦልኝ፤ ሆቴል እያማረጥኩኝ፤ በተገኘው ቦታ ሁሉ የራሴን ሰው እዬወተፍኩኝ አይደለም፤ አልነበረም። ዝና ብፈልግ ሥርጉተ ሥላሴ እኮ ገናና አለማዊ ሥም አላት። ደግሞስ ክብር ዝና ዕውቅና ጋሜዬን ከርክሞ ነው እኮ ያሳደገኝ። ከአገር መሪ ጀምሮ ሥርጉትሻ በአካል ሊሂቃን አግኝታለች። ስለዚህ ብርቋ አይደለም። ምኑም ነገር። ይህ ሥም ብቻ ያለው ማንፌሰቶ ጽፎ ፓርቲ ነኝ ማለትም ቢሆን መደበኛ ሙያዋ ማደረጃት እኮ ነው ምን ቸግሮ በተደረደረ ግን አስፈላጊ አልነበረም።

 

የሆነ ሆኖ ሚዲያዎቼ ከትውስት አንድም ነገር የህሊና ምርት ይሁን የሰው ገንዘብ አይወስዱም። ለመጻፍ ምን ጠፍቶ ከእቴጌዋ ሞገደኛ ሥርጉተ ሥላሴ ቤት። ራዲዮ ሎራ የፕሮግራም መሬዎች ግርም ነበር የሚላቸው። ምክንያቱም እንደ እኔ ተሰናድቶ የሚሄድ ማንም ስሌለ። ለናሙናም ሲጠየቁ ጸጋዬረ ራዲዮን ነበር የሚሰጡት። እሱንም አስቆሙት ብቻ ሥሙ አለ … የጸጋዬ ራዲዮ፤ እንኳንስ ሊከፈለኝ እኔ እዬከፈልኩ ነው እምሰራው የነበረው። አሁንም እከፍላለሁኝ።

 

አሁን በጸጋዬ ራዲዮ ከዬትኛውም ሚዲያ ከአገርም ውስጥ ይሁን የውጭ መልካም ነገሮች፤ ጠቃሚ ነገሮች ይተላለፉበታል። ድምጼን መዝጋት አሰኛቸው እንደ ፈለጉት ሆንኩላቸው። ምክንያቱም ወጀብ ሲኖር ዝቅ ብዬ ማሰለፍ ልማድ ነው። ፈተና እራሱ በፈተና አስልጥኖኛል እና። አሁን የብላቴ ሎሬት ጸጋዬ መታሰቢያ ሲዊዘርላንድ ላይ ቢኖር ምን የሚከፋ ነገር ኑሮ ነው? 


ጋሼ ጸጋዬ እኮ የሉላዊቱ ዓለም የቅኔ እጬጌ ነው። ኩራታችን ነው! አገራችን ከፍ አድርጎ ያስጠራ መቅደሳችን ነው የቅኔው ልዑል። ቀድሞ ነገር እሱን የሚተካ ሰው ኢትዮጵያ አላትን? ለሃቅ የቆመ? ለእውነት ያደረ? ፍቅርን አጤው ያደረገ እናቱን ጽላቱ ያደረገ፤ ኢትዮጵያዊነት መልኩ አቋሙ ማንን ይመስላል ቢባል ሎሬቱን ነው።

  

የሆነ ሆኖ ሰሞናቱ የጽጌ ፆም ነበር። የድንግልን ስደትን አስምልክቶ ከመስከረም 26 እስከ ህዳር 6 የሚቆይ የፈቃድ ፆም አለ፤ አዘውትሬ የምናገረው ነገር ነበር የጽጌ ፆም ጉርሻዋ የላይኛው ነው እላለሁኝ። እናም የጽጌ ፆም ትሩፋት ነበር። ሰው የማያውቀው፤ የተጫነኝን፤ የተዘጋብኝን፤ የተጋረደውን የበርሊን ግንብ የደረሰመው የዋልታ ተሌቪዥን ጋዜጠኛ ሥሜነህ ባይፈረስ ይህ ወንድሜ  እንደ ሳተናው ሃቅን ደፍሮ ሥሜን አነሳው። መነኩሲቷ እናቴ የብዕር ሥሜን የክርስትና ሥሜ መሆኑን ስለምታውቅ የኢትዮጵያም የሚዲያ ደንበኛ ስለሆነች ታዳምጠዋለች ብዬ አስባለሁኝ።

 

ምክንያቱም በእሷ ፍቅር የተለወጠ የነፃነት ተጋድሎ ውስጥ ልጇን ሥም ስትሰማ አምላኳን ታመሰግናለችና። እሷም ልታዬኝ በርሃ የተከላተመችበት ሁኔታ አለበት። በፈተና አስገርፌያታለሁኝ።  በእኔ ህይወት ውስጥ እሷም አለች፤ በ እኔ መገለል ውስጥ እሷም አለች፤ በ እኔ እስራት ውስጥ እሷም አለች።

 

ከሁሉ በላይ ግን የልጄ ልፋት ከንቱ አልቀረም ትልም አለች። ጋዜጠኛውንም አቶ ሥሜነህ ባይፈርስ እንደ ሳተናው ትምርቅዋለችም። ሳተናውን ትጸልይለታለች። ዜና ወሬ ስለ ልጇ ደህንነት ነጋሪዋ ነበር እና በዛ የድቅድቅ የጨለማ ዘመን።


የእብዬ አጽናኟም ነው ሳተናው በመንፈስ። አይዞሽ ልጅሽ ይህችትና ማለት ነው ሲያትምልኝ። በዚህ አካሄድ  የድምጽ አልባዎችን የኢትዮጵያ እናቶች ሰቀቀንም ተጋርቷል ብዬ ስላማምን ነው እኔ የ2010 የዓመቱ የቀንበጥ ብሎጌ ምርጤ የሆነው - ሳተናው። በሌላ በኩልም በአብዩ አሜኑ አክቲቢዝም ላይ ቀንድ ሚዲያ ነበር። እርግጥ ነው ዕወቅናው እና ሸር ጉዱ የት ላይ እንደነበር በትዝብት ተመልክቸዋለሁኝ። ማን እንደ ሳተናው ተጋና ለ አብይ ለአዲሱ የለውጥ ሂደት፤ በፍጹም ቅንነት ነበር የተጋው።   

 

አቤቶ የግንቦት 7 ካድሬዎችም ሥሜን በዋልታ በሚዲያ ሲሰሙ የማያስቆሙት፤ የማያግዱት ነገር ስለሚሆንባቸው ምጥ እና ዳጥ እንደሚሆንባቸው የታወቀ ነው። እኔ ከግንቦት 7 ፍትሃዊ ነፃነት አልጠብቅም። አስሮኝ፤ ቀፍድዶኝ፤ መክሊቴን መና እንዲቀር ያደረገ ድርጅት ነው። ብዙ ነገር ነው የተቀበረው። ብዙ አቅም ነው ቅስሙ ተሰብሮ የቀረው። የጋሼ ጸጋዬ መንፈስ ተቆራርጦ ተሸንሽኖ መና እንዲቀር ያደረገ ድርጅት ነው ግንቦት 7። በጽኑ ሲያሳድደኝ የኖረ ድርጅት ነው ግንቦት 7 ሙንሽንን ሳይጨምር።

 

እኔ ለእሱም ቢሆን የደከምኩ ዜጋው ነበርኩኝ። የመጀመሪያው ሥብስባ ተሰካ ሊለው የሚችለው፤ ለቀጣዩም ስኬት ያ ምጥን ክውን ያለ ሥርጉተ ሥላሴ ፍራንከፈርት ላይ የመራችው ስብሰባ ነበር። ብቻ ይሉኝታ ቢስ ስለሆነ ግንቦት 7 የብልጠት ፖለቲካው አይደንቀኝም። ነገም የፈለገውን በፈለገው ልክ ማንኛውም ዜጋ ይሁን ድርጅት መስዋዕትንት ይክፈልለት ለግንቦት 7 ጉዳዩ አይደለም፤ ከድልድይነቱ በኋዋላ ዞር ብሎ አይመለከትም፤ ቢሆንማ እንደ እሱ ማን ዕምነት የተጣለበት ድርጅት ነበር እና።  

 

·       ሹልከት።

 

ትንሽ ስለ ነፃነትን ዓዋጅን ነጋሪነት ለጎሰም ደፋር ጋዜጠኛ አቶ ስሜነህ ባይፈርስ ግራሞቴን፤ አድናቆቴን፤ ትሁታዊ አክብሮቴን መግለጽ ችያለሁኝ። በምልሰትም በደፈናው ሳይሆን ግልጡን ማሳዬት ያስፈልጋል። እስረኛን ነፃ ስላወጣ። የሠርጉተ ሥላሴ ብዕር እንደ ሳተናው ነፃ አውጪም ነውና።

 

ክብረቶቼ  አሁን በቀጥታ ወደ ቃለ ምልልሱ እንሂድ። ቃለ ምልልሱን አዳመጥኩተኝ። ዶር መራራ ጉዲና ከመኢሶን ጀምሮ ስላደረጉትም  የነፃነት ፍለጋ ልፋት እና ተጋድሏቸው ገልጠዋል። እኔ እማውቃቸው ከኢተፖድህ ጀምሮ ያለውን ስለሆነ የቀረቡት ጥያቄዎች እኔም ባገኛቸው እምጠይቃቸውን ነው። ለመሆኑ አንዲት ሴት ሊሂቅ ለማውጣት ስለምን እንደ ከበዳቸው ቢጠዬቁ መልካም በሆነ ነበር። 


የኢትዮጵያ የወንዶች ዓለም የፖለቲካ ሊሂቃን በሴት ሊሂቃን በድርቀት የተመታ ምድረ በዳ ስለሆነ። አሁን በተስፋ ይዣቸው የነበሩት ጠ/ሚር አሜኑ አብይ አህመድ ግን ታምርና ገድል እያሳዩን ነው። ተመስገን ብለናል እኔም ብቻ ሳልሆን የሉላዊቷ የመቻቻል እናት የጀርመኗ ጠ/ሚር አንጌላ ሜርክልም በመንፈሳቸው በሴቶች ልቅና ላይ ያለውን ሥር ነቀል ለወጥ የልቤ ሳይሉት አይቀርም።  

 

ውዶቼ እኔ ወደ ቃለ ምልልሱ ዝርዝር ጉዳይ ብዙም አልገባም። ምክንያቱም የዶር መራራ ጉዲና መሃል ላይ ገትሮ ሸብልሎ የማስቀርት ትዕይንታቸውን ስለማውቀው። የሚገርመው ነገር ቀደም የነበረው ትሁት ፊታቸው እና ፈገግታቸው ዛሬ የለም። በዚህ ውስጥ ያዬሁት አንድ ትልቅ ነገር አለ። ይህን ሁኔታ በአቶ በቀለ ገርባም ከእስር ሲፈቱ አይቻለሁኝና። የተሰጠው መዳህኒት ምን ሰልመሆኑ ዘመኑ ባለቤት ስለሆነ እንዳሳቸው የቃለ ምልልስ ዘይቤ እኔም ሸብለል አድርጌ ልተውላቸው። ባለቅኔ አይደሉ ይፍቱት …

 

የሚገርመው ድርጅታቸው ከአቶ ዳውድ ኢብሳ ከኦነግ ጋር አብሮ ለመሥራት ሂደት ላይ መሆኑ አዳመጥናል፤ በዛ ላይ የምጽዕት የጨለማ ቀን እሩምታ የተኮሱበትን የ5 የኦሮሞ ድርጅቶች መግላጫም በህጋዊነት አሉበት፤ እናም ሙልጭ አድረገው ለመካድ፤ ለመሽሎክ ጥረት አድርገዋል ልክ ጋዜጠኛ ክንፈ አሰፋን እንደ ሸወዱት ማለት ነው። 


ቀድሞ ነገር ድርጅታቸው እሳቸው ውጭ ሄዱ አገር ኖሩ መንፈሱ እንዲህ ብትን ነውን? ይህን ያህል ከ አካሎቻቸው ጋር ተለይተዋልን? ይህ ከሆነ ስለምን መሪ ተባሉ?  የድርጅት እኮ መርህ የሚባል ነገር አለው እኮ። እሳቸው ሳያምኑበት የሚሆን አንዳችም ነገር የለም። ለዛውም ዛሬ ማህበራዊ ሚዲያ እንዲህ ዘመን ሲሰጠው። ብቻ በተረብ ሸብለል ማለት እና ጊዜ ሲመጣ ደግሞ ማፍረጥ የተለመደ ነው። ግን እስከ መቼ እንዲህ በድፍን ጉዞ? ኢትዮጵያ ለምን ይሆን እምትፈለገው? ኦፌኮን ኢትዮጵያን ስለምን ይሆን የሚፈልጋት? አይገባኝም እንዲገባኝም አልፈልግም።

 

እውነት ብናገር እኔ በአካል ሳውቃቸው እንዲህ አልነበሩም። „ዕውነቱን ተናግሮ ከመሸበት“ የሚባሉ ግልጥ ነበሩ።  ይህ አዲስ ማንነትን የተጎናጸፉት ከአውሮፓው ህብረት ጉባኤ በኋዋላ ነው። በጣም ግልጽ እና ሰውን የሚቀርብ ትሁት ሰብዕና ነበራቸው። የማይከብዱኝ ነበሩ። ቅልል ብለውኝ የሚሰማኝን ጥያቄ የምጠይቃቸው። ተናግረውም የማይጠገቡ ነበሩ። ዛሬ ደግሞ በዚህ ዕድሜ ሌላ የማናውቃቸው ሰው ሆነዋል። ለውጡን በሚመለከት ተመስገን ነው „ጉልቻ ቢለዋወጥ ወጥ አያጣፍጥም“ ከሚለው ወጥተው „እያጣጣምነው ነው ስጋት እና ተስፋ አለ“ ብለውናል። ሁለት የቦርድ አባላነት ብቻ ሳይሆን ወደ የሚወዱት የመምህርነት ሥራ ተመልሰዋል ይህ መሰለኝ ማጣጣም ያሉት ነገር።

 

·       „ህግ ተላላፊዎችን ጠላሁ“ ልብ አምላክ ዳዊት አለን። እኛስ?

 

አንድ የነፃነት ታጋይ በሰላማዊ መንገድ እታገላላሁ ብሎ አገር ቤት እስካለ ድረስ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ህግ የማክበር ግዴታ አለበት። ዛሬም እሳቸው በዛ ስር ናቸው ያሉት። በሌላ በኩል ድርጅታቸው ህግ ተጣሰ ህጋዊ ያልሆነ ሰንደቅዓላማ አዲስ አበባ ላይ ተውልበለበ ብሎናል እኮ እና ህግ የማይሰራው እነሱ ዘንድ ኦፌኮን ሲደርስ ነውን?

 

እኛ እምንነጋገረው አሁን ጠ/ሚር አብይ አህመድ ጠ/ሚር ከሆኑ በኋዋላ የሚሰጡትን „እኛም አሸባሪ ነን“ ጉዳያ አይደለም። እሳቸው የመጀመሪያውን አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጥሰው ብራስልስ በተገኙበት ጊዜ ሆነ ሁለተኛውን አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጥሰው  ከእስር ከተፈቱ በኋዋላ ወዛቸው ሳያርፍ፤ ሁኔታውን ሳያጠኑ፤ ልክ እንደ ኮበሌ ወጣት ነቀምት ሲሄዱ እንኳን ጠ/ሚር አብይ አህመድ ያችን ቃል አይናገሯትም ነበር። በፍጹም። በተወሰነ ደረጃ አንጻራዊ መረጋጋት ከተፈጠረ በኋዋላ ለዛውም ጥያቄ ተነስቶባቸው ነው ያን ሥንኝ የተናገሩት።

 

ምን ማለት ነው ይሄ? ግንቦት 7፤ የኡጋዴን ነጻ አውጭ ድርጅት፤ የኦሮሞ ነፃ አውጭ ድርጅት በአሸባሪነት ተፈርጀዋል የወያኔ ሃርነት ትግራይ በባላይነት በሚመራው ግንባር በኢህአዴግ። ለእኛ ትክክል ላይሆን ይችላል። ለወሰነው አካል ግን ትክክል ነው ባይ ነው። ጥያቄው ሥልጣኔን ይነጥቁናል ብሎ ይርድ ስለነበር ነው። በሌላ በኩል ያን ጊዜ የሰብዕዊ መብት ተሟጋቹ ፈይሳ ሊሊሳ አገር ቤት ቢገባ ይምሩት ነበርን? ትናንት ዛሬ አይደለም። ችግሩ ታሪክንም የሚዳኙት የአሮሞ ሊሂቃን በዚህ ብሂል ስለሆነ የተለመደ ነው። የ18ኛውን ክፍለዘመን የማድረግ አቅም ከ21ኛው ምዕታ ዘመን ጋር ካልገጠመ አይጥማቸውም።

 

ወደ ቀደመው ምልሰት ሲሆን በዚህም ምክንያት የግንቦት 7 ሊቀመንበር ፕ/ ብርሃኑ ነጋ ሞት ለዛውም ሁለት ጊዜ ተፈርዶባቸዋል። የ አቶ አንደርጋቸው የጠለፋ ትዕዕንትም ነበርንነበት። እና በዛ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ዕገዳ ያን ጥሶ መሄድ ጤነኝነት አልነበረም። ዘገባውን ውጭ ላለ አካላቸው በፋክስ ልከው እሳቸው መቀረት ነበረባቸው። 


የፖለቲካ ሳይነቲስትነት ለዚህ ካለገለገለ ለምን ሊያገለግል ነበር? ተመክሮው ልምዱም ለዚህ ጥንቃቄ ኢንበስት ካልተደረገ ለመቼ ሊሆን ነበር? እያንዳንዱ ልጅ ሲወለድ መክሊት ይዞ ስለሚወለድም እሳቸውም የራሳቸው ጸጋ አላቸው ብዬ አምናለሁኝ፤ ይህን ሁሉ ለማን አበድረውት ይሆን አስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ጥሰው ብራስልስ የተገኙት? የሚገርመው ህግ መጣስን አሁንም ትክክል ነኝ ባይ ናቸው። ያሳዝናል።  

 

 በዛ ጉባኤ ከተገኙ ደግሞ ጊዜው እስከያልፍ ድረስ ሳይመለሱ ውጭ አገር መቀመጥ ነበረባቸው። ነገር ግን የታሰበው በታሰበው መልክ ሄደ ወይ ለሚለው የተጠበቀው አንቦ አንበሳው ነበር፤ ጸጥ ረጭ ያለ ሁኔታ ነበር የታዬው። ከዛ ነው የቆሼ ትዕይንት የተከተለው። የቆሼ የመከራ ትዕይንት ይህ በማን ተከናወነ ለሚለው ሙያዬ አይደለም፤ ታሪክ አንድ ቀን ያወጣዋል።

 

ሲታሰሩ እኔ ወደ ሞት የገሰሰገሰ ኢትዮጵያዊ ማንዴላ ብዬ ጽፌ ነበር። የስኳር በሽተኛ መሆናቸው እራሱ እረፍት የማይሰጠኝ ነበር። ሲፈቱም እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ ዜጋ ደስታችን ወደር አልነበረውም። መፈታታቸው ብቻ ሳይሆን የጀርመን መንግሥት ራሱ የሰጠው ክብር ከልቤ የገባ ነበር። ያም የሆነው የአማራ የህልውና የማንነት ተጋድሎ ውጤት ነው። ምክንያቱም ተፎካካሪዎች ለመጀመሪያ ጊዜ ወጉ ደርሷቸው፤ ክብር አግኝተው ከመቻቻል ሉላዊ እናት ከጠ/ሚር አንጂላ ሜርክል ጋር የመወያዬት ዕድሉ ስለነበራቸው ከልብ የገቡ፤ ቀልብም የሳቡ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል።

 

ጉዝጓዙ ግን ሲዊዘርላንድ የተሠራ የተከደነ ሲሳይ ነበር። የጎንደር ቅዳሜ ገብያ የጎንደር መቃጠል ማለት ነበር፤ የ አርበኛ ንግሥት ይርጋ እስር ቋያ ነበር። ይህው አሁን ሰብበሰባ ላይ የምትገኘው እሷ ብቻ ናት። ሌላ ወጣት ሴት እዛ አካበቢ የመተከት ስራ አልተሰራበትምና። ስለዚህ ዓይኔ ስለነበረች ቁጣዬ ልክ አልነበረውም። በ27 ዓመት ውስጥ የወጣች ለግላለጋ የፖለቲካ አቅም ስለነበረች። የሆነው ሆነ የተገኘውም ስኬት ነበር።  

 

የተባባሩት መንግሥታት ድርጅት የቀድሞው ጸሐፊ ከሬቻ ጭፍጫፋ ማግስት ወጥተው ሶልዳሪቲ አሳይተዋል። ያም ሲዊዘርላንድ የተሰራ ሥራ ነበር። መረጃውም ምን እንደተላከም በእጄ ይገኛል። አያቃልሉት የአማራን ተጋድሎ እንደ ማለት ነው። „ጣና ኬኛን ኢትዮጵያዊነት ሱሴንም“ ለግብ ያበቃው የአማራ የማንነት የህልውና ተጋድሎ ነው። በውጭም በአገር ሌት እና ቀን ተግተንበታል በሁሉም ዘርፍ በሎቢም በብራናም። ካለ አማራ ታገድሎ የኦሮሞ ፕሮቴስት የትም አይደርስም ነበር። ካለ ገዱ ደመቀ የለማ አብይ ትልም እብድ የዘራው አዝመራ ሆኖ ነበር የሚቀረው ተጋድሎው። መሪ አጥቶ እኮ ነው ቅንጅት መራራ ስንብት ያደረገው። ይህ እኮ ዛሬ ትናንት የነበረ ታሪክ ነው … መሬ ሲያገኝ ህዝባዊ ተጋድሎ አጀብ ያሰኜ ተግባር አይን እያዬ ነው። በዬእለቱ እሸት።  


·       የተፈቀደ ድጋሚ የእስር ራህበተኝነት፤

 

ለድጋሚ እስር ደግሞ ዶር መራራ ጉዲና ሁለተኛውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሽረው ከአቶ በቀለ ገርባ ጋር ነቀምት ተገኙ።  የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን በመጣስ ሪከርድ የሰበሩ የፖለቲካ ሳይንቲስት ቢባሉ ዶር መራራ ጉዲና ናቸው። ለህግ የማይገዙ። ለዛውም የራሳቸው መንፈስ የልቤ የሚሉት ማህበረሰብ ሙሉ ድጋፍ ላይ እያለ። እናም ነቀምት ላይ ታገቱ ተባለ። እነዛ እስረኞችን ለማስፈታት ጉርቦ ለጉሮቦ የተናናቁት መልሰው ደግሞ ሄደው ቀለበት ውስጥ ሲገቡ ምን ይበሉ። የህጻን ሥራ እና ውቂ ደብልቂ ነበር። ጎንደሮች ይህንን „ልጅ ያቦካው ለራት አይበቃም“ ይሉታል።

 

ከእስር ሲለቀቁ እስሩ እንደ መያዦ ይፈለግ ስለነበረ የምሥራች ታዳሚ ያልነበሩት ሁሉ ሲታገቱ ርዕሰ ዜናቸው ሆነ። የሚገርመው በሳቸውም ጉዳይ ሆነ በአቶ በቀለ ገርባ የጻፍኩት ጹሑፍ ላይ የራሳቸው ሰዎች እንኳን ሸር ለማድረግ ፈቃደኞች አልነበሩም።

 

የሆነ ሆኖ ያን ውጥረት ለመጨመር እና ለማፈንዳት ስለምን ተፈለገ ለሚለው፤ በግልጽ ቋንቋ ሙሽርነት ሳያስፈልገው ዕውነቱ በግርግር የሽግግር መንግሥት የመመስረት ትልም ስለነበረ ነው። ውጭ አገር ጄኒራሌ የሚሉት አቶ ጃዋር መሃመድ እሰከ ሰራዊቱ ይገፋል፤ ሌላውም የአዬር ላይ ተስፈኛው ያጅባል፤ ባለመጎዱ ሁሉ ያሟሙቃል የጥገናዊ ለውጡ መንፈስ አከርካሪ ለመስበር፤ ለማደናቀፍ ሆን ተብሎ ታቅዶ የተከወነ ነበር፤ እንጂ ከዛ ሁሉ የጭብጨባ እና የአጀብ ማህል እንደገና ሌላ ክብር እና ዝና የሚያስፈልግ ሆኖ አልነበረም። ለዛውም አላዛሯ ኢትዮጵያ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ላይ ሆና። ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ጎንደርም ጎጃም ሄዶ አይቻለሁኝ። የጋበዙት 5 ወገኖች ብቻ ነው የነበሩት። ኋላ ላይ ወሎም ሄደው እንደ ነበር ሰምቻለሁኝ። አዩ ልዩነቱን። አንዱ ፍላጎቱን በአደብ ሲከውን ሌላው ደግሞ በአፍላ ወጣት ስሜት።

 

እውቅና ለኦህዴድ ላለመስጠት ብዙ ተጉዛችኋል። የእናንተ የፖለቲካ የተግባር መስክ ያልቻለውን ለሞከሩ የራሳችሁ ወገኖች መደገፍ ሲገባ መሰንጠቅ ነበር የተያያዛችሁት። ማሳጣት ነበር የተያያዛችሁት። ያ ለኦሮሞ ህዝብ ታስቦ ሳይሆን ያው የ4 ኪሎ ወንበር ምኞት ነበር ትርምሱ። ነገም ያ ምርጫ ተብዬው ሲመጣ የሚሳካላችሁ ከሆነ ይቅናቸውሁ ብለናል …

 

ነቀምት ስትሄዱ ያን ረብ ያለ የተረጋጋ መንፈስ ወለጋን አሳምጻችሁ ነበር የተመለሳችሁ። ለዛን ጊዜ ለኦህዴድ ፈተና ነበር። መዋቅራቸው ችግር ገጠመው። አንጀት የርህርህና አልነበራችሁም።  በዛ ጭንቅ እያሉ እነዚህ የአገር ጌጦች ሌለ ፈተና ሰርታችሁ ደግሞ ፍዳቸውን አስከፈላችሁ። በምስራቁ የአገራችን ክፍል 700 ሺህ ህዝብ ተፈናቅሎ በሌለው አቅጣጫ 50 ሺህ የሙያሌ ተፈናቃዮች የተወሰኑት ወደ ኬኒያ እዬተጓዙ እዬተሰደዱ ዶር መራራ ጉዲና የሚመሩት የኦፌኮ ቡድን ደግሞ ያን ጫና በመፍጠር ኦህዴድን አደናቅፎ ለመጣል ያሴሩት ሴራ ነበር። ከዛ በኋዋላ ወለጋ ልቡ ሸፈተ። 


ደንቢ ደሎ እነ ዶር ለማ መገርሳ እና ዶር አብይ አህመድ ሲሄዱ አኩርፎ ነው የተቀበላቸው፤ አሁንም ኦነግን እንኳን ደህና መጣህልን ባይም ሆነዋል። መስሏቸው ነው እንጂ ዶር መራራ ጉዲና ጠ/ሚር ቢሆኑ እንኳን ደንቢ የራሷን ንጉሥ ብቻ ነው የምትፈልገው። ይህንንም በተደጋጋሚ ጽፌያለሁኝ።

 

ዶር ለማ መገርሳ እና ዶር አብይ አህመድ አንድ ወጥ አንድርገው ሲመሩት የነበረውን የኦሮሞን የተስፋ መንፈስእነሱ ከተፈቱ በኋላ ተረተሩት። አሁን ደግሞ አቶ ዳውድ ኢብሳ ፈለጡት። ነዋሪዎቹ እኮ ለማን፤ አብይን፤ አማራን ብትነካ ወዬልህ ብለው ድንቅ ትዕይነት ነበር ያሰዩት። ግን ምን ይሆናል „በጥባጭ ሳላ ማን ጥሩ ይጠጣል“ ሆነ የአሁኑ መከራ እርሾ ራሱ ኦፌኮን የፈጠረው ስንጥቅ ነው። ነቀምት ውስጥ የነበሩ የኦህዴድ መዋቅሮችን አነቃንቀው የታደሉን መከራ የሚጋሩ ነፍሶችን ለድጋሚ እሮሮ አሰናድተው ነው የተመለሱት ዶር መራራ ይሁኑ አቶ በቀለ ገርባ።

 

ህግ የሚዳኘው በዬዘመኑ ባለው ሁኔታ እንጂ አሁን ባለው አይደለም፤ ሊሆንም አይችልም። አንድ የአገር መሪ መጀመሪያ ራሱ ከማን አልብኝነት የህሊና አመጽ ወጥቶ ለህግ ለመገዛት፤ በህግ ሥር ለመሆን መቁረጥ ያለበት ድርጅት ብሎ ማንፌስቶ የቀረጸ ዕለት ነበር። ይህን አላዬንም በዶር መራራ ጉዲና ይሁን በአቶ በቀለ ገርባ። ማንም ሰው ደግሞ ከምድራዊም ከሰማያዊ ህግም በላይ አይደለም። ህግ የማይገዛው አገርም ህዝብም የለም።

 

·       የእስር ቤቱ ሌላው ድራማ።

 

በኦህዴድ ላይ ጫና ለመጨመር የብሄራዊ የለውጡ መሪ አካላት ተስፋ እነሱ ስለሆኑ መጥተው ለክሳችን ምስክርነት ካልሰጡ ተብሎ ሁሉ አንድ ልዩ  ወከባና ጠንከር ያለ ዘመቻ በማህበራዊ ሚደያም ነበር። ስለምን እነሱን በህዝብ የማስተፋት ተልዕኮ ስለነበር። አልመሰክር አሉ የኦሮሞ ልጆች በእስር እየማቀቁ ለማስባል እና አመጽ ለማስነሳት።  „ለማ ፊቱ ኦሮሞ ይመስላል“ ቅኔውም ይኸው ነው። ፊቱ እንጂ ውስጡ … የጥያቄ ምልክት።

 

ይህን ካነሳሁት አንድ ነገር ልበል ኢንጂነር ታከለ ኡማ የኦሮሞ ወጣቶችን ለይተው አዲስ አባባ ላይ ስበስበው ነበር። እና አንዲት ወጣት ተነስታ ጥያቄ ስትጠይቅ„ ሰዎች አንቺ ኦሮሞ አትመስይም ይሉኛል ኦሮሞ መልኩ ምን ይመስላል?“ ብላ ጠየቀች፤ እንግዲህ የዶር መራራ ጉዲና አስተምህሮ ይህን አጠናክራችሁ ቀጥሉበት ነው። ለእኔ ኦሮሞ የሚመስለው ሰው ነው። በቃ። ቀይ የደም ሴል እና ነጭ የደም ሴል ያለው።  

 

ብቻ አውሎ ያሳድራል ኦህዴድን ጠልፎ ለመጣል የነበረው አሳር፤ የተኖረ ተኑሮ እነዚህ የለውጥ ሐዋርያ የሚባሉ ዶር ለማ መገርሳ፤ ዶር አብይ አህመድ፤ ዶር ገዱ አንዳርጋቸው፤ ዶር አንባቸው መኮነን አሁን ደግሞ አብረው እንደ ነበሩ የሚነገርላቸው አቶ ደመቀ መኮነን ጭንቅ ላይ ነበሩ ያን ጊዜ። እሰረኞችን የማስፈታት፤ ማዕካላዊን የማዘጋት፤ የሥልጣን ሹም ሽር ያመስደረግ፤ የአብዮታዊ ዲሞክራሲን ሂደት እና ጥፋቱን የመመርምር፤  መንገድን የማስተካካል፤ ሰፊ ታገድሎ ላይ ነበሩ። ስላለፈ እንዘነገዋለን። ዓይናቸውን ስታዩት እኮ እንቅልፍ የሚባል አንዳቸውም አልነበረም። የነጻነት ፈላጊው ደግሞ በእስር ቤትም መጥተህ መስክር አለበት፤ ውጭ ያለውም ብዕር የጨበጠ ሁሉ፤ ማይክ ያለው ሁሉ፤ ሚደያ ያለው ሁሉ ያዋክባቸው ነበር።

 

ወያኔ ሃርነት ትግራይ ጡረተኞቹን ሁሉ ሰብስቦ ግስላውን አቶ ጌታቸውን አሰፋ አሰልፎ በዬቤታቸው ጫና ፈጥሮ ልጆቻቸው ሁሉ ከት/ቤት በተቃቡበት ወቅት ነው ለማ እና አብይ ለምስክርነት እንዲጠሩ እንፈልጋለን የተባለው። ለዚህ ብአዴን በፍጹም ሁኔታ ዕድለኛ ነው። ብዙ አናውክበውም። እኛ ለብአዴንን አደብ አብዝቶ አለን። ወደፊትም ቢጠነክርለን እኛ ሦስት አራት ድርጅት ምን ያስፈልገናል። የአማራን ዬህልውና ታገድሎን ድምጽ አድምጦ እኮ ነው ለውጡን እዚህ ደረጃ ያደረሰው።

 

መስዋዕትነቱ ባክኖ እንዲቀር አላደረገ፤ የኮ/ ደመቀ ዘውዱን ክብር በ አሳሪ ሽፍቶች ቁርሾ ያላስደፈረ፤ የቀደመቱን ትውፊት በክብር ያስጠበቀ ጥቃት ያላስገባ ነው።  ስለዚህ ለ እኛ ሊቆ ዲሞሳችን ነው። አቅም ነው እምናዋጣለት እኛ። ጣና ኬኛን ሲቀብል እልል ነው ያልነለት። አባይ ኬኛን ሲቀበል ብዕሩም ብራናውም አልበቃን ነው ያለው ዓይናችን ሁሉ ነው የሳቀው። ጠ/ሚር አብይን ድምጹን ሳይከፋፍል ሲሰጥ አቶ ደመቀ መኮነን ራሳቸውን ከእጩነት ሲያገሉ እልል ነው ያልነው። የዚህ ሁሉ ትምክህትም መሰረቱ ምንጩ ይህው ነው። ዛሬን ያስገኘው በትልቁ ብአዴን እና የ አማራ ይህልውና ተጋድሎም ነው። አከርካሪ ነው ለነጻነት ውጤታማነት።   

 

ብቻ ኦፌኮን በዚህ ውስጥ የሚታዬው የሴራ ሁኔታ ለነፃነት ትግል በሸታ የመሆን አባዜ ነው የታዬበት። ተናዳፊ ሆነ። በዛ ላይ ዶር መራራ ጉዲና የስኳር አቶ በቀለ ገርባ ደግሞ የደም ግፊት ስላለበት አቶ በቀለ ገርባ ዓይኑ ችግር ቢፈጠርበት ወዮም ነበረበት። ተፈተውም እነዚህ ብልሆች ዶር ለማ መገርሳ እና ዶር አብይ አህመድ በአንድ መንፈስ ያደራጁትን የኦሮሞ ልጅ ነቀምት ሄደው  የኦህዴድን መዋቅሩን እንኩትኩት አደረጉት። ህግ ጥሰው ነው የተገኙት። ይህ በዶቼሌ፤ በቢኦኤ ከሚሰጡት ማጣጣል በላይ ነበር። ከልባቸው የሚገባ አንድም ነገር አልነበረም። ለውጡን እኛ እንመራው ድሉም የኦፌኮን ይባልልን ነበር። ድሉ ግን የግንጭ አብዮት እና የጎንደር አብዮት ያስገኙት ነበር። አድማጩም የገዱ መንፈስ እና የለማ መንፈስ ነበር። ሃቁ ይኸው ነው።

 

ቀድሞ ነገር ያ  እሳቸው እዳሪ ያስቀመጡት እንደ ምናምኔቴ ያዬት የአማራ ተጋድሎ ገናና ተጋግድሎ እና ሽዋ አንቦ ላይ እንጅ  ገርቤ ጉራቻን እንኳን አልጨምረም የኦሮሞ ተጋድሎው ያን ባያዳምጡት እነዚህ ብርቆች ግራቀኙ ያን አቅም ለመጠቀም ባይታትሩ ከዚህ ደረጃ ዛሬ አይደረስም።  ሌላ በዚህ ላይ ላነሳው እምሻው ከግንጫ አብዮት በፊት 500 የጎንደር ወጣቶች በ2014 „የፈራ ይመለስ“ የሚል ቲ ሸርት በራሳቸው ወጪ አሰናድተው አደባባይ ላይ ወጥተው ነበር። የግንጭው ካዛ ቀጥሎ በሆዋላ እንዲያውም በዓመቱ የተከናወነ ነው። እኔ ለመጨረሻ ጊዜ የተገኘሁበት የኢሳት ፈንድ ራይዚንግ የሄድኩትም መሰረታዊ ምክንያት የመይሳውን 500 የትውፊት አርበኞች ሥም ለማስጠራት ነበር። በእነሱ ሥም የድርሻዬን ለማድረግ።

 

·       አሁን ኦን ላይን መንገድም ትምህርትም በሽ ሆኗል ዕድሜ ለዘመነ አሜኑ!

 

መሪነት ምን ማለት እንደሆን ሁለችንም ቁጭ ብለን እዬተማርን ነው። የማድርግ አቅሙ እኮ እንደሌለ ቢሮውን በማዬት ብቻ መወሰን ያስችላል። ሰው ከራሱ ነው መጀመር ያለበት። በሚኖርበት በሚሠራበት አካባቢ ኑሮውን እንዴት ይመራል ነው ፍሬ ነገሩ። ያ ዝርክርክ ቢሮ እና የኢትዮጵያን ዝርክርክ ያለ መልክ ያልያዘ ፈተና ሲታሰብ ምን እና ምኑን ማገናኘት ይቻላል? የኢትዮጵያ ችግር ዝርግፍግፍ እያለ ነው እያዬነው፤ ይህን መምራት ማስተዳደር እንዲህ በቀልድ የሚቻለውን? ለዛውም ሁሉም ሳይጎድልበት ነው የአሁን የማስተዋል መርህ ብልሃት እዬታዬ ያለው፤ በዝግታ፤ በስክነት፤ በክህሎት በልበ ብርሃንነት።

  

የአብዮታዊ ዴሞክራሲን ቅስም የሰበረው የኦህዴድ ውሳኔ ነበር፤ ጥሪ ያቀረበ። ያን ውሳኔ በጥንቃቄ እንደሚዩት ሁሉ ተንጠራርተውበት ነበር። በባዶ አዳራሽ እርቅ ድርድር ሲሉ ተከዝነው እንዳልኖሩ ሁሉ። ምርጫ እያሉ ለዛ ለእርግጫ ዘመን አብረው ሲሰለፉ እንዳልነበሩ ሁሉ። የእነሱ ልጆች ኑልን ሲሉ ፊታቸውን ነበር ያዞሩባቸው።

 

 ሌላው ቀርቶ በጥረታቸው መንፈሱን አንድ ያደረጉት የኦሮሞ ማህበረሰብ በአቀባባሉ ላይ በዝቶ ሲገኝ ተደባልቋል ነበር የተባለው። ለእነሱ የፓርቲ ደጋፊያቸው ብቻ ነበር ወይ መቀበል ያለበትን? ለነፃነት ግርዶሽ አለውን? ለደስታ ግንብ ይሰራለትን? ባያውቁት ነው እንጂ እኛ ቤታችን ውስጥ ስንት ሻማ ጨርሰናል። አንድነቱን እራሱ የኦሮሞን አይፈልጉትም ሊሂቃኑ። በዬማንፌስቶው መታኩሱ ነው እረፍት የሚሰጣቸው ማለት ነው። የኦሮሞ እናት ደግሞ በዬዘመኑ ማንፌሰቶ አለኝ ላለው ሁሉ ማህጸኗን ትገብር፤ ለእነሱ በቃኝን ለማያውቀው የዝና አክተርነት።  

 

የአማራ እና የኦሮሞን አንድነት በሚመለከትም እነሱ „የእኛ ናችሁ ይሉናል ዕውነት ይሁን ውሸት አናውቀውም“ ነበር ያሉት ዶር መራራ ጉዲና። አሁን ይህን አውሮፓ የሚኖረው ኢትዮጵያዊ ሲሰማ ምን ይላቸው ይሆን? አሁን እኮ ነው ከሚኒያ ጋር እርቀ ሰላም ወርዶ ተጋባዥ እንግዳ ሲሆኑ የሰማነው። በዛ ክፉ ጊዜ ግን እኛ ነበርን አጋዣቸው፤ የመንፈስ ማረፊያቸው። እና ይህ ሁሉ ሲጠቃለል ብሄራዊ መሪ ለመሆን እጅግ ይከብዳል። አገር ግልጽ ልጅን ትሻለች፤ በዬዘመኑ አቋሙ የማይለወጠውን ወስጧ ያደረገ ብልህ የማስተዋል ብርሃን ትፈልጋለች አላዛሯ ኢትዮጵያ። እግዚአብሄር ይመስገን በዬሄደበት ሁሉ አግሩ ለምለም የሆነ የአሮን በትር እዮር ሰጥቷቷል።

·       የትውልዱ የብክነት ፍዳ።  

 

አንድ ሰው ፍጹም አይደለም። ስህተት ይሰራል። ስህተቱን የማይቀበል ግትር መሪ ለትውልድም ፍዳ ነው። የትውልዱ አብነታዊ መሪ የሚስማማበት ማጣቱም በዚህ ምክንያትም ነው። አሁን እሳቸው አስተማርኩት የሚሉት የፖለቲካ ሊሂቅ ሆነ አክሰሱ ያላቸው ታዳጊ ወጣቶች ከእንሱ ምን ይማሩ? የላቁ ሲመጡ እንዲህ ማቄን ጨርቄን እዬተባለ።፡

 

ማንም ሰው ከህግ በላይ አይደለም አይሆንም። እሺ ይሁን ያን ህግ ጥሰው ሲሄዱ አንድ አጋዚ አባል ልክ ባህርዳር ላይ እንደሆነው በተኩስ እሩምታ ነቀምት ላይ ቢጨርሳቸው ወይንም አካላቸውን ቢያጎድለው የማን ያለህ ሊባል ነበር። ለነፃነት፤ ለፍትህ የምትታገል ሰው አንተ ህግ አፍረስህ ለሚደርሰው ማናቸውም ነገር ተጠያቂ አንተው ነህ። ብቻ በኢትዮጵያ ፖለቲካ አጠፋሁ ተሳሳትኩ ይቅርታ ብሎ የሚጠይቅ ሊሂቅ አይቼ አላውቅም። ሁሎችም ትክክል ናቸው፤ ሁሎችም ከሰማዬ ሰማዬት የወረዱ ባለክንፍ መላዕክታን ናቸው¡እንደ ገናም ከህግም በላይ።

 

ሌላም አንድ ነገር ላንሳ መቼም አቶ በቀለ ገርባ የዛሬን አያድርገው እና እኔ የፍቅራዊነት ሐዋርያ አድርጌ ነበር የማያቸው። የሚገርመው አዲሱን ሰብዕናቸውን እስከ አሁን ድረስ ልለምደው አልቻልኩም። የሆነ ሆኖ እስር ቤት እያሉ ባባዶ እግራቸው መሄድ፤ መዝሙር በችሎት ላይ መዘመር ጥሩ ነው። ለዳኞች አለመነሳት ግን ጸያፍ ነው። ህግ አለ ህግ የለም መንግሥት አለ መንግሥት የለም አይደለም ጉዳዮ ኢትዮጵያ በተጻፈም ባልተጻፈም ህግ የምትተዳደር አገር ናት።

 

‚በህግ አምላክ‘ ሲባል እንኳን ሰው ወንዝ ይቆማል የሆነባት የትውፊት አገር ናት - ኢትዮጵያ፤ በዛ ላይ ለዓለም ዴሞክራሲን በገዳ ሥርዓት አስተማርንም አለበት እና ገዳ ይሄ ነውን? ዳኞች ሲመጡ አልተነሱም፤ ስለዚህም 6 ወር ተጨመረባቸው፤ እነ ለማ አብይ ደመቀ ገዱ አንባቸው ደግሞ እነዚህን ሰዎች ለማስፈታት አይፈቱም ካለው ቡድን ጋር ግብ ግብ ገጥመዋል፤ በተጨማሪ ቀደም ብዬ እንደገለጽኩት የደም ብዛት ስላለበት አቶ በቀለ ገርባ ካልተፈታ ወዮ ይላል የጃዋር ሚዲያ ደግሞ፤ ህሊና ያለው ሰው፤ መንፈሱ ከራሱ ጋር የሆነ ሰው፤ ይህን ይመዝነው በኦህዴድ ላይ ጫን ተደል ጫና ለመጨመር የተሄደበት የማሰናከያ መንገድን። ቀርበው ይመስክሩ፤ በቀጠሮ ቀን ለዳኞች አለመነሳት የእስር ጊዜ ተጫማሪ ቅጣት መኖር እዩት ውጥረቱን … ፍርድ ለራስ ነው። 


ኦህዴድን የወያኔ ሃርነት ትግራይ ከታገለው በላይ በድምጽ አልባው አመጽ ኦፌኮ ፈትኖታል። እንደ ባላንጣ ነበር ያያቸው። ያዙት ምሩት ቢባሉ እኮ ዕድሜ ልክ ታይቷል። ሙሉ መሰናዶ ያደረገው አንበሳማ እዬሳዬ ነው።

 

ብቻ የተፈለገው የተጠነሰሰው ኢህአዴግን ሙሉውን ደርምሶ የራስን መንግሥት ማቋቋም ነበር። ያ ቢሆን ደግሞ የ5 የኦሮሞ ድርጅቶች በዬዘመኑ በፈጠሩት መልክ የጨለማውን ጊዜ ማሳወጅ ነበር። እነዚህን ዓለምን ጉድ ያሰኙ መሪዎችን አስወግዶ የራሰን ልዕለና፤ለ የራሰን ኢጎ ማፋፋት ነበር የተያዘው። 


ነገር ግን እግዚአብሄር ደግ አምላክ ነውና በአራቱም ማዕዘን የተጠመደውን ቦንብ በጣጥሰው ዛሬን ከዚህ አደረሱ ጀግኖቹ አምስቱ ሐዋርያት። አሁን በርከትከት ብለዋል። በሌላ በኩል ቅብዕ እዮራዊ ነው። የታደለ ብቻ ነው የሚያጘኙት። ያልታደሉት እንደተመኙት ተንጠልጥሎ መቅረት ነው። ቅብዕው ካለ ደግሞ አጋጅ የለውም። ብቻ ትግሎ ኦፌኮ ከፈጣሪ ከማድረግ አቅም በላይም ነበር።  

 

ሲያድርጉት የነበረው ትብትብ ኢንትሪግ ሊጸጽታቸው፤ ሊቆረቁራቸው ይገባል። በጣም ኦህዴድን የተፈታተኑን እነሱ ኦፌኮኖች ናቸው። ኦህዴድ እነሱን ለማቀፍ፤ ለማቅረብ ጥረት ቢያደርግም የእነሱን ልብ ግን የሚገኝ አልሆነም። ውጭ አገር ወጥተው ነበር ዶር መረራ ጉዲና ጽፌበትም አለሁኝ፤ „የተጽዕኖፈ ፈጣሪዎች መንግሥት መቋቋም“ አለበት ሁሉ ብለዋል።

 

https://sergute.blogspot.com/2018/07/blog-post_26.html

አዲሱ የፕሮፌስር መራራ ጉዲና የተጽዕኖ ፈጣሪ አንድነት መንግሥት ሽል።

 

የኢትዮጵያ ህዝብ እኮ ኑሮበታል። በተረብ  ወዘተረፍ ብሄራዊ ችግርን መምራት አይቻልም። አገር ናት ኢትዮጵያ። ከአብይ የበለጠ መሪ ሊገኝ ለዛውም። ዶር አብይ አህመድን በ100 ዓመትም አናገኛቸውም። ሁለመናቸው ከመሪነትም በላይ ነው። ብቁ ናቸው። ሰው ስለሆኑ ሮቦት ስላልሆኑ እንደ ሰው መሳሳታቸው ደግሞ የሚፈለግ ነው። ሰው ናቸዋ!

 

እንደ ፖለቲካ ሳይንቲስቱ እንደ ዶር መራራ ጉዲና ዕሳቤ ተጽዕኖ ፈጣሪ እንግዲህ እራቁት መሄድም ሚሊዮን ፈን ያስገኛል። የዛ ስብሰብ ኢትዮጵያን ያህል አገር ይምራ ብለውን ነበር። ያልተመቻቸው ነገር የህዝቡ ድጋፍ ልዕልና ምኞታቸውን ጣሪያ አስነካው እና እኛም አናርፍም አገር መምራት ይችላሉ እያልን ስለምንቸከችክላቸው ያልተገባውን ምስል እራሳቸው ለራሳቸው ሰጡ እና „ጉልቻ ቢለዋወጥ ወጥ አያጣፍጥም“ ብለው ኦፌኮኖች ተነሱ። ለውጡንም በመረበሽ፤ አቅሙን በመፈታተን ሰፊ ተጋድሎ አድርገዋል ህግ እዬጣሱ።

 

ህግ የሚባለው የወያኔ ሃርነት ትግራይ እና አሁን አብረው የሚሠሩት ኦነግ ያሰናዱት ነው። ስለዚህ ወገኖቻቸው መክረው እና ወስነው ላጸደቁት ህግ መገዛት ግድ ይላቸው ነበር። ይህም ይሁን እንደ ሌላው ሁሉ ይህን ሸብልለው ለመሄድ ያደረጉት ጥረት ቢያስገምታቸው እንጂ ክብራቸውን ሊያስጠብቅ አይችልም። እውነት ነው ክብር፤ ራስን ማረም ነው ክብር፤ ራስን ለማረቅ መሰናዳት ነው ግርማ ሞገስ። ይኸው ሞጥረን የምናከብራቸው ሁሉ እዬሞገትናቸው ነው።

 

የድሮ ትህትናቸው እንጂ ይህ ልኩን ያለፈ በራስ የመተማመን፤ የ አልደፈረም ስህትት አይነካካኝም ጉዳይ ማንንም አልጠቀመም። አሁንማ እንደ ወረርሽኝ መለያቸው እዬሆነ መጥቷል። የብዙዎችን ጹሑፍ ቃለ ምልልስ ሳዳምጥ። ዝቅ ማለት ያስፈልጋል። ትህትና ነው ክብር። አንድ ሰው በህይወቱ ውስጥ የመጀመሪያ መርሁ ከህግ በላይ አይደለሁም ብሎ ነው መኖርን መጀመር ያለበት። ከዚህ ከወጣ ሰብዕናው ይጓደላል። እስኪ አሁን አንዱን ሰው መንገድ ላይ በጥፊ ይምቱ እና ህግ ይምራቸው እንደሆን ያዩታል። አስከ አሁን መቼም ተቆላምጠዋል። አቶ በቀለ ገርባ እኮ በኦህዴድ ጉባኤ ላይ ፕሬዚደዬሙን አድሬስ አላደረጉም። ያሳፍራል!

 

እርግጥ ነው ራሱን ጠ/ሚር አድርጎ ለሾመ የተገባ ይመስላል። መታበይ ከረፋ። ይህን የባከነ ትውልድ መልሶ መንፈሱን ለማባከን መታበይን ማስተማር ከአንድ የእውቀት አባት ወዮልሽ ቤተ ሳይዳ ነው። አባቴም ሆነ ታላቅ እህቴም መምህራኖች ናቸው። መምህርነት ትልቅ የትውልድ ሃላፊነት ነው። መምህርነት ቤተሰብነትም ነው። መመህር ህይወቱም ትውልድን ያስተምራል።

 

አሁንም ህጉ ያው የወያኔ እና የኦነግ ማህበርተኞች የሠሩት ነው የሚአስተዳድረው። አስቸኳይ ጊዜ አዋጅም ቢሆን ለውጡን ለመገደብ ተብሎ የወጣ ቢሆንም እስከ ወጣ ድረስ ግን ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ዜጋ የማክበር ግዴታ አለበት። ፈረንሳይ ለተራዘመ ጊዜ በበዛ የአሸባሪዎች ደባ ስትናጥ በተደጋጋሚ አውጥታለች። ዜጎቿም ቀጥ ሰጥ ብለው ያነን ያከብሩ ነበር።

 

የሚገርመው ህግ ተፈጻሚነቱ በአውጪው አካልም ጭምር ነው። ይህን ኢትዮጵያ ውስጥ የማዬት ዕድሉ አልነበረነም። እንዲያውም እኔ ፋክልቲውን ለምን አይዘጉትም ብዬ እጽፍ ሁሉ ነበር። አሁን ተጠያቂነት እና ሚዛንን ይህን እያዬን ያለነው ሰሞኑን ነው፤ ይህን የሌለ ነገር ለማስከበር ነበር ተፎካካሪ/ ተቀናቃኝ/ ተቃዋሚ የሚባሉ ድርጅቶች የተመሰረቱት፤ እነሱው እራሳቸው ህግ ጣሽ ሆነው ህግ አስከባሪ ለነገ ለትወልዱ ይሆናሉ ብዬ እኔ አላስብም። ህግ ማክበር ከራስ ነውና የሚጀምረው። ቢያንስ ትክክል አልነበረም የሠራሁት ማለት ማንን ይገድላል?  

 

በጥቅሉ ኦፌኮ ለኦህዴድ/ ለኦዴፓ እንደ ሥርጉተ ሥላሴ ዕይታ ተፎካካሪ ፓርቲው ሳይሆን ተቃዋሚ ፓርቲው ነው። ጫና በመፍጠር በማሳጣት፤  ተፈንግሎ እንዲወድቅ ተግቷል። ሲተጋ ከመድረክ ጋር ነው። ኦዴፓ ደግሞ ከአዴፓ ጋር ስለሆነ አለተቻላቸውም። ወደፊትም ኦዴፓ ለአዴፓ ጋር ያለውን የሰመረ ግንኙት በባላይነት ሳይሆን በእኩልነት ላይ የተመሠረተ ግንኙነቱን ካጠናከረ ለቀጣዩ ምርጫ ለድል ይበቃል። አማራ ክልል አዴፓን ይመርጠዋል፤ አዴፓ ተመረጠ ማለት አብይ በጠ/ሚርነት ቦታው ቀጠለ ማለት ነው። ለዚህ ደግሞ በተከታታይ ሥራዎችን እኛ እንሰራለን። ማን ወጥቶ ማን እዛች ቤተ መንግሥት ሊገባት።

 

ስለድርጅታቸው ጥንካሬ ቢተውት ይሻላቸዋል ዶር መራራ ጉዲና። አንድ ሚዲያ እንኳን በሥማቸው ለማደራጀት አቅሙ ሃሳቡም ፈጠራውም አልነበራቸውም። አንድ አዲስ መሪም ማውጣት አልተቻላቸውም ይህን ያህል ዘመን እሳቸው አንቀው በያዙት ድርጅት ውስጥ፤ ትናንትም እሳቸው ዛሬም እሳቸው። ለመሆኑ በራሪ ጹሑፍን እንኳን አስበውት ያውቁ ነበርን? አንድነት ፓርቲ ልሳንም እንደነበረው ይተወቃል። ብቻ „ከእውር ቤት አንድ አይና ብርቅ ሆኖ“ ካልሆነ በስተቀር ስንት እሳት የላሰ ትንታግ ወጣት ላፈራች አገር ብዙ መመጻደቅ አይገባም መድረክ ደግሞ ምኑ አለና? ለመሆኑ ነፍሱ አለችን?

 

እራሳቸው „የተጽዕኖ ፈጣሪዎች አንድነት መንግሥት“ እንመስርት ባሉበት ጊዜ ያቀረቡት ምክንያት „ተቃዋሚዎች አቅም ስሌላቸው“ ነበር ያሉት። አቅም እኮ የሄደት ውጤት ነው። አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ተነሳ እነሱ ግን ውጭ አገር ነው የባጁት። ሌላው ቀርቶ 700 ሺህ ህዝብ የተፈናቀለበትን ቦታ እና እንመራዋለን የሚሉት ህዝብ የጉስቁልና ሁኔታ፤ ነገ የድምጽ ኮረጆዬ ላይ ተገኝልኝ የሚሉትን ያን መከራ የገረፈው ቅን ህዝብ በተለዬ ሁኔታ አዬዋለሁ የሚሉትን፤ ኦሮሞ ኦሮሞ እያሉ ልባችን ውልቅ የሚያደርጉት ወገኖቻችን እስከ ዛሬዋ ዕለት ድረስ ሄደን እንይ እንኳን አላሉም። እነሱ አውሮፓ እና አሜሪካ ንግሩን ባይ ..

 

 አቶ ጃዋርም በአይፒ ደረጃ ሲንቀባረር ሰነባብቶ ተመልሷል። የህዝብ ወገን የሆነ ግን መጀመሪያ ከቤቱ ከመግባቱ ጭፈራ እና አጀብ ከማስፈለጉ በፊት እነዛ በመፈናቅል ምክንያት ከወላጆቻቸው ጋር የተለዩ ልጆችን፤ መንገድ ላይ የወለዱ አራሶችን፤ በምግብ እጥረት ያለፉ ወገኖችን ቤተሰቦች፤ ህክምና ያልደረሰላቸውን ተጎጂዎች ሄዶ ማዬት ነበር። ኦህዴድን አራሱ ምን እንርዳችሁ ብሎ በትህትና መጠዬቅ ነበር ሳይንቲስትንት።

 

አሁን እኮ ወደ ሁለት ሚሊዮን ደርሷል ተፈናቃዩ። ክብር ማለት ወገናዊነት ማለት ለነፃነት መታገል ማለት ለእኔ ይህ ነበር። ነገር ግን አገር ውስጥም ያለውም፤ ውጭ አገር ኖሮ አገር ቤት የገባውም እነዛን ተጎጂዎች ከማዬት ይልቅ የዝና እና የዩልኝ እኔ እበልጥ እኔ እበልጥ ፉክክር ነው የታዬው። ይህን ሳሰበው ውስጤ ይታረዳል። በበዛ መከራ ውስጥ ላለች አገር እንዲህ ዓይነት ወደ እራስ አለመመልከት ያቆስላል ማህጸንን።

 

ሌላው እንደተለመደው ስለ አንቀጽ 39 ሲነሳባቸው የሰጡት መልስ ቤቴ እስኪሰነጠቅ ድረስ ነበር ያሳቀኝ። አንዲት ሴት ነፍሰጡር ሆና የምትወልደው ልጅ ወንድ ይሁን እንስት ማወቅ ፈልጋ ወደ አዋቂ ዘንድ ሄደች አሉ። „ጸንሻለሁኝ ከቶ ሴትን ወይንስ ወንድ እወልድ“ ይሆን ብላ ጠዬቀቻቸው፤ ጠንቋዩም „ወይ ወንድ ወይ ሴት አሉ“ ይባል። የሳቸውም መልስ እንዲሁ ነበር። ሁለቱም መንገድ ተፎካካረው አሸንፊ እና ተሸናፊ ሲሆኑ ጠይቀኝ አይነት መልስ ነው የሰጡት፤ ይህ እንግዲህ በሰላማዊ መንገድ ለሚታገል ሰው ግልጽ እና አጭር መልስ የሚያስፈልገው ሆኖ ሳለ ዙሪያ ጥምጥም በመሄድ ቢጠማዘዙም ያው ተዚያው ተብሎ ይደመደማል። ደንብልብል።

 

የገረመኝ በአሁኑ ውይይት አጤዎቹን፤ ኮ/ መንግሥቱ ሃይለማርያምን ያነሱበት መንገድ ነው፤ ለዚህ እንኳን አበቃቸው ብያለሁኝ ወገኖቼ ናቸው …  ለኦሮሞ አጤዎች ለዬጁ ኦሮሞች ቀን ወጥቶላቸዋል በህሊና መራራ መንፈስ ጎጆም ተቀልሶላቸዋል።

 

·       ሰው ሲፈጠር።

 

መታመን ቢያንስ ሃይማኖቱ ከኖረ ለፈጣሪ እንዴት ያዳግታል፤ ሃላፊነት መወሰድ የማይችል የፖለቲካ ሊሂቅን አዲሱ ትውልድ  ከእንግዲህ ማስተናገድ መንፈሱንም መስጠት አይገባውም። ስህተት ነበር ማለት ወንጀለኝነት አይደለም፤ ሰው እኮ እንዲሳሳትም ሆኖ ካልተፈጠረ ያ ሰው ሳይሆን ሮቦት ነው ማለት ነው።

 

„ሸማ በዬዘርፉ ይለበሳል“ ይላል ጎንደሬ ሲተርት…  አንደ አስተማሪ መሰሉን ብቻ አይደለም የሚልቀውን ለመፍጠር ነው የሚታታረው፤ እና ያሳታመረው የሙያ ልጁ በልጦ ልቆ ተወዳጅ ሆኖ ሲያው ደስ ሊለው ይገባል። እኔ ሁልጊዜ እምከታታለው ደግሞ እኔ አስተምሬሃለሁ አንተ እኔን ልታስተምር ወይንም ልቀህ ልትታይ አይገባም አይነት ነው።

 

አሁን ችግሩ ያለው ዶር ለማ መገርሳም የፖለቲካ የሙያው ሊሂቅ መሆናቸው ብቻም ሳይሆን መንፈስን የመግዛት አቅማቸው ሉላዊ መሆኑ ነው ችግሩ። በዶር መራራ ጉዲና በታች መሆን ነበረባቸው። እሳቸው ሥር ዶር አብይ አህመድ ቢኖሩ ይህን ዶር ለማ መገረሳ የወሰዱትን እርምጃ አይወስዷትም ነበር። ትናንትም ዛሬም እሳቸው ናቸው፤ ተተኪ አላዬንም። ነገም በዚኸው ይቀጥላሉ። ዶር በቀለ ገርባ ከሌላ ድርጅት ነው የመጡት። እሳቸው አላበቀሏቸውም።

 

አበልጦ፤ አበቅሎ፤ አስብሎ አንድ ሊሂቅን ማዬት አለፍቅድ ነው ያዬነው። መከራው ዶር መራራ ጉዲና ውስጣቸውን፤ ቃለ ምልልሳቸውን በኦህዲዶች / አዴፓዎች በሁለት አብርሃም ወአጽባህም ሊሂቃን ጋር ያለውን ዕድምታ መመርምር በእጅጉ ያስፈልጋል። እነዚህ ሊሂቃን ሥልጣን የማይቀናቀኑ ቢሆኑ ኖሮ ይህን ያህል ሴራ ባለታጨላቸው ነበር።

 

ተጀምሮ እስኪያልቅ ድረስ ከወያኔ ሃርነት ባላናነሰ ኦፌኮን የፖለቲካ ሳይንቲስቱን የዶር ለማ መገርስን የብልህነት፤ የማስተዋል ብቻ ሳይሆን የማድረግም አቅም ሲፈትነው ነው የባጀው። ዶር ለማ መገርሳ ችግርን የመሸከም አቅማቸው እኮ ሲንጠባጠብ ታይቶ አይታወቅም። ሁለት ነገር ተፍጥሯል ሻሸመኔ እና ቡራዩ እሱንም አደራጁን ቀን ያወጣዋል።

 

ሌላው በጣም የሰለቸኝ እና እጅ እጅ ያለኝ ነገር ማስተማሩ እኮ በነፃ አልነበረም፤ እዬተከፈለ በመሃያም ነው። ያ ደግሞ ግዴታ ነው ተማሪዎች አስምርቆ የማውጣት፤ ይህን ብዙውን ጊዜ ሲመጻደቁበት እሰማለሁኝ። ይህም የተገባ አይደለም። ሰው ለሳቸው ከሰጠው ስዕል ጋር አይመጥንም። አገር የመሥራት ዕድሉ ኗራቸው አገር ቢሠሩ ምን ሊሉን ይሆን? ደሞዝ እዬተከፈለ ለተሠራ ሙያዊ ግዴታ ይህን ያህል እዬተደጋገመ የሚያነሱት ስሞታ ስልችት ብሎኛል፤ አንተ ተማሪዬ ነበርክ እኔን ልታስቆም አትችልም፤ እሱ ተማሬዬ ነበር እሱ ማን ሆነና አያስኬድም፤ የሰው ልጅ እኮ የተለያዬ ነው። መማር ብቻውን ግብ አይደለም። መማር ደግሞ በዬትኛውም ሁኔታ እና ጊዜ መሆን አለበት። ብቻ ውዶቼ እኔ የጠፉብኝን ፈገግታ ስንቁ፤ ትህትና ቤቱ የነበረውን የመራራ የቀደመ ንፈስ እዬፈለግኩኝ ነው። ከቻላችሁ እንሆ አፈላልጉኝ ብያለሁኝ ….

 

 

ኢትዮጵያዊነት ከመፈጠሩ በፊት ፈተናን አሸንፎ የተፈጠረ ሚስጢር።

 

የኔዎቹ ኑሩልኝ።


መሸቢያ ጊዜ።

                                            እኔው። 

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።