የፌስቡክ ተቀናቃኙ ጠ/ሚር ሌጋሲ ዶከክብኝ።

እንኳን ደህና መጡልኝ

„ወደ ትዕቢተኛ እና ወደ ሐሰተኛ
ያልተመለከተ ሰው ምስጉን ነው“
መዝሙር ፴፰ ቁጥር ፬

የሩኽ
ስቅዛት።

ከሥርጉተ©ሥላሴ
 Sergute©Selassie
 13.04.2019
 ከእመ ዝምታ ሲዊዘርላንድ።

                                    ጀግኖቼ! ድንግልዬ ትጠብቅልኝ ጽናቶቼን!


እንዴት ናችሁ ውዶቹ ውቦቹ? ይህን ጹሑፍ ስጽፈው ከራሴ አገር በአፅህኖት
 እዬታገልኩኝ ነው። በተለይ እነዛን 100 ቀኖች ሳስባቸው እና ዛሬ ያለውን 
እውክ ድባብ ሳስተውለው አቅም የሚያሳጡኝ በርካታ የህሊና ሙግቶች ናቸው
 ያሉብኝ። 

የወረት የሆኑ ጉዳዮች ለባከነው ትውልድ ካሳ አይሆንም። እንዲሁም መድህን ነው
 ብዬ አላስብም። ቋሚ የሆነ ዛሬን ለነገ በጽናት ሊያበቅልል የሚችል ተከተታይነት
 ያለው የተግባር ስንቅ ያስፈልጋል። እንደ አንድ አገር መሪ የተግባር ትልም እና 
ክንውን።

ጊዚያዊ ደስታ ፈጥሮ የማይተን የማይበን። ጤዛም ጎርፍም ያልሆነ። ዛሬን የሚያኖር
 ነገን የሚተከል፤ ከነገወዲያን የሚያበቅል ልባም ተግባር ያስፈልጋል። አንዲት ሻማ
 ስትበራ ብርሃኗ ለብዙ ትደርሳለች ስትጠፋ ግን ያው መልሶ ድቅድቅ ይሆናል። 

እኔ ብዙም በጠንካራ ጎኖች ላይ ማተኮሩ የሚበቃ ይመስለኛል። ውዳሴውም 
ይበቃል ባጀንበት። ይልቁንም ትኩረት ባጡ ወይንም ትኩረትን አቅምን ወደፊት
 ሊሻሙ በሚችሉ ውጥን መሰናክሎች ላይ የበለጠ መስራት የሚያስፍልግ 
ይመስለኛል። አሁን ያለው ሁኔታ ግልጽ ነው።  

ስቅዛቱ አዬለ፤ ውጋቱ ጠና። ሰቀቀኑ አና አለ። „በጣና ኬኛ“ ፕሮጀክት ጠ/ሚር 
አብይ አህመድ ስለማህበራዊ ሚዲያ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተው ነበር። የልቤ 
የተባለለት። ህሊና በልግስና የተሸለመ። 

ያን ጊዜ እኔ መተርጎሚያ ስንኝ እስካጣ ድርስ እንደ ሪፈራንስ ወስጄው ነበር። 
ዛሬ ክብር ያጎናፃፏቸውን ውዳሴ ሲያረቡላቸው ውለው የሚያድሩላቸውን፤ 
የልቤ ጌጥ የተባሉትን፤ ነገ ደግሞ ድርሳን የሚያዘጋጁላቸውን፤ ትናንት ግን በትጋት
የተቃዎሟቸውን አካላት ሁሉ በዛ በእጅጉ ተስፋ አድርጌበት በነበረው የጠዳ፤ 
ለዛማ ቃናን ዋቤ አድርጌ፤ በጽዱ መንፈሳቸው ውስጥ ሆኜ ሞግቼበታለሁኝ። 

ንጽህና የነበረው ቃለ ምልልስ ስለነበር። ተስፋ ነበረኝ ለሚዲያ ነፃነት አንቱ የሆነ
 ፍቅር፤ ወገንተኝነት ይኖራቸዋል የሚል። እንዲያውም መቼ ተፈተው የነፃነት 
አርበኞቻችን ጋዜጠኞች በማለት አስቤ ነበር፤ እንዲህ ነገር ዓለሙ ዞጋዊ ሆኖ 
አረባ እና ቆቦ ሊሆን ... እጠብቅ የነበረው ጋዜጠኞችን ሲያዩ በፍቅር ዓይን ይከተሏቸዋል ብዬ ሁሉ ነበር። 

እንዲህ  በአንጡራ ጠላትነት ፈርጀው ጦር ይመዛሉ ብዬ አላሰብኩም ነበር። 
ጭራሽ መንፈሳቸውን በርቀት ሳያስጠጉ በባዕድ ስሜት ነበር በጎሪጥ ሲዩ የባጁት። 
እኔ በጣም ታዝቤያቸዋለሁኝ። 

እኔ እንዲያውም የመንፈስ ባልንጀራዎቸቸው ሞጋች ጋዜጠኞች ይሆናሉ ብዬ 
አስብ ነበር። ውሃ የበላው ቅል ሆነ እንጂ ተስፋዬ … እግዚአብሔር ይይላቸው። 
ትምክህቴን ሁሉ „አሞራው በረረ ቅሉ ተሰበረ“ አደረጉት። አሁን እሳቸውን 
ማን ነክቶ የሹም ዶሮ ነኝ ብለው አረፉት ከበረከተላቸውስ//// ንግሥናው 
አጤነቱ … ዘውዱም ከጸና … የውነት ይቅናቸው። 

Ethiopia ታሪክን በሚገባ ያብራሩበት ሙሉ ቪዲዮ


ይህን ውዶቼ ግማሽ ሰዓት ብቻ ስለሆነ ከልብ ሆናችሁ አዳምጡት። ያን ጊዜ ቅን 
በነበሩበት ወቅት ነበር ይህ ጸደይ መንፈስ። አሁንሳ? አሁንማ ቅንነታቸው ተኗል። ቅንነታቸው በኗል። ርህርህናቸው ራሱ ውቃቤ እርቆታል። ጌዴኦ ላይ እንዳዛ 
እንዳያቸው አልፈልግም ነበር። የደግነት ድፈረታቸው የት እንደገባ እራሱ 
ይጨንቀኛል።

ወደ ቀደመው ጉዳዬ ስሄድ ዋና ጦራቸውን በማህበራዊ ሚዲያ ላይ አሹለዋል። 
በአደባባይ ጦርነት ካወጁት በተጨማሪነት። እሳቸውን የሚሞግቱ ነፍሶችንም 
ጦርነት አውጀውባቸዋል። ያው በሴራ ፖለቲካ "እንዳያማ ጥራው እንዳይበላም
 ግፋውን" በበላይነት እዬመሩ ነው ያሉት። ሌላ መደበኛ ሥራም ያላቸው አይመስልም። 
ያን ያህል የምሳሳለት መንፈስ ግን ምን በላው? የት ሄዶ ተቀረቀረ? 

ይህ በውነቱ አለመታደል ነው። „ የአህያ ስጋ ከአልጋ ሲሉት ከአመድ“ ነው የሆነው። በትእዛዝ የማይተዳደረውን የሚሊዮን መንፈስ ተረግጬ እገዛለሁ ማለት ለጋዳፊም አልበጀም፤ ለፈጣሪያቸው ለሄሮድስ መለስ ዜናውም አልበረከተም፤ እንኳንስ ለሳቸው ባረገረገ፤ ውሃ በቀጠነ ቁጥር በመባተት ላይ ባለ ወንበር  ላይ ላለ ስልጣን … ቀድሞ 
ነገር ነፍስ አለው የሚባለው አካል ማን የሳቸው ደጋፊ እንደሆነ ራሱ የሃይል አሰላለፉን አያውቁትም። ጥጋቸው፤ መካታቸው፤ ጋሻቸው እኛ ልንሆን ይገባ ነበር። 

የሰሞናቱ ሰሞነኛ ጉዳይ እጅግ አሳዝኖኛል። እስካሁን ባለው የአንድ ዓመት ጉዞ ሐሴት ያገኘሁባቸውን በአዎንታዊነት ቋት ውስጥ አስቀምጬ የቆሰልኩባቸው ገጠመኞችም፤ ያዘንኩባቸው አገላለፆች ወይንም የአፍ ወለምታዎች ቢኖሩም እንደዚህ ግን ውስጤን ያፈረሰው ጉዳይ የለም። እኔ የፌስ ቡክ ተጠቃሚ አይደለሁም።

ጥቅሙ ጠፍቶኝ አይደለም። ግን ራሱን የቻለ ሰብዕናን ስለሚጠይቅ ለዚያ ስንዱ ስላልሆንኩ ብቻ ነው። አብሶ ጥቁር ዜናዎች ለስለስ ብለው በድህረ ገፆች ሲወጡ 
ይሻለኛል በሚል ነው። አንጀቴ አይችልም። አስደንጋጭ እርእስ ያላቸውን ዩቱቦችን
 እራሱ አልከፍታቸውም።

·       ልቤም፤ መንፈሴም፤ ህሊናዬም ማህጸኔም የተቆረሰበት ጉዳይ።

ጠ/ሚር አብይ አህመድ ከፌስ ቡክ ባለቤቶች ጋር በስልክ ንግግር ማድረጋቸው የሚሰጉበት ጉዳይ ካለ ይችላሉ። በራስ መተማመኑ ስደት ከላኩት ማለት ነው። ስንት መከራ መሬት ላይ እዬዘነበ፤ ዘንቦ ተባርቆ ለሚመጣው ኤሌትሪክ፤ በወረፋ ለሚገኘው ኤሌትሪክ በምንም ደራጃ ካለው የኢንተርንቴ ተጠቃሚ ይልቅ ቀዳሚ ብዙ ጉዳይ አለ። ቁልል ማነቆ የተሸከመች አገር ናት ኢትዮጵያ ማለት።

የሆነ ሆኖ እጅግ ያዘንኩበት ወደፊትም ርህራሄ የሚባል ነገር እንዳይኖረኝ ያደረገው
 ድርቀት መሰረታዊ ጉዳይ ዬፈስ ቡክ ባለስልጣናትን ቡድኑን አዲስ አባባ ድረስ 
በልዩ ሁኔታ ጋብዘው ህሊናን ለመጠምዘዝ የሄዱበት መንገድ የልባቸውን ልክ አይቸበታለሁኝ።

በውነቱ በተቆፈረ ጥልቅ እብንነት ውስጥ ነው እኛ የእኛዊነት ሐዋርያ ስንላቸው 
የባጀነው። "ሙሴያችን የአሮን በትራችን" ያልናቸው። ልባቸውም፤ መንፈሳቸውም 
ፈጽሞ አይገኝም። ጥቁር ወይንም ጠራጠሮ ነው። 

ለማንም ለምንም አይራሩም ከከብራቸው ጋር ዝንፈት ከገጠመ። እንዲህ 
አላስባቸውም ነበር። ይህ ሁሉ እልቂት እና የመከራ ነዶ እያለ እሳቸው ጉዳያቸው ስለክብራቸው ቅቡልነት፤ ስለድርጅታቸው ኦዴፓ ግድፈት ታፍኖ መቅረት 
አስፈላጊነት ነው ጭንቀታቸው። 

እንዲዚህ ዓይነት ትብትብ ነገር ውስጥ የሚገባ የአገር መሪ አዳጋው እጅግ የከፋ ነው። በህዝቡ ላይ ያለው እምነት ደርቆ የ100 ሚሊዮን ህዝብ መንፈስ አሳልፎ መስጠት 
ለእኔ ጲላጦስነት ነው።

አንድ የአገር መሪ እንዴት ህዝቤን ነፃነቱን አሟልቼ ሩሁን ላስደስት ከማለት በኔት አንደበትን ካቴና ማስበጀት በውነቱ ሰላም እና ደህንት ላጠና ባለሙያ፤ የሰላም 
ሚ/ር ብሎ ለሰዬመ፤ የፍቅር፤ የመደመር፤ የምህረት እና የእርቅ አባት ነኝ ካለ መሪ በፍጹም የሚጠበቅ አይደለም። 

ክርስቶስን ይሁዳ አሳልፎ እንደሸጠው ነው እኔ የተመለከትኩት። የራስን ወገን፤ 
የራስን ገመና ሽክፍ እድርጎ መያዝ እንጂ እንዲህ ገመናን ቄጤማ ለማድረግ፤ ለባዕድ አሳልፎ መስጠት የአገር ክህደትም ነው - ለእኔ። ይህ የህሊና ቁርጥማት ነው። 

የአገርን የማሰብ ነፃነት መንፈስ ውርስ ቅርስ ተደርጎ ለባዕድ አይሰጠም። ይህ 
እኮ ቅኝ ተገዢነትንም መፍቀድ ነው። ነውር ነው ለሰማይም ለምድርም የማይመች። ኢትዮጵያ ድረስ እንዴት ይጋበዛሉ የፌስ ቡክን ቲም? መንፈስ ለማገት? ነፃነትን አሳልፎ ለመስጠት ግን እንዴት? ከዚህ ምን እንማራለን? ምን ሲሉ አቅዱት? ከስልክ ግንኙነት አልፎ የራስን ወገን አንደበት፤ ልሳን ለመዝጋት በዚህ መልክ መገኘት? 

ይህን ዜና ስሰማ በውነቱ ሳናውቃቸው ነው የመሰከርንላቸው ብያለሁኝ። እንዴት ይህን ያክል ይጓዛሉ? እኔ ባከበርኩት፤ እንደዛ በምሳሳለት፤ ሌሊቱን ሁሉ ደህና ስለመሆናቸው ለምጨነቅለት ብልጹግ ሰብዕና፤ ንጽህና በልኩ ከሳቸው ላገኝ አልቻልኩም። በደርበቡ እንኳን የለም።

መተመናቸው ተቀዶ ተናዶ አምድ ነው የሆነው። ስንት መንገድ እያለ እንዲህ ህዝብን
 በይፋ በአደባባይ ስጋት እንዲገባው፤ እንዲረባባሽ፤ እንዲሸበር ማድረግ - በፍጹም
 የተገባ አይደለም። ሸብር እና ማስፈራሪያ ነው እዬለቀቁ ያሉት፤ ሉላዊው ዓለምም በመዳፌ ነው የማለት ያህል ነው። እንደ መልካም ነገር እዬተነጋጋርን ነው ማለታቸውን አዳምጫለሁኝ። የክብር እንግዳ አድርገው ግን በኢትዮጵውያን መንፈስ ማነቆ እንዲህ ይፈጽማሉ ብዬ አላሰብኩም። 

ይህ የጭካኔ አማርኛ ነው። የህዝብን የመተንፈሻ ቧንቧ ለመዝጋት በዚህ ውስጥ ሰምጦ መገኘት መራራ ነው ጎምዛዛ።  ለነገሩ በደህንነት ሙያ አንድ አገር መሪ ሲኮን መከራው ወዘተረፈ ነው። ያሳዝናል። እኔ ለአገር ሉዕላዊነት ይውላል ነበር ምኞቴ ግን አልሆነም። አሁን እኮ የሰውን የግል ነፃነት ሁሉ የማስጎርጎሩን ሃላፊንት አሳልፈው ነው የሰጡት።  

እንዴት እንዲህ ያደርጋሉ? እጅግ ያሳዝናል። ቲሙን ወደ ኢትዮጵያ መጋበዝ አልነበረባቸውም? በተለያዬ ሁኔታ እና አቀራረብ የሚሊዮንን ነፃነት መዳፍ ውስጥ ማስገባት ያልተገባ ጥምልምል መንገድ ነው።

እኒህ ሰው የዓለም መሪ ቢሆኑ ብላችሁ እሰቡት ውዶቼ? ሥልጣኔን ለመግታት ምን
 ያህል ርቀት እንደሚጓዙ? እጅግ ከባድ ሰው ናቸው። ያ ቤተሰባዊ፤ አቃፊ፤ አቅራቢ ገፃቸውን ሁሉ አሁን ሳስበው እኔ ከዚህ በርቀት ሆኜ መፍራት ጀምሬያለሁኝ። 
ሰብዕናቸው ተነጠለ። 

ክፋት ክፉ ነገር የሚያበረክተው የለም። እሳቸው እንደሚሉት ሙስና መጀመሪያ
 የራስን ቤተሰብ ነው የሚበትነው ብለዋል እኔ በዚህ „የመሰሪ ግንብ“ ያዬሁት ነገር ሁለማናቸው ሊበረክት እንደማይችል ነው። ልጅም አያወጣም። ምረቃትም ያስነሳል። ሰንባቹ ማን ተሰናባቹስ ማን እንደሆን የሚያውቀው አንድዬ ነው? ለቀጣይዋ ሰከንድ ዋስትና የለም። 

ይህን ያክል አንደበትን ለመዝጋት፤ የሰውን ልጅ አልተፈጠርክም ብሎ መንፈሱን
 ለማሰረዝ እንዴት ይህን ያደርጋሉ? እምነቱ ካለ እውን በክርስትና ዪሚያምኑ ከሆነ? 
? ? ?  ከቶ መካሪ የላቸውንም? ለምድሩ ሥልጣን ይህን ያክል? እንዴት የፌስ ቡክን 
ቲም አገር ቤት ጠርተው ይህን ጉዳይ ከድርጅቱ ጋር ይወያዩበታል? የሚገርም የጉድ 
ቁንጮ ነው። በሁለመና ክፍት ማድረግ የዜጋን ነፍስ ... ያሳዝናል። 

ጀርመን የፌስ ቡክ ተጠቃሚዎችን በሚመለከት ህግ አውጥቷል፤ ፋሽዝም እንዲያቆጠቁጥ አንድ ፓርቲ በመደበኛ እዬሰራበት ስለሆነ። ይህም የሶርያ ስደተኛ ስለበዛ ከዛ የተነሳ ነው። 
ይህም ቢሆን በሰለጠኑ አገሮች ብዙ ሰብዕዊ መተንፈሻ ተቋማት አሉ። 

መጽናኛ እንባ አባሽ አውነተኛ ድርጅቶች አሉ። እራሱ የሃይማኖት ተቀሟት ሰውን
 እኩል መርዳት እንጂ ለአማኞቻቸው ብቻ የተነጠለ ድጋፍ ማድረግ ተፈጠሯቸው አይደለም።  

የዴሞክራሲ ሥርአቱም የተገነባ ነው። ሥልጣኔው ሆነ ሰው መንፈሱ የሚያርፍበት ብዙ መስክ አለ። የመኖር ዋስትና አለ። እያንዳንዱ ዜጋ የህግ ዋስትና አለው። በዜጎች መካከል እንደ ኢትዮጵያ አንዱ ልጅ ሌላው የእንጀራ ልጅ፤ አንዱ የክት ሌላው የዘወትር አይደለም።

ኢትዮጵያ አንድ የሚያስመካ ነገር በሌለበት፤ ሁለመናው በተፋፋነበት፤ በተዳፈነበት ሁኔታ ይህም ተቀንቶበት ይህን ያህል ለአንደበት መቃብር ቆፋሪነት ለዛውም ከባዕድ አገር ተቋም ጋር እንዲህ ትጉ መሆን በውነቱ ከአንድ አፍሪካዊ የተስፋ መሪ ተብሎ ከተዘመረለት ነፍስ የሚጠበቅ አይመሰለኝም። እኔ እንዲያውም የሻብያን መንገድ ፈለግ እየተከተሉ ያሉ እዬመሰለኝ ነው። በቃ ድፍንፍን ያለ ጉድ። 

በሰልክ ማነጋገር እና ቡድን ጠርቶ ህሊናውን ማጠብ፤ መጠመዘዝ ሌሎችን ማነቆዎችን ማደረጃት ከፈጣሪ ጋርም በእጅጉ የሚያጣላ እኩይ ተግባር ነው። 

ይህን ያክል የሚያስፈራ ዓላማ ተሸክመው ነው ወደ ስልጣን የመጡት ወይ? 
ምነው በራሳቸው ላይ እንዲህ ዕምነት አጡ ጠ/ሚር አብይ አህመድ? ኮሽ ባለ
 ቁጥር ምኑ  ይሆን የሚያባትታቸው?

ከዛ ወንበር ጋር እንዳይላቀቁ ሆነው በማስትሽ ተጠባቀው የተፈጠሩ እኮ ነው
 የሚመስሉት … ለዬትኛው ጊዜ? ለማንስ ብለው? ይህ ለኢትዮጵያ ማሰብ
 እንዳይባል እና እንዳልስቅ …

ኢትዮጵያን ቢወዷት ይህን ያክል በዬቀኑ ጭንቀት አምራች ፋፍሪካ ባልከፈቱ ነበር። ወጠሯት እኮ ኢትዮጵያን በጭንቀት እና በስጋት? ኢትዮጵያ ካለልጆቿ መንፈስ እኮ
 ምንም ናት። በጣም ተጫኗት ተዳፈሯትም። 

Ethiopia || ሰበር ዜና - ፌስቡክ / አብይ ያልተጠበቀ ነገር ሊያደርግ ነው || Abel


ሌላው ደግሞ የጥላቻ ንግግር ፈር ለማስያዝ አንድ ረቂቅ አዋጅ ውይይት ላይ እንዳለ አዳምጫለሁኝ። ይህንም ስናዬው ለአብይ ሌጋሲ እንዳሻው ይፈነጭ ዘንድ ሌላው 
ተጨማሪ ካቴና መሆኑ ነው። ህግ አርቃቂዎቹ፤ ፈራጆቹ፤ ዳኞቹ፤ አቃቢ ህጎቹ፤ ደህንነቶቹ፤ መከላከያዎቹ፤ ፖሊሶቹ እነሱው ናቸው። በውነቱ የማግስት ትንግርት ይታይበታል
የተባለው የአብይ ሌጋሲ ዶከከብኝ
ዶከከብኝ
ዶከከብኝ
አኞም ሆነብኝ፤ 

በኢትዮጵያ ለሰዎች መገደል ምክንያት የሆነውን የጥላቻ ንግግር፣ ህግ ይገድበው ይሆን?

12 ኤፕረል 2019

እውነት ለመናገር አሳርረው ያሰደጉትን የቁቤ ትውልድ በአዲስ ንጽህና ህሊናውን
 ለማጠብ በለብለብ ሳይሆን መደበኛ ተግባርን ይጠይቃል። ለዛውም አሰበውበት አያውቁም። የ ኢትዮጵያዊነት ጠረን ከዛ ድርሽ እንዲል አይፈለገም። አዲስ አባባ
 ለይ ያሉ ንግግሮች ደግሞ በአንድ ቀን ስብሰባ ሁሉም ችግር ብትን የሚል 
ይመስላቸዋል። 

እኔ ሳያቸው ጠ/ሚር አብይ አህመድን አቅልለው ነው ሁሉን አመክንዮ 
የሚመለከቱት። አቅልለው ሰለሚመለከቱትም መፍትሄ ብለው የሚያመነጩት
 ማናቸውም ነገር ገና ከውጥኑ ይወድቃል። አሁን ከሆነ በተንሳፋፊ እና በደራሽ ነገር የተመሰረት ህልም ነው ያላቸው። ለዚህም ነው ደንጋጣ የሆነው መንግሥታቸውም ካቢኔያቸውም።

መነሻውም መድረሻውም የክስተት የኩነት የአመክንዮ አደብ ትንሽ የለውም። ተደሞ ይፈልጋል አገር መመራት። ኢትዮጵያን መምራት የእድር ወይንም የጽጌ ማህበረ ደቦ አድረገው ነው እዬተመለከቱት ያለው። 

አይደለም የቀደመው እሳቸው ከመጡ ወዲህ የተፈጠረውን ምስቅልቅል ጉድ ቁጭ
 ብሎ ማጥናትን ይጠይቃል። እሳቸው በቃ ኮሜቴ፤ ኮሚሽን በማቋቋም፤ ወይንም
 አዲስ ዓዋጅ በማረቀቅ ብቻ ችግር መፍትሄ የሚያገኝ ይመስላቸዋል፤ ያለውን ህግ
 እንኳን እንዲሰራ ማድረግ አልቻሉም …

ሌላው የተንጠራራ በራስ የመተማመን ችግር የፈጠረውን እያዩት ነው። ያለምንም
 መሰናዶ ሁሉም ገመናውን እንደያዘ እንዲገባ ተደረገ ተፎካከሪው/ ተቃዋሚው/ ተቀናቃኙ። አሁን በተስተካከለ አገራዊ መልክ ባለው ሁኔታ ይህን በወጥነት ገርቶ ለማስተዳደር አቅም አጠረ። በዬቤቱ ስንት ገመና ተከዝኗል። 

ሰው ተገድሎ ተዝቅዝቆ ሲሰቀል፤ 18 ባንክ ሲዘረፍ፤ የውጭ ኢንቨሰተሮች ሳይቀር ተገድለው ሲቃጠሉ ያን ማስከበር አይችሉም። የተፈናቀሉ፤ በጦርነት ከቀያቸው
 የለቀቁ ዜጎችን እንኳን እርዳታ እንዳይደርስ ስላደረጉት አይጨንቃቸውም እሳቸው። እሳቸው በቃ በፓራሹት መውጣት እና መውረድ ሴልፊ በቃ … አንድ ቀን ደግሞ 
ፓይለት ሆነው እናያቸው ይሆናል። ነፍሳቸው አዬር ላይ ናትና ያለችው። 

ግርም የሚሉ ነገሮች ናቸው ያሉት። ችግር መጥቶ እንኳን ችግሩን ለማስወገድ
 ፍጥነት የለም እንኳንስ ችግሩ ከመምጣቱ በፊት መተንበይ፤ መተንተን ያን 
አቅዶ በተደራጀ ሁኔታ ለመግታት ተሰናድቶ መጠበቅ አልታዬም። ችግሩ የትም
 አይደረስ ነው የሚባለው። ችግሩ ግን እዬዋጠ ነው። 

አንድ አኔ ያየሁት የሱማሌ ችግር የተፈታበት መንገድ ብቻ ነው። ሁለተኛው
 የቀዳማዊ እመቤትን ቢሮ አቅጣጫ በማለም እና ወደ ተግባር በመሸጋጋር … 
ያለው የተባ ተግባር አበረታች ነው። ያውም ከዛም እሳቸው ማናጀር ናቸው።

ለነገሩ እሳቸው ብዙ ናቸው … ልክ እንደ ጨው ከሁሉ ቦታ አሉ። ችግሩ ድርጅታቸው
 ችግር ሲፈጥር ግን እሳቸው አለሰሙም አላዩም ወይንም ከአገር የሉም። ለነገሩ
 ወንበሩን እኮ የሚቀመጥበት ሰው ሲገኝ ነው።

ግን ጠ/ሚር አብይ አህመድ ወንበሩን ስለምን ፈሩት? መቼ ነውስ የሚቀመጡበት? 
አቶ አባዱላ ገመዳን ጉብ አደርገው እሳቸው ቢገላገሉ ይሻላቸው ነበር። የውነት።

… ወይንም ጃዋርውያኑን አቶ ንጉሡ ጥላሁን … ቁምጥ ብለው ይፈልጓታል
 ለሳቸው እርክክብ ቢያደርጉ በበጀ፤ይልቅ ይልቅ  መጪው ሳምንት የድል 
ቀን ነው ለሳቸው የኢህአዴግ የሥ/ አ/ ኮሜቴ አባል ሆነው ኦዴፓን ወክለው
ይገኛሉ ጃዋርዊው አቶ ንጉሡ ጥላሁን - ቀጣዩ ምክትል ጠ/ሚር ... 

ኦዴፓን ነው ያልኩት … አቶ በረከት ስምኦን በብአዴን ኮታ ህውሃትን እንደሚወክሉት ማለት ነው። ከከምሴ ውክል አካል ኮታው በብአዴን ኮታ ግን በኦዴፓነት እንደተሾመው ባለድል ባለጊዜ ማለት ነው። አቤት ስንት ድራማ እኮ ነው ያለው።  

·       የሰቆቃ በረድ፤ የስጋት ደመና …

አሁን ከሆነ ጠ/ሚር አብይ አህመድ የያዙት የስጋት የፍርሃት ናዳ መልቀቅ እና 
ማስለቀቀ ነው … ህዝብን በሰሰቀቅን ማራድ። ምን አደረገ ይህ ህዝብ? መከራ ሰንቆ ተስፋው ተራቁቶ ያለ ምንዱብ።

ለቀን ልብስ፤ ለለት መጠጊያ፤ ለጉሮሮ ማርጠቢያ ያጣ የነጣ ህዝብን አካሎቻቸው የሚጭኑቡት በፈረቃ የስጋት ጫና አልበቃ ብሎ እሳቸው ደግሞ መከራን አደረጅተው በተነፈሰ ቁጥር ለመቀፍደድ የተለያዬ ዘዴ እዬተጠቀሙ ይገኛሉ። ምን ማዕት ወረደብን?

እውነት ለመናገር የኢትዮጵያን ነፍስ እያስጨነቁት ነው ያሉት። ለዛውም እኮ 
ወንጀል፤ ጥላቻ የሚበረታታ ለዛም ድጋፍ የሚያደርግ ሁኔታ እራሳቸው አልጋ 
ሆነው ነው የሚታዩት ለዞጋቸው ድርጅት። ኢትዮጵያን መናህሪያ አልባ ለማድረግ 
መስራት ለአንድ አገር ብሄራዊ መሪ ወንጀል ሆኖ አያስጠይቀውም። 

ድርጅቱም አይከሰስም አይነቀሰም፤ አይወቀስም። በውነት ኢትዮጵያ የወላድ 
መካን ነው የሆነቸው። የአንድ አገር ሉዑላዊነት በውስጥ ተፈቅዶለት፤ ህጋዊ ሽፋን እዬተሰጠው ይህን ያክል ሲደፈር በእኔ ዕድሜ የመጀመሪያው ነው። ኢትዮጵያን 
ለመወጋት ኮማንድ ፖስቱ ኢትዮጵያ ውስጥ ነው ያለው። 

እነሱን አይደለም መገሰጽ ሥማቸውን ለማንሳት ይርዳሉ። አንድ ያበደ "ይሉናል
ማነው እሱ ስለምን አይናገሩትም? ጠ/ሚር የአገር መሪ አይደሉም ወይ? ትንፍሽ
 ማለት ተሰኗቸው ነው እያዬን ያለነው።

ማናቸውም ህዝባዊ በደል በራሳቸው ወገን ሲፈጸም ወንጀል አይደለም። ወንጀል 
የሚሆነው ማናቸውም እንቅስቃሴ ከራሳቸው ወገን ውጪ ሲሆን ብቻ ነው … ይህ
 የፌስ ቡክ ድንጋጌ ይሁን የጥላቻ ንግግር የህግ ረቂቅ ማንን ኢላማ እንደሚያደርግ ይታወቃል። የት ያዬነውን ፍትሃዊነት ነው ትምህክት ልናደርግ የምንችለው። 

አሁን ወገብን ጠበቅ አድርጎ ይህን ዘመን እምንገላገልበትን ጥንካሬ አምጦ 
መውለድን ይጠይቃል። እንግዲህ በዚህ ጊዜ ነው ልማታዊ ጋዜጠኛ እና የፋክት
 ጋዜጠኛም የሚለዬው ማንዘርዘሪያው።

·       የለመደበት

ሌላው ቲያትር ደግሞ „ሸብር“ በሚመለከት በአደባባይ በዓዋጅ እዬተነገረ ሳይሆን በተሟላ መሰናዶ፤ የሎጅስቲክ ድጋፍ እዬተደረገለት ደግሞ እሱንም መግለጫ ለመስጠት የተሄደበት መንገድ በራሱ ቅጥ አንባሩ የጠፋው የጉድ ጉድጓድ ነው። 

ማነው አሸባሪው ቀድሞ ነገር? የኢትዮጵያ መንግሥት ማንን ነው እዬረዳ፤ ሽፋን
 እዬሰጠ የሚገኘው? መዋቅሩንስ እንዴት ነው ያደራጀው? ለማን ስለማን 
እንዲያመች አድርጎ? ይህ አያስጠይቅም? ይህ አያስከስስም? ዘመነኛውን።

በዚህ በሚዲያ ላይ በጥዋቱ የተጀመረው አንባገነናዊ የልምምድ ስልት ይህ ሁሉ
 ሂደት የሚያሳዬው የኦነግ መንፈስ ተፃረው ለሚመጡ ንዑድ መንፈሶች አርቀው፤ ገድለው፤ አስረው፤ ገንዘው የአነግ ግን አቅም እና ጉልበቱን አበርተው ኢትዮጵያን እንዳሻቸው ለማድረግ ምቹ ድልዳል የሚፈጠር ሥርዓት እዬዘረጉ መሆኑን ማዬት
 ይቻላል … 

የጠ/ሚር አብይ መንገድ … ጠረኑ እኔ ፕ/ ኢሳያስ አፈወርቂን ዓይነት እዬሆነብኝ
 ነው … እዛ የተደፈነ ነው፤ የእኛው ደግሞ ለታይታ ከፍቶ ግን ውስጡን ሌላ በር 
አዘጋጅቶ መከርቸም ነው። 

የሚገርመው ህግ ይረቃል የሚባለው በፌድራል አቃቢ ህጉ ነው። አቃቢ ህጉ ደግሞ
 የኦዴፓ የሥ/አ/ኮሜቴ አባልና የኢትዮጵያ አዬር መንገድ የቦርድ አባል ናቸው። 
ስለዚህ ማንኛውም ህግ የሚያረቀው በኦዴፓ ኦሮማማ ቅበረኝ መንፈስ ይሆናል 
ማለት ነው። ይህ ከሆነ የማንን ጥቅም ለማስጠብቅ ብሎ ማሰብ ይገባል። እኔ
 አንድም ነገር አላምናቸውም … አሁን ከሆነ ጣዕም ያለው ነገር ስለማላይ …

·      ከትከት!

የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ አቶ ብርሃኑ ፀጋዬ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ የሰጡት መግለጫ
Published on Apr 12, 2019
የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ አቶ ብርሃኑ ፀጋዬ በሙስና እና በሽብር
 ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር የዋሉትን ግለሰቦች አስምልክተው የሰጡት መግለጫ።
„የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ በተለያዩ ርዕስ ጉዳዮች ላይ መግለጫ ሰጥቷል። 
ህገ-ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር፣ ሊፈጸም ታስቦ ሳይሳካ ስለቀረ የሽብር 
ጥቃት፣ በሃገሪቱ በተለያዩ ስፍራዎች ስለተከሰቱት ግጭቶች፣ ትናንት እና ዛሬ
በሙስና ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር ስለዋሉት ግለሰቦች በመግለጫው የተነሱ
ጉዳዮች ናቸው። ከአልሸባብ ጋር ግንኙነት አላቸው የተባሉ ተጠርጣሪዎች 
በአዲስ አበባ የሽብር ጥቃት ሊፈጽሙ ሲሉ በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን 
ጠቅላይ አቃቤ ሕጉ ተናግረዋል።
አቶ ብርሃኑ ጨምረውም ከፍተኛ የሽብር ጥቃት በሀገሪቱ ለመፈፀም ሲዘጋጁ የነበሩ ቁጥራቸው ያልተጠቀሱ ተጠርጣሪዎች መያዛቸውንና ተጠርጣሪዎቹ ከሌሎች ዓለም
አቀፍ የሽብር ቡድኖች ጋር በመሆን በኢትዮጵያ ውስጥ ሽብር የሚፈፅሙበትን 
ስልት በመቀየስ እና ቦታ በመለየት ላይ እንደነበሩ ጠቁመዋል።“ ቢቢሲ አማርኛው እንደዘገበው ማለት ነው።

በዚህ ውስጥ ጠ/ሚር አብይ አህመድ ዓለም አቀፍ ድጋፍን ለማግኘት ጉዳዩን
  ከአለሸባብ ጋር ለማያያዝ የሄዱበት ስልት በራሱ ላንቁሶ ነው መላቢስ። በሌላ
 በኩል አቅም አለን ኣይነትም ከሽብርተኛ ህዝባችን እዬታደግነውም ይኽም 
ኩሸት ነው።

እርግጥ የተወሰኑ ሰዎችን አደራጅቶ ገንዘብ ባንክ ውስጥ አስቀምጦ ኪኖ ለዓለሙ ማህበረሰብም እንደሚሰራ ወደፊት አስባለሁኝ። የዋዛ አይደለም ስልጣን ላይ 
ያለው ቲም። የሆነ ሆኖ ብዙ ኤክሰፕርቶች አለማችን ስላላት በሳትላይ ሁሉንም
 ነገር ስለሚከታተሉት ራስን ማሞኘት ይሆናል። ኢንባሲዎች፤ ቆንስላ ጽ/ቤቶች እኮ 
መደበኛ ስራቸውም ይኸው ነው።

ለዛውም የአፍሪካ ቀንድ፤ የመካከለኛው አፍሪካ ጉዳይ እንዲህ በውሃ ቅዳ ውሃ መልስ የሚወራረድም አይደለም። ያው በሀተታ በትናጋ ድርሳን ለሚማልለው ቅን የኢትዮጵያ ህዝብ ግን ይሆናል … እኔ ራሱ አሁን አሁን ይህን ያህል ዶላር መሳሪያ ተያዘ የሚባለው እራሱ ስሜት ሊሰጠኝ የማይችል ነገር ነው የሚሆንብኝ ...ይህን መሰል ዜና ስሰማ ሞገድ መጸሐፍን አስታውሰዋለሁኝ፤፡  
  
·       የኦነግ ልማታዊ ጋዜጠኞች ተደሞ።

ልማታዊ ጋዜጠኞች ለይቶላቸዋል
ያዝልቅላቸው እንጂ ቅልቅል ቢጤ ላይ ናቸው።
ፍቅሩ ደርቷል፤
            መወደሱ          ፋፍቷል፤
       ሁለመናው አልባብ ባልባብ    ተሁኗል
  ተዋውጠዋል¡

እነሱ በመንግሥት ሚዲያ እየተንፈረሳሱ ምስኪኑ ጋዜጠኛ አቶ እስክንድር ነጋ 
ደግሞ  በአገሩ፤ በባዕቱ ያን ያህል የካቴና ቤተኛ የነበረ ጀግና ብትን አፈር አጥቶ፤
ተግባሩን ተረጋግቶ እንዳይከውን ልማታዊዎቹ ጋዜጠኞች አቅም እያዋጡ 
ለኦነጋውያኑ መንፈስ ይሄኛው ንዑድ አገራዊ መንፈሰ የጫና ሰለባ እንዲሆን
 እያደረጉት ነው። የእነሱ ጠቅልሎ መግባት ለዚኽኛው ኢትዮጵያዊ መንፈስ
 የመከራ ቀን በዬሰከነዱ እንዲያመረት ማዳበሪያ ሆነዋል።

https://www.youtube.com/watch?v=Dn4e8sFEn5M

Ethiopia -በድጋሚ የባልደራሱ ምክርቤት ስብሰባ ተሰረዘ

Published on Apr 13, 2019

ትእግስት ሲያልቅ ፍቅር ይሰደዳል።

የኔዎቹ ቅኖቹ ኑሩልኝ።
የቻላችሁ ፌስ ቡካችሁ ላይ ቤት ለእንግዳ በሉልኝ።

መሸቢያ ጊዜ። 

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።