ገበር።

ገበር።
ይቺ ጥበብ ብቻዋን አስቀድሞ የተፈጠረ
 አዳምን ጠበቀቸው። ከተፈጠረም በኋላ
 እንደ አደራ ዕቃ ጠበቀቸው ከራሱ
ኃጢያትም አዳነችው።“
 መጽሐፈ ጥብብ ፲ ቁጥር ፩
ከሥርጉተ© ሥላሴ (Sergute© Selassie)
ከገዳማዊቷ ሲዊዘርላንድ
07.07.2010


እንዴት ናችሁ የእኔዎቹ ባለለዛዎቹ፤ ባለአደቦቹ የቀንበጥሻ ታዳሚዎቼ። ይህን ጹሑፍ በሌላ አውደ ግንባር ሆኜ የኮልሙኩት ነበር። ተቀምጦ የኖረ ወግ ቢጤ ነው። ያው አእምሮ ያፍታታል። ቃል እና ቃሉን ስታሟግቱት፤ ተጠዬቅም ስትሉት።

እና አደግድጌ ዛሬ እስኪ ቀንበጥዬ ቤት ለእንግዳ በይው ስላት „መሰናዶዋ ሙሉ ነው አምጪው“ አለችኝ ቀልጠፍ ብላ። ለዛውም ለአደብ የተፈጠረች እኮ ናት ቀንበጥሻ፤ ካለ ዕድሜዋ ምርቋን ዋጥ ያደረገች ናት። „ሁኖልኝ! ነውንም“ አከለችበት። ቀጠለችው  በረጅሙ … ትንፋሿን አስከንድታ …  „ይኸው አረቲው ቡክቡካው፤ ነጭ ራያኑ ጠጅ እሳሩን ቅይጡን … አለችና በልዩ አውድ አሰተናገደችልኝ። ስለምን እንደጻፍኩት እኔ እና ህሊናዬ ብቻ ነው የምናውቀው። ብቻ ለፍንጭ ታህል ያልታለመ እንግዳ ነገር ድንገት ከች ብሎ ስለነበረ …

·       የወግ ገበታ።
እነዛ ደማም ፍኩ ርትዑ ቀናት ይዳስሱኛል። እነዛ ዓይነ ግቡ፤ ባለ ውሽክታ ሰዓታት ያጫውቱኛል። እነዛ የንጋት ኮከብ ሰከንዶች ያነጋግሩኛል። ሁሎችም ሰማያዊ ሥጦታዎቼ ናቸውና … እንደ ሰማይ ፕላኔቶች የራቁ መጥምቆች …. መጠመጡኝ በትዝታና ናፍቆት ….   ሽሽ ሽሽ ሽሽት አሰኘኝ ወዴት? አላውቀውም 
…. ሽውታ …

ግን እንዴት አለህ? … አነተ ሳትሆን እኔ ታስሬያለሁ። አንተ ሳትሆን እኔ ምርኮኛ ሆኛለሁ። አንተ ሳትሆን እኔ ተዘግቶብኛል። አንተ ሳትሆን እኔ እርቆብኛል። አንተ ሳትሆን እኔ ተራቁቼ አለሁ ግን እስከ መቼ …?

ቆይታዬ ለአጭር ነበር፤ የተቀመጥኩት ለተወሰነልኝ ቀናት ብቻ፤ የተደላደልኩት በደንበር ብቻ። ግን ሰናይ የተሞላበት፤ ትርምስ የመነነበት ፍጹም ሰላም የሰፈነበት የሥጋ ቤቴ … በጸጥታ ሰኔል።  የእርጋታን ጥራር ተተንርሼ። የገበቴን ሰፈፌ ተደግፌ፤ የሰፌድን ማጣሪያ ይሁን ብዬ …

ጨዋታዬ ከልብ ነበር፤ ዳንኪራዬም ከውስጥ ነበር፤ ሳቄም የመንፈስ ነበር፤ የተፈታታ ~~፡ የተመቼ ~~፡ ~~~፡ የተረጋጋ ~~፡ የአማረበት ማዕዶት ነበረኝ። ስክነቴን በዝላይ ሳስነካው ተቆጭ አልነበረበኝም። መወራጨቴን በእርገጫ ሳስነካው ምላሹ ፍቅር ነበር፤ ለቅሶዬን ሳስነካው አቤት ቁልምጫውና ቅብጥና ቅልጡ የደራ ነበር፤ ግን ዛሬ አዎን! ዛሬ የት ላግኘው …. ዓውዴ … ማዕዴ ቀናት አስገድደውኝ፤ ገፋፍተው … የጥሞና ሠርግ ዕለት ዳሩልኝ። የተደሞ ራት ማዕልት ተሰናዳልኝ። የዕድምታ ፈገገታ ቀትር ገብ ይሁን ተባለበት።
  
የቤተ … ውስጡ የነበረው ብርሃን የዕውነት ነበር። አስራ ሁለት አካላት ተባብረው ማሾ ይዘው ቀን ከሌት ያፍነከንኩኝ ነበር። ውስጡ የነበረው ሙቀት ተፈጥሯዊ ነበር። ውስጡ የነበረው ፍራሽ እጅግ ምቹ ነበር። አንሶላው፤ ትራሱ፤ ካሊሙ፤ ጋቢው እሱ በእሱ የተሰራ በደምና በሥጋ የተሞናሞነ፤ ዘንካታና ዘንጣፋ ነበር፤ ቤቴ በልክ የተሰራ ሆኖ እንደ ቀናቱ ጭማሬ አብሮ ተመጥኖ ያጸደያል። ግን እውነት እንዳአሳኘኝ እቦርቅበት ነበር ግን ምን ይሆናል በነበር ከበረ … በአለፈ ሽምጥ ጋለበ።

እስትንፋሴ ሀዲዱ አህዳዊ ነበር። መተንፈሻ ቧንቧዎቼ ግን ግን እልፍ ነበሩ፤ ጉዞው በጋራ ነበር፤ እንቅልፉም እንዲሁ፤ ሞሰቡም እንዲሁ፤ ብርሌውም እንዲሁ፤ ሁሉም በአብሮነት ያመራበት እጅግ የተዋበ - ቆንጆ - መሸቢያ ዘንጣፋ ስንጥቅ አልቦሽ።

ቀናት በቀይ ጃኖ፤ ሰዓታት በካባ፤ ደቂቃ በበርኖስ፤ ሰከንዱ በመለከት ልግስና ሞልቶ የተትረፈረፈበት የሥጋና የመንፈስ ገነት …. ይደላ ነበር በነበር ብቻ ነበር ሰረገበት። ነበር ግጥግጡን አስነካበት ….

ጌጣማ ሰላማዊ እርምጃችን እኩል ነበር፤ እማደምጠው በቃና አፍንጫ፤ እምጣጥመው በተስፋ ቋት፤ እምጠበቀው በጉጉት ፏፏቴ፤ ቀን ቆጠራውም ተናጠላዊ አልነበረም፤ በህብረት ~~፡ በወል ~~~፡ በማህበር ~~~~፡ በጋርዮሽ ዝክረ ታድሎ። የዛሬው ትርታ ሁነኛው ወፍ አላወጣውም  ትናንትን በነበር አቆላምጦ፤ ነበርን ከሽኖ ትን ያለው ነገር በበር ገበር መጪታ …  

እያንዳንዱ ሰከንድ የሰጠኝ ሐሤት ምንዛሬ የለውም። ወለድ አገድ አልነበረውም። ብድር ክሬዲት እንደ እናንተ ምንትስ ቅብጥርስ ብሎ ነገር የዓለም ጣጣ ምንጣጣ አልነበረውም። 

የተዋጣለት ወጥ ቀጥተኛ የሰቅ ማስመር ግን የመገጣጠሚያ ባላንጓ፤ ገደብ ያለተሰራለት ክንድዮሽ፤ መጠነ ሰፊ ባለተረከዝ ጆሮ፣ ሊመዘን፣ ሊለካ ከቶ የማይችል ቧ ያለ ጥርሰ ከናፍር ዛሬ የማይገኝ የሩቅ ህልም ሆነ እንጂ … አጀማመሩማ አንቱና አናት ነበር …የሃሳብ ዝማማዌ ዘና ብሎ ግን ሳይቸኳኮል አለን አለን ይላል እንደመኖሩ ሊያኖር፤ እንዳለመኖሩ ሊለካ ሊመዝን ሊከናዳው። በመኖር ውስጥ ያለ እህል ውሃ በውሃ ውስጥ የሰገረው ዋነተኛው …

·       እንዲህም አለኝ …
„እንዳልመለስ ገረጀፍኩኝ፤ እንዳልሄድ ባለሁበት አረርኩ፤ እንዳልበቅል ጠነዘልኩኝ፤ እንዳልጓዛ ዘነጠሉኝ፤ እንዳለፈራ ነቀሉን፤ እንዳልተወው ነፍስ በቀጠሮ አልወጣ አለኝ።

ገሃዱ ዓለም አከሰለኝ …. አሳከከኝ። ቀምቶኝ እስረኛ አደረገኝ። ቀምቶኝ ተጠማኝ አደረገኝ፤ ቀምቶኝ ሃሰብ አበራከተኝም፤ ቀምቶኝ … ብቻ ቀምቶኝ ስስቱ ገደለኝ። ግን ስለምን ይሆን አልኩት?ይመጣል እያሉ ጥበቃው ገደለኝ፤ ዛሬ ነገ እዬተባለ ልቤ ተንጠልጥሎ አፈር እንዳልሆን ሰጋሁኝ ግን መቼ ነው ከናፍቆቴ እንቁላሌ ጋር እምገናኘው …. ትካዜ … ሲዘመዘም።“

             የጥዋቱ ቤቴ
             መዳህኒቴ ክብረቴ
             ሳወሳህ ናፍቆቴ … ትዝታ ብቻ ስንቄ
             የጽንሰት ድንቄ ……

„ህም! ሳለጋኝህ እንደተመኘሁኽ የቀረኸው የዓይኔ መንፈስ ሆይ! ገፍቼህ፤ ቁብ ሳልሰጥህ፤ ለእትብት ቤተኞቼ አድልቼ አንተን በማስቀዬም ድርሻህን አከሰምኩት። እውቅና መንሳቴ የህሊናዬ የፈተና ትርታ ሆነ። ስለሆነም  እንዲህ ናን ለግሶ ስንስመነመን ከመሼ ስገነዘበው ፈራሁት። ለተገነዘብኩት ኪራይ አለመጠዬቄን ግን አመሰገንኩት“ አለኝ።
አቤቱ ፈጣሪያችን ሆይ! የዕውነት ቀኗን ስጠን።
የኔዎቹ ኑረሉልኝ።
መሸቢያ ጊዜ።

እግዚአብሄር ያጽናችሁ።

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።