የኢዴፓ እጩነት /አዲስነት ትልሞሽ/
እንኳን ደህና መጡልኝ።
የኢዴፓ እጩነት። የሚቀድመው
የትኛው ይሆን? ግን ገነገነ
ወይንስ ገነነ ልበል ከቶ!
„የፃድቃን አፍ ጥበብን ያስተምራል፤
አንደበቱ ፍርድን ይናገራል።“
መዝሙር ምዕራፍ ፴፭ ቊጥር ፴
ከሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
25.02.2018
ከእመ ዝምታ - ሲዊዘርላንድ።
ትናንት በዋለው የአጋር ድርጅቶች ይሁን የአጋር ክልሎች ዓወደ ህዝባዊ ስብሰባ ጠ/ሚር አብይ አህመድ ወደ ወጥ ፓርቲነት ድርጅታቸው እንደሚሸጋገር አብስረዋል። ጉደኛው ኢህአዴግ ወደ „ኢትዮጵያዊ ፓርቲነት“ ሊለወጥ ደስ ይላል። ኢትዮጵያዊ ፓርቲነቱን ሲያልም ግን የቋንቋ ፌድራሊዝምን ተሸክም ይሆን?
ብቻ መሰናክሉን ማለፍ ከተቻለ ወሸኔ ነው ማለፊያ። መሰናክሉ የህሊና ለውጥን ነው የሚጠይቀው። የቅርቡን የወ/ሮ ሀቢባ ሲራጅ ቃለ ምልልስ ብቻ በቂ ነው። ምን ያህል የዘለበ ገማና ኢትዮጵያ እንዳለባት።
አሁን እንኳን በዬቦታው የራስን ሰው ለመሸጎጥ ማራቶኑ ተንጠራርቶ አገር እያመሰ ስጋት እያቀና መሆኑ ነው የሚደመጠው። የሳቸው ቸር ምኞት ግን ሁልጊዜም ይገርመኛል። እስኪ ያሳካላቸው … አሜን አሜን ይሁን ይሁን ብለናል።
ወደ ቀደመው ምልሰት ሳደርግ እኔ እንዲያውም ኦዴፓ አውራ ፓርቲ ሆኖ ለመውጣት ሥም ሲያድል ብአዴን ተቀብሎ አዴፓ ነኝ ከዛሬ ጀምሮ ሲል ምን አለ ኢዴፓ ብትባል ብዬም ነበር/ የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ። / ማለቴ አማራ ክልል ነው እና ኢትዮጵያዊነትን ተሸከም የሚበላው በዬዘመኑ። እነ አቶ በረከት ስምዖን፤ እነ አቶ አዲሱ ለገሰ፤ እና አቶ ዮሴፍ ህላዊ፤ እነ አቶ ተፈራ ዋልዋ፤ እና አቶ አለምነህ መኮነን ምን ተዘርዝሮ ሲያልቅ ... አሁንም ስልጣን ምንችንም አይደለም ከሰማይ ደጅ ጸጋችን እናገኛለን ባዮች ናቸው እነ ዶር ገዱ አንዳርጋቸው። ቀድሞ ነገር ብአዴን ቀይ መሰቀል ነው የሚመሰለኝ ...
ስለሆነም ወጥ ፓርቲ እንሁን ለሚለው ከሁሉም ግር የማይለው ድርጅት ቢኖር ብአዴን ብቻ ነው። የኖረበትን ማስቀጠል ነውና … መሸከም ደግሞ ስለለመደበት ብአዴን ጭነት ቢቀርበት እንኳን ቅር ቅር ይለዋል … ጭነቱም ቀለል ካለው አያስችለውም እባካችሁ ጨመርመር አድርጋችሁ እከሉኝ ባይ ነው፤ የውጭ አገር ጉዞዎችን የጠ/ሚሩን፤ የውጭ አገር መንግሥታት ጋር የሚያደርጉትን ግንኙነት ስመለከት ምን አይነት በረዶ ድርጅት እንደሆነ ብአዴን ግርም ይለኛል።
በልሙጥ እኮ ነው ያለ። ለመጣው ሁሉ እሺ ይሁን እያለ። ስለምን? የተደራጀው ለስልጣን ሳይሆን መብራት ይዞ ቁሞ ለማብላት ነውና። ድርጅቱ አይማርም ፈጽሞ። ህውሃት እንዴት እንደቀለደበት ሳይማር አሁን ያን መከረኛ ህዝብ ከፖለቲካ ውጭ አስደርጎ ተንበርክኮ ፍርፋሪ ይለምናል ...ኩነኔ!
በሌላ በኩል እኔ በመስከረሙ የኢህአዴግ ጉባኤም ኢህአዴግ ወደ ኢዴፓ ይቀዬራል የሚል ዕሳቤ ነበረኝ። ሃሳቡን ብቻ አንስቶ እና ወስኖ ሳይቀዬር ነበር የተለያዬው። እንዲያውም ያን ጊዜ ቢሆን የተሻለ ጊዜ ይመስለኛል። ከአሁኑ ከተወጠረው ቅራኔ አንጻር። የሃይል አሰላለፉም በቅራኔ እንደ ስልቻ ተወጥሮ ሊፈነዳ አፋፍ ላይ ነው።
የሆነ ሆኖ እጩው ኢዴፓን /የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲን/ ሌላ ሥምም ከኖረ ይሁን … ለመቀበል ማን ብሎን እንቀበላለን - ቅኖች። ለጣና ኬኛ እኮ ማቄን ጨርቄን አላልነም፤ ካለምንም ቅደመ ሁኔታ ነበር የተቀበልነው። ይሉኝታ ጠፍቶ የመቀጥቀጥ መከራ ደግሞ አላባራ አለ እንጂ። መገለልም በዬፈርጁ በዬጅረቱ አና ብሏለኝ። ዕውቅና በመስጠት እረገድም ግርዶሹ እንዲሁ። ይሉኝታ አጣ ኦዴፓ? ?
ጠ/ሚር አብይ ሲናገሩ ለወደፊት የአማራ፤ የሱማሌ የአፋር ወዘተ ፓርቲ ብሎ ነገር የለም ነው ያሉት። እሰዬ እልል ብለናል። ግን ክልሉስ ነው አብዩ ጥያቄ? የአማራ ክልል፤ የአፋር ክልል፤ የኦሮሞ ክልል፤ የቤንሻንጉል ክልል ወዘተ … እያልክ እንዴት ነው የዞግ ፓርቲዎች ከስመው ወጥ የፖለቲካ ድርጅት ለመሆን ኢህአዴግ የሚቃጣው?በሽታ እኮ በመስታገሻ ሳይሆን በፈዋሽ መዳህኒት ነው የሚድነው። መገላገል ካለበት ምጥ ቆርጦ እና ደፍሮ መገላገል ከዛ የዘገጠ አይዲዮሎጂ።
የሆነ ሆኖ የትኛው ነው መቅደም ያለበት? የቋንቋ ፌድራሊዘመንን አሰናብቶ መልክዕ ምድራዊ ፌድራሊዝም ወይንስ ወጥ ፓርቲ? አሁን ምን የሚያጣድፍ ነገርስ ምን መጣ? የተሰረዙት ዜጎችም ቢሆኑ „7 ዓመት ዓይኗን ያጣች ባተሌ አንድ ቀን እደሪ ብትባል እንዴት ብዬ እንደለችው“ ሆኖ አሁን ጎሰም የሚያደርገ አስተያዬት ይሰጣሉ። ለውጡ ባይመጣስ? በደርግ ጊዜ እኮ ኢሠፓ የክትና እና የዘወትር ዜግነት አልነበረበትም። ፖለቲካ ኢንስቲቱትም እኩል ነበር ምልመላውም ሆነ ምደባው ተሳትፎውም እንዲሁ ፍጹም ነው ባይባልም እንዲህ ዞግ ገዝ አልነበረም። እኔ ለድርጅት አባልነት ከደረስኩበት ጊዜ አንስቶ ያዬሁት።
በሌላ በኩል በህውሃት የፕሮፓጋንዳ ጫና ይመስለኛል እኔ ነገሮችን ቀድሜ በቅንነት ስለማይ ኦዴፓ „በፌድራሊዝም አልደራደርም“ እያለን ነው። እና ይህ እንዴት እና እንዴት ብሎ ሊታረቅ ነው? ፌድራሊዝም ሲባል የቋንቋውን ወይንስ የመልክዕምዳራዊ ፌድራሊዝም? ይህም ድብልብል እንዳለ ነው በደፈናው የተገለጸው። ከዚህ ጋር ተያይዞም በሰሞኑ የጠ/ሚር አብይ ቃለ ምልልስ ፕሬዚዳንታዊ መንገድን እንደሚፈቅዱም ተደምጧል … ይህም ሌላ የቤት ሥራ ነው ለታዳሚው። ቢሆን ግን ተማራጭ ነው … አማራጭ ኦዲዬንስ መኖሩ ራሱ የተስፋ ማህደር ነውና። አቅም መለኪያ ይሆናል። ለዛ ግን 100 ሚሊዮን ህዝብን ሥነ ልቦና በድርጊት ማልማት ይጠይቃል፤ ገለጻ ሌላ መሬት የምትመሰከረው ሌላ ከሆነ ግን አሁንም እንቦጭ ነው።
የሆነ ሆኖ መቼም በዚህ ዘመን አህዳዊ ይሁንልኝ ብሎ የሚፎገላ ነፍስ አይኖርም። ፌድራለዚም ቀለል ያለ፤ በቅጡ ከተያዘ አሳታፊም ለህዝብ ቀረብ ያለ አዳምጭ አደረጃጃት ስለሆነ። ብቻ ግን የ27 ዓመቱ የቋንቋ ፌድራሊዝም ምን ያህል ነፍስን ከጥቅም ውጪ እንዳደረገ ይታወቃል። ዛሬ በዬጓዳው የሚፈነዱ ፈንጂዎች የዛ ቅምረት ውጤቶች ናቸው። ፈንጆቹ ደግሞ ፈንድተው የሚያልቁ አይደለም ቀጣዮች ናቸው። በአንድ ሰብዕና ውስጥ ወዘተረፈ ማንነቶች አሉና።
በአንድ ጀንበር ብን ትን የሚሉ አይደሉም። አንድ ትውልድ እኮ ተገነባበት። ትግራይ ኦሮምያ ላይ ደግሞ ከዛም ያለፈ ዘመን ነው። እራሱ ኦደፓ አዴፓ የሚለው ስያሜ እኮ በፓርቲ መርሆ አደረጃጀት የመጣ አይደለም። ምኞት ነው ወይንም ፖለቲካዊ ውሳኔ።
„ቸር ተመኝ ቸር ታገኝ“ እንደሚበላው ዓይነትም ሊሆን ይችላል። ኦዴፓ የተመኘውን ቸርነት በወጥነት ፈጻሚ ባያገኝም ያው ብአዴን ወርሶለታል። ብአዴን ከ አባቶቹ ሌጋሲ አፍነግጦ ፊደል ቆጣሪ ስለሆነ፤ የዘመን የኔታዎች የሚሰጡትን ስልቅጥ ማድረግ የለመደበት ነውና ብአዴን። ካለ ምርቃት ነው ታዲያ … አነገትም የለምም ሙጥጥ በሎ አልቆ አሁንም አለሁ ይለናል። ተገፍቶ ተገፍቶ የት ላይ እንዳለ አደባባይ ላይ ቁልጭ ብሎ እዬታዬ ነው።
ሌላው የ"ፓ" ነገር ፓርቲ የሚለው ስያሜ ግዳጁ እና አፈጻጸሙም ብዙ አመክንዮ በህብር ያሉበት ነው። እንደ ዴንማርካውያን ተገጣጣሚ ቤት አይደለም አንድ ጽኑ የፖለቲካ ፓርቲ። ወይንም እንደ ምጥን ሽሮ … ቀልቀል አድርጎ ዋጥ ዋጥ የሚደረግ። የህሊና እና የማደራጀት ብርቱ ተግባርን ይጠይቃል። አድካሚ ሥራ ነው። ለእኔ ኢትዮጵያ ውስጥ የፓርቲ የአደረጃጃት ሥነ ምግባር ሆነ ሥነ ደንብ ያሟላ አንድም የፖለቲካ ፓርቲ የለም። ለዚህ ነው ተፎካካሪ/ ተቀናቃኝ/ ተቃዋሚ ለሚባሉት አትርበትበቱ ሁሉም ከዜሮ ነው የሚጀመረው እኩል ለ እኩል ናችሁ የምለው፤ በህሊና ብቃት አበቃቀል አመራር አቀነጃጃት ደረጃ ማለቴ ነው። በሃይልና በጉልበት ኢህአዴግ አለው ...
በሌላ በኩል ደግሞ ፈጽሞ ፍቺ የማላገኝለት አጋራ ድርጅት የሚባሉት ናቸው። ዛሬ ሲንተገተጉ አዳምጣለሁኝ። 27 ዓመት ሙሉ መብራት ይዘው ሲያበሉ ለመሆኑ የት ነው የባጁት? የሚገረም እኮ ነው? ከዜግነት ውጭ እኮ ነው የነበሩት። የበይ ተመልካች ወይንም ደንገጡር። ይልቅ ዛሬ እግዚአብሄርን ማመስገን ብቻ ሳይሆን የአማራ የህልውና ተጋድሎንና እና የኦሮሞ ንቅናቄን ያመስግኑ። ዜጋ ናችሁ ተብለዋልና።
በዬትኛውም ምድር እንዲህ አይነት ቀልድ ተፈጽሞ አያውቅም። በዬትም አገር። ወሳኝ ማን ነበር ለሚለው ግን አውራው ፓርቲ ህወሃት ነበር። ሌላው የግንባር አባላቱም ፍርፋሪ ነው ሲለቃቅም የኖረው። ለዛውም እንዲጠፋ የተፈረደበት ማህበረሰብ እማ ሁለመናውን በሎሌነት ያስገዛ ነበር አይዋ ብአዴን። ህዝቡን አንገቱን ደፍቶ እንዲኖር እንዲመነጠር ፈቅዶ እሱ የሰላ የበታችነት ማዕደኛ ነበር። ህወሃት ልቡን የገጠለመት። ገራሚው ነገር ዛሬስ ነው?
ቁጥሩ ነው አራት እንጂ ድሮም የነበረው አንድ አራጊ ፈጣሪ ገዢና ነጂ ነው የነበረው ዘመነ የህወሃት ሥርዕዎ መንግሥት ለዛውም ከመሰረቱ ጀምሮ አድዋኛ። ወደ ሚስጢሩ ስንዘልቅ ተገላዩ እልፍ ነው እንደማለት። አለሁ የሚባለው ሁሉ እንደ አሮጌ አካፋ እና ዶማ የሚፈለገው እስከ አገለገለ ድረስ ነው … ሶሻሊዝም እንዲህ ነው …
የሆነ ሆኖ ወጥ ፓርቲን ለማምጣት ጥናቱ ብቻ ይፈይዳል ወይ ነው የእኔ ቁምነገር? ዛሬ አንድ ዜጋ ከአንድ ክልል ወደ ሌላ አገር አይቶ ለመመለስ የማይቻልበት ወቅት ነው። ይኸው ብሄራዊ ፓርቲ ነን የሚሉት እኮ ከአንድ ክልል ብቻ ነው ተኮርኩመው እንዲቀመጡ የተደረገው። ለዛውም ዕድሜ ለብአዴን እሱ ባይፈቅድ ደግሞ የሚዲያ ስንቅም አይገኝም ነበር። ለምዕራባውያንም የዲሞክራሲ ምህዳር ምንትሶ ቅብጥርሶ ቅርጥምጣሚ አይገኝም ነበር። ይህን ሁሉ በርደን የተሸከመው ብአዴን አሁን እግርጌ ነው።
እና በምን የህሊና ምጥቀት ነው ከፈለገው ቦታ ከፈለገው ነፍስ ብቁ የሆነ ለአገር መሪነት መወዳደር የሚቻለው? ተጨባጩ ይፈቅዳል ወይ? ምን ያህልስ ጠንካራ አሳማኝ ብቁ ትንታግ ሠራተኞች አሉ? ብብሄራዊ ደረጃ የሚሰጡትን ገለጣዎች እኮ እንከታተላለን። ህሊናን ለመለወጥ ራስን ማብቃት ይጠይቃል? አንድ ሰው ደግሞ ሁሉንም ሊሆን አይችልም። የበዙ ብቁዎች ሊኖሩ ይገባል። ተናግረው ማሳመን የሚችሉ ...
ፍቅር አብሮነት እኛነት በዓዋጅ አይመጣም። ቢመጣማ ኑሮ የጠ/ሚር አብይ አህመድ ልፋትም የንግግር ለዛም የጥላቻውን ግንብ ንዶ አሁን በ9 ወራት ከተገኘው በላይ ብዙ ድል በተመዘገበ ነበር። አንዱ ሲክብ ሌላው ሲነድ፤ አንዱ ሲንድ ሌላው ሲክብ መሽቶ ይነጋል።
ከሁሉ በላይ በችግሩ ምንጭ እራሱ ስምምነት የለም። የቋንቋ ፌድራዚም መሰረቱ አጀንዳው የተተከለው „አማራ ሌሎችን ጨቁኖ ነበር ነው።“ የዚህን አይዲኦሎጂ መከራ አዳምጦ፤ አምኖ በመቀበል ከሥሩ ለመንቀል ጀግንነትን፤ ራስን ማሸነፍን ድፍረትን ይጠይቃል። አገር ውስጥ ያዬሁት አቶ ሙስጠፋ ኡመርን ብቻ ነው። አሁንም ግፊያ አለ ያፈጠጠ።
ለመሆኑ ለምንም ይሁን እንግዳ አትምጡብን የሚለው የወልዮሽ መከራ እንዲት ሊያዝ ይሆን? „አትምጡብን“ ነው ያለው። እውን ኦሮምያ ላይ ብቃት ያለው ክህሎቱ የዳበረ፤ ተወዳጅ፤ ሳቂተኛ አንድ አማራ አመራር አካል ሆኖ ወደ ላይ እዬተመረጠ ለአገር መሪነት መወዳደር ይችላልን? ጠ/ሚር አብይ አህመድ በአዋሳ ጉብኝታቸው ስለ አዬር ማረፊያ ተጫማሪ ተጠይቀው „እሺ እሺ ብዬ ሄጄ ደግሞ ብለው በቅርብ ጊዜ አይመስለኝም“ የሚል መልስ ሰጥተው ነበር። እኔም አይመስለኝም ነው እምለው። „የማይሆን ነገር ለሚስትህ አትናገር ነው።“ በሚባለው ውስጥ የአኔ ቦታስ ማለት ይገባል። እምታዘባቸው ነገሮች ስላሉ።
ብቻ … እንዲህ በሆነ ባላሆነው ሳንክ እዬገጠመው ድፍርስርስ ሊል የተሻለ ሳይሆን ፈጽሞ ያልታለመ የፈጣሪ ስጦታ፤ መልካም ጊዜ ነበር የመጣው። በፍቅር መንፈሱ አንድ ሆኖ እርጋ የተባለው ሁሉ እኮ በሳንክ ብትንትኑን ነው ያወጣው የሴራ ፖለቲካ መስከረም ላይ። አደብ ገዝቶ ይህ ቢሆን ዋነኛው ዓላማ ይታወካል የለም። ፈጽሞ ከራስ ኢጎ ያለፈ ብልህነት አልታደልንም። አለመደበንም እኛ በጎ ነገርን ዘላቂ አድርጎ ለማስቀጠል። መንቀል እንጂ ማብቀል ሃራም ነው በእኛ ቤት።ለዛውም ህወሃትን ያህል ጉደጓድ ድርጅትን አላዛሯ ኢትዮጵያ ተገላግላ።
አንዳንድ ጊዜ እኔ በምልሰት እነዛን ብርቅ ሰዓታት፤ ቀናት፤ ስኬቶች በምልሰት ሳያቸው ሆዴን ባርባር ይለዋል። የጠ/ሚር ጽ/ቤት ቀኑ አልበቃው ብሎ እሸት እሸቱን በአፍ አፋችን ሲያኮምኩመን እንደገና የመፈጠር ያህል ነበር። „በጥባጭ ሳላ ማን ጥሩ ይጠጣል“ እንዲሉ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ በስክንት ሊገኙ የሚችሉት ሁሉ በጥድፊያ እና በወከባ ምን ያህል አደጋ ያ የስኬት ጉዞ እንደገጠመው ስራዬ ብለን ለምንከታታል ይታዬናል። ተፈልጓል እኮ ይህ ህወከት በአንድም በሌላም። የሚበልጥን ማድነቅ የትናጋ ዕዳ ብቻ ነው … ከዚህ ባለፈ በተገኘቸው አጋጣሚ ደግሞ የራስነገርን ማጉላት ...
አንድ ምሳሌ እንኳን ባነሳ በ20 ዓመት የማይገኝ የተስፋ ግንባታ በ5 የኦሮሞ ድርጅቶች በጥዋቱ አፈር ነው የጋጠው። ውጊያ የተጀመረው በዛ በራሱ ቀዬ ነው። ለውጡን አስግልብጦ እንዲነበብ ከህወሃት ባልተናነሰ የተጉት ኦነጋውያን ናቸው። ከሁሉ በላይ የኢትዮጵያዊነት መጉላት የህሊና ሪህ ነው የሆነው። ለዚህ ዕድል ያበቃው ግን "ኢትዮጵያዊነት ሱሴ ነው" ነበር።
ብቻ እኔ መቼውንም የሚድን አይመስለኝም በዚህ ዙሪያ ምን አልባት እኔ ጨለምተኛ ባልሆንም ግራጫ ነው የሚታዬኝ። ከዚህ በላይ የፈድራሉ አቅምስ ምን ያህል ይሆን? የማስፈጽም አቅሙ? ይህም ሌላ ዳገት ነው። ይህ ወጥ ኢትዮጵያዊ ፓርቲን ስናስብ ማለቴ ነው። ሌላው ለይደር ተቀጥሮ ...
ሌላው እትጌ ትግራይ በራስ ገዝ? በኮንፌደሬሽ? በምን ሂሳብ ነው አብራ ቀጣይ የምትሆነው? መላ አለ ወይ? ወይንስ ህወሃት ራሱን ችሎ እንደ አንድ የፖለቲካ ድርጅት ተነጥሎ ሊወዳደር? ከህውሃት ጋር እያሉ በለውጥ አለሁ የሚሉት ደግሞ በሁለተኛው ድርጅት አብረው ተደራጅተው በውስጥ አርበኝነት ሌላ መከራ ለመሸከም ይሆን?
አልገብቶም!
እርግጥ ነው ዝርዝር የአፈጻጸም ሁኔታ እንደሚኖር አሰባለሁኝ። ነገር ግን የቤት ሥራውን ስለተሰጠን ነጥቡን አንስተን መወያዬት ግድ ይላል። የፈለገ ቢቧከሱ ህወሃታውያን አንድ ናቸው። የቁርጥ ጊዜ የመከራ ጊዜ አንድ ናቸው አካል እና አምሳል። ይህም ሌላው ውሃ ያዘለ ተራራ ነው። ማመን እና መታመን አይሸመት ነገር እንደ ሸቀጥ።
በሌላ በኩል ከምርጫ በፊት ነው በሆዋላ ውህደቱ? የጠ/ሚር አብዩ አህመዱ ቃና በቅርብ ጊዜ ሲሆን የአቶ ብናልፍ አንዱዓለም ቅላጼ ደግሞ በዓመቱ መጨረሻ ዓይነት ነው። ይህም ራሱ መታረቅ አለበት። የህሊና መሰናዶ ስለሚያስፈልገው።
ትናንት ከአማራ ቴሌቪዥን ሳደመጥ ወሎ ለናሙና በሰሩት ጉዳይ ላይ አብዛኛው ሰው ስለ የህዝብ ቆጠራ ምንም ግንዛቤ የለውም ብቻ ሳይሆን ስለመኖሩም የማያውቁ እንዳሉ ነው ያዳምጥኩት፤ ለነገሩ መዲናዋ ላይም ይህ ይኖራል ብዬ አስባለሁኝ። የአኛ ነገር ያዝ ለቀቅ ነው እና ተግባራችን … መሠረት ያለው ሥራ አንሰራም። በደራሽ ውሃ ነው እምንጥለቀለቀው … ወይንም በ አውሎ ንፋስ ነው አቅጣጫችን እምንመትረው ...
ወደ ቀደመው ምለሰት ሲሆን ከታች ወደላይ እዬተወከለ ከተባለ እኮ ኢህዴግም እንደ ሌሎቹ ተፎካካሪ/ ተቀናቃኝ/ ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች ከመሰረታዊ ድርጅት ጀምሮ እዬተመረጠ እዬመረጠ በተወካዮች ውክልና ጉባኤውን እያደራጀ መምጣት ግድ ይለዋል ማለት ነው። ያው ከዜሮ ይጀምራል ማለት ነው እንደ ሌሎቹ።
በአዲሱ ደንቡ፤ ፕሮራሙ ላይም አባላቱ ከታች ከህዋስ// ከመሰረታዊ ድርጅት ጀምሮ እዬተወያዩ መሰረታዊ ሰነዶችን ማሻሻል፤ ማዳበር ይኖርባቸዋል። ስለዚህ ከምርጫ በፊት ኢህአዴግ አዲሱን ፓርቲውን አዴፓን ሲወልድ ዓርማውን፤ ፕሮግራሙን ደንቡን ከማጽደቅ ማዕከላዊ ኮሜቴውን፤ ፖለቲ ቢሮውን እና የቁጥጥር አካላትን መምረጥ ይኖርበታል በጠቅላላው ብሄራዊ ጉባኤው። ይህ በራሱ በአነሰ ግምት ድፍን ሁለት ዓመት ይጠይቃል። በፖለቲካ ውሰኔ ከሆነ ግን በ አጠረ ጊዜ መከወን ይቻላል … ባቋራጭ። ይህ ደግሞ „የነ ተሎ ተሎ ቤት ግድግዳው“ ይሆናል …
በሰል ያለ ሥር የሰደደ ዘላቂ የሆነ የትውልድ መሰረት የሚሆን ፓርቲ ላደራጅ ከተባለ ግን የሰከነ ጊዜ ይጠቅ ይመስለኛል። በታሪካችን የዘለቀ ፓርቲ ሳይከፈል፤ አንጃ ሳይፈጠርበት ኑሮን አያውቅም።
እራሱ የሚዘጋጀው የሰነድ፤ የቅጽ፤ የመታወቂያ ዓይነት ወዘተረፈ ነው። ማብራሪያው ቢጋሩ ሲናሪዮ ስንቱ መሰናዶ … ይህ ሁሉ በአፍነጫ ይወጣ ከተባለ ዘመንን እዬገደሉ መጓዝ ነው የሚሆነው … ትውልድም እዬባከነ ... እና ይህ በጎ ዕሳቤ አስመጪው ወይንም ገፊው ጉዳይ ወሳኝ ይሆናል ማለት ነው።
ያው አቅም መዋለ መንፈስ መዋለ ንዋይ ስለሚፈስበት… ጥንቃቄ በብርቱ ይሻል። ያ ደግሞ ከድሃ በሚገኝ ግብር እና ብድር ነው … ወጪ የሚሆነው … ሠርቶ ለሚፈርስ፤ ፈርሶ ለሚሠራ ሁልጊዜ ብክነት ዘመን ይዞ ተዘመን። አሁን ኢሠፓ ሲደራጅ ስንት መዋለ መንፈስ፤ መዋለ ንዋይ፤ መዋለ ዕድሜ ነው የፈሰሰለት ሲቀልጥ ግን የሰሞናት በቃ። ላይመለስ መራራ ስንብት አደረገ … ራሱን የደመሰሰ ድርጀት።
በሌላ በኩል ደግሞ ጠ/ሚር አብይ አህመድም እንደማንኛውም አባል ከታች ጀምረው የመመረጥ ግዴታ ሊኖርባቸው ነው ማለት ነው። ይህ ከሆነ የአሁኖቹ የካቢኔ አባላት ደግሞ ተሽረው ሌላ እናያለን ማለት ነው። በማዋጣት ሳይሆን ወጥ በሆነ መንፈስ። እንግዲህ ከምርጫ በፊት ከሆነ ኢህአዴግ ይህን የሚከውነው ሦስተኛ የካቢኔ ሹም ሽር ደግሞ ይኖረዋል ማለት ነው። ሌላ ጉጉስ … ሌላ የፍልሚያ ሜዳ …
በዞግ ድርጅትስ እንቀጥላለን የሚሉትስ ምን ሊሆኑ በዓዋጅ ሊከስሙ? ወይንስ በድርድር በወጥነት ሊጠቃለሉ? ወይንስ ራሳቸውን እንደተለመደው ቀዬርን ብለው በተነሱበት ዓላማ ሥር ሊወሸቁ? ኦዴግ አሁን እኔ ከኦዴፓ ጋር እዋህዳለሁ ሲል ፍጹም የሆነ ሐሤት ነው የተሰማኝ፤ ሲዳማ ላይ ሳዳምጥ፤ አሁን ኤል ቲቢ ላይ ቃለ ምልልሱን ሳዳምጥ ደግሞ ቢወቅጡት እንቦጭ ነው።
ለመሆኑ እነ ኦዴግ ሰሞኑን የ7 ቤት አገው 79 ዓመቱን የፈረስ ጉግስ ሥርዓተ ባዕሉን ሲያከብር ምን ብለው ይሆን? ልሙጥ ነበር የእሰተዛሬው አሁን ነው ህብርነቱ ሲሉ ነው ያዳመጥኳቸው፤ በሌለ ባልነበረ ፉርሽ አመክንዮ ስንት ትውልድ ተመተረ? ወጥነት ቢኖር አንድ ሃይማኖት፤ አንድ ቋንቋ፤ አንድ ባህል ብቻ ነው ሊኖር የሚችለው … በቅኝም ብንገዛ እንዲሁ … ክብር ለቀደሙት አያት ቅድመ አያቶቻችን የተግባር አርበኞች!
ለመሆኑ ኢህአዴግ አሁን ያሉትን 7 ሚሊዮን አባላቱን አብሮ አዋህዶ ነው ወይ ይህም ሌላ መከራ ነው? ስንቱ ከእሱ ጋር ሊቀጥል ይወዳል? እንደገናም ወደ እሱ ወደ አዲሱ ፓርቲ ኢዴፓ እጠቃለላሁ የሚል ተፎካካሪ/ ተቀናቃኝ/ ተቃዋሚ ቢኖር እንዴት ለማስተናገድ ተሰናድቷል። ለምሳሌ ህወሃት ከወጣ ቁምጥ ብለው የሚጠብቁ ድርጅቶች ሊኖሩ እንደሚችሉ ከተፈጥሯቸው መተንበይ ይቻላልና።
የሆነ ሆኖ ማፍረስ ቀላል ነው፤ መገንባት ግን በወጥ አይዲኦሎጂ ለዛውም እጅግ ከባድ ነው። አሁን እኮ አገር እያመሱ ያሉት የራሱ ካድሬዎች ጭምርም ናቸው የኢህአዴግ። እንደ እኛ ዘመን ተበትነው ፍዳን ስላልቀመሱ። ሠራዊቱም ውስጥ አና ያሉ መንፈሶች መበተንን አላዩትም እና ነው ያን ያህል ጣሪያ የነኩት ለአንደበታቸው አጥር ያልተበጀለት። አንድ ህዝብን "ሽፋታ" ሲሉ ምን እንደሚያስከትል አያስተውሉትም።
እርግጥ ነው „የሚራገፈው ይራገፋል“ ብለዋል ጠ/ሚር አብይ አህመድ በዬትኛው ጊዜ? በዚህ አዲስ የምርጫ ቦርድ፤ በዚህ የህዝብ ቆጠራ? በዚህ የወጥ ፓርቲ ምሰረታ? በዚህ ሚሊዮን በዬቀኑ የሴራ ፖለቲካ የሚያመርተው ወዘተረፈ አሳር? በዚህ የኦኮኖሚ ድቀት፤ በዚህ የራህበተኛ ቁጥር ማሻቀብ … ሌላም ኩዴታ ሊኖር ይችላል ብሎ መሰናዳትም ይገባል፤ ስንቱ እና የቱ ነው ማኔጅ ማድረግ የሚቻለው። በዚህ ማህል ደግሞ ክፉን ያርቀው እንጂ ነፍስ ባቁማዳ አትያዝ ነገር … የ አፍሪካ ቀንድ ጉዳይ ሲታከልማ ያታክታል ...
እንዲሁም አሁን ደቡብ በሦስት ክልል ሊሸነሸን ነው። የክልል ጥያቄ እኮ የብሄረሰባችን ሊሂቃን ቦታ ያግኙ ነው ሚስጢሩ። ይህስ በምን ሊታይ ነው? ወጥነት በአንድ በኩል በሌላ በኩል ደግሞ ራስነት ወይንም እንደራሴነት?
· ግን የገነገነው ግን …
የሚቀድመው የትኛው ይሆን?የገነገነው የመከራ ቀንበር አውልቆ መጣል ወይንስ በጠለቀው መጥለቅለቅ?
የኔዎቹ ችግሬ ምን እንደሆነ ታውቃለችሁ ጥድፊያ አልወድም። የተጠዳፉ ነገሮች ቀልቤን ያውኩታል። ብዙ መርሃ ግብሮች አሉ ተስፋ ሰጪ ናቸው፤ ግን ከፈተናዎቹ መበራከት ጋር ጊዜ አደብ እዮባዊነት ስለሚጠይቁ ቅደም ተከተላቸው እንደ አፋጣኝነታቸው ቢሆን ምርጫዬ ነው። የኔዎቹ ቅኖቹ ... በዚህው ልከውናው።
#EBC አንድ ሀገራዊ ፓርቲ ለመመስረት እየተደረገ ያለው ጥናት ወደ መጠናቀቂያው መድረሱን ኢ.ህ.አ.ዴ.ግ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ብናልፍ አንዷለም ገለጹ፡፡
#EBC አጋር ፓርቲዎች ከገዢው ፓርተ ጋር እኩል የሚሳተፉበት አንድ ሀገራዊ ፓርቲ በቅርቡ ይፋ እንደሚሆን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ገለጹ፡፡
ኢትዮጵያዊነት ከመፈጠሩ በፊት ፈተናን አሸንፎ የተፈጠረ ሚስጢር።
ኑሩልኝ። ማለፊያ ጊዜ
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ