ኢትዮጵያዊነት ዩንቨርስቲ ሊከፈትለት የሚገባ ገናና ማንነት ነው።

እንኳን ደህና መጡልኝ።

ዘመን ኢትዮጵያዊነትን
ይከሳል - ይፈውሳልም!
„ኃይልን የሚያስታጥቀኝ፤ መንገዴን የሚያቃና፤
እግሮቼን እንደ ብሖር እግሮች የሚያረታ፤
በኮረብቶች የሚያቆመኝ፤ እግዚአብሄር ነው።“
መዝሙር ፲፯ ከቁጥር ፴፪ እስከ ፴፫

ከሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
06.03.2019
ከእመ ዝምታ - ሲዊዘርላንድ።

                                                                     መካሻ!

·       ወግ ቢጤ በሲቃ …

እኔዴት ናችሁ ክብረቶቼ? ዛሬ ወግ ወግ ብሎኛል … እንዲህ … 

እኔ ውጭ ስወጣ ከገጠመኝ ፈተና አንዱ የኢሠፓ መደበኛ ሠራተኛ መሆኔን እንድደብቅ ነበር ምክሩ እና ዝክሩ። እኔ ደግሞ ምንም የማፍርበት፤ አንገቴንም የሚያስደፋ አንዳችም ጸያፍ ነገር ስላልሰራሁ በአደባባይ የኢሠፓ ቋሚ መደበኛ ሠረተኛ እንደ ነበርኩኝ አወጅኩኝ።

 የሚገርመው ይህን የሚሉት በዘመነ ኢሠፓ የገበሬ እና የሠራተኛ ልጅ እዬተባሉ፤ ወይንም በራሱ በ ኢሠፓ ለከፍተኛ ትምህርት የተላኩት አውሮፓን ያጥለቀለቁት በስኮላርሽፕ ተልክው የተለያዩ ሙያ ሊቀ - ሊቃውንት የሆኑት ናቸው። የበሉበት እጅ የሚቆረጥሙ … ደርግም እንደ ብአዴን እጁ አመድ አፋሽ ነው … ተጠቃሚው እራሱ አያመሰግነውም እኮ … ተጠቃሚው ስል በገሃዱ ዓለም ጨርቅና ወርቅ አይደለም ሙልጭ ያለ ድሃ ነው የ ኢሠፓ ይሁን የደርግ ሠራተኛ ፤ ግን በመንፈስ ልዕልና ጽናቱ አነቱ ነበር … 

ሰብ በመቀረጽ ሂደቱም እጬጌ ነበር። ፍጽምና ከማንም ባይጠበቅም ለዛ ዘመን የሚመጥን የሚልቁ ብቁዎች ነበሩበት አበረው አመድ ለብሰው አይሆኑ ሆነው ባከነው ቀሩ እንጂ …  እማዝነው አሁንም ትውልዱ ለአዲስ ብከነት ኦነጋውያን አና ብለው ተያይዘውታል፤ ህወሃት የለመደበት ነው፤ ለነገሩ ባልና ሚስት ከአንድ ወንዝ አንዲሉ …

ኢሠፓ ፓርቲዬ መራራ ስንብቱ በራሱ ጊዜ የተጠናቀቀ ቢሆንም፤ በትኖን ቢበተንም፤ እምለሳለሁ ቢል ቤተኛ ለመሆን ባልፈቅድም ግን እማፍርበት የፖለቲካ ፓርቲ አለመሆኑን ግን አንገቴን ቀና አድርጌ በኩራት ነው እምናገረው።

እኔ እና መሰሎቼ ያደራጀነው እኮ ነው አሁን ህውሃት ይሁን ብአዴን፤ ደህዴን ይሁን ኦህዴድ የሚዘበነኑበት። ቆላ ደጋ ተወጥቶ ተወርዶ በእግር 6 ቀን ተጉዞ እሳር ላይ እዬታደረ፤ ወንዝ እዬተሻገረ፤ አቀበት ቁልቁለት ተማስኖ ነው ህዝብ የሚደራጀው። የዛ እርሾ ነው ያለው። እሱ የበላውን በልተን፤ እሱ የሚኖረውን ኑሮ ኑረን አፈር ሆነን ትቢያ ለብሰን

 ወጣትነታችን በፈቃዳችን ሳንሳለት ገብረን … ኑሯችን ሳንጠነቀቅለት ሰውተን … ነው ህዝብ ያደራጀነው … ህወሃት በሰላው ገብቶ ነው ጉራውን ሲቸረችር የባጀው … እሱማ በአይነ ምድሩ ግድግዳ ላይ ማሌሊት ያሸንፋል ይል የነበረ ከንቱ ድርጅት ነበር …
   
ውዶቼ … በዘመኑ በነበሩ መንግሥታዊ አካል በደርግ ተዘርዝረው የማያልቁ መልካም ነገሮች ነበሩ። አብሶ ሰብዕን ሙሉ አድርጎ ብሄራዊነትን አጉልቶ በማውጣት እረገድ ያልሞትን ያልታመምን በምንም ጸያፍ ሆነ ወራዳ ነገር ስማችን ተነስቶ የማያዋቅ እሱ ኮትኩቶ ያሳደገን ጽኑ ልጆቹ አለን።

በሃሳብ መለያዬት ያለ የነበረ ቢሆንም በዘመን ደርግ አንድ ሰው ለፖለቲካ ሃላፊነት ሲታጭ እንዲህ በመደዴው አልነበረም። ሰልጥኖ ነው። ወደ ኢሠፓ አባልነትም  በእጩ ጊዜ አንድ አመት ተጥንቶ ነበር ሙሉ አባል የሚኮነው። ስንት ውይይት ፍጭት ተደርጎበት። አስተውሉ ወገኖቼ ለአካልነት አይደለም ለተራ የፓርቲ አባልነት ... ሰው ማበጀት ፓርቲዬ ኢሠፓ ያውቅበታል። 

እያንዳንዷ መመሪያ፤ አወጅ፤ ማብራሪያ፤ የአፈጻጸም መመሪያ ሁሉ በሥርዓት ተጠንቶ፤ ተመረምሮ ነው ለህዝብ የሚቀርበው። ለህዝብም እንደለ አይቀርብም ማንኛውም አዲስ ነገር። እራሳችን ወርደን አስጠንተን ነው የሚፈጸመው። ለዬትኛውም ጥያቄም አፋችን ሞልቶ የሚያናገር ብቃቱ ነበረን።

በሌላ በኩል ዛሬ የምናዬው በቀላሉ ሰውን ለማግኘት የሚያስችለው የገበሬ ነዋሪዎች፤ የከተማ ነዋሪዎች ማህበር ያን ጊዜ የተፈጠረ ነው። የአገልግሎት የህብረት ሥራ ማህበራት ሁሉ ነበሩ። ለገበሬዎቹ የሸቀጥ ዕቃ የሚያቀርቡ። የራሳቸው ወፍጮ ቤት ሁሉ የነበራቸው …
የቤት ቁጥር ቀበሌ ከፍተኛ ወዘተ በደርግ ዘመን የተከወኑ ናቸው። የመሬት ላራሹን እና የከተማ ትርፍ ቤቶችን አዋጅ ተከትሎ ብዙ መንግስታዊ ተቋማት ነው የተገነቡት።

ከእያንዳንዱ ዓዋጅ ቀጥሎ የሚ/ር መ/ቤቶች ይደራጃሉ፤ የሥራ መስክ ይፈጠራል፤ የሥልጣኔ በር ይከፈታል … ወዘተ ወዘተ … በዛን ጊዜ ከዩንቨርስቲ የመሚመረቅ ማንኛውም ምሩቅ እራሱ መንግሥት ነበር የሚመደበው።

ከዩንቨርስቲ ብቻ ሳይሆን ከኢንስቲቲዮች፤ ሆነ ከኮሌጆች የሚመረቁትን መንግሥት ነው ሥራ የሚደለድላቸው እንጂ የትም አይበተኑም፤ ዛሬ እንጨት ተለቅሞ ማሰሪያ እንደሌለው ማንም ባለቤት የለውም። ለዛውም ምን ባይረስ ህሊናው ተሸክሞ እንደሚወጣ ደግሞ አሁን ያላቸውን ኢትዮጵያን ማንበብ ነው። ሰው መሆኑ ተደርምሶ ነው በህሊናው የሚመረቀው። 

የህውሃት፤ የኦነግ ተልዕኮ ትውልዱን በራሱ ውስጥ ማጥፋት ነው። ራሱን አስክዶ ንፋስ ላይ ማንሳፈፍ። ሴሉ የወጣ ነፍስ። መነሻ የሌለው መድረሻ … ብቻ ህወሃት አረሳት ኢትዮጵያን በብተናው ሴራው … የፖለቲካ ሊሂቃናትም … እንዲሁ ... 

የሚገርመው ዕድሉን አግኘተው ሚዲያ ላይ የሚወጡትም የደርግ ወይንም የኢሠፓ መደበኛ ሠራተኞች ቢሆኑ በዛ ዘመን የነበሩትን በጎ ነገሮች ለመግለጥ አንደበታቸው እስር ነው። ይፈራሉ። ይሸማቀቃሉ። የካራማራ ድልም እንዲህ ሆኖ ተምሶ ተቀብሮ የኖረው አገራዊ ታላቅ ገደል በዚህ ምክንያት። ሻብያም ኢህአፓም ያን ህዝባዊ ቁጣ ለማርገብ እና የሱማሌ አሸናፊነት በኢትዮጵያ ላይ እንዲረጋገጥ ቢሰሩም  ….

ቀደም ብዬ በገለጽኩት የአደረጃጃት ስልት አማካኝነት በከተማ እና በገጠር ህዝብ በሰፊው ተቀስቅሶ ኢትዮጵያ ከሱማሌ ባርነት ተገላገለች። እሰቡት ወገኖቼ ሱማሌ ከኢትዮጵያ ተሽላ ነው ኢትዮጵያን ለመግዛት በመታበይ የተነሳቸው … ሱማሌ ገዝታን ቢሆን ብላችሁ እሰቡት?

አሁንም ይህን መሰል መከራ እንዳይመጣ እሰጋለሁኝ። የጃዋርውያን ጉዞ እሱ ስለሆነ … ክፍት ሲሆን ኦነጋውያን አያርፉላትም ለሚጠሏት ኢትዮጵያ ዛር አውልያ አለባቸው … የሚያሳዝነው ያ ሁሉ ፍቅር የዘነበለት „ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው“ የግድግዳ ጌጥ ሆኖ ቀርቷል። ቢያንስ ለሰብዕዊ መብት መቆም ተስኖት ወገኖቹን እያስለቀሰ ይገኛል። ማስለቀሱ ብቻ ሳይሆን ማስለቀሱ ህጋዊ ሽፋን መሰጠቱ ነው የሚያንገረግበው።

27 ዓመት አና ብሎ ስልጣን ላይ የቆዬው ህወሃት ሆነ አሁን በእግሩ የተተካው እንቦቅቅላው በመዳህ ላይ የሚገኘው ኦነጋዊ መፈንቅለ መንፈስ ለዚህ ድል የበቁት የዛን ጊዜው የተጋድሎ ሰንደቅ ባስገኘው ገደል ስለሆነ ማተብም ልብም አንገትም አልሰራላቸውም። መልሰው ድንጋይ ጫኑት። 

ወደ ቀደመው ምልሰት ሲሆን ከሱማሌ ቅኝ ተገዢነት የታደገው ያ የተደራጀ የአርበኝነት ውሎ ያ ገደል ውሹን ያነሳ ውሹ ተብሎ 27 ዓመት በኦነጋውያን በወያኔውያን ጋብቻ ተምሶ ተቀብሮ ተኖረ።

ሌላው ቀርቶ ደማቸውን ያፈሰሱላት ኢትዮጵውያን ድሬ ላይ ምንያህል ሰቀቀን ምን ያህል በግዞት በ40 /40 /20 ተሰቅዘው እንደኖሩ ይታዋቃል። ያቺ አፈር የደም መሬት ፍሬ ነበረች። መምረጥ እንጂ መመረጥ ተነፍገው፤ የበይ ተመልካች ሆነው የኖሩት ኢትዮጵውያን በደማቸው ላይ የቆሙ በባለጊዜዎች ተረገጥው እንሆ በምድራቸው በባይታዋርንት እያተገላበጡ ግፍ እና መገለል ሲያንገበግቧቸው ባጁ። አሁንም እንደማዬው ነገረ ድሬ እና ነገረ አዲስዬ መከራቸው ገና ነው። ራሱ የጠ/ሚር የህዝብ ለህዝብ የግንባር ንግግር አልተፈቀደላቸውም። ተዘለዋል። ለምን> እዮር ይጠዬቅ ... 

የሆነ ሆኖ እንሆ ዘመን እንዲህ ይክሳል እና ትናንት በዬሚዲያው የካቲት 26 ቀንም ቀን ሰጥቶት ወግ ደርሶት ተዘከረ። ድሬም፤ ጅጅጋም፤ ካራማራም፤ ጎሬም ደስ ይበላቸው። ሐረር የፍቅር አገር የወትሮዋ ለዚህ ቀን ያበቁን የአዲስ አበባ ብሩህ ወጣቶች ትናንት በመነሻ ሥሙ ነው እኔ እምገልጸው በድላችን አደባባይ ተገኝተው ጉንጉን አበባ ከ27 ዓመት በኋዋላ አስቀምጠዋል።

ለዚህ ድል ራሺያ፤ የመን፤ ኪዩባ ነፍሳቸውን፤ መንፈሳቸውን ኑሯቸውን ገብረዋል። ግን እኛ ውለታ ቢስ ነን። ቢያንስ እነሱን መዘከር ተሳነን። አሁን ካሱን የአዲስ አባባ ወጣቶች። መካሻ! ለዚህ ድል የኮ/መንግሥቱ ቆፍጣና አመራር የወቅቱ ቀንበጥ የጦር አዛች እና መሪዎች፤ የ አዬር ሃይል፤ የምድር ጦር ቅንጅታዊ ገደል፤ የኢትዮጵያ ህዝብ ሙሉ እና ቅን ተሳትፎ ዛሬን ሰጥቶናል። ቢያንስ አገር አለን እንድንል። ቢያንስ በቅኝ አልተገዛነም እንደልን አስችሎናል። ኢትዮጵያዊነት መካሻ ወደር የማይገኝለት ማንነት ነው።

እኔ እንባዬን እያፈሰስኩ ነበር የታደምኩት። እኔም በደርግ ዘመን ነው ያደግሁት፤ የተማርኩት፤ ሥራ የያዝኩት፤ በፖለቲካ ጉዳዮችም ሳድግም ለቁምነገር ስደርስ በጥዋቱ በቀንበጥነቴ ነበር ሳላስበው ተጠልፌ ገብቼ የታደምኩኝ ስለነበረኩኝ እንደገና የተፈጠርኩ ያህል ነበር የተሰማኝ። መዝሙሩን ስሰማ ራሱ የተለዬ ስሜት ነው ያለኝ። 

እነዚህ የአገር አድባር የሆኑ የአዲስ አባባ ወጣቶች ምን ሲል እንዲህ ዓይነቱን ቅን መንፈስን የሚያድስ፤ ቁስልን የሚፈውስ በኽረ ጉዳይ እንዳሰቡት እራሱ ግርም ነው ያለኝ። ምን ሲል ትዝ አላቸው ግን? 

በዛን ዘመን የተሰዉ በስሜን ይሁን በምስራቅ ለሉዕላዊነት ኢትዮጵያውያን ህይወታቸውን ለገበሩ አርበኛ ልጆች የህጻናት አንባ ዝዋይ ነበር፤ አካላቸው ለጎደለው ደግሞ የጀግኖች አንባ ነበር። ሁለቱንም ቦታዎች የካቲት 66 የፖለቲካ ኢንስቲቲዩት ተማሪ በነበርኩበት ጊዜ ሄጄ አይቸዋለሁኝ።

የልጆች አያያዝ ትዝ ይለኛል። እናትም አባትም እንዳያማራቸው አዛውንታት ሞግዚት ሁሉ ነበራቸው። የጸጉራቸው የሴቶቹ አሳራር፤ ሪባናቸው፤ የዩኑፎርማቸው ጽዳት አይረሳኝም። የክፍላቸው እና የግቢው አደረጃጀትም እንዲሁ። ያ ሁሉ ነው በበቀል እምሽክ ብሎ የደቀቀው። ራሱን የቻለ አገር ነበር። 

ደርግ የሚያስወቅሰው እንዳለ ሁሉ እጅግ የሚገርሙ በዛ ዘመን ሊታሰቡ ከቶም የማይችሉ፤ ዛሬ እንኳን የሌለን ድንቅ ተግባራትን ሲከውን ነበር። የሚገረመው ልጆች 12ኛ ክፍልን ከጨረሱ በኋዋላ ደግሞ ወደ ኪዩባ ለከፍተኛ ትምህርት ይላኩ ነበር።

እራሱ ለጥበብ የነበረው ድንቅ ህልም  … የኪነት ቡድን በማደራጀት ሰፊ ተግባር ይከወን ነበር። በዬ15 ቀኑ የፖለቲካ ትምህርት ቤት ተማሪ ሆነን፤ ብሄራዊ፤ ራስ፤ አገር ፍቅር፤ ማዘጋጃ ቤት ቲያትር ቤት ሁሉ እንድንሄድ ይደረግ ነበር። 

መ/ቤቶችን፤ ድርጅቶችን ተቋማትን እንጎበኝ ነበር ሁለንትናዊ እወቅት እንዲኖረን፤ ተግባራቸውን ደግሞ በመሰናዶ የት/ክፈለ ጊዜ በወል በአዳራሽ እንማር ነበር … ዶር ላፒሶ ላሬቦን እማስታውሳቸው ያን ጊዜ ነው። ሰሞኑን ጋዜጠኛ አበበ ገላው ከአንድ አፍታ ጋር ከጸሐፊ አቶ ስዩም ተሸሞ ጋር በነበረው ቆይታ "ደርግ ሶሻሊዝምን ራሱም አያውቀውም" ሲል አዳምጨዋለሁኝ፤ ሥራችን ምን ሆኖ? አሳምረን እናውቀዋለን የምንመራበትን አይዲኦሎጂ። 

ለዛውም በሚገባ ሰልጥነን በአገር ውስጥም በውጭ አገርም ስለሶሻሊዝም ንደፈ ሃሰብ ራሰሱን ችለን እንማረው ነበር፤ ያ ብቻ ሳይሆን ለቃላቶች መፍቻ እራሱ መዝገበ ቃላት ሁሉ ነበር።

ፍልስፍና አንዱ በመደበኛ የምንማረው የትምህርት አካል ነበር፤ ካፒታል የማርክስ የሰርፕላስ ባልዩ አፈጣጠር ቲዮሪ፤  የዘመኑ ባህሪ ሌላው ነበር ይህ ደግሞ ለዲፕሎማሲያዊ እሳቤ የሚረዳ ወይንም ዓለም አቀፍ ግንኙነት ለሚለው ዘርፍ የሚረዳ ነበር፤ የኢትዮጵያ ታሪክ በጥልቀት ነበር የምንማረው፤  የዓለም ታሪክ፤ የአፍሪካ የነፃነት ታሪክ እና ፓን አፍረካኒስትነት። የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ፤ የንግግር ጥብብ ወዘተ …

አንገናኝም እኛና ሌላው የፖለቲካ ካድሬ። ለዚህ እኮ ነው የትኛውንም የፖለቲካ ድርጅት ሳንቀላቀል የኖርነው አብዛኞቻችን። በቋንቋም በልምድም አንገናኝም። ልንግባባም አንችልም። እኛ ህጋዊ ሆነን መሬት ላይ የሠራን ነን። ሌላው ደግሞ ቲወሪ ላይ የተንጠለጠለ፤ ህጋዊ መሬት ያልነበረው ነው። በሌላ በኩልም በመደበኛ ዕድሉን አግኝቶ ሶሻሊዝምን አልተማረውም።

ይህ ሁሉ በመጸሐፍም ተጽፎም፤ 20 አመት ሙሉ በተለያዩ ሚዲያዎች ተጽፎም ተነቦም የማያልቀው ምንጩ እኮ ፓርቲዬ ኢሠፓ ስላስተማረኝ ነው። እሱ ብቻ አይደለም በማዕቀብ ተከድኖ ተቀብሮ ቀረ እንጂ ስንት እንቁ ነገር አለ በእኛ ውስጥ እሱም እራሱ አቤ ያውቀዋል ሠርቼ እማልደክም ሴት መሆኔ። ስንት ሃሳብ ህሊናዬ ውስጥም እንዳለ። 

በግል ኑሯችን እራሱ ሰው ለእንግድነት መጥቶ ተምሮ ነው የሚሄደው። ምድረ በዳ ይሁን ኑሯችን በቅጡ አደራጅተን የመኖር አቅሙ ተዝቆም አያልቅም … ሙሉ ሰው አድርጎ ነው የሚፈጠርን ፓርቲያችን። ደርግ ይመራበት የነበረውን ዲሞክራሲያዊ አብዮት ሽግግሩ ወደ ሶሻሊዝም የነበረውን አሳምሮ አበጥሮ አንጠርጥሮ ያውቀዋል። 

በገጠር አማራቾች ህብረት ሥራ ማህበራት፤ ማልባ ወልባ ወላንድ ስንቱን ልዘርዘረው … እድጋታቸውን ጠብቆ ገጠሩን ኢንደስትሪያላይዝድ የማድረግ ውጥኖች ነበሩበት፤ ለዚህ ደግሞ እነ የትኑራን ለናሙና ማንሳት ይቻል ነበር፤

በሌላ በኩል ለህሊና ማጎልባቻም… እጅግ በሳል የሆነ ያን ጊዜ የሚታታም በዬሶስት ወሩ የሚወጣ የንድፈሃሳብ መጽሄት ነበር መሰከረም። እሱ ራሱ ፖለቲካ ት/ቤት ነበር። እርግጥ ትንተናው ከበድ ያለ ነበር። 

የኢሠፓም የራሱ ልሳን ነበረው ሠርቶ አደር … ቀድሞ ነገር ያን የመሰለ በሳል የንደፈ ሃሳብ መጽሄት ዳግም አልተፈጠረም። መስከረም መጽሄትን የመሰለ የንድፈ ሃሰብ በሳል መጽሄት ትክክል በእሱ አቅም ልክ የሆነ አላዬሁም። ጦቢያ፤ ሙዳይ እና አፍሪካ ቀንድ አቅጣጫውን እርግጥ ነው ጀምረወት ነበር ... ሌላው ግን ዘበት ነው፤ የጦብያ አዘጋጆችም ነፍሳቸው ክህሎቱ ከዛው የተቀዳ ነው ከቤተ - ኢሠፓ። 

ይህ ደግሞ በሲቢሉ ብቻ ሳይሆን በሠራዊቱም እኩል የንቃተ ህሊናው ደረጃ ስለነበር ዕድሉ ሙሉ የመንፈስ አቅም ነበረን፤ የማያሳፍር፤ አንገትም የማያሰደፋ አሁንም ዲታ የሆነ የለማ የነቃ የበሰለ ህሊና አለን። እኛን ተጠግቶ ነው ሁሉም ተኮፍሶ አንቱ ሆኖ የኖረው …

እኛ የተጠገናው ደግሞ ስኬት ነው። መፍጠር ለእኛ? ተርፎም ይናኛል … ሶሻሊዝም ፍልስፍናም ሳይንስም ነው፤ ስኬቱና ውደቀቱ ደግሞ የራሱ ሂደት አለው፤ ይህም የሆነው በዘመኑ ባሕሪ ለውጥ ነው 

… መታወቅ ያለበት ግን ፓርቲያችን አይዲኦሎጂ ነበረው። ያ አይዲኦሎጂንም አሳምሮ ተጠብቦበት ነበር። በደመነፍስ አይደለም ስንመራ የነበረው። ኢሠፓን ማጣጣል አይቻልም። ድፈረትም ነው። በዬትም ሁኔታ አሉ የሚባሉ ሊሂቃን የዛ ቤተኛ ናቸው። አናፍርበትም! ዓላማችንም ግባችንም እናውቀው ነበር ... ሴራ እና ኢጎ ነው ፓርቲያችንም አገራችንም ያፈረሰው፤ በሌላ በኩል በግሎባሉም የዘመኑ ባህሪም በመለወጡ ምክንያት ...  

·       ገድለኞቹ የአዲስ አባባ ወጣቶች።

ወደ ቀደመው ምልሰት ሳደርግ አዲስ አባባ ብሄር የላትም። ብሄርአልቦሽ ኮዝሞ ከተማ ናት። ጎንደርም በ16/17ኛው መቶ ክ/ዘመን እንዲሁ እንደነበረች አውሮፓውያን ብዙ ብለውላታል።

ለነገሩ አሁንም ከአዲስ አባባ ለጥቃ በህዝብ ብዛት ጎንደር ስትሆን በዬዘመኑ ደግሞ መከራ በውድማ የሚቃናባት አሳረኛ ናት እንደ አዲስ አበባ፤ በአብይ ዘመን ያልፍላታል ስትባል 90ሺህ ልጆቿን ሚዳ ላይ ኤሉሄ ማለቱ ላይበቃት የጦርነት አዋጁም አና ብሏል። በመንግሥት በኩልም በስውር በዬዘመኑ በቋሳ እንሆ እንደወትሮው ሁሉ ዛሬም እዬተደቃች ነው … በደቦ ... 

ወደ ቀደመው ምልስት ሳደረግ ኢትዮጵያ ምን ትመስላለች ቢባል አዲስ አባባን ነው የምትመስለው። የአዲስ ልጆች መለያቸው ሥልጣኔያቸው ብቻ ነው።

እነዚህ የገድል አንበሶች፤ እነዚህ የታሪክ አውራዎች፤ እነዚህ የትናንት የዛሬ የነገ የነገ ወዲያ የወርቅ ድልድዮች፤ እነዚህ የዘመን ዜማዊ  ጌጦች ሰብሰብ ብለው አገራቸውን ያስከበረ፤ ለነፃነት ፍጹም የሆነ ክብር የሰጠ ልዩ ጀብዱ ፈጽመዋል። እንዴት የበራ የድል ቀን ነበር ትናንት።

ሥርጉተ ተስፋኛ ናት እና የዛሬ ዓመት ከዚህ የበረከተ አርበኛ ይገኝበታል ብዬ አስባለሁኝ በዚህ ገድለኛው የማስተዋሻ አደባባይ። ከአገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን ከውጪ አገርም ብዬ አስባለሁኝ።

ቅኖቹ ታዳሚዎቼ የዛ ዘመን መልካም አሻራዎች አልተነገሩም፤ አልተብራሩም እንዲያሩ፤ ተኮድኩደው እንዲቀሩ፤ አንገታቸው ተሰብሮ እንዲቀር ተደርገው አንገታቸውን ደፍተው ተቀብረው ነው የሚገኙት። 

አሁን ስለ ህገ መንግሥት ስለ ፌድራዘሊም ይደሰኮራል፤ በደርግ ጊዜም ህገ መንግሥት ተረቆ ህዝብ ተዋይቶበታል እኔ እራሴ ለሰቲት ሁመራ እና ለጎንደር ከተማ አወያይ ነበርኩኝ፤ መልክዕምድራዊ ፌድራሊዝም ነበር፤ የብሄረሰቦች ኢንስቲቲዩት የሚባል ትልቅ ተቋም ነበር፤ በፓርቲው ውስጥ ራሱን የቻለ መምሪያ ነበረው የብሄረሰቦች መምሪያ የሚባልም እንዲሁ ... 

ወደር እና አቻ የማይገኝላቸው ዘመን ቁመው የሚያናግሩት በርካት የምግባር ተቋማት ነበሩ በዛ ዘመን። ጦርነቱ መገዳደሉ እንደሆን ሁሎችም አብዛኞቹ አሁን ያሉት አዛውንት ፖለቲከኞች ሁሉ ዕድምተኛ ነበሩ። ሁሉም ተጠያቂ ነው። ተጠያቂነቱ እንደ መንግሥት እና እንደ ተቃዋሚ ድርጅት ሲሆን ደረጃው ቢለያይም። ስክነት ጠፍቶ ትውልድ ባከን። አሁንም ዓመት ድገመኝ እያለ ነው። እነዛውና አሁንም ያሉት … እያመሱት ነው። ቀን ቀን ተመሳስለው፤ ሌሊት ሌሊት ደግሞ ተለያይተው ይሸርቡታል "የቡዳውን ፖለቲካ" እንደ ለመደባቸው ... 

በዘመነ ደርግ ከኢትዮጵያዊነት በላይ በዛ ዘመን ንጉሥ አጤ ማንም አልነበረም። እርግጥ ነው ኢትዮጵያን በጥርሱ የያዘ ግለሰብ ይሁን ድርጅት ከዛ ሥርዓት ውርሰ ብሄራዊነት ጋር ንክኪ ያላቸው ነገሮች ሲነሱ ዛር አለባቸው። ያስጎራቸዋል።

ግን ዘመን ደግሞ እንዲህ ይከሳል ተወደደም ተጠላም። ብሄራዊ ሰንደቅ ዓላማችን አረንጓዴ ቢጫ ቀኝ የሚፈሩት የባንዳ መንፈስ ቤተኞች ብቻ ናቸው። የኢትዮጵያ ድል ያርበተብታቸዋል። መገኛው የ ዓርማው ቃልኪዳን ነውና። አዎን! ኢትዮጵያዊነት ተፈሪ ማንነት ነውና!

የሆነ ሆኖ ኢትዮጵያዊነት ቢገፋም፤ ለሚጠሉት ተብሎ ለጊዚያዊ የፖለቲካ ትርፋ ትርፍ ቅርጥምጣሚ በግርዶሽ ቢጠቀለለም ምን ያህል አሸናፊ እንደሆነ ግን ሰኔ 16 ቀን 2010 አስመስክሯል። ዶር ለማ መገርሳን ቁንጮ ያደረገ፤ በመላ ኢትዮጵያ እጬጌ ያደረገው የቄሮ ትግል ሳይሆን „ኢትዮጵያዊነት ሱሴ ነው“ እነ አቶ ሌንጪ ለታ፤ አነ ዶር ዲማ ነግዖ እኮ  በኢትዮጵያውያን መንፈስ ውስጥ አብሰንት እኮ ናቸው። ራሳቸው በፈፈሉት መንፈስ ባሻገር ሌላ ቤተኛ መንፈስ ቅንጣቢ አያገኙም። 

አብይን መላክ አድርጎ መንፈስን ሉላዊ አድርጎ ያሰረገደለት ኢትዮጵያዊነትን መንፈሱን ስላስጠጋ ብቻ ነው። ሌላ ቀምር የለውም። ትናንት እኮ እነዚህ ሰዎች ነበሩ፤ ማን ያውቃቸው ነበርና? ኢትዮጵያዊነት እንዲህ በአደባባይ ሲጠቀጠቅ ደግሞ ፍርዱን ይሰጣል - ያራግፋል። ኢትዮጵያዊነት ህግም ችሎትም ነውና!

ኢትዮጵያዊነት ሊጠና የሚገባው ፍልስፍና ነው። ኢትዮጵያዊነት ሳይንስ ነው። በዚህ ኢትዮጵያዊነት ፍልስፍና እና ሳይንስነት ዙሪያ የተጀመረ ነገር የለም። አይደለም አሁን በቀደመው ዘመንም።

ኢትዮጵያዊነት ዩንቨርስቲ ሊከፈትለት የሚገባ ገናና ማንነት ነው። ነገር ግን የዘመኑ ባለሥልጣኖችን ኢጎ እና መወድስ እንጂ ከዛ መወደስ ጀርባ ምን ሚስጢር አለ ተብሎ ተፈትሾ አይታወቅም። የአብይ ኬኛ መንፈስ ምንጩ ሥሩ ምንድነው ሲባል? „ስንኖር ኢትዮጵያዊ ስንሞት ኢትዮጵያዊ ነን“ ነበር። በቃ! 

የዛ ሁሉ ዓለም ይዞ ዓለም ድረስ መወድሱ የተናኘው አንኳር ሥር ጉዳይ ይህ ነበር። እንጂ አብይማ እንደ እኛም ሰውም ነው፤ ከዚያም በላይ በኢንሳ፤ በሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ሚ/ርነት እንዲሁም በኦህዴድ አካልነት እኮ ቆዬ … „ምርጫችን መደመርም“ ያው ነው ኢትዮጵያዊ እንሁን ነው ፍልሰፍናው እሰተምን ድረስ ይዘልቃል የሚለው ጊዜ ይፈታዋል።

የቀደሙት አባቶቻችን ሚስጢር ናቸው። ካለምክንያት የሚከበር ባዕላት የለም  በእነሱ ቤት። ካለምክንያት የተፈጠረ ሥያሜ የለም። ካለምክንያት የሚከወን አንዳችም ነገር የለም። ስለምን? ሲባል እነሱም ሚስጢር ስለሆኑ። „ኢትዮጵያ“ ብለው ሥያሜውንም ሲሰጡ ራሱን በቻለ ንጥረ ሰማያዊ ፍልስፍና ተቀምሞ ነው።  

ኢትዮጵያዊነትን የጋህዱ ዓለም ፈላስፎች አልፈተሹትም። አቅሙም የላቸውም። ፖለቲከኞች ደግሞ ሸቀጣቸው ነው፤ የማይኖርበት፤ ሲሞላና ሲጎድል በገብያ ህግ የሚያስተዳድሩት። የጓሮ አንትን ... 

መንፈሳዊ አባቶቻችን ግን አብሶ የቅደስት ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሊቀ ሊቃነት ግን የበዛ ጸጋ የፈሰሰላቸው ስለሆነ ገሃዱንም መንፈሳዊ ዓለምን ያነቡታል፤ ይተረጉሙታል፤ ያመሳጥሩታል። ተፈጥሮ ሥነነቱን ተክህነውበታል።

ከእኛ ይልቅ ትንሽ የሚሻሉት ጀርመኖች ናቸው። ገኖ እንዳይወጣ ቢሹም ኢትዮጵያዊነት አቅሙን ሚስጡርን ግን ፈልፍለው ወደ ራሳቸው አስጠግተው አገራቸውን በጽኑ፤ በድርጁ መሰረት በመገንባት እረገድ ቆምሰውበታል። ግዕዝ ዓዋራ ዋልታ እና ማገራቸው ነው። ሚስጢር ይቀዳል ከመንደረ - ግዕዝ።
  
ኢትዮጵያዊነት ውቅያኖስ ነው። በዚህ ውቅያኖስ ውስጥ ከሰውም፤ ከሃሳብም ከፍጥረትም በላይ የሆነ ሚስጢር 13ኛ ፕላኔት አለ። ያ ደግሞ ኢትዮጵያዊነት ነው።  ኢትዮጵያዊነት 13ኛው ፕላኔት ነው። ኢትዮጵያዊነት ጸጋም ነው። ይህ  ለአራራስውያን፤ ለጃዋርውያን፤ ለሌንጫውያን፤ ለመለሰውያን፤ ለህዝቃኤላውያን፤ ለበቀላውያን ህመም ነው። ወይንም የሚያንደፈድፍ እና እራስን አስቶ ዛር የሚያስወርድ።

ገናናው እና ተፈሪው ማንነት ኢትዮጵያዊነት ዬዬዘመኑን ደራጎን መንፈስን አንበርክኮ ካህዲው ባንዳዊ መንፈስ ተገዶ ተነበርክኮ ወይንም ተሽኮርምሞም ቢሆን ይቅርታ የሚያስጠይቅ ድንቅ ማንንነት ነው ሥነ - ብጡል።

እሱን የረገጡ ዕለት ደግሞ ጀግናው ማንነት አድብቶ አመድ ያደርጋል። እንደ ዋንጫ ቂጥ አውልቆ ይጥላል። ለዚህ ነው ዛሬ አብሶም ከጎንደር የአማራ የህልውና ማንነት ገድለኛ አብዮት ወዲህ ዓይኑን የገለጠለት ሁሉ በገባጣም፤ በመላጣም ፊቱን ወደ እሱ አዞሮ እፍግም ሲል የሚገኘው … ኢትዮጵያዊነት ደም መላሽ ነው። ይክሳል!

የሚገርመው እነ አቶ ሌንጮ ለታ እንዳይከፉ ነበር ኢትዮጵያዊነት ሲጠቀጠቅ የኖረው ራሱ ውጪ አገር፤ ዛሬስ? ዛሬማ ፍቅሩ ሲያልቅ ደግሞ እሱኑ ጀግናውን ኢትዮጵያዊነት የሙጥኝ አውጣኝ ሆኗል።

የሚያስደስተውና የሚያኮራው በዚህ የሊሂቃን ኢጎ እና የበታችነት ስሜት ፍዳውን ሲከፍል በነበረው ኢትዮጵያዊነት ውስጥ የሽታ ሽቶ ፍዳውን ተጋሪ ሆኖ የኖረው አዲሱ ትውልድም ደግሞ መንፈሱን ጥራኝ ብሎ ወደ ቀደመው አቮው ሚስጢር እዬተመለሰ ይገኛል። ፉከራው፤ ቀረርቶው፤ ሽለላው፤ ሥነ - ቃሉ ምልስት እያደረገ ነው። ይህ ያጽናናኛል።

·       ምልሰት ወደ ልጅነት …

የካራማራ ጦርነት ጊዜ እኔ ልጅ ነበርኩኝ። ነገር ግን እናቴ ለጦርነቱ ስንቅ በቀበሌ ሲዘጋጅ እዛ በዬዕለቱ ትሄድ ስለነበር ከት/ቤት መልስ ቁልፍ ልቀበል ስሄድ ያ የህዝብ ተሳትፎ የሚደንቅ ትዕይንት ነበር።

በተርታ ከላይ እሰከታች ቁጥሩ በርካታ የሆነ ብረት ምጣድ ተጥዶ የበሶ ቆሎ ሲቆላ፤ በዛው መጠን ሙቀጫ ተዘጋጅቶ ሲሾከሾክ፤ በበዛ ሁኔታ ሴቶች ተሰልፈው ገብስ ሲያበጥሩ - ሲያንተረትሩ፤  ወንዶች ተሰልፈው እንጨት ሲፈልጡ፤ ጆንያ ሲያዘጋጁ በመደዳ ሙጎጎ ተጥዶ አንጀራ ሲጋገር፤ በመደዳ አዳዲስ ሰኔል ተዘርግቶ እንጀራው ለድርቆሽ ሲሰጣ እና ሻሽ በላዩ ለይ ሲደረብ የሚገርም ትዕይንት ነበር።

የቀበሌው ነዋሪ በሙሉ እቃውን እየያዘ በጥዋቱ ልጆቹን ወደ ት/ቤት ሸኝቶ እዛው ይገኝ እና በፍቅር፤ በአብሮነት፤ ፍጹም ተገልፆ በማያልቀው አገራዊ ስሜት፤ በወበራ በህብረት ያን የመሰለ ብሄራዊ ተግባር ሲከውን ዛሬ ላይ ሳስበው ጎንደር ላይ በእርስ በእርስ ጦርነት 90 ሺህ ሰው ሲፈናቀል ሁለቱንም የታሪክ አጋጣሚዎች ሳስባቸው መንፈሴ ይሰነጠቃል።

ባጋጣሚ የጭልጋን ገበሬ በአደራጅነት እያንዳንዱን ነጥብ ጣቢያ በእግሬ ተጉዤ አውቀዋለሁኝ፤ የደንቢያን እና የአለፋን ጣቁሳን ጉዳይ በሙያ ማህበራት እና በህዝባዊ አደራጅነት በአካል አውቃቸዋለሁኝ።

እንዲህ ዘመን ተገልብጦ ያ ቅን ሰው በልቶ የጠገበ የማይመስለው ህዝብ እርስ በእርሱ ተጨካክኖ ሲዋጉ፤ ሲጨራረሱ ሳይ የበደሉን ዓይነት ትርጉም አጣለታለሁኝ። በውነቱ ከሁሉም የተበደለው ኢትዮጵያዊነት ነው። ህወሃት፤ ኦነግ፤ እና ሻብያ የሰጡን የሸለሙን ይህን ነው ኢትዮጵያዊነትን መበደል።

·       ትናንት እና ኢትዮጵያዊነት።

ዛሬ ኢትዮጵያዊነት ለማሟያነት እንጂ የለም። ሥሙ ብቻ ነው ያለው። ነፍሱ መንፈሱ ርቋለኝ። ራሳችን እንሸንግል ካልልን በስተቀር …

ያን ጊዜ ሌላው ቀርቶ ሰኔ ላይ የወላጆች ቀን እንዘጋጅ ነበር በት/ቤት። ነገረ ድሉን ካደግን በሆላ አቤቱ ሰኔም አድሎት ኤግዚብሹን ይጋጅለት ነበር። መነሻችን እንዳንረሳው ይደረግ ነበር።

ተማሪዎች ተመደብን የድሉን ግኝት በፎቶ ግራፍ በተደገፈ ማብራሪያ እንሰጥ ነበር በዛ ዕድሜ ገና ታዳጊ ወጣት እያለን። ተማሪ እያለሁም እኔ እጅግ ንቁ ጎበዝም ተሸላሚም ተማሪ ስለነበርኩኝ አንድ ክፍል ላይ ገላጭ ነበርኩኝ። ት/ቤቶች እንዲህ ነበሩ። አሁን ደግሞ ት/ቤቶች የዞግ የጦርነት ዓውዶች። ዩንበርሲቶች የቁርሾ ፏፏቴዎች።

በዚህ ሁሉ ፍዳ፤ በዚህ ሁሉ ጥቁር ቀን፤ በዚህ ሁሉ አሳር መሃል ትናንት የአዲስ አበባ ዕንቁዎች እንሆ ያን ድል እንዴት ባጀህ፤ እንደምን አከረምህ ቁሩ፤ ወጀቡ፤ አውሎው፤ ሀሩሩ እንዴት ይዞሃል ብለው፤ አለንልህ  አይዞህ ብለው የክብር ተክሊል ደፉለት፤ ለወግ ለማዕረግ አብቅተውታል።

ታሪኩን በሚመለከት በስፋት ወጣቶቹ አቅርበወታልና ውዶቼ ትታደሙበት ዘንድ በታላቅ ትህትና አቀርባለሁኝ። በዚህ አጋጣሚ አንድ አፍታ ሚዲያንም አመሰግናቸዋለሁኝ።

„Ethiopia: የካራማራ ድል 41 አመት መታሰብያ "ክብር ለሀገር ድንበር

ሲዋደቁ ለተሰዉት ሰማአታትያሬድ ሹመቴ“


ዘመን መመለሱ የሚታወቀው እንዲህ ባለውለታዎችን ማስታወስ ሲቻል ነው። እንደ ኢትዮጵውያን ራሳችን ያሾለክን በምድር የሚገኝ ሌላ ዜጋ ያለ አይመስለኝም። ሌላው አገር የሌለውን አለን እያለ ስንት ከምድር በታች ሲጭር እኛ ግን፤ በቅዱስ ወንጌል በቅዱስ ቁራዕን የተወደስን እራሳችን አቃለን እነሆ በሁሉም ነገር ከዓለም ተርታ በታች፤ በለጥን ብንል ከአፍሪካ እንኳን ሁለት ሦስት አገር ብቻ ነው።

ይባረክ እንጂ ዛሬ ዛሬ አንድሮ ሜዳ የጂቲቪ ፕሮግራም አሁን እዬዘረዘረው ነው በጥልቀት ገናናውን ኢትዮጵያዊነት፤ ህዋ ላይ ሥማቸውን የሚያሰይሙ ድንቆች አገር ሆነን ግን ጥበብ ነሳን። የሰው መፈጠሪያ ብቻ ሳይሆን የሳይንስም ክህሎት አህዱ ነን እኛ። 

ይህም የሚሆነው ሁሉ እያለን በፖለቲካ ሊሂቃን ኢጎ እና በበታችነት ስሜት በመታመስ ምክንያት ይኸው አለን እንዳለን፤ አለፈንው፤ ተሻገረነው ስንል፤ ፕ/ መስፍን ወ/ማርያም እንዳሉት ከዛው መሆናችን ማህጸንን ደም ዕንባ ያስለቅሳል።

·       የኔ ክብሮች የአዲስዬ መካሻ መካች ወጣቶች  ሆይ!

ተባሩኩ! ኑሩልን! ታሪካችን ናችሁ! ድላችንም ናችሁ! አመሰግናችሁ አለሁኝ።

ኢትዮጵያዊነት ከመፈጠሩ በፊት ፈተናን አሸንፎ የተፈጠረ ሚስጢር!




የኔዎቹ የጹሑፌ ታዳሚዎች ኑሩልኝ፤ መሸቢያ ጊዜ።

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።