እንደ ሴት እንደ እህትም እንደ እናት እንደ ዜጋም ምን ይሰማችኋል?

እንኳን ደህና መጡልኝ።
 እንደ ሴት እንደ እህትም
እንደ እናት እንደ ዜጋም
ምን ይሰማችኋል?

በዚያ ቀን እግዚአብሔር ፈጣኑን እባብ ሌዋታንን፣
 ጠማማውን እባብ ሌዋታንን በጠንካራ በታላቅም
 በብርቱም ሰይፍ ይቀጠዋል በባህርም ውስጥ
ያለውን ዘንዶ ይገድላል።
ትንቢተ ኢሳያስ ፳፯ ቁጥር ፩
ከሥርጉተ©ሥላሴ
 Sergute©Selassie
 14.01.2019

ውዶቼ እንዴት ናችሁ? ደህና ናችሁ ወይ?

የኢትዮጵያ እናቶች መቼ ይሆን ዎህ የሚሉት ይሆን? መቼ ይሆን የሚያርፉት - ከሰቀቀን? መቼ ይሆን ከሞት በመለስ ባሉ የልጆቻቸው የመኖር ውጤታማ፤ ስኬታማ ትርጎሞች እያዩ እፎይ የሚሉት? ከቶ መቼ ይሆን ያቺ ምስኪን የኢትዮጵያ እናት ከጉንጯ አልፎ ደረቷን በሚያርሰው የህሊና ወራጅ የዕንባ ቋት ተላቃ የልጆቿን ቁም ነገር አይታ ነገን በመልካምነት የምታስበው? መቼ ይሆን የኢትዮጵያ እናቶች ከስጋት የሚወጡት?

የኢትዮጵያ መንግሥት አንድ ሰው በቁም እስር ማስቀመጥ ተስኖት አሁንም የወለጋ እናቶች ያለቅሳሉ። የወ/ሮ ታደሉ እንባ በቃህ እንዳይባል አንድ የዘመን እሾኽ ተፈጥሮበት አሁንም ዋይታ በረከተ። 

አሁን ያን ሁሉ የሬቻ ዘግናኝ መከራ ያዬ፤ ያን ሁሉ የካቴና ዘመን ያሳለፈ፤ ያን ሁሉ መገፋት እና የስላቅ ዘመን በቃህ የተባለ ነፍስ እንደገና በትግሉ ባመጣው ነፃነት መጠቀም ሲገባው በአውሮፕላን ጥቃት ተፈጸመበት መባል ሲሰማ እኔን ሥርጉተን እንደ ሴት፤ እንደ እህት፤ እንደ እናት፤ እንደ ዜጋም ከሬቻው ጭፍጫፋ ባለነስ  ውስጤ እርር ኩምትር ብሏል።
 
ደግሞም ከጅምሩ „ትጥቅ አልፈታም አላለም ተብሎ በተንታኞች ሲተረጎም፤ በመንግሥትም ለጨዋታ ሟሟያ ነው ሲባል መጪው ጊዜ እንዳሳሰብኝ ቃል በቃል በዝርዝር በተከታታይ ጽፌዋለሁኝ። እኔ ያን የጻፍኩበት መሰረታዊ ምክንያት በመታበይ ውስጥ ፍትህ እና ሰላም ዋጋ እንደሌላቸው ስለማውቅ ነው።

አቶ ዳውድ ኢብሳ ኤርትራ በነበሩበት ጊዜ ከዶቼሌ ጋር በነበራቸው ቆይታ ዶር /ፕ/ መራራ ጉዲናም አቶ ካሳሁን ጎፌ ባሉበት ሲወያዩ "የ30 ሺህ እስረኞች ከ እስር መፈታት በቂ አይደለም“ ሲሉ ከሰው ስለመፈጠራቸው ሁሉ ተጠራጥሬ ነበር። አንድ ሰው ቢያንስ 5 ቤተሰስ ቢኖረው 150 ሺህ ነፍሶች መዳናቸው ለሳቸው ከቁጥር የሚገባ አልነበረም።

 በዚህ ስሌት አገር ሲገቡም ብጣቂ ተስፋ አልነበረኝ በሰላም ውስጥ አያቸዋለሁ የሚል። ቃለ ምልልሳቸው፤ ንግግራቸው ሁሉ ውስጡ የጃርት ተፈጥሮ የነበረው ነበር። እና ያሰቡትን ባሳኩት ትልም እንሆ ወለጋ ድውለት እዬሆነላቸው ነው። በዚህ የሬሳ ሰርግ እሳቸው ከሥልጣን መውጣት ነው ህልማቸው። ለእኛ ደግሞ የሀዘን ቀን ነው።

አሁን ይህን ዜና ትናንት አዳምጬ ዝም ያልኩትም አቀናጅቼ መጻፍ አቅምን ከዬት ልውለደው?  እሳቸው የወለዱት ልጅ አይደለም እያለቀ ያለው … አንድ ልጅ በአንድ ቀን አይደርስም? ግፍ ነው በዚህ ዘመን እልቂትን ማሳወጅ፤ የእሳቸው እብሪት ነው ይህን ሁሉ ነገር ያመጣው።

እንዲህ ዓይነት ሰብዕና አይደለም ለትውልድ ለራስም የማይበጅ ነው … ዘመንና ታሪክ የሚገድል … ይህን እሳቸው በማድረጋቸው ኢትዮጵያ አትጠፋም … አትፈርስም፤ እሳቸው ኢትዮጵያ የሚለው ሥም እንዲከስል ነው እዬተጉ ያሉት። ነገ ደግሞ ሌላ ሐውልት ይገነባበታል የጥላቻ … ከገብረ ጉንዳል አቶ ተስፋዬ ግርፍ ምን ሲጠበቅ? እሱ የሚመራው ነው የሚመስለኝ።

·       ድመጥ … ሲሳን …

ቀድመን ስንጽፍ ስንናገር የትም አይደርስም እዬተባለ ዛሬ ይህን ያህል መከራ እና ዕንባ ፈሰሰ … የጉለሌውን መንግሥት ማሸገ አይቻልም ነበርን? የጉለሌውን መንግሥት ከረባት ለብሶ እዬተጎራደደ ህዝብ እንደ ቅጠል እንሆ ይረግፋል? 

ያ መታበይ እንዳሻህ እንደ ፈለግህ ሁን ተብሎ ስለምርጫ ዲስፕሊን እዬተወያዬ፤ ሽምግልና ከ16 ጊዜ በላይ ደጅ እዬተጠና ቅምጥልጥል እዬተደረገ፤ እሱ ባገኘው ጊዜ እና ምቾት ሁለመናውን አደራጅቶ፤ የመንፈስ ዝርፊያ ሲያካሂድ አሁን ዙሮ ዙሮ ያ ህዝብ ተጎዳ። እኔ ይህን ጉዳይ በተብራራ መልኩ ጽፌዋለሁኝ። እኛ እስክንደራጅ ትውር እንዳትሉ ተብሎ ሲፎከር የት ሊደርስ እንደሚችል በጥሞና ገልጬው ነበር።

መስቀል አደባባይ ላይ „የፉክክር ቤት ሳይዛጋ ያድራል" እንደሚባለው ሁሉ ያለ የሌለው አቅም ሁሉ አትንኩት ተብሎ ከሺህ በላይ የአዲስ አበባ ወጣቶች በግፍ የታሠሩበት፤ የ5 ንጹሃን ዜጎቻችን ደም በጠራራ ጸሐይ አዲስ አባባ ላይ ካሳ አልባ፤ ይቅርታ አልባ  ሲረሸኑ፤ የቡራዩ እልቂት እና ግብዕቱ በዛ መልክ ሲከዘን፤ የአዲስ አባባ ህዝብ በደረቅ ወንጀል፤ በሺሻ፤ በጫት ሰብዕና የተሰጣቸው ሚስጢር እኮ ለአቶ ዳውድ ኢብሳ የተንጠራራ የቤተ ጉለሌ ዙፋን ሲባል ነበር። አይደለም ወይ?

በመንግሥት ደረጃ፤ በኦሮምያ ክልል ደረጃም ከልክ በላይ በይፋ በአደባባይ ይህን ግትር መንፈስ ካልኩ ወጣጥሮ ከሚገባው በላይ የተንጠራራ ምልከታ እንዲኖረው የመንፈስ ግብር በገፍ አቅርቦ ሲያበቁ አሁን ደግሞ ሌላ ጨዋታ መጣ …

ለመሆኑ መስከርም ላይ ምን እና ምን?  እንዴት እና እንዴት ነበርን? አድማጭ ነበረውን የእኛ ኡኡታ? ያን ያህል የፌድራሉ የፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነሩ/ የአዲስ አባባ የፖሊስ ኮሚሽነር/ የአዲስ አባባ ምክትል ከንቲባ/ 5 የኦሮሞ ፓርቲዎች፤  የኦሮሞ አክቲቢስቶች የሰጡት የቀጥል የበርታ የድጋፍ መግለጫስ እንኳን ይህን ሌላ ቀውስ በድርብ ቢያመጣ ኢትዮጵያን ወደ ሶርያ መንገድ ቢወስድ ሊፈረድ ነውን?

የፌድራል ጠቅላይ አቃቢ ህግ ቃል አቀባይ/ የኦሮሞ ሚዲያዎች አክቲቢስቶች፤ የኦህዴድ ከፍተኛ አመራር ሳይቀሩ ፌስ ቡክ ላይ የነበራቸው ምልከታ ሁሉ ምን ላይ የቆሙ ነበሩ? ምንን ያመላከቱ ነበር? የጦላይ ስቃይ ቤተኞች ነበሩን? ብናኝ ሰብዕዊነት ነበረውን? 

የዛ ሁሉ ድርብ ንብርብር ዛሬን ያላሰበ፤ የስሜት የፈረስ ግልቢያ በገፍ የተሰጠ በረከት የአቅም ቅለባ ነው ዛሬ የጉለሌው መንግሥት እንዲህ ሰማይ ላይ እንዲንሳፈፈ ያደረገው።

ያን ጊዜ እሰቡት ሌሎች ተፎካካሪ / ተቀናቃኝ የሚባሉ የፖለቲካ ድርጅቶች ሁሉ እኮ ከመጤፍ አልተቆጠሩም ነበር። ራሱ ለኦህዴድ ብቃት የኢትዮጵያ ህዝብ ለሰጠው ወደር የለሽ ክብር እና ልዕልና፤ ብአዴን ለሰጠው ዘመን ከፍሎ ለማይጨርሰው የአደራ መክሊት፤ እንዲሁም አብሶ የአዲስ አበባ ፍቅር የሆነው ህዝብ ልቡን የሸለመበት ዕሴት ተድጦ፤ ተረግጦ፤ በዛ ያልተመጣጠነ፤ በግብታዊነት በታጨቀ፤ ፈጽሞ ያልተሰበበት እንዲሁም ያልተገራ ድጋፍ ያመጣው ጦስ ነው ይህ ሁሉ ፍዳ። ዛሬ የወለጋ እናት በግራ በቀኝ አሳሯን ትበላለች። ፍዳዋን ታያለች። ሌላ የጨለማ ጊዜ ታውጆባታልና።  

አደማ ላይ  ሰላም ስለሆነ ይህን ያክል ፕሮጀክት 442 ሚሊዮን የፈጀ 20 ፕሮጀክት ተመርቆ ተከፈተ ይላል የሰሞኑ ዜናው፤ ይህንን አስቤ ወለጋን ሳስብ ምጥ ነው። በተሳሳተ ሰብዕና፤ በተሳሰተ የመንጠራራት አይዲዮሎጂ አጋጣሚውን ተጠቅሞ ህዝብን ተጠቃሚ ከማድረግ ይልቅ አቶ ዳውድ ኢብሳን አሳብጦ፤ አንጠራርቶ በውጭ ሚዲያ የአብይ መንግሥትን ማሳጣት ወይንም አስግድዶ የኦሮሞን የበላይነት በሁሉም መስክ ማረጋገጥ ወይንም ከህውሃት ጋር ተደራድሮ አንድ የጭካኔ መንግሥት መፍጠር ታሰበ ያ አልተሳካም - ለጊዘው፤ ነገን መተንበይ እንችልም ማጣሪያ ወንፊት እዚህ እሩቅ ሆነን ስለሌን። 

ባልተሳካ ቁጥር ብስጭት ወለድ እርግጫ ይኖራል በቀጣይነት፤ ብስጭት ወለድ እርግጫውን ለመሳቆም መንግሥት የሃይል እርምጃ ለመውሰድ መገደዱ ደግሞ አይቀሬ ነው። ከዛ በፊት ግን ሁሉንም በልክ ቢይዘው ይሻለው ነበር። 

ምን አያመጡም ጉርፍ ነው ጤዛ ነው ያልተገባ በራስ መተማመን የማጣው ዕዳ ነው   የአሁኑ። በርህን ከፍተህ ሆድ ዕቃህን ካስረከብ በሆላ ልክነደነው ቢባል ጋዳ ነው። ቀድሞ ነገር የፖለቲካ ድርጅት፤ አክቲቢስት ሲገባ እኮ ያን ያህል መጠኑን ያለፈ ድርጊት አያስፈልገውም ነበር። 

ሁሉም ነገር በልክ ሲሆን ነው የሚያምረው። አንድ ነገር ላጫውታችሁ ምንም እንዳትልኪልኝ ብዬ አስምዬ አስገዝቼ ለ እህቴ ነገርኳት ዕድሜው ከኖረ ያለው በቂ ስለሆነ አንድ ዝምን ያለ ፖርሳ ላከችልኝ ለፈረንጆች አዲስ ዓመት ይዠው ብወጣ የሲዊዝ ሰው ይስቅበኛል ወይንም እንደ ጉድ ያዬኛል በስኒከር ሊያዝ የሚችል ስላልሆነ እንደ ገናም እኔ የትልቅ ተቋም መሪም ስላልሆነኩኝ። ማዕቱን ነው ያፈሰስኩባት። 

ለማዬት እንኳን አልፈልግም እኔ እንዲህ ዓይነት ፖርሳ፤ የናጠጡ ሱቆች እኔ እራሴ ሂጀም አላውቅም። ስለማያስፈልጉኝ። አካባቢውን ሁኔታውን ማወቅ ይገባል። ጎንደሮች "ልክን ማወቅ ከልክ" ያደርሳል ይላሉ ... አቀባበል ላይ የነበረው ነገር ልቅ ነበር ... ግነት የበዛበት። አሁን ያነን ለመሰብሰብ ቸገረ፤ አዲስ አባባ 5 ልጆቿን ገበረች ወለጋም ቀጠለች ... ቡራዮም ደቀቀች ...  

ግብዕቱ መመርምር ነበረበት። አቅርቦ ከማረቅ በልክ መያዝ ይገባ ነበር። የሆነው ሁሉ ሚዛን አልቦሽ ነበር። ስድ ለቀህ ከገረዘዘ በኋላ ለመመለሰ ያው የ ኢትዮጵያ እናቶች ያልቅሱ እንደለመደባቸው። ለተሰዉ፤ ለተንገላቱ፤ ከሥራ ለተፈናቀሉ ሃላፊነት የሚወስድ፤ ይቅርታ የሚጠይቅ፤ የተጎዱንት የሚያጽናና የለም። የ አዲስ አባባ 5 ነፍሶች ከቶ ማን ቤታቸው ሄዶ አጽናናቸው? የትናንቱ ቀርቶ የዛሬውን?  

ይህ ሁሉ መሆን የሚገባው ግን ቀድሞ ተፎካካሪ/ ተቀናቃኝ/ ተቃዋሚ /  የሚባሉ የፖለቲካ ድርጅቶች እንዴት ሊገቡ እንደሚችሉ የተጠና ስልት ቢኖር ነበር። ልኩን የሚያውቅ፤።

አሁን ስለተፈታተሹ ድርጅት የሚባለው እኮ ጥሩ ገልጸውታል ጠ/ሚር አብይ አህመድ ድርጁ "የቤተሰብ ማህበር" ነው ያሉት።  አንድ የቁብ ድርጅትን የማያክሉ ስብስቦች ዘመን ይዞ ከዘመን ያላባራ ሰቆቃ - ዕንባ መፈናቀል - ሞት - መሳደድ ቀጥሏል።

የሚገረመው ይህ ዕንባ ይህ ሰቆቃ ይህ መፈናቀል ይህ ሞት እትጌ ትግራይን አይመለከተም። ኧረ ምን በወጣት? ይህ እንኳን የሚገባው ሰው ሊሂቅ አይገባውም። የችግሩ የመነሻ ሥር ተከትሎ ሲሄዱ የት እንደያደርሰን ይታወቃል።

ለምን ብሎ ከአንድ ቦታ ቆሞ የሚጠይቅ የለም? ብዙ ጊዜ ሲነገር እሰማለሁኝ በደረግ ጊዜ ትግራይ ተሰውቷል ይባላል ኤርትራስ? ወሎስ? ጎንደርስ? ሐረርስ? ሰው የታጨደባቸው የጦርነት ቀጠናዎች ናቸው።

ትግራይስ? ከባድመ ጦርነት በኋላ ልባም ልጆች ስላሏት ዝንቧን እሽ ያለ የለም። ዛሬ ያለው መዋቅር በሙሉ ከላይ እስከታች እኮ ዕድሉ ስለተሰጠ የተገኘ ነው አመዛኙ መዋቅር የተጋሩ የሆነበት ምክንያት - የመማርም የመሰለጥንም ዕድሉ በገፍ ስለተገኜ።ይህ አይገረብጠውም የአቶ ዳውድ ኢኢበሳ ህሊና።

የዝቅዝቅ ትንፋሽ ርሶት? 

27 ዓመት ተዘቅዝቆ ሲተነፍስ የነበረው የኢትዮጵያ ህዝብ ያለደረሰለት ተቃዋሚ/ ተፎካካሪ/ ተቀናቃኝ የፖለቲካ ድርጅት የመፍትሄ አካል ከመሆን ወያኔ ሃርነት ትግራይ አቅም አግኝቶ ጎልብቶ እንዲወጣ ተግቶ ይሰራል። 

መንፈስ መበተን፤ መንፈስን ማባከን ዛሬም አልቆመም። በዚህ የአቶ ዳውድ ኢብሳን ኢ - ሰብዕዊ ድርጊት ሲወገዝ በዚህ ደግሞ የተደራጀ የሃሳብ ብክነት ይፈነዳል? ህም!ያልገባው ሰው ወያኔ ሃርነት ትግራይ ማለት ምን ማለት እንደሆነ ነው? አልገባውም ኢትዮጵያዊው ሰው። ይህ ሥርዓት ተመልሶ ቢመጣ ምን ሊኮን እንደሆን ያዬው ሰው ሁሉንም? 

ለማን? ለምን? እንዴት? መቼ? የት? እነዚህ በአግባቡ ቁጭ ብሎ በመፈተሽ አቅምን በውል አደራጅቶ ቋሚ ሥርዓት ለመፍጠር ከመትጋት በዚህም በዛም በመናኮር ዛሬም እንደ ትናንቱ ለቅሶ፤ ዋይታ … የአውሮፕላን ድብደባ፤ የጥይት ሩምታ እንዲቀጥል ይተጋል? ?

መንግሥት ተገዶም ቢሆን እንደ እኔ ላለ ስብዕና ግን ዕንቅልፍ የሚያስተኛ አይደለም። ራሴን እራሱ ለመሸከም አልቻልኩም። ረጅም ጊዜ ሆነኝ የራስ መርዝን በሽታ ከተወኝ አሁን በዚህ ዜና ግን ራሴን አዲስ ፋስ ይፍልጠዋል።

·       አንደበትን ለመክፈት የተሳናው የደከመው?

ምራ ቢባል የጉለሌው መንግሥት ሆነ በስውር የሚደግፉት የሚአበረታቱት ተስፈኞች አቅም አላቸውን? ምን አቅም አለ? የክህሎት - የሞራል - የብቃት - የሉላዊነት - የሰብዕዊነት - የአብሮነት - የአቃፊነት -  የአድማጭነት - የትህትና - የአዛኝነት? አቅም ሲኖር ነው ደረትን ነፋ አድርጎ እኔ የተሻለ ማራጭ ሃሳብ አለኝ ማለት የሚቻለው። ቃለ ምልልሱን ግድ ስለሆነ ነው እንጂ እምናዳምጠው ምን ፍሬ ነገር ኑሮት ይደመጣል? ለማድመጥ ራሱ አቅም የለንም። ንጥረ ነገሩ አሰር ስለሆነ።

እንኳንስ ከዶር ለማ መገርሳ ጋር ለማወዳደር ዝቅ ካለው አካል ጋር እንኳን ቢሆን አገር ለሚባለው „ኦሮምያ“ ተብሎ ሲታሰብ በልክ ያልተሰፋ እጀ ጠባብ ወይንም ጥብቆ ነው። ፍርጃ ነው አሁን ኦሮምያን አቶ ዳውድ ኢብሳ ይምሩት ቢባል ለራሱ ለኦሮሞ ልጆች። ኦሮምያ ላይ ደግሞ ሌሎች ማህበረሰቦችም ይኖራሉ። በግርዝዝ ደረቅ ፍልስፍና ህዝብን በ21ኛው ምዕተ ዓመት ለመምራት ጋዳ ነው በረዶ። ንደት ነው የሚሆነው ወይንም ፍርሻ።

መመካት መልካም ባይሆንም ያለው ሰው ባለው ልክ ቢመካ ይሁን ይባላል፤ ለሰፈር እድር እንኳን በማይሆን ልክ የገዘፈ ህልም ይዞ እንዲህ የህዝብን ተስፋ በእልህ በቦንብ ማስደብደብ ሃይማኖቱ ካለ ሃጢያት ከሌለም ወንጀል ነው። ፋይዳው ሲለካ ከምኞቱ ጋር የማይመጣጠን ነው።

እንኳንስ የጉሌለው መንግሥት ሌላው የሞገድ መንግሥት ስንት ሊሂቃንን ያሰለፈው ማለቴ ነው ራሱ አሁን ባለው የአብይ መንግሥት የብቃት ልክ ለመመጠን ባለመቻሉ ራሱን አፍርሶ ፓርቲ አዲስ ለመፍጠር እፍግብ ላይ ነው።

ዘመኑን ብቻ ሳይሆን የአብይን ልሁቅ መንፈስ በቀዬሰው መስመር ልክ የሚሆን ነገር ለመፍጠር ሌት ተቀን ተተግቶ ከተቻለ የሚታይ ነው። የ አብይ መንፈስ ዝቅ ብሎ ቁጭ ብሎ ለመማር የፈቀደ ነው። ይህ በራሱ ዘመን ነው። 

ዛሬ የአብይ ካቢኔ መንፈስ በሰዎች ህሊና ያሰደረውን ተጽዕኖ ጥሶ ለመውጣት የሚመጥን የህሊና አቅም መፍጠር እንግሊዘኛ ቀላልቅሎ በመናገር፤ ወይንም ተራራ የሚያክል ተስፋ በማቀንቀን፤ ወይንም ህዝብ የፈቀደውን አቅጣጫ በመከተል ብቻ የሚሆን አይደለም። የሚመጥን የህሊና ትሁት ለምነት ይጠይቃል ለመደመጥ ራሱ። እያንዳንዱ ሊሂቅ አክቲቢስት በራሱ ላይ የመለወጥ አብዮት እንደገና መወለድን የግድ ይጠይቃል። ይህ መንፈስ ጥበበ - ገብም ነው። ይህ ደግሞ ገብያ ተሂዶ የሚሸመት አይደለም። መክሊት በጀምላ እና በችርቻሮ የገብያ ንግድ ስለማይተዳደር። 

ይህ እንግዲህ የህሊና ጥሪት ለነበራቸው ለእነ አቤቶ "ለ" ነው፤ ይህን ያህል የገዘፈ ቻሌንጅ አፋጧቸው ያለው። ከዚህ አቅም ጋር ሊመጣጠን ለማይችለው የሚዲያም ቤተኛ ላልነበረው እነ አቤቶ "ሐ" ደግሞ ምን ያህል ይሆን ተራራው?

ዛሬ እነሱ ማለቴ እና አቤቶ "ለ"ከተኮፈሱበት ወረድ ብለው ከመላዕክታታዝ ዘርነት ወጣ ብለው ሰው መሆናቸውን በመቀበል ላይ ናቸው፤ ዝቅ ብለው ለመታዬት ጥረት እያደረጉ ነው እዬተፍጨረጨሩ፤ ምክያቱም ፕሮጀክት ይሁን ድርጅት ውጤት አልባ ከሆነ የኪሳራ ድርድር ነው፤ የኪሳራ ድርድር ደግሞ አይደለም ለማግስት ጥሪት ሊሆን ለራሱም ታሪክ ቁመና ቢስ ሆኖ ባክኖ ነው የሚቀረው፤ ተሠራ ፈረሰ። በቃ። በፈረሰ ላይ ታሪክ የለም። ይቆማል። ቀጥ እንደ ሥልክ እንጨት" 

በመፍረስ ውስጥ አዎንታዊ ታሪክ የለምና። መታመን በተራቆተ ቁጥር ውጤቱ ዜሮ እንደሚሆን እንኳን ቀድሞ ስላልታሰበበት ያን የተበተነ፤ የቆሰለ፤ የደማ፤ የባከከነ፤ ያዘነ በታማነው ልክ አልመታመንን እንዲቀበል ለተገደደ ህዝብ ከዜሮ ስትጀመር ምን ያህል መከራ እንደሆን ማሰብ ነው፤ እንኳንስ ተሸብልሎ የኖረው የአቶ ዳውድ የመሪነት ህልም … ስ … ?

በኩዴታ ዕድሉ ቢገኝ በዛ በተኮደኮደ ጥብቆ፤ ጭካኔን ገና ባልጠገበው መንፈስ ውስጥ መከዘን የሚሻ አንድ ስለ ሰባዕዊ ፍጡር ግድ የሚለው ዜጋ የመንፈስ ቤተኛ ለመሆን ምርጫው አይሆንም። ማግዶነት ለሚዘልቅ ለሚያዘልቅ ተስፋ በዕሴቱ ልክ ሲሆን ያስኬዳል በስተቀር ግን በመፍረስ ውስጥ ያለ መኖር እየሰመጠ የሚያሰምጥ ነው የሚሆን፤ በሰብ ቁምና ልክ ያለ መስመጥን መራጭ አይሆንም …

ምክንያቱም የብርሃን ጮራ ወጥቷል መሪነት ምን ማለት እንደሆን። ኦን ላይን ላይ ዛሬ ሰው ቁጭ ብሎ ብዙ ነገር ይማራል። ርህርህናው፤ ቸርነቱ፤ እርጋታው፤ ስክነቱ፤ ሰብዕዊነቱ፤ ይቅር ባይነቱ፤ ሁለንትናዊነቱ፤ አቅራቢነቱ፤ አቃፊነቱ፤ ጥልቅነቱ፤ ታሪክ አዋቂነቱ እና ለዜግነት የተሰጠው ዕውቅና አቅም፤ ሃላፊነት እና ተጠያቂነትን የማዋደድ ዝንባሌው፤ አጥፈተናል የማለቱ የጀግንነት ድፈረት፤ ድንገቴ ፈተናዎችን በመፍታት እና መልክ ለማስያዝ ያለው የማስተዋል ጥልቅነቱ እያንዳንዱን የፖለቲካ ድርጅት ፈተና ውስጥ ስለጣለው የግርግር ፖለቲካውን እርግፍ አድርጎ ትቶ በስሎ ለመታዬት አዋጭ መንገዱን እያሰላ ነው የሚገኘው። ንግግሩን ሳይቀር ለመግራት እዬታገለ ነው ከማንህሎኝነት ወጥቶ። ስለምን አዬሩ ራሱ ስለሚያፈናጥረው። 

አንዳንዱ ኦርጅናሉን ሳይሆን ግልባጩን ለመሆን ሲዳዳው ሁሉ እናስተውላለን። ምን ለማለት ነው ይሄ አቅም ያለው፤ የነበረው ያን ያህል እርቀት ተጉዞ ወቅትን ለማድመጥ እዬተጋ ነው አዋጪ ስለሆነ … ተው እያልን ነበር በቁም ቤት የፈረሰው፤ ቆሞ የሚጠበቅ ስታግነናት የሆነ አምክንዮ ዓለም አስተናግዳ አታውቅም፤ ትእግስት ሲያልቅ ፍቅር የሰደዳል እያልን ስንናገር አድማጭ አልነበረም ... "መፈረስ ያለበትም" ስንል አድማጭም አልነበረም። አሁን ባልነው ልክ እዬሆነ እያዬን ነው። 

መደማመጥ ቢኖር አቅም አይባክንም ነበር። ዛሬ ቅኖች ባለመነው ልክ ከ ገጠመው ችግር ጋር ካፈጠጠው የ50 ዓመት ፈተና ጋር ኢትዮጵያ ብቁ አራት ዓይናማ ሙሴ አግኝታለች። ችግር ቢኖር እንኳን አቅም ያለው ችግሩን ለመረዳት፤ ለማስጠናት፤ መፍትሄ ለማምንጨት፤ መፍትሄውን ለማደረጀት፤ መፍትሄውን ወደ ስኬት ለማሸጋገር። 

ማህበራዊ ንቃተ ህሊናውን የሚመጥን እንዲያውም ያለፈ መሪ ኢትዮጵያ ስላገኘች ያነን ተቀናቅኖ ይሁን ተፎካክሮ ለመውጣት ብዙ መሥራት ግድ ይላል … ቁጭ ብሎ ሃሳብ ማፍለቅ። ቁጭ ብሎ መሥራት። ድርጅት ቂጥ ይፍለጋል። አብዝቶ መቀመጥ። ስለቹ አለመሆን። አቋራጭ መንገድን አለመሻት። ፈተናን መድፈር። ተጠያቂነትን መድፈር። ትችትን መድፈር።  

የ አሁኖቹ የለውጥ ፈርጦች ወጣት ናቸው። ይህም ሌላ ቻሌንጅ ለ66ቶቹ ነው። በፈርጦቹ የለውጥ ሐዋርያት እና በመሪዎች መሃከል እና በትውልዱ ክፍተት የለም። 

ከአዲሱ ታዳጊ ወጣት ጋር የግንዝቤ ወይንም የዕድሜ ልዩነት ሳይሆን በበዛ መልኩ መቀራረብ አለ። ከዚህም በላይ መሬት ላይ የነበሩ ናቸው ማለት በሁኔታዎች ውስጥ ያሉ የነበሩ። ይህም ሌላው ቻሌንጅ ነው ከውጭ ለገባው የፖለቲካ ድርጀት፤ በድርጅታዊ ሥራ መቆዬቱም በህዝብ አገልግሎት ላይ ተሳትፎ መኖሮም ሌላው ቻሌንጅ ነው።

 ስለዚህም የአብይንም መንግሥት ተቀናቅኖ ለማሸነፍ ጋዳ ነው። ራሱ ገንጠል ብሎ የሚታዬው ህውሃት መሪው ዶር ደብረጽዮን ገ/ ሚኬኤል መስሎ አቅም ያለው ሆነው ለመታዬት እየዳከሩ ነው። 

ቅጂ ነገሮችን እያሰዩን ነው በህዝብ ማህል ዘና ብሎ መሄድ፤ የቤተክርስትያን ዶግሞ ተጥሶ ተክሊል መድፋት፤ ህዝብን ሲያነጋግሩ ፊት ለፊት ላብቶፕ ማድረግ፤ ትንሽ ቆይተው ደግሞ ስላይዱንም ያክላሉ ብለን እናስባለን፤ ፎቶ አብሮ መነሳት ይህ ሁሉ ግን የሃሳብ ልቅና ከሌለ ከንቱ ድካም ነው። ጥሪት ያስለፍጋል። 

አሁን አንድ ዜና ሳደመጥ የሱዳንና የኤርትራ የ እስልምና ዕምነት ተካታዮች ጉብኝት እዛው ትግራይ ላይ ነበር ... የሱዳን እና የኤርትራ መሪዎች ጅማ ላይ እንደተገኙት የዛ ግልባጭ ነው ... ያው የመቀሌው መሪ መንግሥት ነን ዓይነት ነው። በልጅነቴ አንድ መጸሐፍ ላይ ያነብበኩት አንዲት ጦጣ ታደርገው የነበረውን ነው ግልባጭ እያዬሁኝ ያለሁኝ። የቁንጣን አይነት ፉክክር ... ግልብ የሆነ ነገር ... 

ሙሉ መሰናዶ ኢትዮጵያን ከውስጥ ከመቀበል ጋር መዋደድ አለበት። ከሴራ ጠንሳሽነት እስከ አስፈጻሚነት ያለውን ትብትብ መፍታት ነበር የሚበጀው። ከሁሉ በላይ ግጭትን እያደራጁ ህዝብ ማጫረስ የሰማይ ቁጣ የመጣ ዕለት ማስቆሚያ የለውም።

አሁን ያለውን የብቃት ውስጠት ለማንበብ ራሱ አቅም ይጠይቃል። ራሱ የጠ/ሚር የቢሮ አደረጃጀት ተቀይሯል። ሲያዩት ፍንትው ያለ ነው አውሮፓ ነው የሚመስለው። ጽዳቱ አዬሩ ጠረኑ አደረጃጀቱ ራሱ ኑልኝ ምጡብኝ የሚል ነው።

በሌላ በኩል ሰሞናቱን ስንቃኝ በዚህ ሁሉ ቀውስ ውስጥ ካቢኔው ተሰብስቦ ነበር፤ የመከላከያ ጉባኤው ተሰብስቦ ነበር፤ የኢኮኖሚ ሊሂቃኑ ተሰብስበው ነበር፤ ዲፕሎማቶችን ጋር ተወያይተዋል፡፤ በተቀናጀ ሁኔታ ገና እና ሰብዕዊነት ደግሞ ለማጣፈጫ ነበር / የ እመት ዘውዲቱ መሸሻ ድርጅት ጉብኝት/ስለዚህም ራሱ የተግባሩ ቅደም ተከተል የሚገርም ነው። ድርጁ ህሊና በጥልቀት ማሰተዋል ይቻላል በዚህ ውስጥ። 

 የሚገርመው ግን እንደ እኔ እውነትን ለወገኑ ብቻ ይሆናል ይህ የሚታዬው። እውነትን ለወገኑ ችግሮቹ ራሳቸው የነበሩ ብቻ ሳይሆኑ ቆስቋሽም ያላቸው መሆናቸውን ልብ ይሉታል፤ ምክንያታዊ የሆኑ ሠው ሠራሽም ችግሮች በርካታ መሆናቸውን ከልብ ለሚቀበሉት እዬሆነ ያለውን፤ እዬገጠመ ያለውን ካለው የመምራት አቅምና ብቃት አንጻር ሌሎች ቢሆኑስ ምን ይበጀን ነበር ብለው ይመዝኑታል?

የአንዳቸውም የተፎካካሪ/ የተቀናቃኝ፤ የተቃዋሚ ድርጅት መሪዎች ሆኑ ቲማቸው ይህን ፈተና የመሻገር አቅሙም ብቃቱም የላቸውም። አንድ አክቲቢስት ተናገረኝ ብለው አባላቸውን ሰብስበው የሚቆዝሙ መሆናቸውን ስለምናውቅ። የፖለቲካ ድርጅት ዲስፕሊን ስሌለ ሲንጠባጠቡ እናዳምጥ ነበር ... 

·       ውና።

ይህን ምስቅልቅል ለመግራት የህሊና ተግባር በአዋጅ በምሽት ኮንሰርት በግርግር ፖለቲካ አለመደፈሩን ከልብ ስለምንቀበል ቅኖች፤  በእርጋታ እና በማስተዋል ሂደቱን እንከተላለን እያለቀስንም ቢሆን የድምጽ አልባ እናቶች ጉዳይ ጉዳያችን ነውና።

የሆነ ሆኖ የወለጋን አውሮፕላን ድብደባ ዜናውን ስስማ ዕንባዬ እየፈሰሰ ነው ያዳምጥኩት። በዚህ ዘረፋ፤ በዚህ እገታ፤ በዚህ ደግሞ ሞት ለቅሶ ዋይታ … በዚህ ስሌት ሲኬድ የሰኔ 16 የግድያ ፕሮግራም አቅጣጫው አመላካች ነው የሚሆነው….  

·       ሰላም ባለበት አዳማ እንዲህ ጸሐይ እንዲህ ወጥቷል፤
ዋልታ ቲቪ 6/05/2011 . የጠዋት 1230 ዜና | Walta TV News 6:30 AM 1/14/2019
·       በተቀናጀ በተባበረ የፖለቲካ ሴራ ጨለማ የታወጀበት ወለጋ ደግሞ፤
በወለጋ መከላከያ የኦነግ ታጣቂዎች ላይ የአየር ጥቃት አደረገ
January 14, 2019

v   መቼ ይሆን ከዚህ መከራ መከረኞቹ የኢትዮጵያ እናቶች የሚወጡት?

ኢትዮጵያዊነት ከመፈጠሩ በፊት ፈተናን አሸንፎ የተፈጠረ ሚስጢር!


                                  የኔዎቹ ኑሩልኝ።

                                  መሸቢያ ጊዜ። 

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።