? የመጨረሻው ዳርቻ የት ነው?!

እንኳን ደህና መጡልኝ።

? የመጨረሻው ዳርቻ የት ነው?!


„አምላኬ አምላኬ ለምን ተውኸኝ?“
መዝሙረ ዳዊት ፳፩ ቁጥር ፩
ከሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
22.02.2019
ከእመ ዝምታ - ሲዊዘርላንድ።

አሁን አንድ ዜና ሰማሁኝ። ዶር ለማ መገርሳ የለገጣፋው መፈናቀል እንዲቆም ማዘዛቸውናን እና ከህዝቡ ጋር ለመነጋገር መፍቀዳቸውን። እንግዲህ ነፍሰ ጃውርውያን አቶ ንጉሹ ጥላሁን እና አቶ አዲሱ አረጋ አነ ሰውር ሐዋርያቱ ከጎበኙ በኋዋላ የተሰጠ ተስፋ መሆኑ ነው።  ዜናው ዕውነት ከሆነ መልካም ነው። እኔ ግን መጨረሻው ፍርጥርጥ ብሎ መታወቅ አለበት ባይ ነኝ።

ብልጥ  የኦሮሞ አክቲቢስቶች ቀስ ብሎ መከወን ነበር እያሉን ነው። ይህ ማለት ሙሉ ለሙሉ መደላደል ከተረጋገጠ በሆዋላ እንደማለት ነው። ያን ጊዜ 5ቱ የኦሮሞ ድርጅቶች መግለጫ ሲያወጡ ያሉትን ነው የደገሙት አሁን መሆን አልነበረበትም ብለውን ነበር። መቻል እኮ መቻል ከተሰጠው ባለመክሊት ብቻ ነው የሚገኘው …

እውነት ደግሞ ቀን አይቀጠርለትም ለውጡን እንመራለሁ የሚለው ቲም ለማ ኢትዮጵያዊ ለውጥ ወይንስ የኦሮሞ ኢንፓዬር ለመገንባት ነው እዬተጓዘ ያለው? ይህ በፈጣጣው በግልጥ መንገድ ሊገለጥ ይገባል። ልክ ያጣ ነገር እኮ ነው እዬታየ ያለው። ቲም ጃዋር እኮ ስለመምራቱ ምንም አያጠራጥርም።

ራስ እግሩ እኮ ህዝብ የሚያሸብር እና ስጋትን ያዘመተ ድርጊት ነው እዬተፈጸመ ያለው። ፋታ ጠፋ እኮ? ለዛውም ጉድጓዱን ህወሃትን አስቀምጦ። የሚገርመው አገር ጠቅልለው የገቡት የቆረበ ሰው ይመስል አፋቸውን ዘግተው በተረታው መስመር የተሰጣቸውን ብቻ እዬከወኑ ይገኛሉ። ድንቅ ያለኝ ደግሞ ስንት ጊዜ በሚበላው የኮሚሽን አባልነቱኝ እሰዬው ብለው መቀበላቸው ነው። የ እነሱን ያቋቋሙትን ድርጅት በወኪል ሊመሩት ይሆን? ጥገኝነት ስልምን አስፈለጋቸው?

ወደ ቀደመው ምልሰት ሳደርግ ነገረ ኦሮምያ ሩጫ ነው፤ ጥድፊያ ነው ሥልጣን ቦታ ሁሉ ትንፋሽ ቁርጥ እስኪል ድረስ ማካለል ነው፤ የት ለመድረስ ነው? ልክም ደንበርም እኮ የለውም። ምንድን ነው ይህ ሁሉ ጥድፊያ በጥድፊያ የሆነው ነገር። 

ሁሉ ነገር ተጠቅልሎ ተሸጉጦ ቢያዝ ይወደዳል እንደ ጨርቅ እጥፍ እጥፍ ብሎ ቢከዘን። ይህን ያህል የሥልጣን ረህበተኛ ነበሩን? ሥልጣን እኮ ተፈጥሮን የሚቀይር ጉድ ነው። አዎን ጨካኝ ነው የሚያደርገው። 

እውነት ለመናገር ሱባኤ የሚያስገባ ነገር ነው። አገር እኮ በመንፈሰም በአካልም በሽብርም ተዋራ ነው ያለችው። ምንድ ነው ጉዱ? ለዚህ ነው ዕድሚያችን ሁሉ የታገልነው? ለዚህ ነበር ወጣትነታችን የገበርነው? ለዚህ ነበር ጤናችን ያጣነው?

ዜጋ በግሪደር እንዲታረስ? መኖር በግሪዳር እንዲታረስ? ተስፋ በግሪደር እንዲታራስ? ነፍስ መጠጊያ አጥታ ሜዳ ላይ ጠያቂም ተጠያቂም አልባ በግፍ እንድትንገረገብ? ለዚህ ነው የታገለነው? ለዚህ ነው የተሟገትነው? ለዚህ ነው ጤናችን ያጣነው? እኔ ጥሞና ጊዜ ላይ ቆይቼ ስመጣ ቸር ወሬ አገኛለሁ ስል የለመድኩት መከራ ነው የጠበቀኝ።

አይገባቸውም መከራ እና ጭካኔ እንዴት እንደሰለችን? እንዴት ብለን እንንገራቸው ይሆን? 3ሚሊዮን ህዝብ አገር ውስጥ ተፈናቅሎ በበቀል በቋሳ በፖለቲካ ትርፍና ኪሳራ፤ በኢጎ አርበኝነት በዚህ ደግሞ ስለ ነፋሻማ ዘመን ስለ መዲናዋ ይሰበካል? ትናንት አራስነት በእስር ቤት ነበር ዛሬ ደግሞ አራስነት በግሪደር ነው?

መጨረሻው ዳርቻው የዚህ ግፍ እና ጭካኔ የት ነው? ደሃዋም እኮ ሴት ናት? ደሃዋም እኮ ሰው ናት? ደሃውም እኮ የፈጣሪ ፍጡር ናት? ለመሆኑ በዚህ ሰሞናት አንቅልፍ ተኝቶ የሚያድር፤ እህል ውሃ ቀምሶ የሚያድር የለውጥ መሪ ነኝ የሚል፤ ተደመርኩ ተባዛሁ የሚል ነፍስ ይኖራልን? አሁን እኮ የሱባኤ ጊዜ ነው። ነነዌ እኮ ያለው ኢትዮጵያ ውስጥ ነው ለዛውም በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ።

እንዴት አይገባንም? ሰርክ ባልተቋረጠ ሁኔታ ዕንባ፤ ሞት፤ እንግልት፤ መዘለፍ፤ መሳደድ፤ መቼ ነው የሚያበቃው? እነሱ ስለፌደራል ቋንቋ ይተረኩልናል እነሱ ስለነገ ለምለሚቱ መዲና ይተርኩልናል ዛሬ ነፍስ መጠጊያ አጥታ በዋይታ እና በኡኡታ ላይ ትገኛለች። ካልተቻለበት አልቻልንበትም ተረከበን ህዝብ ይገባል። 

ተጠቅለሎ መንፈሱን ለጠለፈው አካል ለጃውርውያን አስረክቦ አጭብጭቦ መቀመጥ ነው። የተገለበጠ ማጅራት የሆነ ጉድ።፡ 

ለዬትኛው ጊዜ ነውስ ይህን ያህል ትርምሱ? ማን ስለቀጣዩ ቅንጣት ሰከንድ ያውቃል? ማን ነፍሱን ቋጥሮ ይዞታል? ስንት መከራ ስንት ለቅሶ ስንት ዋይታ ስንት መሰደደ ስንት ተስፋ ማጣት በባጀባት አገር ዛሬ እነሱ ጥድፊያ ላይ ናቸው - አነጋውያን፤ በተገኘው ቀዳዳ ሁሉ ቦታ ለመያዝ፤ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ የኦነግን ዓላማ እና ተልዕኮ ለማስፈጸም ደፋ ቀና ነው።

·       ሰው ከሰው ተፈጥሮ እንዴት ስለሰው አያስብም?

ነፃነት ፍቅር ሰላም መቻቻል እኮ በመሆን ውስጥ ያሉ ሰፋፊ የመኖር ህዋሶች ናቸው። ክልልህ ያለውን እያፈናቀልክ እኔ የኢትዮጵያ ነኝ አገርም እመራለሁኝ በምንም መስፈርት አያስኬድም። እኔ እውነት ብናገር አሁን እንዲቆም አዘዙ የሚባለው ዶር ለማ መገርሳ እንደሆኑ ነው እምሰማው። በሳቸው ዘመን በሳው ክልል አንድ ነፍስ ዋስትና ያጣል የሚል ህልም አልነበረብኝ።

ሰው በሰው እንዴት ይጨክናል? ሁሉም አኮ እናት አለው፤ ሁሉም ልጅ አለው። ሁሉም ትዳር አለው። በእኔ ቢደርስ ተብሎ እንዴት አይታሰብም። ይሉኝታ የሚባል ደግሞ አለ። ይሉኝታ የለም ያፈጠጠ ጉድ ነው አሁን ያለው። 

ባልተስተካከል በዘበጠ ቅርቃር መንገድ ላይ ለውጡ እንዳለ ማወቅ ያለባቸው ይመስለኛል - የለወጥ ሐዋርያ ነን የሚሉት። ያው ግርባው ብአዴን ልብ ስለተገጠመለት በለመደው ዝንፍል ይደብዝዝ …

 እነ ለማ ቲም ለሽብርተኛው ቡድን ስልጣኑን በይፋ በአደባባይ ያስረክቡና ዓለምም እኛም እርማችን እንውጣ። ለክርስትና እምነትም መጪው ጊዜ ከባድ ስለሚሆን አቅም ያለው ይተጋበታል። ይለይለይለት ቁርጡ። ካልጎሼ አይጠራምና። እነሱ ሽፋን ግን ለውጥ ለውጥ እዬተባለ በግርዶሽ በሰባዕዊ መብት ረገጣ እና በኢትዮጵያዊነት የዜግነት ጭፍለቃ ተከባብሮ ለመዝለቅ ቀኑ እያለቀ ነው። ስንቱ ይቻል? ስንቱን እንሸከም?

ኢትዮጵያ አሁን ከቀደመው በላይ አስፈፊ ሁኔታ ላይ ነው ያለችው። ወይ እነ ቲም ንጉሱ ወይ ቲም ለማ ምርጫው አንድ እና አንድ ነው። „አለባብሰው ቢያርሱት በአረም ይመለሱ“ ነው ….

ብሶተኛው ኢትዮጵያዊ ዜግነት ዛሬም ያነባል?
ለእውነት ቀጠሮ አይስፈልገውም!



                                                የኔዎቹ ኑሩልኝ።

                                                መሸቢያ ጊዜ። 

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።