ፕ/አሻግሬ ይግለጡ የኢትዮጵያን ህዝብ ይቅርታ ጠዬቁ፤ የመደመር ፍልስፍናንም ፈቀዱት!


እንኳን ደህና መጡልኝ።
ቀን የሰጠው ዕውነት!
„ጥበብን ውቅ ዘንድ፤
 በምድር የሚሆነውንም
ድካም አይ ዘንድ ልቤን ሰጠሁ።“
መጽሐፈ መክብብ ፰ ቁጥር ፲፮

ከሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
24.01.2019
የቅኔ ዘጉባኤ።

·       እፍታ። 

ጤና ይስጥልኝ የኔዎቹ እንዴት ናችሁ? ደህና ናችሁ ወይ? የአይዋ በረከት ጉዳይ እንዴት ያዛችሁ? ስልኩ የጉድ ነበር አሉ በዬአቅጣጫው አገር ቤትም ውጭ አገርም የእንኳን ደስ አለን። ደስታ ቀላል? ፍትህ በእግሯ ቁማ የሄደችበት ዘመን። ለዚህ ነበር “ኢትዮጵያዊነት ሱሴ ነውን” ለመቅጨት የወረፋ ሩጫ በነበረበት ወቅት አደብ ግዙ እያልን ስንመክር የነበረው። ጎንደሮች ይህን “የረጋ ወተት ቅቤ ይወጣዋል” ይሉታል። ይኸው ተጋድሏችን ፍሬ አፈራ እንዲህ ... 

አሁንም ቢሆን በላይ በላይ የቤት ሥራውን ከመደርደር ልባሞች ስለያዙት አደብ እንላለን ከጭምቷ ሲዊዘርላንድ፤ ይህንም ጎንደሮች “የፊት የፊቱን ይላል ጓያ ነቃይ” ይሉታል። ግን ጓያን ታወቁታላችሁን? ጎንደር ደንቢያ አካባቢ የሚበቅል የጥራጥሬ ዘር ዓይነት ነው፤ እንደ ሽንብራ ይቃጣዋል … የጓያ ሰባራም የሚባል አለ፤ ሽፋኑ ለጤና አይመረጠም፤ ብቻ ዘሩ እንደ አንዱ ነው ልክ የቋንቋ ዘርፍ የሴም - የካም - የኩሽ እንደሚባለው ዓይነት …

·       ጠብታ።

ለ4 ሳምንታት የጋዜጠኛ ሲሳይ አጌና ቃለ ምልልስ ሲያሸን ባጅቶ ዛሬ አጠናቋል። የአውነት ነው ማሸት የሚለውን ነገር የተጠቀምኩት። ልቤ ተንጠልጥሎ ነው የሰነበው። ክፍል አንድ አነሰች እንደገና ሳምንት ጠበቅን፤ ክፍል ሁለተም እንዲሁ ... የናፍቁት ነገር ቀርቦ ሲርቅ የደረሰበት ያውቀዋል ... 

ብቻ ድምጣቸውን ስላሰማን እጅግ አድርጌ በአክብሮት አመሰግነዋለሁኝ። ዕድለኛም ነው እሱ እራሱ እንዲህ ከዘመን ዕንቁ ጋር ቁጭ ብሎ መወያዬቱ። በእልህ የቀረበለትን ጮማ ዕድል አልሻም ብሎ ቢሆን ኑሮ እሱም እንደሌሎች ፈርጥ ጋዜጠኞች ባክኖ ይቀር ነበር። ቀንን ዝቅ ብሎ ወጀቡን ማሳለፍ በዚህ መልኩ ሲሆን ይመስጣል። ብልህ ነው።

ብቻ ይህ 4 ሳምንት መቆዬት መጠበቅ፤ እኔ በደርግ ዘመን ላድግኩት ኢሠፓ ፓርቴዬ እንደ ዓይኑ ብሌን ተንከባክቦ ላሳደገኝ ሥርጉተ ሥላሴ ግን ረጅም ነበር 4ሳምንት መጠበቅ? ረዘመብኝ። ፓርቲዬን ኢሠፓን እወደዋለሁኝ። ደግሞም ድንግላዬን አላቆሽሽኩም። የዬትኛውም የፖለቲካ ድርጅት አባል ለመሆን አልፈቀድኩም። አይታሰብም። እራሱን ሳያድን በታሪክ ክስም ማለቱ የተገባ ቢሆንም ግን ወጣትነታችን አልፍሶታል። 

እንደገና አግግሞ ቢነሳ ሁልጊዜም እንደምለው ባዕዴ ነው የሚሆነው - ለእኔ መንፈስ። ተክፍቼበታለሁኝ። ጥበቃ ሳያደርግልን ሜዳ ላይ እንደበተነን ነው ሽው ያለው። የዛሬዎቹ 7 ሚሊዮን የብአዴን አባላት፤ የሚደያ ሰዎች፤ የመንግሥት ባለስልጣነት ሁሉም በተደሞ አብይ አምላካችን ሊሉት ይገባል። ከስንት መከራ ከስንት ወጀብ ከስንት በረዷማ ረግረግ እንዳወጣቸው ከልባቸው ሆነው ሊያዳምጡት ይገባል። ብዙ መከራ ነው የታለፈው ... 

አይደለም 8 ሰ ዓት 24 ሰ ዓት ቢሳራም ለአብይ ሌጋሲ ከስንት ጉድ መዘዘ መሰስ አድርጎ ያወጣቸው ጥበብ ስለሆነ እግዚአብሄርን ሊያመስግኑት ይገባል። እራሱ ኢህአዴግ ውስጥ ለውጡን ያመጡት እያሉ አሁንም ይህ ድፍርስ ታሪክ ካልተደገመ ለውጥ የማይመስላቸው እንዳሉም ልብ ሊሉት ይገባል። 

ለነገሩ "የያዙት ወርቅ ከመዳብ ቁጥር" ሆኖ አንዱ በሞገደኛው ዳውድ ኢብሳ ሌላው  በአፍራሹ ህውሃት ሥር ሆኖ እያመሰ፤ እዬተማሰ ይገኛል። ፓርቲ ሲፈርስ ህይወት መፍረስ ስለመሆኑ ከደርግ ዘመን ሊማሩ ስላልቻሉ፤ የእነሱ ደጋፊዎች ከአክተር ዘመነኛ የሊቃናቱ ትውና ጋር አብረው ዘጭ ዘጭ ሲሉ እኔ ከዚህ ሆኜ በጅልነታቸው እስቃለሁኝ የምር። ስንት የመከራ ዓይነት እንዴት እንዳስተናገድን ማን በነገራቸው እላለሁም፤ እስከ ቤተሰቤ ድረስ።

እሳቱ ነዶ ከጭንቅላቴ ላይ አመድ ነው የሆነው። ገራሚው ነገር ተሰድጅሜ ያሳለፍኩት ፍዳ ተዘርዝሮ አያልቅም። በዬጓዳው እንቅፋት ነው። በዚህ ዝብርቅ የፖለቲካ ድርጅት በሚባል ውሎ ጉዞ በሌለው ጸንቶ በማይቆም፤ ሲፈርስ እና ሲናድ ውሎ ቢያደረው ፍርክርክ ድርጅት አባል ካልተሆነ ፍዳ ነው። 

 … አሁን ይልቅ ፕ/ አሻግሬ ይግለጡ ተናግረውታል ምን አቅም ያለው ድርጅት ኑሮ ሲሉ ወዘፍ አድርገው ቅኔዋን ጣል አድርገውታል … እኔም እምለው ያንኑ ነው … መሆን የነበረበት በግል መጣር ነው፤ ያ ደግሞ ድርጅት ነኝ ከሚለው ያለነሰ ተግባር ተከውኖበታል። ሰንሰለቱም አሜኬላውም ቢያልም ሳንረታ ዛሬን አግኝተናል። ቀሪው ጊዜም ትርፍ ነው። ተስፋ ከተገኜ ለትወልዱ ብክንት ስክነት በቂ ነው። 

የሆነ ሆኖ ረጅሙን ቃለ ምልልስ እዬደገምኩ እዬሰለስኩኝ አዳመጥኩኝ። እማዝነው እሚቆረጣጥመኝ ይህን መሰል አቅም እንዲያ እንደዋዛ ባክኖ በኖ ተበትኖ መቅረቱ ነበር። ይህ የዛሬው የአብይ መንፈስ ከዚህ ሁሉ የሚታደግን በመሆኑ መጋቢት 24 ቀን ባገኛት ቀለበት አስርላት ነበር። ምን ቀለበት ብቻ ዠርከክ ያለ ሃብልም አስርለት ነበር። የምርም የእውነትም።

አንድ ሥርዓት ሲፍር ብዙ ነገር ነው የሚፈርሰው፤ የሚበተነው ቁምነገር የሆነው ነገር እራሱ ብቄተ ቢስ ነው የሚሆነው። በቅርቡ የፎለቄዋ የአርቲስት ወይኒቱ አንዱር የህይወት አንዱ ምስክር ነው። በዚህ ሳምንትም ሌላ መከራ ዜና ታድመንበታል። 


ሥምን መላዕክ ያወጣዋል እንዲሉ የፕ/ ምንዳርአለው ዘውዴ ጉዳይ ሌላው የግፍ የፍዳ ድርስናችን ነው። እኒህን የመሰሉ የፍልስፍና ፈላስፋ፤ እና የአንትሮፖሎጂስት ሳይንቲሰት በዛ ሁኔታ? ደግነቱ ስሙን ሊነግሩን ያልቻሉት ሰው ሳጅን በረከት ይሆናሉ ብዬ ነው እማስበው፤ ጊዜ ገቢረ ለእግዚአብሔር ሆነና እንዲህ እና እንዲያ ሆነ ምስክሩን እዮር ገለጠ።



ሳጅን በረከት ስምዖን ኮንፕሊክሳም ስለሆኑ አቅም ያላቸውን ንዑዳን ማሰዳድ የተፈጠሩበት ነው። የሴራም ውቅያንስ መሆናቸው በተጋጋሚ ጥፌዋለሁ። ትግላቸው የፈረሰች ኢትዮጵያን ማዬት ነው። እንዳትሞትም እንዳትድንም አድርጎ መለመላዋን በሁለመና ማስቀረት የተፈጠሩበት ነው። በኢትዮጵያ ታላቅነት - ሚስጢርነት - ረቂቅነት - ሁለመናነት ድብን ነው ብለው ነው የሚቀኑት።

ይህን አዲስ ለውጥ ማዬትም፤ ማድመጥም፤ ማስተዋልም የሚገባን በግርፉ፤ በለብለብ፤ በግርድፉ ሳይሆን ውስጡን በማጥናት መሆን ይገባዋል። ጠ/ሚር አብይ አህመድን "አንተ እና አንቺ" እያሉ የሚያብጠለጥሉ ወገኖች በጥልቀት ይህን አመክንዮ ሊያስተውሉት ይገባል። የብቃቱን ትርፉን ትቶ የመንፈስ መፈናቀል ትርፉን እናስበው ብንል ብጹዕ አባታችን የሰሜን ጎንደር አገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ አቡነ የሖንስ እንዳሉት የሆነ ሁሉ ነገር "ከትርጉም ባለይ ነው።" በሌላው መስክ ደግሞ ሁሉ ነገር የቱማታ ማህበርተኞችም እንዲሁ አደብ ይግዙ እናላለን በትህትና።

የአንድ ሥርዓት መፍረስ ሰው ነው የሚፈርስበት። ልድገመው የአንድ ሥርዓት መፍረስ ሰው ነው የሚፈርስበት። ደርግ የመፍንቀለ መንግሥቱን ሁኔታ በጽሞና አይቶ ከመፍንቅለ መንግሥቱ አድራጊዎች ጋር ቁጭ ብሎ ተወያይቶ ቢሆን ኖሮ በሞት ላይ መኖር እንዲህ አና ባለለም ነበር። አለን የምንለው ዝም ብለን ለጨዋታ ሟሟያ ብቻ ነው። ሰውን ሰው ጠልቶት፤ ሰው ተፈጥሮውን ጠልቶት መኖር አይደለም። አትምጡብን? ለእኛ ትውልድ ያሳፍራል ያሸማቃል? ውጡልንም መንፈስን ይግጣል - በውርዴት፡፤ 

ኢትዮጵያም አልቃ ዘነዘናዋን በቸርነቱ የቃልኪዳን አገር ስለሆነች ነው ያለችው። ከዚህ በላይ የትውልዱ ብክነትስ- መስፈሪያ፤ መለኪያስ፤ መመተሪያስ አለውን? የመዋለ መንፈሱ ብክነትስ? የሥነ- ልቦና ጉዳቱስ? የልቅሶው ተደሞስ?

·       መነሻ።

ESAT Yesamintu Engeda Dr Asagre Yegletu January 2019 part 1


ESAT Yesamintu Engda Dr Ashagre Yigletu Part II Wed 09 Jan 2019

ESAT Yesamintu Engeda Dr Ashagre Yegletu part 3 January 16 2019 HD

ESAT Yesamintu Engeda Dr Ashagre Yegletu part 4 January 23 2019

·       ዕውነት ቀን ሲወጣለት።

ዕውነት ቀን ይወጣለታል - ምን አሳሩ ቢረዝም፤ ምን የፍዳ ጉዞው ቢወይብም፤ ምን የፍዳው የብክነት መንገዱ ቢጠንዝልም። በዚህ ቃለ ምልልስ ብዙ የነጠሩ ዕውነቶች ነበሩበት። 

ብልጠት እና ብልህነት በፖለቲካ አስተሳስብ ጥበብ ጉዳቱና ጥቅሙ፤ ለትወልድ ዕዳ ማስረከብ እና ጦሱ? ይህን እኔ በ2008 የአማራ ተጋድሎ ላይ በስፋት ጽፌበታለሁኝ። ፕ/ አሻግሬ ይግለጡ "የማጭበርበር ፖለቲካ መባቸነቱን" አበክረው ገልጸውታል። 

የትውልዱ ብክነት እና ብክነቱን ለማስቆም ሊደረጉ ስለሚጋበቸው ጥበባዊ አምክንዮዊ ጉዞዎች? መሪ መሆን ምን ማለት ነው? በመሪነት ውስጥ ያለው ፈተና እና ስኬቱ፤ ከውድቀቱ ለመማር መፍቀድን አስፈላጊነት፤ የመሪ የማድመጥ አቅም እና ትርፋዊ ዕሴቱ፤ የሄርድስ መለስ ትወልድንን የመሰንጠቅ ናዚያዊ ፍለስፍና፤ የመሪዎች አልህኝነት እና የመሪነት ጥበባዊነት መፋደስ ያላቸውን ተቃርኖ እና ውደቀቱን፤ በዬዘመኑ የሚፈጠሩ ቃላት እና የሚኖራቸው ትውልዳዊ ጫና እና ተጽዕኖ፤ ሂደት እንደ ክስቱ-  ሂደትና  ትሩፋቱ እና ሂደትና ሽልማቱ፤ ስክነት እና ጥድፊያ ከአገራዊ ክብር እና ልዕልና ጋር ያለውን ዝምድና አርምሞ፤ የውጭ የዕዳ ጫና እና የእጅ አዙር ቅኝነት ጦሱ፤ ዕወቅት እና ዕድምታው፤ የአቅም አያያዝ ጥበብ እና ትሩፋትነቱ፤ የመሪዎች ከቂም - ከቁርሾ - ከበቀል ተፋቶ የምህረት ሰውነታቸውን እንዴት ማበልጸግ እንደሚገባቸው፤ ስለ አንድ ጠንካራ የፖለቲካ ድርጅት መኖር አለመኖር የተስፋ አድርሻ እጅግ ብዙ ወሳኝ የሆኑ ጉዳዮች ተነስተዋል።

በዚህ ውስጥ ዕውነት ጎልታ፤ ጎልብታ፤ ደምቃ እና ተውባ ወጥታለች። ይህ ዕውነት ለትውልድ ግንባታ ማዋል ከተቻለ ትልቅ የማስተማሪያ ሰነድ ነው። ትምህርተ ዜግነት ላይ እነዚህ መሰል ቁምነገሮች ለማውጫነት ይጠቅማሉ። እራሱ ቃለ ምልልሱ ሰነድ ነው። 

ብልጠት እና ብልህነትን በጥቂቱ …

በዚህ ቃለ ምልልስ ብልህነት እና ብልጥነት ሲናገሩ ጋዜጠኛ ሲሳይ አጌና ግር ያለው ነገር ነበር።  ሮም ላይ በነበረው የሰላም ድርድር አወያዩ ስለ ኢትዮጵያ የቡና ሰብል ጣምዕዊነት ሲያወሱ በጣልቃ ሄሮድስ መለስ ዜናው ገብተው እኛነትን ያሳዩበት መንገድ ነበር ብልጥኑቱ። አንድ ትግራይነትን ነጥዬ እገነጥላለሁ የሚል ቡድን ኢትዮጵያን ጠልቶ ስለሆነ በሃብታቷ ተመስጦ አለኝ ብሎ በአቀሯጭ እንደ ደራሽ ፈረሰኛ የውሃ ሙላት ሲገባ ያ ሰፊ የሆነ አመክንዮ ነበረው። በዛ ብቻም አላበቃም።

የወቅቱን የአወያዩን ኢትዮጵያን የማክበር ብቻ ሳይሆን ህወሃት ፖለቲካ ፍልስፋና ያን ጊዜ /ማሌሊት/ ነው የነበረው እጀ ጠበባብ መሆኑ ብሄራዊ ሃላፊነት የመወጣት አቅሙ አፍ ያለው መቃብር መሆኑ በአደባባይ ስለሳጣ - ስለተሰጣም  ይህን አስተሳብ ለመገልበጥ ሰፊ ቀጠሮ እንዲኖር በማድረግ ኢትዮጵያን እንወክለላን የሚል "ኢህአዴግ" የሚል ጊዜያዊ በሄሮድስ መለስ እጅ የተበጀ  ቅርፊት የተደራጀበት መንገድ የቡናው ፖለቲካ ያመጣው በብልጠንት የተከሸነ የፖለቲካ በለቀ ነበር። ለምዕራቡ ዓለም ህሊና ደጋፊነት ያበቃቸው አንዱ ዘርፍም ይኽ ነው። 27 ዓመትም ያስገዛቸው በዚህ የቡና ፖለቲካ የብልጠት እርሾነት ነበር። በሌሉበት ኢትዮጵያዊነት ውስጥ አስመስሎ ተለብጦ የተኖረበት የገመናው ቁንጮ። እዬጠሏት እያፈረሷት ግን ሲገዘግዟት የኖሩበት ምህንድስና ነው "የብልጠት" ፖለቲካ ያሉት። 

በስፋት የኢትዮጵያ ሚዲያዎች የተፎካካሪ/ የተቃዋሚ/ የተቀናቃኝ ከፍተኛ መሪዎች ሳይቀር ኢህአዴግን እንደ መሪ የፖለቲካ ድርጅት አድርገው ሲመለከቱት ተው ስንል የነበረውም በዚህ ምክንያት ነው። ከህወሃት የወጡት የተጋሩ ሊሂቃን ኢህአዴግ ላይ የሙጥኝ የሚሉትም ይህ የለበጣ ጉዞ ሲጋለጥ ህወሃት ተነጥሎ ተጠያቂ እንዳይሆን ነበር ሽፋን ሲሰጡ የኖሩት።

እማዝነው ያን የጨለማ ዘመን ለመቃወም ሰላማዊ ሰልፍ ላይ ሁሉ ይህ የሄሮድስ መለስ ዜናዊ የብልጠት ፖለቲካ ዕውቅና ተሰጥቶት “የኢህዴግ መንግሥት” እዬተባለ ሲወገዝ ነበር። የፍልስፍና ችግር ነበረበት ራሱ የተጋድሎው መነሻም ሆነ የመዳረሻ ራዕዩ ...። ችግርን መፍትሄ ለመስጠት ከችግሩ የፍልስፍና አፈታት መነሳት ግድ ይል ነበር። ሰሚም አድማጭም አልነበረም። የሆነ ሆኖ የሄሮድስ መለስ የዛች ቅጽበት የቡናችን ቤተኝነት የብልጠት ፓለቲካ 27 ዓመት ሙሉ በአደናግሬ ጉዞ ሲያደናብር ባጀ። ሌላም በዚህ ዘመን አንድ ነገር ማስታወስ እሻለሁኝ።

የብልጠት ፖለቲካ ሌላ የቅርብ ጊዜ ለማገናዘቢያ ማቅረብ እሻለሁኝ። የአማራ ይህልውና ተጋድሎ “የነፃነት ሃይሉ መባሉ” እና አገራዊ ንቅናቄው ምስረታ፤ የአንድ አማራ ድርጅት መፈጠር፤ የአገራዊ ንቅናቄ እና የአውሮፓ ህብረት እድምታ፤ ተጽዕኖ ፈጣሪዎችን ጅራት መከተል ለምሳሌ የሰብዕዊ መብት ተሟጋቹ አትሌት ሊሊሳ ፈይሳ ጉዳይ የነበረው የጥድፊያ አመክንዮ ቁልጭ ያለ የብልጠት እንጂ የብልህነት ፖለቲካ አልነበረም። ለዚህም ነው የብልጠት ፖለቲካው መንገድ ተፈረክርኮ የቀረው። እኔም በስፋት ጽፌበታለሁኝ። የብልጥነት ፖለቲካ አትራፊ መንገድ አለመሆኑን። ሰሚ የለም።   

በሄሮድስ መለስ ዜናዊ የሰራው የዛ ዘመን ብልጠት በዚህኛው ዘመን ሳይሰራ ፉርሽ መሆኑ ብቻ ሳይሆን ስንት የመንፈስ ሃብትን እንደናደ ብልህ ነውና ጋዜጠኛ ሲሳይ አጌና ዛሬ ላይ በምልሰት ቃኝቶት ህሊናው ሊዳኘው የሚገባ ይመስለኛል። ለዚህም ነው እኔ ትእግስት ሲያልቅ ፍቅር ኢሰደዳል ያልኩት። 

በዚህ ቃለ ምልልስ ትዝብቶች አንድ አቅጣጫ ብቻ ሳይሆን ሁልአቀፍ በመሆኑ አስተምህሮው ለሚዲያውም ለተሰፋው የፖለቲካ ድርጅትም በቀስታ የሚገሩ ብልህነቶችን ሊቁ ጠቆም አድርገዋል። “ልብ ያለው ሸብ” ደግሞ የብልሆች መንገድ ነው … ቃለ ምልልስ ራሰንም ለማረቅ፤ የራስንም መንገድ ለማስተካከል ከተጠቀሙበት ብዙ ድርሻ ያበረክታል። ካልተጠቀሙበት ደግሞ ያው ብክነት የባጀንበት ነው ... 

·       የተገለጠ በአስተርዮ ሚስጢር።

ፕ/አሻግሬ ይግለጡ ድምፃቸው ጠፍቶ ነበር የባጀው። ከልባቸው የገባ ነገር ስላለነበረ ሰብሰብ ብለው ተቀምጠዋል። ይህም ብቻ ሳይሆን ጸጥተኛ ተፈጥሯቸው ስክነት ይጠብቅ ስለነበር አደብ በገዛው የፖለቲካ ሙቀት በፈቃዳቸው ወደ የሚያከብራቸው ብዙሃን ህዝብ ብቅ ብለዋል። ድምጻቸውን በመስማቴ እጅግ ደስ ብሎኛል። 

እርጋታቸውን አብዝቼ እወደዋለሁኝ። በዝምታ መቆዬታቸውም የተጋባ ነው። እዬተንጨባረቀ ከሚበጠብጠው ሊሂቅ የሳቸው ክውን ሽክፍ ብሎ መቀመጥ በስንት ጣዕሙ። ፈርሶ መሰራት፤ ተስርቶ መፍረስ በራሱ የክብር ልዕልናን ይሸራርፈዋል። ከዚህ ሊቀ - ሊቃውንቱ ፕ/ አሻግሬ ይግለጡ ድነዋል ልባዊነታቸውም ዘመንን ይገነባል  በአዎንታዊነት።

በሌላ በኩል የሰብዕናቸውን ክብራቸውን አስጠብቃዋል። የሳቸው ክብር ብቻ ሳይሆን ቢፈርስም ፓርቲያችን ኢሠፓንም ክብሩን አስጠብቀውለታል። በፈለገ ሁኔታ የዛ ፓርቲ አባልን አካል የሆነ ሰው ድርጅት መስርቶ እታገላለሁ፤ አታግላለሁ ማለቱ መልካም ቢሆንም ስክነት ሲጎድለው፤ ሲንጨባረቅ፤ አደብ ሲያጣ፤ ከዛም ከዛም ጋር ሲጋጫ ሌሎችም በትርፍ የቃላት ጉሽምታ ነገር ሲያውክቡት እኔ እንደ ሥርጉተ ሥላሴ ሰውነቴ ይቀረደዳል። አርፎ ቢቀመጥ ምን አለ እላለሁኝ።

ስለዚህ የቀድመው የኢትዮጵያ መንግሥት ም/ጠ/ሚር ፕ/ አሻግሬ ይግለጡ ጨዋ የሆነው ተደሟቸው እጅግ መስጦኛል። ክብርት ዳኛ ብርቱካን ሜዲቅሳን ብናስባትም ቅንጅት ላይ ብቅ አለች፤ አንድነት ላይም ጎላ ብላ ተከሰተች ካቴና እና ወጀቡን ተጋፍጣ በመጨረሻው ሰብሰብ ብላ፤ ጥልቅ ጥልቅ ሳትል እራሷን አስከብራ የሰከነን ቀን ጠበቀች፤ እንሆ ለፈጣሪ የሚሳነው ነገር የለም እና የእናቷ የክብርት ወ/ሮ አልማዝ ጸሎትም ረድቷት የጠበቀቸውን ቀን አገኘች፤ ዕድለኛም ናት ተፈለገች፤ አሁን አገሯ በምትፈልጋት ወሳኝ ቦታ ላይ ሆና ዕውነትን ታናጋርላች ማለት ነው። እንዲህ ዓይነት ሰብዕናዎች ይመስጡኛል። ርጋታ ጥሩ ነገር ነው ላደለው።

እኔ ፕ/ አሻግሬ ይግለጡ ራሳቸው ሚስጢር ናቸው ብዬ ነው የማያቸው። የተከደነም ሲሳይም ናቸው። ያው በተደጋጋሚ እንደምገልጸው ዶር ካሳ ከበደ እና ኮ/ጎሹ ወልዴ አሁን ለለውጡ የበኩላቸውን ተሳትፎ በማድረግ ላይ ይገኛሉ። እራሱ አገራቸው መሬት መገኘታቸው በራሱ ጠረኑን ህብራዊ አድርጎታል ብዬም አስባለሁኝ። የ አውቀት፤ የልምድ፤ የተመክሮ መዋረረስ መልካም ነገር ነው ለቀጣዩ ትውልድ። በፍልስፍና ዶግማዊ ቀመርም ይህን መስል ምህንድስና ይደጋፍል። 

እንደዚሁም አሁን እነ ዶር ታይ ወ/ሰማዬት/ እነ ፕ/ አሻግሬ ይግለጡ ዓይነት ዕንቁዎች ከዚህ የለውጥ መንፈስ ጋር ቢዋህዱ አላዛሯ ኢትዮጵያ ትጠቀማለች። ትውልዱም በመንፈስ ይታነጽበታል።

እናት እህት የሁሉም አላቸውና እነሱም ሰናይ ያደርጋሉ። በዜግነት ሁሉም እኩል ሲታይ ትውልድን በዛ ለማብቀል ቀላሉ ምህንድስናም ይመስለኛል። አሁን ድረስ የተጎዱ እናቶች አሉ። ልጆቻቸው ደክመው፤ ጥረው፤ ግረው፤ ወጣተነታቸውን አባክነው ግን ተረስተው ሲቀሩ እኔ ዜጋ እኔ  አይደለሁምን ይላሉ ድምጽ አልባዎቹ የኢትዮጵያ እናቶች? የእኔ ማህጸን ያፈራው/ ያፈራትስ ዜጋ አይደለም/ አይደለችንም እያሉ በሥነ - ልቦና ህመም የሚንገላቱ ይኖራሉ … ስለሆነም ፕ/ አሻግሬ ይግለጡንም አላዛሯ ኢትዮጵያ የክብር እጇን ልትዘርጋላቸው ይገባል። እኔ እራሴ ድምጻቸውን በመስማቴ ሐሤቴን አግኝቻለሁኝ። ጓዴቼ ይናፍቁኛል። ሽው ትዝ ይሉኛል። የፍቅር ቤትም ነበር። 

·       ውስጥነት።

በዚህ በመጨረሻው ክፍል 4 ላይ ያደመጥኳቸው ቁምነገሮች ጸጸት እና ይቅርታ መጠዬቅ ኢትዮጵያን ውስጥ ከማድረግ የመጣ ቅንነት ነው ያዬሁት። ይህ መታደል ነው። ማንም ያልደፈረው። የኢትዮጵያ ሊሂቃን ተቃዋሚ/ ተፎካካሪ/ ተቀናቃኝ የሚባሉት ለባከነው ትውልድ ተጠያቂነታቸውን በሌላ ሲያላክኩ እንጂ እንደዛ ዘመን ተወናይነት እኛም ተጠያቂ ነን ሲሉ አላዳምጥም። ይህም በ አድመጭ እና በታዛቢ ዘንድ ክብራቸውን ቆራርሶታል። 

ከቂማቸውም ትንሽ ሽራፊ ይቅርብን ሲሉ አላዳመጥኩም። በብጽዕና ብቻ ተኮፍሰው ነው እኔ እማያቸው። ይህ ዛሬ የሰማሁት ታላቅ ነገር ግን ፕ/ አሻግሬ ይግለጡ የኢትዮጵያን ህዝብ ይቅርታ መጠየቃቸው ወርቃማና ደፋር ውሳኔ ነው።

ሌላው የኢትዮጵያ ከውጭ የተበደረችው ዕዳ ውስጣቸውን እንደጎረበጣቸው ሳይ እኒህ ታላቅ የአገር ሃብት ምን ያህል ስለትውልዱ ጭንቅ እንደሚላቸው ንጽህናቸውን ለማዬት አስችሎኛል። እንደሚታወቀው ዕዳ የሚከፈልበትን ጊዜ እንዲራዘም በማድረግ ጠ/ሚር አብይ አህመድ በቻይና ጉዟቸው ያተኮሩበት መስክ ነበር።

አሁን ፕ/ አሻግሬ ይግለጡ ያመጡት ሃሳብ ግን ይህን ተቋማዊ የማድረግ ብልሃት ነው። በተከታታይነት እና በቋሚነት መሰራት እንዳለበት ነው አዲስ ሃሳብ ያመነጩት። በዴፕሎማሲ፤  በኤኮኖሚ ዘርፍ ያሉ ባለሙያዎች ይህ ተልዕኮ በኢትዮጵያ መንግሥት ዕውቅና ተሰጥቶት ባሉበት ሆነው እንኳን ይህን የዕዳ ዘመን የማራዘም፤ ዕዳ የማስቀነስ እና ዕዳ የማሰረዝ ጉዳይ ሎቢ እንዲያደርጉበት ብልህነት ያለው አዲስ ምህንድስና ስለሆነ ጠ/ሚር አብይ አህመድ ይህን በስካይፒ፤ በስልክ ከባለሙያዎች ጋር በቀጥታ ተነጋግረው ከውጭ ጉዳይ ሚ/ር/ ከኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት ጋር በመሆን አንድ ነፍስ ያለው በዚህ ዙሪያ ብቻ የሚሰራ አካል ማዋቀር የሚቻል ይመስለኛል። ባለቤት ለመሆን ፕ/ አሻግሬ ይግለጡ ራሳቸውን ገልጠው ፈቅደው አቅርበዋል። ይባሩከ!

እኒህ እርጉ ልሂቅ ልምዳቸው፤ ተመክሯቸው፤ ርጋታቸውን ተሻምቶ መበዝበዝ ይገባል። ጊዜ ሊሰጠው የሚገባ አይደለም። ምክንያቱም ተተኪው ትውልድ ጥቂቶች የበለጸጉበትን ዕዳ ተሻካሚ ሲሆን መንፈሱ ይጎብጣል። ተስፋውም ያራል፤ እዬደከመ እዳ ገፍጋፊ ሲሆን ብርታቱ ይሰተጓጎላል።

 ከሁሉ በላይ ዕዳ መክፍል ባልተቻለ ቁጥር የሉዕላዊነት ክሬድትም ሊኖር እንደሚችል ነው እኒህ ታላቅ ዲፕሎማት፤ የሰላም መልዕክተኛ፤ እና የኢኮኖሚ ሊሂቅ ያስገነዘቡት። ነፃነትን መብደር እንዴት ክፉ ነገር ነው። 

ይህን ፍልስፍና በፈለስፋው ፕ/ የምንዳርአለው ዘውዴ ቃለ ምልልስም አዳምጬው ነበር። ኢትዮጵያን ውስጥ ያደረገ ሰብዕና ነፃነትን በዚህ ልክ በጥልቀት ይመራመርበታል። ኢትዮጵያዊነት ረቂቅም፤ ሚስጢርም፤ ሊተረጎም የማይችልም የሚባለው በዚህ የአቅሙ ዲካ የለሽነት ነው። ኢትዮጵያዊነት ነፃነት ነው፤ ነጻነት ደግሞ የህሊና ሥልጣኔ ውጤት ነው። "ለሆዱ ብሎ ነፃነቱን የተበደረ አሳማ ነው፤ ነፃነቱን ያልተበደረ ግን ሲኖር ጀግና ሲሞትም ሰማዕት ነው" ሲሉ ነበር ቅኔውን ያሳደሙን ፕሮፌስር የምንዳርአለው ዘውዴ።

ለዛሬው ህወሃት ፈጠርኩት ለላው ትውልድ ሉዕላዊነት አይገባውም። "ፈርስት" የሚሉት ዞጋቸውን ነው። አገር አልባ የተንሳፈፈ ተስፋ፤ የዋለለ ፍላጎት፤ እና መሬት አልቦሽ ራዕይ ላይ ኑሮውን የመሰረት ስለሆነ። ግን አገር አልባ ክብርም መኖርም፤ መንፈስም፤ ሃይማኖትም፤ ትምክህትም፤ ነፍስም፤ራይም፤ ተስፋም ራሱም ዞግም የለም። ለዞግ ክብር አገር መኖር አለባት። ለዞግ ክብር ነፃነት መኖር አለበት። 

ነገ ኢትዮጵያ በቻይና የመንፈስ ቅኝ ተገዢነት የምትሆንበት መስመር እንዳለ ፍንጭ ይሰጣል ይህ የቃለ ምልልስ ተደሞ። ይህን ደግሞ ለማርገብ፤ መልክ ለማስያዝ፤ ከመንፈስ ቅኝ ተገዢነት በፊት ቀደመው ሊውሰዱ በሚገባቸው ብልህ የማስተዋል ጉዳዮዎች ላይ ሁነኛ ተግባር መከወን ግድ ይላል።

ምን እንኳን በዚህም በዚያም የአብይ ሌጋሲ ቢወጣጠርም ይህም ወሳኝ ዘርፍ ስለሆነ ካለ ኢኮኖሚ መረጋጋት አዲስ ፖለቲካው ሥርዓት መመስረት ህልም ነውና የጠ/ሚሩ አፋጣኝ እርምጃ ከዚህ መሰሉ ብልህ አፍላቂ የግኝት መስመር ጋር መገናኘት ለይደር የማይቀጠር ይሆናል።  ይህ ዕድል ሊያመልጥ አይገባም። 

ይህ ብልህነት ፈሶ እንዳይቀር ባሊህ ቢሉት ዶር አብይ አህመድ መልካም ይመስለኛል። ይህ መንገድ የውጭ ጉዳይ ሚ/ር ሆነ የፕሬዚዳንቷ / ጽ/ቤት ሥራ  በእጅጉ የሚያቃል ጥበባዊ ጉዞ ይመሰለኛል። ሰብሳቢ ሃሳቡን ያፈለቁት ፕ/ አሻግሬ ይግለጡ ቢሆኑ እርጋታቸው ራሱ ተቋም በመሆኑ ስክን ላለው ተልዕኮ ወሳኝነት ያለው ይመስለኛል። አድማጭነታቸው የመደመጥ አቅም ያስገኝላቸዋል። 

ይህ ደግሞ አላዛሯን ኢትዮጵያ ተጠቃሚ ያደርጋታል። የፖለቲካ ሰዎች እርጋ ያሉ ሲሆኑ ጉዟቸው ትርፋማ ነው። በበቂ ሁኔታ አትኩሮትም ዕውቅናውን ካገኙ። ነገር ግን ባለቀ በፈረሰ ሰዓት ከሆነ ለእነሱም የተደሞ ጊዜ ስለሚያስፍለግ ላይሳካ ይችላል፤ ቀደም ብሎ ሰፊ ጊዜ ከተሰጣቸው ግን ይህ መሰል ሰብዕና ያላቸው ሰዎች ተልዕኮውን አትራፊም ዕሴታዊም ያድርጉታል። 

ያ የሮም ስምምነት ያልተሳካው ደርግ / ኢሠፓ ፖሊት ቢሮ ርጋታ ስለነሳው እና ሙከራው ባለቅ ሰዓት መሆኑ ላይበቃ ድርብ የጥድፊያ ግድፈቶችን ስለፈጸመ ነበር።  ራሱ የፕ/ አሻግሬ እርጋታ እና ተልዕኮው ከመንግሥት ፍላጎት ጋር አጣጥሞ ለመጓዝ ለሳቸው የረጋ ሰብዕና የሚመጥን አመራር ይጠይቅ ነበር ከቃለ ምልልሱ የተገነዘብኩት ይህን ነው እኔ። የመንግሥት ፍላጎት እና የተልዕኮ አስፈጻሚው በሰብዕና አገነባብ አልተመጣጠኑም።  

·       ግልጥነት።

ሌላው በዚህ ውይይት የማረከኝ ጉዳይ ግልጽነታቸው ነ። የህወሃት ሊቃናት ደጉን አቶ ገ/መድህን አርያን አይመለከትም ከህወሃት ሲወጡ ገመናውን አመቅው በመያዝ ነው። ፍንጭ አይሰጡም። የዘር ሐረጉን ማህተም የሚጥስ አንዳችም ፍርፋሪ ነገር አትገኘም። ውልፍት አይሉም። እነሱም ብቻ አይደሉም ኦነጋውያን፤ ሻብያውያን፤ ወያኔያውያን የፈጸሙት የጋራ የደቦ ግድፈት አለ። እሱም ውልብልቢቱ አይወጣም። ለዚህ ነው የህዝብ ጭፍጫፋ ታዳፍኖ፤ ባለቤት አጥቶ፤ ደመከልብ ሆኖ የኖረው። የዚህ መከራው ኢትዮጵያን በጎሪጥ ከማዬት የመጣ ነው የሚመስለኝ። ህዝባችን አይሉትም የሚጎድቱን ወግን። ጉዳያቸው አይደለም  እናት አገር የወል እንባ።

ከዚህ የደቦ ነገር ያፈነገጠ ዕውነት በእኒህ ታላቅ ሙሁር ቃለ ምልልስ አዳምጫለሁኝ። ምክንያቱም ሌላ ሳይሆን ኢትዮጵያን ውስጣቸው በማድረጋቸው ነው። በሚያውቋቸው ጉዳዮች ላይ በቀረበላቸው ጥያቄ ልክ በግልጽነት መልሱን ሰጠተዋል። ይህ መቼም በኢትዮጵያ የፖለቲካ ሊሂቃን የማይደፈር አመክንዮ ነው። ሁሉም በድርጀቱ ውስጥ የሰራውን ኢንትሪግ፤ የሚያውቀውን እውነት ከመናገር ይልቅ ዝጉት፤ አታንሱት፤ አታውሱት ነው የሚለው። 

ስለምን? እራሱን ተወቃሽ ላለማድረግ ብቻ ሳይሆን ይቅርታ ለመጠዬቅም ድፈርቱ ስሌለ ነው። ይህን የጣሰ እውነት ነው ዛሬ እኔ ያዳመጥኩት። ለትውልዱ እንዲህ መሰል ግልጽነቶች ያስተምሩታል። ኑዛዜ ነው ያሉት እኔ ግን ግልጥነት - ንጽህና - የእውነት ወገናዊነት - ሃላፊነት እና ተጠያቂነትን የመቀበል ብቃት በሚል እወስደዋለሁኝ።

·       ትውልዳዊ ሃላፊነት፤

በዚህ በፕ/ አሻግሬ ይግለጡ የግልጥነት ውይይት የተረዳሁት ቁምነገር ለትውልዱ ብክነት ያላቸውን የነጠረ ተቆርቋሪነት ነው።፡ በነገራችን ላይ ፓን አፍሪካኒስትም ናቸው። በሚችሉት ሁሉ አፍሪካን ለመርዳት የአፍሪካን ወጣቶች ቅድሚያ በመስጠት እረገድ  የድርሻቸውን እንደተወጡ ተረድቻለሁኝ።

ባለመታደል ኢትዮጵያ በዕድሉ ተጠቃሚ መሆን አልቻለችም። ወደፊት ይህ የሚቻል ቢሆንም። ቀደም ብሎም የሚቻልበት መንገድ ነበር። በተለይ የየኢትዮጵያ ስደተኛ በዬትኛውም ዓለም ስለምንገኝ ለኢትዮጵያ ስደተኞች ይህን ፕሮጀክት ተሳታፊ አድርገውት ቢሆን ኖሮ መልካም ነበር። 

ምክንያቱም ፓርቲያችን ኢሠፓ ሰብበሳቢ አልባ ልጆቹን አፍሶ ሜዳ ላይ መና አድርጎ ያሰቀረን የዛን ጊዜ ወጣቶች አውሮፓም ሆነው አፍሪካ እንገኛለን። አውሮፓ ሲባል አልጋ ባልጋ የሚስለው ሊኖር ይችላል። በብድር ለመማር በማይቻልባቸው እንደ ሲዊዘርላንድ ባሉ አገሮች ሳንማር ባክነን የቀረን ወገኖቻቸው ጓዶቻቸው ነበርን። የእኛ በይሻላል ሲታሰብ አፍሪካ እስያ አውሮፓ አብሶ ጣልያን ላይ የተሰደዱት ደግሞ የከፋ ዕድል ገጥሟቸዋል። 

ስለዚህ ኢትዮጵያ መሄድ ባይችሉም ስደት ላይ ያሉ ኢትዮጵውያንን የመማር ፍላጎት ያላቸውን ለመርዳት ጥረት አድርገው ቢሆን ኑሮ መልካም በሆነ ነበር። የሆነ ሆኖ እማማ አፍሪካ ላይም ፕሮጅክታቸው መስራቱ መልካምነቱ ደግነቱ ፓን አፍሪካኒስት ሊያሰኛቸው መቻሉ ግነት አይሆንም። በዚህ ዘርፍ ኬንያ ላይ ነፍሳቸውን ይማረው እና ሳይንቲስት ኢንጂንር ቅጣው እጅጉ ነፍስ ያለው ተግባር ከውነውበታል።

አሁን ባለው ሁኔታ ለመረዳት ያሰቡበት መስክ የኢትዮጵያ ዩንቨርስቲዎች የብቃት አቅም ቁልቁል መወርድ በእጅጉ አሳስቧቸዋል፤ ይህንም ለማጋዝ ቀናነት አይቸባቸዋለሁኝ። በዚህ ዘርፍም ፈንድ የማግኘት ዕድል እንዳለ ነው የጠቆሙት። ይህን ለምለም ሲሳይም የአብይ ሌጋሲ ቁምነገሬ ብሎ ሊጠቀምበት ይገባል - በፍጥነት። ሁለተኛ ዕድል ማለት ነው። 

አንዱ ስለ ብድር ዕዳ ጉዳይ ሲሆን ሌላው አካዳማዊ የሆነ ጉዳዮችን ቅጥ በማስያዝ እረገድ ነው። ከዚህ ጋር ባለፈው ጊዜ በትውልድ ግንባታ ላይ የአካዳሚ ነፃነት አለመኖር ጉዳቱን ጽፌ አትኩሮት እንደሚሻው አሳታውሼ ነበር። እንዲዚህ መሰል ሉላዊ ተልዕኮዎችን ለመፈጸም ሆነ ለማስፈጸም የአካዳሚ ነፃነት ጉዳይ አንድ ቢባል መልካም ነው። ነፃነት የሌለው ሊሂቅ ነፃነት የሚሰማው ትውልድ ሳይሆን ከርኩድ ነፍስ ነው የሚያምርተውና። 

በሌላ በኩል ሌላም ዕድል ያለ ይመስለኛል። ዛሬ በስካይፕ ሁሉ የኦን ላይን የነፃ ስኮላር ሽፕ መስጠትም ይቻላል። አገር ውስጥም ቢሆን ወርክሾፕ ለወር ለሁለት ወር አዘጋጅቶ አቅጣጫ ማመላከት የሚችል ይምስለኛል። 

እግዚአብሄር ይመስገን ዛሬ እንደ ኢትዮጵያዊው የኩራታችን ማማ የሆኑ እንደ ውዱ ፕ/ ምንዳርአለው ዘውዴ፤ እንደ ረ/ፕ አበባው አያሌው/ እንደ ፈለሳማው ዶር ዳኛቸው አሰፋ ዓይነቶች ትጉህ ዕንቁ ሊሂቃን ስላሉ ከእነሱ ጋር ተቀናጅቶ በቁጭት የትምህርት ደረጃውን ከወደቀበት በማንሳት አቧራውን አራግፎ ወደ አዲስ ምዕራፍ ማሻገር ይቻላል።

ፕ/ አሻግሬ ይግለጡ እጅግ አስደስቶውኛል እንዲህ መሰረት ያላቸውን ዕሳቤዎችን በማንሳታቸው፤ ለዛም ያላቸውን የነጻ አግልግሎት ፈቃደኝነት እና  ተነሳሽነታቸውን አዎንታዊነትና ቅንቱን በግልጽነት በማዬቴ ደስ ብሎኛል። 

ለዚህ ነበር ጠ/ሚር ሳይሆኑ ዶር አብይ አህመድ የሳይንስ እና የቴክኖሎጂ ሚ/ር በነበረቡት ጊዜ በም/ጠ/ ሚር ደመቀ መኮነን በተመራው አንድ ወደ እስራኤል ባቀና ልዑክ አባል በነበሩበት ወቅት ጋዜጠኛው "ኢትዮጵያን የዛሬ 25 ዓመት እንድምን ታልማታለህ" ሲላቸው "ከዛ ባነሰ ጊዜ እኔ እማልማት ኢትዮጵያ ዕውን ትሆናለች፤ ይህን የምልበት ምክንያት ውጭ ያሉ ምርጥ ልጆቿ ሊሂቅ ልጇቿ፤ የአገር ሀብት ከሆነው ህዝቧ ጋር የመለወጥ ዕድሏ ሰፊ ነው" በማለት  በእርግጠኝነት የተናገሩት። ይህ መቼም የልብ አውቃነት ነው።

እና እናማ በሩ ቧ ብሎ ተከፍቷል። ይህን በር ከሴራ - ከኢንትሪግ - ከሸር፤ ከጠልፎ ከመጣል የጸዱ ቅኖች በሙሉ ልብ፤ በቅንነት፤ በቸርነት ማገዝ ከቻሉ አንደ ህልማችን ኢትዮጵያ በአንጡራ ሃብቷ እንደ ሌሎች አገሮች የመሆን ዕድሏ ሰፊ ነው። ከሁሉም ያነሰንበት ምክንያት፤ ያጣነው ቅንነት ነው። እንዲሁም አዎንታዊነት ላይ ድሆች ነን።

·       እኔ የማለት።

„መደመርን“ ፍልስፍና ብለውታል። እኔም በተደጋጋሚ ይህንኑ ገልጫዋለሁኝ። ባለፈው ዓመት እራሱ ይህን ጉዳይ አንስቼው ነበር። አሁን በዓለም የኢኮኖሚ ፎርም ስብሳባ ላይ „መደመር“ በእንግሊዘኛ ሳይተረጉሙት ጥሬ ቃሉን በቀጥታ እንዳለ በሦስት አብይ እርእሰ ጉዳዮች ተንተን አድርገው አቅረበውታል ቅኔኛው ጠ/ሚር አብይ አህመድ። 

https://www.youtube.com/watch?v=f3B_D_ZNgBs

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በዓለም ኢኮኖሚክ ፎረም ላይ ያደረጉት ንግግር

 

በዚህ ፍልስፋና ለመታቀፍ ፕ/ አሻግሬ ይግለጡ ፈቃደኛ ናቸው ከእነ የሚያስጎመው እርጋታቸው ጋር። እኔ ተመስገን ብያለሁኝ።

ሌላው ባለፈው ዓመት ቅኑ ሳተናው ድህረ ገፅ እና እና የሥርጉተ ሥላሴ በብዕር የተጋችበት የጠ/ሚር አብይ አህመድ ልዩ ስጦታና ክህሎትን እሳቸውም አትመውበታል። እንዲያውም ማህተመጋንዲን ይመስላሉ ብለው አክለውበታል።  እኔ እንኳን ኪንግ ማርቲን ሉተር በማለት ለእኔ ብሄራዊ ቀኔ ናቸው ብዬም ነበር። በአብይ ኬኛ ክፍል ስድስት ማጠቃለያው ላይ። ወደ ማዲባም አስጠግተዋቸዋል። የሳቸው የሚለዬው ጥበባቸው በራስነገር ላይ መመሰጣቸው ነው።፡"መደመር" እንዳለ በ አማርኛ ቋንቋው ነው የወሰዱት። አብዛኞው የውጭ አገር ጉዟቸው አማራኝ ቋንቋን ነው የሚጠቀሙት። ነፃነታቸውን ተርጉመውታል። 

ወደ ቀደመው ምልሰት ሳደርግ ፕ/ አሻግሬ ይግለጡ አድናቆታቸው፤ አክብሮታቸው ታማኝነታቸውን ያለ መቁንን ፈቅደው ለመስጠት፤ ቅንነታቸውን በገፍ ለአብይ ሌጋሲ ለማብርከት ዝግጁ ናቸው። መቼም ባለቅኔው ጠ/ሚር ዕድለኛም ናቸው። እንደዚህ የመሰሉ ትውልድ በ50/100 ዓመት የማይተካቸው ሊቀ - ሊቃናት የሚሰጡት ምስክርነት ከወርቅም፤ ከአልማዝም፤ ከዕንቁም በላይ ነው። ምክንያቱነም ሃብትነቱ የመንፈስ ነውና። መመሰጥ መወደድ መታመን የሰማይ ስጦታ ነው። 

ሌላው በዚህ ገለጻ የተረዳሁት በድፍረት እና በሙሉ ልብ በ50/100 ዓመት የማይገኙትን ጄ/ ፈንታ በላይን አገር መምራት ይቻላሉ ብለው መስክራዋል። እኔም ይህንን በተለያዬ ጹሑፌ ገልጨዋለሁኝ። ከዚህ ጋር በ50/በ100 ዓመት የማናጋኛቸው ሳይንቲስት ቅጣው እጅጉም እንደዋዛ ያጣናቸው አገር ሊመሩ የሚችሉ የተስፋ ማህደር ነበሩ።

አሁን ተመስገን የሚባለው ሰላማዊ የለውጥ ሽግግሩ እነ ዶር አብይ አህመድን፤ እነ ዶር ለማ መገርሳን፤ እነ አቶ ደመቀ መኮነን፤ አነ ዶር አንባቸው መኮነን አላሳጣነም፤ የተገበረ የቀረበ ታላቅ ቆመሶ ግን አለ። ቆሞስ ተስፋዬ ጌታቸው።

በሌላ በኩል ፍርሻው ስላልገጠም ወይንም ተከስቶ ስላልታዬ ብዙ ሊቃናት ሳይባክኑ በቀደመው ተግባራቸው ላይ አሁን አሉ። የቀደሙት ዩንቨርስቲ መምህራን መባረር፤ መሳደድ አልደረሰባቸውም እንደ ዘመነ የህውሃት ቂመኝነት። 

እንደቀደመው ቢሆን አፍልሶ - አፍርሶ - በፍርስረሹ ላይ እዲስ አንባገነን ማነጽ ነበር። አሁን ከዛ መሰል ጭዳዊ የቀፎ ጉዞ ተላቀን መሪዎቻችን ከሞትም፤ ከመፍንቀለ መንግሥት ሙከራም ፈጣሪ ታድጎን ዛሬን እዬዬነው ነው።

ከሰኔ እስከ ጥቅምት ኩዴታ፤ የግድያ ሙከራ በጽኑ የተያዘ ጉዳይ ነበር። መደበኛ ሥራም ነበር መግደል ማስገድል፤ መፍንቅል ማድረግ የመንፈስም የ አካልም ሙካራ ነበር። ብክንት - ውድመት- ፍርስትን አብዝቶ የናፈቀ የጮርቃ ዕሳቤ። አሁን እንደ መስከን ያለ ቢሰልም ልብ የሚያስጥል ግን አይደለም። በተለዬ በኢህዴግ ውስጥ አብሮ ሲሳራ የነበረው ሁሉ፤ ሠራዊቱን ጨምሮ ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርበታል።

ለውጡን የመጠበቅ፤ ለለውጡ ዘምብ አድር የመሆን ለደቂቃ ሊዘናጉበት የሚገባ አይደለም። በመፍረስ ውስጥ ተራፊ የለም።  የአካል፤ የመንፈስ፤ የተቋም፤ የሥነ - ልቦና፤ የጥሪት፤ የታሪክ፤ የትውፊት፤ የጥበብ ውደመት ነው ትርፉ። ባላተረፍንበት መንገድ ላለመጓዝ ደግሞ ቀኑ ዛሬ ነው … የአብይን ሌጋሲ በቅንት በትህትና በአክብሮትም ማስቀጠል። ልብ ይስጥን ፈጣሪ፤ አሜን።
 https://www.youtube.com/watch?v=76IFoT-5yrg&t=582s

አፈሬ ነው መስመሬ(23 06 2018)


ኢትዮጵያዊነት ከመፈጠሩ በፊት ፈተናን አሸንፎ የተፈጠረ ሚስጢር ነው!



                                           የኔዎቹ ኑሩልኝ።
                                           መሸቢያ ጊዜ።



አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።