ነፍስ ይማር ሁላችንም ጠበቂዎች ነን ... መሰሉን ...

ዴሞክራሲን ሊኖሩት
የፈቀዱት ብቻ
ብፁዕን ናቸው።
„እንደ ጠቢብ የሆነ ሰው ማን ነው?
ነገርንስ መተርጎም የሚያውቅ ማን ነው?“
መጽሐፈ መክብብ ፰ ቁጥር፩

ከሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute© Selassie
ከጭምቷ ሲዊዘርላንድ።


ለሌላው የተፈቀደ የተስፋ ዘመን ለሌላው ደግሞ የተቀፈደደ የጨለማ ዘመን ነው። አንዱ ያገኘው ያገኘውን ንጹህ አየር ሌላው ሲያገኝ ይቀናበታል። አዬሩን ሰጪ እኮ የነፃነት አዳዩ እኮ እሱ አይደለም። አለመታደል። ዛሬ ሁሉም የኢትዮጵያ ልጆች የናፈቃቻቸውን አገራቸው እና ህዝባቸውን ማግኘት እኩል መብት ሆኖ ሳለ ግን ገደብ መጣል ወንጀል ነው። ጥፋት ከኖረም ካለም ቁጭ ብሎ መነጋገር ይቻል ነበር። እንዲህ ከሚሆን?  

·       ዶቼ እንዴት ናችሁ ይህን ስጽፍ ለኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ተስፋ እያለቀስኩኝ ነው …

የአላዛሯ ኢትዮጵያ ዴሞክራሲን ህልም ፈተና የጣለ አዲስ ክስተት ትንሽ ቀደም ባሉ ሰዓታት አነብኵኝ። ማመን ለመቻል ራሴን ከሁኔታው ጋራ ለማዋህድ ጊዜ አስፈለገኝ እና አንድ ሦስት ሰዓት ዘገዬሁኝ። ኢትዮ ሪጅስተር አልከፍትልኝ ካለ ሁለት ሳምንት አልፎታል። ለማረጋገጥ ፈልጌ አልቻልኩኝም። ዘሃበሻን ሰንበት እንዴት ይዟሃል ልል ስገባ፤ ሻማ የበራበት ፎቶ አዬሁኝ። ጹሑፍ እንዲሁ፤ ሥሙን እና ፎቶው አልመጣልሽ አለኝ። እኔ በአካልም በፎቶም አላውቀውም። እማውቀው ብራና ላይ  የብዕሩን ጠብታ ብቻ ነው።

እርግጥ ነው እሱም እኔን ያውቃል በዜና፤ እኔም አሱን በዜና አውቀዋለሁኝ። እንድ - ደወልልት ስልክ ተሰጥቶኝ ትደውልልኝ ብሎ አልደወልኩለትም በ2013/2014  ይመስለኛል። እኔ በመደወል፤ በመተዋወቅ ዝንቅ ዝንቅ በማለት ባህል እጅግ ደካማ ነኝ ከምል አልተፈጠርኩበትም። ሰው ደውሎም ራሱ አላነሳም። ኢሜል ብቻ ነው የሚመቸኝ።

ብቻ መደወል ለማላውቀው ሰው እንኳን ከባድ ነው ለእኔ ሰብዕና። እንኳንስ በአካል የማላውቀውን አስቤ ልደወል ቀርቶ። ለማውቀውም ቢሆን በደንበር ነው የእኔ ነገር ደግሞም ጠቅሞኛልም- ቁጥብነቴ። አቅጄ እራሱ አልደውልም ለማውቃቸውም። ለጉዳይ ሰው አገኛለሁኝ ጉዳዩ ሲያልቅም ግንኙነቱ ያበቃል።

ስብሰባም የምሄደው ዜና ለመስራት ነው፤ የመጣ ቢመጣ ሥርጉተ ሄዳ ቆማ ከእንግዳ ጋራ ፎቶ ተነስታ አብራ ተወያይታ ቀጣይ ግንኙነት ፈጥራ መገናኘት የለም፤ አይታሰብምም። ተግባሬን ከጨርስኩ ደቂቃ አልጠፋም ወደ ቤቴ ነው እምመለሰው። ይህም ሆኖ ነው ጠባቂ የሚመደብልኝ … በግራ እና በቀኝ … እንዳልገናኝ ነፍሳቸው ጥፍት እሰኪል ጥበቃ የመደረግብኝ።  

እናም ሟቹ ጋዜጠኛ ደምስ በለጠ እንድደውልት ስልክ ቁጥሩም እንዲሰጠኝ ቢፈቅድም እኔ ግን አልደወልኩለትም። እኔ እና ጋዜጠኛ ደምስ በለጥ ያገናኘን የዘሃበሻ የብራና ሙግት ነበር። እንደማንኛውም አይመቸኝም እንደምለው ሃሳብ ሞግቸዋለሁኝ።

በኋዋላ የአማራ ድምጽ ራዲዮ አዘጋጅ ሲሆን ደግሞ ከአንድ ፓልቶክ ጋር አማራነትን በሚመለከት በሰጠው ትንተና በድጋሚ ሞግቸዋለሁኝ። ቋንቋ በመናገር እና ባለመናገር የቤተሰብ የዘር ሐርግ አይተረጎምም ብዬ። አማርኛ ቋንቋ የማይነገሩ ዘራቸው አማራ የሆኑ አሉ፤ አማርኛ ቋንቋ ተናጋሪዎችም የቤተሰብ ሐረጋቸው አማራ ያልሆኑ ብዬ።

የአማራ ታገድሎ የተነሳበት ሰሞን ደግሞ የመጀሪያ ዝግጅቱን ከረንት አፊርስ ላይ ተለጥፎ አግኝቼ አዳምጨዋለሁኝ። ከዛ በኋዋለ ግን አዳምጬው አላውቅም። አውስትራልያ ያሉ ቤተሰቦቼ ግን እንሚከታተሉት በመደበኛ አውቃለሁኝ። ጹሑፍ ቢጽፍ ግን አነብ ነበር። የበለጠ እኔ ዝንባሌ ያለኝ ጹሑፍ ማንበብ ስለሆነ።

በሌላ ነገሮች ከሌላ ከቆዩ ነገሮች ጋር ሚዲያ ሲነካካም ብዙም አይመቸኝም። የአማራ ተጋድሎ የጠራ መስመር እና ዓላማ እና ግብ ይዞም ስለተነሳ በዛው ላይ ነው ሚዲያው ሊሰራ የሚገባው። 

እሱ ደግሞ ፕሮፌሽናል ጋዜጠኛ ነው። ስለሆነም እንደ ጋዜጠኛ ሊሂቅነቱን አዲስ ሚዲያ በተመሰረተበት መንገድ ብቻ እንጂ በቆዩ ቁርሾዎች ላይ መጓዝ የለበትም ባይ ነኝ። ማንኛውም የፍትኃብሄር ህግና ሥርዓቱ፤ የወንጀለኛ መቅጫ ህግ እና ሥርዓቱ ፍርድ ወደኋላ ተመልሶ አያይም እና። 

·       ዞ እና ህልፈት።

አነ ጋዜጠኛ ሳዲቅም አገር እንደገቡ አዳምጫለሁኝ። ለእሱ ለብቻ ስለምን ሞት ታጨለት? ዘሃበሻ ላይ ወደ ኢትዮጵያ እንደሚሄድ ባለፉት ሳምንታት ዜናውን አዳምጫለሁኝ። ከእኔ ጋር የቀረበ ግንኙነት ቢኖረን ግን እንዳይሄድ እነግረው ነበር። ፈቀደም አልፈቀደም። አደመጠኝም አላዳመጠኝም፤ አደረገውም አላደረገውም አትሂድ ማለቴ ግን አይቀሬ ነበር።  

እኔ ከቆሞስ ኢንጂነር ስመኘው በቀለ ሰማዕትነት ወዲህ ዕምነት የለኝም ኢትዮጵያ ባለው ሁኔታ። በዛ ላይ እኔ በዚህ ዙሪያ በጣም ፈሪ ነኝ። ሁልጊዜም ነው ማሳሰቢያ የምጽፈው። ድፈረት ሊኖር የሚገባው አለኝ የሚባል አቅም ያለው ብረት መዝጊያ የሆነ አቅም ሲኖር ብቻ ነው። አስተማማኝ መከታ ሲኖር። ይኸው እነ አቶ ዳውድ ኢብሳ ጦርነት አውጀው አብረው ቁጭ ብለው ደግሞ ይወያያሉ?
  
ሌሎች ጉልበታም ሚዲያዎች አገር ቢገቡ ህጋዊ ዕውቅና በጠቅላይ ሚኒስተር አብይ አህመድ አንደበት በይፋ ተሰጥቷቸዋል። የራሱ የጠ/ሚር ቢሮ ሰፊ አክብሮት እና አትኩሮት አለው ለሌሎች። የእኔ ቢጤ ተማላ ዝንጣይ ባተሌ ግን በግል ደህንነት ጠበቂ አንዳይቆም እንዴት ተብሎ ድህነቱ ያስራል፤ መንግሥት ጥበቃ ያቆምልኛል አይባል ዕውቅና አልተሰጠም፤ አብሶ አማራ ነክ ጉዳዮች ምንም ዕወቅና ሲሰጥ አልተመከትኩኝም፤ ድርጅቶቹም፤ ሚዲያዎች፤ አክቲቢስቶች ጸሐፊዎች ሊቃነቱ ተንሳፋፊ ናቸው እንደ ውሃ ላይ ኩበት። 

እርግጥ ነው በለውጡ ላይ የሞረሽ ወገኔ ራዲዮ ምን ዓይነት አቋም እንደ ነበረው አላውቅም። ስለማላዳምጠው። 

ብራና ላይ ጋዜጠኛ ደምስ በለጠ ሲያነሳቸው የነበሩ ጉዳዮች ደግሞ ከኢትዮጵያም አልፎ ኤርትራንም የሚያካት ነበር። እዛም ሄዶ ስለነበር … በኢትዮጵያ አርበኞች ትግል … ዕውቀት ስለነበረው የራሱ አቋም ነበረው። ያ ደግሞ ሰብዕዊ መብት ነው፤ አልተመቸንም ያልነው ደግሞ በወቅቱ ሞግተነዋል። ውሎ አድሮ ግን መከራ ሊያወርስ አይገባም ባይ ነኝ …

የሆነ ሆኖ በዚህ የሽግግር ወቅት ሚዲያ ላይ የሰራውን እያወቀ ኢትዮጵያ መሄድ ሞትን መናፈቅም ነው። ለመሆኑ ማንን አምኖ ሄደ? ማን አለው? ደጋፊ እንደሆን ጎርፍ ወይንም ጤዛ ማለት ነው። ኢትዮጵያ እንኳንስ ለእሱ እዛው ወዙን ጠብ አድርጎ በቅንነት በርሃ ለበርሃ ተነከራቶ ላገለገለው ለቆሞስ ኢንጂነር ስመኘውም አልሆነም። አባቱ የሚኖሩበት ቤት ሸንቦቂት እራሱ የወፍ ጎጆ ናት።

ወደ ቀደመው ምልሰት ሳደርግ ሁነኛ ሳይኖር እንዴት ብድግ ብሎ ሄደ? ማን ገፋፋው? ማን አለሁህ አለው? አለሁህ ያለው አካልስ ለራሱ ምን ዋስትና አለው? ደፋር እርምጃ ነው የወሰደው። የሚገርመው በመንግሥት ሚዲያ እራሱ ወደ አገሩ እንደተመለሰ ሲዘገብ አላዳምጠኩኝም እንደ ሌሎቹ። ሌሎች እንደሱ የሄዱት ቀን ከሌት ሲዘከርላቸው አዳምጫለሁኝ። ብቻ ደመ ከልብነቱን ራሱ ነው የፈቀደው። ሁነኛ ሰው ያስፈልጋል። 

ዕድሜም - ሙያምም  -ተመክሮም እንዴት ለራስ መካሪ አይሆንም? ቅራኔ የገባባቸው መስመሮች ሁሉ ቀይ መሰመሮች ናቸው። አንዱን ቢያልፍ ሌላውን አያመልጥም። ራሱን እንደ አሳ መረብ ውስጥ ነው የጨመረው …  እዚህ በስደት ያለው መከራ እኮ የሚቻል አይደለም፤ እንኳንስ ተሂዶ።

አርብ ዕለት እኔ ሰልክ ቁጥሩ ያልወጣ ስልክ ተደውሎልኝ ነበር። በዛ ሰዓት የምጠብቀው የውጭ ስልክ ስለነበር ሳነሳው Goodbye የሚል መልዕክት ተነግሮኝ ተዛጋ፤ አክሰንቱ የአውሮፓ እንግሊዝ አይደለም አሜሪካዊ አክስንት ነው። የሃብሻም ቃና አይደለም።
ብቻ መልዕክቱ አልገባኝም ነበር። ያው የተለመደ ነው የሥራ ፈቶች፤ የሃሳብ አቅም የሌላቸው የኢጎ አርበኞች፤ ዘመንም የማይሰተምራቸው ከንቱዎች ዘወትራዊ ተግባር ነው ብዬ ተውኩት። ስልክም አንስቼም አላውቅም። ይቻላል መክስስም፤ ማሰገድም ግን ካልደከማቸው ይቀጥቅጡት።

ብቻ አሁን የዘሃበሻን ዜና ሳነብ ስለ እሱ ይሆን Goodbye የሚል መለዕክት የተላለፈልኝ ሁሉ ብያለሁኝ። ተረኛዋ አንችም ነሽን ይሁን? አላውቅም።

የሆነ ሆኖ ብረት መዝጊያ የሆነ የሥጋ ዝምድና ግንኙነት ይሁን የፖለቲካ አቅም ያለው ወይንም የዘር ሐርግ አሰተማማኝ ሃይል ሳይኖር አገር መግባት በእጅጉ አስጊ ነው ለባተሌዎች ምስኪነታዎች።

እርግጥ ነው ጋሼ ሙሉጌታ ሉሌም ሆነ ጋሼ አሰፋ ጫቦ አሜሪካ ላይ ነው የተሰወቱ የትም ቢኬድ ሞትን ቀጠሮውን ማለፍ ባይቻልም ከእግዚአብሄር በታች ግን ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል። መቾኮልም አያስፈልግም። ለሞላው ቀን ምን ያጣድፋል? ለዛውም ብአዴን አሜሪካ ስለመጣ ለራዲዮ ጣቢአው ለሞረሽ ቅርብ ጉዳይ የነበር ይመስለኛል። 

ብቻ ከትዳር፤ ከጓደኛ ምርጫ፤ ከሚዘወትርባቸው ቦታዎች እና ግንኙነቶች ሁሉ ራስን ማቀብ ያስፈልጋል። ይህ ደግሞ የሚወሰናው ሃያሲነት መድፈር ከጀመሩበት ማግስት ሳይሆን ከራስ ጋር መክሮ ለመጀመር የወሰኑ ዕለት ነው።

የተለዬ ሃሳብን መቀበል፤ መፍቀድ፤ ትችትን ማፍቀር፤ ከትችቱ ራስን ማረም እና ማስተካከል እኮ የህሊና ሥልጣኔ ሲኖር ነው። ይህ በሌለበት ሁኔታ አገር ለመግባት ተወስኖ ሲገባ ግን እያንዳንዱ መስመር የጥቃት ክፉ ደወል አለበት።

በዚህ ከራራ የፖለቲካ መስመር /ሃርድ ቶክ/ ለመትጋት ሲወሰን እኮ እንዲህ ዓይነቶቹ ለሁሉ የሚፈቀዱ ነገሮች እንደማይፈቀድ ሁሉ ማሰብ ያስፈልጋል። በዚህ ውሳኔ የሚቀር ነገር የህይወት ጉዳይ ይኖራል። ግን ህይወት ከማጣት ወይንም ነፃነትን ራስ ቀምቶ ከመኖር ዘግቶ ገዳማዊ ህይወት ለመኖር መወሰን የተገባ እርምጃ ነው። 

በገዳማዊ ህይወት ውስጥ ሆኖ ግን ያመኑበትን ማድረግ። ዕውነት ደስ ይባለት ዕብለት ትበድ ጨርቋን ጥላ። ይህን መንገድ ዕውነትን የወገነ ሰው እጥረት ቢገጥም፤ የብዙ ሰው ፈን መሆን ባይቻልም ፈጣሪ ይከተለዋል። እግዚአብሄር ዕውነት ነውና።

·       ሰማይ ላይ ያለው የኢትዮጵያ ዴሞክራሲ …

ዴሞክራሲ ማለት ቃሉን ማሽሞንሞን እና መፈለግ ወይንም መመኘት መሆን መቻልን አምጦ አይወልድም፤ በፍጹም። ዴሞክራሲ የሚቀርበውን የህይወት ፈተና ተጋፍጦ አሸናፊ መሆን መቻል ነው። ችሎ መቻል። ድከምት ሲነገር የቁርሾ የቂም ተራራ አለመገንባትን ይጠይቃል ዴሞክራሲ …  ቂምን ተሸክሞ ዴሞክራሲን ማለም የድቡሽት ቤት መገንባት ማለት ነው። ዴሞክራሲ የሚጀመረው ቁርሾን ከመጠዬፍ ነው ...

ለኢትዮጵያ የፖለቲካ ሊሂቃን ዴሞክራሲን እንደ ጣት ቀለበታቸው ያሻሹት ቃሉን። ከዚያ በተረፈ ግን ከሞት በመለስ ሃሞታቸው ነው። ወኔ የላቸውም። ፈሪዎችም ናቸው። ዴሞክራሲ ልክ በሴት ማህጸን ደም እረግቶ ጽንስ ሆኖ ልጅ ሆኖ የመወጣት ያህል ረቂቅ ነውና።

አሁን ጋዜጠኛ ደምስ በለጠ የተገደለው በቁርሾ ነው። በቀል ነው እሱን ህይወቱን ያሰጣው። ለአንድ የዴሞክራሲ ታጋይ ድርጅት ሆነ ግለሰብ ግን ሰው የሚለው ታላቅ ፍጡር በቂም በቀል ህይወቱን ማሳጣት ማለት ፈጠርኩት ባለው የድርጅት ዓላማ ውስጥ አልተፈጠረም ማለት ነው። ያ ነፍስ ገና እጭ ነው ማለት ነው።

ይህ ሳይረታ ነው አሁን ስለ ህዝባዊ የምርጫ ሥርዓት ሴሪሞኒያዊ ተግባራት የተጀመረው። እሱ ተገላገለ አረፈ፤ ነገር ግን ስደት ላይ ያለች ልጅ ደግሞ አለችው። ለዛውም በዚህ ኢትዮ ኤርትራ ፍቅር በፍቅር በሆኑበት ዘመን። ወላጅ እናቱ በህይወት ከኖሩም አድሎ እንደተፈጸመባቸው ነው እኔ የሚረዳኝ። ሌላው ልጁን እያዬ እሱ እንዲህ አፈር ሲሰነቅለት...

ሌላው ግን ሰው የሆነ ሁሉ ህሊናውን የሚሞግተው ምን ትጠብቅ ቀንበጥ ልጁ? ወገን አለኝ ይበል? አገር አለኝ ይበለን? እሱም ዜጋ ነው። እሱም የትውልዱ ቤተኛ ነው። አንድ ለዴሞክራሲ የሚታገል ድርጅት ወይንም ግለሰብ እነዛ ምንም ያለጠፉ ቤተሰቦች በፖለቲካ ሃሳብ አንድ ባለመሆን ምክንያት ሊቀጡ አይገባቸው የሚል ሰውኛ መንፈስ ሊነረው ይገባል። ፍትህ እንዲህ ተጣማም አዲስ ትውልድ አይገነባም።

አሁን የወለደው ልጁ አባት አልባ ሆኖ ነው የሚያድገው ከእሱ በመፈጠሩ። የአባት ዕዳ ልጅ ይውረስ ብሎ አዲስ የዴሞክራሲ የግንባታ ብሎ ሂደትን ማሰብ ይከብዳል።

ይህን ቅጥ መጠን የሌለው ዝንቅ ዳጉሳዊ አመላችን ይዘን ነው ለትወልድ እንታገላለን የምንለው። ሰው ለራሱ ነው ማልቀስ ያለበት። እኔ እራሴ የምጠብቀው ሞት በዚህ መልክ ነው። ምክንያቱም በአስተሳብ የሰለጠነ ተቋም ስለሌለን። ዴሞክራሲ የጨዋታ ሟሟያ ብቻ ነው ለኢትዮጵያ ፖለቲካ። ልብ እንዲገጠምልን የማንሻ፤ ተናጠል የነፃነት ታጋዮች እጣ ፈንታችን እንዲህ ደመ ከልብ ሆኖ መቅረት ነው። ደግነቱ ልጅ የለኝም። በዚህ እጽናናለሁኝ።

እኔን የሚጠበቅ አሟሟትም ይህን መሰል ነው የሚሆነው። ይህን ተሸክሞ አገራዊ ብሄራዊ ዕርቅ እኔ እንጃ ይከብዳል። በህመም ሞተ ለማለት ያስችል ከሆነ አላውቅም፤ እኔ ግን ታሞ ነው የሞተ ብዬ አላስብም …

ሚስጢር ያወጣል እንዳይባል ይሰማው የነበረው፤ የሚያውቀውን ሁሉ ነበር የሚጽፈው፤ ራዲዮ ፕሮግራሙም ከብራና ከሚጽፈው ውጪ ይሆናል ብዬ አላስብም። ሰው የሚጸፈው ራሱን ነው፤ ሰው ሚዲያ ላይ የራሱ ዝግጅት ሲኖረውም ራሱን ነው የሚያቀርበው። 

ስለዚህ ምን ስለ አሰጋ እንደ ተገደለ ግራ ያገባል። ምኑን ይሆን የፈሩት? ምን አራዳቸው? አሁን የሱባኤ ወቅት ነው ሱባኤ ይመርምረው ከማለት ውጪ ሌላ ምንም ማለት አልችልም። መካሪ በማጣቱ ግን አዝናለሁኝ። ኢትዮጵያ ለመግባት መድፈር አልነበረበትም።

ዕውነት ለጊዜው ብትሰወርም አንድ ቀን ግን ትወጣለች፤ ለነገሩ የጋሼ ሙሉጌታ ሉሌም ሆነ የጋሼ አሰፋ ጫቦ ህልፈትም እንዲሁ የውሻማ ሞት ሆኖ ነው የቀረው … ተረኞች ደግሞ እንጠበቃለን፤ በሃሳብ ልዩነት የተረታው ሁሉ፤ የሃሳብ አቅም ፈጥሮ ጥሮ ግሮ ላቡን ጠብ አድርጎ ማሸነፍ የዴሞክራሲን ዲስፕሊን ሆኖ ሳለ፤ አቅም የለም። ይህን በሚመለከት የቁም ሰማዕት ዶር ለማ መገርሳ ሁነው አሳይተውናል … በዚህ እንጽናናለን።

ከዚያ የተረፈው ግን በፍሬም አድርጎ ማስቀመጥ ነው ቃሉን ዴሞክራሲን። ማነው ባለሳምንትን? እንጠብቃለን፤ ተረኝነቱንም ቀጥ ብለን፤ በሙሉ መሳናዶ … እነ ባተሌዎች … እስከ አለንበት ከመጣም በጸጋ እናስተናግዳዋለን …

በሰው እጅ ማለፍ የቁም ሰማዕትነት ነው። ኃጢያት ሙሉው ይሰረዛል። የህልፈታችን አወሳሰን አለማወቃችን ነው እንጂ እንዲህ በሰው ዕጅ ማለፍ የሚያስገኘው ጸጋ እና በረከት ውርሱ ሰማያዊ አክሊል የገነት ነው። የጽድቅ ጉዞ ደግሞ መታደል ነው። እንዲህ ሳይሰቃዩ፤ አንሱኝ ጣሉኝ ሳይሉ፤ ከውን ሽክፍ ብሎ ማለፍ በራሱ መታደል ነው። 

ለጎጂዎች ግን የህሊና ክፉ የዕድሜ ልክ ደወል ነው፤ ልጅም አያወጣም። ትውልድም አያበረክትም …  እሱማ በጽድቅ ጉዞ መንገዱ ተጠርጎለታል … ይብላኝ ለዕለታዊ አሸናፊዎች የሰብዕ መንፈስ ተጻራሪዎች - የቀርሾ አርበኞች። ዳኝነት የህሊና ነው። 

የሰው ደም ደግሞ እረፍትም አይሰጥም። የአቤል ደም ይጮኃል፤ የራሄል ዕንባም እንዲሁ እዮርን ያንኳኳል። የአላዛሯ ኢትዮጵያ እናቶችም እንደሆን ይኸው ነው ልጅ ሰርክ መገበር የለመዳባቸው ነው …

·       በመጨረሻ።

ለቀጥተኛ ተጎጂዎቹ ለጋዜጠኛ ደምስ በለጠ  ባለቤት፤ ልጅ፤ በተሰብ፤ እንዲሁም ለወጆቹ እና ለአድናቂዎቹ ሁሉ እግዚአብሄር አምላክ መጽናንትን ይሰጣቸው፤ እሱማ የጽድቅ ተጓዥ ነው … ነፍሱን በአጸደ አርያም ፈጣሪ ያኑረው። አሜን!



  • ፎቶው ከዘሃበሻ የተወሰደ። አቶ ሸንቁጥ ከጻፉት የተወሰደ። 


ቋሳ ኢትዮጵያ ምድር የሚወገድበት ዘመን ይናፍቀኛል!


የኔዎቹ ኑሩልኝ። 

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።