ውስጥን ለማሳዬት ፍርሃቱ እስከ መቼ?

ውስጥን ለማሳዬት
ፍርሃቱ እስከ መቼ?
"እንደ ጠቢብ የሆነ ሰው ማን ነው? 
ነገርንስ መተርጎም የሚያውቅ ማን ነው?"

መጽሐፈ መክብብ ምዕራፍ ፰፩
ከሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
 23.12.2018
 ከጭምቷ ሲዊዘርላንድ።
                         ዛሬ -አላዛሯ ኢትዮጵያ አድማጭ ሙሴ አላት!
  • መነሻ!


ዋልታ ቲቪ 13/04/2011 . የማታ 130 ዜና በቀጥታ
| Walta TV News Live 7:30 PM 12/22/2018

ጤና ይስጥልኝ የኔዎቹ እንዴት ናችሁ። ደህና ናችሁ ወይ? አሁን አንድ ዜና አዳመጥኩኝ ከዋልታ ቴሌቪዥን። የሚገርመው አገር ውስጥ የነበሩ ተፎካካሪ / ተቀናቃኝ የፖለቲካ ድርጅቶች ከሁለት ዓመት በፊት የኦሮሞ እና የአማራ ህዝባዊ ተጋድሎ ሲነሳ ያን ለማርገብ እና ትጥቅ ለማስፈታት እነ ሳጅን በረከት ያሰናዱት አንድ የበረዶ ግግር ጋር ታዳሚ ነበሩ። 

ያ ቁም ነገር ሆኖ አብረው የቡና ማህበር መስርተው እንደ ልዝ እንጨት ወይን አይነዱ ወይ አያናዱ ህዝባዊ ተጋድሎውን አቅጣጫ ለውጦ በተኛ ፖለቲካ አስተሳሰብ ልፍስፍስ ብሎ እንዲቀር ሰፊ ድርሻ አበርከተዋል። ተዉ እያልናቸው። ያን ጊዜም እኔ ወጥቼ ሞግቻለሁኝ።
መልካም ጅምር ነው ሊበረታታ ይገባዋል ካሉት ወገኖቼ ጋር።

ያ የአማራ የህልውና የማንነት ተጋድሎ እና የኦሮሞ ንቅናቄ መሪ የፖለቲካ ድርጅት አለመኖሩን የተረዳው በሁለቱ ክልሎች የተነሳው አብዮታዊ ሞገድ በአንቦ፤ በጎንደር እና በጎጃም የነበረው ማህበራዊ ንቃተ ህሊና ተጋድሎ በፖለቲካ ድርጅቶች ማንፌሰቶ ውስጥ ያለነበሩ፤ በህዝቡ ማህበራዊ ንቃተ ህሊና የመጡ ስለነበሩ እኔ ነኝ ያለ የፖለቲካ ድርጅት አገር ውስጥ ይሁን ውጪ አገር የነበረ እንዳሻው ጠምዝዞ የራሱ ሰረጋላ ለማድረግ አልተቻለውም ነበር። ምክንያቱም የማይመጣጠኑ ስለነበሩ። ተጋድሎውን የመራው ወቅትን ያደማጠው ማህበራዊ ንቃተ ህሊና ስለነበር።

ተጋድሎው እዬጠነከረ ሲመጣ ያን ተጋድሎ ያደመጡ አሁን እንደሚነግሩ ዶር ለማ መገርሳ ለ7 /8 ዓመት ቆስለን ነበር የኖርነው እያሉ ነው እነሱ ይህን የህዝብ መሰረት ያለው የተጋድሎ አድማስ ሲያገኙ ሁለቱም ክልሎች አማራ እና ኦሮሞ አቅሙን ወደ ጥቅም ለማዋል በማስተዋል የተቀመረ፤ በልዩ ክህሎት የተደመጠ፤ በስፋትና በጥልቀት በተጠና ሁኔታ ታገድሎውን ተቀላቀሉ፤ መሩት ለግብም አደረሱት። እነሱ የበቃ የጸደቀ፤ የሰበለ የፍልስፋና የህሊና ጥሪት ስለ አላቸውም ነው ለግብ ያበቁት። የዚህ ዘመን የድል ሚስጢር   ይህ ነው፡ ይህን ዕውቅና ለመስጠት ራሱ ዳገት ነው እውነትን ለማይደፍሩት።

የአማራ ታገድሎ እና የኦሮሞ ንቅናቄ የማህበራዊ ንቃተ ህሊና የሚመጥነው አቅም በአንድም ተፎካካሪ/ ተቀናቃኝ/ ተቃዋሚ በሚባል ድርጅት አለመኖሩ ነው እዛው ኢህአዴግ ውስጥ ያሉ ብልሆች በበሳል የፖለቲካ አመራር ጥበባቸው ተጋድሎዎችን ለመምራት አስቻላቸው እና ህዝባዊ ተጋድሎዎች + ብቁ የፖለቲካ ሊሂቅነት ተዋህደው ለውጡን እዚህ ያደረሱት።

እነዛ የበረዶ ግግርን አምልከው በኬክ ቆረሳ ሃኒሙን ላይ የነበሩ አገር ውስጥ የነበሩ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች የመንፈስ እስረኞች ራሳቸው ነፃ የወጡት በዚህው በታገድሎ ነው። ዛሬ ደግሞ ይዘማነናሉ። 

ከወያኔ ሃርነት ትግራይ ብጣቂ የደቂቃ የመናገር መብት ተነፍጓቸው እንደዛ፤ በፍጹም ሁኔታ "ኢትዮጵያን አታውቋትም" ሁሉ ሲባሉ እዬተብጠለጠሉ፤ ከፍ እና ዘቅ እዬተደረጉ፤ በአገራቸው መሬት በሲሶ ዜግነት ሲንገላቱ የነበሩት የአገር ውስጥ የፖለቲካ ድርጅቶች ዛሬ ይህን በመሰለ ግርማ ሞገስ ባለው፤ በበቃ አመራር፤ በተደራጀ ብልህነት፤ በነቃ አምክንዮ ምርጫ እና ሂደቱን ለለምራት በሚያስችል ጉዳይ ላይ ተከብረው ጦርነት ያወጀው የአቶ ዳውድ ኢብሳን ኦነግን ጨምሮ ይህን መሰለ የትህትና፤ የአክብሮት፤ የመቻቻል አዲስ ጥበብ በሚታይበት በአሁኑ ወቅት የጫጉላ ጊዜ አሰኝቷቸው የሚያነሱት ሃሳብ ሁሉ በእጅጉ ያቅለሸልሻል። 2 ሚሊዮን ወገን የተፈናቀለ አለን፤ አሁንም ሞቱም መፈናቀሉም ቀጥሏል።  ገና የሚፈናዳ ፈንጅም አለ እዬተባለ ነው ... 

የሚገርመው ገለልተኛ ነው ገለልተኛ አይደለም የምርጫ ቦርድ ሲሉም ይደመጣሉ። ሰብሰባቢዋ እኮ የነፃነት አርበኛዋ ክብርት ዳኛ ብርቱካን ሚዲቀሳ ናት፤ እንደነሱ የተፎካካሪ ብሄራዊ ፓርቲ ሊቀመንበር የነበረች ናት። ይህ ወርቃማ ዕድል ነበር እነሱ ቢያውቁበት። ይህን የተፎካካሪ/ የተቀናቃኝ/ የተቃዋሚ ፓርቲዎች በስንት ልፋት እና ድካም ሊያገኙት የሚገባ ነገር ግን የአብይ ካቢኔ በስንት ጫና ራሱን ገብሮ በሰውርም ህዝብ እዬተፈናቀለ የተገኘ ዕድል እንጂ በብላሽ የመጣም አይደለም። አሁንም ግብር እዬተከፈለበት ነው። በ ዬእለቱ ነፍስ እዬተቀጠፈበት።

ለነገሩ ባለመሃያዎችም እኮ አሉ። እንደገናም በሬሳ ሃሳብ ትውልድን እያባከኑ ገበርዲ እና ከረባት እያሳዩ ነግሦ መኖርም የሚያከትምበት ጊዜ ነው አሁን። አጀንዳው አልቋል። ስለዚህ አጀንዳ እንዳያልቅ በሌላ የሃሳብ እግረኛ ሠራዊት በመዋጋት ቀናውን መንገድ ለማጠወልግ ይታክታሉ። መረገም!

ከቶ ከዚህ በላይ የሰማይ መላዕክ ሊመጣላቸው ነውን? እንዴት እንደሚያቅለሸልሽ ማን በነገራቸው። በሌላ በኩል በአንድ አገር መንግሥት እያለ ነው ተፎካካሪ ፓርቲዎች የሚወዳደሩት። የትም አገር በሰለጠነውም ባልሰለጠነውም። ዛሬ ኢትዮጵያ ሃላፊነት የሚሰማው፤ ተጠያቂነትን በሃላፊነት የተቀበለ መንግሥት አላት። ምንም የሚመካኝበት ነገር የለም። ለሁሉም እኩል የሆነ መንግሥት ነው ያለው። ለዛውም በግራ በቀኝ ጦርነት ታውጆበት።

እንደ ማንኛውም አገር መንግሥት አቻነት ያለው የ ኢትዮጵያ መንግሥት የትኛውም ድርጅት ተፎካክሮ ስልጣኑን መረከብ ወይንም ማስረከብ እንዲችል ሃላፊነት አለበት። አሁን እዬሆነ ያለውም ይኸው ነው። የሚገርሙት ሃሳብ አቅራቢዎች ኢትዮጵያ መንግሥት አልባ ሆና ነው ወይ እንወዳደር የሚሉን? ለመሆኑ ምን ይሆን የሚፈልጉት? የሳጅን በረከት ስምዖን የጫማ ክር ተጎንብሶ ማሰር ይሆን ያማራቸው እና የናፈቃቸው ወይንስ የአቦይ ስብሃት ነጋን ጃኬት ተሸክሞ ማጀብ? ወይንስ ላብ እያሰመጣቸው በጠበንጃ አፈሙዝ ታግተው መንተባተብ?

ይህ ሁሉ ሥር ነቀል እርምጃ እተወሰደ ያለው በኢህአዴግ በፖለቲካ ድርጅቱ ፈቃድ አይደለም፤ ኢህአዴግ እንደ ድሮ መሪ ቢሆን ኖረ አንዲት ስንዝር መራመድ አይቻልም ነበር። ክብርት ዳኛ ብርቱካን ሚዴቅሳም አትሾምም ነበር። በ50 ዓመት የኢትዮጵያ ታሪክ የተኖረው ተኖሯል።

እጅግ የከፋውበግራ ፖለቲካ ፍስፍና አራማጆች ዕድሉን አግኝተውት ቢሆን ኖሮ ወያኔ ሃርነት ትግራይ ካደረገው በዙር ተመልስ ይደገም ነበር፤ የግራ ፖለቲካ ድርጅቶች ሁሉንም ጠቅልሎ በመሪነት ቁብ ብሎ መንግሥት እና ህዝብ ሚና አልቦሽ የሚሆኑበት፤ የባይታወርነት፤ መከራ የተከዘነ ዘመን ሌላ ቀጣይ 50 ዓመት ይኖርም ነበር።

ይህ ምን ማለት ነው? ያለፈው 50 የመከራ ዓመት ብቻ ሳይበቃን ቀጣይ 50 በአንድ አውራ ፓርቲ የመመራት ህልም ሂደት ነው አሁን የተቋረጠው። ተጨናግፎ መቃብር የተላከው። ሰዉ ያልገባው ይህን ነው። 

መንግሥት እና ፓርቲ አሁን ባለው የአብይ ካቢኔ ተለያይተዋል። እንዲያውም እዬመራ ያለው መንግሥት ነው። የኢትዮጵያ መንግሥት በሙሉ አቅሙ መንቀሳቀስ በመቻሉ ነው ይህ ሁሉ ድል የተገኘው። ይህ ደግሞ የኖረው ህልማችን ነው። ሚሊዮኖችም እራሳቸውን እዬገበሩ አሁንም ያሉበት።

ይህ የለውጥ ወርቃማ ዘመን መሆኑ ረቂቅ ነው። ሊታይ የማችሉ የገነገኑ የመከራ ቁልል፤ አይደፈሬ አመክንዮች እዬደረመሰ ነው ያለው። ይህ የሚራዳው ደግሞ ከእኔ ለቀደመው ትውልድ፤ ወይንም ለእኔ ትውልድ ሳይሆን ለቀጣዩ ትውልድ ታላቅ የምሥራች ነው። ይህን ነገር በሠለጠነ መንፈስ መደገፍ ያለባቸው ወጣቶች ናቸው። ስለምን ዘመኑ የእነሱ ነውና።

ለዘመናቸው ደግሞ ማህንዲሶችም ዲዛይነሮችም እነሱው ናቸው። ለውጡም የመጣው 50 ሺህ የአማራ እና የኦሮሞ ወጣቶች በካቴና ተገብረው ነው። ተንኮላሽተው፤ አካላቸውን አ ጠ ፡፡ጥፍራቸውን አጥተው፤ መንፈሳቸውን ተቀምተው፤ ዘር መተካከት ተፈጥሯቸውን ተነቅሎ ነው እና ቀልዱ እንዲቆም ሊፋለሙት ይገባል ይህን ሬሳ ሃሳብ - በተለይ ወጣቶች እና ሴቶች /እናቶች። የሁሉም የዘለበ መከራ ተሸካሚ እንሱው ናቸውና።

በቂም በቁርሾ ፖለቲካን መምራትን ውርስ እና ቅርስ እንዳይሆን ነው እዬተሠራበት ያለው - አሁን። የአውራ ፓርቲ አለመኖር የሚያስፈልገውም በዚህ ምክንያት ነው። የአውራነት ፓርቲ መርሆዎች በኢትዮጵያ ፖለቲካ የሃቅ አውራዎችን እያጠፉ፤ የእውነት አርበኞች እዬተደመሰሱ ነው እነሱ ራሳቸውን የሚራቡት። ልክ እንደ እንፉኝት ማለት ነው። እፉኝት ሲረገዝ አባቱን ሲወለድ ደግሞ እናቱን ይገድላል። የተለመደው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ይህ ነበር። በማፈረስ ላይ ፍሰሃ እና ሰናይ ... በብክነት ላይ የምሥራች። ብክነቱ ደግሞ የትውልድ የማደረግ አቅም እና ክህሎት ነው።

አሁን ተስብሳቢዎቹ የዚህ ዘመን ሰዎች ስላልሆኑ፤ መጪው ጊዜ አስፈርቷቸዋል። አጀንዳ አልባ ስለሚሆኑ። ይህን ወርቃም ዕድል እንደለመደባቸው ተባትበው አባክነው ጫና ፈጥረው አቅመ ቢስ ለማድረግ ነው እዬጣሩ ያሉት። አዲሱን ካቢኔም ለማሳጣት እና ተጨማሪ የሥራ መደራረብ መፍጠር ... ሌላ ምን ሥራ ሲኖራቸው። 

ቀድሞ ነገር በሥም የማይታወቁ ብዙ ፓርቲዎች ነው አገር ውስጥ ያሉት። በውጭም ደረጃ አንዲት ቀን በረባ የሚዲያ ሽፋን አግኝቶ የማያውቀው የአቶ ዳውድ ኢብሳ ኦነግ ራሱ ከተረሳበት አሁን ነው የሚዲያ አውራሪስ ሆኖ እዬታዬ ያለው። ሌሎችም ቢሆኑ ሳምሶናይታቸው ብቻ ነው የተመዘገበው።

አሁን ይህ ሁሉ ክብር ከሰማይ ዱብ ሲልላቸው መሬት ላይ ሠርቶ ማሸነፍ ሲሳን በቅርጥምጣሚ ጉዳዮች ጊዜ ያቃጥላሉ። አቅጣጫ ለማስለወጥ ይታክታሉ። ብዙዎች እኮ ከራሳቸው ውጪ አባል አለን ቢሉ ጓደኛቸው ወይ ቤተሰባቸው ነው ያለው። እንደ ጸበል ማህበር ያህል እንኳን አቅም ያለው አባል ያለው የፖለቲካ ድርጅት ምን ያህል ቢባል አደባባይ ያውቀዋል።

በሥም ተመዝግቦ ወርሃዊ ክፍያ የሚከፍል አቅርቡ ቢባል ራሱ መሪ ነኝ የሚለውም ሳይከፍል የአባልነት ግዴታውን ሳይወጣ ነው ዘመንን የሚቆጥረው … ዕውነቱ ይህ ነው። ለዚህ ነው እኔ ኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲን መርህ ያሟላ ድርጅት የላትም የምለው። የፓርቲ አባልነት የገብያ ወይንም የኮንሰርት ውሎ አይደለም እና። እንኳንስ አባሉ አመራር አካሉ የከፈልክበትን ደረሰኝ አሳይ ቢባል የለውም።  ከአባላቱ ጋርም በመርህ ደረጃ ዝቅ ብሎ ተሰብሳቢ ሆኖ አያውቅም። 

የሚገረመው የተፎካካሪ/ የተቀናቃኝ/ የተቃዋሚ ፓርቲዎች አቅማቸውን ስለሚያውቁ ውይይቱ ሙግቱ በጓዳ እንዲሆን ሁሉ ይሻሉ። ሚዲያ የሚፈሩ ከሆነ ሳምሶናይታቸውን ታቅፈው ቤታቸው መቀመጥ ነው። በቃ። ሚዲያ የተሠራው ለዚህ የዴሞክራሲ ግንባታ ተግባር ነው። ከህዝብ ተደብቀው የህዝብን ጥቅም ለማስጠበቅ እንተጋለን ማለት ዶሮ ማታ ነው። አቅማቸውን ልናዬው፤ ልንፈትሸው ይገባል። እስከፈለገነው ድረስም ልንተቸው፤ ልናብጠለጥለው ይገባል። አባዝኞችን እንዲያውም እኛ የህዝብ አባል የሆነው ኢትዮጵያዊ ዜጎች አናውቃቸውም ቁጥር ብቻ።

በሌላ በኩል „ሚዲያዎች ገለልተኛ“ አይደሉም ለሚለው ይህ እውነት ነው። ሁሉም ሚዲያ የፓርቲዎች አገልጋይ ነው። ይህም ዕውነት ነው። ጋዜጠኛ የፖለቲካ ድርጅት አባል ከሆነ እንደምን ይቻለዋል ገለልተኛ መሆን? ወይንም ጋዜጠኛ በአንድ ወቅት በተፈጠረ አለመግባባት ያን የቂም ኩትኩት በብብቱ እንደ ታቀፈ እንደ አንድ የፖለቲካ አይዲኦሎጂ ወስዶ ሚዲያን የሚያስተናግድ ከሆነም ይህም ሌላው መከራ ነው፤  በምክንያት ከመሞገት የቂም ማወራራጃ ካደረገውም ልሳኑን ሆነ ብዕሩን ይህም ሥነ - ምግባሩን የጋዜጠኛውን ይጥሰዋል።

ሌላው ገለለተኛ ለመሆን በሚያስቡትም ላይ ያለው ጫና የተኖረበት ነው። ጫናው በግልም በጋራም በነፃነት አገር የነበረ ነው፤ እስከ ህልፈትም የሚያደርስ መከራ ነው ያለበት የኢትዮጵያ ሚዲያ ሠራተኛ … 

የማሰር አቅም ያለውም ቁጫኑን እንዴት እንደተወጣ ወጣቶችን እንዴት አርጅተው ከእስር ቤት እንደወጡ እነ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ እና ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋን ለናሙና መውሰድ ይቻላል፤ ጋዜጠኛ ሰርካለም ፋሲል እስር ቤት አርግዛ ከዛው ነበር የበኽር ልጇን የተበከረችው። 

ሁሉንም በኖርንበት ዘመን አይተነዋል፤ የማሰር አቅም የሌለውም እዚህ ውጭ አገር ማህበራዊ ተቀባይነትን በማናጋት፤ በደቦ ጦርነት አውጆ እስከቻለው ድረስ ተግቷል። 
ከፈጣሪ በታች ጥንቃቄ ነፍስ አትርፎ ካልሆነ በስተቀር ዘነፍ ያለች ሁኔታ ቢኖር ኖሮ ይህን ቀን ለማዬትም አይቻልም ነበር። ካቴናው ሁሉም ቦታ ነበር። ወደፊትም አይታወቅም የሚሆነው ... 

ገለልተኛ ሚዲያ ምን አልባት የዛሬ 20 ዓመት ዕድለኛ ከተሆነ አዲሱ ትውልድ እኛ ካለፍን በኋዋላ ሊኖረው ይችላል። በስተቀር ግን እንዲህ ባጭር ጊዜ ውስጥ ገለልተኛ ሆነ አማራጭ ሚዲያ ማግኘት አይቻልም። ደግሞም የለም። ስለዚህ ባለው ሚዲያ መረጃዎችን መስጠት ማግኘትን መፍቀድ ግን የተገባ ነው። ከሰማዬ ሰማዬት ቅዱስ ሚዲያ አይወርድም። 

የፖለቲካ ድርጅት መሪዎች እነሱ ዕውነትን እዬፈሩ ዕውነትን የደፈረ ሚዲያ መጠበቀም፤ መመኘትም፤ ማለምም ሌላው የራስግጥት ፈተና ነው። ውይይቱ በጓዳ ይሁንልን እያሉ ነው። እነዚህ ናቸው እንግዲህ የነፃነት ታጋዮች፤ እነዚህ ናቸው እንግዲህ ለሃሳብ ነፃነት የሚሟገቱት?

እነሱ እኮ እንዳይጋለጡ አቅማቸው አደባባይ እንዳውል ስለሰጉ ነው ዝግ ይሁንል እያሉ የሚማጸኑት። ራሳቸውን እራሱ ነፃ ገና አላወጡም። ራሱን ነፃ ያላወጣ የፖለቲካ ድረጅት መሪ እንዴት ብሎ ይሆን የዲሞክራሲ መርህ ጠበቃ፤ ዋቢ ሊሆን የሚቻለው? እንዴትስ ብሎ ይህን የእኩልነት መንፈስ አስከብርልሃለሁ ብሎ ምረጡኝ ብሎ ዓርማ እንደሚያዘጋጅ እራሱ የሚገርም የጉድ ቁልቁለት ነው።

መቼም የአብይ ካቢኔ ከእነማን ጋር ብቻ ሳይሆን በምን የሰፋ ሆድ ይህን ፈታኝ ዘመን ሊሻገር እንደሚችል ፈጣሪ ይሁነው። እራሱን መምራት የማይችል ጋር ተፎካካሪ ሆኖ መቅረብ ራሱ የራስ መርዘን ነውና። ቋንቋ ጠፋ!

ይህ ዘመን እኮ ሁሉንም ነው የገላገለው፤ የነፃነት ትግል በተራዘመ ቁጥር ቃና ማና የለሽ ሆኖ ጠንዝሎ ይቀራል። በመኖር ውስጥም ማርጀትም መሞትም ይኖራል። ተቀባይነት እራሱ ያረጃል - ያፈጃል። ዘመን አዲስ ከሚወለደው መንፈስ ጋር ለመዋህድ ጥረት አለማድረግ ደግሞ የኢትዮጵያ የግርግሩ ፖለቲካ ግትራዊ መንገድ ነበር። ሁለት ዓመት ቢጨመር የነፃነት ተጋድሎው በራሱ ጊዜ ሾልኮ ባክኖ ይቀር ነበር።

ይልቅ እድሜ ለለማ እና ለገዱ መንፈስ ማለቱ እና ይህን አክብሮ መነሳት ይገባል። ዛሬ ሁሉም ባለቀይ ምንጠፍ ነው። ዛሬ ሁሉም ባለ ክብር ነው። ታናሽ የለ ታላቅ የለ። እንዲያውም የኢትዮጵያ መንግሥት ችሎቱን ሰጥቶት ጥፋቱን እያመነ፤ ይቅርታ እዬጠዬቀ ከተገባው በላይ ለተፎካካሪዎች/ ለተቀናቃኞች/ ለተቃዋሚዎች ልቡ እያወቀ የተጋነነ ዕውቅና እዬሰጠ እያባበለ፤ እያቆላመጠ ለዛውም አክብሮ በትህትና ራሱን ገርቶ ከቂም፤ ከበቀል፤ ከቁርሾ ራሱን በፍጹም ሁኔታ አጽድቶ እጁን ዘርግቶ ሁሉንም ተቀብሏል።

እነሱ ራሳቸው ተቃዋሚ/ ተፎካካሪ/ ተቀናቃኝ የሚባሉት መቼ ላጠፉት ነገር ይቅርታ ጠይቀው ያውቁና። ጥፋታቸው ራሱ ተዘርዝሮ ያልቃልን? በዬዘመኑ ስለሚገበረው ትውልድ ማን ይሆን ተጠያቂው? ቀርሾውስ? 

እነዚህ ብልህ መሪዎች ያላቸው የፖለቲካ ሳይንስ ብቃት ንፋስን የሙጥኝ ያለ አይደለም። በራሳቸው የመተማመን አቅማቸው ተንሳፋፊ አይደለም። አላቸው። ባላቸው ልክ ሳይንጠራሩ፤ ሳይኮፈሱ፤ ግን ዕውቀታቸውን በማሸጋገር፤ በትህትናዊ ጉዞ፤ በበሳል ብልህነት ነው ዘመኑን እዬመሩ ያሉት። ለእኔ ወርቃማ ዘመን ነው። ብዙ ፓርቲዎች ፍላጎታቸውን ፈጸሚ ካገኙ እነሱም እንዲህ በውሽልሽል አቅም ከሚጋለጡ ራሳቸውን በራሳቸው ቢያፈርሱ ይሻላቸዋል። የአብይን መንፈስ ሞግቶ የለማን መንፈስ ሞግቶ ዳገት ነው? 

ኢትዮጵያ ከዚህ በኋዋላ 100 ዓመት ብትጠብቅ ይህን መሰል ከቂም በፍጹም ሁኔታ የጸዳ፤ በሁለመናው የበቃ እና የተደራጀ፤ ራሱን ነፃ ያወጣ የፖለቲካ አቅም ያለው የፖለቲካ ሊሂቀ - ሊሂቃን አመራር አታገኝም። ዕድለኞች ነን።

እነዚህ ዕንቁዎች የት ነበሩ እላለሁ እኔ እራሴ የማዬው ነገር እየገረመኝ። በአንድ ወቅት መድህን ፓርቲ ሁለት ወጣት ረ/ፕሮፌሰሮች መሪ ነበሩት፤ ያን ጊዜ ከእነሱ ጋር የነበረኝ ቆይታ በፍጹም ሁኔታ ተስፋው ያሸተ ነበር። ሁለመናቸው ቁምነገር አዘል ምራቁን የዋጠ ነበር። ሁለቱም በተመሳሳይ ዕድሜ የነበሩ ወጣት መንትዮሽ የሚስሉ ነበሩ የዩንቨርስቲም መምህራን ነበሩ በአገረ አሜሪካ። እነዛ ብርቅዬ ሊቀ ሊቃናት አድራሻቸውን ሁሉ ሰጥተውኝ ነበር እኔ በዚህ መሰል ዙሪያ ትጉህ ባለመሆኔ ግንኙነታችን አልቀጠለም። 

አሁን ለእኔ ኢትዮጵያ የለው የአመራር ስክነት እና ብጡልነት አቅም ያን ጊዜ የተሰማኝ ያተ የተስፋ መንፈስ ነው አሁንም እዬተሰማኝ ያለው … ሁልጊዜ ነው እኔ አግዚአብሄርን እማመሰግነው። ሁልገዜም ነው ሻማ እማበራው …

እንዲህ በአጭር ጊዜ ውስጥ አብዛኛውን የሚያረካ የፖለቲካ ሊሂቅ ለዛውም ወጣት እናገኛልን የሚል ህልም አልነበረኝም። የአማራር ጥበብ በእግሩ ቆሞ እዬሄደ ነው የማዬው እኔ … ለዛውም ከበቃ ከተሟላ ትእግስት ጋር … ከጨዋነት ጋር፤ ከርህርህና ገር፤ ከሙሉ ሰብዕና ጋር። ኢትዮጵያ እናት መሪ ነው ያገኘቸው። ተመስገን! ለእኔ ዘመኑ የምርቃት ዘመን ነው። 

በአግባቡ ለማያዝ ግን የመንፈስ ጨዋ አቅምን ይጠይቃል። አቅሙ አንጎል ያለው ሁሉ ሳይሆን አንገሎም ህሊና ወይንም አዕምሮ ላለው ብቻ ነው ይህን ዘመን ማደመጥም መመጠንም የሚችለው። 

የግድፈቶች፤ የትችቶች፤ መሰረታዊ ጉዳይ በአመዛኙ አሁን ኢትዮዮጵያ የደረሰችበትን የፖለቲካ ሥልጣኔ ካለማወቅ የተነሳ ነው። መመጣጠን አልተቻለም። እርምጃ ላይ ለሚገኝ አቅም እና ኩሬ ላይ የታቆረ እንዴት ይጣጣም?

በጣም የሚያሳዝነው 2 ሚሊዮን ህዝብ ኑሮ መፈናቀል ጉዳያቸውም፤ አጀንዳቸውም አይደለም? ያላበራው የሰላም እጦት ጉዳያቸው አይደለም? ብሄራዊ ሃዘን ላይ ነን አሁን፤፡አገር እንመራለን ሲባል ይኽም እኔን ይመለከተኛል፤ ቢያንስ መንግሥት ያለበተን ጫና ለመቀነስ ከእኔ ምን ይጠበቃል የለም? ሁሉንም ነገረ ተጠቅልሎ መንግሥት ይወጣው ነው? የድርሻን ሳይወጡ መሪነት? እም!

መንግሥት ይህን ያን ያድርግልን እንጂ እኛ ይህን እናደርጋለን፤ ይህን ክፍተት እኛው እንሸፈናለን የለም። ራሳቸው የቤት ሥራ ሆነው ተሸከሙን ባዮች ሆነው እኔ የማዬው። ሌሎቹ ደግሞ ጫን ተደል መከራ በዛ መከረኛ ህዝብ ጭነው የወ/ሮ ታደሉ ዕንባ ማህበርተኞች እንዲበራከቱ እያደረጉ ይህንንም እንደ ጀብዱ የሚያዩም አሉ።
እሚሰጡት አስተያዬት እራሱ ቁስል ነው የሚያደርገው። አንዳንዱ አይገባም። 
አለመግባቱ ይሻላል።

ብቻ ይህን የመሰለ ማዕረግ ብቻ ሳይሆን ለሁሉ ራሱ እያንዳንዱ ቀን ኦን ላይ ት/ቤት ተከፍቶለታል ቀደዳውን ሁሉ እዬወታታፈ ነው። በጣም ዲታዎች ናቸው የዚህ ወቅቱን እዬመሩ ያሉት ልበ ብርሃን መሪዎች።

ተባረኩ! ኑሩልንም!


አሁን የብአዴን ሉዑክ አሜሪካ ነበሩ። ብልሆች ናቸው። እንደ ገና አያጨናንቁም ቅልል ያሉ ጀርመኖች አይነፋህ የሚሉት ዓይነት ሰብዕና ያላቸው ሆነው ያዬኋቸው። በርቀት እየተከታተልኳቸው በአካል የማውቃቸው ያህል ነው የተሰማኝ። ይህ ጸጋ መቼም ገብያ ተሂዶ አይሸመትም። እንደ ቤተሰብ ልታዮዋቸው የምትችሏቸው ናቸው … ተረባቸው ራሱ እንዴት መንፈስን ይገዛል …

እኔ አስግቶኝ የነበረው ህይወታቸው ነበር። ፈሪ ስለሆንኩኝ። እዛም ያለው ጉዳይ ሌላ ዕዳ እንዳይመጣ ስጋት ስለነበረኝ በዚህ ወቅት አሜሪካ መሄዳቸውን እለደገፍኩትም ነበር። ወቅቱ ሽግግር ስለሆነ አላስፈላጊ ከሆነ መስዋዕትነት ለመውጣት መታቀብ፤ ቁጥብ መሆን በ እጅጉ አስፈላጊ ስለነበረ ብዙም አልተመቸኝም ነበር።

የሆነ ሆኖ ባካሄዱት ስብሰባ ብልህነታቸው እና ዲፕሎማት መሆናቸውን ቀለል ብሎኝ አስተውያለሁኝ። ስሜታዊ ፈጽሞ አይደሉም እንደ ሽሮ ከላይ ከላይ አይተነፋፍሱም። ያሉ ናቸው። የኢትዮጵያን ፖለቲካ አደጋ ውስጥ የከተተው ስሜታዊነት ነው። የቂም መንገድ ተከታዮች አይደሉም። አሁን ተመስገን ነው። ይህን እያዩ አደብ ለነሳቸው ነፍሶች አዬር ላይ የተንሳፈፉ ነፍሶች ሁሉ መሬት የሚያስረግጥ ስክንት ዘመኑ አስገድደዶ ለዛ ረብነት ጨዋ ሰብዕና ያበቃቸዋል ብዬ አማናለሁኝ - እኔው።  

ዓራት ዓይናማው መንገዳችን የ አብይ ሌጋሲ ብቻ ነው!
አብይ ኬኛ!

የኔዎቹ ቅኖቹ ኑሩልኝ።
መሸቢያ ጊዜ። 



                                           መሸቢያ ጊዜ።   

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።