የኢትዮጵያ ህዝብ መኖርን ነው በትህትና እዬለመነ ያለው።
እንኳን ደህና መጡልኝ።
ርህርህና
የመሰረት
ድንጋይ።
„በአንደበቴ እንዳልስት መንገዴን እጠብቃለሁ“
መዝሙር ፴፰ ቁጥር ፩
ከሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
25.02.2018
ከእመ ዝምታ - ሲዊዘርላንድ።
ይህ ኪዳን የሁልጊዜ እንዲሆን እመኛለሁኝ!
ጤና ይስጥልኝ ውዶቼ እንዴት ናችሁ? ደህና ናችሁ ወይ? ኦህዴድ እውን ኦዴፓ ከሆነ ልለው የምሻው ነገር ይኖረኛል ዛሬ። ከሁሉ በፊት፤ ከሁሉ አስቀድሞ መከወን ያለበት መሪዎቹን በዬደራጀው ያሉትን በፌድራልም ይሁን በክልሉ ሆነ በዞን ይሁን በወረዳ የሚያስቀምጣቸውን ወገኖች ሞራላዊ ሰብዕን መገንባት ያለበት ይመስለኛል። አውራ ፓርቲ ስለሆነ አብነቱ ከዛ ነው የሚጀምረው እና። ሁለቱም በፍጹም የተገራ ሰብዕናቸው ነው ህዝብ ከሰማይ እንደወረዱ መላዕክት የሚያቸው። እና ተከታዮቻቸውም እንደ እነሱ እንዲሆኑ ማድረግ ግድ ይላል።
ከሁሉ አሰቀድሞ ከሁሉም በፊት የህዝብ ሃላፊነት ለመስጠት ከማቀዱ በፊት ሁሎችም በውስጣቸው የቋጠሩትን ቂም በቀል እና ቁርሾ እንዲያራግፉት ማድረግ ይጠበቅበታል - ኦዴፓ። በሩን ዝግት አድርጎ፤ ከሚዲያ ውጭ በሆነ ሁኔታ ይምከር - ኦዴፓ። በውነቱ እጅግ የሚያሳዝኑ ነገሮች ነው የሚታዩት። የሚደመጡት። የእኔ ለመባል የእኛ ማለትን ይጠይቃል። አብሶ እላፊ መሄዱ ነው የሚጎረብጠው ከሚፈጸው አሰቃቂ ኢ-ሰብእዊ ተግባር በላይ።
በአዲስ አባባ ጭፍጫፋ እና እስር ጉዳይ "ዘራፊ፤ ሃሺሸኛ፤ ሌባ ወሮበላ" ነበር የተባሉት የተሰዉትም የታሠሩትም ዜጎች። አሁን ደግሞ "ህገ ወጥ ወራሪዎች ናቸው" የሚባሉት በለገጣፎ ያሉ ነዋሪዎች ዜጎች። ትናንትም የነበረው እራሱ ኦህዴድ ነው፤ ዛሬም ያለው ኦህዴድ ነው ራሱ የሰራውን ሥህተት ዕዳ ከፋይ እሱ እራሱ ኦህዴድ - አንጂ ህዝብ የበቀል ማወራረጃ ሊሆን ፈጽሞ አይገባም።
ተደጋግሞ የሚነሳው ህግ ማስከበር ነው ይባላል። ለህግ ቀናኢነት ቢኖር እኮ ኢንጂነር ታከለ ኡማን የአዲስ አባባ ም/ከንቲባነት ለአንዲት ሰከንድም ቢሆን ህጉ አይፈቅድላቸውም ያን ቦታ ለማግኘት።
እኛ ስንፈጽመው የህግ ጥሰት ትክክል የሚሆንበት ሌላው ሲሆን ደግሞ ጥሰት የሚሆንብት ምንም ምክንያት የለም። እኔ አደራጅ ስለሆንኩኝ በአምክንዮ ደረጃ በምንም መስፈርት ቢሆን የተወሰደው እርምጃ የህዝብ የመደራጀት የመምረጥ እና የመመረጥ መብትን የጣሰ ስለመሆኑ አሰተርጓሚ አያስፈልገኝም።
እርግጥ ነው ምርጫው የሶሻሊዝም በድርጃታዊ ሥራ ቢሆንም ግን ከታች ወደ ላይ በውክል አካል ጉባኤ፤ ምክር ቤት ተመርጦ ከዛ ነው ሥ/አ/ኮ የሚወጣው። ሥ/አ/ኮ ተሰብስቦ ደግሞ ከንቲባውን ይመርጣል። ወይንም በቀጥታ ምርጫ ከሆነ ምክር ቤቱ ምክትል ከንቲባውን የመምረጥ ሥልጣን በደንቡ ከኖረም በዚህ መልክ እንጂ ከንቲባ በሹመት የማይሆን ነው። ይህ ትክክል ከሆነ ዛሬ ህግ ልናስከበር የወሰድነው እርምጃ ትክክል ነው ብሎ ሙግት የሚያስገጥም አንዳችም ነገር የለም።
በሌላ በኩል ወ/ሮ ሃቢባ ሲራጅ ከሁለት ክልል ጋር ችግሩን አያይዘውታል። ይህ ደግሞ ሌላ ገማና መሆኑ ነው። እነዚህ ሁለት ክልሎች ራሳቸውን የገበሩ አውራ ፓርቲ ኦህዴድ ሆኖ እንዲወጣ ህዝባቸውን ተጭነው ፍላጎታቸውን የሸለሙ፤ ታሪካቸውን ስጦታ ያበረከቱ ናቸው። ዛሬም ከ80 ሺህ ህዝብ በላይ በጎንደር መፈናቀል የዛ ቁርሾ ውጤት ነው፤ያ የብአዴን ውሳኔ ያልተመቸው አካል ነው ዛሬ ህዝብን ሜዳ ላይ እንዲፈስ ያደረገው።
ሌላ ቃሉ እራሱ እንደ ሴት እኔ ሳዬው እጅግ ዘገነነኝ። „ጫጫታ“ ያንት ያለህ ነው ያልኩት። እኛ 600 ወገኖቻችን ሬቻ ላይ ሲጨፈጨፉ ያን ያህል ቀን እና ሌት እንቅልፍ አጥተን የባዘነው „ጫጫታ“ ነበርን? የተባበሩት መንግስታት የወቅቱ ዋና ጸሐፊ አደባባይ ወጥተው ሶልዳሪት እስኪያሳዩ የተደረገው እኮ የዕንባ፤ የአንጀት የወገን ጉዳይ ስለሆነ ነው። ለመሆኑ እሳቸው ያን ጊዜ ምን አደረጉ? ፊት ለፊት ወጥተው ህውሃትን ሞግተው ራሳቸውን ለካቴና አሳልፈው ሰጡን?! ታሰሩ? ጥፍራቸው ወለቀ? ተዘቅዝቀው ተሰቅለው በጨካኞች ተደበደቡ? የትኛው ቦታ ላይ ነበሩ?!
ሌላም ለቃለ ምልልስ ቀርቦ ስልክ ከጆሮ መዝጋት ለአንድ ከተማ ከንቲባ ለዛውም ለሴት ይከብዳል። ደግሞ ቃለ ምልልስ አድራጊዋ ጋዜጠኛ እዬሩሳሌም ተ/ፃዲቅ ደግሞ የረጋች እና የሰከነች ጋዜጠኛ ናት። ደርባባ ናት። ወገናዊነቷም፤ ተቆርቋሪነቷም እኩል ነው እኔ አልፎ አልፎ እንደምከታተላት ከሆነ።
እማልደብቀው አብዝቼም መስጥሬም እማከብራት ጋዜጠኛ ናት። ባትሆን እንኳን መሪ እና የህዝብ ተጠሪ በዛ መልክ ቃለምልሱን መዝጋት የተጋባ አይደለም። ስልክ ከጆሮ መዝጋት እጅግ ጸያፉ ተግባር ነው። አክሰሱ ያላቸው ልጆች ከዚህ ምን ይማራሉ? ለዛውም በፆታ ተመሳሳይነትም አለ። ይህም ሌላ የሚያስተሳስር ለመደማመጥ አደብ ሊሰጥ የሚጋው ጉልህ አምክንዮ ነበር።
እኔ ሴት ሆኖ ያን ያህል እንባን መርገጥ፤ ስለ እናቶች እንባ ግድ አለመስጠት ከዬት ተፈጠረ ይህ ነፍስ ያሰኛል? እንዴት አይነት ቤተሰብስ ውስጥም ታደገም ያሰኛል?
በጄ/ ብርሃኑ ጁላ፤ ሜ/ጄ ደግፌ በዲ አሁን ደግሞ ወ/ሮ ሀቢባ ሲራጅ የንግግር ውስጠት እና የቃናውን ምት ለናሙና ስወስድ ኦዴፓ ከመሰረቱ ያልሰራው ተግባር እንዳለ ነው እኔን የሚገባኝ። ሥልጣኑን ይያዙ ነገር ግን እንደ ሰው እንደ ባህልና ትውፊቱ የሰው ልጅን አክብሮ መነሳት ግድ ይላል። ሊመከሩ፤ ሊነገራቸውም ይገባል።
በጣም የሚገፈትር፤ በጣም የሚገለማ ከጥዋቱ ሽብር የሚለቅ የታወከ አዬር ነው ያለው። ይህን መልክ ማስያዝ ደግሞ የራሱ የድርጅቱ ተግባር ነው የሚሆነው። ህዝብ መንፈሱ በጽኑ ታውኳል - ፈርቷልም - ሰግቷልም። ደግሞም አይፈረድበትም።
አፍ እላፊ አለ። ማን አለብኝነት አለ። ማን ይነካናል አለበት። ግፍም አለ። ይህ ደግሞ ለሰውም ለእግዚአብሄርም አይመችም። አንደበት መታረም የሚገባው ከወንበሩ ቁጭ ከማለት በፊት ነው። ትግሉ እኮ ለሰው ከሆነ የሰው ልጅ እኩል ነው። ድርጅት የሰው እንጂ የዕቃ አይደለምና።
ረጋ ብሎ፤ ሰከን ብሎ ዘመን ሰጥ ነገሮችን መያዝ ይገባል። የሰውም የፍጥረትም የነፍስም ግፍ አለው። መስሎን እንጂ ያ እንዳለፈው ሁሉ ይህም ያልፋል። ቋሚ ነገር ምድር አስተናግዳ አታውቅምና።
እኔ ዙሪያ ገባውን ስቃኘው የመጀመሪያው ተግባር አልተከወነም ባይ ነኝ እኔ። ኦዴፓ ማድረግ ያለበት እንደ እኔ ያን በውስጥ ታምቆ ያለውን ቂም እና ቁርሾ እስኪወጣላቸው ድረስ አካሎቹ እንዲያወጡት፤ እንዲተፍሱት ማድረግ ይኖርበታል። በስተቀር ቂም በዬዕለቱ እዬፋፋ እዬዳበረ እያገረሸ በሌላ በኩል ደግሞ „ኢትዮጵየዊነት ሱስ ነው“ የሚቻል አይሆንም።
በአንድ ክልል ህብራዊ የአኗኗር ዘይቤ ነው ያለው። በሰው አገር ተከብረን እዬኖርን እንዴት ሰው በአገሩ ይህን የመሰለ ባይታዋርነት እንዲሰማው ይደረጋል።
ከኑሮ መፈናቀል ከተስፋ መፈናቀል ከህይወት መሰረዝ ዕውን „ጫጫታ“ ነውን?!
በዚህ ውስጥ ደግሞ ጠ/ሚር አብይ አህመድ ከሰሞኑ በሰጡት መግለጫ ወጥ ፓርቲ ለመሆን ጥናት እንደተጀመረ እዬነገሩን ነው። ብክሉ አውሎ እንዲህ አደብ አጥቶ እዬተወራጨ፤ ጭንቅላት ውስጥ የከተመው የደነደነ ቂም እና በቀል በምን ማርከሻ ቢና ጢናው ወጥቶ ነውና ይህን ግዙፍ ዓላማ ማሳካት የሚቻለው?
የተደባለቁ ነገሮች ነው ያሉት። ኦዴፓንስ ከቶ ማን የትኛው መንፈስ ይሆን እዬመራው ያለው? የሚሻል የሚያጽናና ነገር እኮ እዬጠፋ ነው። ሰውኛው ተፈጥሮኛውም መንፈስ የናፈቅን ያ ርህርህና ምነው በአጭር ጊዜ እንዲህ ትነት ገጠመው? የህሊና ስራ ገና አልተጀመረም ባይ ነኝ እኔ።
ባለመጀመሩ ነው እንዲህ ከትውፊታችን ያፈነገጡ እና እኛን የማይገልጹ ተግባራት የሚከወኑት፤ የሚደመጡት። መቼም ቤት ሳይጸዳ በረንዳ አይጸዳም እና ዶር ለማ መገርሳ ይህን መልክ ማስያዝ ያለባቸው ይመስለኛል። ለዬትኛውም ቦታ ሪኮመንድ የሚያደርጓቸውን አካሎቻቸውን በተለዬ ሁኔታ በር ዘግተው መምከር ይኖርባቸዋል። በጣም የተንጠራራ ነገር ነው ያለው። ይህቺ አገር የሁሉም ናት። አንዱ የክት ሌላው የዘወትር አይደለም። ስለሆነም አካሎቻቸው ይህን የቁርሾ መንገድ ትተው ወደ ነፍሳቸው ይመለሱ ዘንድ መግራት ይኖርባቸዋል።
ምክንያቱም እሳቸውን አምነን መንገዱን በቅንነት ከጥዋቱ የደገፍን ንጹሃን አለንና። የሳቸውን የበዛ ትህትና ለበታቾቻቸው መቀለብ፤ የበታቾቻውን ማሰልጥን ይኖርባቸዋል። ሌላው ቀርቶ ዶር ለማ መገርሳ የማይመች ነገር ቢናገሩ እንኳን እኔ ብዕሬን አላነሳም። ለምን ቢባል የአቀራረባቸው ትህትና ይገዛኛልና። ሳይመቸኝም አልፈዋለሁኝ።
በሌላ በኩል ዛሬ ሌላም ዜና ወጥቶ አንብቤያለሁኝ። ተስፋ ከማደርጋባቸው አንስት ሊሂቃን መካካል ወ/ሮ አዳናች አቤቤ አንዷ ናቸው። እሳቸው በሚመሩት የሚ/መ/ቤትም ሌላ አዲስ መርዶ አለ። ይህን የተገባ ትኩረት ተሰጥቶት በፍጥነት እንዲስተካከል መሆን ይኖርበታል። አካሄዱ ጠናና ነው።
ዜጋ ግዴታውን ሊወጣ የሚችለው መብቱ ሲጠበቅለት ብቻ ነው። መብት ተረግጦ ግዴታ አሟላ አያስኬድም። ምንጩ ይህውና ሳተናው ድህረ ገጽ ገብቶ ማንበብ ነው።
„የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ሰራተኞች በደረሰባቸው የዘር መድሎ ተማረው መፍትሄ እንዲሰጣቸው እየጠየቁ ነው (ከተቋሙ የተላከና ጠቃሚ ስለሆነ በትዕግስት ይነበብ)“
· እና።
በጥቅሉ እኔ ሳዬው ያፈነገጠ ወይንም የዘበጠ ጉዳይ አገር እዬመራ ባለው አውራ ፓርቲ በኦዴፓ የበታች ይሁን የበላይም አመራሮች ነው እዬተከሰተ ያለው። ለውጡን እንዲያመርር፤ በለውጡ ጥርጣሬ እንዲኖረው ህዝብ የሚያደርጉት የራሱ አካሎች ናቸው። ይህ መሆኑ ግድ ቢልም ጊዜው ልጅ ስለሆነ መጠኑ እያለፈ ሲሄድ ደግሞ አደጋው የከፋ ነው የሚሆነው።
በግልጽ እና በቀጥተኛ ቋንቋ ይህ ድል እንዴት እንደተገኘ ተደፍሮ ለህዝባቸው ሊነገሯቸው ይገባል ዶር ለማ መገርሳ። ይህ ድል ዕውን ኦህዴድ ብቻ ታግሎ ዕጣ ነፍሱን ቆሞ ያመጣው ነውን? የድሉ አስመጪ ሃይል ኦህዴድ ብቻ ነው?
ተለባብሶ ስለተሄደ ነው አሁን ይህን መሰል መከራ ያ የተገፋ ህዝብ እንደገና የመከራ አራጣ በድርብ በሁለም አቅጣጫ ክፈል የሚባለው።
በጣም ያለፈ በጣም የሚያሰደነግጥ ንግግር ነው በዬጊዜው የሚደመጠው። ይህ ለተስፋ ነቀርሳ ነው። ተስፋ ከሞተ ደግሞ አብሮ መሞት ነው። ፍቅርን ሳይሰስት ለሰጠ ወገን ይህን መሰል የቁርሾ ንግግር በውነቱ የተገባ አይደለም። እዮር ያያል።
የለገጣፎ ከንቲባ ስራ አስፈፃሚ ወሮ ሀቢባ ሲራጅ ከ ኢሳት ጋር ያደረጉት ቃለ ምልልስ እነሆ።
አይቶም ዝም አይልም ምርቃቱን ያነሳል። ማዕትም ባልታሰበ ሁኔታ ሊያመጣ ይችላል። በጣም የታወከ አዬር እንዲኖር የሚያደርጉት የሚያውኩትም የራሳቸው ወገኖች ናቸው ለውጡን።
በሌላ በኩል 9 ወር ሙሉ ሌት እና ቀን የተባተለበትን፤ የተደከመበትን አረማሞ ያለብሰዋል ይህን መሰል ተባደግ ግጥግጦሽ። ሆድ የሚያባቡ፤ ልብን የሚያሸብሩ ነገሮች አሉና። መኖር ሲኖር ነው ተስፋ የሚሰነቀው። መኖር በቋሳ እዬደቀቀ ተስፋን ነገን ማሰብ ከባድ ነው።
ሜዳ ላይ የፈሰሱ ከ2 ሚሊዮን በላይ ዜጎች እያሉ አሁን ስለ መዝናኛ ማዕከላት እራሱ ቅንጦት ነው። የኢትዮጵያ ህዝብ ኬክ ሳይሆን የወዙ ማሳረፊያ መኖርን ነው እዬለመነ ያለው። መኖር የተነፈገው ህዝብ ነው ያለን። ህዝብን ቀርቦ አይዞህን በመለገስ ቢያንስ በራበው አንጀቱ ተስፋን እንዲጠብቅ ማበረታት ሲገባ „ሆድ ለባሰው ማጭድ አታውሰው“ ነገሩ ሁሉ።
ወገኖቻችን መጀመሪያ እስኪ እሚበሉትም፤ እሚጠለሉበትም ላጡት ወገኖች አይዟችሁን ይቀለቡ። አሁንም እነዛ ህዝቦች ከዛው ከደሃው ጀርባ ላይ ነው ወድቀው የሚገኙት። ለመሆኑ መከራ በባጀበት ህዝብ ሌላ መከራ ማዋጅ ግን ይህ ሰውነት ነውን?
ሴት ሆኖ ማዘን ከተሰነን ሴት ሆነን መፈጠራችን ራሱ አለት ነው። ሴትማ አዛኝ ሩህሩህ መሆን ይገባታል። ጭካኔ ሴቶችን አይገልጽም። አረመኔነት የሴቶች መለያ አይደለም። ሴቶች አድማጮች መሆን ግድ ይላቸዋል። ቂመኝነት ለሴቶች ሰብዕና አይመጥነውም። መታበይም ፆታችን አይወክልም። ሴቶች እናትነት ያህል ጸጋ የተሰጣቸው ናቸው እና።
ለሴት የፖለቲካ መሪዎች እራሱ ወደ ተፈጥሯቸው እንዲመለሱ ራሱን የቻለ ተግባር መጠዬቁን አሁን እኔ እያስተዋልኩኝ ነው። ሴቶች ቦታ መያዝ፤ በሙያ ብቁ መሆን ብቻ ሳይሆን ሴቶች ተፈጥሯዊ መክሊታቸው ያልተነሳ መሆኑ የመጀመሪያ መስፈርት ሆኖ መገኘት ያለበት ይመስለኛል። እናትነት ከትርጉምም ከሚስጢርም በላይ ነውና።
ቢያንስ ልስልስ አንደበት፤ ቢያንስ ሰው አክባሪነት፤ ቢያንስ አድማጭነት፤ ቢያንስ ስህተትን መቀበል እንዴት ለአንዲት አንስት ያቅታል? ደግነትን ከሴቶች በላይ ለማን ይሰጥ? እናትነትን ከሴቶች በላይ ለማን ይሸለም? ሰሞኑን በማዬው በማዳምጠው ነገር አብሶ በሚሰጡት መልሶች ማህጸኔ ነው የታረደው።
እኔ እንዳመስበው ከሆነ ኦዴፓ መጀመር ካለበት ቦታ ላይ አልጀመረም። ህሊናን ከቁርሾ ማውጣት ቀዳሚው ተግባር ነው ሊሆን የሚገባው። በአንድም በሌላም የማዬው የዚህ ደም ማነስ ጉዳይ ነው።
ሌላው መረጃ ቲቪ የቡራዩንም በትክክል የዘገበ ሚዲያ ነው። ደፋር እና ጀግና ሚዲያ ነው። ይህ ደፋር ሚዲያ በዛች በተወሰነች የጊዜ ክልል ከመንግሥት ሚዲያ በላቀ መልኩ ለህዝብ ዕንባ ቅርብ ሆኖ ነው እኔ ያገኘሁት። አሁን እንደምሰማው ደግሞ ጋዜጠኛ እስከመደብደብ ተደርሷል። ሁሉም ነገር ልክ አለው። ሲከር ይበጠሳል፤ ሲሞላም ይፈሳል። ትእግስት ሲያልቅም ፍቅር ይሰደዳል። በዚህ አያያዝ የማግስት የሚዲያ ነፃነት፤ ነፃ ምርጫ የሚባሉ ነገሮች ? ? ? ይሆናሉ።
ኢትዮጵያዊነት ከመፈጠሩ በፊት ፈተናን አሸንፎ የተፈጠረ ሚስጢር ነው!
የኔዎቹ ኑሩልኝ።
መሸቢያ ጊዜ።
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ