ኢትዮጵያዊነት የደሜ ዕምነት ሥነ- ሕይወት! 31.12.2014ትን በምልሰት።

ኢትዮጵያዊነት የደሜ ዕምነት ሥነ- ሕይወት!

„ለፍጥረቱ ሁሉ ትራራለህ ይቅርም ትላለህ።“
 መጽሐፈ ጥብብ ፲፩ ቁጥር ፳፯

ኢትዮጵያዊነት የፍጥረት ዓይነ - ህሊና ነው!
እውነተኛ ሐሴትን የመፍጠር አቅሙ ሙሉዑ! ኪናዊ!

ከሥርጉተ© ሥላሴ (Seregut© Selassie)
ከጭምቷ፡ሲዊዘርላንድ። 31.12.2014


  • ለመነሻ።

የኔዎቹ የፈተና ጥጉ ከ እሰከ የማይበልልት ኢትዮጵያዊነት በ2013 አዲስ ያገረሸ መከራ ነበረበት። እነ አቶ ጃዋር መሃመድ ወደ መድረክ ብቅ ያሉበት ጊዜ ነበር። የዛን ጊዜ ወጣት ጃዋርውያን በሁሉት ዙር ኢትዮጵያዊነትን ወጥረው የያዙበት ወቅት ነበር። በዓይነት ነበር ፓልቶኩ። ለመስማት ቀርቶ ሰምቶ ለመኖር ፈታኝ ጊዜ ነበር። እናም ይህን ጻፍኩኝ። ዘሀበሻም ፖስት አድርጎት ነበር። ዛሬ በምልሰት ሳስበው የዛን ጊዜው ጉግስ በተለያዬ ሁኔታ እዬታዬ ነው።

ኢትዮጵያዊነት ጎላ ብሎ ሲወጣ ኦነግውያን እና ወያኔውያን ደማቸው ይፋላል፤ እሱን እንደ አንጡራ ባላንጣቸው ነው የሚዩት። ልብ ለልብ ሳይገናኙ እነሆ ዘመናት ነጎዱአ እነሱም አፈጁ። ትውልዱም አዲስ ዓራት ዓይናማ አብቅሎ ቀስ እያደረገ እያለበው ነው ጉድፋ ጉድፉን ጉንፋን ዕሳቤ። ተመስገን ነው። በታህሳስ 31 ቀን 2014 የተጠፈው በዛሬው ታህሳስ 11 ቀን 2018 ቤት ለእንግዳ ትለዋላች እትጌ ቀንበጥ። እትጌዋ አብራችሁ ትሆኑም ዘንድ በሞንሟናው ኢትዮጵያዊ አክብሮት ታከብራችሁለች። ማክብረን አትሰስትበትም እና።

·       ይህ ነበር መንፈሱ …  ዛሬ ላይ እትጌ ትግራይን ሳስባት እንደ እኔም እሰቧት በዚህ ውስጥ … የእነ ማህበረ የወያኔ ሃርነት ትግራይ መሳፍንታት የትጥቅ እና ስንቅ ጉዞ … መለከት መቼትን ይጠራል? ስለዚህም ደግሞ ማቅረብ ግድ አለ።

ውህዳዊ የደሜ ልዩ ጽጌያዊ ህልው ንጥረ ቅምረት፤ ውስጤን አስውቦና አሳምሮ፤ ደንግጎ እኔን ሰጠኝ።
ወደ ውስጤ ለመግባት ይለፍ የሚሰጠው በኢትዮጵያዊነት ዋና በር ብቻ ነው። የዕልፍኙ ዕድምተኝነት ፈቃድ የሚያገኘው ከዚህ ከነጠረ፤ ዓለምን ከፈጠረ ማንነት ላይ ሲነሳ ብቻ ይሆናል። እምነትህን ከልብ ስትቀበለው ሚስጢሩ ይገለጽልኃል፤ አቀባይህ መንፈስ ቅዱስ ነውና። ሚስጢሩ ሲገለጽልህ ደግሞ ውስጥህን ትተረጉመዋለህ። ውስጥህን የመተርጎም ዬጸጋህ ብቃት የማንነትህ ጌታ እንድትሆን ይዳኝኃል። ሚስጢሩን በውስጥ አደላድሎ በድል ላይ፤ በአሸናፊነት እስቀምጦ እኔን የገለጸኝ ደግሞ የደሜ ዕምነት ሥነ - ሕይወት አትዮጵያዊነት ብቻ ነው - ለሥርጉተ።

የውስጥ ውበቴ ጅረት የሚመነጨው ከዚህ ጥልቅና ምጥቅ፣ ረቂቅ ማህደረ - ገነት ውስጥ ፈለቀ። ኢትዮጵያዊነቴን ሳስብ ልክ ቅድስት ድንግል ማርያምን በመንፈሴ አደባባይ መንበር ላይ ሳስቀምጣት የሚሰማኝን መርኃዊ፣ ስናዊ ሰናይ ያህል ይመግበኛል። ዜግነቴ የተፈጥሮ ህግ ጭብጥ ነውና።

የስደትን ሁለገብ ፈተና የሰበርኩት ታላቁ መሳሪያ፤ ቋሚ ቅርሴ፤ የብቻዬ ውድ የጽናት ዋንጫ፤ የብርታት ቀንዲሌ፤ የአሸናፊነት ብርታቴ፤ የተፈሪነት እርስቴ፤ የትእግስቴ ቅዳሴ፤ በራስ የመተማማን ጉልበታም መንፈሴ መቅኑ ያለው ከመኖሬ ግንድ ከገናናው ኢትዮጵያዊነት ላይ ብቻ ነው።

መሪዬ፤ የፖለቲካ ፓርቲዬ፤ የቅኔ ዘ-ጉባኤ ሊቀመንበሬ፤ የተስፋዬ ቀንድ፤ ኢትዮጵያዊነት ብቻ ነው። በፍላጎቴ ሙቅ ስሜት ውስጥ የዕለታዊ ገጠመኞቼ ስንኞች ሁሉ ዘኃቸው ከኢትዮጵያዊነት በታች ሲሆኑ ከእሱ በላይ ያለው ግን አንድዬ አማኑኤልና ድንግል እናቴ ብቻ። ምዕራፉ ተገልጦ ተገልጦ የማያልቀው ቀለማሙ ማንነቴ፣ አይጠገቤው ልዩ የመንፈስ የጸዳ፤ አደባባዬ የተዋጣለት - ጉልቴ - ምልክቴ ኢትዮጵያዊነት።

ፍጥረታዊ ነገር ፈራሽም ፍሳሽም የሌለው። የማይሞት መንፈስ ቢኖር ኢትዮጵያዊነት ብቻ። ምንም እንኳን ሀገር በቀልም ሆነ ጠጉረ ልውጥም ጠላት ባያበራላትም። ጠለል፣ ደለል የሌለው የተጣራ ዓለምዓቀፋዊ ስመጥር ማንነት ነው ኢትዮጵያዊነት። በህይወትህ የማትሸሸውና የማትሸሸገው ህብር፤ የውስጥ እኔነትህ ውበት ቢኖር፤ ህሊናህንና ኢትዮጵያዊነትን ብቻ! … ፍቅ እርቦ - ሲሶ - ሳይሆን ውስጥን እንደ አሻው አሳምሮና አሳምኖ የሚገዛ ሙሉ ዕጅ ሰንደቃዊ ዐጤ - የማርያም መቀነት! አበጀህ የካምና የሴም የኩሽ መለሎ!

ህም! እም! ባላንጣው አይሎ ጦር የመዘዘበት የሰባት ሰማያት ሚስጢር። ባላንጣው እሱን ለማጥቃት ለዘመናት አልሞ የተነሳበት ግን ድል ያደረገ ቋሚ ቁርጠኛ የአርበኝነት ቤተ - ማዕዶት - የእኛ! የነፃነት ፍጽምና የትርጉም - መጸሐፍ። እያለ በቁሙ የጸደቀ ድንግል።

 ወጥ ህብራዊ ማንነት። የልተቀዬጠ የውስጥ ሰላም ማግ። የጠላቱ ሆድ እቃው ሳይቀር ለፍልሚያ ያላሩለት - የእኛ- ጹዕመ ልዑል። ግጥምጥም ያልሆነ። ሽብሽብ ያልሆነ። ሽምቅቅ ያልሆነ። ጭምትር ያልሆነ። ደቃቅ ያልሆነ። ኮረኮንች ያልሆነ። ቡላማ ያልሆነ …. ያልተቀረቀረ … ያልተጣበበ - ያልተጣበቀ - ያልተዋሰ - ያልተለጠፈ …. ያልተረተረ … ያልተጋደመ … ቀኙ ቀጥተኛው መንገድ፤ እሱን ቀዶ ጥገና ለማድረግ ማንም የማይችለው፣ በሙሉ ቀን የተፈጠረ የሥነ- ሕይወት ግጥም- ቋሚ አዛውንት - ንዑድ!

ፈጣሪ አምላክ ለአማንያን የሁላችን ነው፤ እንደ እራሱ አድርጎ የፈጠረን። የኢትዮጵያዊነት ውስጠት ደምና ሥጋ፤ ነፍስና እስትንፋስም …. ውህድ - በአምሳል። ብሩህ ነበልባላዊ ላንቃ! የሚያበራ … ፍጹም ደማቅ … የሚያሞቅ ጃኖ፤ ነፍስን የሚታደግ የሰማያት ፍጹም ሽልማት፤ ቅመመ ብዙ - ልዩ ጣዕም፤ ሁሌ እንደ ሸት የሚኖር ያመረበት። እርጅና ከቶም ዝር የማይልበት - ሀመልማለ ህብሬ፤ የወስጠት - ሰላማዊ ዕንቁ - ለእኛ። ለወያኔ ሃርነት ትግራይ እና ለመሰሎቹ ግን አንጡራ ጠላት፤ ለባላንጣው የፋመ ረመጥ። የእኛ የርትህ - ክብረ - ዝናር፤ የእኛነታችን ልዕለ - ባለአደራ፤ የጥቁር ደም የግንባር ማህተም፤። ወርደ ሰፊ፤ ሆደ ሰፊ ማንነት፤ ደንበር ዬለሽ ሐርግ ነው ኢትዮጵያዊነት።  በተጋድሎ ድል አብዝቶ የተቀለበ! የአሸናፊነት በትረ - ሰገነት! የነፃነት - ቅዱስ መንፈስ።

·       ዘንካታ!
መጠነ ሰፊ ንጥር ሚስጢር፤ እራሱን ለመግለጽ ሆነ ለማብራራት የማይቸግረው የድህነት ፍጹም ኤዶማዊ ስጦታ። የዜግነታችን መለዮ ግርማ - ሞገሰ - ዘውዳችን! እውነትን ጸንሶ እውነት የተገላገለ። በእውነትም እውነትን አሳድጎ የቀመረ የተመረቀ። እውነትን ያነጠረ የሰብዕዊነት መረቅ። እውነትን ጃንደራባው በማድረጉ ዓለምን ከነሙሉ ዘሩ የፈጠረ የሥነ -ፍጥርት ድንቅ፤ ጥልቅ አልማዝ፤ የድንቅነሽ ክታብ፤ ለፍጥረታት ሁሉ ቅርንጫፍ ያልሆነ መሰረት - ኢትዮጵያዊነት። ግንድ!

የተፈጥሮ አጥር! ከብረት ቁርጥራጭ የተሰራ የጽናት ወተት ጠጥቶ ያደገ፤ በፈተና ተፈትኖ ታሽቶ፤ ተሰልቆ የፈለቀ ወርቅ- ኢትዮጵያዊነት። እኔን - ለእኔ፤ እርሰዎን - ለእርሰዎ እያነጋገረ ቀጥ ያለ ንጹህ ቡናማ ሐዲድ ዘርግቶ የሰራ አካላትን በመግዛት ፍቅር ሰጥቶ፣ ፍቅርን ተቀብሎ፣ ፍቅር ሆኖ፤ ፍቅርን አፄው ያደረገ ዓውራ መረኃ - ፅድቅ። ሐመረ - ሕይወት።

ልግለጽህ ወይንስ ትገጠኝ?
ውስጤን ስታይ አባብለህ - ስትመስጠኝ
የእኔ በመሆንህ ሳጌጥብህ
ልኖርብህ በመንፈሴ ሳደላድልህ፤
ነፍሴ ታጋለች፤ በሰናይ
ትሰግራለች ኤዶምን በፍሰኃ ልታይ፤
ትፈጥናለች ትሆናለች በአንተ ሐሤት አዳይ።
የትንፋሼ መቀነተ - ሙቀት ወሸባ ቃታ ….
እሱ በእሱ ያመረበት በድንቅነሽ ገበታ
ታደገኝ ሁሉን በገፍ ሰጥቶ - በንድምታ።

·       የውበት ማህደር!

ቀለማም፤ የመስከረም አድዮ አባባ፤ የጸደይ ጽጌረዳ፤ የክረምት ፏፏቴ፤ የበልግ እሸት፤ የበጋ ጣና ዘገሊላ። እኔን ያጀራገደ፤ እርሰዎን ያዘናከተ፤ እኛን ያሞናሞነ፣ ሳቂተኛ - ፍልቅልቅ፤ ባለ ማጫ - ግራጫ፤ ባለ ካባ - ኩሩ፤ ባለ ጃኖ - ከሩቅ ጠሪ፤ ባለ ጭራ - ንጹህ፤ ባለ ከዘራ - ምርጥ ዘር - ዘርቶ ያበቀለ፤ ባላ እጀ ጠባብ - ዓዕማድ፤ ባለ ጋሻ የቀደምት ሁለገብ አብነት፤ ባለ ጎራዴ ጠላትን ጎራርዴ፤ ባለ ጦር የነፃነት - ሰቅ፤ ባለ ማህተም - የፍቅር ማህደር፤ አንበሳ! - የቅኝ ግዛት ምኞትን ያከሰረ - ከሥሩ አምክኖ ለድል የበቃ! የአብነት ዘውድ በጥቁር መሬት የደፋ አዛዥ! ሁለመናው እርስ -በእርሳቸው በተያያዙ ባለ ቃልኪዳን ሴሎች ተመስጥረው የሚገኙበት የውበት ማዕዶት ኢትዮጵያዊነት። ጉልህ!

·       ሳተና!
ጥሩ ሰብሳቢ፣ መልካም አደራጅ፤ ሸጋ አስተናባሪ፤ ውብ አድማጭ፤ የውስጥ አሳ - ሰጋር፤ ኣራት ዓይናማ፤ መንገዱን ያወቀ፤ ፍላጎቱን የተረዳ፤ እሩቅ አልሞ፤ የፊቱን በስልት ከውኖ፤ ነገን በቅጡ ለማሰናዳት የማይታክተው እንቅልፍ አልባ ታታሪ፤ ትናንትን በድርጊት ዘክሮ መነሻውን ለመድረሻው  በመሆን መቻል ተፈጥሮ ድሮ - ኩሎ፤- ማጫ አማቶ፤ መልስና ቅልቅሉን በድል የሚቋጭ ስልጡን ማንነት - ኢትዮጵያዊነት - የታሪክ መምህር። ቀለማም ትውፊት!

                                  ጌታ!
                               የማመናታ
                               የማማታ!
                               የማ~~~~ ም ~~~~ ታታ!
                               ትብብን የ ~~~~ ሚፈታ
                               ከከርኩድ - የሚፋታ!
                                                 ለጠላቱ የማይሰጥ ታ።
                                                 ያልተዛናጋ፤ በማሌሊት ድንፋታ፤
… እጥል የገፈተረረረረ
የቆረጠ … የተረተረ …. ያሳረረረረ
                                                  ንቆ ያሰወገደ የልዩነት ቅብታ!
                                                                           አሰተዋይ፤
                                                   የአረንጋዴ ቢጫ ቀይ ሲሳይ
                                                   ውሉ ያለ፤ ከሰማዬ - ሰማይ።

·       ቆቅ!
ዓራት ኣይናማ ሥነ - ጥበብ። የጊዜን ህግጋት ከመፈጠሩ በፊት ተቀብሎ የዋጠ፤ ቀደምትነትን - ያበቀለ። አስራሁለት አካላትን በአኃትዮሽ ለማንቀሳቀስ የታ ፖሊሲ ፈጽሞ ጠይቆ የማያውቅ - ዕውቅ ስንዱ። የሥነ - መኖርን ዶግማ ከራሱ ጋር በፋቃዱ አዋህዶ ለነባቢተ ነፍስ ታላቅ ዩንቨርስቲ የከፈተ የመንፈስ መብራት። የማይተኛ፤ የማያንቀላፋ። የማያንጎላች የ24 ሰዓት ሙሉ አገልግሎት ለመስጠት ከአረንጓዴው ወርቃችን ጋር በሥራዓተ - ተክሊል የተገባ ንቁ፤ ብቁ - ዘብ አደር ኢትዮጵያዊነት። መዳፍ!

·       ማህደር!

 የማያልቅበት። የመልካም ነገሮች ሁሉ ሙዳይ። የጨዋነት ሞሰብወርቅ። የሆደ ሰፊነት ዋሻ። የትህትና ቀለበት። የቅንነት ማተብ፤ የእንግዳ ተቀባይነት አዳራሽ። ሃዘን ተፍሰኃ የመጋራት ድሪ። የዕምነት ማህደር። የአክብሮት ተቋም፤ የይሉኝታ ማርዳ፤ የይቅርባይነት ፍትኃት - ኢትዮጵያዊነት የሰው ተፈጥሮ መንበር። መቅድም!

·       ወበራ!
የሥራ ወዳድነት መንክር በተፈጥሮው የተደራጀ። በኽረ - የአፍሪካ ልጅ፤ የድርጀት ፅንሰ ሃሳብ የፈለቀበት ማንነት። የፈትል፣ የስፊት፣ የእርሻ፣ የአረም፣ የጉልጓሎ፣ የአጨዳ፤ የመንሹ ሙሽራ - ኢትዮጵያዊነት። ጥቁር አንበሳን አደራጅቶና መርቶ ለዓለም የሽምቅ ውጊያ ደንብና የአፈጻጸም ስልት በመቅረጽ ገጸ በረከት የሰጠ- ቀደምት፤ ያሰተማረ ብሩክ መንፈስ - ኢትዮጵያዊነት።

የሰው ልጅ በህብረት ተረዳድቶ መኖርን ያስገነዘበ፤ የድርጅትን ጽንሰ ሃሳብ ድርጊት ላይ በማዋል ልዩ ዓርማው ያደረገ - ሰልጥኖ የተወለደ። ማህበራዊነትን በመበተን ሳይሆን ተፈጥሮውን መርምሮና አጥንቶ በተሰበሰበ መልኩ እንደ ባህሪው በተከታታይ የመራና ያሰተዳደረ ሊጋባ። ለማህበራዊ ኑሮ የዕድሜ ልክ የጉባኤ ሰብሳቢ። እንደ ማስረጃ …  ሰንብቴው፣ ጽጌው፣ አድርሽኙ፣ ማህበሩ፣ እድሩ …ን፣ ሀሳብን በሃሳብ አታግሎ እምነታዊ ጉባኤዎችን በድምጽ ብልጫ የቋጨ መቅድመ - አብነት። እንደ ዬባህሬያቸው ከነሥነ - ምግባራቸው ወስዶ ማገናዘብ የቻለ - ችሎትንጋት!

·       ተመስገን!
የኢኮኖሚስት ሙሑር ነው ኢትዮጵያዊነት። የባንክን ጽንሰ ሃሳብ በመጀመር እረገድ በቁቤ፤ እንዲሁም በወለድ ብድርን መስጠት በሚመለከት ቀዳሚ ነው። አዎና! የማራቶን አሸናፊ - ኢትዮጵያዊነት። …. ስለዚህ ዛሬ ዓለም በተለያዩ ሁኔታዎች እንዲህ ተደራጅታ በተመሳሳይ ፍላጎት ተዋህዳ ለመፈጠሯ ዘ - ኢትዮጵያዊነት ፋና ወጊ ነው።

ኢትዮጵያዊነትን ፍተሻ ስናደርግለት የናሙና ተምሳሌነቱ የምህረት ዓውድ ነው። ኢትዮጵያዊነት ዓለምን በመፍጠር፤ በመቀመር እረገድ መነሻም መድረሻም ፌርማታ ነው። ግዴላችሁም እንስማማ …. ብዙ ያልተነኩ መዋለ ኃብታት ያሉት ዲታ፤ የምርምር ዕምቅ ጥሪቶች ባለቤት ነው - ኢትዮጵያዊነት። አንቱነት!

·       ማህጸን።
 ዕውቀት አድጎና ጎልምሶ በ21ኛውን ምዕተ ዓመት እንዲያሸበርቅ የረዳው መነሻ መሰረቱ የቀደምቱ በሐረግ በጽጌረዳ አባባ የተንቆተቆጡት፤ ከበሬና ከፍዬል ቆዳ ተፍቀው ከተሰሩት ብራና፤ በሸንበቆ የቀለማት የንድፍ ጠብታ የፈለቀ ነው። የዛሬው የአስትሮኖሚ የምርምር ማዕከል የትናንት የቤተክርስትያናት ሊቃውንት ጥልቅ የምርምር ውጤት ነው። ሊቃውነተ - አውሮፓውያን ዕውቅናቸው የተቀዳው የፈለቀው ከቀደምቱ ኢትዮጵያዊ ሥነ -ህሊና ጭማቂ ነው።

ይህን ፈረንሳይ፤ ስፔን፤ ኢጣሊያን፤ ባቲካን፤ ጀርመን፤ ኢንግላንድ ካሉ ዩንቨርስቲዎች ማዕከላዊ ከሆኑ ዕወቅ ቤተ -መጸሐፍቶች ጎራ ይባልና ይፈተሽ፤ የሥልጣኔው ታቦት፣ የጥብቡ ማሳ፣ የዘመናት ቆጠራ፤ የሳይንስ መሰረት፤ የፍውሰት ብልኃት፤ የፊደሉ ግባዐት ይመሰክራሉ ይናገራሉ …. የሥነ - ጹሑፍ እድገታቸውም መሰረቱም ኢትዮጵያዊነት!  …. ለሁለመና - ኢትዮጵያዊነት። አንጎል!

·       መዳህኒት!
ዛሬ በዓለማችን በልማዳዊ ወይንም ባህላዊ መዳህኒት በቀደምትነት የሚጠሩት እነቻይና ናቸው …. ነገር ግን ዋገምትን፣ ሳማን፣ …. ሽፈራው ቅጠልን፣ እርድንና ጥቁር አዝሙድ ቅመማትን እሰቧቸው፤ ተልባንና ጤፍን ሰሷቸው፤  ነጭ ሽንኩርትንና ዝንጅብልን - ዱባን ዳስሷቸው …. የባህር ማሽላ የጭራውን ሻይ፤ የአብሽን ሻይ … እሰቡት …. መቀንደብን አሳሉት …. ደመ ካሴን ወይንም አረግሬሳን፤ የምድር እንቧይን እሰቡት፤ እሬትን፤ ላንቁሶን፤ ስሚዛንና እንዶድን፤ ወይራን ሁሉንም ዳስሱት የኢትዮጵያዊነትን ባይወሎጂስታዊነት ቀደምትነት ያስነብባል፤ ይተረጉማል፤ ይመሰጥራል ….

ስለሆነም የጤና ህክምና ባህላዊ ኮሌጅ መናገሻው ኢትዮጵያዊነት ነው …. ለሰው ልጅም ለእንሰሳትም … አስሮኖሚነትንም አክሎ …. ከዚህ ጋር ጸበሉ፣ ዕምንቱ፤ ፆም፤ ጸሎቱ  የተዘጋን የእነ አፄ ሰርጸ ድንግልን አንደበተ የመከፍት አቅሙ ወደር የለሽ ነው። በሌላ በኩል ዐፄ ልብነ ድንግል ለአስር አመት ሰላም በመሆኑ ግንባቸውን በጦር እዬወጉ አፍርሰው የተጠጉ ነዳያን አለቁ። ጦር እንዲታዘባቸውም ጫን* እጣን ለጣና ቂርቆሰ ጫን* ዕጣን ለደብረ ሊባኖስ ገዳም በመላክ ጦር አውርድለት ብላችሁ ጸልዩልኝ ሲሉ መልእክት ላኩ፤ የወደዱትና የለሙኑትን አሳዝዟል። የዋዛ!

                                                            ፈዋሽ
                                                     ዳሳሳሽ
                                               አራሽ!
                                         የቀደምትነት - ማሟሻ - መቋደሻ
                                         የድርጊት ትረኖሰ- ማዳጎሻ
                                         አሳሽ።
                                              ቅድሳት - በስክነት
                                              እርቀት - በፍልቅት
                                               ምርቃት - በምጥቀት
                                                እርገት በመሆን ጥምቀት።
                                         ቅድመት … በዕምነት
                                         በህግጋተ - ሥርዓት፤
                                         የዶግማ - ቅምረት
                                          - ድልነት
                                         ብሥራተ - ኢትዮጵያዊነት
                                         ሥርዬት ምህረት። ድህነት።

·       ውቅራት!
ዛሬ የውበት ማዕከል ሆኖ የዓለምን የመገናኛ አውታሮች ያጠበበው ትናንት ሃብትነቱ የኢትዮጵያዊነት ነበር። አሃ! ካለምንም ማጋነን ኢትዮጵያዊነት በዘርፉ ማሾ ነው። ለጌጥነትን ከእምነት ጋር አስተጋብሮ፤ በመስተዋድድ አስተፃምሮ ሥራ ላይ ያዋላ … አንቱ ነው ኢትዮጵያዊነት … ለጀግንነት መለያ ጉትቻው፤ ለብሄረሰብ ባህሉ ክብሩ፤ ጌጡ ለተብዕት ከቀደምቱ የተዛቀ ነው። የውበት ማዕከላት፤ እንሶስላው ጉርሽጡ አደሱ ድሪው ስንድዱ ድኮቱ - ወሸቤው … መራዊነት!

·       ዋው!
ዛሬን እዩት አስተውላችሁ። የጸጉር ቆረጣን …. አፍሮ፤ ሹሩባ፤ ጋሜ፤ ቁንጮ፤ ታሬ፤ ቅምቅም፤ ሰርዴታ፤ ስርንቅ፤ አለባሶ ሁሉም ቤቱ ከኢትዮጵያዊነት የተነሳ ነው። እራሱ ለዓለም አዲስ የሆነው የወንዶች ሹሩባ፤ የወንዶች ሎቲ የትናንት የጀግኖቻችን የአንበሶቻችን መለያ መታወቂያ ካርዳቸው ነበር …. እንዲንጠፍላቸው፤ እንዲጎዘጎዝላቸውና የትዳር ጓደኛቸውን ፈቃድ ለማግኘት ይለፍ የሚያገኙበት ደማቸው ነው። ስለዚህ ለኢትዮጵያዊነት የነበረ ተፈጥሮ፤ ለዓለም ግን በ20ኛውና 21ኛው መቶ ክፈለ ዘመን ብርቅዬ ሆኖበት ሲንደፋደፍ …. እናያለን። አቅጣጫ መሪነትን እንዲህ ይገለጣል ኢትዮጵያዊነት!

·       እሰይ!
ትናትን ከዛሬ ጋር የሚያጋባው የሀገር ሽማግሌውን ሥነ -ጹሑፍስ አተኩራችሁ እዩት። የላቀ ትውፊት። በራስ እንደራስ ሆኖ የተፈጠረ የውስጥ መስታውት። ባለቤትነቱ ኢትዮጵያዊነትን በከብር ያንቆጠቁጠዋል። ዝክረ ቤተ መዘክር ፊደላችን፤ ድርሳናት፤ ስንክሳራት፤ ወርቀ ዘወንጌል*፤

ድጓው፤ ፆመ ድጓው፤ ቅኔው፤ ዝማሜው፤ ትርጉሙ፤ ሃዲሱ፤ ብሉዬ፤ አቋቋሙ፤ ጽናጽሉ፤ ወረቡ፤ ገድላት፤ ታምራት …. መሰል መጸሐፍታት፤ ታሪከ ብራና፤ ቀለም ጠጭ ብዕር፤ ቀለምን የመፍጠር ሂደት፤ ተክለ ኢትዮጵያዊነትን ለምለም ዋርካ ያደርገዋል። የሥነ - ቃል፤ የሰዋሰው ህጋግት፤ የቃላት እርባታና ፍሰትን፤ የሥነ ጥብብ ፍጹም ጥልቅ ሚስጢር በቅንብር፤ በሚጨበጥና በሚዳሰስ ሁኔታ ተግባር ላይ የዋለበት ውስጡ ኢትዮጵያዊነት ነው።

ግጥም ስድ ቦዝ ገላጭ ተራኪ ሙግት መንትያው …. የሥነ - ሥዕልን አዛውንትነት ረቂቅነት፤ የሙያው ጥልቅነት ህይወትን ሲመክር፤ ስለ ትናንት  በአደባባይ ሲመሰክር …. መለ አካላትን ሲያፍነሸንሽ፤ ሲዳስስ የሺ ዘመናት ቅኝት ድርና ማግ መቢያ ትዕይንት ነው። ውርስ!

·       የርትህ መክሊት! 
ተጠዬቅ! ጥብቅና፤ የውርርድ አነሳስ ስልቶች፤ የዋርካ ችሎትና ሥርዓታት …ዋው! ነፍስን ይታደጋል ከሳሽ የተከሳሽን ገመና ዘረዘርኩ ብሎ …

„በላ ልበልሃ!
ያጤ ሥራቱን የመሰረቱን
አልነገርም ሃሰቱን
ሁሌ እውነት እውነቱን።
ላምህ ብትወልድ ዛጎላ
ሚስትህ ብትልበስ ነጣላ
                    አንተ ብትውል እጥላ ….“

ተቀላዩ ተሟጋች ምንም እንኳን አደባባይ የማያዘወትር፤ የኑሮ ደረጃው ዝቅ ያለ ቢሆንም ቅሉ ነገር አዋቂ ነበርና እንዲህ ሲል መለሰለት ….

„በላ ልበልሃ!
ላሜ ብትወልድ ዛጎላ
አውራውን አስመስል ብላ።
ሚስቴ በትለብስ ነጠላ፤ ቀን እስኪያለፍ ብላ
እኔ ብውል እጥላ፤ የአንተን ብጤ ነገረኛ ብጠላ …“
(ከተጠይቅ ከደራሲ አቶ ሺበሺ ለማ ገፅ 22 እስከ 23 “)
መጽሐፍ የተወሰደ ነው።

ስመ ጥሩው ጀርመናዊ ፕሮፌሰር ኢኖ ሊትማን ጨምሮ ለዓለም ህዝብ ያላቸውን አስተያዬት፤ የጥበቡን እድገትና ብልጽግና እንዲሁም አድናቆታቸውን በተባ ብዕራቸው አሳውቀውበታል። ይህ የሚያሳዬን ኢትዮጵያዊነት ጠበቃ፤ ዳኛ፤ ጥሩ ተናጋሪ፤ ገጣሚ፤ ባለ ቅኔ፤ ጥሩ ተከላካይ፤ የተዋጣላት አቃቢ ህግ በተፈጥሮ ብቻ - ለፍትህ ያደረ ስለመሆኑ ነው።

 ከዚህ በተጨማሪ ለኢትዮጵያዊነት ሌላው ፈርኃ እግዚአብሄር የውስጥ ደንቡ ነው። ነጋስታቶቻችን ሁሉ ከትልማቸው በፊት አምላካቸውን ያማክራሉ። የህበረት ሱባኤ ይጠይቃሉ። በቅርባቸው ካሉት ሽማምነት ጋርም ይመክራሉ፤ እጅ ያነሳውን ሃሳብን ተቀበለው ይፈጽማሉ። መንፈስ!

ታሪከ ነገሥት፤ መዋለ ነገሥት፤ ክብረ ነገሥት፤ ብዕለ ነገሥት፤ ፍትሃ ነገሥት፤ የገዳ ሥርዓት፤ የወንጀለኛና የፍትሃብሄር መቅጫና ሥርዓቱ ማንነቱ የጎለመሰበት ምንጮች ናቸው - ለእጬጌው ኢትዮጵያዊነት። እንኳን ሰው ግመልም ተፈጥሮውን ስላማወቁ አፋራዊ ህሊናችን በአርምሞና በተደሞ አመሳጥረውልናል።

እንዲሁም በንጉሥ አምላክ …. ሲባል እንኳንስ የሰው ልጅ ነፋስን ቀጥ የሚያደርግ ጸጋ ነው ኢትዮጵያዊነት። ኢትዮጵያዊነት ባለ ሚዛንነቱንና ላነቱን ለዓለም ህዝብ እርሾ የሆነ ነው። ስለሆነም ኢትዮጵያዊነት እራሱ ህግ ነው። የመኖር ተፍጥሯዊ ህገ - መንግሥት ይሉኃል ኢትዮጵያዊነት። ደልዳላ!

·       ቀዛፊ!
ያለ ተቀናቃኝ እንዳሻው በደም ውስጥ የመንሸራሸር አቅሙ ከቶም መመጠን አይቻልም። የውስጥ አሳነቱ ቅዝፈቱ አስመችቶን እሱም ተመችቶ ነው። እሳት ለብሶ እሳት ጎርሶ ጠላቱን ያግዳል። ተፈሪነቱን ያመሳክራል። አይበገሬነቱን ያውጃል ትናንትም ዛሬም።

እስኪ ለአፍታ እውነተኛው ሰንደቅ ዓላማችን ቃኙት፤ ወይንም ስለ ኢትዮጵያዊነት የተዘመሩትን፤ የተደረሱትን ዜማዎች ሁሉ በአርምሞ ቃኟቸው። አገኛችኋት ብልኃቱን? መጻፍ፤ መናገር፤ መተንተን ይችላልን? … ፈጽሞ አይቻልም። ይርባል …. ልበለው? … ይወራል ልበለው? በውስጥ ይወርባል …. ልበለው? የቱ ይሻላል? …. ያሸበሽባል … ይባል? መግለጫ የለኝም።

…. ሲቃ - የፍሰኃ፤ ፍንደቃ - የፍካት - እልልታ፤ - የድህነት …. ሆታ፤ የናፍቆት ሁሉንም ነው …. ኢትዮጵያዊነት። እንኳን ተፈጠረ መርቁልኝ። ስስታም አትሁኑ ከፍ አድርጋችሁ ድምፃችሁን አጉልታችሁ ለዘለዓለም ኑርልን በሉልኝ …. የእርገተ ነፍስን ፈዋሽ ….. የብርኃናት ድርሰትን ኢትዮጵያዊነትን ….

·       ለስላሳ!
ሸከራ አይደለም። ሲፈጠር ሞንሟና ነው ጤፍ እንጀራ በእርጎ። በአጠገባችሁ ሲሆን ልዩ ሙቀትን ይለግሳል። ስትንቀሳቀሱ ጉልበት ይጨምራል። ስታስቡት ይጠግናል። ስታጋግሩት በተደሞ ያዳምጣል። ስትከፉ በቅርብ ሆኖ ተመክሮውን በማቅናት ያባብላችኋል። ስታኮርፉት መላሾ ሰጥቶ እቅፉን ያንተርሳችኋል።

ፊት ስተነሱት ሐዋርያ ሆኖ እራሱን ዝቅ አድርጎ ያስተምራችኋልኢትዮጵያዊነት ጥበብ ነው። መሻገሪያ ስታጡ የአረንጓዴ መሰለላል፤ የቀይ ድልድይ፤ የቢጫ ሰገነት ያዘጋጅላችኋል። ትንፋሻችሁን መልሶ በፍቅር ዓይን ዓይናችሁን በማዬት ይስማችኋል። አስጠግቶ ሽጉጥ አድርጎ ይይዛችኋል። የውስጥ ጠረናችሁን ቀረብ ብሎ ይጠጠዋል። ትርቡታላችሁ። ትጠሙታላችሁ። ይወዳችኋልና።

የእኩል ዓውደ ምህረት፣ ብሲል ከቀሊል የማይለይ፣ ታይቶ የማይጠገብ ማር ወለላ። ታጋሽ! ኢትዮጵያዊነት ሁሌ ለጋ ወተት ግን አደብ የገዛ፤ ዕድሜ ጠገብ ተመክሮ ያለው፤ ሊቅ ሙሑር ነው - ኢትዮጵያዊነት። እንደ ወጣትነቱ ያሸተ፤ እንደ ጎልማሳነቱ አስተዋይና ሆደ ሰፊ፤ እንደ አዛውንትነቱ ደግሞ መካር ዳኛ። ደማም - ሚዛን!

·       ፈጣን!
ሲነሳ ወኔን ቀልቦ፤ ሲያስብ እልህን ሰንቆ፤ ሲታጋ ጀግንነትን አስቀድሞ፤ ሲንቀሳቀስ የተፈሪነት ሰራዊት አስታጥቆ፤ ለድል ሲባቃ አብሮነትን ከሽኖ፤ ሲመራ አኃታዊነትን አመክንዮ አድርጎ፤  አስራሁለት አካላትን ሲሰርጽ ነፃነትን አጎናጽፎ፤ በራሱ ጊዜ ተወዳጅነትን አፍልቆ፤ ነፍስን የሚታደግ የልብ አምላክ ቅኔ ነው ኢትዮጵያዊነት። የእኛ ክብረት!

እልፍ ሰራዊት በእልፍ ብቃትና ተምክሮ አሰልፎ፤ ከራሱ ተርፎ የጥቁር ዓለም መወድስ የሆነ። የአፍሪካዊነት ልዩ ዝማሬ፤ የዓለም የነፃነት ታሪክ ሥልጡነ -ቀንዲል፤  የአርነት ሰንደቅ፤ ትናንት የነበረ፤ ዛሬም የሚኖር ነገን የቀደመ ህላዊ የድርጊት አባት፤ የመሆን መቻል አንባሳደር ነው ኢትዮጵያዊነት። ጌጥ!

·       ጉልላት!
የታሪክ ቅድመ አያት። የመኖር አንባ። የሰው ልጆች መነሻ። የሥልጣኔ እንብርት፤ የአዶሊስ ዓውራ፤ የተግባር ልምድ አቮል ተቋም፤ የፓን አፊሪካኒዝም ጫጉላ፤ የጥቋቁር ፈርጦች እልፍኝ፤ ለጠላቱ የመያበገር፤ ለወዳጁ የአለኝታ ዋስትና ሳያወላውል የሚሰጥ ጸዓዳ - መቅደስ ነው ኢትዮጵያዊነት። አብነት!

·       መዝሙር!
የመንፈስ ሐሤት መቋሚያ፤ የረቂቅነት ቅኔ ዘጉባኤ፤ መንፈስን የሚጋራ ድጓ፤ የሚያድን ድርሳን፤ የሚፈውስ ጸበል። የሚመርቅ አባወራ፤ የሚያጸድቅ ግብር ሰናይ፤ የሚዳኝ ባለ ሃቅ ሚዛን፤ የሚችል የትእግስት ማዕድ፤ የሚመከት የጥንካሬ አው፤ አርቆ የሚያስብ የቅዱስ ወንጌል - የቁራን እልፍኝ ቅዱስ መንፈስ ነው ኢትዮጵያዊነት። ዬልብ!

·       ጤና አዳም!
ጠረነ መልካም፤ ከሩቅ ወዙ የሚያሳሳ፤ መቃረቢያ ትንፋሹ ያመረ የሰመረ፤ የጥርስ መፋቂያ ዘመናዊ ኮልጌት ወይንም ጦር ማስቲካ የአፍ ማሟሻ የማያስፈልገው፤ ታጥቦ የፈጠረው ደንበር አልባ የስኬት ቁልፍ ነው ኢትዮጵያዊነት። ኢትዮጵያዊነት ሲሰላ ወይንም ሲታሰብ ውቅያኖስ የሆነው ተፈጥሮው ያፋጣል። ስለምን? ሁሉንም ልዘርዝር ቢባል የማይቻል በመሆኑ። ሁሉን የሚችል አምላክ አዶናይ ኢትዮጵያዊነትን መርቆ፣ አንጽቶ ስለፈጠረልን፣ የእኛም ስለአደረገው ጭምር እናመስግነው። ፈጣሪያችን ከእሱ ሳይለዬን ከአብረንታት ጋር ያኑረን። አሜን በሉ! ይሁን በሉ! ኢትዮጵያዊነት አብርነትታት ነው ዝማሬ ቃናው።
    
                           እኔ የአንተ - አንተም የእኔ
                                        የፍቅር ጠመኔ
                                         የናፍቆት ጠኔ
                                         የሽውታ ህመሜ
                                         አንተ የእኔ
                                       እኮ! …  ለምኔ?
                                     …. ለመንፈሴ
                                         ለሩሄ ፈውሴ።
                                ሥሜ
                                             አነተዬ ደማሜ
                                     ላወሳሳህ ደጋግሜ፤
                                   ባገግም - ከቁስለቴ
                                  በስደት ስለት ከተሰነጠረው መንፈሴ፤ ከሰለው ቀለበቴ
                                 አንተ የእኔ ንጹህ ስስቴ
                                 የአድርሽኝ - መስታውቴ
                                 እኮ!~ አንተ አፈሬ የእኔ!
                                  የውስጤ  እውኔ~! ~~~!
                                   ና! ወደ እኔ
                                    ኑርልኝ - በእኔ
                                     ሰብስቤ እኔን - በእኔ።

·       መፍታታት።
 ትንሽ … ይባልለት። ዋናው፤ አደኑ፣ ትግሉ፣ የእግር ጉዞው፤ ጉጉሱ፤ ፈረስ ግልቢያው፤ ሻምላዊ ትዕይንቱ፣ የገና - የገበጣ - ጨዋታው መሰረቱ ከፍጥረተ - ምንጩ ከኢትዮጵያዊነት ነው። ዛሬ ዓለምን እዬገዙ ያሉ የስፖርት እቅስቃሴዎች አብዛኞቹ ከእኛነት የተቀሰሙ ናቸው። በሌላ በኩል ዜግነት በመስጠት በኢንተግሬሽን በኩልም ፋና ነው ኢትዮጵያዊነት። የአጥቢያ ኮከብ! ኢትዮጵያዊነት ታላቅ ትርጉምን መስጠሮ ለቀጣዩ ትውልድ ነገ ሰፊ የምርምር የሥራ መስክ ከፍቶ ይጠብቀዋል አንቱ ለማደረግ። ዓይነታ ማህተም!

ዝና … ዘና ያደርጋል … ገው፣ እንቢልታው፣ ክራሩ፣ ከበሮው፣ ጽናጽሉ፣ ዋሽንቱ፣ ነጋሪቱ፣ የዝማሬ ያያሬድ ኖቶች ውዝዋዜውው፤ ሽብሽባው ምቱ - ስልቱ - ቅኔ ዘረፋው፣ ቅላጼው የ80 ብሄረሰቦች እሰቡት …  ዲካ የለሽ።

·       ክውና!
ኢትዮጵያዊነት ጣዝማ ነውና ፍወሰቱን፤ ድህነቱን፤ ነገን ሳይሰጋ እንደ አማረበት ለመቀበል ዝግጁነቱና እርግጠኝነቱ በሙላት ነው። ኢትዮጵያዊነት ልብም ልካችንም ነው። አክብሮ - ያሰከበረን፤ ተወዶ - ያስወደደን፤ ነፃነት ቀልቦ በራስ የመተማማን ብቁ የመንፈስ ልዩ ዝናር የሸለመን ዘለዓለማዊ ማንነት ነው። ታውቆ ዕውቅናን ያለበሰን ጥንግ ድርባችን ነው ኢትዮጵያዊነት።

ሥጦታ! ዶር. ኦባንግ ኢትዮጵያን (አቶ ኦባንግ ሜቶን) አሰብኩት። ውስጡን ያደነ። ውስጡን ያሸነፈ፤ ለውስጡ ፈቅዶ ከስርክራኪ ቅኝነት እራሱን ነፃ ያወጣ። ሚስጢር የተገለጠለት ለዘመናችን ጥሩ ምልክት ነው።  አብረን ቆየን በውስጥነት።  መልካም የነጮች አዲስ ዓመት። ደህና ሰንብቱልኝ - የኔዎቹ!

ማሳሰቢያ 
       ሀ.   የግጥም አፃፃፍ ፍሰቴ ከውስጤ ፈንገጥ ብሎ የተፈጠረ ስለሆነ እርእሶች በጉልህ የተፃፉት የተሰመረባቸው ናቸው። ቅርፃቸውም በመንፈሴ የተሳሉ በንድፍ የተቡ የውስጥ ለውስጥ መንገዶች

ለ. ወርቀ ዘወንጌል አክሱምና ጎንደር ደብረ ብርሃን ሥላሴ ብቻ ነው የሚገኙት።

. አቶ ኦባንግ ሜቶን እኔው ነኝ ወደ አምስት አመት ሆነኝ ዶር. ኦባንግ ኢትዮጵያ የምለው። „አንተ“ ማለቴ ደግሞ እሱ የፈጠረልኝ ያሰናዳልኝ ቅን አያያዝ ነው - ነፃነት።


ሁሉን የረታ፤ ቅንነቱ - ጸድቆ - አሽቶ - አፍርቶ - አስብሎ ያኖረዋል - ኢትዮጵያዊነትን!
ኢትዮጵያ አምላክ አላት፤ ፈተናዋን ሁሉ የዶግ አመድ የሚያደርግ። ተመስገን!  

መፍቻ ጫን። ጫን ማለት አስር ማድጋ ማለት ነው። አንድ ማድጋ ማለት ደግሞ 25 ኪሎ ማለት ነው። ሁለት ጫን ሃያ ማድጋ  500 ኪሎ ማለት ነው።

ኢትዮጵያዊነት ከመፈጠሩ በፊት ፈተናን አሸንፎ የተፈጠረ ሚስጢር።


እግዚአብሄር ይስጥልኝ ኑሩልኝ።

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።