ሰሞናቱ ለረ/አውሮፕላን አብራሪ ሃይለመድህን እንዲሆን በጸሎት እንትጋ!
እንኳን ደህና መጡልኝ።
„የሰው ልብ መንገድን ያዘጋጃል፤
እግዛብሔር ግን አካሄዱን ያቃናለታል።“
ምሳሌ ፲፮ ቁጥር ፱
አማኑኤል ዛሬ እና ሰሞናቱን
አንድ የተባረከ ነገር
እንዲያደርግልን እማጸነዋለሁኝ።
ይርዳን አንድዬ!
ከሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
22.01.2019
ከእመ ዝምታ - ሲዊዘርላንድ።
የተባረከ አሜን ለተባረከ ትውልድ!
ዛሬ ጠ/ሚር አብይ አህመድ ሲዊዘርላንድ እንደሚመጡ ዜና አዳምጫለሁኝ። እመኛው እሻው የነበረ ቀን ነው። እዚህ አንድ ውድ የሆነ የኢትዮጵያ ጀግና አለን። ይህ ጀግና ጀግንነቱ በተግባሩ ብቻ ሳይሆን በሰብዕናውም ጭምር ነው። ስለ አገሩ አብዝቶ ያስባል፤ ስለ አላዛሯ ኢትዮጵያ በበዛ ሁኔታ እስኪገርመኝ ድረስ ይጨነቃል። በፈጣሪው እጅግ ያምናል አብዝቶ ይጸልያል።
በባህሪው ጨዋ ወልዶ ጨዋ ያሰደገው ከመልካም ቤተሰብ የተፈጠረ፤ አሳዳጊውን ይባርከው የሚያሰኝ ነው። በመልካም ቤተሰብ በጥንቃቄ ያደገ ወጣት በመሆኑ በሁለመናው እጅግ ቁጥብ ነው። ብዙ የማይናገር፤ ብዙ የማይል፤ ብስጭት የሌለበት በፍጹም ሁኔታ የተረገጋ ወጣት ነው።
ስላደረገው ብሄራዊ አርያነት አብነት ያለው ብጡል ብሄራዊ የጥቁር አንበሳ ገድል እና ወጣትነቱን ሳይሳሳ የማገደበት፤ ህይወቱን የሰዋበት መንገዱን በፍጹም ሁኔታ ይህን በማድረጉ እና ነፍሱን ችግር ውስጥ ማስገባቱ የማይጸጽተው ስለ እናት ምድሩ ቀን ከሌት የሚያስብ ንቁ ደፋር ሩቅ ወጣት ነው።
በጠ/ሚር አብይ አህመድ አመራርም እጅግ የተደሰተ ተስፋም ያደረገ ወጣት ነው። ተስፋ ያደረገው ስለ እሱ ቀጣይ ኑሮ አይደለም። በፍጹም። ስለ ዘላቂ እና ቋሚ የዲሞክራሲ ምስረታ እና ግንባታ፤ ስለትውልዱ ብክነት መቆም፤ ስለቂም በቀል ፖለቲካ ስንብት፤ ስለምህረት እና ስለ ፍቅር አስተምህሮ ነው።
ወጣቱ በማንም በምንም ላይ ቂም የሌለበት፤ ለሁሉም የኢትዮጵያ ልጆች ቅን ዜና፤ መልካም ብስራታዊ ዜና ማድመጥን ብቻ የሚፈልግ፤ ለዚህ ፈጣሪ እንደሚያደርገው በአንድዬ ተስፋ ያደረገ ጨዋ ወጣት ነው። ይህ ቁጥብ፤ ይህ አስተዋይ፤ ይህ ሚዛን፤ ይህ ታታሪ ብልህ ወጣት እንደ ተስፋው እንደ ምኞቱ ከቤተሰቦቹ ጋር ተቀላልቀሎ እናት አገሩን በፍቅር ያገለግል ዘንድ ምኞቴ ነው።
እርግጥ ነው እናት ሲዊዝ ሸክፍ አንድርጋ ክድን አድርጋ ፎቶውን እንኳን አደባባይ እንዳይወጣ አድርጋ መያዟ በራሱ የ እሱ ተጋደሎ እዮራዊ መሆኑን ለ እኔ ያመሳጥርልኛል። ስለሆነም እናት ሲዊዝም ትመሰገን! በሌላ በኩል አብዛኛው ወገኑ ለ እሱ ያለው ፍቅር እና ታማኝነትም እንዲሁ ልዩ ነበርና እያንዳንዱ በግል ሁሉም በጋራ ስላደረገው ነገርም ምስጋና ይሁን።
እንደ እናት እኔ እማስብለት አግብቶ፤ ተድሮ፤ ወልዶ ከብዶ ባገሩ መሬት እንዲኖር እመኛለሁኝ። እኔ እንደማስበው ውጭ የመኖር ፍላጎት ቢኖረው ኖሮ ያን እርምጃ አይወስድም ነበር። አማራጮች ነበሩለት። ያን ያደረገው በተከደነው የዕድምታ ተደሞው ጥልቅነት ነው - እኔ እንደማስበው።
እኔ በህይወት ኖርኩኝም አልኖርኩኝም የከፈለው መስዋዕትነት ፍሬ እንዲያፈራ የዘወትር ምኞቴ ነው። እጅግ አድርጌ እሳሰለታለሁኝ፤ እጅግ አድርጌም አስበለታለሁኝ። ከሰው ተፈጥሮ ከሰው እንዳልተፈጠረ ይህን ያህል ዘመን በዚህ ሁኔታ መኖሩ ውስጤን ማህጸኔን ያስለቅሰዋል።
እጅግ ያዘንኩበት ነገር ጀርመን ላይ ጠ/ሚር አብይ ሄደው በነበረ ጊዜ አንድ እህቱ ብቻ ፖስተሩን ይዛ ተገኝታለች፤ ስሜን አሜሪካ ጠ/ሚር አብይ ሄደው በነበሩበት ጊዜ አንድም ሰው ስለዚህ ጀግና ሲያወሳ አልሰማሁም። ፎቶውንም አላዬሁም።
የሚገረመው ስሜን አሜሪካ በዶር ገዱ አንዳርጋቸው የተመራው ቡድን ባደረገው ህዝባዊ ስብሰባም አንድም ሰው ጉዳዬ ብሎ ሲያነሳው አላዳመጥኩኝም። እናም እጅግ አድርጌ አዘንኩኝ። እርግጥ ነው በጎንደሮች ተደስቻለሁኝ ሀምሌ 5 ሲያከብሩ የእሱን ፎቶ ፊት ለፊት አድርገው ነበር። ትክ የለሽ ጀግናችን ነው ብናውቅበት። በረከትን፤ ምርቃትን ማባከን አይገባም ነበር።
ይህን ወጣት መርሳት አይገባም። አደራ መብላት ነው። ታዲያ በዚህ ሁኔታ እንዴት ነው ተተኪ ጀግና ሮል ሞዴል የሆነ ትውልድ ማፍራት የሚቻለው? ትናንትን ማከብር ካልቻልን ነገን ማግኘት አይቻልም። እዚህም በተለያዬ ጊዜ ስብሰባ ተገኜቼ ነበር። ወቀሳን ታኮ በስንት ዘመኑ ሥሙ ከተነሳው በስተቀር አንደም ቀን ጉዳዬ ተብሎ ሲነሳ አልሰማም ነበር።
እናም ውስጤን ይከፋዋል። በታሪክ ይህን የመሰለ የሰብዕዊነት ተግባር ኢትዮጵያ አዬር ላይ ስትከውን ረ/ አውሮፕላን አብራሪ ሃይለምድህን አበራ የመጀመሪያው ነው። ከዬትኛውም አገር ተጓዞች ሆነ መንግሥታት ጋር ደም አላቃባነም። እጅግ እጅግ ብልህ ምራቁን የወጣ ወጣት ነው። ንብረትም አላወደመም። እልህኛ ወጣት ባለመሆኑ። ቁጡ ወጣት ባለመሆኑ። የበዛ ታጋሽ እና የመቻቻል ተምሳሌት በመሆኑ።
ይህ ታላቅ የማስተዋል ገድል ነው። ለእኔ ከኮ/ አብዲሳ አጋ፤ ከዘራዕይ ደረስ፤ ከአብርሃም ደቦጭ እና ከሞገስ አስገዶም የሚለዬው አንዳችም ነገር የለም። በዚህ አጋጣሚ አሜሪካን አገር ድረስ መጥተው ጉዳዩን የተከታተሉት የህግ ባለሙያን ዶር ሼክስፔር ፈይሳን አመሰግናለሁኝ። እሳቸው ብቻ ብቸኛው ፈርጥ ናቸው። እሳቸው እራሳቸው ትውልድ ናቸው።
በዚህ ስመጥር ጀግና በልቡ ያለውን፤ በውስጡ ያለውን፤ በህሊናው የሚያስበውን ብታውቁት ይህ ጀግና ራሱ ትውልድ ነው። በጨዋነቱ ልክ እናት አገሩ ኢትዮጵያ በአካልም በአምሳልም በዚህ ሁኔታ ላይ እያለ አብዝቶ ያስባታል። ቅኖቹ ውዶቼ እጅግ ልታከብሩት፤ ልታስታውሱት፤ ልትሳሱለት የሚገባ ትንታግ ወጣት ነው።
ከሁሉ የሚደንቀው ሁሉንም ነገር ቀለል አድርጎ የሚያይ ወጣት መሆኑ ነው። ምንም የተፈጠረ አይመስለውም። ተግባቢነቱ እና ማህበራዊነቱ በራሱ ልዩ ዓለም ፈጥሮለት መጽናናትን ችሮለታል።
በሁሉም ነገር ደስተኛ ነው። አያማርርም። እንደ ቅዱሱ ሐዋርያው ወንጌላዊው ጳውሎስ „ይበቃኛል“ ያለ ድንግል ነው። ራሱን የገበረለት የፍትህ፤ የርትህ፤ የነፃነት፤ የአዲስ ሥርዓት ግንባታ ዛሬ ይህን በመሰለ ወጣታዊ ተጋድሎ ለፍሬ መብቃቱ ቢያስደስተውም ዘላቂ የዴሞክራሲ ግንባታ ግን ህልሙ ነው።
ዛሬን ሆነ ሰሞናቱ የምጠብቀው ትልቅ ዜና ቢኖር ኢትዮጵያን ቁም ነገር ለማድረግ ከሰማይ የተሰጠው በረከት ማለትም ጠ/ሚር አብይ አህመድ ዛሬም እንደተለመደው የተባረከ ነገር ከውነው፤ የአብይ ሌጋሲ ህልሙም ራዕዩም የተበተኑ ወገኖችን ማሰባሰብ ነውና ታማኙን ጀግና ፍጹም ጨዋ የታናሽ ወንድምን፤ የአስተዋዩንና የብልሁን የጀግና ሃይለመድህን አበራ ጉዳይ እልባት ያገኛል ብዬ አስባለሁኝ። ልክ እንደ ወንድማቸውም እንደ አቡሽም ቢዩት ምኞቴ ነው። ረቂቅ የሆነ ወጣት ነው። አስተሳሰቡ በሳል ነው። አሜኑ ቢያንስ አጀንዳቸው ይሆናል ብዬ አስባለሁኝ።
ተስፋ አያልቅም እና ታማኝ የጠ/ሚሩ ፓይለትም ይህ ጀግና ይሆናል ብዬ አስባለሁኝ። ውስጡ ፍሬ ነው። ውስጡ ቁም ነገር ነው። ከሁሉ እማደንቀው ቂም የለበትም። ንጹህ ነው እንደ ዝናብ ውሃ። ቀለሙም ውሃማ ነው። ፓይለት ሃይለመድህን አበራ አዲስም ቀን ነው።
ዛሬን በሱባዬ ነገን ምንአልባት በየምሥራች ዜና … ለእናቱ ለእመት ክብርት ለጀግና ወላዷ ለወ/ሮ ዝማም ስዩም የማህጸን ሃዘን ለዛ በግፍ ለተገደለው ለሊቀ ሊቃውንቱ የዩንቭርስቲ መምህር ላሳደጉት አጎቱ ደመ ከልብ ሆነው ለቀሩት ለፕ/ እምሩ ስዩም የነፍስ ካሳ ይህ ቀንበጥ፤ ይህ ለጋ፤ ይህ ጀግና ለአገሩ መሬት በሰላም እና በሰናይ ቢበቃ ምኞቴ ነው።
አማኑኤል ይርዳን። አሜን! ሰሞናቱ ለረ/አውሮፕላን አብራሪ ሃይለመድህን እንዲሆን በጸሎት እንትጋ!
ኢትዮጵያዊነት ከመፈጠሩ በፊት ፈተናን አሸንፎ የተፈጠረ ሚስጢር!
ብርቴን በቃሽ ያለ አምላክ ሃይልዬንም በቃህ ብሎ ለሚወዳት
እናት አገሩ መሬት ያብቃልኝ አማኑኤል። አሜን!
የኔዎቹ ኑሩልኝ።
መሸቢያ ጊዜ።
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ