ሁሉም ነገር ያስፈልጋል ሁሉም ነገር ጠቃሚ ነው ከሁሉ ግን የሉዑላዊነት ከብርን ማስጠበቅ የበለጠ ነው።
እንኳን
ደህና
መጡልኝ።
ጠጣር።
„ኖን። መንገዳችን እንመርምር እና እንፈትን።
ወደ እግዚአብሔርም እንመለስ።“
ሰቆቃው ኤርምያስ ፫ ቁጥር ፵
ከሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
01.02.2019
ከእመ ዝምታ ኪሲዊዝሻ።
· ጠብታ።
ውዶቼ እንዴት ናችሁ። ዛሬ ቪንቲ ከፋፍቷታል። እንዲህ ከፍቷት እኔ ደግሞ ጫና ብጨምርባት
ሆድ ይብሳታል ብዬላችሁ መውጣቱንም ተውኩት እንጂ ዛሬ የዓመቱ ቅዳሜ ብዙ ነገር ታልሞለት ነበር። የውርጩ ገጹ ጭጎጎት አስመስሎ
ይታመሳል።
ጠብታውም መጣሁ ሄድኩ እያለ እሱን እራሱን በተፈጥሮው ውስጥ ሆኖ ይነሳስተዋል። ፊታውራሪ ጉምም አይቅርብኝ ብሎ አብሬ
ልታደም ብሎ ዕለቱን የሙጥኝ ብሏል። ሻሾ ግን ብቅ አላለም ትናንት መክሰስ ዛሬ ቁርስ አልሰጡትም መሰል። እና ሥርጉቱሻ በሶስት
በአራት ለመሰለቅ ስለምን ትታደም እትዬ ዛሬን? ካሊሟን ደራርባ ጉብ ብላ እስቲ ብራና ሆይ! ይትናንቱን ልቀጥልህ ብላ ኮቢ ፍለጋ
ስትማስን ሳይጠሩሽ አቤት በራሷ ጊዜ ከች።
· መነሻ።
Ethiopia : [አዋረዳት] ጠ/ሚ አብይ ይህቺን ሃገር እንደ አዜብ መስፍን የበዘበዘ እና የሰረቀ ሰው የለም የቀለጠች ሌባ ናት
· የፍሬ ነገር የሆድ ዕቃ።
„በመጀመሪያ የተከበረው ምክር ቤት እንዲገነዘበው የምፈልገው ኢትዮጵየ ውስጥ ወንጀል
ሰርቶ ወንጀል በመሠራቱ በመንግሥት ዲክለር
ተደርጎ ያልታሰረ ሰው የለም። ልዩነቱ መንግሥት ባዘጋጀው እስር ቤት ውስጥ መንግሥት እዬጠበቀው፤ መንግስት እዬቀለበው
መታሰር እና እራሱን ማሰር ካልሆነ በስተቀር አልታሰረም የሚል እሳቤ በግሌ እኔ የለኝም። ምክንያቱም ሰው የማይታሰረው በህሊናውን
እና እማይተሰረው ደግሞ ፊዚካሊ በመንቀሰቀስ ነው። ሰው ገድለህ፤
ወንጀል ሰርተህ ህሊናህ ነፃ ሆኖ መተኛት አትችልም። ያው የታወቀ ነገር ነው። በነፃም መንቀሳቀስ አትችልም። አንድ ቦታ እራስህን
አቅበህ መኖር ወዶ ታሳሪ መሆን እንጂ ያልተሰረ መሆን አይደለም። በእኔ እምነት ሁሉም ታስሯል።“
የጠቅላይ
ሚኒስተር አብይ አህመድ አመክንዮ እውነት ነው። አመክንዮው ይህ ከሆነ ግን ተቀሟት ስለምን አስፈለጉ? ህግ ማርቀቅስ ማጽደቅስ ውሎው
የት ይሆን? ፓርላማው እራሱ ስለምን ተቋቋመ? የፌድረሽን ምክር ቤትስ ምንሰርቶ ይደር?ፌድራሉ ጠ/ፍቤት ሆነ የባታቾችስ? አቃቢ ህግስ? የህግ ፋክሊቲዎችስ አዳራቸው ምን ይሆን
ነው ቁምነገሩ?
ሌላው መንግሥት ህግ የሚፈልጋቸውን ሰዎች እስኪመጡ መጠበቅ ወይንስ ካሉበት ድረስ ሄዶ በህግ ሥር ማድረግ? የትኛው
አግባብ ነው የኢትዮጵያ መንግሥት ህግን ሲያስፈጽም የኖረው? እንዲህ አንጋጦ እያዬ መና ከሰማይ እዬጠበቀ ወይንስ ባደራጀው አካል
አስፈጻሚነት እዬተንቀሳቀሰ?
በተን ሲል።
ክብረቶቼ ይህን ስንኝ ጠ/ሚር አብይ አህመድ በትናንቱ የፓርላማ ጉባኤ ለቀረባላቸው ጥያቄ
የመለሱት ታዳሚውንም ከልቡ ያንከተከተ ነበር። እኛም በያለንበት ሃላፊነት ስለሌበን ውሽክ ያደረገ አብይ ጉዳይ ነው። በህሊና የመታሠሩንማ
ዘረፋውንም፤ ግድያውንም በደሉንም ሁሉን ያሻቸውን ያህል ተፍነሽንሸውበት፤ ደልቀውበት ዛሬ ፍትህ አፍጥጦ ሲመጣ ውጭ አገር የወጡት ሳይቀር በህሊናቸው እስረኞች ናቸው።
አይደለም መቀሌ ላይ
ከዛ በዛው በፓርላማ ውስጥ አብረው የታደሙትም ቱባ ቤተ ፓርላማ አባላት ፊት ለፊት ጉብ ብለው እየታደሙበት ነው። ድምጽም ሰጪም
ናቸው። ድምጽም አልሰጥም ባይ ናቸው፤ በታዕቅቦም መብታቸው የተጠበቀ ነው። ወንጀለኞች በወንጀለኞች ላይ ለመወሰን እንዴትስ ይቻላቸዋል?
እዛው ፓርላማ ውስጥም የወንጀሉ መረብ ዘርጊ እና መሪዎች አደራጆች አቀናጆች ስላሉበት። አሁን የእነሱው የእጅ ሥራ ነው የሚሊዮኖች በአገራቸው በገፍ የመፈናቀል ሚስጢር።
እነሱ ከነከረባታቸው ይሁን ቀሚሳቸው ጤነኛ
ነን ቢሉም እስር ቤት ሆነው ስለመታሰራቸው አብረው ይመክራሉ። እነሱም ታሰረው ነው ጉባኤውን የሚታደሙት ውሽክታውንም አብረው የሚያስነኩት።
በአነሰም በበዛም በተለያዬ የፖለቲካ ፍላጎትም የሰው ነፍስ እንዲጠፋ ምክንያት የሆነ የፖለቲካ ሊሂቃንም ሁሉ በዚህ ማዕቀፍ ውስጥ አሉበት። የአቤል ደም
ምንጊዜ ይጮኻል። ከደም ነፃ የሆነ ብቻ ነፃ ነው። የሰው ደም ክፉ ነው። ልጅም አያወጣም።
ስለዚህ በመታሠር የሰው ነፍስን ያሰቃዬ፤ የገደለ፤ የበደለ በአንድ ጎራ፤ በመፈታት 27 ዓመት ሙሉ የተሰቃዬ የተገደለ ሁለቱም መሳ ለመሳ ነው የሚገኙት።
ራሱ ከስጋት መውጣት፤ ከዛ መገላገል መፈታት ነው። አዬሩ ራሱ
እግዚር ይፍታህ ተብሏል። አሁን በዬቦታው ምክንያት እዬፈለገ ሰው የሚሰበሰበው እኮ የመፈታቱ ፍቅር ናፍቆት አልወጣለት ብሎ ነው።
ብርቅ ሆነበት። መሽቶ እስኪነጋ ካቴንን የሚያልመው ምልዕት ሁሉ እድሜ ለአማራ የህልውና ተጋድሎና ኦሮሞ ንቅናቄ፤ ተጋድሎውን ላዳመጡትም አስተዋዮች ዛሬ ከዛ በተጋድሎው ተገላግሏል።
ስለሆነም አጋጣሚው ሁሉ እንደ የፌስታ ቀን ደምቅ ብሎ የሚገኘው በዚኸው ነው እንጂ
የሚበላውም የሚጠጣውም ካለፈው የተሻለ ነገር በ9 ወር ተሟልቶለት አይደለም። በ9 ወር ቀርቶ በቅርብ ዓመታት ይህ መከራ አይቀረፈም።
ግን ነፃነቱ የሰጠው እፎይታ ህዝብ ምክንያት እዬፈለገ የነፃነቱን ክብር እና ልዕልና እያደመቀው ይገኛል።
አሁን እኔ የሰሜን ጎንደር የዝግጅት ነገር ግርም ነው የሚለኝ። ዕለት እለት ፌስታ
ነው። ፍንደቃ ነው። ስለምን ብዬ ስጠይቅ ህዝቡ በሙሉ እስረኛ ስለነበር ሊጠግበው ስላልቻለ ነፃነቱን ስለመሆኑ ይረዳኛል። ባህርዳርም
አዲስ አባባም እንዲሁ ነው። ምክንያት ካገኘ ነፃነቱን በዬዕለቱ ያወድሳል። በተገኘችው ቀዳዳ ሁሉ ይጠቀምባታል።
ሃይማኖታዊ ይሁን
አዘቦታዊ አመክንዮችን እንደ አድዋ ድል ነው ዛሬ ላይ የሚመለከተው ህዝቡ። ስለምን የበደለው መንፈስ እራሱ በነፍስ ወከፍ ታስሯል፤
የ27 ዓመቱ እስረኛ ደግሞ በነፍስ ወከፍ ከእስር ተላቋል። ኦሮምያ ላይ ግን እንደ ጠዬመ ነው የነፃነት
ብርሃኑ ታፍኗል። ተቀፍድዷል። ለዛውም የሥነ - ልቦና የበላይነቱ ችግኝ በተሟላ ሙቀት አለስልስ እያለ …
ወደ ቀደመው ጉዳዬ ስመለስ „ አንድ ቦታ እራስህን አቅበህ መኖር
ወዶ ታሳሪ መሆን እንጂ ያልተሰረ መሆን አይደለም። በእኔ እምነት
ሁሉም ታስሯል።“ ይህን
ጠጣር አመክንዮ ባሊህ ማለት ስላለብኝ ነው ይህን ጹሑፍ የጻፍኩት።
በዚህ ውስጥ ወንጀለኛ መቅጫ ህጉ እና ሥርዓቱ፤ የፍትሃብሄር ህጉ
እና ሥርዓቱ፤ የህጎች ሁሉ የበላይ የሆነው ህገ መንግሥቱ፤ የጸጥታ አስከባሪ አካላቱ እና ህግ አስፈጻሚው ሆነ ተርጓሚው አካል፤ የፍትህ ሥርዓቱን
ስናይ አንድ ሰው ባጣፋው ጥፋት ህሊናው ስለቀጣው ታስሯል ከተባለ እነዚህ አካላት ስለምን አስፈለጉ ወደሚል ይወስደናል። መንግሥት
እራሱ ህግ ማስከበር እስካልቻለ ድረስ ስለምን ይኖራል ወደሚልም በቀጣይ በተደሞ ይወሰደናል። እንዲህ ልቅነት ቀጥል ከተባለ። ወይንም ልቅነት በትርጉም ተቃንቶ ምንም አይደለም እንልመደው ከተባለ።
ስለዚህ በትርጓሚ
መቃናት መብራራት ይኖርበታል አገላለጹ። እንዲህም ሁሉም ታስሯል ከተባለም የክፉ ነገር ቸረቸራ ሳጅን በረከትም እኮ ከታሰሩ ቆይተዋል።
የትም ቦታ በነፃነት መንቀሳቀስ አይችሉም። በስውር መረብ ነው ንደቱን ሲያስከነዱት የነበሩት። ስለዚህ የአማራ ክልል የወሰደው እርምጃ ትክክል አይደለም ማለት ይሆን በዚህ አገላለጽ? አሻፈረኝ ያለ እንደልቡ ይሁን ይሆን? ነገስ ትግራይ ላይ የሽምቅ ውጊያ ሌላ ዘመቻ ይኖርን?
መንግሥት አቅም ሰለሌለኝ ወይንም ላስከፋው ወይንም ልጫነው የማልፈልግ ህዝብ ስላለ፤
ወይንም የምፈራው ሌላ ህዝብ የማያውቀው ጉዳይ ስላለብኝ በህሊናው እንደታሰረ ቆጠሬ በዚህ እራሴን አሳምኜ ህዝብንም አግባብቼ ህግ
የማስከበር ሃላፊነቴን ለነገ እንደቀጠርኩት ወይንም በመንፈስም በአካልም እንዳሰርኩት ተቆጥሮልኝ መታሰሩ በሪሞት ኮንትሮል በአሻጋሪ
እያዬ ይበል፤ ጎሽ! ይበለኝ ከሆነ በምንም አመክንዮ በምንም የህግ አግባብ ተቀባይነት አይኖረውም።
መንግሥት ከህግ በላይ የሆኑ ዜጎቹን ህግ በማሰከበር ከህግ በታች ስለመሆናቸው እርምጃ
ወስዶ ማህበረሰቡ እንዲያምነው ካለደረገ ነገም በዬመንደሩ አሻፈረኝ የሚሉ ጉልበተኞች እዬተፈጠሩ ዘመነ መሳፍንት ስለመመለሱ ምንም
ማሰተባበያ ማቀረብ አይቻልም። ለመሆኑ መንግሥት ማሰተዳደር በማይቻላቸው ክልሎች፤ ማዘዝ በማይቻላቸው ክልሎች በምን ሁኔታ ይሆን መሪ
ነኝ ብሎ ደፍሮ መናገር የሚችለው?
ጉዳዩ እዬበሉ እየጠጡ መታሰር እና እና እየፈሩ መኖር አይደለም። ይህ የሉዕላዊነት ጉዳይ ነው። ከህግ በላይ የሆኑ ሰዎችን በህግ ሥር የማድረግ አቅም መንግሥት
ከሌለው መንግሥት ነኝ ብሎ ለመናገር በጭራሽ ድፈረት አይኖረውም። እዛም ቢኖሩ ታስረው ነው እዚህም ቢመጡ ታስረው ነው አያስኬድም።
አቅም አጥቻለሁኝ አንድ ነገር ነው።
ወይንም የማይደፈረውን መድፈር ተስኖኛል ሌላ ነገር ነው፤ ወይንም እኔ ¾ኛው የኢትዮጵያ
ክፍልን ነው እማስተዳደረው ከተባለም እንዲሁ ሌላ ዘይቤ ነው። በአንድ አገር ውስጥ ሁለት ሦስት አፈንጋጭ ተቀምጦ ይህን መሰል አመክንዮ
ማቀረብ በፍጹም አግባብም አይደለም ከህግም፤ ከፍትህ ሥርዓትም፤ የሰባዕዊ መብት የማስከበርም ተልዕኮም አንጻር ይሁን ከፍ ካለው
የሉዑላዊነት አቅምም አንጻር።
የኢትዮጵያ መንግስት በጀቱን ማቆም ይችላል። በመንግሥት ሥርዓት አልገራም ላሉ የፌድራል አባሎቹ
የህውሃት ከሥልጣናቸው ማንሳት ይችላል። ድርጅቱን ህወሃትን በፓርላማው ውስጥ አስወስኖ ከግንባሩ ማሳገድ ይችላል። እራሱን ችሎ እንደ
አንድ ተፎካካሪ ፓርቲ ለመወዳደር እራሱ በህግ መንግሥቱ ጥላ ሥር ሲሆን ብቻ ነው።
የዚህ መንትዮሽ ጣምራ ችግር ዋነኛው ምክንያት በጉለሌው ኦነግ ላይ ቅጥ ያለው አናታዊ እርምጃ
እንዳይወሰድ አዲሶቹ የገዳ መሪዎች አቶ በቀለ ገርባ እና አቶ ጃዋር መሀመድ ፌድራሉ መንግሥትን የመጫን ሁኔታ ነው በዛ የሽምግልና
አምክንዮ የታዬው። ነገ የአባ ገዳዎች የመምራት አቅም ወደ ፌድራል ለማምጣት ሀሁ እዬተባለ ነው። ሌላ የልምምድ ሁኔታ።
ይህን መደፈር
ስላልቻለ ፌድራል መንግሥቱ ያን ካስታመመ የግድ ትግራይ ላይ በለዛለዞ ጨዋታ ጉዳዩን እያስታመመ ይገኛል። በሁለቱም ዘርፍ የኢትዮጵያ
የሉዑላዊነት ጉዳይ ነው። ለሉዑላዊነት አመከንዮ ደግሞ ቆልምጫ አንዲት ስንዝር አያስኬድም።
የኢትዮጵያ ህዝብ ቻይነቱ እስኪከር ድረስ ነው። ሲከር ትእግስቱ መበጠሱ ሲሞላም መፍሰሱ
አይቀሬ ነው። እንኳንስ በስንት ጥበብ እሽሩሩ ተብሎ የተያዘው 10 የኦሮሞ ድርጅቶች ዝንቅ ቅይጥ ፍላጎት ቀርቶ በወጥ ፍላጎት ላይ የቆመው ህወሃት
እንኳን አልቻለውም።
አሁን ባገኙት የሥነ - ልቦና ሙላት እንኳን ብስለት አልቦሽ ጉዞ ላይ ናቸው ያሉት የኦሮሞ 10 ድርጅቶች። ዕድላቸውን አሳልፈው ለመስጠት ሾልከው እንደለመደባቸው
ለመቀረት ነው ሌት እና ቀን እዬማሰኑ የሚገኙት።
ይህ የአብይ ካቢኔ ባይቀጥል በለመዱት መልክ ተበትነው እንደሚቀሩ አላስተዋሉትም፤ ዘመን
ተማልዷቸው ሁለት እንደ እናት ጡት ጥበበኞች አግኘተው ፍላጎታቸውም ዝበት ሳይኖርበት በማስታመም እና በመቻቻል ያለው ሂደት በራሱ
ስለታደሉት የተገኘ ነው።
ምንም ሳይቀርባቸው ሁሉን አልባብ ባልባብ በሆነ ነገን መግራት … ያለው ብልሃት ይኸው ነው። ለዚህም ይመስላል
ዶር ብረሃነመስቀል አበበ "የኦነግ ወራሽ አብይ ነው ያሉት።" አብርሃም ወአጽብሃም በስልት ነገሮች እየተከወኑ ስለመሆኑ ለማጠዬቅ፤
ለነገሩ እሳቸውም ሳት ብሏቸው ያወጡት ፍንጭ ነው።
የሚነግሡ ልቅናቸው አብዛኛው ከእነሱ ሥነ - ልቦና ውጪ የሆኑ አይደለም እንኳንስ ሌላው።
አፍቃሪው አጋዢ እረጂው ደግሞ ያው የቸርነቱ ንጉሥ የኢትዮጵያ ህዝብ ነው። እነሱ ያላከበሩትን ወርቅ እኛ አክበረን ከብከብን ያለነን
መንፈስ ሁሉ ሸልመን ተግተንበታል። የኦሮሞ ሊሂቃን አክቲቢስቶች ግን ይህን እንኳን በፍልስፍና አመክንዮ መተርጎመም ማመሳጠርም
አልተቻላቸውም። ይህ የመመጣጠን አምክንዮ ጉዳይ ነው።
ስለዚህም ነው ነገሮችን የታዘቡ ነፍሶች አልፎ አልፎ በተለምዶ ከማዬት ወጣ ያሉ አስተያዬቶች በርከት ብለው የሚታዩት፤ የአያዬዝ እና
የአጠቃቀም ፍገት ስላለበት የኦሮሞ ሊሂቃን ፍላጎት እና ጠርዝ። ሁሉ ተሁኖላቸው እርካታቸው ደግሞ ወና ነው።
ሥልጣን ላይ የወጡት ሁሉ ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ውስጣቸውን ያሰዩናል። ልብ ያለው ደግሞ
ሸብ ያደርጋል። ሌላው ቀርቶ የግንጫ ተጋድሎ በአማራ ታገድሎ ባይታገዝ የትም አይደርስም ነበር። የእነሱም የ40 ዓመት ትግል ምንም
ፋይዳ ባለው ነገር አልተቋጨም።ይህን እንኳን የፖለቲካ ሊሂቃን ነኝ ባዩ ፈቶ አፍታቶ በትኖ መተንተን አልተቻለውም። ስለምን? "አማራ" የሚል አስፈሪ ተፈጥሮ ስላለ።
እንኳንስ የግንጫው የሳብያው ማሰተር ፕላንን ብቻ ተመርኮዙ የወጣው መሪም በቅጡ ያልነበረው
ብሶት ያፈነዳው ንቅናቄ ቀርቶ በአፍሪካ የመጀመሪያ የሆነው ጽኑው እና በቅጡ የተደራጀው „የድምጻችን ይሰማ ተጋድሎ“ እንኳን ሥርዓት መለወጥ
አልቻለም። ድርጁ ነበር። መሪ ነበረው። ስልቱም አጓጊ እና ልብ አንጠልጣይ ነበር።
ከዚህ ባለፈ ብአዴን የተጫወተው ሚና ዕውቅናውም ሆነ የተደማጭነት አቅሙ በማግኘት እረገድም ባክኖ የቀረ ጉዳይ
ነው። አንድም የኦሮሞ ሊሂቅ ሆነ ሌላውም ሲያነሳው ሰምቼ አላውቅም። በራሳችን በራሳችን ልጆች ሲባል ነው የሚደመጠው። ትርፉም እንዲሁ። ለዚህ
ነው የአብይ ካቢኔ ኢንጂነር ታከለ ኡማን ከፍ አድርጎ ሦስተኛ ሰው አድርጎ ለማውጣት የታከተበት፤ የደከመበት የሄደበት መንገድ ሳያፈራ የቀረው። መክኖ ነው የቀረው። አማራ
መሬት ሄደው ዜናችን አልነበረም። ድንቅ ወዘተ የሚባለው ዜና ምናችን አይደለም ...የፈለገ የተፈጥሮ ቅንነት ቢጫነንም ለለውጡ ማንዘርዘሪያችን ከአፎቱ አይጠፋም ... እንጥፍጣፊም ቢሆን።
· ውሳኔ ለይደር ማግስትን ያዳክራል።
ወደ ቀደመው ምልሰት ሳደርግ በጉሌለው መንግሥት በሽምግልና የተሸበበው የአገር ሃብት ዘረፋ ይሁን የሰብዕዊ መብት ረገጣ ሆነ ህግ
ትግራይ ላይ ተፈጻሚ ለማድረግ ያለው ዳገታም ጉዳይ በዚህ ዙሪያ ጥርት ያለ አቋም እና ውሳኔ ሳይዘገይ በጥራት መወሰን ካልተቻለ
„አለባበሰው ቢያርሱት ባረም ይመለሱ“ ይሆናል ማለት ነው። ሁለት አፈንጋጭ ቡድን አኩል እርምጃ ሊወሰድባቸው ይገባል። ሌላም አፈንጋጭ
ከመጣ እንዲሁ። ምክንያቱም አገር በወሳኝ የህልውና
ጉዳዮዋ ላይ አትደራደርም እና። የውጫሌ ውሉን ልብ ይሉ …
ከዚህ በላይ ህዝብ በመንግሥት ላይ ያለው የዛሬው ሙሉ ታማኝነት ደግሞ ጸንቶ ይቀጥላል
ማለት አይቻልም። የልብ ለልብ ግንኙነቱ በእውነት ማዕቀፍ ካልተሸመነ። በዬዘመኑ እኮ መሰል ወቅታዊ የድጋፍ ጎርፎች ነበሩ። ያን
የድጋፍ ጎርፎች አድምጦ አጽንቶ ለማስቀጠል የትናንት ሳይሆን የዛሬ የጠራ ብቁ ተግባር ወሳኝ ይሆናል። ቅንጅትን ሚሊዮኖች ተቀብለውታል።
ዛሬ ያን መንፈስ እናምጣ ቢባል አይቻልም። በተሰጠው ፍቅር ልክ ፈተናውን ጥሶ በስልት እና በጥበብ መንፈሱን የሚያስቀጠል መሪ ስላልነበረው።
መስውዕትነቱ ባክኖ ነው የቀረ።
የሰኔ 16 ቀን የ2010 መስዋዕትነትም ባክኖ ከስሎ እንዳይቀር ያን ድጋፍ ለማስቀጠል
በመሆን ውስጥ መዝለቅን ይጠይቃል። ሁሉም ነገር
ያስፈልጋል ሁሉም ነገር ጠቃሚ ነው ከሁሉ ግን የሉዑላዊነት ከብርን ማስጠበቅ የበለጠ ነው። ሌላው ቀርቶ ያልታዬ ያልተመረመረ ጉዳይ
አለ። ዶር ለማ መገርሳ አቶ ደመቀ መኮነን የከፈሉት መስዋትነትም አለ። ያም ባክኖ መክኖ አሮ እንዳይቀር መማስን ያስፈልጋል።
አገላለጹ ለእኔ ከልቤ ጠብ አላለም። ሰው በድሎ ህሊናው መታሰሩ የታወቀ ነው። ግን
ለህሊናው ብቻ የሚተው አይደለም። ህግ የሚወጣው
ለንባብ ወይንም ለማስፈራሪያ ሳይሆን በሰዎች ዘንድ ተፈፃሚ ይሆን ዘንድ ነው። ማንም ከህግ በላይ ካልሆነ ከህግ በላይ አለመሆኑ
መሬት ላይ ወርዶ መተግበር ይኖርበታል።
ይህ ከሆነ ሰው ህሊናው የሚዳኘው ከሆነ የህግ ፋክሊቲዎችን፤ የጸጥታ አስከባሪ አካላት
መዋቅሮች፤ ማሰልጠኛ ተቋማትን በዓዋጅ መዝጋት ነው። የሚገርመው እዛው ፓርላማ ውስጥ አንድም ሰው ይህን ሞግቶ የተነሳ
የለም። ልክ ስሜን አሜሪካ
ያሁሉ ሊሂቅ፤ ያ ሁሉ የፖለቲካ ድርጅት አጨብጭቦ ጠ/ሚር አብይን እንደሸኛቸው ማለት ነው።
ያን የማይገኝ ዕድል እንደተቃጠለ ሸማ ነው እኔ የማዬው። ማፍቀር ማድነቅማ ከሥርጉተ
በላይ ላሳር ነው። ግን መሞገት በሚገባቸው ደግሞ ከጥዋቱ ነው የሞገትኳቸው። ለሳቸውም ለኢትዮጵያም ጤናአዳሙ ጉዳይ ይኸው ነውና።
የጥበብ ሰው ካለተተቼ ሙቷል መክሊቱ ማለት ነው። እሳቸው ደግሞ የወጣላቸው የሥነ - ጥበብ ቤተኛ ናቸው፤ ያውም ባለቅኔ። ስለዚህ መተች
ቢጠቅማቸው እንጂ የሚጓዳቸው አይደለም።
ጠ/ሚር አብይ አህመድ መሞገት ባለባቸው አምክንዮ መሞገት አለባቸው። በስተቀር ነገ የተለመደውን በፍጹም ሁኔታ ያንገሸገሸን የመሪዎች አትንኩኝ ባይነት እና የማንህሎኝነት አባዜ እኒህ ሙሴ
የማይከተሉበትም ምንም ምክንያት የለም።
ሞግቷቸው። ለሳቸውም እንደ ሰውኛ የመሆን ጸጋ ስለሆነ ያጠነክራቸዋል፤ ያበረታቸዋል፤ ተጨማሪ ጉልበት ይሰጣቸዋል። ለሳቸው
ብቻ አይደለም ጠ/ሚሩ ያለው እኔም አለኝ ለሚለው ፖለቲከኛም እንዲሁ የሚያሰተምር ነው የሚሆነው። ለነገሩ ፓርላማ ላይ የነበረው የጠያቂ ሰዎች ምርጫ እና የንባብ አቀራረብ ድርጅታዊ ሥራ ይሆን የሚልም የተሰረከረከ ነገር አለ ...
ወደ ቀደመው ምልሰት ሲሆን ይህ ሰፊ የአገር መዋለ መንፈስ የተቀጠቀጠበት ወንጀል፤ በሉላዊው ዓለም ስንት የሰብዕዊ
ድርጅቶች የደከሙበት ጉዳይ፤ በገንዘብ፤ በጊዜ ቢተምን የ27 ዓመቱ ቀርቶ የ7 ቀኑ ግምቱን ማውጣት አይቻልም።
ለዚያ ተጠያቂ መሆን
ያለበትን አካል „በመንፈስ ካሰረንው ይበቃዋል“ ከሆነ ቀድሞ ነገር ስለምን የእስር ትእዛዝ ወጣ? ስለምንስ የፌድራሉ አቃቢ
ህግ መግለጫ ሰጠበት? ወይ አለመጀመረ ነው ከጀመሩ ደግሞ ከፍጻሜ ማድረስ ነው። „ወትሮ ባልዘፈንሽ ከዘፈንሽ ባላሰፈርሽ ነው“
በነገራችን ላይ ይህ ይታሰር ይወገድ ይፍረስ በሚለው ላይ ጠንከር ያለ ጹሑፍ ጽፌ እንኳን አላውቅም።
ምክንያቱም እዮባዊነት የሚጠይቁ ብዙ ነገሮች ስላሉ፤ ጥገናዊ ለውጥ ስለመሆኑ ስለማውቅ፤ በሌላ በኩል ጥበባዊ ጉዞው እና ፈተናዎችን
ሥራዬ ብዬ ስለምከታተላቸው ከርር ያለ፤ ድርቅ ያል ዕይታ በሁሉም መስክ የለኝም፤ አሁንም ከተነሳ አብሶ በጠ/ሚር ደረጃ ግን መሞገት
ስለሚገባው ነው … የተሰጠው ማብራሪያ እና መሆን የሚገባው ጉዳይ በትርጉም መቃናት ስላለበት።
በወንጀል የተጠረጠሩ ግለሰቦችን መደበቅና እንዳይያዙ ማድረግ የፍትህ ስርዓቱ ተግዳሮት መሆኑን የፌደራል ጠቅላይ አቃቢ ህግ ገለጸ
·
ይህን ጠ/ሚር አብይ አህመድ ሲገልጹት እንዲህ ብለው
ነው።
„በመጀመሪያ የተከበረው
ምክር ቤት እንዲገነዘበው
የምፈልገው ኢትዮጵያ ውስጥ
ወንጀል ሰርቶ ወንጀል
በመሠራቱ በመንግሥት ዲክለር ተደርጎ ያልታሰረ ሰው የለ“
ይህ ከሆነ ስለምን አቃቢ ህግ በዛ መልክ
ማቅረብ አስፈለገው ለተወካዮች ምክር ቤት። አቅቶኛል እገዙኝ እያለ እኮ ነው …
„ አንድ ቦታ እራስህን አቅበህ መኖር ወዶ
ታሳሪ መሆን እንጂ ያልተሰረ መሆን አይደለም። በ እኔ እምነት ሁሉም ታስሯል“
በዚህ መለክ ይታይ ከተባለ
ግን በወንጀል የተጠረጠረ ሰው
ወንጀለኛ አለመሆኑስ በምን
አግባብ ተጣርቶ ከወንጀለኝነት
ተጠርጣሪነቱ እንዴት ነፃ
ሊሆን ይችላል?
በህግ አግባብ ታይቶ ወንጀለኛ መሆኑ ከተረጋገጠስ ከወንጀለኛ ድርጊቱ
እንዴት ነው ማረም የሚቻለው
በምንስ አግባብ? ለህግ
ተማሪዎችም አንድ ትልቅ
የምርምር ማዕከላቸው የሚሆነው
እንዲዚህ ያሉ ነገሮች
ሲጠሩ፤ ተበጥረው ሲለዩ
ብቻ አይደለም ወይ?
በሌላ በኩል ወደፊት ስለሚፈጸመው የወንጀል ዓይነት ይሁን የሰብዕዊ መብት
ጥሰትም ህሊናው ይዳኘዋል፤ እረፈት ይነሳዋል ተብሎ ሊታይ ነው? አስተምህሮቱ በዚህ በአምክነዮ
እስጣ ገባ ሳይሆን በህግ አተረጓጎም
እና አፈጸጸም ስርዓታዊ መንገድ
ካለተከተለች አንዲት አገር
ወንጀልን ለማስቀረትስ በምን
አግባብ ይሆን የሚቻለው?
ስንቱስ ነገር ነው
ተፈርቶ የሚዘለቀው?
ያ የተከወነው በእውቀት
ማነስ የተከናወነ አይደለም። ታቅዶ ተደግፎ ተደራጀቶ የተከወነ ነው። በሌላ በኩል ይህ አሁን ያለው የፈድራሉ
ህገ መንግሥት የፖለቲካ ውሳኔ እንጂ ህገ ህዝብ አለመሆኑ ይታወቃል።
በእርሾነት ግን ወደ
ህገ ህዝብ ለመቀየር
የሚቻለው ከአፈጻጸሙ ጥንካሬ
እና ድክመት ይሆናል። ነገር የህግ
አስፈጻሚ አካልን ስልጣን
እዬተጋፉ ከሆነ ጠቃሚውን የህግ አካል እና ጎጂውን ለመለዬትም ሆነ ለመመዘን አያስችልም። አሁን
ባለው የኢትዮጵያ ህገ መንግሥት "በህሊናው ታሥሯል" የሚለውን
ለጨዋታ ማሟያ ሳይሆን
በቀጥታ ህገ መንግሥቱን ምዕራፍ ምዕራፍ ሁለት በማዬት መቀሌ ላይ ያለውን ዕውነት የሚያሳዬን ይሆናል። የጥሰቱን መጠን።
አንቀጽ 9
የሕገ መንግሥት የበላይነት
1 ሕገ መንግሥቱ የሀገሪቱ የበላይ ሕግ ነው፡፡ ማንኛውም ሕግ ልማዳዊ አሠራር እንዲሁም የመንግሥት አካል ወይም ባለሥልጣን ውሳኔ ከዚህ ሕገ መንግሥት
ጋር የሚቃረን ከሆነ ተፈጻሚነት አይኖረውም፡፡
ይህ የሰሞናቱ የበቀላውያን እና የጀዋርውያን ጉዳይም ይመለከታል። በ አባ ገዳነት ደግሞ ብቅ የማለት ሁኔታ።
2 ማንኛውም ዜጋ፣ የመንግሥት አካላት፣ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ ሌሎች ማኅበራት እንዲሁም ባለሥልጣኖቻቸው ሕገ መንግሥቱን የማስከበርና ለሕገ መንግሥቱ ተገዢ የመሆን ኃላፊነት አለባቸው፡፡
ይህን የመፈጸም የማስፈጸም አቅም የት ላይ ነው ያለው?
3 በዚህ ሕገ መንግሥት
ከተደነገገው ውጭ በማናቸውም አኳኋን የመንግሥት ሥልጣን መያዝ የተከለከለ ነው፡፡ ይሄ የጉሌለውን
መንግሥት ብቻ ሳይሆን የመቀሌውን የመንፈስ ኮንፈድራዊ መንግሥትን ይመለከታል።
4 ኢትዮጵያ ያጸደቀቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች የሀገሪቱ ሕግ አካል ናቸው፡፡ አልፍ
ሲባል በሰባዕዊ መብት ረገጣ ሉላዊው አለምም ብዙ ደክሞበታል ኢትዮጵያ በሰው ልጆች የድንጋጌ ውስጠት የመከተም አቅም
እንዲኖራት። የዛሬው አድናቆትም ምንጩ ያ ነው።
አንቀጽ 10
ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች
1 ሰብዓዊ መብቶችና ነፃነቶች ከሰው ልጅ ተፈጥሮ የሚመነጩ፣ የማይጣሱና የማይገፈፉ ናቸው፡፡
2 የዜጎች እና የሕዝቦች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ይከበራሉ፡፡ ይህ ከሆነ ክሱ የሰባዕዊ መብት ጥሰት ስለሆነ ይህን አልቀበለም አላስፈጽም ያለ አካል በቀጥታ አንቀጽ 10 ተጻሮ ነው የቆመው ማለት ነው።
በሌላ በኩል „ምዕራፍ አምስት የሥልጣን አወቃቀር እና ክፍፍል አንቀጽ ስለ ሥልጣን አካላት አወቃቀር“
አቀጽ 1 የፌዴራል መንግሥት ሥልጣንና ተግባር“ ላይም እንዲህ ይላል …
1
ሕገ መንግሥቱን ይጠብቃል፤ ይከላከላል፡፡
ይህን አስታርቆ ለመጓዝ እንደገባን፤ እንደምናምንበት ልክ ሳይሆን እንደ ህግ ትርጓሚ እና አፈጻጸም ልኩ አቅሙ የማድረግ
ሥልጣኑ ነው መታዬት የሚገባው ባይ ነኝ። ህግ ያለውን ሆኖ እንዲገኝ ነው እኔ እምሻው። በስተቀር ግን የርትህ ጥነት ማግስትንም
አጥንኖ የጆሮ ደግፍ በሸተኛ ያደርገዋል። እንደ ለመደነው ማለት ነው።
ውዶቼ ጠ/ሚር አብይ አህመድ ትናንት ከሰጡት
ማብራሪያ ያልተረዳኝ ሳይሆን ተረድቶኝ የማልቀበለው
በጽኑም እምሞግተው አመክንዮ ነው።
„በመጀመሪያ የተከበረው
ምክር ቤት እንዲገነዘበው የምፈልገው ኢትዮጵየ
ውስጥ ወንጀል ሰርቶ ወንጀል
በመሠራቱ በመንግሥት ዲክለር ተደርጎ ያልታሰረ ሰው የለም። ልዩነቱ
መንግሥት ባዘጋጀው እስር
ቤት ውስጥ መንግሥት እዬጠበቀው መንግስት
እዬቀለበው መታሰር እና
እራሱን ማሰር ካልሆነ
በስተቀር አልታሰረም የሚል
እሳቤ በግሌ እኔ የለኝም።
ምክንያቱም ሰው የማይታሰረው
በህሊናውን እና እማይተሰረው ደግሞ
ፊዚካሊ በመንቀሰቀስ ነው።
ሰው ገድለህ፤ ወንጀል ሰርተህ
ህሊናህ ነፃ ሆኖ
መተኛት አትችልም። ያው
የታወቀ ነገር ነው።
በነፃም መንቀሳቀስ አትችልም።
አንድ ቦታ እራስህን አቅበህ መኖር
ወዶ ታሳሪ መሆን እንጂ
ያልተሰረ መሆን አይደለም። በእኔ
እምነት ሁሉም ታስሯል።“
እሳቸው መሪ ናቸው። መሪ መሪነቱን የማስጠበቅ
አቅሙ በአቅሙ ልክ ህግ የፈቀደለትን በማስፈጸም እና በመፈጸም እረገድ ጽናቱ ከእዕይታው ያለፈ ህግን ቁምነገር የማድረግ ጉዳይ ሊሆን ይገባል ነው። „በህሊናው ታስሯል“ ብሎ በህግ ጥሰት ይቀጥልበት የሚያሰኬድ የድርድር
አምክንዮ አይደለም - ለእኔ ለሥርጉተ ሥላሴ።
የሉዕላዊነት መሸራረፍ የሚመጣው የማዕከሉ ህግ አፈጻጸም ላይ ባለው ልልነት ወይንም ጥንካሬ ይወሰናል። በዚህ ዙሪያ ከዬትኛውም አቅጣጫ የሚመጣውን ማናቸውንም ሙግት ለመቀበል ዝግጁ ነኝ።
የሉዕላዊነት መሸራረፍ የሚመጣው የማዕከሉ ህግ አፈጻጸም ላይ ባለው ልልነት ወይንም ጥንካሬ ይወሰናል። በዚህ ዙሪያ ከዬትኛውም አቅጣጫ የሚመጣውን ማናቸውንም ሙግት ለመቀበል ዝግጁ ነኝ።
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ