ምርጫ ለዋንጫ ወይንስ ...

ምርጫ ለዋንጫ ወይንስ ለመበላለጫ ወይንስ ለመፋጫ ወይንሰ ለጋ ወይንስ ለርቱ -በሰላም ግቡ?
„እግዚአብሄርን የምትፈራ ሰውነት የተደነቀች ናት።“
መጸሐፈ ሲራክ ፴፩ ቁጥር ፲፰

ከሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
 01.01.2019
ከእመ ዝምታ - ከሲዊዝ።

·       ብታ።

ቅኖቹ እንዴት አደራችሁ? በዚህች ቅጽበት እኔ በምኖርበት ገዳማዊ ከተማ ነፍስ በዓዋጅ ጸጥ እንዲል የታወጀ ይመስላል። ኮሽ አይሏ ባዕት ከተፈጥሯዋ በላይ በድርብ ላይ ትገኛለች። ጸጥ፤ ረጭ፤ ዝም። መኪና እንኳን የለም። 

ከቶ ሲዊዚሻን እማ ዝምታ እንበላትን ይሆን? ግዴላችሁን እንበላት። ጎረቤቶቼ እራሱ ልጆች አሏቸው። ቤት ውስጥ እንዳሉ አውቃለሁኝ። ነገር ግን ልጆችም ዛሬ ከተለመደው ውጭ ሆነዋል? የጣሪዬ ጉጉቶችም የሉም። እንሱ ደግሞ ምን ሆንኩ ብለው ይሆን። አዬሩ እራሱ ጫን ያለ ነው። ደመመን ተጭኖታል። ከብዶታል እንደማለት። አይዋ ሻሾም ትውር አላለም። እናም አገር ምድሩ እንደ ራስ ዳሽኑ ወይንም እንደ ኪሎ ማንጃሮ ነፋ እደርጓል የጉሮሮን ማዋኛውን ሁለት የደጀሰላም አዋራ በር።

አኔስ? ተምን ላይ ነኝ። እኔ ደግሞ ቅልል ብሎኛል። ጸጥ ረጭ የምመኘው የገነት የተድላ ኑሮዬ ነው። ግርግር ሁካታ አልወደም። አራት ነጥብ የሌላቸው ተናገሬዎችም ግጥሜ አይደሉም። በር ስትከፈት እና ስትዘጋ በእኔ ቤት ስለምን ይሰለቅ የበር አወቃቀር ብዬላችሁ እኔ እህታችሁ የህፃን ልጅ ያህል ብርቱ ጥንቃቄ ነው … ምችት ብሎኛል። በር ለ አኔ ቤቢ ነው። ይህን መሰል ጸጥተኛ ርጉ ዓለም እውደዋለሁኝ - ኮሽ አይሌውን።

·       ምርጫ ደግሞ መጣሁ መጣሁ እያለን ነው ይሆንለት ይሆን? 
.... ዕለቱን በዚኸው ልባርከው ብሏል ... 

ምርጫ በመጣ ቁጥር ሙግት አና ይላል። ሙግት ይቆምሳል እንደማለት። አሁን እኔ ምርጫው ይራዘም አይራዘም ቢራዘም ምን ባይራዘም ምን ለማለት አይደለም። ግን ኢትዮጵያ ምን ላይ ናት የሚለውን ትንሽ ልሞካክረው ብዬ እንጂ። ፍተሻ ቢጤ ወይንም ብርበራ ልንለው እንችላለን ... 

ይልቅ አንድ መልካም የተስፋ ዜና በዚህ በዋንጫ የመሰልቀጫ ምኞት የክብርት ዳኛ ብርቱካን ሚዴቅሳ የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ መሆን አንድ መልካም ዜና ነው። ተዚህ ባሻገር ያለው ግን ጫን ያለ የተግባር ፈተና አለበት እንደ እኔ። እራሱ ህገ መንግሥቱ። ህዝብ ቆጠራው። የሲቢክስ ድርጅቶች የነጻነት እንቅስቃሴ ራሱንም አካሉን በማወቀር ያለው ፈተና፤ ሰው ጠሉ የወል ገመና፤ ህውከት በማደረጀት ያለው ውሃ ያዘለ የሴራ ተራራ … ምን ቅጡ …

ህገ መንግሥቱን ዘለል ላድርገው ነፃ የዳኞች ጉባኤ አንዳንድ ነገሮችን እንደጀማመሩ አዳምጫለሁኝ። ጠ/ሚር አብይ አህመድም ያነሱት መሰረታዊ ጉዳይ ተሰማምቶኛል። ኦዴፓውያን እንዳትሉት ብለውናል። ትክክልም ነው። 

ህዝብ ቆጠራ ሌላው ሞጋች ጉዳይ ነው። በነገራችን ላይ በ80ዎቹ መግቢያ በነበረው የህዝብ ቆጠራ የሥነ - ጹሑፍ ብሄራዊ ውድድር ነበር። እናላችሁ ሥርጉትሻ ሦስተኛ ወጥታ በዛን ጊዜ ብዙ ነው የ300.00 ብር ሽልማቷን ላጥ አድርጋለች። እኔ እራሴ ማሸነፌ ግርም እስኪለኝ ድረስ ነው ያጣጣምኩት ያነን 300.00 ብር እንዲህ እንዳይመሰልችሁ ያስደሰተኝ። እህቴም እኔቴንም እትዬን ትንሽ በትራንስፖርት ወጪ ረዳሁበት። የእሷ በጀት ለእኔ በዬወሩ የጋዜጣ እና የትራንስፖርት ወጪ የኪስ ገንዘብ ትሰጠኝ ስለነበር። 

መደበኛ ሠረተኛ ሆኜ ግን እኛ ፓርቲያችን ሲፈርስ መልሰን ከቤተበስ እጅ ነው የወደቀነው። የዛሬዎቹ እነ ሥም አይጠሩ ደግሞ እስከ ቤተዘመዱ ነው ሚሊዮኑ የተዛቀው …

·       ቆጠራ

የህዘብ ቆጠራ ወሳኙ ጉዳይ ነው። በግምት ላይ የተንጠለጠለው የኢትዮጵያ ሁለገብ አንጡራ ነፍስ መቼ ተረገጥ ሊሆን እንደሚችል ፈጣሪ ይውቀው። ምን አልባት ዘለግ አድርጌ ባስበው የዛሬ 20 ዓመት። ሁሉ ነገር በግምት ነው። 

ግምት የሌለበት አንድም የመረጃ ቋት የለንም። የሆነ ሆኖ አሁን የታለመው የህዝብ ቆጠራ ፈተና ላይ ያለ ይመስለኛል። ቀን ደግሞ ተቆርጧል። ግን በዬትኛው የሰላም እና የደህንነት ዋስትና ነው ቆጠራ የሚካሄደው? አሁን አሁን በኦነግ ሥም ሲባል የነበረው ግልጥልጥ ብሎ የአቶ ዳውድ ኢብሳ ኦነግ በምእራብ ወለጋ ኦዴፓን ከመዋቅር ውጭ እንዳረገው እዬተደመጠ ነው። 

በቤንሻንጉልም ት/ቤቶች መዘጋታቸው ትናንት አንድ መግለጫ አዳምጫለሁኝ። ያው ዶሮ ከእንቁላል ሰለሚጀመር ህዝብም ከአንድ ሰው ስለሚጀመር አስፈጻሚ አካላት ሰላም በሌለበት አካባቢ እንዴት ተዘዋውረው ቆጠራውን ሊያካሂዱት ይችላሉ ነው መሰረታዊ ጉዳይ?ተቆጣሪውስ በዬትኛው የመንፈስ እርጋታ? ትራንስፐርቱስ ምን እርግጥ ያደርጋል ለ አቶ ዳውድ ኢብሳ ብቻ መረጃው ሹክ የተባለ ወደ 40 የሚጠጋ ፈንጅ መጠመዱም ተነግሯል። 

ለማሸበር ይሁን ተልብ ወፊቱ ትጠዬቅ ብቻ ዙሪያው ... ግብግብ ላይ ነው። ህውሃት ሥልጣን ኬአዘ ጀምሮ ይህ ብዙም ተደምጦ አያታወቅም ነበር። ህውሃትም፤ ኦነግም ቢዘህ ባለሙሉ እንደራሴዎች ነበሩ። አዎ አርሲ ወደ አርባ ጉጉ ብዙ ፈንጆች ይጠመዱ ነበሩ ጎንደር በወገራ መስመር በሊቦ መስመርም እንዲሁ ... ታሪክ ለጥፋት ራሱን እዬደገመ ነው። በ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ... ምድሪቱን ዎህ ማለት አልቻለችም።  

ሌላው ገጠር አካባቢ ልጁን ቀንሶ ነው የሚናገረው። ቢስ እንዳያይብኝ ስለሚል። ይህም ሌላ የሥነ - ልቦና ዝግጅት ይጠይቃል። ማለቴ ለናሙና እንደ መነሻ ተውሰዶ አንድ አካባቢ አይሆን ነገር ብሄራዊ ነው ጉዳዩ፤ ከሁሉ በላይ ለዴሞክራሲ ግንባታ መሰረትም ነው የህዝብን ትክክለኛ ቁጥር ማወቅ። ለማናቸውም አገራዊ ጉዳይ ድልድል የህዝብ ቁጥርን ከግምት ወጥቶ ጥራት ባለው ሁኔታ መረጃ ቀመስ መሆን አገር የሚለውን የዜጎች መኖሪያነት በትክክል ገላጭ ይሆናል።

የምርጫ ጉዳይ ቁጥር ነው። ቁጥር ደግሞ በግምት አይደለም። ቁጥር የራሱ ማንነት አለው እና።  ቁጥር የራሱ ማንነት ሲኖረው አንድ ማህበረሰብ ደግሞ ማንነት የለህም ይባላል። በዚህ አያበቃም መደራጀትም የለብህም አለበት። ይህም ብቻ አይደለም በዬትም ቦታ የሚኖር አማራ እንደ ሰው ስለማይቆጠር ውክል አካል የለውም። የተረሳ፤ የተዘዘለለ፤ የተዘነጋ። ይህ ነው ዴሞክራሲ ርቦን የቆዬነው።

አሁን ባለው ሁኔታ የህዝብ ቆጠራ ወሳኝ ከሚያደርጉት መሰረታዊ ጉዳይ በመንግሥት ደረጃ እውነት ያልተደፈሩበት አመከንዮዎች የአደባባይ ነጭ ለባሽ መሆን ስለሚችሉም ነው። ግን ይቻላል ወይ በያዝነው ዓመት በተያዘለት ቀነ ገደብ መከወን ለሚለው በሁለት ወራት በምን ታምር ይህን ታላቅ ብሄራዊ ጉዳይ መከውን ይቻል ይሆን?

የህዝብ ቆጠራ መሬት ላይ የሚሠራ ተግባር ነው። ንደ አንድ የፖቲካ ድርጀት 2 ሰዎች ተነጋግረው ፕሮግራም ነድፈናል ብለው የሚያውጁት አይደለም። አንድ ሁለት ሦስት እራት አምስት እየተባለ ሁለት እና ሁለት ሲደመሩ አራት ይሆናሉ እዬተባለ ከዚህም ባለፈ በዕድሜ በፆታ በብሄረሰብ በሃይማኖት በሙያ በወር ገቢ በተማረ እና ባልተማረ የሰብ ሙሉ ቋትን ከአውነት ጋር አደባባይ ማውል ነው ቆጠራ ከተባለ። መቼም የአብይ መንፈስ ልግብግብ ነገር ግጥሙ እንዳይደለ ልብ ልክ ነው። ዘለግ ያለ የሃሳብ አቅም ነው ያለው።

እና አሁን ባለንበት ሁኔታ በስውርም በግልጥም ኦነጋውያን በሚያተራምሱት የሃሳብ ብተና፤ ሙት መሬቱን የሙጥኝ ያለው በተልዕኮ የግጭት አዋራሪስነት ፊታውራሪ የወያኔ ሃርነት ትግራይ የማንፌስቶ ራሮቶች ባሉበት ይቻላል ወይ ነው ቁም ነገሩ? ሌላም የጃዋርውያን አክቲቢስት የመንፈስ እሰጣ ገባም አለ። እሱ አያንቀላፋም ቀዳዳውን ሁሉ ይጠቀምበታል። ከድርጅት በላይ ነው። ሰው አቅልሎ ሲያዬው ይገርመኛል። አንድ አዶልፍ ሂትለር እኮ ነው ያን ያህል ሉላዊ ትርምስ የፈጠረው። ግራጫማ ሰብዕን ለ አሉታዊነት ከሆነ አደጋው ሰፊ ነው። ሌላም አለ ስንሳሰብ ባጅተናል ... እኔና ብዕሬ። ጉብ ብሎ ፊታውራሪ ደርባቤ። 

ትግራይ ላይ ይቻላል ህውሃት ከፈቀደ ቆጠራው፤ ሌላ ቦታ ላይ ግን እንዳይቻል ራሱ ህውሃት አደርጎታል። ለምሳሌ አማራ መሬት ላይ ጭልጋ ዋና ዒላማቸው ነው። ቤንሻንጉል ሌላው ምሽጋቸው ነው። የታፈነው ያለዬለት ሃረሬም ላይ መሰሉ ፈንጅ ተጥመዷል። ይህን በጥምረት ጃዋርውያን፤ ኦነግውያን እና ህውሃታውያን አስፍስፈው የሚጠብቁት ነው። እና መጋቢትን ይዞ እስከ ሚዚያ? እኔ አይመስለኝም ነው። ከተሳካለት የአብይ ካቢኔ ጥሩ ነው። ይርዳው! ግን መርግ ነው እራሱ ትክክለኛ የቆጠራ ውጤትን ለመጠበቅ።

·       መርግ ሃሳብን ወይንም የትልም ጅረትን ይዘን ስንጓዝ ደግሞ ... 

መርግ ሃሳብን ወይንም የትልም ጅረትን ይዘን ስንጓዝ አንድ ብልህ ነገር ኦነጋውያን በሙሉ ምርጫው በታቀደለት ሁኔታ እንዲካሄድ ፈልገዋል። ይህ ራሱን የቻለ ትንተና ይፈልጋል፤ የሆነ ሆኖ ለህብዝ ቆጠራው አለመደናቀፍ እንደ አንድ መልካም አጋጣሚ ብንወስደው እንኳን ቤት የሌለው 2 ሚሊዮን ህዝብ አድራሻዬ የት ብሎ ይመዘግብ ሌላው የሚያፋጥጠን ጉዳይ ነው … 

አድራሻ የለሹ ወገን ሰፊ ነው። ስፋቱ ገና ቀጣይ መሆኑን ሰሞኑን ቤብሻንጉል ክልል ያሉ ዜጎችን ሰላምን ለማስጠበቅ በመከላከያ ሠራዊት በአዬር ወለድ መንገድ ተዘግቶባቸው  በእነሱ ጥረት መኖር ጢስ ጢንቢስ እያለ ስለመሆኑ ዶር ለማ መገርሳ ነገረውናል።
ይህን መርግ ሃሳብ ይዘን ስንጓዝ የምርጫው ገበታንስ እንዴት ወደሚለው ይወሰደናል።

·       ምርጫ ምን ይፈልጋል።

አንደኛ - ትክክለኛ ቋሚ አድራሻ ያለው ህዝብ ይፈልጋል።
ሁለተኛ - የተረጋጋ ማህበረሰብን ይሻል፤
ሦስተኛ  - ተደማጭነትን አና አድማጭነት መዋደድን ይሻል።
አራተኛ  - ሰላምን በጽኑ ይመኛል፡
አምስተኛ - ሰውኛነትን በተደሞ ይሻል።
ስድትሰተኛ -  አዲስ ሃሰብ አመንጭነትን ይፈልጋል በዚህ የጠ/ሚር ቢሮ ችግር የለበትም።
ሰባተኛ - የቀረበ ግንኙነትን ይፈልጋል።
ስምንተኛ - ተከተታይ ተግባራትን ይጠይቃል።
ዘጠንኛ - ነፃነትን ሴሉ እንዲሆን ይሻል።
አሰረኛ - ሙሉ የሎጅስቲክ አቅምን ይፈልጋል።
አስረአንደኛ - ገበሬውን ዜጋ ነህ የሚል ግልጽ ቁርጠኛ አሳታፊ አቋም ይጠይቃል።
አሰራሁለተኛው - ስክነት አብዝቶ ይጠይቃል።
አስራሦስተኛ - የጠራ የፖለቲካ መስመርን ይሻል።
አስራአራተኛ - አዲስአዊነት / እሸታዊነት / ያማትራል።
አስራአምስተኛ - ሥልጡን አሰተሳሰብን በዘመኑ ልክ ይራል።
እስራስድስተኛ - ግልጽነት በንክሮ ይሻል።
አስራሰባተኛ - ሙያዊ የህሊና የማደራጀት የፖለቲካ ብሰለት አቅምን ይጠይቃል።
አስራ ስምንተኛ - ነፃ ሚዲያ የነፍስ ያህል ነው።    
የምኞት ቀለበት ከምርጫ ጋር ለማሰር ባነሰ ግምት እንዚህን ይሻል …

·       እሸታዊነት

ውዶቼ ሁሉንም አላነሳም የተወሰኑትን ነጥቦች ብቻ ነው ማንሳት እምሻው። በሥነ - ልቦናው የተሰናዳ ሥልጡን አስተሳሰብን ምርጫ ይሻል፤ ለዚህ ኢትዮጰውያን በቅንጅት ያሳዩት ምስክር ቢሆንም ከዛ ወዲህ ያለው ምስቅልቅል ብቻ ሳይሆን አሁን ሌላ አዲስ ታዳጊ ትውልድ ደግሞ በአዲስ መንፈስ አለ። ዲጅታሉ ዓለምም ሌለው ሞጋች ጉዳይ ነው።

ኢትዮጵያ የታዳጊ ወጣቶች አገር ሆና ነው እማያት። ከ13 እስከ 17 ዕድሜ ያሉ ወጣቶች የሚገርም ብቃት እና ንቃት አይባቸዋለሁኝ። አገራዊ ተሳትፏቸውም እጅግ የሚደንቅ ነው። ይህ አይገባቸውም ቅንጅትን መንፈሱን እንመልሳለን የሚሉ ወገኖች። አብሶ የአማራ የህልውና ተጋድሎ ይዞ የመጣው የፖለቲካ ለውጥ እንደዛ ከሁለት ዓመት በፊት በሞገድ አጣጥሎ አብጠልጥሎ ሻንፕዮን መሆን የሚቻልበት ወቅት ላይ አይደለም። የአማራ የህልውና የማንንት ተጋድሎ የመንፈስ ዲታ ነው። ይህን ልብ የሚለው የለም። 

ዝም ተብሎ ገብያ ላይ እንዳለ ገብያተኛ ብትፈልግ በዚያ ባትፈልግ በዚህ ተብሎ በጉልበት ተጥሶ ዘው የሚባልበት አይደለም። ሞገደኛ መንፈስ ነው። አክብሮ ለሚነሳ ብቻ ነው ቀልብን የሚሸልመው። አቃሎ አጣጥሎ ለሚያው ጊዜ አያቃጠልም፤ አንድ ነገር ተከሰተ ሲባልም ንቡ እንደተነካ ቀፎ ቆቅ ሆነው ነው እዬጠበቀ ያለው። በጥሰት ትርፍ ፈጽሞ አይታፈሰም። ሌላ አሻም ከመጣ ደግሞ ምድር ቁና ትሆናለች። አማራ የአኔ የሚለው አቅም ላይ ነው። የማይታይ ይመስላል ግን መንፈሱ ጉልበታም ነው። የመረጃ ልውውጡም ቀላል እንዳይመስላችሁ። 
 
የአብይ መንፈስ በአማራ ብሄርተኛነት ገኖ መውጣት አሳስቦት እንደ ግንቦቶች ሞክሮት ነበር በመባቻው አልቻለውም። እኔም ጽፌ ነበር። የዲያቆን ዳንኤል ብትልናም ባክኖ ነው የቀረው። ለዚህ ነው አሁን ከመሼ በልዩ ሁኔታ ከአብን ጋር የጠ/ሚር ቢሮ እና የም/ጠ ሚር ቢሮ ልዩ ምክክር ያደረጉት። ይህም በራሱ በቂ አይደለም።

ከአብን መንፈስ ጋር የሆኑም ያልሆኑም እንዳሉ ማሰብም ይገባል። ልክ እኔ ሥርጉተ ሥላሴ  ከአማራ ድምጽ ራዲዮን ዓላማ እና ተግባር ጋር አብሰንት እንደነበርኩት ማለት ነው። ይህ ማለት በጣም ረቂቅ ያደቡ የማይታዩ መንፈሶች አሉ። ለምሳሌ የዶር ገዱ አንዳርጋቸው የስሜን አሜሪካን ገለጣ ላይ ስለሰጡት መልስ "ስለ ሥልጣን ማንሳት ስንፍና" ነው ሲሉ ቤተ እስኪነቃነቅ ድረስ ነበር የሳቁት። በአጀንዳም ከሌሎች ጋር ተወያይተንበታል። ቤተሰብ ድረስ ይዘልቃል - ዛሬ።

አንድ ሰው በሌለበት ካቤኔ ያን ያህል እርቀት መሄድ ከተቻለ ለምን አዴፓ / ብአዴን እራሱን አያፈርሰም በአዋጅ። የትራንስፖርት ሚኒስተሯን ወ/ሮ ዳግማዊት ሞገስን ስቼ አይደለም። የእሳቸውን ወደዚህ ስልጣን መምጣት እራሱ በፖለቲካ ትንተና ለማዬት አዴፓ /ብአዴን አቅሙን ያዬሁበት አጋጣሚ ነበር። አልፈተሸውም። 6 ለዜሮ በሆነ ውድድር ምን ላይ እንደቆመ ፈተና ላይ ስለመሆኑ ብአዴን አላውቀውም ወይንም አልገባውም። 

ፖለቲካ ለመወሰን አቅም ማግኘት ማለት ነው። መወሰኑን አስረክቦ ገለባውን እጓዛለሁ ካለ ነገን መጠበቅ ነው። እንደነዚህ ዓይነት አመክንዮችን እንዳለ ወይንም እንደ ወረደ እማንቀበል ነፍሶች አለን። አንድ ሰው አይናቅም። አንድ ሰው ብዙ ነው። ለመገንባትም ለማፈረስም። የናቀ ደግሞ ይወድቃል። ያከበረ ግን ይከበራል። ክብረቱ ደግሞ የመንፈስ ነው። ረቂቅ። የድምጽ ቆጠራውም ሆነ የምርጫው ሁኔታ በዚህ ረቂቅ ሁነት መመሰጥ ይኖርበታል።

 የሚወጡ አዳዲስ የሃሳብ ማስከኛ አዳዲስ አዋጆች፤ የሰዎቹ ምደባ እና ስምሪት ሥራዬ ብሎ ማዬት ያስፈልጋል። ስለምን ይሆን የአብይ ካቢኔ በምክትል ሚ/ር ደረጃ የተመደቡትን ዝርዝር ለማውጣት የታቀበው? በዜና ግን ለቅሞ ቀመሩን መስራት እንደሚቻል አላወቀውም። ግልጽነት ጥሩ ነገር ነው። ብአዴን ራሱ የተደራጀበትን ዓላማ አያውቀውም። ትናንትም አውቆት አያውቅም ዛሬም። በፈጣሪ ቸርነት ነው አሁን አማራ መሬት ላይ የአብይ ፍቅር ገኖ ያለው። በዚህ ግዴለሽነቱ አንሳፎት እንዳይቀር ስጋት አለብኝ። ለዚህ ነው ተግቼ በለማ እና በአብይ መንፈስ ለተከታታይ ቀናት የሠራሁት። 

 በዚህ ውስጥ በቁጥራቸው አነሳ የሆኑ ብሄረሰቦች ደግሞ አሉን። እነሱም ዜጎቻችን ናቸው። ለዚህ የሰሞናቱ ምስጋና ይግባው የአማራ የብዙሃን መገናኛ እና የአርቲስት ወይኒቱ ጉዳይያችን ያለ ጥሩ መሰናዶ አቅርቧል። እርግጥ ዘግይቷል። ያችን  የመሰለች የአገር ፈርጥ ምን መሰላ ተጎሳቁላ የትም ተጥላ ስናይ በኢትዮጵያዊነት ውስጥ ያለውን ፈተና ተመልከተነዋል። 

እሱ ብቻ ሳይሆን ባለቤት የሌላቸው ባለውለታ ወገኖቻችን ጉዳይ የ27 ዓመቱን የሙት በቃ ዘመን ቅኝት በምልሰት እንድንሄድበት አድርጓል። ለወጉ የብሄር ብሄረሰቦችን አስከባሪው የግንቦት 20 የሰማዕታት መታሰቢያ ደረጃው በሚገባ ተፈትሾበታል። የብሄር ብሄረሰቦች ቀን ስለሚባለውም።   

እራሱ የዛ ትንታግ የአርበኛ ቲቶ አንጎል አርበኛ ኮ/ አብዲሳ አጋ ባለቤት ያሉበትን ሁኔታም ሌላው ማሳያ ነው። ይህ የ27 ዓመት መከራ ብን ብሎ በአንድ ጀንበር ይብናል ባይ አይደለለም ሃሳቡን ያነሳሁት። ህዝብ ቆጠራ ዜጋ ላይ ስለሚጀመር ገና ለብዙ አብይ አመክንዮች መንፈሳችን ዝግጁ አይደለም ነው ቁም ነገሩ። ችግሮቻችን እራሱ አላወቅናቸውም። በምናውቃቸው ችግሮቻችን ላይ እራሱ አልተስማማነም። 

በችግሮቻችን ላይ ሳንስማማ መፍትሄዎቻችን ቢፈልቁ እንደ ፏፏቴ እንኳን የመፍታት አቅማቸው ህሊናው ሥነ - ልቦናው ጉዳይ ስለሚጠይቅ ተግባር ላይ ወገቤን ማለታችን አይቀሬ ነው። አሁን ያለው መከራ እኮ እነዛ ባለስልጣኖች እንደ ተለመደው ልቅምቅም ብለው አይሆኑ ሆነው ቢሆን ኖሮ ይህ ፈተና አይኖርም ነበር። 

ግን ፈተናውን በአዲሱ መንገድ እዬቆሰለ ይጀመር በሚል ደፋር እርምጃ ነው ጥቂቶችን ነፍስ ለማትረፍ ይህን ያህል ህዝብ ፍዳውን እዬከፈለ ያለው፡ ይህም ሆኖ ስለምን ይህ ሆነ የሚለውን ዕውቅና ለመስጠት አቅም የለንም። አቅም አዋጡ ሲባል ደግሞ ታይቷል። ቀን ሙገሳ ነው ሌሊት ንደት ነው። ሰባራ ሰንጣራ እዬጋጣጠሙ ሃሳብ መበትን። 

አሁን ከዚህ ላይ የመንግሥት ሠራተኛው እናውሰድ በዛ 5 ለአንድ መጠርነፍ ሲቀርለት፤ ጥላውን ማማን ተስኖት፤ ወጥቶ መግባት ከተራቆተበት ዘመን መላቀቁ አልገባው ብሎ ለሚከፈለው ማህያ እንኳን መስራት አልቻለም። „ደርሶ መልስ“ የቴሌቪዥ ድራማ አመትባል የያዘችው ካራክተር ያነን ነው። የሚከፈለው ግን የማይሰራ ማህበረሰብ ነው ያለን። ስለምን? ነፃነት ማለት ምን ማለት እንደሆነ የግንዛቤ ድርቀትም እርቀትም ስላለብን። አገር ሰለሚለው የመኖር ትርጉምም እንዲሁ። 

እናመሰግናለን የለም። እናመሰግናል ማለት ምን ያህል የሥነ - ልቦና መሰናዶ ስለመሆኑ አናውቀውም። በዬወሩ ደሞዝ ሲወሰድ የሰው ልጅ ለሠራበት ሊመስለው ይችላል። ያን ቦታ ስለማግኘቱ፤ ለዛ ቦታ ያበቃው ሂደት እና የማህበረሰቡ ተሳትፎ፤ አገር የምትባል መሬት መኖሯ ስለመሆኑ ለዛ የተከፈለው መሰዋዕትንት ትዝ አይለውም። ስለዚህ ደሞዙን ሲቀበል አንድ ሰው ከገንዘብ ከፋዩ  ወይንም በባንክ ሲላክለት አመሰግናለሁ አይልም። በዚህ ብቻ ስትሄዱ ምን ያህል ቁም ነገሮችን ዘለን ዴሞክራሲን እንደምንናፍቅ … ማስተዋል ይቻላል።

ስለዚህ ኢትዮጵያዊው ሰው ራሱን ማሸነፍ መጀመር አለበት - ከሊቅ እሰከ ደቂቅ። ምህረት ማድረግ ካለበትም ለራስ ቀድሞ ምህረት ማድረግ ይኖርበታል። ለራስ ምህረት ማድረግ ይህም አዲስ እሸታዊ እሳቤ ነው እስቲ እንጀምረው … ምህረት ለራስ ሳይሰጥ ምህረትን እንናፍቃለን፤ ለነገሩ ምህረት መናፈቅም በደንበር ነው የእኛ ነገር … ለሁሉም ነገር ክትር አለበት። የክት እና የዘወትር። በዚህ ሁሉ ሂደት አይዋ ምርጫ ደግሞ መጣሁ መጣሁ እያለን ነው … እና ምርጫው ደግሞ ህዝብን ለሥልጣን ለማብቃት ይባላል? እንዴት በምን መንገድ? ለመሆኑ ዜጋ ለሚባለው እኩል ዕውቅና አለን? 

·      

እና አቤቶ ምርጫን እንኳን ናልን እንበለው ወይንስ ቆይልን። ወይ ባላንባራስ ምርጫን ሂድልን ወግድልን እንበለው? እሱ አይታክተው እኛም ይደከመዋል የማንል ልበ ደንዳኖች ነን። ለነገሩ እሱም አታካትኳችሁ ብሎ አያውቅም። አንድ ዓመት ከአራት ወር ለወረቀት ላይ ብዙ ነው። ዛሬ ጥር ነው። ከአንድ ወር በኋዋላ የካቲት ይሆናል። ከዬካቲት በኋዋላ መጋቢት ይመጣል። ዶር አብይ አህመድ ጠ/ሚር ከሆኑ አንድ ዓመት ሊሞላቸው ስንት ቀን ቀራቸው? ስንት ሰዓት? ስንት ደቂቃ? ሥርጉትሻ እና ቁጥር ጋሼ ሙላት ይጠዬቅበት። 

"ጨዋታን ጨዋታ ያነሳዋል" ይላሉ ጎንደሬዎች --- እስኪ እንዋዛው ወጉን ... እንዲህ  ...

ወይ ጋሼ ሙላት መምህሬ ነበር። የሂሳብ። የታላቅ እህቴም ባለቤት የልብ ጓደኛ አብሮአደግ። እናላችሁ የኢሠፓ ሠራተኛ በመነበርኩበት ጊዜ እኔ ክ/ አገር ላይ እሱ አውራጃ ላይ ተገናኘን። ለካስ መምህር ሲኮን ብቻ ነው አባት እና ልጅነቱ … እሱም ብቻ አይደለም ነፍሷን ይማረው እና እትዬ ሙሉዬ መመህሬም በአኢሴማ አመራር ሆነ ስትመጣ እኔ ደግሞ የፖለቲካ ድርጅት መሪዋ ሆኜ ቁጭ። „አሁን ማን ያምናል ያቺ ሚጢጢ እንዲህ የመድረክ ሰው ትሆናለች ብሎ“ ትልኝ ነበር፤ በነገራችን ላይ ጎረቤቴም ስለነበረች ለሰኞ ማክስኞ ጨዋታ ልቤ ውልቅ ሲል ሁሉ ታውቃለች። መሬቱን ጉድጉድ ሳደረገው። በኋላ ደግሞ ኮስታሪትን ... 

… የሆነ ሆኖ መምህራኖቼ እምታወቀው የማት ነገር ቁልቁለት ነው እና ቁጥሩን ሳልጠዬቅ ቀናቶች ወረቀት ላይ ብዙ ቢመስሉም መሬት ላይ ግን ላፍ ወይንም እፍፍፍፍ ነው የሚሉት … እና ይህቺ አንድ ዓመት ከምንትሶ ቀናት ምንም ማለት አይደለችም … በጣም አጭር ጊዜ ነው። አዲስ ለውጥ እና ፍላጎትን አቀናጅቶ አዲስ መሰረት ለመጣል። 

እራሱ የምርጫ ቦርድ ብሄራዊውን ማለቴ ነው ቢሮው እራሱ አፋኝ አፋኝ ስለሚል ጠረኑ በአዲስ አዬር፤ በአዲስ አደረጃጀት ሰውኛ ሰውኛ እንዲል ሥር ነቀል የሆነ ማደራጀትን ይጠይቃል። ከዚህ ላይ የህግ ባለሙያነት ብቻ ሳይሆን ምህንድስናም ይሻል።

ያ ግራጫማ ብቻ ሳይሆን ያ የመንፈስ የተከዘነ፤ የመታሰሪያ፤ የመታፈኛ፤ የመደብደቢያ፤ የመሰዳጃ በመንፈስ የኦሾቲዝም አንባ አዲስ አዬር እንዲኖረው የምህንድስናም አዲስ ቅኝት ይጠይቃል። የዕብለት ማመረቻው ፋፍሪካው እራሱ ዶሴው ሁሉ ወደ ሙዚዬም መግባት አለበት። ትናንት በጻፍኩት አንድ ጭብጥ „የተባረከ ትውልድ ለተባረከች አገር“ ይህ መቼም የደልዳላዋ ቀዳማዊት እመቤት የወ/ሮ ዝናሽ ታያቸው ቢሮ በትልቁ አሰርቶ ግቢው በር ላይ መሳቀመጥ ይኖርበታል።

ቢሯቸው ለዚህ መትጋታቸውን የሚያሳዩ እሸታዊ ተስፋዎችን የዘመኑ መርሆዎች ቀልብ የሚያርፍባቸው ሆነው ተደራጅተው ከሆነ እሰዬው ነው፤ ካልተደረጀ ግን እንደዛ ቢሆን ምኞቴ ነው … አሁን ምን አመጣው ልትሉኝ ትቻላለችሁ። ምርጫ እኮ የትውልድ መሠረት ነው። ይህ ቀጣዩ ምርጫ ከቀልሃ የራቀ ግን በሃሳብ ልዕልና መሰረት የሚጣልበት ነው ከተባለ ለነገ አዝመራ አስቧል ማለት ነው። ነገ ደግሞ ትውልድ ነው። ግጥም በሉት ስዋሰው ተዚህ አንጻር ይታይ ..

ስለ ቢሮ አደረጃጃት እኔ ይህን ሃሳብ አብይ ሆይ በሚለው ወ/ሮ ፈትለወረቅ የዲሞክራሲ ግንባታ ሚ/ር ቦታን ሲይዙ ተቃውሜ በጻፍኩት መጨረሻ ላይ ማዬት ይቻላል።


 አቤቱታ አስራስምንት ላይ „ከሆድ ውስጥ ስለታሰረው የግማድ ገመድ“ ይላል ንዑስ እርእሱ። ስለዚህ እሱን ብቻ ልታዩ የፈቀዳችሁ ማነበብ ትቻላለችሁ - ትእዛዝ ግን አይደለም ትሁታዊ ማሳሰቢያ እንጂ። 

በአረመኔነት መርዝነት ፍዳ ለከፈለ ዜጋ የመንፈስ መጠገኛ ያስፈልገዋል። „መርዝ  ለእሰረኛ የተፈቀደበት መከራ“ „ለኦሮም እና ለአማራ።“ ይህ ግንቦት 7 የሚበላው ቅርፊት ነው መሸፈኛ። አማራ ነው የተማገደበት። አሁን እንኳን ከኤርትራ ተመለሰ ስለተባለው ሰራዊት ፌድራል ለመረከብ አቅም የለውም። ሚስጢሩ የአማራ ሠራዊት ስለሆነ ነው። ከፊሉም ሥራ ፍለጋ ከስደት ወደ ስደት ሱዳን ነው ያለው። 

የሆነ ሆኖ በዚህ የመከራ ዶፍ ለኖረ ማህበረሰብ በዴሞክራ ግንባታ ያሉ መንፈሶችን እንግዳ እንዴት መቀበል እንዳለባቸው፤ እንዴት ቢሮ ተናፋቂ ሊሆን እንደሚገባው ዘርዘር ያለ ሃሳብ አቅርቤ ነበር። ያ የዴሞክራሲ ግንባታ ቢሮ ቢቀርበት የምርጫ ቦርድ ቢሮ ግን ተስፋን የሚያባባል፤ ቅንነትን የሚያቆላመጥ አይዟችሁን የሚያበሰር መሆን ይኖርበታል። ጎንደሬዎች „ከፍትፍቱ ፊቱ“ እንዲሉ …

ስለዚህ ያን ተስፋ ሲማቅቅበት የኖረበትን ቢሮ በአዲስ መንፈስ ማደራጀት ሲባል ግቢው እዩኝ እዩኝ ቆይብኝ ቆይብኝ እንዲል አድርጎ ለማደረጃት አዲስ ዲዛይነር መሆንን ይሻል። ከዛ በላይ አብረው የሚሠሩትም ሆኑ አዲስ የሚመጡትን አዋህዱ ለማምራት ራሱን የቻለ የሥነ - ልቦና መሰናዶ ይጠይቃል። ከጭካኔ ወደ ርህርህና፤ ከአረመኔነት ወደ ሰዋዊነት፤ ከተጫኝነት አድማጭነት፤ ከገፊነት አቅራቢነት፤ ከተራጋጭነት አባባይነት ወዘተ ... ለመምራት ብቃትን አምጦ ለመወለድ ጊዜ ይጠይቃል ... 

ከዚህ አለፍ ሲል የበታች አካላትን ማወቃር ደግሞ መዘረግቱም ሌላው ፈተና ነው። አብሶ ኦሮምያ ላይ ኦነግን ያልሰነቀ ለማግኘት ብዙ ጣሪያ የነካ ፈተና አለበት፤ እራሱ የመንግሥት ሚዲያው OBN  … በሌላም ቦታ ቢሆን ከፖለቲካ ነፃ የሆነ ለማግኘት ዳገት ነው። ፖለቲካ አባል ካልተሆነ ጉሮሮ ዝግ ነው የነበረው። ቄሱ ከ እነ ክህነቱ ተነክሮበታል እኮ። 

ትግራይ ሉዑላዊት መንግሥት ናት ራሱ በአዲሱ የምርጫ ቦርድ ለመመራት መፍቀዷ ገና ፍ/ቤት የሚገተር ይሆናል።ግን ጠበቃ አሰናድቶ ይሆን የጠ/ሚር ቢሮ። ከህውሃት ውጪም ሰውን ከዛ ለማስቀመጥ አንድ ሃሳብን የተለዬ ለማስተናገድ በማይቻልበት ቦታ ነፃ እና ገለልተኛ የምርጫ ቦርድን ማሰብ ከመርግም በላይ ነው።

ይህ እንግዲህ ገና ቢሮውን በማደራጀት ያለው ፈተና ነው። ተፎካካሪ/ ተቀናቃኝ/ ተቃዋሚ የሚባሉት ደግሞ ተዘዋውረው መዋቅራቸውን ዘርገትው ለመሥራት ፈቃዱ እስከምን ነው ሲባል ጸሐፊው ሳይቀር አብን ሽዋ ቢሮ ከፈተ ብሎ ሲጦፍ ነበር። 

እንግዲህ አንድ ጸሐፊ የሥነ - ጥበብ ቤተኛ ነው። አይደለም ሽዋ የትም ቦታ እኔ እማደራጃቸው ማህበረሰቦች አሉ ካለ አንድ የፖለቲካ ድርጅት መብቱ ነው የትም ቦታ ጽ/ቤቱን የመክፍት። ሽዋ ላይ አማራ በሚያሰተዳድረው ነው እንግዲህ አብን ቢሮ መክፈት የለበትም የተባለው። ድርጅት የሰው ማህበር ነው። ሰው ዜጋ ነው ሲባል ድርጅቱም ዜጋ ነው ማለት ነው። 

ሌላው ሲስረከረክ የከረመው ገመና ደግሞ በወጋ ጠቀም ለዓመታት መንፈስ በመናድ ሲባተን የነበረው መንፈስ ለይቶለት „ጎጃም የራሱን ክልል“ የሚል ሌላም ሃሳብ ተነስቶ አንብቤያለሁኝ። „የሸዋ ፓርቲም“ እንዲሁ። በዚህ ውስጥ ህብረ ብሄር ነን የሚሉትን ፈተና ማዬት ይቻላል።

·       ድርጅት።

ድርጅት ከምለው ሰዋዊ መንፈስ ስንነሳ የኢህአዴግ አራት የግንባሩ አባላት ጉባኤ ሲያካሂዱ እንደ አንድ ግንባር ሆነው ውሳኔ ወሰነዋል። ያ መቼም አዬር ላይ ተንሳፎ የቀረ ጉዳይ ይመሰለኛል። የወረቀት ነገር እንዲህ ነው። ህውሃት እንደ ድርጅት በግንባሩ ውስጥ ነው ስለሚባል ጤና ጥበቃን / ብአዴን ስለሰጠው ልዩ ሽልማት/ የሴቶች የህፃናት እና የወጣቶች ሚ/ር እንዲሁም የኢንደስትሪ ሚነስተርን በካቢኔ ይዟል። በፎርፌ ከወጣው ከብአዴን በተሻለ 5% ከኦዴፓ ጋር የተጠጋጋ የካቢኔ ቦታ አለው ህውሃት። ፌድሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ብቻ አይደለም ከሥር ካሉትም ወሳኝ ክፍሎች የህውሃት ማንፌስቶ አስፈፃሚ አካሎች ናቸው የቢሮው ፊታውራሪዎች።  ይህን ሰው አንስቶት አያውቅም። 

ይህም ሆኖ የህውሃት አካላት ደግሞ ለፌድርሹን አንገዛብ ብለው የራሳቸወን ግዛት ፈጥረው ተቀምጠዋል። ለፌድሬሽን ባለ የራስ ገዝ ጉብታ ላይ ነው ያለው ህውሃት። ህውሃት እንደ ድርጅት ኢህአዴግን ተፈካካሪ ሆነ ለመውጣት ከግንባሩ ሳይወጣ በሁለት መሰረታዊ ጉዳይ ተጠቃሚ ሆኗል። በአንዱ በኩል መብቱ ይጠበቃል ልጆቹ ወሳኝ ቦታቸው ላይ አሉ። በፌድሬሽን ቦታ አለው። ግዴታውን ለመወጣት ግን አንዲት ስንዝር አልተራመድም። 

ስለዚህ ኢህአዴግ አንደ ግንባር አለ ወይ ለማለት አያስደፍርም። የአነጋውያን መፏለልም ከዚህ የመጣ ነው። የፖለቲካ ፓርቲ ኢትዮጵያ አላት ለማለት አንችልም። ያላት ድርጅት ነው። ድርጅቶች ናቸው እንጂ ለመጪው ምርጫ ተፎካካሪ ሆነው የሚቀርቡት የፖለቲካ ፓርቲ ለመሆን የአባላት ምልመላ ስልጠና ስምሪት እና የእጩነት ጊዜ አይፈቅድም። ባለ ቀለብ ተካፋዮች እንደ ቀድሞው አንድነት፤ እንደ ቀድሞው ቅንጅት ያሉት ምስሎች ደግሞ ለተውኔት ህውሃት ምን ያህል እንዳሰናዳቸው ደግሞ እዛ ጉባኤ ላይ በሚያቀርቡት ወልጋዳ ሰባራ ሰንጣራ ጥያቄ ማዬት ይቻላል።

አሁን አንድም በፓርቲ መርህ ሥር የተደራጀ የፖለቲካ ፓርቲ ሳይኖር ነው ቀጣዩ ምርጫ የታሰበው። የማህበር ውድድር ይባል ምን አንበለው አላውቅም። ወይንም የደጋፊዎች ፉክክር ቢባል የሚሻል ይሆናል። ራሳቸው ሊሂቃኑ ሥርዓት ባለው ደንብ እና ፕሮግራም፤ ፖሊሲ ኖሯቸው በዛ ውስጥ የበቀሉ አይደሉም። በዛ ላይ በፖለቲካ ውሳኔ የተመደቡም ብዙ ናቸው። 

ሊሂቂ መሪው ማለቴ ነው በፓርቲ ህገ ደንብ ከታች ግዴታውን ተወጥቶ፤ ዝቅ ብሎ እንደ አንድ አባል ተወያይቶ ከታች ተመርጠው የመጡ አይደለም። ንቅንቅ የለም ከታች ተመርጠን መጣን ቢሉ ለማሟያ የሆኑ የሥራ ክፍሎችን እንጂ ዋንኛውን የሊቀመንበሯን ቦታ በተለመደው በድርጅታዊ ሥራ ለአክተሮቻቸው ሰጥተው ነው ብቅ የሚሉት ተጣመርን ተዋህድን የሚሉትም ቢሆኑም። 

ትናንት የምናውቃቸው ሊቀመናብርት ነገም ይመጣሉ … ነገም የምናውቃቸው እንዲሁ ዴሞክራሲ የላሜ ወለደች ምኞት ነው ለእኛ። በዚህ ውስጥ ደግሞ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ምኞተኞች ነን … ይህን የጣሰ አንድ ነፍስ ቢኖር የለማ ገናና መንፈስ ነው። የለማ መንፈስ ትውልድኛ ነው።

ሌላው ፈተና ያለው በኦዴፓ ውስጥ ነው። አባሉን ትቼ አካሉ እራሱ ከኦነጋውያን ከጃዋርውያን መንፈስ የጠሩ ስለመሆናቸው ማንዘርዘሪያ ያለው አይመስልም። ዱራኛዊ ወይንም ሰርገኛ ጤፋዊ። ስለዚህ በመጪው ምርጫ ኦዴፓ የሚፎካከረው ከራሱም ከሰገሰጋቸው ተፎካካሪዎቹ / ተቀናቃኞች/ ተቃዋሚዎች ጋር ይሆናል። 

እንግዲህ ፕሬዚዳንታዊ አሰተዳደርን ካልመረጠ አውራው ድርጅት ኦዴፓ በስተቀር ለኢህአዴግ በቀጣይነት ወድድር ፉክክር ላይ ሁለቱን ኢትዮጵያዊነትን የጸነሱ መንፈሶችን ለማስቀጠል እራሱ ግማድ ነው። እነሱን አልባ ደግሞ ከባህር የወጣ አሳ ይሆንና ኢህአዴግ በፎርፌ ቦታውን ለቆ ለአዲስ መንገድ ተከታዮች ብቅ ለሚሉ ይሆናል ድካሙ ሁሉ። …

ኦዴፓ አለኝ የሚለውን መንፈስ ቅጥ በሌለው ቅንነት እራሱን በራሱን አሳጥቷል። የሄደበት መንፈስ የኦሮሞን ሊሂቃን የመሰረቷቸውን ድርጅቶች ሁሉ ከበቂ በላይ ዕውቅና አሰጥቶ፤ ዝናቸውን አስግንበቶ በመንፈሰ አንድነት የ ኦርምያን ጥቅም መንበር ላይ ማዋል ነበር።

እንደ ስለት ልጅ አውቁልኝ እያለ በአጀብ ሲያቀማጠል የራሱን የተጋበትን፤ የደማበትን መንፈስ አሰረክቦ ቁጭ አለ። አሁን በበዛ ትእግስት በምንትሶ በቅብጥርሶ የሚለው ራሱን ማሳጣት ሳያሰኘው በግልጡ መንገድ እሱ ባሰበው ልክ ከዞጉ ሊሂቃን ባቀነው ቅንነት ልክ ልብ ለልብ መገናኘት አልቻለም። እነሱ በመቁንን ነው ፍቅር የሰጡት ለመሻገሪያ ድልድዬነት ብቻ ... 

ስለሆነም አሁን ሁሉም በአደብ እንደጀመረው ያለ ይመስላል … ምክንያቱም በዛን ጊዜ „ኢትዮጵያዊነት ሱሴ ነው“ ተጎድቷል። ተጋግጧል። ቋስስሏል። ተፈግፍጓል። ብዙ መንፈሶችም አዝነዋል። ስለሆነም አሁን ኦዴፓ በሚሰጣቸው መግለጫዎች ጋር መንፈስን አቀናጅቶ ለመተሳሰር አቅም ጠፋ። 

ይህን የታመቀ ፍላጎትን ለማቅናት ሸማቹ አልፈቀደም። አሁን መልሶ እነሱን እንደ ጥፋተኛ እዩልኝ ቢልም ኦዴፓ ብዙ ሰው በዝምታ ውስጥ ያለበት ምክንያት በዚህ ነው። ፍቅርን ታማኝነትን በአግባቡ የማስተዳደር አቅም ማነስ ብቻ ሳይሆን አሁን በአንድም በሌላም የመስከርም 5ቱን ግርግር ደጋፊዎችን የፌስ ቡክ አርበኞችን ነው ወደ ሥልጣን ያመጣው። ትናንት ከ አንድ ሙሁራቸው አንድ እርሰ ጉዳይ ተነስቷል። 

"አብይ የኦነግ መንፈስ ወራሽ ነው ይላል።" ጅል አይሁኑ ሊሂቁ።  ነፍስ ያለው ኢትዮጵያዊ ዜጋ ኦነግን አምልኮ ፍቅርን ያህል ክቡር ነገር አይሰጠውም። ኢትዮጵያዊነት ለኦነግ አንጡራ ጠላቱ ነው። አሁን እዬወደቀ እዬተነሳ ያለበት ሁኔታም ይኸው ነው። በኢትዮጵያ ይቀናባታል ኦነግ። ክብር ደግሞ የፈጣሪ ነው። በቅዱሱ መጻሐፍ የተቀደሰች ናት ኢትዮጵያ።
https://www.youtube.com/watch?v=fn4E4z1LA1s

የኦነግ ትግል ወራሽ ዶ/ር አብይ ነው Ethiopia Abiy Ahmed "አዲስ ፈንጅ!"

ለጠላት ፍቅር ቀርቶ ማድመጥ አይፈቀደም። ሌላው የአብይን ሥነ ግጥም አላነበቡትም ሊሂቁ ዶር። "አንቺ አገር ኢትዮጵያን።" በዚህ ውስጥ ነው አብይ ቅኑ ያለው። ግጥሙ ብቻ ሳይሆን እስራኤል ላይ የተናገሩትም በተለያዬ ሁኔታ ያደረጉትም ንግግር መንፈሳቸው ኢትዮጵያዊነትን ቀድሶ የተነሳ ነው። ለዚህም ነው ወታደራቸው ለመሆን ፈቃደኞች የሆነው። 

https://sergute.blogspot.com/2018/11/blog-post_22.html

የፈጣሪ፤ የእናት እና የልጅ ውለ ወግ -በቅኔ ዘጉባኤ ህዋዊ ጠረጴዛ።


በዛ ሥነ - ግጥም ውስጥ ኢትዮጵያ ደምቃ ነው የወጣችው። ፍቅራችን ትግላችን አነሱ በቡድን ተዳርጀተው ሲፋለሟቸው ፊት ለፊት ወጥተን የተጋፈጥነው በፍጹም ሁኔታ ዶር አብይ አህመድ የኦነጋውያን የመንፈስ ወራሽ ባለመሆናቸውም ነው። አሁን ጥርጣሬ እንዲነግስ ደግሞ ሌላ ክብሪት ተለኩሷል። በዚህ ወቅት ይህን ማንሳት ይህም ሌላ ቀይ መስመር ማለፍ ስለሆነ በሚገባ ሊፈተሽ ይገባል። 

እርእሱ ተሰማሚ አይደለም። እኛ ኦነግን መሬት ላይ የምናውቅበት እና ዶሩ ብርሃነ መሰቀል የሚሰጡት ትንታኔ ህሊና ሊሰጠው የሚችል አይደለም ከዶር አብይ ጋር ማለካለክ አልነበረባቸውም። ትንታኔው በሳል ነው የሞሞገቻ አቅሙ አንቱ ነው ግን አብይ "የኦነግ መንፈስ ወራሽ" የሚለው ከባድ ነው ለመቀበል። ብዙ ነገር ይንዳል። በነገራችን ዶር ብራሃነ መሰቀል የሚጽፉት ጹሁፍ ከራራም ይሁን ለዘብ ያለ ታዳሚ ነኝ። የለብ ለብ አይደለም። ፖለቲካዊ አቅም አላቸው። በመንፈስ ያሟግታሉ። ስለዚህም ታዳሚያቸው ነኝ።  

በሌላ በኩል እኑ ሙሁሩን የአማራ ተጋድሎ እና የኦሮሞ ንቅናቄን በጠ/ ሚር አብይ አህመድ የሰሜን አሜሪካ ጉብኝ አዘጋጅ ኮሜቴ ውስጥ ሲሳተፉ የኢህአፓን ጥያቄ ነው የወረሱት ብሎው ነበር ተጋድሎዎቹ። ኢህአፓ ነው አማራ እንዲደራጅ የሚፈቅደው ዋና ሴሉ የትግሉ እኮ አማራ ጨቋኝ ነበር ነው። እርግጥ ነው ለኢህአፓ ጀሌነት አማራ ራሱን ገብሯል። ቀየኑን አቃጥሏል አንድዷል። ትውልዱንም አምክኗል። አክተሮቹ አሉ አሁን የመድረክ ተዋናዮች ናቸው። አንጋቹ አማራ ደግሞ የአፈር ሲሳይ ሆኗል። የአማራ ተጋድሎ የኢህአፓን ዓላማ አንግቦ አልተነሳም። በፍጹም። የዘበጠ ትንተና ነበር። የሌለን ሬሳ መንፈስ ማጠጋጋት። አሁን ያዬሁት ኦነጋውያን ወራሾች ኢትዮጵያን ወደ አዲስ መንገድ ወሰዷት ዓይነት ነው ... አይመችም። 

ይህም ሆኖ እነ አይታክቴ ቅኖች በቅንነት አዎንታዊ በሆነ መልኩ ድጋፍ እዬሰጠን ነው። በጣም ተፈታኙ ኦዴፓ ይሆናል በመጪው ምርጫ። ሰርገኛ ጤፍ ሆኖበታል አሁን እራሱ ድርጅቱ። ማን ምን እንደሚያስብ አያውቀውም። ሁሉም መንፈሱን የመሸገው  በኦነጋውያን በጃውርውያን በበቀለውያን መንፈስ ውስጥ ነው። ኦዴግ ግልጽነት ያለው ነገር ቢታይበትም ርስተ ሃሳቡን ግን ከሥር ነቅሎ ከአብይ እና ከለማ መንፈስ ጋር ለመጋባት እርግጠኛ የሚያደርግ ነገር ይኖራል ብዬ አላስብም። ይህ ቢሆን ኖሮ ከ5ቱ ውሳኔ ሰጪዎች እራሱን የመነጠል ደፋር እርምጃ ይወሰድ ነበር።  

ኦዴግ አቋሙ እንደ አዬሩ ጸባይ ስለሆነ ልብ አያስጥልም። እርግጥ ነው ኦዴፓ ፈተና ላይ ባለበት በአሁኑ ወቅት ከጎኑ የቆመ አንድ ድርጅት ቢኖር ኦዴግ መሆኑ እንደ ተጠበቀ ሆኖ። በዚህ ማህል ምርጫን እንዴት? የለማ ዲዛን አቋራጭ ገብቶ ፕሬዚዳንታዊ ከሆነ ያዋጣል … የተሻለ ብቻ ሳይሆን ጥሩ መንፈስ በተወሰኑ ክልሎች ስላለ … 

ከዚህ ባሻገር ግን ያን በብዙ ድካም የገነባውን መንፈስ ለመናድ ራሱ ዕውቅና የሰጣቸው ሃይሎች አስጥሰውታል። ሌላ ቦታ የነበረውን ተቀባይነቱንም አዲስ አበባ፤ ቡራዩ፤ አስፈሪው የሻሸመኔ ጉዳይ ለዛ ተልዕኮው የታጨ የታቀደ የበሰለ ጉዳይ ነበር … ይህም ሆኖ አብዝቶ ትእግስቱን የሰጠው የኢትዮጵያ ህዝብ በአደብ በአውንታዊነት ሂደቱን እዬተከታተለ ነው። ወደዚህ ህዝብ ፊትን ማዞሮ ይገባል። ዶር ለማ መገርሳ ሲደክሙ የባጁበት ምላሹን ያዬት ይመሰለኛል። 

·       ሰውኛ።

ሰውኛ መንፈስ አለ በጠ/ሚር ቢሮ ላይ። ሰውኛ መንፈስ አለ በጠ/ሚር ህሊና። ሰውኛ መንፈሱን ግን ለመጋራት የፈቀደው ምን ያህሉ ነው? እንግዳ ክብር መሆን ትውፊቱ ከተፋቀ 27 ዓመት ተቆጠረ። በዬለም ያለ ሰውኛ ግን አለ። ሰውን እንደ ማስፈራሪያ ታይቶ መጣብን ከተባለ ሰውኛነት አለ ለማለት አያስደፍርም። 

ሰው ይፈራል አሁን ላይ። መተመማን የለም። ተጠራጣሪነት ነግሷል። መታማመኑም እራሱ በቃሉ አይገኘም። በቃሉ የሚገኘው ንፋስ ብቻ ነው። ማለቴ የሞገድ ማዕበሉ ወጀብ በለጋው ቁጥር በቁጥር ስፍር ህብረ ቀለማት ሞገዱን ተደራሽ ያደርጋል። ያ ደግሞ ለሳንባ ምችነት እንጂ ፈዋሽ አይደለም። በዚህ ምክንያት በተራራቀ መንገድ ፍላጎትን አቀራርቦ ለማፎካከር ገና ብዙ የቤት ሥራ አለበት። ሁሉም።

·       ነፃ ሚዲያ።

ኢትዮጵያ ነፃ ሚዲያ ኑሯት አያውቅም። ህልም ነው። ወደፊትም በአጭር ጊዜ  ነጻ ሚዲያ ይኖራል ብዬ አላስብም። ካለ ነፃ ሚደያ ደግሞ ነፃ ምርጫ ጋዳ ነው። ሚዲያ ያላቸው የፖለቲካ ድርጅቶች ግን የተሻለ ተስፋ አላቸው ብዬ አስባለሁኝ። ኦነጎች በጣምራ አላቸው የመንግሥቱም ለእነሱ ስለሚሰራ በስውርም በግልጽም። ግንቦቶችም አላቸው። ኢህአዴግ አለው።

ከዚህ ውጭ ያሉ የፖለቲካ ድርጅቶች ግን ተስፋ ቢስ ናቸው። ስለዚህ ልብ ያላቸው የፖለቲካ ድርጅቶች ጠንካራ ሚዲያ ማቋቋም ግድ ይላቸዋል። ራዲዮ ፕሮግራም በቂ ነው። አብሶ አብን። እርግጥ ነው ማህበራዊ ሚዲያ ሚና ቢኖረውም ለተደራጀ ተከታታይ የህሊና መሰናዶ ተመራጭ አይደለም። ከመረጃ ልውውጥ ባሻገር ፋይዳው በድርጅት ጽንሰ ሃሳብን አስርፆ ትንታግ ወታደሮችን ለማፍራት አያስችለውም። ወታደሮቹ ደግሞ  ትውልድን የጸነሱ የማግስት ማወች።

ድርጅት የሰው ልጅ ህሊና የሚታነጽበት ተቋም ነው። ለዚህ ተቋም በጽኑ መሰረት ላይ መዋቀር ተከታታይ የሚዲያ ተግባራት ያስፈልጋል። በ2015/16/17/ ገነው የወጡ የፖለቲካ ድርጅቶች እና ዛሬ መሬት ላይ በ2018 ያለው አቅማቸውን ስትመዝኑት ግነቱን ጉልላት ያደረገው ሞገድ ብቻ መሆኑን ማዬት ትችላላችሁ።

መሬት ላይ ወደ ምርጫ ሲገባ ከዜሮ ነው ሁሉም አህዱ ብሎ የሚጀምረው። ፕሮፖጋንዳ ላይ ያለ ወጀብ እና መሬት ላይ የሚሠራ የድርጅት ተግባር ማወዳደር አይደለም አቃራርቦ መሳብ እንኳን አይቻልም። የሚያስደስተው ነገር ሁሉም ለቀጣዩ ነገር ገዢውን ኢህአዴግን ጨምሮ ከዜሮ ነው የሚጀመረው። የሚበልጠው በጀት ስላለው፤ ሁለተኛ የኢህአዴግ ሊቀመንበር አዲስ ሃሳብ ማፍለቅ ጸጋቸው መሆኑ ብቻ ነው። የወጣላቸው ተሟጋችም የወጣላቸውም ተናጋሪም ናቸው። በንግግር ጥበብ እራሱ የሚፎካካራቸው ሊሂቅ ከሌሎች የፖለቲካ ድርጅቶች ማግኘት አይቻልም። ሞጋች ናቸው። 

በሌላ በኩል ክንድ እና መከታው የጸጥታ ሃይሉ የኢትዮጵያ ከሆነ ሌላው መልካም ዜና ነው። ለዚህ ደግሞ ቆርጫለሁኝ እያለን ነው የጠ/ሚር ቢሮ። እኛም ያደርግልን ብለናል። አሁን ባለው መሥፈርት ኢህአዴግ እንደ የፖለቲካ ድርጅት ጠንካራ አይደለም። ጥንካሬው የት ላይ እንዳለ ገልጫለሁኝ። 

ይልቅ ባልተገመተ ሁኔታ የኢትዮጵያ መንግሥት በሙሉ አቅም ላይ ይገኛል። ድህነቱ እንዳለ ሆኖ። የኢትዮጵያ መንግሥት በሙሉ አቅም ራሱን ችሎ በፓርቲ ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነትን ካቴና ቀንበር ሳይጫን መቀጠሉ ሰው አላስተዋለው ካለሆነ አንድ ሥርነቀል እርምጃ ነው። የ50 ዓመቱ ሥልጣን ላይ የነበሩ፤ ሥልጣን ለማያዝ የተፋሉም ድርጅቶችን ህልም ትልም ምህንድስና ሁሉ የናዳ የዘመን በርከት ነው። በዚህ አዲሱ ትውልድ እንኳን ደስ አለህ ልለው እሻለሁኝ።

አሁን የሚታዩ የአዲስ የመንገድ ዝርጋታ እራሱ የለማ ምህንድስና በአቋራጭ ገብቶ መንግሥት ላይ መሥራቱ ነው ያዋጣው። ይህ የሚጠቀመው ደግሞ ለተፎካካሪ/ ለተቃዋሚ/ ለተቀናቃኝ ድርጅቶችም ጭምር ነው። እራሱ ድርጅታቸውን ከተነሳፈፈ የአዬር ላይ የዝና ግነት አውጥተው ወደ ትክክለኛው የትወልድ ትሩፋት ወደ የሚሆን ፓርቲ ማሸጋጋር ይጠበቅባቸዋል ግራ ተኮር ድርጅቶች ሁሉ። ይህ በዚህ እንዳለ ነው ምርጫ የሚታሰበው … ገና ዜሮ ላይ ነው። … የህሊና ተግባር እንደ ፖለቲካ ድርጅት ቁመና ለመቆም።

 በዛ ላይ አክቲቢስቱ፤ ጋዜጠኛው፤ ተንታኙ ደግሞ መንፈስ በመሰብሰብ ለትውልድ ቋሚ በሆኑ ሞራላዊ ዕሴቶች ላይ እዬተጋ አይደለም እና ይህን ምርጫ ሳስበው እኔ እንደዬዘመኑ የገና ጨዋታ ነው እማዬው። ዘልቆ የሚታይ ነገር ላይ መደበኛ ተግባር ስለሌለ። ዕለታዊ ተኩር ነው። በዚህ የሚመሰገነው ብን ብሎ የቀረው ፓርቲዬ ኢሠፓን ነው። አልተንጨባረቀም። ትወልድን ለተደጋጋሚ ጊዜ በወፌ ኢላላ ተስፋ አላባከነም ….

·       መፈናቀል።

የመንፈስ ማፈናቀል ማይክ የጨበጠ፤ ብዕር የጨበጠ፤ ብራና ያለው ሁሉ የቅኖችን መንፈስ ለማፈናቀል የተደረገው የወበራ ዘመቻ እንቅልፍ ላይ የነበረው መንፈስ ሁሉ አቅም እንዲያገኝ የበኩሉን አስተዋፆ አበርክቷል። 

በሌላ በኩል የአካል መፈናቀሉ ሌላው የገዘፈ መከራ ነው። አካሉ የተፈናቀለ አድራሻ የሌለው ለጊዜው 2 ሚሊዮን ወገን አለን። ቀጣይም ነው። ይህ ወገን መቀመጫውን ወይንስ ዴሞክራሲ ተብዬውን ህልም ነገር ይሰብ? ከዚህ ጋር አብሮ የሚታዬው ሚሊዮን እርህብተኛ ወገንም አለን። እሱስ እህል ውሃ ወይንስ ዴሞክራሲን መና ከሰማይ ያውርድልኝ ብሎ ይጠብቅ? 

ለራበው ወገን፤ ቤቱ ንብረቱ ተቃጥሎ ሜዳ ላይ የፈሰሰው ወገን ምርጫ ቅንጦት ብቻ ሳይሆን ዘመናይነት ነው? 2 ሚሊዮን ወገን ቤት አልባ ነው? ልጆቹ አይማሩም። መደበኛ የሚባል የመኖር ንድፍ የለውም። መኖር በሌለበት የዴሞክራሲ ምርጫ? በጥቂቱ ይህ ይበቃል። ትንሽ የመተንፈሻ አዬር ያስፈልጋል።

·       አገራዊነት

አገራዊነት በሥንት ክፍልፋይ መንፈስ እዬበታለ ነው? ዝርፊያ፤ የመሳሪያ ግዥና ሽያጭ ጦፏል፤ የዶላር የኢሮ ሽሽት እና በገፍ ታድኖ መያዝ፤ የደረቅ ወንጀል እና ውጤቱ፤ የሰላም ፍላጎት እና ጭብጡ፤ የመደበኛ ሠራተኛው ልግመኝነት፤ ፍላጎታችን እና አቅማችን አለመመጣጠን፤ የውስጥ መረጋጋት እና ስጋት ማዬል። ሞራላዊ ዕሴቶች ድጠት። በዚህ ቅይጥ ሁኔታ ምርጫ እንዴት ባለ መንፈስ
ርጋ ይበል?

·       ከዚህ በላይ ገበሬውን በውክልና ወደ ሥልጣን ለማምጣት 27 ዓመት ሁሉ እያኖረ የተሰረዘ ዜጋ ነው ገበሬው። ሁሉም ተፎካካሪ/ ተቀናቃኝ/ ተቃዋሚ የሚባሉት ዜጋ የሚሉት ከተሜውን ብቻ ነው። ይልቅ መፈክሩ "ዴሞክራሲ ለከተሜው ባርነት ለገጠሩ" ቢባል የተሻለ ነው። ሁሉም ዳገት ቁልቁለት አይደፈሯትም። በገበሬ አገር?!

·       ሁለማነችን ስንፈትሸው ፍላጎቱ መኖሩ እንደ አንድ የዕድል አጋጣሚ ብናዬውም የህሊና መሰናዶ እና ተጨባጭ ሁኔታው ግን አልተገናኘም። አዲሱ ለውጥን በመንፈስ እዬሄደበት ያለውን ጉዞ በጥሞና ለማጥናት፤ ለመመርምርም አቅሙም ፈቃዱም ስስ ነው። በኩረጃ ለመሄድ ቢመከርም ዳጥ ነው። ይህን ለማገናኘት ታማረኛው የ100 ቀን ዑደትን በተመለስ በተደገም በናፈቀን ና ና ና ብንለው እንኮን በሦስት መንግሥት እዬተናጠ ላለው አዲስ ሰዋዊ ተፈጥሯዊ ዕሳቤ ትርጉም ገብ የምርጫ ውጤት ለመጠበቅ ህሊናን ይፈትናል ወይንም ይፈትላል። ተስፋን በሹሊት አለመፈንከቱም እሱ ሆኖ ነው ሩህሩህ። 

    የአገር ጤንነት ታውኳል ነው የጹሑፈ ዕድምታዊ ቁም ነገር። ህውከቱ በሚታዬው ተኮር ስለሆነ ነው እንጂ ሌላ መፈንቅል ወይንም ኩዴታም ቢኖር ብለው ፆም ጸሎት ላይ ያሉ መንፈሶች ይኖራሉ። ከተቻለም በምግብ ብክለት። ከውጭ ወደ አገር ከገቡት በምርጫ ቦርድ የተመዘገበው አንድ የዶር ኮንቴ ሙሳ ድርጅት ብቻ ነው። የየአቶ ዳውዱ ኦነግ እንደ አዲስ አለመዘገብም ብሎ አሻፈረኝ ብሏል። ይህን ብጥብጥ ደግሞ ጃዋርውያን ይፍለጉታል።

·       ኩዴታዋ በለስ ከቀናት ትደገማለች፤ ትሰለሰላች። የቆረጠ ተግባር ሳይሆነ በቆረጣ መግባት ዕድሜ ልኩን ላለመ ተግባር ፈሪ መንፈስ ምቹ ጊዜ ከተገኘች … ጉሮ ወሸባዬ ነው። ተፈላጊው ቦታ ጠ/ሚር ብቻ ስለሆነ። ዴሞክራሲ፤ ለህዝብ ጥቅም የሚባለው የተጎዳው ቤተሰብ ሁሉ ያውቃዋል። ለዬዘመኑ አዲስ መስዋዕትነት የትናንቱ መስዋዕትነት እንደ አካፋ እና ዶማ የትሜና ተጥሎ፤ ሃላፊነትም መውሰድም የለም። ነገረ ትውልዱ ለዕለታዊ ማህበርተኞች ምናቸው አይደለም። እነሱ የማይችሉትን ሲፈርዱ ሲቀዱ ግን ማን ብሏቸው፤ … 



    መተማመኛቸው ሃይል እና እርግጫ ስለሆነ በመፍረስ ውስጥ የሚገነባ ቅብ ዴሞክራሲ … ነበር ህልማቸው። ባልኖረበት ዲሞክራሲ ህልም። እና ዘመን በቃችሁ ብሎ ይህን አዲስ ቀና ቅን ዘመን አምጥቶ ገላገለን። 

ስለዚህ የጠ/ሚር ቢሮ ሆነ የተወካዮች ምክር ቤት በማስተዋል ሆኖ የቆመበትን ደርብ እና ምድር ይመርምር እንላለን እኔ እና ግልጧ እና ቀጥተኛዋ ብዕሬ … ለነገሩ እኔም የግንባር ሥጋ ነኝ። እኔ የሥላሴ ባሪያ ከፈጣሪዬ በታች የምፈራው ምንም ነገር የለም። "ደርሶ መልስ ፊልም" ላይ አህድን እያዩ እነ ጓድ ገ/መድህን በርጋ እኔን እንደሚስተዋሱኝ ነው። ሳልጠይቅ አልቀበልም የፈለገ ትዝዛዝ፤ አድራሻው ባልተዋቀ ተግባር አልሰማራም። ት/ቤትም እንዲሁ ነበር። ላመንኩበት ደግሞ አይተውኛል አለቆቼ።

ሳይገባኝ ተቀብዬው የማውቅ ትእዛዝ የለም። ሲሰኘኝም ከተጠራሁበት እቀራለሁኝ። አንድ ጊዜ ጓድ ፍቅረ ሥላሴ ወግደረስ ጎንደር መትተው ነበር። ከዋናው ጉባኤ ሳንጠራ ራት ግብዣ ላይ ተጠራን። አልሄድኩም። ደውለው አንደኛ ጸሐፊው ሲጠይቁኝ ለትራፊ የመሄድ ግዴታ አልነበረብኝም ነበር ያልኳቸው። 

ሰንበት ቀን እንድም ቀን ሥራ ስገባ ዩኑፎርም ለብሼ አላውቅም። ትርፍ ሰዓቴን ለሥራ ሳውል ደስ የሚለኝን ልብስ ለብሼ የመሄድ መብቴን ደግሞ አስከብራለሁኝ። ትርፍ ሰዓት አውደ አመት ጨምሮ መስራት ብቻ ሳይሆን ማትራሰ እና አዳርም አለበት። ግዴታዬን ለመውጣት መብቴን መጠበቅ ግድ ይለው ስለነበር ፓርቲዬ አይናገረኝም። ቢናገረኝም ሙግቴን አይችለውም። ራሱ ዩኒፎርሙ በሞድ ነው የሚሰፋው  ባፈነገጠ ሁኔታ። ዩኑፎርሙ ይለበሳል ግን ራሴ ባወጣሁት ዲዛይን …

ስለዚህ የምወደውን የማከበረውን በበዛ ተስፋ የምጠብቀውን የአብይ ካቢኔም የሚሰማኝን ለመግለጽ ጋዳ የለብኝም … እሱም ተነካሁ ብሎ ጦር እንደማያዘምትብኝ ተስፋ አደርጋለሁኝ፤ የሰፋ የተባ የፋፋ የሃሳብ ሙሉ አቅም ስላለው ሙግት ግጥሙ መሆኑን ቀድሜ አውቃለሁኝ እና። ሥርጉተ ትከላልኝ እንደማይልም ነው ... ሰውኛ ስለሆነ እንደ አረመኔዎች ስላማያሰብ ... እንዲያውም ሳይከፈለኝ እንዲህ በነጻ መባተሌን ያዝንለትም ይሆናል ዜጋው ስለሆንኩኝ። ነፃ አገልግሎትም ግጥሙ ስለሆነ ክብርም ስላለው። 

ያለው ድርጅት ከሆነ ሊሂቅም ቢሆን ፍርሃት ድርሽ አይልበትም። መሄሱን ይወደዋል። ጓዳ ጎድጓዳውንም ይሞላበታል። ለዲሞክራሲ ግንባታ ላይ ሥም ከሰጠኋቸው አንዲት ፖለቲካ ምኗም ያለሆነ ግን ሰብዕዊነት ህሊናዋ የሆነች ነፍስ በሆነ ሃላፊነት ተመድባ አዳመጥኩኝ። እናም ሐሤት አደረኩኝ። ሌላም ቅድስት አለች። ስለ እሷም እጥፋለሁኝ ራሱን አስችዬ። ከእሷ ጋር መሰራት አይደለም ለተወሰነ ደቂቃ መቆም የነፍስ ትፍስህት ስለሆነ።

ስለዚህ መደመጤን በአንድም በሌላም አረጋግጫለሁኝ። ስለሆነም አንጥፋለን ልባችን የሚለንን ግን በአዎንታዊነት እና በቅንነት … ልባሞች ደግሞ ያዳምጡናል እንደ ሌሎቹ የውጭ አገር የዲግሪ አምላኪ ፖለቲከኞች አያዘመቱብንም … 

እሺ ውዶቼ ስለምርጫ ያለኝ ይኽው ነው። እንደ ወትሮው አይደገመም አይሰለሰለም በዚኽው ይከወናል። ይራዘመም አይራዘመም ሃሳቤ አይደለም ግን ሁኔታዎችን ያዬሁበትን ገለጥኩኝ። ተፈጠመ።  

ኢትዮጵያዊነት ከሃሳብ በላይ ነው!

የኔዎቹ ቅኖቹ መልካሞቹ ኑሩልኝ።

መሸቢያ ጊዜ። 

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።