ዴሞክራሲ ሲቀርጡበት። ሳይቀጥሩበት ሳይቆርጡበት።
እንኳን ደህና መጡልኝ።
ዴሞክራሲ ሲቀርጡበት።
ሳይቀጥሩበት ሳይቆርጡበት።
„ፊታቸውን ሳይሆን ጀርባቸውን ሰጡኝ፤
በመከራቸውጊዜ ግን ተነስተህ አድነን ይላሉ።“
ትንቢተ ኤርምያስ ፪ ቁጥር ፳፯
ከሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
20.02.2019
ከእም ዝምታ - ሲዊዘርላንድ።
ዴሞክራሲ ነጭ ከረሚሎ ነው። ሁሉ ይወደዋል። ሁሉም ይሳሳለታል።
ሁለም ሰፍ ብሎ የትናጋው ማሟሻ ያደረገዋል።
እስታሁን ባለው ዘመን ስልጣንን ፈቅዶ በማስረከብ ኮ/ጎሹ ወልዴን አይተናል። የራስን ክብር ዝቅ አድርጎ ሌላውን ከፍ በማድረግ
በዶር ለማ መገርሳ አይተናል።
እንዲሁም ሲነሪቲውም የመሆን መቻል አቅሙም እያለ እሱን እለፈኝ
ብሎ ለኢትዮጵያ ሲባል እራስን ገርቶ በመገኘት ደግሞ በአቶ ደመቀ መኮነን አይተናል፤ የህውሃት የቆይልን ተማህጽኖ እያለም ግን
በቃኝ ብሎ ሥልጣንን በፍሰሃ በማሰረከብም በአቶ ሃይለማርያም ደስአለኝም አይተናል። እንደ ድርጅትም በታሪክ ታይቶ የማይታወቅ
ታሪኩን አሳልፎ በመሸለም እረገድ ብዴን አንደኛ ነው ዲከርድም በጣሽ ነው። ባይሆን ...
ሌላው የተወካዮች ምክር ቤት አብዛኛው እጅ የ108 ድምጽ
ተቀብሎ ጠ/ሚሩ በሚሰጡት መመሪያ ሥር ራሱን አስገዝቶም አይተናል ከኮንፌድሬሽኗ ትግራይ በስተቀር።
ዴሞክራሲ መራራ መሆን ከመቼውም ጊዜ በላይ ህውሃት በአካል
ያዬታዬበት ዘመን ይህ ነው። ፈተናውን ድርጅቱ ማለፍ አልቻልም። ወደቀ። ስለምን በፊትም አልነበረበትምና። 33ቱ አባላቱ
የተቃወሙትን፤ በአብዛኛው ድምጽ የጸደቀውን የተወካዮች ምክር ቤት ውሳኔ አሻም ብሎ በድጋሚ ውይይት በማድረግ የበላይ አካሉን
ውሳኔ አልቀበልም ሲል ዴሞክራሲ ቀድሞ ባልተፈጠረበት እና ባልነበረበት ሲዘመርለት መባጀቱን አሳይቶናል አይዋ ህወሃት።
ፌድራሊዝም ከቃል አለማለፉንም አሁን ይኸው እያዬን ነው።
ለማዕከላዊ መንግሥት አልገዛም አልተዳደርም በዚያ ማለት ኢትዮጵያ በፌድራሊዝም ውስጥ አልነበረችም ማለት ነው ለእኔ
የሚሰጠኝ ምላሽ። ክልሎች አጼዎች ሆነው የማዕካላዊ ፌድራል መንግሥቱን ውሳኔ ሲያነጥሩት ከላይ እሰከታች የነበረው ነገር
የወረቀት የነበር ስለመሆኑ ሃቁ ፈጦ እዬታዬ ነው። ደግሞ ወግ አይቀርም ህገ መንግሥት ተጣሰም ይደመጣል። እንሱ ያላከበሩትን
ማን እንዲአከብርላቸው ይሻሉ ... ስንት ጥሰት ነው የታዬው በዚህ ባለፉት ወራት ..
በሌላ በኩል ለነፃነት፤ ለፍትህ እና ለዴሞክራሲ እታገላለሁ
የሚለው ወገን በግል እና በጋራ በራሱ ላይ ሲደርስ ደግሞ ወገቤን እያለ እያዬን ነው። ሰሞናቱ የአማራ አክቲቢስቶች
ተበሳጭተዋል። የተበሳጩበት ምክንያት ደግሞ ግንቦት 7 በማርቆስ የተሳካ ስብሰባ በማድረጉ ነው።
አሁን እኔ ይህ ምኑ እንደሚያበሳጭ አይገባኝም። ጎንደርም፤
ባህርዳርም፤ ወሎም ያደረገውን ተመሳሳይ ነገር ነው ግንቦት 7 በማርቆስ ያደረገው። እውን ዴሞክራሲ ለናፈቀው ነፍስ ይህ መሰል
ፉክክር ቢያስደስት እንጂ የሚያስከፋ ሊሆን ባልተገባ ነበር። የውነት በመንፈልገው ውስጥ አለመኖራችን ይህ ሌላው ማመሳካሪያ
ነው።
ፉክክር በመጥፋቱ እኮ ነው በልሙጥ ማንአህሎኝነት ስንባዝን የባጀነው። ይህን
ስል ዴሞክራሲ በራሱ በግንቦት 7 ውስጥ አለ እያልኩኝ አይደለም። እነሱም ደፍረው አለን እንደማይሉ ነው። ጠቅላዮች እንደሆኑ
እነሱም ያውቁታል እኛም እናውቀዋለን። ነገር ግን ዘመን ሰጥቷቸው እነሱም እንዲህ መሬት ላይ መማር እንዲችሉ ፈጣሪ ይህን ዘመን
ስላመጣ አበክሬ አመሰግነዋለሁኝ። ላባቸውን ጠብ አድርገው ጥረው ግረው ካሸነፉ ደስታው የዴሞክራሲ ነው የሚሆነው።
ኢትዮጵያ ህብር ናት። ህብርነቷ በብዙ ነው የሚገለጸው።
በፍላጎት፤ በራዕይ፤ በተስፋ፤ በችሎታ፤ በባህል፤ በወጓ፤ በክህሎት፤ በሙያ፤ በጾታ፤ በዕድሜ፤ በመክሊት፤ በቋንቋዋ፤ በአለባበሷ፤ በአረማመዷ፤ በአመጋገቧ፤ በታሪኳ፤
በዕይታዋ፤ በዕምነቷ፤ በይዘቷ፤ ባሀሳቧ። ይህን ህብርነት ጠብቆ ለመሄድ አቅል አደብ ከሁሉም ይጠይቃል። ይህን ራሱ ግንቦት 7
እንደ አውራ ፓርቲነቱ ዘሎት ወይንም ደፍጥጦት ነው የኖረው። ጭራሽ ትዝ ብሎትም አያውቅም ነበር።
ይልቅ የገረመኝ የማርቆሱ ስብሰባ ላይ ወ/ሮ አሳዬች ታምሩ
የግንቦት 7 ማዕካላዊ ምክር ቤት አባል መባላቸው። ከሆነ ለዚያ ካበቃው ግንቦት 7 ጥሩ ነው። እኔ እማውቀው ግን ነው እሳቸው
የፍራንከፈርት የኢሳት ውክል አካል ሆነው ነው። በሌላ በኩል ከሳቸው በእጥፍ የሚያስከነዱ እጅግም የደከሙ አንስቶችም እንዳሉ
ነው የማውቀው። ለኢሳቱ ውክልናም ከመሼ ነው። ለዛውም ጥሰት ተፈጸመ የሚሉም ነበሩ። ምክንያቱም የአውሮፓው አካል ሳያውቀው
በግል ድርድር ነበር እና አጀማመሩ። ግልጽ ደብዳቤም ለወቅቱ ለግንቦት 7 ኤድትራያል ቦርድ ተጽፎለትም ነበር።
የሆነ ሆኖ ግንቦት 7 በምስረታውም በማጠናከሪያውም እኔ
ፍራንክፈረት አማይን ነበርኩኝ እሳቸውን አላዬሁኝም ነበር። እና የዛሬው ካርድ እንዴት እና በምን ስሌት መሆኑ ይልቅ ግራ
ያጋባል ትዝብትም ይጭራል። ጀርመን አንበሶች ለዛውም የተግባር ያሉበት ስለመሆኑ አሳምረን እናውቃለን። ይህ መሰል ገልባጣ ጉዞ
ቀዳዳ ያበዛል። ዕውነት ዳር ደንበር አለውና።
በራስ ውስጥ ያለው ብቃት ላይ መታመኑ ይበልጥ ያጎላል ሁልጊዜ
ምርኩዝ ከመፈለግ። አጃቢ የቀበሌ ሰው አያስፈልግም ውስጡ ለበቃ ሰው ማዕከሉ ዜግነት ላደረገ የፖለቲካ ድርጅትም። ዶር አብይ
አህመድ ይሁኑ ዶር ለማ መገርሳ የሠፈራችን ሰው ሆነው፤ አብረውን አድገው አልነበረም ሽንጣችን ገትረን የተሟገትንላቸው። አቅም
ያለው ከዬትም ይሁን አቅሙ እንጂ ሌላው ትርፍ ነገር ነው።
እራሱ ግንቦት 7 የመንደር ሰው በዬሄደብት እዬፈለገ ነው፤
ሌላውን ዞገኞች እያለ የሚጠርበው … ዜግነት ማዕከሉ ሰውነት እንጂ የአጥቢያ ድብርነት ድብቆሽ ጨዋታ አይደለም። እውነት ከሆነ የዜግነት ፖለቲካው … ወይንም አሁን እንጀምረው ከተባለም።
በሌላ በኩል ግን ለማናቸውም ነገር አደብ እና አቅል ብቻ
ሳይሆን ራስንም መግራት ይጠይቃል። በራስ ላይ መፈጸም መጀመር። ስለዚህ ዴሞክራሲ የሚፈልግ አንድ ነፍስ በሃሳብ ብልጫ መፎካከር
ነው እንጂ የህዝብን ነፃነት ፈጽሞ መጋፋት አያስፈልገውም።
ነፃ ህዝብ የሚፈልገውን ይምረጥ! ይመቸኛል
ካለ ይመረጥ። የሚመርጠውም፤ የሚያድነውም እሱ ራሱ በወሰነው ድምጽ ይሁን ነው ታገድሎው አይደለም ወይ? እና ይህ አፍጥጦ ሲመጣ
ስለምን ማቄን ጨርቄን ይባላል? ሰው የፈለገውን ድርጅት ይቀላቀል፤ ይደግፍ። የምን ማዕቀብ መጣል ነው።
የነፃነት ተጋድሎው ህዝብ ሃሳቡን የመግለጽ፤ በመረጠው የመመራት
መብቱ ተነፈገ ነው እኮ ወጣትነታችን የገበርንበት ብሂል። ሌሎችም በሲኦል የተቀቀሉበት ሚስጢር። ስለሆነም ስለምን የህዝብ
ነፃነት ይታፈናል? በዚህ ላይ ከሁለት ከሦስት የሚወለዱ ቅይጥ
ማንነት ያላቸው አሉ። የዞግ
ፖለቲካን የማይፈልጉ ይኖራሉ። የሌላ አገር ዜግነት ያላቸውም ትውለድ ኢትዮጵያዊ ይኖራሉ። እነዚህ ነፍሶች ጥግ ያስፈልጋቸዋል። አማራጭ ሊኖራቸው ይገባል። ይህ እኮ ሌላ
ምንም ሳይሆን ሰብዕዊነትም ተፈጥሯዊነትም ነው።
ስለዚህ አማራጭ ነው ባሉት መሰባሰብ መብታቸው ነው የደብረማርቆስ ነዋሪዎች። ሊወቀሱ ሊነቀሱ አይገባም። አብዛኞቹ
የአውሮፓ የግንቦት 7 ጠንካራ ውክሎች ደግሞ የጎጃም ልጆች ናቸው። እና ግንቦት 7 እዛ መሰረት የለውም ማለት አይቻልም። ሁሉም
ወላጅ አለው። ሁሉም ወገን አለው። ለወገኑ መወገን ደግሞ ተፈጥሯዊ ነው። ግንቦት 7 የምንሞገትው ሰውችም ብንሆን ወገኖቻችን
ግንቦት 7 ይደግፋሉ። እኔ ገጥሞኛል። መብታቸው ነው። ነፃነት እያልኩ ጩኼ ነፃነቴን ለግንቦት 7 እሸልማለሁ የሚል ቤተሰቤ
አልጋፋውም፤ አልጫነውም። ኑሮውን የሚኖረው እሱ ነውና ...
እኔ ከግንቦት 7 እሻላለሁ፤ እልቃለሁ የሚለው ደግሞ አማራጭ
ሃሳቡን አቅርቦ ለገብያተኛው ያቀርብ እና ይፎካከር። ዴሞክራሲ እኮ የሃሳብ ገብያ ነው። ሸማቹ የሚመቸውን አማርጦ ይሸምተው። ይልቅ
እኔ እማይገባኝ ጎንደር ሲሄዱ የጎንደር ሰው አዝሎ፤ ወሎም ሲሄዱ ወሎኛውን አስልቶ እሱን አንጠልጥሎ፤ ማርቆስም ሲሄዱ እንዲሁ
ማድረጉ በራስ ላይ እምነት አለመኖር እና እርግጠኛ ካለመሆን ከመሆኑን በላይ የዜግነት ፖለቲካ አራምድ አለሁ ለሚለው ግንቦት 7
ግምት ውስጥ ይጥለዋል። አይመጥነውም። መንደርን መፈለግ በራሱ የተገባ አይደለም። ዜግነት ማዕከሉ ሰውነት ብቻ ነው።
በዚህ አቋም ላይ መጽናት ግድ ይላል ምርጫዬ ነው ካለ ከመሼ ግንቦት 7… እስታሁን እንዳለነበረበት ይታወቃል። ዜግነት ተገርብቦ በደርበቡ ነው የነበረው።
ነበርኩ የሚለውን ለራሱ መልሶ ይንገረው። እኛ መስካሪዎች ስላለን። ምንም ዓይነት የሃሳብ ተቃርኖ ሆነ ተፎካካሪም የማይሻ
ነበር። አቅምን አብዝቶ የሚፈራ ነው የነበረው። አሁን እራሱ ጥሎበት ነው በዚህ ፈታኝ መከራ ውስጥ ሀ ብሎ የገባው። ስለዚህ ያለበት የራሱ ችግር ይበቃዋል …
አንጫጭነው …
የሚያስከትላቸው „ምርጥ ዜጎች ጓዷቹ“ ደግሞ
የዕውነት ቢሆኑ መልካም ነው። እምንታዘብ ስላለን። ከዚህ ባሻገር ባለው ነገር ግን ግንቦት 7 ኢትዮጵያዊ ድርጅት ነው አካልም
ነው ለሚያቀርባቸው መለክዕምድራዊ ክፍሎቹ። ሌሎች የፖለቲካ ድርጅቶች ባሉበት ቁመና ውስጥ ያለ ነው። አይበልጥም
አያንስም። የዜግነት እሩቦም ሲሶም የለም በአገሩ በመሬቱ ሌላው ያለው
መብት እሱም አለው።
ሌላው ገንዘብ በመበትን የሚልም
አድምጫለሁኝ። ውድድር
እኮ ነው። አይደለም ገንዘብ ነፍስም ይገበርበታል። ስለዚህ ይህም ነውር አይደለም። እንደተለመደው በከተሞች በሁሉም ዕድሉን
ካገኘ ግንቦት 7 የማሸነፍ ዕድሉ ሰፊ ነው። ዕድሉን ለማስፋት ነው አሉ የሚባሉ ጋዜጠኞቹን አሁን አገር ቤት
ያስገባው።
ኢሳትን ያህል ሚዲያ ይዞ ግንቦት 7 ነጻ ምርጫ ከኖረ ከተሞቹን
ሁሉ የመርታት ዕድሉ ሰፊ ነው። መረጃ እኮ ነው አሸናፊው። መረጃ በፕሮፖጋንዳ ተቀምሞ ሲቀርብ ህሊናን ረትቶ አሸናፊ ያደርጋል።
ግንቦት 7 አይደለም ለሌላው ድርጅት ለራሱ ለኢህአዴግም ፈተና ነው የሚሆነው። እጥፍ ዘርጋነቱን ደግሞ እስኪዘረዝር ድረስ ያውቅበታል። ካህን ነው ለዚሀ ለዛውም የቆመሰ።
ስለማሸነፉ ግን ሥሙ ገናና ነው። በሥሙ ልክ ቁመናው
ሲባል ብዙ ነገሮችን ብዙ ጭብጦችን በማቅረብ መርታት ይቻላል። ፀንቶ በዓላማ አለመዝለቅ ራሱ በቂ ነው ሌላው ሳይብራራ ...
ኢህአዴግ 7 ሚሊዮን አባል አለኝ ነው የሚለው። ከእሱ ጋር ምን
ያህሉ እንዳለ የሚያውቅ ንጹህ መረጃ የለውም። የመንፈስ ሽፍትነት ደግሞ ከሁሉም የሚበልጥ አደጋ ነው። የተዳፈነ ፈንጅም ነው።
እንዲያውም በለውጡ ምክንያት እትብቱ መስመሩ የተቋረጠ ነው የራሱ የኢህአዴግ። ላይ ተንጠልጥሎ ነው ያለው ኢህአዴግ።
እንዳሻው እንዳይንቀሳቀስ ደግሞ አሁን አቶ አስመላሽ ወ/ሥላሴ
ያህል እግር ብረት ቀንበር ማዕከል ላይ ይሁንብኝ ብሎ እኛንም ይግረማችሁ ብሎ አሳምሮ አስተካክሎ በድርብ መጫኛ ወጣጥሮ ጭኖለኝ። የለመደበት ግርባው ብአዴንም ኦኬ በኦኬ ለጥ ብሎ ሰግዶ ጭነቱን
አደላድሎ ተቀብሏል። ትንፍሽ የለም።
ወ/ሮ ፈትለወርቅ ገ/ እግዚአብሄር በነበሩበት ጊዜ
ሌላም የሚ/ር መ/ቤት ደርበው እዬመሩ አማካሪ አልበረም አሁን ያው አማራ አይታመነም ሌላ ሰንሰለት ታክሎለታል። ለተፎካካሪ/ ለተቀናቃኝ/ ለተቃዋሚዎችም ቢሆን እርምጃው
ማስፈራሪያ ይሁን ቀይ ምልክት አይታወቅም … ብቻ የተጀቦነ ሹመት ተስጥቷለኝ።
ሌላው አሁን በኦነጋውያን ሊሂቃን ያለው አስፈሪ ነገር አይደለም
ግንቦት 7 ሌላም ቢመጣ ምራኝ ማለቱ ህዝብ ግድ ይለዋል። ግንቦት 7 የመንፈስ አቅም አለው ወይ ቢባል ደግሞ ሁላችንም
ስለምናውቀው በአንድ ጀንበር ጳጳስ የሚያደርገው አቅም ሊፈበርክ ፈጽሞ አይችልም። ዴሞክራት ነኝም አይልም፤ ተረብ ስለሚሆን … ሊበራል ነኝ የሚለውም ለጨዋታ መሟያ ነው የሚሆነው። አንድ ብዕር የሚያርደው እዬዞረ „አስወገዱልኝ እገዱልኝ“
እያለ የድህረ ገጽ ባለንብረቶችን ሲማጸን ውሎ የሚያድር ወቃሳን በጽኑ የሚፈራ ግን ፖለቲካ ድርጅት ለዛውም አውራ።
ስለዚህ አቅም አለኝ የሚል ሁሉ አቅሙን በረጋ መንፈስ አደራጅቶ
ቀምሮ ተፎካክሮ ለመውጣት መሬት ላይ መስራት ይገባዋል። ግንቦት 7 አልተመቸኝም የሚል ሁሉ እንጂ ግንቦት 7 አማራ ክልል ህዝብ
መሰብሰብ የለበትም የሚለው ውግዘት የተገባ አይደለም።
ይህን የሚባል ከሆነ ሁሉም ሰው በኢትዮጵያዊነት መንፈስ ውስጥ አብሰንት
ሁኗል ማለት ነው። ይህ ይልቅ የሚያስፈራ ነው የሚሆነው። አማራ
ክልል ቢሮ መክፈት መብቱ ነው ከማንም የማይለምነው፤ ሃሳቡን ካለምንም ተጽዕኖ የመስበክ መብቱ ነው ከማንም ተንበርክኮ
የማይማጸነው፤ ዜጋ ነው ግንቦት 7 እንደ ድርጅት ድርጅቱ፤ አባላቱም እንደ ተፈጥሯቸው። ሊገደብ ፈጽሞ አይገባም። መብቱ እኩል
ነው።
ማን ዜግነትን ሰጪ ማን ዜግነትን ነሽ ነውና። ይልቅ
ተደራጅትህ መመከት ነው። ይቅርበኛል ከእሱ አላገኘውም የምትል ዜጋ ሁሉ የፊት ለፊት የተጋድሎ መስመርህ በብልጫ አዲስ እሸት ሃሳብ
ተፎካክረህ በነፃ ሜዳ ላይ ማሸነፍ ወይንም መሸነፍ። መሸነፍ ከመጣ ደግሞ ልክ አንደ ማርቆሱ ሰሞናት በጸጋ ለመቀበል ከሁሉም ይጠበቃል።
ሌላው ጠ/ሚር አብይ አህመድ ደጋግመው የሚሉት ነገር አለ። „ከተሸነፍን እንለቃለን ይላሉ።“ ከሆነ ጥሩ ነው። ሠራዊቱ
ባዕል ላይ ግን ለእኔ ይህን አላመለከተኝም። ያም ብቻ አይደለም። ተፎካካሪዎች በሙሉ የሚገኙት አማራ ክልል ላይ ብቻ ነው። ይህ ጭንጋፍ ጉዞ
ዴሞክራሲን አምጦ አይወልድም። በፍጹም። ምስሉ ጠንጋራ ነውና …
ማናቸውም ብሄራዊ ፓርቲ በሁሉም ክልል ተዘዋውሮ ዓላማውን
አሳውቆ፤ ሰብኮ፤ ሙግቱን እረቶ ቢሮውን ከፍቶ በሰላም ወጥቶ ገብቶ፤ ጥሮ ግሮ ለፍቶ ከሥልጣን እንዲወጣ የሚያደርግ ምንም ቅድመ
ዝግጅት የለም። የመንፈስ እንኳን። ቀኑ እዬሮጠ ነው፤ እርምጃው ደግሞ እንደ ጉም ሽንት አማራ ክልል ብቻ ቻል ተብሎ ቸክሏለኝ።
አውራው ፓርቲ ኦዴፓ በጉባኤው ላይ
እኮ ብሄራዊ ፓርቲዎችን አላሳተፍም። ማሳተፍ ቀዳሚ ተግባሩ መሆን ነበረበት አብነት የ አውራነት ከዚያ ነበር የሚጀምረው። ብሄራዊ ፓርቲዎች ህዝብ ማነጋገርም አልቻሉም። ኦሮምያ፤ ትግራይ ቤንሻንጉል፤ ጅጅጋ፤ ሀረሬ፤
ጋንቤላ፤ ላይ የየክልሉ ሊሂቃን እንዳሻቸው ተፎካካረው ይወጣሉ አማራ መሬት ግን በድርብብርብ፤ በንብብርብ ዲስክርሜንሽን በመጫን
የአማራ ሊሂቃን አቅማቸው እንዲታወክ፤ አቅማቸው እንዲሳሳ በሚያደርግ ስልት ዴሞክራሲ አይመጣም። ፈጽሞ። ግልብጥ ዴሞክራሲ ነው
የሚሆነው በአንድ እጅ እንደ ማጨብጨብም። ዝንጥል ዴሞክራሲ ደግሞ አገርን ለትውልድ በሚተርፍ መልክ አያተርፍም። ግንጥል ጌጥ ነውና።
እርብርቡ የአማራ ከፖለቲካው መስመር የ27 ዓመት መገለልን
የሞት መንገድ ነው እኔ አሁንም በተሃድሰ እማዬው። በዚህ በተፎካካሪዎች ስብሰባ ላይ ያዬሁት ምስል እና ሳቅና ፍንደቃም
ሚስጢሩ ያ ነበር ከፎቶው እንደተረዳሁት። ፎቶ አንባቢ ነኝ እኔ። ፍንክክንክ ነው ያሉት በመፍለቅለቅ። አማራ ሙጣጭነት ተቀብሎ እስከ መቼ?
ምክክርም የተደረገበት ይመስለኛል ራሱ ብአዴንም
እንደለመደበት አሻቅቦ መጠዬቅ ከባብዶታል። ኢህአዴግ
ድፍረቱ ካለው በሁሉም አገሪቱ ክፍሎች ለብሄራዊ
ተፎካካሪዎች በሩን ይክፈት። እኔ
አሁንም ስጋት አለኝ ቢሸነፍ ኢህአዴግ ግስላነቱ
አይቀሬ ይሆን እላለሁኝ።
መቼም የኦሮሞ ልጅ ይህን ዕድሉን አሳልፎ ይሰጣል ተብሎ
አይታሰብም፡፤ ፈጽሞ። ለዚህም ነው አንድም ተፎካካሪ ድርጅት በክልሉ ሳይፈቀድ ኦዴፓ በሌላው ትክሻ ዴሞክራሲ መሰረት ይጣላል
የሚለው። ይህን ተፎካካሪ ነን
የሚሉም ከፍርሃት ቆፈናቸው ወጥተው ጠ/ሚር አብይ አህመድን መሞገት ይኖርባቸዋል። የህዝብ
ተወካዮች ምክር ቤትም።
በተዘነጠለ የዜግነት ግዴታ ግርዶሽ
አገር አትቆምና። ዜግነት የሁሉም ድርሻ እንጂ የአንድ ክልል ብቻ ግዴታ አይደለም። ለዛውም
በጠላትንት በተፈረጀ ማህረሰብ። ይህን ሚዛን ማሰተካከል ይገባዋል ፌድራሉ መንግሥት። ዴሞክራሲ ማለት ከራስ መጀመር ማለት ነው። ግብር
ከፋዩም እኮ አማራ ነው። ለዛውም ከሁሉም ክልል በእጥፍ ድርብ የታክሲ ታሪፍ። ድህነቱም አማራ ላይ ነው።
ሲጠቃለል የአማራ አክቲቢስቶች ረብ በሉ። አማራነት ኢትዮጵያዊነትም ነው። ኢትዮጵውያን ሁሉም
ቤታቸው ነው። ወገኖችም ናቸው። ደሞቻችንም ናቸው። ለእኛ አይሆኑም
ስጋቱ የተገባ እና በተግባር የታዬ ነው። ነገር ግን ይህን መመከት የሚቻለው በተደራጀ እና በሰከነ ብቃት እንጂ ዳር ድንበር
ሰርቶ አይደለም።
በኢትዮጵያዊነት ውስጥ የዳር
ልጅ፤ የእንጀራ ልጅ፤ የጡት ልጅ የሚባል የለም። በፖለቲካ ድርጅት የተለመደ ነው። እኛ እርቦ የዜግነት ድርሻ ሳይኖረን በስውር
እስር ቤት ነው የባጀነው … ግን በእምዬ ቤት ሁሉም ልጅ ነው የጡት ሰብል።
በሌላ በኩል ለሰው ልጅ አማራጭ እንዲኖረውም ፈቃጅም ነሺም
የለም። ሊኖርም አይገባም። ይልቅ ሁሉ ክልል ክፍት ሆኖ በእኩልነት መንፈስ ፉክክሩ ህብራዊነቱ እንዲደምቅ ፌድራል መንግሥት
አፋጣኝ እርምጃ መውሰድ ግድ ይለዋል። ያመጣጥነዋልም ቀለሙም ህብራዊነቱም ማራኪ ያደርገዋል። ጫናውንም ውጥረቱንም ይቀንሳል።
የራሰን በር ከርችሞ ሌላው ተሸከምልኝ ገመናዬን ግን ይሉኝታ
ቢስነት ነው … አብሶ ለአገር መሪው
ለኦዴፓ። በሌላ በኩል ብሄራዊ ነኝ የሚሉው
ግንቦት 7 ቢሆን 80 ብሄር እና ብሄረሰብ አገር እንመራለን ከሆነ ህብረነቱን የሚያስጠብቅበት መንገድ መፈለግ
ይገባዋል። ወይንም የአማራ ድርጅት ነን ብለው
ይወጁ እና ይለይላቸው። ጫካ በአማራ ትክሻ አገር ቤትም በአማራ ትክሻ ላይ ብቻ የዜግነት ፖለቲካ አያስኬድም ሎጅኩ።
ለገዢው ፓርቲ ለኦዴፓም ለምዕራባውያን አንድም ተፎካካሪ ውጭ
የሌለ አለመሆኑ ሳይሆን ቁምነገሩ ተፎካካሪው በመላ አገሪቱ ተዘዋውሮ የመሥራት መብቱ እስተምን ተከብሮለታል ነው ቁምነገር ሊሆን
የሚጋባው። ቢሮ የመክፍት መብቱን ማስጠብቅ ነው ቁም ነገሩ … ፎቶ ስንቅ አይሆንምና …
ዴሞክራሲ ታሪፍ አይደለም።
ዴሞክራሲም መቀጣጫም አይደለም፤ ዴሞክራሲም ለአንዱ ዕዳ ለሌላው ገጸ በረከት አይደለም። ከእኔ ቤት አትድረስ ብለህ ዴሞክራሲ
ምርጫ አደርጋለሁ ማለት ዘበት ነው።
መጀመሪያ
የራስህን ቤት ቧ ፏ አድርገህ
ክፈት አቤቶ ኦደፓ አውራው ፓርቲ… ነህና! ዘመን ተዘመን በጭነት ይስመጥ፤ ትንፋሹስ ይሰነግ የእኔታው ማህበረሰብ ማለቱንም
እባክህ ተለመነን ተግ አድርግለት 9 ወራት ሙሉ አንድ ክልል ላይ መጫን ሁሉን ነገር መጫን? በውነቱ ግፍ ነው … እሺ አቤቱ ኦዴፓ!
· ለማጠቃለያ የሚሆነው ግን …
አገር የጥላቻ ማመረቻ መሆኗ ይሰቀጥጣል። መጣችሁልን ቀርቶ
መጣችሁብን ያማል። ምን ይሁን ምን እንግዳ የአብርሃም ነው። ውሻ እንጂ የሰው ልጅ በቤቱ መኩራት አይኖርበትም። ለዛውም ለጋራ
ቤት … „ፍቅር ነሳን፤ ፍቅር ፈራን“ ታላቅ
ትንቢት ነበር ለካ … ሞትም እንዳለ እንሰበው ...
ዴሞክራሲ ከጫዋታ
መሟያነት ትንሽ ፈቅ ብሎ ለማዬት ናፈቀኝ!
አገር የሁሉም
መንፈስ ናት!
የዜግነት ሲሶ
እርቦ የለውም!
የኔዎቹ ኑሩልኝ።
መሸቢያ ጊዜ።
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ