የግርግር ፖለቲካ ግብዕቱ ተፈጽሟል።

የግርግር ፖለቲካ ግብዕቱ ተፈጽሟል።

„የሰው ልብ መንገድን ያዘጋጃል
እግዚአብሄር ግን አካሄዱን ያቃናለታል።“
ምሳሌ ፲፮ ቁጥር ፱

ከሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
20.12.2018
 ከጭምቷ ሲዊዘርላንድ

·       መቅድም።

ጤና ይስጥልኝ የኔዎቹ ቅኖቹ እንዴት ናችሁ? ደህና ናችሁ ወይ? አላዛሯ ኢትዮጵያ ከምትታመስበት መከራ አንዱ በግርግር ፖለቲካ ነበር። በግርግር ፖለቲካ አቅም አላግባብ መባከኑ ብቻ ሳይሆን፤ በገፍ ተጨፍለቀው ወይንም ተደፍጥጠው የሚቀሩ ቅኖችን  ዘመን ሲያስተናግድ ኖሯል በድል አጥቢያ አርበኞች።
  
·       እፍታ።

በአንድ የግርግር ማዕቀፍ የሚነሱ ሃይሎች የሰከኑ ጉዳዮችን በአሉታ እና በማግለል የመንፈስ ጥሪትን መበከላቸው ብቻ ሳይሆን፤ የቅንነት አንበሎችን ጽልመት በማልበስ ከሜዳ ውጭ በደቦ የሚያደርጉበት ዘመን ጠገብ መከራ እንሆ ዘንድሮ አላዛሯ ኢትዮጵያ መገላገሏን መጋቢት 24 ቀን 2010  አብሯል።

በጣም የዘለበው የአላዛሯ ኢትዮጵያ አሳር የነበረው፤ አውሎን የተጠለለ ውሃ ያዘለው ተራራ ማለት ያስችለኛል የግርግር ፖለቲካ ነበር። አንድ ህዝባዊ ንቅናቄ በተነሳ ቁጥር በኮፒ ራይት በመታመስ አዳዲስ ድርጅቶችን በመፍጠር፤ መንፈስ በመበተን ሲተራማስ የነበረው፤ ጭራሽ ስክነት የነሳው ወጀብ ከኢትዮጵያ የተነቀለበት አዲስ ምዕራፍ ላይ እንገኛለን - ዛሬ።

ዛሬ የሰከኑ፤ ደርባባ፤ በሳል የፖለቲካ ሊህቆች የግል ኢጎቸውን ሳይሆን ለ50 ዓመት የዘለቀውን የግራ ፖለቲካ የሥልጣን ጥማት ባይረስ በአመራር ብልጫ፤ በጥበብ በተዋደደ ክህሎት ተሟጦ ከኢትዮጵያ እንዲሰደድ አድርገውታል።

እራፊ ትራፊ ማሳ ቢኖረው ትግራይ ላይ ብቻ ነው። የግራ ፖለቲካ መርዛማ ጭራ አገር ምድሩን በወጨፎ አምሶ የመንፈስ ጥሪትን በማምከን፤ አቅም ያላቸውን ብርቅዮችን በማስገለል፤ እንደ ጠላትም በማዬት፤ እንዲያም ሲል በማስወገድ ሰፊ የሆነ በደል በትውልድ ላይ ተፈጽሟል።

 በቁርሾ እና በቋሳ ትውፊትና ትሩፋቶች ሳይቀር ፍዳቸውን በልተዋል። መተሳሰብ አንዱ ትውፊታችን ነው፤ መከበባር ሌላው ትውፊታችን ነው ግራ የበጎ ነገር ምክነት ስለሆነ የተፈጥሯን ንጡህ ጻዕዳ ቅባኦቻችን ዶግማውን ሁሉንም አጭዶ ቅርጥም አድርጎ ባልተወለደ አንጀቱ በልቷቸዋል ወይንም አሰምንኖ አፈናቅሏቸዋል።
 
ዕድሜ ለአማራ የህልውና የማንነት ታገድሎ እና የኦሮሞ ንቅናቄ እንጂ ሥር የሰደዱ የአልዛይመር በሽታዎችን ሁሉ እንዳይደገሙ፤ እንዳይሰለሱ፤ እንዳያጨበጭቡም፤ ፈላቸው ሳይቀር ግብዕታቸው ተፈጥሟል። ተመስገን!

አቅምን፤ ቅንነትን፤ ደግነት፤ አብሮነትን ሲበላ የኖረው የመንፈስ ፍዘነት አውራሪስ የግራ ፖለቲካ ቆሌ ቅስሙ አይሆኑ ሆኖ ተስበሮ ዛሬ በመቻቻል፤ በመደማመጥ፤ ሆኖ በመገኘት ማህደር ውስጥ መንፈስ ይሰከን ዘንድ ዘመን የአደብ ጠበለ ጣዲቅ የረጫጨበት ወቅት ላይ እንገኛል። ተመስገን!

·       ዕለታዊነት።

የፖለቲካ ድርጅቶች ከተነሱበት ዓላማ ውጪ በሆኑ ጊዜያዊ ህዝባዊ ሞገዶች ውስጥ አለን በማለት ያከበሩትን ብትህትና ወይንም በጥገኝነት እንደ ድምጻችን ይሰማ ዓይነቱን ወይንም የኦሮሞ ንቅናቄን፤ የናቁትን ደግሞ እንደ አማራ የማንነት የህልውና ታገድሎ በመጫን እና ካለተልዕኳቸው ንቅናቄዎችን የራስ በማድረግ በእለታዊነት በግርግር ይተሰቡ የነበሩ የሥልጣን መራኮቶችን ይህ ዘመን አርቆታል። ገሮተታል። 

ይህም ምራቁን በዋጣ የፖለቲካ መስመር አገር እንዴትን መምራት እንደሚቻል፤ የህዝብ አንጡራ ታሪካዊ ተጋድሎች እንደምን መከበር እንደሚቻላቸው፤ አዲስ በምክንያት የሚያምን ትውልድ እንዴት መፍጠር እንደሚቻል፤ ዘመኑ እራሱ ከሊቅ እሰከ ደቂቅ ላሉ ለፖለቲካ ስልጣን ሹም ሽር ለሚተጉት ሁሉ ተቋም ሆኖ ቆሞ እያስተማራቸው ይገኛል። ተመስገን!

በኢትዮጵያ ባልተለመደ ሁኔታ የተገኘው ይህ የምርቃት ረድኤት ልብ ያላቸው ቅኖች የእኔ ብለው ካደመጡት ትውልድን በጠዳ፤ በፍጹም ሁኔታ በሰከነ፤ በፍጹም ሁኔታ በተረጋጋ ብቃት አገር እንደ አገር ማስቀጠል ብቻ ሳይሆን፤ መጪው የትውልዱ ዕጣ ፈንታ የተከዘነ የቂም ዕዳ የማያወራርድበት፤ የማይወቅስበት - የማይነቀስበት፤ በታሪኩ አንገቱን የማይደፋበት፤ አንዱ ባይታዋር ሌላው ቤተኛ፤ አንዱ አሳዳጅ - ሌላው ተሳዳጅ፤ አንዱ የክት ሌላው ባይታዋር የማይሆንበት ሥርዓት የመፍጠር ብጡል ጊዜ ላይ እንገኛልን። ተመስገን!

የነገ አገር ተረካቢዎችም በሚኖራቸው ዘመን የራሳቸውን ዘመን ገርተው፤ መርተው ለመልካሙ ነገር የሚመሰገኑበት መልካም ላልሆነው ነገር የሚወቀሱበት ሁኔታዎችን በማመቻችት ላይ ይገኛል ይህ አዲሱ የፖለቲካ ባህል። ራስ በሰራው መወቀስ የተገባ ነው። ራስ ባበጁትም መሞገስ የተገባ ነው። ንጥቂያን ዘረፋ የታሪክ የአያት ቅደመ አያቶቻችን ሌጋሲ አይደለም። ያለጠፋም መወቀስ መነቀስ ትሩፋታችን አይደለም። ይህ መጤ የተስቦ በሽታ ነው። 

በሌላ በኩል በ50 ዓመቱ የዴሞክራሲ ጥማት ተጋድሎ ውስጥ ወጣቶች ከመማገድ ውጪ፤ ወላጆች የወላድ መሃን ከመሆን በዘለለ ያገኙት፤ ያተረፉት ነገር የለም። እንዲያውም በሌሉበት ዕዳ አወራራጅ የሆኑበትን፤ ቀንበር ተሻከሚ የሆኑበት ድርሳን ነው ያለው። 

ይህ እንዳይቀጥል ነው አሁን የለውጥ ሐዋርያት ፊት ለፊት ወጥተው በጥበብ ተጋድሎ እያደረጉ የሚገኙት። ወጣቶችን፤ ሴቶችን ወደፊት በማምጣት ዘመናቸውን እራሳቸው እንዲመሩ፤ እንዲገሩ፤ እንዲገስጹ፤ እንዲያሳምሩም ሁኔታዎች ባልተለመደ ሁኔታ እየተበጁ ይገኛሉ። ይህም ማለት መወቀስ ወጣቶች ካለባቸው ራሳቸው በተረከቡት የሃለፊነት ቦታ ልክ ይሆናል ማለት ነው። የቀደሙው ግን ወጣቶች ይማገዳሉ አክተሮች ደግሞ ከእነ ዝናቸው ዘመን ተዘመን ይሸጋገራሉ በቃኝን ሳያጠጉ ... 

·       ወጣት ሆይ!

ወጣቶች ዘመኔ የእኔ የሚሉት ሥርዓት ለመፍጠር የሚካሄደውን ትግል በሙሉ አቅም እና ክህሎት ከደገፉት፤ ካገዙት እነሱንም የሥልጣኑ ባለቤት ለመሆን የሚያስችል፤ ግፊያ ሆነ ግት የሌለበት፤ ይልቁንም አቅምና ክህሎት ተመጣጥኖ እንደ ምዕቱ ሥልጣኔ የድርሻቸውን ይወጡ ዘንድ ክርችም ብሎ የተዘጋው በር በላቀ ዳዊታዊ ምስብክ  ብሎ የተከፈተበት ዘመን ላይ እንገኛለን። ተመስገን!

ወጣቶች ባልበሉት ዕዳ ከፋይ የሚሆኑበትን፤ የጠነዘለ ዕሳቤ ሁሉ መልክ ለማስያዝ አዲስ ምህንድስና ላይ ስለተሆነ፤ ዘመኑ ለዘመኑ ወጣቶች በቂ ዕውቅና በመስጠት ላይ ይገኛል። ስለሆን የኢትዮጵያ ወጣቶች እና ሴቶች በረባ ባረባው ሆድ ሳይብሳቸው፤ ሆደ ቡቡ ሳይሆኑ፤ የትርምስ አውራሪስ ሳይሆኑ፤ ጥቅማቸውን ተጻረው ሳይቆሙ ለዚህ አዲስ የፖለቲካ የባህል ለውጥ ዘበኛ፤ ጠባቂ፤ አዳምጭ፤ ተዋናይ በመሆን የድርሻቸውን መወጣት ይኖርባቸዋል። የራሳቸው ዕድል ነውና።

·       ውሃማ ቀለም ያለው ዘመን ትርፋማ ነው።

በዬትኛውም አቅጣጫ የሚሰነዘረው ወጀብ እነሱ በለውጡ በዘለቄታ ተጠቃሚ እንዳይሆኑ፤ ሥልጣን እርስተ ጉልት አድርገው ያያዙት አያቶቻቸው የቦታ አልቀም ግርግር መሆኑ ልብ ብለው፤ ለአብይ ሌጋሲ ማቄን ጨርቄን ሳይሉ፤ መንፈሳቸውን የትም ሳያብክኑ ከጎኑ መሰለፍ ይኖርባቸዋል።

ዘመኑ ለወጣቶች እና ለሴቶች አዲስ ቀለማም ነው። ቀለሙ ውሃማ ነው። ውሃ ደግሞ ሁለመና ነው። ውሃ ሥልጣኔ ነው። ውሃ ህይወት ነው። ውሃ የጥማት ማርኪያ ነው። ውሃ ሰብል ነው። ውሃ ተስፋ ነው። ውሃ አልባ ነፍስ በምድር አትኖርም።

ስለዚህ ይህ ውሃማ ቀለም ያለው ዘመን ለህልውናቸው ወሳኝ መሆኑን ተገንዝበው ዘመናቸው ለሰጣቸው ምርቃት ተሸላሚ ለመሆን ልባቸውንም እስፍተው፤ መንፈሳቸውን አድርገው በቅንነት እና በአዎንታዊነት ነገሮችን የማዬት ሁኔታን በልቦናቸው መፍጠር ይገባቸዋል።

ለወጣቶች ሆነ ለሴቶች ጠቃሚው መንገድ የአብይ ሌጋሲ መሆኑን አምነው በመቀበል፤ በውስጡ ለመዝለቅ የእኔ ሊሉት ይገባል። ወጣቶች ጥቅማቸውን ተጻረው መቆም አያስፈልጋቸውም። እንደ ገናም የኢትዮጵያ ወጣቶች የአማራ እና የኦሮሞ 50 ወጣቶች ራሳቸውን ገብረው ላመጡት ለውጥ ዘብአደር መሆን ይጠበቅባቸዋል። ለውጡ የራሳቸው ትሩፋት እና ታሪክ ነውና አሳልፈው መስጠት አይገባቸውም።

ወጣቶች ሆኑ ሴቶች በአጃቢነት እና በእግረኛ ተሰላፊ ታገይነት ከመሰዋት በስተቀር አቅም ባለው የፖለቲካ ተሳትፎ ላይ በመቁንን እና በበይ ተመልካችነት የነበረው ዘመን አሁን ደህና ሰንበት እዬተባለ ስለሆነ ለዚህ እርምጃ ባላ እና ወጋግራ መሆንም ይጠበቅባቸዋል።

ይህ ውሃማ ቀለማም ዘመን የኢትዮጵያ ወጣቶች እና ሴቶችን በሙሉ አቅም፤ በክህሎታቸው መጠቀም የሚያስችልበት ዕውቅና በመሰጠት እረገድ በመሽኮርመም ሳይሆን በግልጥ እና በድፍረት እውን እዬሆነ ያለበት ዘመን ላይ እንገኛለን - ዛሬ።

እርግጥ ነው ይህ ሂደት ትግራይ ላይ ለጊዜው እውን ባይሆንም የትግራይ ወጣቶች እና ሴቶች ከበረቱ ግን የረድኤቱ፤ የበረከቱ ተሳታፊ ይሆኖ ዘንድ እናት አገራቸው አላዛሯ ኢትዮጵያ ብሄራዊ ጥሪ አቅርባላቸዋለች። እናታቸው ምንግዜም እጇን ዘርግታ ትጠብቃቸዋለች።

እንሱ ከወንጀሉም፤ ከጭካኔውም፤ ከቋሳ ማወራረጃውም፤ ከሰባዕዊ ረገጣውም፤ ከዝርፊያውም፤ ከመስፋፋቱም፤ ከማሰደዱም እጃቸው እንደለለ አሳምራ እናታቸው ታውቃላችና። በዚህ መስጋትም ተስፋ መቁረጥም አይኖርባቸውም። ተጠያቂዎች ተቀምጠው እነሱ የሚጠዬቁበትም ምንም የሃቅ ማህደር የለም እና። እናት ኢትዮጵያ ሚዛን አላት፤ እሷም ሚዛን ናት፤ እሷም እራሷ ችሎትም ህግም ናት እና። 

ከሁሉም የሚጠቀመው በዚህ በአብይ እናታዊ ሌጋሲ የትግራይ የዛሬ ወጣት፤ የነገ ታዳጊ ወጣት፤ የነገ ወዲያ ህጻናት ከቁርሾ፤ ከቂም እና ከሸር በጸዳች ኢትዮጵያ ውስጥ የመኖር ዋስትናቸውን በሚያስከበረው አዲስ ፖለቲካዊ ባህል ብቁ ልባቸውን ብቻ ሳይሆን ህሊናቸውንም በመስጠት አደብ ገዝተው መጪውን ብሩህ ዘመን አስበው ከለውጡ ጎን በማያወላዳ ሁኔታ መቆም ይጠበቅባቸዋል።

በዚህ የለውጥ ሂደት ከሁሉም የኢትዮጵያ የማህበረሰብ ክፍሎች የትግራይ ቀጣይ ትውልድ ነው የሚጠቀመው። ይህ የለውጥ ምህንድስና ጊዜያዊ የመንፈስ ሃብት አስገኝ ሳይሆን ዘላቂ የመንፈስ ሃብት ሊያሰል የሚችልበት አዲስ መስመር ነውና ይህን አዲሳዊነት ሳያሸልኮ ወይንም ሳያከስሉ ጥበቡን እና ብልህነቱን ፈጣሪ / አላህ እንዲገልጥላቸው ጸንተው በመጸለይ ለለውጡ ውስጥን የመስጠት እርምጃ ጊዜ ሳያጠፋ መከውን ይኖርባቸዋል።

የትግራይ ወጣት ማስብ ያለበት ስላልተወለዱት፤ ስላልተፈጠሩት፤ የነገ ጽንሶች መሆን አለበት። ዛሬ ነገ አይደለምና፤ የወያኔ ሃርነት ትግራይ የማንፌስቶ ማሀበርተኞች መሪዎቹ ዛሬ ትግራይ መሬት ላይ ከምድር በላይ ሆነው ቢፎክሩም፤ ነገ ሞት አይቀሬ ነውና ሁሎችም ከምድር በታች ሲሆኑ ለተተኪው ትውልድ ዋቢ አይኖራቸውም። ትተውላቸው የሚያልፉት ተወቃሽነትን ብቻ ነው። የሰው ህሊና ሊሸከመው የማይችል በደል ፈጽማዋልና። ኢትዮጵያን ባዕድ አገር ቢገዛት እንኳን እንዲህ አይነት አረመኔነት፤ እንዲህ ዓይነት አገር ራቁትን የማስቀረት መከራ አይፈጽምም ... 

ዋቢ ዕውነት ስለሆነ፤ ለእውነት ዋቢ መሆን ጊዜ ሰጥ ትርፉማ ሰብላማ ነው። ነገን ማስቀጠል የሚቻለው እያንዳንዱ የትግራይ የዛሬ ወጣት ከእውነት ጎን በጽናት መቆም ሲችል ብቻ ይሆናል። ቢያንስ የሰው ልጅ ሰቆቃን በእኛ ቢደርስ ብለው ማሰብ ይኖርባቸዋል። ለሚያልፍ ቀን የማያልፍ እድልን ማሳለፍ ብልህነት አይደለምና

·       መደዴ የፖለቲካ ግርግር ትውልድን አያንጽም። 

በኢትዮጵያ የፖለቲካ ሂደት ውስጥ ፓርቲ ስለሚባለው በውል ዶግማውና ቅኖናው ሳይታወቅ ነበር በመደዴ ስንተረማስ፤ ስንቧከስ፤ ስንጋጭ፤ ስንፋጭ፤ ስንረጋገም የኖርን። ስለምን? ፖለቲካች መርሁ ግርግር ስለሆነ።

ድርጅት የሚባለው መግለጫ በመግለጫ የሚሆነው አንድ ህዝባዊ እንቅስቃሴ ብቅ ሲል እንጂ በራሱ ጊዜ ሰክኖ እና ታስቦበት፤ እንዲሁም ታልሞም በፖለቲካ ድርጅቶች የብቃት የማስተዋል አቅም መሪነት የተነሳ ህዝባዊ አመጽ እና ዝልቅ ተጋድሎ ታይቶ አይታወቅም።

በሌላ በኩል ድርጅቶች አለን ከሚሏቸው አባሎቻቸው ጋር የመንፈስ ውህድናቸው አራባ እና ቆቦም ነው። የአባሎቻቸውን መብታቸውንም ጠበቀው አያውቁም እኔ እንደምታዘበው። ሲዋህዱ፤ ሲጣማሩ አንድም ጊዜ የአባሎቻቸውን ፈቃድ እና ይሁንታ ጠይቀው አይውቁም፤ በሌላ በኩል አባሎቻቸው ድርጅቱ ስለተፈጠረበት ዓላማ እና ግብ ስለሚያራምደው አይዲኦሎጂም አቅም ያለው የህሊና ብቃት የላቸውም። 

በህሊናዊ ጉዳይ አቅም ያለው  በአጀንዳ የተያዘ ተከተታይ ተግባርም ተከውኖ አያውቅም። ጥድፊያው በዕለታዊ ጉዳይ፤ በደራሽ ፈረሰኛ ውሃ ሙላት ብቻ ነው። ለዚህ ነው ገና ሳይጠኑ ሲፍረከረኩ እና ሲናዱ የሚታዬት። ተተኪ በማብቀል እረገድም መሃኖች ናቸው። 

አይደለም አባሉ መሪው ራሱም ቢሆን የሚመራበትን አይዲኦሎጂ አያውቀውም። አሁን አቶ አብርሃም ደስታ ከዋልታ ቴሌቪዥን ጋር ሰሞኑን በነበራቸው ቆይታ ዝርክርኩ ነው የወጣው የድርጅታቸው ፍልስፍና። ድርጅቱ በቁሙ ነው ቁሞ ቀር የሆነው። ይህን ገመና ተሸከመው ነው ድርጅቶች አባሎቻቸውን የካቴና የባሩድ ስንቅ ሲያደርጉ የባጁት። እነሱም ሥልጣን ህልማኞች የሚሆኑት የተሻልንም ነን የሚሉት። 

ሌላው ቀርቶ በራሳቸው ጊዜ የተነሱትን ህዝባዊ ንቅናቄዎች እንኳን መብቱን ጠበቀው ዕውቅናውን ለእነሱ ሰጥቶ የተነሱበትን ዓላማ መደገፍ፤ መርዳት ሲገባ መሪ ለመሆን በሚገጥመው ግርግር የተነሱ ህዝባዊ እንቅስቃሴዎች ቅስማቸው ተሰብሮ፤ ህልማቸው ነኩቶ፤ ቀንበጡ ተስፋቸው አፍሮ፤ ራሳቸው የተጋድሎ አስገኞዎች ብቻቸውን ሁለመናቸውን ገብረውበት ግን ለድል ሳይባቁ ባክነው ቀርተዋል። በዚህም ብዙ የሰው ግብር ተገበሮበታል።

የአሁን ከ50 ዓመቱ የግራ ፍልስፍና የአመራር ሂደት የሚለዬው የኦሮሞ ንቅናቄ እና የአማራን የህልውና አብዮት በማድመጥ መስዋዕትነቱን ዋጋ እንዲኖረው እና ብሄራዊ ዕሴት አንዲሆን በማደረግ ታሪክ የሰሩ ብልሆች ከግርግር ፖለቲካ ጋር ንክኪ የሌላቸው፤ በፖለቲካ ሳይንስም ብቁ ሙያዊ ስክነታዊ አቅም ያላቸው፤ በሰብዕናቸውም ሥልጣን አልሻህም ብለው የገፉ፤ ግን ለህዝብ መስዋዕትነት እውቅና በመስጠት ተጋድሎዎችን ያከበሩ አላዛር ልጆች ኢትዮጵያ ስለሰጣት ያ ስንታመሰበት የኖርንበት የ50 ዓመት የግርግር ፖለቲካ ግብዕተ መሬቱ ተፈጽሞ። ዎህ አልን!ተመስገን!

ቀሪው ጊዜ መሬት ላይ በሚሠሩ የበቁ፤ የነቁ፤ በውል የተደራጁ፤ በቅጡ ያስተዋሉ ተግባራዊ ተሳትፎዎች ልኬታቸው በመሰፈር ብቻ ይሆናል ለወንበር የሚያበቁት። ከዚህ ውጪ በግርግር የፖለቲካ ወጀብ እና በምዕራባውያን ግፊት እና ተጽዕኖ 4ኪሎ የማይታስብ መሆኑ ተረጋግጧል።

ሁሉም ራሱን አርቆ፤ አርሞ እና ገርቶ ዘመኑ የሚጠይቀውን የሰከነ ፖለቲካዊ አቋሙን አደራጅቱ፤ ወጣ ገብ የሆነው ሰብዕናውንም ቀጥቶ የፍላጎቱን ራዕይ ማግኘት የሚችልበት መስመር ብቁ ማህንዲሶች አዲስ መስመር ዘርግታዋል።

ቀደም ባለው ጊዜ ዶር ለማ መገርሳ፤ ዶር ገዱ አንዳርጋቸው፤ አቶ ደመቀ ሞኮነን፤ ዶር አንባቸው መኮንን፤ አሁን ከሆነ ደግሞ ክብርት ወ/ሮ ሙፍርያት ካሚልን ጨምሮ የሰከነ፤ የረጋ በእዮባዊነት የበለጸገ አዲስ የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ባህል ምድሪቱ ጀባ ተብሎላታል፤ ወግም ደርሷታል፤ የማይጠገቡ፤ ሊደመጡ የሚፈቀዱ መሪዎችን ፈጥራልናለች። በዚህ ላይ በሰብዕዊ መብት ዙሪያ አቅም ያላቸው አንስት ፕሬዚዳንት ወ/ሮ ሳህለወርቅ ዘውዴ መጨመር ምርቃታችን ጉልበት እንዲያገኝ መልቲ ባይታሚኑን አግኝቷል።  

ይህ ጅማሮ፤ ይህ ውጥን በራሱ በግርግር የተከወነ አይደለም። በቅጡ ታቅዶ በቅጡ ተደራጅቶ በብልህነት ተሰልቶ የተከወነ ነው። አጀመማሩ ቢያምረን፤ ቢመቸን፤ ቢደላን ነው ከጅምሩ በድፍረት ወጥተን እኔ ለማውያን ነን ያልነው የዛሬ ዓመት። ድርጅት ህይወት እንጂ ገበርዲን እና ከረባት ባለመሆኑ። ድርጅት ሲሆኑበት በመሆን ውስጥ እውነተኛ የጠራ መረቅ የሆነ ተግባር ከደላው ቀልቡን፤ ልቡን፤ መንፈሱን ለመሸለም ስስታምነት የለውም እና። የድርጅት ህይወት በዚህ ነው የሚቃኘው።

·       …. ሂደቱ እንዲህ ነበር … ማድመጥ ለሰጣቸው፤

 መጀመሪያ የOBN ባህርዳር ተጉዞ ልዩ ዘገባ ሲያቀርብ ያ አዲስ የመንፈስ ቅኝት ነበር። ወጣቶች በጣና ኬኛ ወደ ባህርዳር ሲሄዱ አብሪ የመንፈስ ወታደሮች ነበሩ፤ በአብይ ኬኛ ጎልማሶች፤ የአገር ሽማግሌዎች፤ አባ ገዳዎች፤ የፖለቲካ ሊሂቃን ባህርዳር ሲሄዱ የግርግር ፖለቲካ የማሸነፊያ መለከት ነበር፤ ደብረብርሃን ላይ የአማራ እና የኦሮሞ ሊሂቃን ጉባኤ ሲያካሂዱ ስክነትን መርህ ለማድረግ ዕወጃ ነበር። ኦህዴድ ለዬት ያለ መግለጫ በምክር ቤቱ ሲያወጣ አዲስ የምህንድስና ነጋሪት ነበር፤ ዲሞክራሲ ማዕካላዊነትን አከርካሪ እንኩት ለማድረግ አህዱ ያለም ነበር።

የዛ ውሳኔ ጥሪ ተፎካካሪዎችን/ ተቀናቃኞችን/ ተቃዋሚዎችን በሚመለከት እራሱ የአዲስ የፖለቲካ ሥርዓት ባህል ዋዜማም ነበር ጥሪው ፍቅር ነበርና - የኑልን። 

ኦህዴድ ዶር አብይ አህመድን የኦህዴድ ሊቀመንበር ሲያደርግ የ50 ዓመት የዴሞክራሲ ጥማት የእርካታ ብሄራዊ አዲስ ቀለማም ቀን ነበር። ጸሐይ ለ ኢትዮጵያ ወጣችላት።

ብአዴን ሙሉ ድምጹን ሳይስስት ደቡቦች 8 ድምጽ አክለው በድምሩ 108 የፓርላማ አንበሶች ዶር አብይ አብይ አህመድን ጠ/ሚር/ አድርገው ሲመርጡ የዴሞክራሲያዊ ማዕላዊነት ድርጃታዊ ሥራ ተቀበረ ከላ ይፍታህ። ለነገሩ በህማማት ስለተከወነ በህማማት ህልፈት ከመጣ ፍትሃት የለም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ህገ ቤተክርስትያን። ሚስጢሩ ያለው ተሰዚህ ላይ ነው። 

ለዚህ የቀብር ሥርዓት የብአዴን ሊቀመንበር አቶ ደመቀ መኮነን ራሳቸውን ከጠ/ሚር እጩነት ሲያገሉ እና ድምጽ እንዳይሸራፍ ሲያደርጉ ያ ቀን የወያኔ ሃርነት ትግራይ የ100 ዓመት ህልም እንዳይመልስ ሆኖ እንጦርጦስ ተላከ፤ ሶሻሊዝም ሙት መንፈሱ ብቻ እጣ ነፍሱን ጭል ባለ በርሃ ውስጥ መለመላውን እንደ ተነጮፋረረ ቁመ ቀርም ሆነ ..አሽዋ ውስጥ። ግራ መጋኛ ነው ... ፈጣሪ ንቅል ያድርግልን!
  
ሲጀመር ጣና ላይ ነበር እርገቱም በጣና ውሳኔ በልበ ሙሉነት ዝቀሽ በሆነ የድምጽ ልዕልና በማህተም ነበር። ሰሞኑን አቶ አሰመላሽ ወ/ሥላሴ የሰጡት መግለጫ የለውጡ ቀንዶች እኛው ነን ባዬች ሆነዋል ያን ጊዜ አንዲት ቆራጣ ድምጽ አልሰጡም እነሱው።

በሌላ በኩል ጠ/ሚር አብይ አህመድ በተሾሙበት እለት ዶር ደብረጽዮን ከመቀመጫቸው ለመነሳት ሰውነታቸው ያረግድ ነበር፤ እራሳቸው አቶ አስመላሽ ፍቅርን አልቀበልም ብለው ሲገፉት አይናችን አይቷል። ለነገሩ ደግሞስ ለቀብራቸው ዕለት ስቀን ነበር ማለቱ ከተረብ ውጪ እዬረሩ መሳቅ ካለሆነ በስተቀር አልፈለጉትም አልፈቀዱትም፤ እዬጎመዘዘቸው የተቀበሉት በቃኝ ለማይለው ህልማቸው ቀንበር ነበር ለእነሱ፤ ለእኛ ደግሞ የድል የምስራች የብሥራት ዕለታችን ነበር። አሁንስ ማነው እያተራመሰ ያለው። ለውጡን ስለደገፉ ይሆን የሙት መንፈስን የሙጥኝ ሲሉ የባጁት?አሁን እኮ ደምር ላይ ናቸው ለስንብት ... 

ወደ ቀደመው ምልሰት ሲሆን የወያኔ ሃርነት ትግራይ ማንፌሰቶ መቀበሩ ብቻ ሳይሆን የግርግር ፖለቲካ በኢትዮጵያ የማከተሙ የከበረ እለት ነበር መጋቢት 24 ቀን 2010 ዓም። ብዙ ነገረ ነው ጥርግርግ ብሎ ከባህር ከገደል የተጣለው። አቅም ብቃት የመሪነት መክሊት የተስፋ በረከት የሚባለው ሁሉ ማንዘርዘሪያ ተገዝቶለታል። ረቂቅ ነው ትርፉ፤ ሚስጢር ነው ትሩፋቱ የመጋቢት 24 ቀኑ 2010 ውሎ እና ስንብቾ …

ከዚህ ጋር በተያያዥ ሁኔታ የሚታዬው የአብርሃም ወአጽብሃም ዘመን በምልሰት ኢትዮጵያን በስንት ዘመኑ ያ ንዑድ መንፈሱ ጎበኛት። በሥህነ - መንግሥት ብቻ አይደለም፤ በቅድስት ኦርቶዶክስ ሃይማኖትም አሁን ኢትዮጵያ ሁለት ፓትርያርክ ነው ያላት።

·       አቅሙ እዳሪ የፈለቀ የኩሬ ውሃ አይደለም።

ዶር አብይ አህመድ የመጨረሻ ድግሪያቸው በሰላም እና ደህንነት ነው ያገኙት፤ ዶር ለማ መገርሳ የፖለቲካ ሳይንስ ምሩቅ ሲሆኑ ከፍተኛ ድግሪያቸውን በዐለም አቀፍ የፖለቲካ ግንኙነት ክህሎት ነው፤ ዶር አብይ የሚሊተሪው ዶር ለማ ደግሞ በሲቢሉ በአገር ደህንነት ጉዳይ ባለሙያዎች ናቸው፤ ይህን ነው እዮር በሥርዓተ ተክሊል በበዛ የመንፈስ ጸጋ ያወዳደው የዋህደው። ዳኑ ሲለን፤ በቃችሁም ሲለን ከግግርግር እና ከበረዶ ግግር ድርድር ሲማለደን። 

በተጨማሪነት አስተዳደራዊ ጥበብ እና ዲጂታሉ ዓለም በመዳፍ ውስጥ መሆን፤ የሥነ - ጥበብ ቤተኛነትን አክሎ የጠ/ሚር አብይ ካቢኔ የአመራር ልቅናው ጥልቀት እና ምጥቀት ምራቁን ከዋጠ ሰብዕና ጋር ተዳምሮ ይህ የለውጥ አመራር፤ እንደ ተለመደው በኮሽ ኮሽ፤ በግርግር የተለምዶ ፓለቲካ ሊደፈር ከቶ አልቻለም። ሃቁ ይሄው ነው።

ይህ ስለታወቀ ነው በ4 ወራት ውስጥ ሶስት ጊዜ የግድያ 4 ጊዜ የኩዴታ ሙከራ ተደርጎ በፈጣሪ ሃይል እና በህዝብ የወል ጸሎት የታሰበው ሁሉ መክኖ የቀረው። ይህ ልቅና ጥበቡን አጉልቶ በሰጠው ብቃቱ የማይደፈር ጥምር ውህዳዊ አቅም፤ ክህሎት፤ ብስለቱ በጥበብ ኪናዊ ቁመና ላይ ስለሚገኝ በኢትዮጵያ ሲያምስ የኖረው የግርግር ፖለቲካ ላይመለስ፤ ላያገግም፤ ላይበቅል፤ ላይደገም፤ ላይስለስ መራራ ስንብቱ እንሆ ተከወነ። ስለዚህም ነው በዬቦታው ምሾ ደርዳሪው በዛዝቶ የከራረመው፤ ተመስጥሮ ነው እንጂ ይህ የዱብ ዕዳ ዘመን ያላዝረከረከው፤ ያልበታታከው ዝልቦሽ ህልመኛን የለም።

ከዚህም ከዚያም የሚደመጡ የሰላም አቅሞች መባተል ይታያሉ። ይህ ለግርግር ፖለቲከኞች አጥሚታቸው ነው፤ አቅም የለም ዝም ብሎ መኮፈስ ብቻ። ለእርዎች ርግባዊ መንፈስ ግን ደልድል ብለው በዘለቄታ ችግሮችን መልክ የሚይዙበትን ሁኔታ ጥናት የሚሠሩበት አንድ የምርምር ማዕከላቸው ነው። ልባሞች ስለሆኑ።

በሚሆነው ነገር አይደናገጡም፤ በሚሆነው ነገር አይርበተበቱም ብሎሆቹ፤ በጅጅጋ ከ700 ሺህ ህዝብ በላይ ተፈናቅሎ፤ ሙያሌ ላይ 50 ሺህ ዜጎች ተጨማሪ ተፈናቅለው፤ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አላዛሯ ኢትዮጵያ ሆና ነው የሰማይ ስጦታዎቻችን በፍጹም ስክነት ሥር - ነቀሉን የወያኔ ሃርነት የማድርግ፤ የመጫን አቅም በመጋፈጥ ጠ/ሚር ቦታውን በመቆጣጠር የወያኔ ሃርነት ማንፌስቶን ሙት መሬት ላይ አስቀምጠው፤ አዲሱን ዘመን ብሥራት ገዢ መሬት ላይ ሆነው ያዋዋሉት።

በዚህ ሂደት የወያኔ ሃርነት ትግራይ ማንፌስቶ የ100 ዓመት ህልም ብቻ ሳይሆን በግርግር ፖለቲካ የነበረው የሥልጣን ውርክብም መራራ ስንብት አደረጓል። ለሁሉም ዱብ ዕዳ ነበር። ለዚህ ነው እኔ የዛሬ ዓመት እነዚህ ሰዎች አታውቋቸውም፤ ለማወቅም አትፈልጉም እያልኩ ስጽፍ የነበረው። ለነገሩ ከአቅማቸው በላይም ነው ብቃቱ ሆነ ጥበቡን ለመተርጎም ሆነ ለማመሳጠር።

ለቀጣዩ ትውልድ ይህ እርምጃ፤ ይህ ውጤት፤ ይህ ስኬት ታላቅ የመሥራች ነው። መከረኛው ቀጣይ ትውልድ መከራውን ከበላዩ ገፈው የቤት ሥራውን እዬሠሩለት ያሉት የለማ እና የገዱ የመንፈስ ሃብታት ናቸው።

ክልፍልፍ አይደለም ሰብዕናቸው፤ ጉሮኞችም አይደሉም፤ ራሳቸውን ለማረም ዝግጁዎች ናቸው። ሩህሩህ ናቸው። ይቅርታ መጠዬቅም አቀበታቸው አይደለም፤ ፈጽሞ አይታበዩም፤ ፈጽሞም ማንህሎኝነት የለባቸውም፤ በራሱ ይህ ጨዋ ሰብዕናቸው ትውልድ ገንቢ ነው። ሊጠኑ፤ የምርምር ተግባር ሊደረግባቸው የሚገቡ አንቱዎች ናቸው። ተመስገን!

በህይወት ኑሬ እንዲህ የመሰሉ ባህካል ጓድ ገ/መድህን በርጋ እና ኮ/ ጎሹ ወልዴን እንዲሁም ዶር ካሳ ከበደን የመሰሉ የእርጋታ፤ የስክነት፤ የክህሎት ተምሳሌትን ለማዬት እግዚአብሄር ስላበቀኝ አዘውትሬ አመሰግነዋለሁኝ።

ዕድሜ ሰጥቷው ከሳቡት ትውልዱን ከብክነት የሚያድን ሥርዓት በቋሚነት ፈጥረው ተልዕኳቸውን ያስፈጽምልኝ ዘንድ ለአማኑኤል በዬዕለቱ ሻማ አበራላቸዋለሁኝ። ከመጋቢት 24 ቀን 2010 ጀምሮ አንድም ቀን አስተጓጉዬ አላውቅም። እኔ ተስፋዬን ከተስፋዬ ላይ አግኝቻለሁኝ።

·       ድርጅት የቁንጥንጦች ቤተኛ አይደለም።

የመንፈስ መደራጀት ነው ትውልድን መምራት የሚችለው። ድርጅት ሙርጥ ይፈልጋል። ድርጅት ስልቹዎች ክፍሎቹ አይደሉም። ድርጅት ባለትልቅ ጆሮ አዳምጫን ይሻል። ድርጅት አቋራጭ መንገድን ሳይሆን አድካሚውን፤ አልፊውን ጥራት አስገኚውን ዘለግ ያለውን ስኩን መንገድ ተከታይ ነው።

ድርጅት ነገሮችን በስፋት ማዬትን ይጠይቃል። ድርጅት የበቀል ማመረቻ መሳሪያ አይደለም - ፈጽሞ። ድርጅት በመቻል ውስጥ መቻልን ማነጸ ነው። ድርጅት ብቁ የህሊና ስንቅና ትጥቅ ይጠይቃል - ሙሉ መሰናዶንም። 

ድርጅት የመዋለ ዕድሜ የክህሎት ውጤት ነው። ድርጅት ዘለቄታን እንጂ ዕለታዊ ክልፍልፍ ግርግር ትልሙ አይደለም። በድርጅት ጽንሰ ሃሳብ እና በአፈጻጻም ሂደቱ እኔ የማዬው፤ የምመለከተው ነገር ሁሉ እጅግ የሚያረካ እጅግም ተስፋ የሚሰጥ ነው። 

አብሶ የጠ/ሚር አብይ ካቢኔ ከዝክንትሉ የፓርቲ አቅመ ቢስ የኢጎ ትብትብ ወጥቶ የኢትዮጵያን መንግሥት በሙሉ የብቃት አቅም እና አቋም ለመገንበት እዬሄደበት ያለው ብልህነት እርስት ሊሆን የሚገባው ነው።

ለመጀመሪያ ጊዜም ነው በ50 ዓመት የግራ ፖለቲካ ዶግማ መንግሥት እና ፓርቲ በዬተልዕኳቸው መባተልን „ሀ‘ ብለው ጀምረው እኔ የማያቸው። ዛሬ ኢትዮጵያ ላይ የአንድ ፓርቲ አራጊ ፈጣሪ ዘመን እያከተመለት መጥቷል ማለት ያስችለኛል። ምክንያቱም እርምጃዎቹ መንግሥታዊ ተልዕኮ ባለው አቅም ልክ የመራመድ ጥበብ እያዬሁ ስለሆነ።

·       ረድኤት እና ስንዱነት ውድነት። 

ዓላማውን አውቆ የተነሳው የጣና የአባይ ኬኛ ንቅናቄ ማግስትን በመገንባት እረገድ አዲስ የፖለቲካ ባህል ለኢትዮጵያ በማበርከትም እረገድ ሂደቱ አንድ የምርምር ተቋም ያስከፍታል።

ወጀቦችን ገፋ አድርጎ ውስጡን ልይ ለሚል ባለቅን ህሊና ይህ ስጦታ የፈጣሪ ስለመሆኑም ያስረዳል። ኢትዮጵያ ዛሬ ያለችበት የፖለቲካ አስተሳሰብ ሁኔታ ሥልጡንነትን አውሮፓዎቹ ያላቸውን ያህል ነው።

በሳል የሆኑ መሪዎች ነው አሁን ኢትዮጵያ ያላት። ይህ ሥልጡን ዐዕምሮ ለአፍሪካም ፖለቲካ አብነቱ ዛሬ ላይታይ ይችላል፤ ነገ ግን በጉልህ ኢትዮጵያ ለአፍሪካ እና ለጥቁር ሉላዊ ዜጎች ለነፃነት ተጋድሎ አርማ እንደ ሆነችው፤ አዲስ የፖለቲካ ባህል በማስፍን እረገድ ከደቡብ አፍሪካም፤ ከጋናም የዴሞክራሲ መኖር ተመክሮ የተሻለ ልብ የሚሸለምለት ዘመን ይመጣል ብዬ አስባለሁኝ። ነውም።

አደብ። በዚህ የለውጥ ሂደት ያዬሁት ትልቁ ቁምነገር ነው። አደብ የልብን መሻት በትልም እንዴት እንደሚከውን ብቻ ሳይሆን አደብ ያለው ትወልድ ለመፍጠርም መንገድ መጀመሩ ነው እያየሁ ያለሁት።

በሙሉ ዕድሜ ላይ ያለው ፖለቲከኛ አደብ የለውም። አንዳንዱ እንደ አልተቀጠተቀጠ ወይፈን ሲገማሸር ይታያል፤ ሌላው ሲባትት፤ ሌላው የአይት ቅድመ አያቶቻችን የተመክሮን ማሳ ሳያውቅ ዘው ያለው የፖለቲከኝነት ሰብዕና በመታበይ ተራራ አክሎ ንፍትፍት ብሎ ይከሰታል፤ ሌላው የእነ ተሎ ተሎ ቤትም እንዲሆን ትቅማጥ እንደያዘው ሲራወጥ ይታዬል፤ ይህ ሁሉ ግግርግርን ከሙት መሬት ላይ ሆነው ሳይሆን ገዢ መሬቱን በአካልም በመንፈስም ተቆጣጥሮ ያለው ዘመነ - ማስተዋል ደግሞ ለጎልማሳውም፤ ለአዛውንታትም፤ ለወጣቶችም፤ ለታዳጊ ወጣቶችም ሚዛናቸውን ይጠብቁ ዘንድ እርምጃዎቹን በቅደም ተከተል ላክ እያደረገ ተቋም ፈጥሮላቸዋል።

ዘመኑ ሁሉም ት/ቤት የገባበት ሲሆን መሪ ማለትም የተነበበበት፤ የተተረጎመበት የተመሳጠረበት አዲስ ብሩህ ዘመን ላይ እንገኛለን። ተመስገን!

ዓራት አይናማው መንገዳችን የአብይ ሌጋሲ ብቻ ነው!

ውዶቹ ቅኖቹ ኑሩልኝ።

መሸቢያ ጊዜ። 

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።