የአማራ ሊሂቃን ጉዞ ወደ አሜሪካ ወቅቱ አይደለም።
መሄድ እንዳለ አለመመለስም
እንዳለ ማሰብ ብልህነት ነው።
„አለንጋ ለፈረስ፤ ልጓም ለአህያ
በትርም ለሰነፍ ጀርባ ነው።
አንተ ደግሞ እርሱን እንዳትመስል፤
ለሰነፍ እንደ ስንፍናው አትመልስለት።“
መጽሐፈ ምሳሌ ተግሣጽ ፳፮፫፬
ከሥርጉተ©ሥላሴ
27.11.2018
ከጭምቷ ሲዊዘርላንድ።
ሞት የትም ቢሆን አይቀርም የሚሉ ይኖራሉ? ዝቅ ብሎ ወጀብን ማሰለፍ ደግሞ ከሞትም ይታደጋል፤ ወደ ሞት ቆርጦ የሚገሰግስው አንድ አጥቂ ብርጌድ ይሁን ሻለቃ ገዢ መሪት ላይ የሚሟተው ሆነ ጉድብ የሚሰራው ሞትን ለመገደብ ነው።
እንዴት ናትችሁ የኔዎቹ ውዶቼ? ሰሞኑን አንድ ዜና ሽው አለኝ። የኢትዮጵያ የተስፋን መንገድ በፈቃደኝነት እና በልበ ሙሉነት እንዲሁም በማይናወጽ ዕጹብ ድንቅ ታማኝነት በተጫማሪም የግል ኢጎን በፍጹም ሁኔታ በመርታት፤ ቃላቸውን ሳያጥፉ ብሩሁን ዘመን ከመሩት ኢትዮጵያዊ ሊሂቃን ውስጥ ሦስቱ ሥላሴዎች ወደ አሜሪካ እንደሚያቀኑ አዳምጫለሁኝ።
አቶ ደመቀ መኮነን፤ ዶር ገዱ አንዳርጋቸው እና ዶር አንባቸው መኮነን። ይህ የግብዣ ቅደመ ሂደት በእንሱ ፈቃድ ወይንስ በሌላ ጋባዥነት ሙሉ መረጃውን አላውቀውም። ብቻ የኢትዮጵያ ኢንባሲ በአሜሪካ ከሰሞናቱ መግለጫ እንደሚሰጥ እያዳመጥኩኝ ነው።
ለምን እንዳስፈለገ ባይገባኝም፤ ያስፈለገበት ምክንያት እና ተጨባጩ ሁኔታ ሊገናኝልኝ ባይችልም እኔ እምለው ነገር ግን ልቅምቅም ብለው አሉ የሉም የሚባሉ የአማራ የህልውና ታገድሎ አድምጭ መንፈሶች የህሊና መቅኖዎች እንዲህ በጉዞ ሊታደሙ ሲታሰብ ከፊት ለፊቱ፤ ከጀርባው፤ ከጎኑ ከኋዋላ፤ በደረቱ ምን አለ ብሎ ማሰብ ይገባል ባይ ነኝ። ምክንያቱም በፖለቲካ ጨዋታ ውስጥ መታመንም ማመንም የጊዜ የቦታ የሁኔታ ጉዳይ ስለሆነ።
ይህ ምን ማለት ነው? ብልህነትን እና ማስተዋልን መዋጥ ያስፈልጋል። የተዘራ ሁሉ አይበቅልም፤ የበቀለ ሁሉ ለጎታ አይበቃም፤ የተወለደ ሁሉም አያድግም። ሐሴትን ሲያስቡ ሐዘንንም፤ ፈንጠዝያን ሲያሰሉ አንገት መድፋትን፤ ማሸነፍን ሲያስቡ መሸነፍን፤ ማትረፍን ሲያስቡ መክሰርም እንዳለ
በጥሞና ሊመረመር ይገባል። የአሁን ጉዞ እኔ በህሊና
ትርፍነቱ እና ግብዕቱ ጋድም ሆኖ ነው የሚታዬኝ። ሩቅ አልሞ ቅርብ እንዳይቀሩ በጥሞና ሦስቱም ሊያስቡበት ይገባል።
ቀድሞ ነገር ክልሉን የውስብስቡን የአማራ ጉዳይ ለማን ጥለው ይሆን እንዲህ ልቅምቅም ብለው ወደ አሜሪካ ለመምጣት የወሰኑት። አንድ ክፍትት ለማስተካከል ስንት መስዋእትነት እንደሚያስፈልግ ያጡታል ብዬ አላስብም። የጠ/ሚሩ የስሜን አሜሪካው ጉዞ እና ውጤቱ መቼም ተከድኖ የቀረ ጉዳይ ነው እንጂ ሁሉን አሳጥቶን ነበር። ሰፊ ክፍተት ፈጥሮም ተግባሩ እስከ አሁን አልተጠናቀቀም። የኦህዴድ /ኦዴፓ ለዚህ መካራ መዳረግ መንስኤው ይኸው ነው።
ቢያንስ ያን ጊዜ ዶር ለማ መገርሳ ኢትዮጵያ መቆዬት ነበረባቸው። የ አሁኑ የዶር ገዱ አንዳርጋቸው ጉዞም ራስ
መርዘንን ለመሸመት ነው። ትንሹን ፋታ በከባድ ቀንበር
ለመሸከም መወጠን። አለመታደል። ዕድል ወርቅ ነው።
ከቀለጠ ይፈሳል። በዚህ የሽግግር ወቅት ድጦ ለማለፍ
እንጂ ቆሞ የሚጠበቅ አንዳችም አምክንዮ አይገኝም።
ታማኝም የለም።
ሌላው የአማራ ሊሂቃን የብዙ ነገር የጥቃት ሰለባ መሆናቸውን ማሰብ ይገባቸዋል። ሁሉም ከአንገቱ እንጂ ከአንጀቱ አለመሆኑን 50 ዓመት ሙሉ የላሸቀው የኢትዮጵያ ፖለቲካ መሰረቱ ጸረ አማራ ስለመሆኑ ከውስጣቸው ሆነው ሊያዳምጡት ይገባል። ለበቀል ሳይሆን የቆሙበትን መሬት ሁልጊዜ መመርመር
ማጥናት ይገባቸዋል። የ አደባ መከራ አይተኛም
አያንቀላፋም።
በሌላ በኩል የወያኔ ሃርነት ትግራይ ዋና የጥቃት ግብ ስለመሆነቸው ልብ ያሉት አይመስለኝም ይህን ጉዞ ይሁን
ግብዣ ሲቀበሉት። በቅርብ በሩቅም ለለማ ቡድን ያሳዩት ታማኝነት እና እዮራዊ ታምርም በጥርስ የተያዘ ጉዳይ ነው። ምክንያቱም በአጀብ ሥልጣን ለመያዝ ያሰበው ሁሉ አከርካሪው ነው የተሰበረው።
ለዚህ ነው አሁን መሬት ላይ በሚጠይቁ ሥራዎች ከመዳፍ ምንም ነገር ሊገኝ ያልተቻለው። ብአዴን ከለማ ጎን ባይሰለፍ ኖሩ የብዙ ባለ አራት ወንበር ምኞተኞች ከስሞ ባልቀረ ነበር። የወያኔ ሃርነት ትግራይም የ100 ዓመት ህልም እልም ባላለ ነበር። የብአዴን ሦስትዮሽ ሦስቱ ሥላሴዎች ደገአ በግራ በቀኝ ተስቅዞ የተያዘ ህልውና ያላቸው መሆኑን ማሰብ ይገባል። እራሱ የለማ ቡድን አሁን ያለው መንፈስ ከቀደመው ጋር በአህትዮሽ ስለመሆኑ እዛው መሬት ላይ ስለሚገኙ ከእኛ ይልቅ እነሱ ለሚዛን አይቸገሩም ባይ ነኝ።
በሌላ በኩል በአጋጣሚ ትራስነት ወደፊትም ጥገናዊ ለውጡን ለመቀልበስ ለማስብ ያደባው ሁሉ የሚያማትረው አማራ
መሬት ላይ ነው። የዕምነት የራስ ታማኝ እንጂ የፖለቲካ
ጓድነት ታማኝንት የለም።
ሁሉም ለራሱ ታማኝ መሆን በተሳነው ዘመን ሁሉንም በር ከፋፍቶ ጥሎ አሜሪካን መሄድ ለእኔ ብልህነት ሳይሆን ልብን መንፈስን አውልቆ እንደመሸለም ነው እማዬው። "የፈሰሰ ያልታፈስ" እንዳይሆን ቢያስቡበት መልካም ነው። „የቆጡን አውርድ ብላ የብብቷን ጣለች" እንዳይሆን እጅግ የሚያሰጋ እርምጃ ነው በአንድነት ለመጓዝ ማሰብ በራሱ።
የአወሮፕላን አደጋውን ጨምሮ በረጅም ጊዜ አሰልስሎ ከጥቅም ውጪ የሚያደርግ የምግብ ሆኖ የመጠጥ ብክለትም አንዱ እና ዋንኛው ታሳቢ ሊሆን የሚጋባው ጉዳይ ነው።
ያ ዘመን የማይተካው ጋዜጠኛ፤ ጸሐፊ የታሪክ አዋቂ ቤተ ሙዝዬም ጋሼ ሙሉጌታ ሉሌ ድንገተኛ ህልፈት የግልጡ ፖለቲከኛ ድንገተኛ የአቶ አሰፋ ጫቦ ህልፈት፤ የሳይንቲስት ኢንጂኔር ቅጣው ህልፈት፤ የቆሞስ ተስፋዬ ጌታቸው ህልፈት መሰረታዊ የመነሻ አምክንዮቸውን ሥራቸውን መፈልግ ያስፍልግ ይመስለኛል።
ሊታውቅ የሚገባው ጉዳይ እንዲህ መቀበሩን ጥሶ የወጡ የአማራ ሊሂቃን በዚህ ዘመን ማግኘት የሰማይ ስጦታ ነው። እራሱ የአማራ ሊሂቃን ራሳቸው ላባቸውን ጠብ አድርገው በከወኑት፤ ራሳቸው በደከሙበት ቦታ ሁሉ የነፍጠኛ ድርጅት ውጤት ይባላል በማለት የህሊና መቅኗቸውን ለሌላ ብሄር ብሄረሰብ ይያዘው ብለው አሳለፍው ወዛቸውን የሸለሙ ሁሉ ሲታሰቡ አማራ በጉልበቱ፤ በልቅናው፤ በብቃቱ ጎልቶ እንዳይወጣ ካለው ጫና የመነጨ መሆኑን እንደ ተቋም ሊማሩበት ይገባል።
ለዚህም ነው ለውጡ ነፍስ እዬዘራ ሲመጣ የዛሬ ዓመት ለዶር ለማ መገርሳ እና ለዶር አብይ አህመድ አድናቆትን እና ምስጋና ሲላክ ያን መከራ ተሸከመው ያሻገሩት የ ብአዴን ሊሂቃን እነ ዶር ገዱ ግን ብጣሽ ከውጭ አገር ያልተላከላቸው።
ለዚህም ነው ሁሉንም ነፃ የዋጣው የአማራ የህልውና ተጋድሎ ተገሎ ተጨቁኖ ዲስክርሜነሽን ሲፈጸምበት የባጀው። ተዘርፎም ከሌላ ማህበረሰብ ለወጡ ነፍሶች ለመሸለም እራሱ የአማራ ታዋቂዎች ትናትም ዛሬም የሚተጉበት ጉዳይ ነው። የአማራ የማድረግ አቅም ሰውኛ ስላልሆነ ተግባሩ ራሱ ይናገረዋል እንጂ።
ለዚህም ነው አፉን ሞልቶ የአማራ የህልውና ተጋድሎ
ያመጣው ለውጥ ብሎ የሚናገር አንድም ሚዲያ፤ አንድም
ሊሂቅ ያልተሰማው፤ ያልታዬው ካለ ዘሀበሻ እና ሳተናው/
ኢትዮ ሪጅስተር በስተቀር። የአማራ የማድረግ የመሆን
የስኬት ቁልፍነት አስፊሪው፤ ፈጽሞም የማይደፈረው
አመክንዮ ነው። ቢሩቅት ቢያርቁት ግን ነፈስ ከመዝራት ሊገድቡት አልተቻላቸውም።
የዛሬ ዓመት የአብይን ክህሎት ሰብሮ ለማስቀረት፤ የለማን መንፈስ መቅኖ አልቦሽ ለማድረግ ሲታሰብ የአማራ ልጆች ነን
ፊት ለፊት ወጥተን የማይደፈረውን አቅም ተዳፍረን ራሳችን ማግደን ተገልን ሞግተን የተበተንን መንፈስ ለመሰባሰብ ሰፊ የሳይበር ተግባራትን የከወን። ሰፊም የሎቢ ተግባር እጅግ እርግጥ በሚያደርግ የሃቅ ወርቃዊ እንክብል ድጋፋችን ምስክርነታችን የሰጠን።
ያን ጊዜ ይህ ሉላዊ ዓለም እና እወቅን ያገኜ ብልህነት ይገኛል ተብሎ አልተገመተም አልታሰበም ነበር። ግን እዮር የሰጠውን
ጸጋ መገደብም ማስቆምም አይቻልም። ያልነው፤ የጻፍነው፤ የመሰከርንለት፤ የተጋልነት ወደፊትም የምንታገልልት የአብይ
ኬኛ ነፍስ ነው ዛሬ ከኢትዮጵያ አልፎ የአፍሪካም ተስፋ የሆነው። አማራ እንዲህ ነው። ጥሶ አቅሙ እንዲወጣ የሚደርገው ቅንነቱ እና ታማኝነቱን አምላኩ ስለሚያከብርለትም ነው።
ህም ግን እም እንዳይሆን ብቻ።
ወደ ቀደመው ርዕሰ ጉዳዬ ስመጣ እነ አጅሬ ምን አሰኝቷቸው ልቅምቅም ብለው ወደ አሜሪካ ለመጓዝ እንዳሰቡ አይታወቅም። ጠ/ሚር አብይ አህመድ ጉዞ ቅኖች ቢያደራጁትም የሀምሌው ዝምታ ጉድ ሰርቶ እንደ ነበርም መታወቅ አለበት። የፈጣሪ ጥበብ ነው ያተረፋቸው። ያን ክፍተት ለማስተከከል ምን ያህል እንደ ገና ሌላ አቅም እና መስዋዕትነት እንደፈለገ ሁላችንም ያዬነው ነው። ይህ ጉዳይ ከተፈለገ ስለምን ያን ጊዜ ዶር አንባቸው መኮነን አብሮ እንዲጓዝ አልተደረገም ነበር? ለምን? አሁንም በቅርቡ የአውሮፓ ጉዞ ሁሉ ነበር? አይደለምን?ስለምን ይህ ነጣላ ጉዞ ታሰበ? አይገባኝም እንዲገባኝም አልሻውም።
የአሁኑ ዕቅዱ በፍጹም አላመረኝም፤ በጭራሽ አልወደድኩትም፤ በምንም መልኩ አልተመቸኝም። በዚህ ጊዜ በያሉበት ሆኖ
አደብ እንጂ ይህን መሰል ጉዞ አይመከረም ለዛውም በቡድን፤ የብአዴን ሙሉ ጽ/ቤት እኮ ነው አሁን ወደ አሜሪካ የሚያቀናው። እም ይማጥለት ....
ምን ያስለፍጋል የአማራ ልጅ እንደሆን እነሱ መጥተው ቀስቅሰውን፤ አደረጅተውን ወይንም አስበውን ወይንም ዕውቅና ሰጥተውን ወይንም ባለቤት ሆነውን ወይንም አስታውሰውን አይደለም ዓመት ሙሉ እንቅልፍ አጥተን በጣና ኬኛ ፕሮጀክት ስኬት የተጋነው።
ምን አለ አደብ - ምን አለ ዕዮባዊነትን ሸምተው እዛው ቢቆዩ። ባረገረገ መርከብ ተሳፍረው ጉድ እንዳይሆኑ ተኝተው ቢያስቡበት መልካም ነው። በሰላም ውሎ መግባት እራሱ ታላቅ ነገር ነው። ሙሉ አካልንም ማጣትም ይኖራል። ሙሉ መንፈስን መቀማትም ይኖራል። ብቻ ግብዣውም፤ ውሳኔውም፤ የውሳኔው ይሁንታም ተቀባይነቱም ብልሃት የሌለው ቅላት ነው።
እኔ ተሳክቶላቸው በሰላም ቢመለሱ እንኳን አስፈላጊ ነው ብዬ አላስብም። ወቅቱን ያልጠበቀ ነው። ክድን ብሎ የልብን መከወን
የአባት አዳሩ ሌጋሲ ተቋም ነው። „ሙያ በልብ“።
ቀድሞ ነገር ምን ሰላም ኑሮ ነውና አሁን ውጭ ወጥቶ ስደተኛን ማነጋገር ያስፈልገው። እኛ ምርጫ የለብን ምን የለብን። ኮሮጆ ቆጠራ አያሰኜን። ናፈቃችሁን ከሆነ ደግሞ አንድ ሰው በቂ ነው። አሁን ዶር አንባቸው መኮነን ተንሳፋፊ ስለሆነ እሱ በቂ ነበር። እሱም ቢሆን በሁሉም ዘርፍ መጠንቀቅ ይገባለዋል። ህይወቱ ታስፈልገናላች። እርጋታው የመንፈሳችን እርካብ ነው።
ብቻ እንዲህ ግን ሙሉው ነፍስ፤ ሙሉው ህሊናህን አዬር አምነህ መጎዝ እጅግ አሳሳቢ አዳጋችም አላስፈላጊ መስዋዕትነት ለመክፈል መሰናዳት ነው። ያልበሰለ ጮርቃ እሳቤ ነው።
ሌላው እኔ በአባ ኮስትር አቶ ንጉሡ ጥላሁን እምነት የለኝም። የራሳቸው ሌጋሲን ማስፈጸም የሚሹ ፖለቲከኛ ናቸው። ከአብይ ሌጋሲ ጋር ነፍሳቸው የለም። የራሳቸው ዓለም አላቸው።
ውስጣቸውን ለማዬትም አይቻልም፤ ድንብልብል እና
ድፍንም ነው። እስከ አሁን ሊታወቁም የቻለም አይመስልም
የውስጣቸውን ምኞት እና መንገድ እጅግ ሩቅ ነው። በቅርብ
ተሁኑ እንኳን እሳቸውን መንፈስ ማግኘት አይቻልም፤ እንኳንስ ሙሉውም እንዲህ ትቶ ሌላ ውቅያኖስ አቋርጦ መሄድ ሊታሰብ ቀርቶ። በዬሰከንዱ ክፍተቱን ለሞሙላት ከሳቸው የላቀ እና የቀደመ አቅምን ይጠይቃል።
የእሳቸውን አቅም የሚመክት ሰው እዛ የለም ብአዴን
ውስጥ። ብአዴን ብለው ነው የሚሻለኝ አሁንም ቲያትረኛ ስለሆነ። እንደ ሥርጉተ ሥላሴ አርፋችሁ ተቀመጡ ነው የምትለው። ሞትንም ጥቃትንም ሽንፈትንም ቅደሙት ነው የምትለው። „አይጥ ለሞቷ የድመት አፍንጫ ታሸታላች“
አይደል የሚባለው። ምን አይነት ጥቃት ይሆን የናፈቃችሁ ይሆን?
የቆሞስ ተስፋዬ ጌታቸው ጥሪ ይሆን? አንባሰደር ካሳ ተክለብርሃን እዛው ናቸው አይደለምን? የኢንባሲ ጽ/ቤቶች በሙሉ በማን መንፈስ ቲፍ እንዳሉም ይተወቃል። ዝም ብሎ ዘው የሚባልበት በፍጹም አይደለም። ከሁሉም በላይ ወያኔ ሃርነት ትግራይ መርሁ በቀል ነው። ለበቀል የሚከፈለውን ሁሉ መስዋዕትነት ይከፍላል።
ፖለቲካ እኮ የቀን ጉዳይ ነው። ሲሰጥ ይሞላል ሲነሳ ይጎድላል። ለመጉደል መታተር ደግሞ ከፖለቲካ ሊሂቃን የሚጠበቅ አይደለም።
በሌላ በኩል ሰው ደክሞታል። ስለደከመውም ያን ያህል የታሰበውን ያህል ተረፈ ዕሴት ማግኘት የሚቻል አይሆንም።
ያ ካልሆነ ደግሞ ሌላ ሽንፈትም ማስተናገድ ይሆናል።
ምክንያቱም ጠ/ሚር አብይ አህመድ የመሩት ቡድን ምን
ያህል የደጋፊ ማዕበል እንደ ነበረው ዓለም እራሱ አይቶታል እና። ተመጣጣኝ ዕድል ቢገጥም እንኳን በፍጹም ወቅቱ አይደለም። ምን ያጣድፋል። ከቶ እዮባዊነት እንዲት ይሸመት?
የአማራ ድርጅቶች ጥቅልል ብለው አገር ገብተዋል። ብልጭ ድርግም ሲሉ የነበሩ ዘልቀው አንድ ዓመት እንኳን ተከታታይ ተግባራትን ያልከወኑት ሚዲያዎችም እንዲሁ አገር ገብተዋል። ስለዚህ አብረው ሊሠሩ ያሰቡት አገር ከገቡ ቀሪው ደግሞ አደብ ገዝቶ ሁኔታውን የሚከታታል የችሎታውን ለማድረግም የሚያስብ ነው።
ብቻ „የሞኝ ለቅሶ መልሶ መላልሶ“ ሆነ። ስለምን ይህ ጉዞ እንደ ታቀደ እንቆቅልሽ ነው? ስለምን ይህ እንደ ተፈለገ ጉራማይሌ ነው? ስለምን አሁን በዚህ ጊዜ እንደ ተሰላም ለዛውም በማን አንባሳደርነት መስተንግዶ ወጣገብ ነው? ግርም የሚል የጉድ ቁንጮ ነው። ምን የጉድ ቁንጮ የጉድ ክምርም ነው።
ራያ ወልቃይት ጠገዴ የራስ መርዘን ቁርጥማት የሆነባቸው ቤተ ነፍሶች ያሰተናግዱን ብሎ ማሰብ ምን ይባል? ስለተ ቢስ ጉዞ ነው - ልብ አይዋስ ነገር። ብልህነት ያተርፋል እንጂ አያከስርም። „አይመጣምን ትተሽ ይመጣልን እሰቢው" ነበር ጉዳዩ።
ብቻ ምንአልባት ያው መድረክን የመምራት ጥማት ያለበት ነፍስ አልሞትም ሊሆንም ይችል ይሆናል። በእኔ ይሁንባችሁም ሊሆን ይቻል ይሆናል። "አይቡን አይቶ አጓቱን ጠገቡት" ግን ወፍ ሲያወጣ ነው፤ ወፍ ካላወጣስ? ሽንፈት። ብዙ ነገር አከርካሪው ይሰባራል አንዲት ቅንጣት ነገር ቢገጠም።
በቅኖች ቢታሰብ እንኳን ውጤቱ ነው መሰላት ያለበት። ወቅቱ ቅንጥብጣቢ ትርፍ ነገሮችን አጠራቅመን አቅም መፍጠር እንጂ አዳዲስ ቁዘማዎችን የመፍጠር ችሎት ግራ ነው። ግራ መንገድ ደግሞ እንቅፋት ነው - ለእኔ።
ይልቅ አደብን ከእዮብ ለመሸመት ቢታሰብበት መልካም ነው እንላለን እኔ እና ደመ ግቡዋ ብዕሬ። ምነው እንዲህ የደመ ከልቡ ቆሞስ እንጂነር ስመኘው ቀን ናፈቃችሁ? እዛው ኢትዮጵያ ሆናችሁ እንኳን እናት እንደምታስበው ለምናስብ ወገኖች ልባችን ተንጠልጥላ ውላ ታድራለች። ብቻ አታውቁትም። የ አላዛሯ ኢትዮጵያ ልጆች እንባ እረፈት ይነሳል።
እናንተ አታውቁት ይሆናል እንጂ በመንፈስ ከነፍሳችሁ ጋር ተጠባቅን ነው ያለነው። በፈለገው ፈተና ውስጥ የእናንተ ነፍስ አላዛሯ ኢትዮጵያ ንጹህ አይሯ ነው። ብታውቁበት። ትናንት አቶ ሌንጮ ለታ አንድ ብልህ ነገር ነገረውናል ከቻልኩኝ ራሱን አስችዬ እጽፈዋለሁኝ። የማይታመኑ በጎ ነገሮች እያዬን ስለሆነ ለውጡ ድጋፍ ከመስጠት ውጪ በቀጣዩ ምርጫ አንሳተፍም ብለዋል።
ደፋር እርምጃ ነው። ሃሳብን ለመክፈል፤ ሃሳብን ለመበትን፤ በክስ ጥገናዊ ለውጡን ከማዋከብ ውጪ ነን ማለት ከብልህነት በላይ ጥበብም ነው። እነሱ የታገሉለት ዓላማ እውንነት መንገድ ከጀመረ ስለምን እንረብሻዋለን ነው ቁም ነገሩ። ሌላው ደግሞ እንደ ተቀጠቀጠ ወይፈን እንብኝ አላረጅም ብሎ በስውር ያምሳል
ቤተ ተስፋን።
የሆነ ሆኖ ከተፎካካሪ ፓርቲ ለዛውም ከኦነግ መሥራቾች ይህ መደመጥ ማለት ጥሞና ይኑረን፤ አደብ ይኑረን፤ አቅም አናባክን፤ አቅምን ልክ እንደ ሰው ልጅ እንጠንቀቅለት ነው። እና ይህን ህግ ተላልፎ የናፈቀውን የጥቃት መሰመር ለማገኜት የሚያስብ ካለ ሃብት ያውጣህ ነው።
እኔ ሌላው ቀርቶ የአዲስ አባባው የድጋፍ እና የምስጋና ሰልፍ እራሱ ወቅቱን ያልጠበቀ ነው ብዬ ሞግቼ ነበር። በብዙ ሁኔታ መሰናዶ ሳይኖር በንፋስ ስሜት የታለመ ነበር።
በእግዚአብሄር ቸርነት ነው አዲሱ የአብይ ካቢኔ የተረፈው እንጂ የሰይጣን ጆሮ ይደፍ እና ሁሉንም በአንድ ላይ አመድ ለማድረግ ነበር ሃሳቡ። ነፍሳቸውም የሰጡ ሰማዕታት፤ አካላቸውን የገበሩ የቁም ሰማዕታት መስዋዕትነት ከፍለውበታል።
እኔ የአሁንን የወልዮሽ የማህበር የብአዴን ሊቀ ሊሂቃን ጉዞም
ከዛ ለይቻ አላዬውም። ይህ የፖለቲካ አማካሪ እጦት ኢትዮጵያ ላይ መቼ መፍትሄ እንደሚያገኝ አይታወቅም። የጠንቃቃ አማካሪ ችግር ነው የዚህ ሁሉ ትርምስ መንስኤው።
አደብ!
የኔዎቹ ኑሩልኝ። ከቻላችሁ ፌስ ቡካችሁ ላይ ሸር አድርጉልኝ። ስለ ትብባራችሁ ትሁት ምስጋና በአክብሮት እንሆ።
መሸቢያ ጊዜ።
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ