ዝቅዝቅ ቁንዳላ!

እንኳን ደህና መጡልኝ።

ዝቅዝቅ ቁንዳላ!

ምንም እንኳን በለስም ባታፈራ፣ በወይን ሐረግ ፍሬ ባይገኝ፣
 የወይራ ሥራ ቢጓል እርሾችም መብልን ባይሰጡ
በጎችም ከበረት ቢጠፉ ላሞችም በጋጥ ውስጥ ባይገኙ
 እኔ ግን እግዚአብሄር ደስ ይለኛል፤
በመዳህኒቴ አምላክ ሐሤት አደርጋለሁ።
ትንቢተ ዕንባቆም ምዕራፍ ፫ ቁጥር ፲፯ ቁጥር ፲፰

ከሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
ከእመ ዝምታ - ሲዊዘርላንድ።



·       ጠብታ

የኔዎቹ አዱኛዎቼ እንዴት አላችሁልኝ? እኔ አምላኬ ክብሩ ይስፋ ይንሰራፋ ደህና ነኝ። ለዛሬ የመረጥኩት ቃለ ወንጌል የመከራ ወጀብ መቋቋም የሚያስችል የህይወት መንገዴ ነው። ቤተሰቦቼ የሥርጉተ ንብረት ይሉታል። አዎን የመንፈስ እርስቴ ነው። 

በዚህ ቃለ ወንጌል አስተምህሮ ተስብሬ ሳልወደቅ፤ ግራቀኝ የማዕበል ሸክሙን፤ የመንፈስ ጭነት ቁሩን እና ሃሩሩን አደላድዬ እና አስመችቼ አስደስቼም የቅዱሱን ሰማዕት የወንጌል አርበኛውን የሐዋርያው ጳውሎስን „የይበቃኛል“ ምህንድስና ምራኝ ብዬ በሙሉ ሰብዕና፤ በሙሉ ሞራል፤ በሙሉ መንፈሳዊ አቅም በተፈጠርኩበት ልክ እና ቁመና መኖርን ደስ ብሎት እንዲኖር የተፈቀደበት ታላቅ የህይወቴ ክፍለ አካል ነው። ዛሬ ላለው እርእሴ የመረጥኩበት ወሳኝ ጉዳይም ስለአለ ነው።

·       እፍታ።

ዛሬ ቅዳሜ ነው። ብራ ነው። ግን ጸጥታው ገኖ ወጥቷል። እናም ዛሬ ልሠራ ያሰብኩትን ጉዳይ ተግ አድርጌ እነሆ እናንተን አገኝ ዘንድ ወደድኩኝ። ቀደም ባለው ጊዜ ጉዳዩን አንስቼ በሳተናው ድህረ ገጽ ጽፌበት ነበር ስለ አቶ አሰማህኝ አስረስ። አሁን ሰሞኑን ደግሞ ያ የጻፍኩበት ነፍስ በአማራ የብዙሃን የመረጃ ድርጅት ከሌሎች ሦስት ሊሂቃን ጋር ቃለ ምልልስ አድርገው ተመልክቻለሁኝ። ቃለ ምልልሱም አልገረመኝ ግርም ያለኝ ጠማዳው ሹመቱ ነው።

ያ 20 ሺህ ወጣት የታሠረበት ሚስጢር እሳቸውን አቶ አሰማህኝ አስረስን ከዚህ ቦታ ለማስቀመጥ ከሆነ ወሸኔ¡ ነው ማለፊያ¡ ታዲያ እንደምን ብለን፤ እንደምን ሆነን ብአዴንን አዴፓ እንበለው። የእኒህ ሰውዬ የጭንቅላት ሃርድ ዌር የወያኔ ሃርነት ትግራይ ማንፌስቶ ነው፤ ነፍሳቸው ደግሞ የሙት መንፈሱ የሄሮድስ መለስ ዜናው እርቃን ሶፍት ዌሩ ነው። ይህን ያገናዘብኩት ዛሬ ሳይሆን በዛሬ አመቱ በነበረው ውይይት ነው።

ውዶቼ ሰሞኑን በአንድም በሌላም ምክንያት አትኩሮቴ በሌላ ጉዳይ ይሁን እንጂ ከዚህ እርእሰ ጉዳይ ጋር ነፍሴ ደረስ መለስ ሲል ነው የሰነበተው። እርምጃው አቁሳይ አክሳይም ስለሆነ። ዓይኑ እያዬ ብአዴን አቶ አሰማህኝ አስረስን ይመድብ? እንዴት ዓይነት ድፈረት ነው? ስለምን አቶ ጌታቸው ረዳን አምጥቶ አይሾማቸውም? 

ይህ እርምጃ ለእኔ በቀጥታ ዘመነ አብይን ለማሳጣት፤ የአማራ ህዝብ እንዲከፋ ሆን ተብሎ ታስቦበት በቀመር የተከወነ ነው ብዬ ነው እማስበው። … አቶ አሰማህኝ አስረስ ለውጡን ራሱ የማይፈልጉ በቀደመው የህውሃት ዘመን ቀጣይነት ምኞተኛ ወይንም ተስፈኛ ወይንም የፍርፋፊ ምኞተኛ ናቸው …  እንደዚህ ዓይነት የህውሃት ካድሬዎች ጠረናቸው በዛ ቢሮ መኖር ጠርጥር እንድንል እንገደዳለን ...  

·       እንዲህ …

የዛሬ ዓመት የአዲግራት፤ የመቀሌ፤ የአክሱም ዩንቨርስቲዎች የኦሽቲዝም ድርማ ምክንያት በማድረግ የአማራ ቴለተቪዥን ሲታታር ነበር። ዕውነቱን ለማግኘት። ስለዚህም ወደ አራት የሚሆኑ ሙሁራንን ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ሚዲያው አቅርቦ ቃለ ምልልስ አደረገ። 

ወግ ደርሶን ሊሂቃኑን አዳምጡ ተባልን። አራቱ አንድ ዓይነት የፋክት ማህደርነትን ሲገልጹ አንዱ ደግሞ የተለዬ ቅላዊ አቋም ነበር ያሰደመጡን። ሌላ አቋም የነበራቸው አቶ አሰማህኝ አስረስ ነበሩ። እኔም ጽፌበት ነበር። 

አራቱ ፈላስማ ዶር ዳኛው አሰፋ፤ ረ/ፕ አበባው አያሌው፤ አቶ ስዩም ተሾመ እና አቶ ውብሸት ሙላት የአላዛሯን ኢትዮጵያ ዕንባ በውስጣቸው ያተሙ ሲሆኑ አቶ አሰማህኝ አስረስ ደግሞ ታላቋ ትግራይን ህልመኝነት በልባቸው ያተሙ ነበሩ። ዛሬ  የአማራ የኮመንኬሽን ቢሮ ዲያሪክተር ሆነው ተመደብው ደግሞ አዬን። የጨለማ ጉዞ ዳግሚያ ቁልቁለት … ደግሚያ ዳጥ እና ማጥ ምጥም... መጥምጥም ... 

እጅግ የማከብራችሁ የአገሬ ልጆች ዛሬ ጹሑፉን ከማንበባችሁ በላይ እንድትጋናዝቡልኝ እምሻው፤ የዛሬው የብአዴን ሹመኛ በቀደመው አቋማቸው ውስጥ ምን ያህል የወያኔ ሃርነት ማንፌስቶ መዝገበ ቃላት መሆናቸውን ብቻ ሳይሆን ከሳቸው ጋር አብረው የተወያዩት ሊሂቃን ዛሬ ምን ላይ ናቸው የሚለውን እንድታገናዝቡልኝ ጭምር ነው? አቶ አሰማህኝ አስረስስ የሚሉትን በንፁህ ህሊና እንዳታገነዛቡት እና እሳቸው የት ሌሎችስ የት የሚለውን መመዘን ትችላላችሁ። ወያኔ ሃርነት ትግራይ ላይ ቢሆንም ሶፍት ዌሮቹ ደግሞ አማራ ላይ እንደተተከሉ ነው።
  
ታስታውሱ ከሆነ የወያኔ ሃርነት ትግራይ የሙት ቀን መባቻ ደወል የነበረው የብሮድ ካስት ልዩ የተደፈርን ስብሰባ ጉዳይ መንስኤው ይህ ነበር - አንድ ለአራት የተባለበት። አቶ ንጉሡ ጥላሁን ጎልተው እንዲወጡ የሆነበት መሰረታዊ አምክንዮም ይኸው ነበር። ቆፍጠን ያለ፤ ኮስተር ያለ፤ ደፋር ሙግት በማድረጋቸው።

በዚህ ቃለ ምልልስ ምድር ቀውጢ ነው የሆነው እንዴት እነሱ በ27 ዓመት ውስጥ እንዲህ ለአንዲት ቀን ተፈቅዶላቸው ቃለ ምልልስ ተደረጋላቸው ተብሎ ነበር ዘረ የወያኔ ሃርነት ማንፌሰቶ ማህበርተኞች ያዙን ልቀቁን ሲሉ የነበሩት፤ ያን ጊዜ የክብር ተክሊል የተዳፋለቸው አቶ አስረስ አሰማህኝ ነበሩ። ዛሬም እሳቸው ተሿሚ፤ ሀቀኞች ደግሞ ከተንታኝነት ያለፈ የተደረገላቸው አንዳችም ነገር የለም። እና የተዘቀቀ ቁንዳላን ሚስጢር በዚህ ታገኙታላችሁ።

በዚህ ሹመት ህመም ብቻ አይደለም የሚሰማኝ ቁስለትም ነው። ቁስለትም ብቻ አይደለም የመገለ ቁስለት ነው። ለእኔ ብአዴን ወደ አዴፓ ተቀዬረ ለማለት ከማያስችሉኝ ምክንያቶች እንዲህ መሰሎቹ ናቸው። 

አሁን ማን ተጽዕኦኖ ያድርግበታል? ዋናው  የህውሃትን ቱቦ  አማራ ክልል የኮምኒኬሽን ዳይሪክትር ሆነው ለመሾም ሥረ መሰረቱ ብአዴን ራሱን ለማጥረት ሌላ መከራ እንዳለበት ያሳያል።። ሌላው ዶር አሚን አማን ደግሞ የጤና ጥበቃ ሚ/ር ሆነው ተመድበዋል፤ ይህ ቧልት እንዲህ እና እንዲያ ይዘናከታል እንደትናቱ ዛሬም ሌላም ሌላም …

ወቅታዊ-በአማራ ቴሌቪዥን ብቻ


በዚህ ቃለ ምልልስ ራሱ አዬሩን ጠረኑን ስታዳምጡት ከቀደመው የህውሃት የመሪነት ዘመን የተሻለ አልነበረም። የሳጅን በረከት ማንፌሰቶ ማህበርተኝነት ነው እኔ የተሰማኝ። አማራን የወገነ ቅንጣቢ አጽናኝ መንፈስ የለውም። በዚህ ውስጥ የባከኑ የአማራ ትወልድ ሳስባው ለማን እና ስለምን እንደሆን ይገርመኛል? ለእነ አቶ አስረስ አሰማህኝ አስረስ ሲባል? ወይንስ ለአቶ ደሴ ጥላሁን?

ሌላው የሚገርመው የሚደነቀው የአማራ እውነተኛ የፖለቲካ ሊሂቃን የሚፈለጉት ውጥረት በመጣ ቁጥር ለማርገብ እንጂ  ለፖለቲካ እውቅና አይፈለጉም። ዶር ዳኛቸው አሰፋም፤ ረ/ፕ/ አባባው አያሌው፤ አቶ ውብሸት ሙለትም ምን ሃላፊነት ሲሰጣቸው  አላዬንም አልሰማንም። የአማራ ብሄርተኝነትን ለማርገብ ግን እነዚህ ሙሁራን ይፈለጋሉ …  

አቶ ንጉሱ ጥላሁን እና ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ያደረጉት ዉይይት 1

አቶ ንጉሱ ጥላሁን እና ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ያደረጉት ዉይይት 2

አሁን ለዚህ ቦታ ሚዲያው ነፃ ይሁን ከተባለ ከፈቀደ እሺ ካለ ሊሆን የሚገባው ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ነው። ጋዜጠኛ ተመስገን ደስ አለኝ የአማራ ተጋድሎ ጥንስስ ነው። „የፈራ ይመለስ“ ከግንጭ አብዮት አንድ ዓመት ቀድሞ በፊት 500 የመይሳው ወጣቶች „የፈራ ይመለስ“ የሚል ቲ ሸርት አሰርተው በራሳቸው ወጪ ጎንደርን ቀውጢ አድርገውት ነበር።


መርሁ ሞዴላቸው ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ነው። በተጨማሪም ረ/ አውሮፕላን አብራሪ ሃይለመድህን አበራ የኮ/ አብዲሳ አጋን ጅግነንት በአውሮፓ ሰማይ ላይ ደገመው። ሁለቱም ወጣቶች ያደረጉት ወደር የሌለው ተጋድሎ ለማግስት አደራ በወርቅ ቀለም የሚጻፍ ታሪክ ነው፤ ካፒቴን ሃይለመድህን አበራ እንዲሆን እኔ በግል እምሻው የጠ/ሚር አብይ አህመድ አውሮፕላን አባራሪ ነው፤ የብአዴን የኮምንኮሽን ዴያሪክተርነት ደግሞ ጋዜጠኛ ተመስገን ደስአለኝ እንዲሆን ነው እሱ ፈቃደኛ ከሆነ። የብአዴን አባል መሆን ግዴታ የለበትም። በሁለቱም ወጣቶች ያለው ታማኝነት ከነተፈጥሮ ያለ ስለሆነ። ለቀጣዩ ትውልድም እውነትን መፍቀድ ምን ያህል ክብር እንደሚያስገኝ የሚያሳይ ይሆናል። 

እዚህ ሲዊዘርላንድ ያለው ጀግና ሃይለመድህን አበራ በሞራሉ፤ በጨዋነቱ፤ በትእግስቱ፤ በማስተዋል ብቃቱ ለአገሩ ባለው ተቆርቋሪነት ከክብርት ዳኝ ወ/ት ብርቱካን ሜዲቅሳ የሚያንስ አይደለም። 

ምንግዜም ስለ አገሩ ያስባል፤ ይቆረቆራል፤ ይጨነቃል ይጠበባል። ስለ ኢትዮጵያ ጉዳይ ጭንቁ ነው። ስለራሱ ህይወት፤ ስለራሱ ኑሮ ቅንጣቢ ጊዜ የለውም። ሙሉ ቀን እና ሌሊት የሚያስበው የኢትዮጵያን ጉዳይ ነው። በመጣው ለውጥም እጅግ ደስተኛ ነው። የጠ/ሚር አብይ አህመድ መንፈስ ተስፋ ለኢትዮጵያ የመሆን አቅም ሊሆን እንደሚችል የሚያምንበት ይመስለኛል።

እንደ አቶ አሰማህኝ አስረስ አይነቶቹ ደግሞ ዘመዳቸው መለበጥ ነው። በራሳቸው ለመቆም ገና ደጋፊ ሌላ ምርኩዝ ያስፍልጋቸዋል። የአዕምሮ ማጽጃ ት/ቤት ራሱ መግባት ይኖርባቸዋል። ሰውኛም ተፈጥሮኛም አይደሉም። ማንፌስቶኛ ለዛውም ለ አፓርታይድ ሥርዓት። ከእንቅልፋቸው እስኪባንኑም ጊዜ ሊሰጣቸው ሲገባ አምጥቶ ከዚህ መሸጎር በውነቱ አገር ውስጥም ውጭም አገር ያለውን የአማራ ህዝብ ንቀት ነው። 

መስዋዕትነቱንም መርገጥ ነው። ያ ሁሉ መስዋዕትነት የተከፈለው የወያኔ ሃርነት ትግራይን ቱቦ ስልጣን ለመሳያዝ አልነበረም። የአማራ ህዝብ የህልውና የማንነት ተጋድሎ መስዋዕትነቱ ጥቅጠቃም ዲስክርሚነሽንም ደርሶበታል። ጊዜ ሊሰጠው የማይገባ ነው። አማራነት ሆዱ ዘመዴዎችን በጽኑ ይጠየፋል። እንዲዚህ ዓይነቶች ነፍሶች ለዬትኛውም ማህበረሰብ አይበጁም፤ ለራሳቸው ከሆኑ ይሞክሩት ... 

ከሁሉ በላይ የአማራ ጋዜጠኞችን ለመምራት ዲግሪ ብቻ ሳይሆን ሰብዕናን፤ ብቁ ሞራልንም ይጠይቃል። ለነገሩ የድርጅት አባል ተሁኖ ሚዲያው ነፃ ነው ለማለትም አይቻልም። በሌላ በኩልም ለተፎከካሪ ፓርቲዎችም አደጋው ሰፊ ነው። የአማራ የመገናኛ ብዙሃን የአማራ ህዝብ ድምጽ ለመሆን ከፖለቲካ ድርጅት ጥብቆ አማራር ወጥቶ ሰዋዊ ምልከታ እንዲኖረው ግድ ይላል።

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ትርምስ ምንጩ እኮ የፖለቲካ ድርጅቶች ባለሚዲያ መሆናቸው ነው፤ ጋዜጠኞችም ሰው ተፈጥሮን አክብሮ ከመናሳት ሰው ሰራሹን ማንፌስቶ አምላኪዎች ስለሆኑም ነው። ለዚህም ነው የእኛ ሊባሉ የማይቻለው። 

እነሱ የእናንተ ነን ሊሉ ይችላሉ እኛ ግን የእኛ አለመሆናቸውን አሳምረን አስረግጠን  እንነግራቸዋለን። አቶ አሰማህኝ አስረስ የዩንቨርስቲ መምህር መሆናቸውን አውቃለሁኝ። ሥማቸው እንደሚነገረኝ ጎንደሬ ናቸው ብዬ አስባለሁኝ። ግን ለሙያው ሥነ ምግብር እጭ ነው መንፈሱ። ለአማራ ህዝብም ታማኝ አለነበሩም፤ አሁንም አይደሉም፤ ለወደፊትም አይሆኑም፤ ቦታውም አይመጥናቸውም።  

·       አቶ ደሴ ጥላሁን አዲሱ የአዴፓ የፖለቲካ ዘርፍ ሃላፊ ከታጠቅ ወይንስ ከሆለታገነተ ወይንስ ከጦላይ?

ሌላው አዲሱ የብአዴን ሹመኛ ደግሞ አቶ ደሴ ጥላሁን ናቸው። እሳቸው ከዬትኛው የጦር አካዳሚ እንደ ወጡ ራሱ ሚዲያው ቢጠይቅልኝ ደስ ይለኛል። ትህትና ብሎ አልፈጠረላቸውም። በጣም የበዛ መታበይ አይቻለሁኝ። ብትፍልግ በዚህ ባትፍለግ በዚያ ባይ ናቸው።

በዚህ መንገድ እማ 27 ዓመት ተኖረበት ከእንግዲህ የፈንግጠው ፖለቲካ የትም አያደርስም። ለሳቸው ለዚህ ሥልጣን ያበቃቸው  የአማራ የህልውና የማንነት ተጋድሎ ነው። ለራሱ ለአቶ ንጉሡ ጥላሁን ለፕሬስ ሴክሬታሪያት ጽ/ቤት ሃላፊነት ሥልጣን ያበቃው እነዛ ሙንዱባን በገፍ ታስረው፤ ደምተው፤ ተደብድበው፤ አካላቸውን አጥተው፤ በተሰባቸውን በትነው ነው ባሰገኙት ለውጥ ነው ዛሬ የሚታዬው የሥልጣን እርከን የተገኘው አይደለም ሌላው …

የሚገርመው የበታች አካለት የዞን የወረዳ የበሰበሱ ከንቶዎቻችን ይቀጥላሉ የሚል መታበይ ነው የሚነግሩን አቶ ደሴ ጥላሁን። እሳቸው ምን አለባቸው? ምንስ ጎደላባቸው? እና ነው። ጥፍሩ የወለቀ፤ የዘር ፍሬውን ያጣ፤ የታፈነ፤ ደም የሸና፤ የተደበደበ፤ ቤተሰቡ የተበተነ፤ ከሥራ የተባረረ፤  የተሰደደ፤ በአደባባይ የተረሸነ የሌላ ቤተሰብ፤ እሳቸው ዘመናይ ናቸው … ማን ነክቷቸው ምንስ ደርሶባቸው …

„ነባሮቹ የበታች አካልት ከሥልጣን አይወርዱም ከሥልጣን መውረድ ወይንም ሰው መለወጥ መፍትሄ አይደለም“ ነው የሚሉት። ሰው መለወጥ መፍትሄ ስለመሆኑ የዓለም ሚደያን ያዳምጡ፤ ኢትዮጵያ በታሪኳ ወደ እንደዚህ ዓይነት የሉላዊ ሚዲያ ቤተኝነት ዘመን ተሸጋግራ አታውቅም።

 የሉላዊው ሚዲያ የፕሬስም የኤሎትረኒክስም ሚዲያ አባልተኛ ሆና አታውቅም በአዎንታዊነት። ምክንያቱ በአንድ ሰው ለውጥ ነው ይህ የሆነው። 27 /50 ዓመታት ሙሉ የተዘፈዘፈ ክምር፤ ደበሎ፤ ጭጋጋማ ጉም ተገፎ ጎህ የቀደደው በአንድ ጠ/ሚር አብይ አህመድ ነው። አይደለም ለእኛ ለአፍሪካ ቀንድ፤ ለመከካለኛው አፍሪካ ባለፈም ለመላ የአፍሪካ የምሥራች ዜናው በአንድ ሰው ቅናዊ አዎንታዊ ብቃት ነው።

ስለሆነም በሌብነት፤ በዝርፊያ፤ በገዳይነት፤ በበደል የበሰበሱ የበታች አማራሮች ተወግደው አዲስ ህዝብ የወደዳቸው መሪዎች መመረጥ ግድ ይሆናል። "ልምድ የላቸውም አዲስ ሆነባቸው" ለሚለው ብአዴን ምን ይሰራል ያስተምራቸው፤ ያስልጥናቸው፤ የክልሉ የብአዴን የሥ/አ/ሥ/ አካላት በቀጠና ተከፋፍሎ ሰንበትን ከእነሱ ጋር ያሳልፍ፤ የልምድ ልውውጥ ፕሮግራም ያዘጋጅ። 

የእነሱ የሥራ ልምድ እኮ ሰው ማስለቀስ ነው ሰው ማስለቀስ፤ ሰው መበደል፤ ሰው ማግለል፤ መስረቅ ነው። ይህ ደግሞ እንደ ሥልጡን ተመክሮ ሊታይም አይገባውም። የበሰበሰ መንፈስ መወገድ ነው ያለበት። ልምዱ ጭካኔን እና ዝርፊያ ስለሆነ ለአሁን ሰውኛ እና ተፈጥሮኛ መንፈስ አገር አብሮ አይሄድም። ጭራቆች ዘመናቸው አልቋል ... 

እኔ ከምን ዐይነት ቤተሰብ ከምን ዓይነት የሥራ መስክ ይሆን እንዲህ አይነት ሰብዕና የሚበቅለው። የሚገርመው እሳቸው ውሳኔ ሰጪ ሆነዋል። ሌላው ጉዳይ ጠ/ሚር አብይ አህመድ እኮ የኦህዴድ የጽ/ቤት ሃላፊ እንጂ ጠ/ሚር አልነበሩም? አዲስ ሆነው በ100 ቀን የሠሩት የ20 ዓመትን ተግባር ነው። እራሱ ሎጅኩ የሚያስኬድ አይደለም። እኔ ጋዜጠኛ አቶ ስሜነህ ባይፈረስ እማከብረው ለዚህ ነው እዛው ላይ ነው የሚያፋጥጠው።  

የሚያሳዘንው ቀደም ባላው በመስከረሙ የብአዴን ጉባኤ የተሰጠው ሥልጣን እዬተጣሰ ነው አሁን ጉባኤተኛው በሌለበት አዳዲስ የተለያዩ ሹመቶች እዬተሰጠ ያለው። የጎደለ ለምሙለት ለሚለው የሚያስኬድ አይደለም። 

አዲስ ተከታታይ ያልተነካካ አቅም ቀድሞ መፍጠር ግድ ይል ነበር። አሁን በባህርዳር፤ በደብረታቦር፤ በማርቆስ በተካሄዱ ስብሰባዎች እስት የላሱ የአማራ ውጣት ሙሁራን አሉ። እነሱን ስለምንድነው ብአዴን አቅርቦ ወደ ስልጣን የማያመጣው? ምን አስፈራው?

ሌላው ያነሱት ሳጅን ደሴ ጥላሁን በቀደመው „አንወቀስ“ ነው የት ነበሩ? የሰላም እና የይቅርታ ኮሚሽን ስለምን የተቋቋመ መሰላቸው? በደሉ ተዘርዝሮ በዳዮች ተናዘው ህዝብን ይቅርታ መጠዬቅ ቢመርም ቀጣዩ ጉዳይ ነው፤ የገለማ ጉዳይ ከኖረም ከደም ጋር ንክኪ ካለም ፍርድ ቤት መገተርም ይኖራል።

የነበሩት በብዙ ክፉ ነገር የከተሙት አይለቁም፤ አስተሳሰባቸው ከተቀየር በዛው ይቀጥላል ነው የሚሉት የብአዴን የፖለቲካ ድርጅቱ አዲሱ ሳጅን ደሴ ጥላሁን። የአስተሳስብ ለውጥ እንደሌለማ ታዬ እኮ ተደመጠ …

የከተሞች መድረክ በወረታ ከተማ ክፍል ሶስት

የከተሞች መድረክ በወረታ ከተማ ክፍል ሁለት


በሌላ በኩል ህሊና ላለው አማራ በወልቃይት በጠገዴ በመተከል በራያ በህውሃት አፓርታይድ ስር ይማቅቃል፤ በዩንቨርስቲዎች ተነጥሎ ይፈናቀላል፤ በወንዝ ውስት ተጥሎ ሞቶ ይገኛል፤ በመተከል ዓለም የፈጠረውን መከራ ይሸከማል፤ ተፈናቅሎ ተሳድዶ ባህርዳር ሲመጣ ደግሞ የሚጠብቁት እንዲህ ዓይነት አመራሮች ናቸው፤ እንደ አቶ አሰማህኝ አስረስ እንደ አቶ ደሴ ጥላሁን አይነት? የት ይደረስ አማራ? የት ይሂድ አማራ? በማንስ ይጽናን? ለችግሩ ማን ቅርብ ይሁን?

ሌላው የዩንቨርስቲ ተማሪዎች ቀኑ ባላፋቸው ቁጥር ለአማራ በሊሂቃን የተከታታይንት ሁኔታ ክፈተቱ እዬሰፋ ይሄዳል ማለት ነው። በዛ ላይ በሥነ - ልቦና ቢሚፈጥረው ጫናም በቀጣይ ትምህርታቸውን ለመቀጠል ተስፋ ቆራጭነት ብቻ ሳይሆን እርግፍ አድርገው ትምህርታቸውን ትተው የቦዘኔ ህይወትም ምርጫቸው ሊሆን ይችላል። ሊታመሙም ይችላሉ። የተቀመረ ነገር አለው። አንድ ሁለት አይደለም …

ለዚህ ነው አማራ በአማራነቱ መደራጀቱ ለድርድር ሊቀርብ የማይጋባ መሆኑን ግድ የሚያደርገው። በዬትኛውም አቅጣጫ የየትኛውም ብሄረሰብ አባል አይሞትም አይፈናቀልም ከዩንቨርስቲ አማራ ብቻ? ይህን የሚሞግት መሪ አማራ ያስፈልገዋል።

 ሦስቱም የተሰዬሙት በዚህ ቃለ ምልልስ ችግሩ ከውስጣቸው የገባ አይደለም። የፈሰሰ ነው … ቅንጣቢ የተቆርቋሪነት የመጸጸት የመጨነቅ መንፈስ የለባቸውም። የእኔ አላሉትም መከራውን። ልጆቹ ፖለቲካውን ውሳኔ ብቻ እንዲቀበሉ ነው መከረኞችን እዬሞገቱ ያዬሁት ሂዳችሁ ሙቱ …. መሪን ማለት ይህ ነውን?! ስለዚህም ብአዴን ከሳጅን በረከት መንፈስ የሚላቀቅበት ዘመን እንደ ትናንቱ ሁሉ ዛሬም ይናፍቀኛል …

ሌላው ግን ሳጅን ደሴ ጥላሁንን ስለምን በአቶ መላኩ ፈንታ ለመለወጥ አይታሰብበትም?


አማራነትን ሳያከብሩ እና ሳያስከብሩ የአማራ መሪ መሆን ይቁም!

የኔዎቹ ኑሩልኝ።

መሸቢያ ጊዜ!

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።