"ሉዕላዊ አገር እንጂ ሉዕላዊ ክልል የለም።" ጠ/ሚር አብይ አህመድ ከተናገሩት ...

 

እንኳን ደህና መጡልኝ።

„ሉዕላዊ አገር እንጂ ሉዕላዊ 

ክልል የለም። እንደ አፈዎ 

ያድርግልንይሁንልን እስኪ

 

ጋሜል። አንዳልወጣ በዙሪያ ቅጥር ሠራብኝ።

ሰንሰለቴንም አከበደ።“ ሰቆቃው ኤርመያስ ፫ ቁጥር ፯

ከሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
 01.02.2019


ከእመ ዝምታ ኪሲዊዝሻ።

 



„ሉዕላዊ አገር እንጂ ሉዑላዊ ክልል የለም“ ይህ ከዛሬው ከጠ/ሚር አብይ አህመድ መልስ የተወሰደ ነው።

 

·       እንደ እኔ ዕይታ እና ተደሞ ልሄድበት ወደድኩኝ። እንዲህ …

 

ይህ የሆነበት መሰረታዊ ጉዳይ አለ። ይህ መሰረታዊ ጉዳይ ትግራይ እንደ ሉዑላዊት አገርነት ነው 27 ዓመት የቆዬችው። ቀደም ባለው ጊዜ እኔ ስጽፍ ተጋድሎው ኢትዮጵያዊነት እና ትግራዊነት ነው እል ነበር።

 

በጣም ለረጅም ጊዜ ስጽፍ ተጋድሎውን ስምለከተው የነበረው ትግራዊነት ኢትዮጵያዊነት ተክቶ ለመውጣት ስለመሆኑ ነበር የሚረዳኝ። ነውም። ሂደቱም ሁኔታው የነበረው ኢትዮጵያ ትታይ የነበረው እንደጠላት አገር ነው። ቅኝ እንደተገዛች አገር።

 

የህወሃት ማንፌስቶ ጸረ ኢትዮጵያ ነው ልክ እንደ ኦነጉ። ኦነግ ሥልጣኑን ቢያገኝም ከቻለ በዚህ መልክ ህወሃት 27 ዓመት በነበረበት ልክ ካልቻለ ደግሞ የራሱን አገር መፍጠር ነው። ህልሙም ዕውነቱም ይኸው ነው። መንትዮሹ መንገዳቸው ይኸው ነው።

 

ባዶ ቤት አግኝተው ጊዜያዊ ጋብቻ የፈጸሙትም በዛ መልክ ነበር። አጅሬው ወያኔ ለቀን ያደረሰውን ሻብያንም፤ ሽፋን ሰጪውንም ኦነግንም በጊዜ ሸኝቶ በለሱን በበለስ አጣፍጦ ተኮፈሰበት እንጂ።  

 

ወደ ቀደመው ምልሰት ሳደርግ ይህን ያክል ጊዜ ቀርቶ ህወሃት ከዚህ ደረጃ እደርሳለሁ ብሎ በህልሙም በውኑም አስቦት በማያውቀው የታሪክ አጋጣሚ እጬጌ አደረገው። እጬጌነቱ ደግሞ ሁሉንም ሰጥ ለጥ ብሎ እንዲገዛለት አስችሎታል። ይህን ዕድል ነው አሁን የጉለሌለው መንግሥት ለእኔ ይገባኛል ተራው የእኔ ነው እያለ እዬሻተ ያለው። እኔም ባለሰምንት ልሁን ባይ ነው። የኦነጋውያን የመንፈስ ጥድፊያም በዚህ ፈትል የተሸመነ ነው።

 

በህወሃት የ27 ዓመት የበላይነት ዘመን ይህን የታቃወሙ አልተመቸን ያሉ የነፃነት አርበኞች በሃሳብ ደረጃ ቢሞግቱትም በመንግሥትነት በአውራ ፓርቲነት ግን 27 ዓመት የህወሃት ማንፌስቶ ቀጥ አድርጎ አንቀጥቅጦ ሁሉንም ገዝቷል። ሁሉንም አሳምሮ ነድቷል።

 

ሉዐላዊነትን እንሱ በሥነ - ልቦና  የበላይነት ነው የመነዘሩት።  በፖለቲካ፤ በማህበራዊ፤ በሃይማኖትም የበላይነት ነበር። ሌላው የዋሁ ደጉ የኢትዮጵያ ህዝብ ደግሞ የትግራይ ገበሬ ከሌላው ገበሬ የተለዬ ያገኘው የለም በሚል ስስ ግንዛቤ ውስጥ ነው የባጀው። ሌላው ቢቀር የሥነ -ልቦናው የባላይነት ለሁሉም ተጋሩ የተመቸው ጉዳይ ነበር። ለዚህ ነው ህወሃትን የሚቃወሙ የትግራይ ሊሂቃን ሳይቀሩ አሁን አብረው ከህወሃት ጋር ቆዛሚ የሆኑት።  

 

ልዕልይ ትግራይ ሁሉን የማድረግ አቅሟ 5% ይዞ ከሚያነሳቸውም ከሚበልጡትም ከልሎች ሳይቀር እኩል በቁጥር የሥልጣን ውክልና ነበራት። የሥልጣን ውክልና ብቻ ሳይሆን የአቀደችውን በፍላጎቷ ልክ የማስፈጸም ሙሉ አቅም ነበራት። ሙሉ አቅሙ የመነጨው ደግሞ ትግራይን እንደ ሉዑላዊ አገር አራጊ ፈጣሪ አድርጎ ከማውጣት ጋር በስልት የተቀመረ ነበር።

 

ሁሉም ክልል እኩል ነበርኩ ብሎ መቼም መናገር አይችልም። ሁሉም ክልል ስብሰባዬ ከክሌ አልፎ ስለ ኢትዮጵያ አጀንዳ ነበረኝ ብሎ መቼም አይናገርም

 

ትግራይ ግን ስለሉዑላዊቷ ትግራይም ስለ ተገዢዋ ኢትዮጵያ የቀጣይ ህይወት ወሳኝ አካል ሆና ቆይታለች። ለዚህ ነው እኮ ጎንደር ድረስ ሄደው አቶ አባይ ወልዱ በማንአለብኝነት ሁሉን የመግዛት አቅሙ ከእኛ እንጂ ከሌላ አይደለም በማለት የፈለግኩትን አስሬ አመጣለሁኝ፤ የፈለግሁትንም ማቃጠል ማንደድ እችላለሁ ብለው አቅደው የተንቀሳቀሱት። ሲከር ይበጠሳል ሲሞላም ይፈሳል ሆኖ ራሱንም ለመጨረሻ ጊዜ ከሥልጣን ኮረቻው አውርዶ ትግራይ ላይ ብቻ ኩርኩም ብሎ ተቀጥቶ እንዲቀመጥ አደረገው እንጂ። „የለመደች ጦጣ ሁልጊዜ  … „ሳይሰራ ውሃ በልቶት ቀረ ... 

 

በ27 ዓመቱ የታላቋ ትግራይ የመሪነት ዘመን የትኛውም ክልል ከትግራይ በታች እንጂ ትግራይን የሚመጥን እኩል የሥልጣን አቅም፤ የመወሰን አቅም፤ የመደመጥ አቅም አልነበረው። ይህን አይደለም እኛ ምዕራቡ ዓለምም ጠንቅቆ ያውቀዋል።

 

ስለዚህ ይህ የገነነ ተለምዶ አሁን ትግራይን በፌዴድራል ሥር ሁኚ ሲባል የሚሆን አልሆንም። "ስድ የለቀቁት ጥጃ ሲይዙት ያጓጉጣል" ሆኖ ቁጭ አለ።

 

ልዕልተይ ትግራይ እራሷን እኩል አድርጋ የምታወዳደረው ከኢትዮጵያ ጋር እንጂ ከክልሎች ጋር አይደለምምን በወጣት?  የትግራይ ሊሂቃንም ከሌላ የተፈጠረ ሊሂቃን በታች ሆነው ይተዳደራሉ በዛ ሥር ተብሎ አይታሰብም ነበር። 


የዛሬው የዶር ደብረጽዮን ገ/ሚኬኤል የፉክክር ሂደት እኮ ስታዩት እኛም ብቁ መሪ አለን ዓይነት ነው። እኛም ተወዳጅ መሪ አለን ነው። እንበልጣልን ማንችሎን ስለነበረ ነው ኢህአዴግን የሚፎካከር ፓርቲ አይመጣም ሲሉ ከራሳቸው ውስጥ ከግንባራቸው ፈንጅ ፈንድቶ ጉድ የሠራቸው። 


"ህገ መንግሥት ይከበር" እኮ ሌላ የትርጉም ፈሊጥ የለው ትግራይን በልዕልና መንበር ላይ አስቀምጦ በልዕልትነት ሌላው በባርነት እንደተለመወደው ይቀጥል ነው። ይህ እኮ ነው ህገ መንግሥታዊው የ27 ዓመቱ ጉዞ … ያን እንመልስ ካልተመለሰ አንገዛም ነው ዛሬ ቢሸፈንም ቢታሸገም ቢቆላመጥም አፍጥጦ ያለው ዕውነት። ነገ ግልጥልጥ የሚለው ... 

 

በሌላ በኩል ክልሎችም ቢሆኑ አማራ ክልል የሚባለው በአንድ የመተንፈሻ ቧንቧ ነበር የሚተነፍሰው። ልብ የተገጠመለት ክልል ቢኖር አማራ ክልል ነበር። ሌላውም ቢሆን ፕ/ አሻግሬ ይግለጡ እንደነገሩን በፖለቲካ ብልጥነት የቡና ፖለቲካ በመጣው ጣጣ ለግንዱ ቅርፊት አስፈለገው እና ህወሃት አገራዊ ፓርቲ ለመሆን አቅሙ ስለተጋለጠ ኢህአዴግ የሚባል ጭንብል በምን ሁኔታ እንደተፈጠረ ብትን አድረገው ነገረውናል። እኛ ስንል፤ እኛ ስናብራራ ባንታመንም ማለት ነው።

 

ስለዚህ ህገ መሠረቱ ትግራይን እንደ ሉላዊ አገር አደርጎ ሌላው በገባሪነት ከመሠረቱ የተቀዬሰ ስለሆነ አሁን ወደ ተመጣጠነ የሥልጣን ክፍፍል እንምጣ ሲባል ወገቤን ሆነ።

 

ይህን በተግባብቶ መንገድ ካልተቻለ ወደ ፊት የሚመጣው ጣጣው የፈለገ በማስታመም ቢያዝም መፈንዳቱ ግን አይቀሬ ነው። ለህወሃት ትንፋሽ በሚሰጡ ልዝ የእርምጃ አያያዝ ነገ ሲታሰብ በወጥ አመራር የመመራቱ ጉዳይ ለእኔ አራባ እና ቆቦ ሆኖ ነው የሚታዬ። የበለጠ ሃይል እንዲያገኙ፤ መረባቸው እንዳይበጣጠስ አቅም ጉልበት የመተንፈሻ ጊዜ እዬተሰጣቸው ነው። ዱብ እዳውን ሳይላመዱት እና ሳይደራጁ ትንፋሻቸውን ሳይሰበስቡት ጥበብ ቀድሟቸው ቢሆን ይመረጥ ነበር። 

 

ትግራይ እኮ ከኢትዮጵያ የምትፈልገው ነገር ሳይቋረጥባት መብቷ በሁሉም ዘርፍ ተሟልቶ ግዴታዋን ግን አሻም ያለች ግንኙነቱ በኮንፌደሬሽን ደረጃ የሚመስል ሁኔታ ነው ያለው።

 

ይህ መቼም አይካድም። የትኛውን መመሪያ ይሆን ትግራይ ክልል ሲፈጽም የታዬው? የሚታየየው? የትኛው የተፎካካሪ ፓርቲ ነው ትግራይ ላይ ዜጎችን አግኝቶ ማወያዬት የሚቻለው?! አንድ ጠ/ሚር በድፈርት ሌባ የተባለበት ክልል እኮ ነው። ሠራዊትን አትሄድም ብሎ ያገተ ክልል እኮ ነው።

 

በዚህ ውስጥ ስለ ዴሞክራሲ ጠ/ሚር አብይ አህመድ የተናገሩት አለ። እኔ 33ቱ ድምጽ አለመስጣቸውን በወሰን አሰተዳደር እና በማንንት ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ መብት ነው ብዬ ሞግቻለሁኝ።

 

ነገር ግን ከውሳኔ በኋላ የብዙሃኑ ውሳኔ ወደ ተግባር ለመቀዬር ከመሰናዳት ይልቅ በራሱ በህወሃት ከፍተኛ አካል እንደገና በአጀንዳ መወያዬት እነሱ እራሳቸው ፈጽሞ የሚያምኑበት ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት ራሱ አይፈቅድም። የመርህ ጥሰት ነው፤ እንደ መብትም ሊታይ አይገባም። አንድ ክልል የመላ ኢትዮጵያ ውክል አካል የሰጠውን በዚህ መልክ መወያዬት ፍርድ እንደ ገና የመታዬት ያህል የህግ ጥሰት ነው። 

 

የብዙሃኑ ውሳኔ በጥቂቱ ተፈጻሚ ይሆናል ይላል የዲሞክራሲ ማዕከላዊነት መርህ እራሱ። እና ፓርላማ ላይ 33ቱ መቃወማቸው የተገባ ሆኖ ትግራይ ላይ የተከወነው ግን የሜንሼቢኮች አካሄድ ነው። በሌላ አገላለጽ ሥርዓት አልበኝነት ነው።


በዝርዝር ይህን ብቻ ነጥለን እንዬው ቢባል የህግ ጥሰት በማንአልበኝነት ነው የተከወነው። ጥሰቱ ደግሞ ንቀትም የትዕቢትም ጫፍ ነው። ለድርድርም የሚቀርብ አይደለም። በሌላ በኩል የሽማግሌ ትውፊትም ተቀጥቅጧል። ተቀጥቷልም። ለወደፊትም ተደማጭነቱ ቁልቁል ነው። እዛው አካባቢ ሽማግሌዎች ሄደው እንደነበርም አሰተውያለሁኝ። 

 

ወደ ቀድሞ ነገር ስመለስ በፖለቲካ አመራር፤ አደረጃጀት፤ እና አወቃቀር ዙረያ እንዲህ መሰል መርህ ነክ ጉዳዮች ሽምግልና የተገባም አልነበረም። የፖለቲካ ድርጅት የአደረጃጀት መርህ ከፖለቲካ ውጪ የሆኑ ሰብዕናዎች ሊዳኟቸው አይችሉም። ውጥኑ ራሱ ዝበት አለበት።

 

በሌላ በኩል ክልሎች የራሳቸው የተደራጀ የሠራዊት አካል አላቸው ሚልሻ ይባል ምን። ያም ሌላው ጉዳይ ነው። በዚህ አያያዝ በማዕከላዊ ደረጃ ሊመራ በሚችል መልኩ እንደገና እስካልተደራጀ ድረስ ያው ዘመነ መሳፍንት ነገር ደርጅቶ መከሰቱም አይቀሬ ይመሰለኛል። ብዙ የተባለሹ ነገሮች ናቸው ያሉ። 

 

ሌላው በፌድራል መንግሥት ከምንም ያልተቆጠር አንድ ነፍስን የሚፈትግ ጉዳይም አለ። ህወሃት ጉባኤውን ሲያካሄድ የቻይና ሉዑክ ነበሩ። ያን በምን አግባብ ነበር ብሎ ማሰብ ይገባል።

 

ህም በመደዴ፤ በግዴለሽነት እንዳሻው ይሁንበት ተብሎ የሚታይ ሊሆን አይገባም። በምን አግባብ ትግራይ ከቻይና መንግሥት አገር ያን የመሰለ ልዩ ግንኙት ሊኖራት ቻለ ተብሎ መታሰብም፤ በወቅቱም እርማት ብቻ ሳይሆን በበሰለ የፖለቲካ አቀረረብ ሊፈታ የሚገባው ነበር። በቸልታ ነው የታለፈው። ረመጥ!

 

የቻይና ሉዕክ ቡድን ለህውሃት ጉባኤ ሲገኙ ለህወሃት አባላትም ሆነ ለትግራይ ህዝብ የሚሰጠው ልዩ መልዕክት የትግራይን ሉዑላዊነት ነው።

 

ህወሃት ሥልጣን ከያዘ ጀምሮ የውጭ አገር ዜጎች የጻፉት መጸሐፍ በትግራይ ሉዕላዊነት መንፈስ ነው። ሥነ - ልቦናው፤ ባህሉ፤ ወጉ፤ ልማዱ፤ ሃይማኖቱ ሁሉመናው የኢትዮጵያ የጋራ፤ የወል ዕሴት መሆኑ ቀርቶ የትግራይን ልዕልና የሚገልጽ ነው።

 

ከ100 ዓመት በኋዋላ እኮ ትግራይ እንጂ ኢትዮጵያ የምትባል አገር አትኖርም ነበር እኮ መንገዱ። ትግራዊነት እንጂ ኢትዮጵያዊነት አይኖርም ነበር ትልሙ።

ይህ ማለት በ27 ዓመት ውስጥ ስንት ነገር በመሸርሸር፤ በመበርበር በማለቀ ላይ እንደ ነበር አስተውሎቱ የለም። በሁለመናው ወረራው ልክም፤ መጠንም፤ ደንበርም አልነበረውም። ለዚህ ነው ዛሬም መሰሉ እንዳይደገም አልፎ አልፎ የሚታዩ ግድፈቶችን በድፈረት እምጽፈው። ምክንያቱም መንገዱ ለህልመኛውም አይጠቅምም ትውልድም አያበረክትምና።

 

አውራ ሆኖ መውጣት የሚጋባው ኢትዮጵያዊ ዕሴት ሆኖ ሥርጭቱም በእኩልነት ሂደቱም ካለምንም ጫና ተመጣጥኖ መሆን ይገባዋል። በስተቀር ነገም ትናንት የታዬው የማይደገምበት ምንም ዋስትና የለም። 


አንዲት ሉዕላዊት አገር አምታስፈልገን ከሆነ አመጣጥኖ አስክኖ መጓዝ በእጅጉ ያስፈልጋል። ዕወቅና አሰጣጡም ወጥ መሆን አለበት፤ እዬነጠሉ ማግነን ማኮፈስ መንገዱን ገደልማ ያደረገዋል፤ ልብንም ያሸፈታል።  

 

ትግራይ ላይ ያለው አሁንም ያለው ግብረ ምላሽ የሚሰጠውም መጫንን በመሳቀጠል ላይ ያተኮረ ነው። „ሉዑላዊ አገር እንጁ ሉዑላዊ ክልል አለመኖሩን“ በአመክንዮ ትክክል ነው በመንፈስ ደረጃ ግን አገላለጹን የሚመጥን አቅም ላይ ነን ወይ? ቢባል አይደለንም

 

በአንድ ሰሞናት ሂደትም ይህን የፈተና ተራራ መናድ ፈጽሞ አይቻልም። በሁለት የተለያዬ ፍላጎት ውስጥ ሆኖ በዚህ አምክንዮ ውስጥ ወጥ መታደምን ማምጣት የሚቻል አይሆንም። እርቀሰላም ያልወረዳባቸው ወሳኝ ጉዳዮች አሉበት እና።

 

ስለምን ይሆን ዶር ደብረጽዮን ገ/ሚኬኤል አባቶችን ለማዬት እና አብረው ፎቶ ለመነሳት የፈቀዱት? ስለምን ይሆን በጽዮን ዕለት ሥርዓት ተክሊል ለመፈጸም የተገደዱት? ስለምን ይሆን ጥምቀትን ከራያ ህዝብ ጋር ለማሳለፍ በዛን ያህል አጀብ እና ቀይ ምንጣፍ የክብር ልዕልና ማግኘትን ያቀዱት? ስለምን ነው አዲስ አባባ ላይ የብሄር ብሄረሰቦች ቀን ሲከበር ትግራይ ላይ መሰሉ እንዲከውን የተፈለገው ለዛውም የጎረቤት አገር የሱዳን ጉርብትና በጉልህነት በልጽጎ?

 

ስለምን ይሆን በመላ ኢትዮጵያ የለውጡ ድጋፍ ሲካሄድ መቀሌ ላይ ሌላ ድራማ የነበረው? የዚህ ሁሉ ድምር ውጤት እኛ መሪ ከሆን አብረን ካልሆን ግን ሉዑላዊነታችን አናስደፈርም ነው። ይህ እኮ የለብ ለብ የፖለቲካ ትርጉም ተሰጥቶት እንዳሻህ የሚባል ጉዳይ አይደለም። ሊለይለት ይገባልማህል ሠፋሪ ላይ ባለ አዬር ግን ሉዑላዊነቱ እዚህም እዚያም መሆኑ በነበር ሳይሆን በተጨባጭ የሚያፋጥጡ የዕውነት እንክብሎች አሉ።  

 

ለዛውም ሁሉም ነገር ህወሃት በዘረጋው ኔት በነበረው እንዳለ በቀጠለበት ሁኔታ። ውክል አካላቱም በወሳኝ ቦታ ላይ በሙሉ ማህያ ተደላድለው በተቀመጡበት ሁኔታ። የህውሃት ጭንቅላት ትግራይ ላይ 11 አካላቱ ግን በመላ ኢትዮጵያ በዬአንዳንዱ ነጥብ ጣቢያ አለ።

 

ይህን ንዶ ወጥ የሆነ ነገር ፈጥሮ ጭንቅላቱን ብቻውን እንዲቀር ለማድረግ ደግሞ የተጀመረ ነገር ጅጅጋ ላይ ብቻ ነው የታዬው። አሁንም እኮ የህወሃት ውክል አባላት በዬትኛውም የሥልጣን ደረጃ ወሳኝ ቁልፍ ቦታ ይዘው የፈለጉትን እንደፈለጉ እያደረጉ ነው።

 

በዬአንዳንዱ የገጠር ከተማ ህወሃት አባላቱ አሉት፤ ተግባራቸውንም በትጋት ይከውናሉ። ጥቅሙን የሚጻረር ተጠቃሚ ከኦሮሞ ማህበረሰብ በስተቀር ታሪክ አስተናግዶ ስለማያውቅ። በዬትም ሁኔታ የሚፈናቀለው፤ የሚገረፈው የሚገደለው ሌላው ነው። ይህን ስናስተውል የህወሃት ሉዑላዊነት እንዳለ ማሰረጃ አያስፈልገንም።

 

ሌላም ምሳሌ ማንሳት ይቻላል፤ ተማሪዎች በወቅቱ ወደ ት/ቤት አልሄዱም በአብዛኞው ክልል ትግራይ ላይ ግን መደበኛ ት/ቤት በተለመደው ሁኔታ ቀጥሏል። ስለምን? ሌላ ቦታ እንቅፋት ከዛ ሰላም እንደምን ሆነ? የትግራይ ሉዑላዊነት እና ገዢነት በራሱ ጊዜ ክልሉን አስጠብቆ ሌላ ቦታ ለማተራመስ ደግሞ ሰፊ የሆነ ቁጥጥር የሌለበት ሃግ የማይባልበት ሁኔታ ነው ያለው። መዋቅሩ፤ መረቡ እንዳለ ነው ያለው። አልተነካም።

 

ሁሉም ይፈራርስ ባይባልም ቢያንስ ቁጥጥር ማድረግ፤ የችግሩን ምንጭ አጥንቶ መረቡን በመቀስ መቆራረጥ ይገባ ነበር። ይህ ቢሆን አንገት አልባ ጭንቅላት ሞቱን ነበር የሚታወጀው። ወይንም መጋቢ ካለገኜ ጭንቅላቱ በራሱ ጊዜ ሬሳ ሃሳቡ እንደተጣበቀ ይደርቅ ነበር።

 

እንዲህ በመሰለ ማስታመም ግን እዬታመሙ ከመሄድ ውጭ አትራፊነቱ አይታዬኝም። ሁሉም ቦታ አሉ። ሁሉም ቦታ የልባቸውን ያደርጋሉ። ቀን ይገነባሉ ሌሊት ይንዳሉ እስከ ተባባሪዎቻቸው።

 

የአቶ አብዲ ኢሌ መታሰርን ህወሃት ተቃውሞ የወጣበት መሰረታዊ ምክንያት አስኳሉ መረቡ ስለተነቀለ ነው። ከሥር ያሉትም በጥናት እና በጥበብ ከተነጠሉ ክልሉን ጅጅጋን ነፃ ማውጣት ይቻላል።

 

ፌድራል ላይ? በሌሎች ክሎችስ? ሲባል ገና ጣር የሆኑ ጉዳዮች አሉ። ሰሞኑን ጭልጋ ሰክናለች አሉ። ስለምን ብዬ ስጠይቅ በጭንቅላቱ መታሰር ብለውኛል። ራሱ ጭልጋ ሲንገሩኝ የቀድመዋ ጭልጋ የለችም አሉ። በትነው ፍልስልስ አደርገዋታል አሉ … ሌላው ክልልም እንዲሁ …

 

የዚህን ያህል መብት የሆነው ደግሞ በሪሞት ኮንትሮል ሉዑላዊቷ ትግራይ የመቆጣጠር አቅሟ ባለመነካት ስለቀጠለላት ነው … ለእኔ አሁን ባለው ሁኔታ ትግራይን በኮንፌደረሽን ደረጃ እንዳለች ነው እማስባት … ሲቀጥል ደግሞ መራራው ነገር ከች ይላል።

 

ስለምን? የመፍትሄው አያያዝ ኤንም እንዳይከፋው ቢንም እንዳይከፋው ሆኖ አይሆንም እና … አንድ ሰው ሁለት እግር አለኝ ብሎ በአንድ ጊዜ ከሁለት ዛፍ መውጣት አይችልም። መምረጥ ይኖርባታል። ገቫሪነት እስከመቼ?

 

በአምክንዮ ደረጃ አንዲት ሉዑላዊት ኢትዮጵያ የምትባል ዓለም አቀፍ እወቅና ያላት አገር አለች። ድርጊት ላይ ግን እእ። የጉለሌውም እኮ የኢትዮጵያ አካል አይደለሁም እያለ አዲስ ላይ ይንጎባለላል? በዓለም ታሪክ እንዲህ ዓይነት ቀልድና ፌዝ በአንድ አገር ሉዑላዊነት ታስቦም ታልሞም ሆኖም አይውቅም።

 

ሌላን ዘራፊ እምታስር ከሆነ ከፊትህ ያለውን ዘራፊ ሌባ ብለህ ማሰር አለብህ? ሌላ የኢሰብዕዊ ድርጊት ፈፃሚን በቁጥጥር ሥር ለማዋል ከወሰከንክ ምዕራብ ወለጋም ሆነ ቤንሻንጉል የሰው ልጅ ነው ያለቀው፤ ልጆችን ናቸው የተደፈሩት፤ ሺዎች ናቸው ከቀያቸው የተፈናቀሉት፤ በርካቶች ነው የታገቱት። በዚህ ውስጥ የሉዑላዊነት ነገር ሲታሰብ ሚዛን ውስጥ ለማስቀመጥ ዕውነት ተፈታኝ ይሆናል።

 

ምርኩዝ።

 

/ / አብይ ከህዝብ ተወካዮች ምክ ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች የሰጡት ምላሽ- ክፍል 1

/ / አብይ ከህዝብ ተወካዮች ምክ ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች የሰጡት ምላሽ- ክፍል 2

ጠቅላይ ሚኒስትር / አብይ አህመድ በፀጥታ ጉዳይ ላይ የሰጡት ማብራሪያ

ጠቅላይ ሚኒስትር / አብይ አህመድ በኢኮኖሚ ጉዳይ ላይ የሰጡት ማብራሪያ

 

https://www.youtube.com/watch?v=USuXhJjPlL8

/ / አብይ ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች የሰጡት ምላሽ- ክፍል 1



                                            የኔወቹ ኑሩልኝ። መሸቢያ ጊዜ።

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።