"የድምጻችን ይሰማ" ስኬት ተመክሮ ዕድምታ በሥርጉተ ሥላሴ ዕይታ።


እንኳን ወደ ቀንበጥ ብሎግ በሰላም መጡልኝ
"የድምጻችን ይሰማ"
ስኬት ተመክሮ 
          ዕድምታ
በሥርጉተ ሥላሴ
          ዕይታ።  

„የሰው ልብ መንገድን ያዘጋጃል
እግዚአብሄር ግን አካሄዱን ያቃናለታል።“  
ምዕራፍ ፲፮ ቁጥር ፱

07.05.2019
ከእመ ዝምታ ሲዊዚሻ።

·       መግቢያ።

እንዴት ናችሁ የኔዎቹ? ደህና ናችሁ ወይ፧ የቀድሞው ፕ/ ዶር ነጋሶ ጊዳዳን ነፍስ ይማር አላልሽም። ለምን የሚል ጥያቄ ቀርቦብኛል። ከቶ እንደ እኔ ስለ ግለሰቦች መልካም ነገር የሚመሰክር ጸሐፊ አለን?

ማንም እኮ ስሌለው አድንቆ፤ አክብሮ፤ ተበራታልኝ ብሎ አይጽፍም። እኔ ግን ሲሞላ እና ሲጎድል የተፈጠርኩኝ አይደለሁም። እውነት ነው በምልበት ሁሉ እተጋለሁኝ። ለዛውም የማይደፈረውን ሁሉ ነው የምደፍረው። ሰተት ብዬም ነው ፈተና ውስጥ ራሴን እምማግደው። መጠለያ ጥግ ሳይኖረኝ። ስለሆነም እሳቸውን በሚመለከት ብዙ ጊዜ ጽፌያለሁኝ። ቅሬታዬንም አክብሮቴንም። ኦዴፓ እንኳን ስላደረገላቸው መልካም ነገር አድንቄ ሁሉ ጽፌያለሁኝ።

ህልፈታቸውን ሳዳምጥም በድንጋጤ ተውጬ እንዲያውም አንድ ቀን ካደርኩኝ፤ ከተረጋጋሁኝ በኋዋላ ጽፌለሁኝ። አንጀቴ ስስ ስለሆነ አገር ቤት ስለ አንድም ሰው በህይወት አለመኖር ተነግሮኝ አያውቅም። እንደ ጹሁፎቼ እና እንደ ሙግቶቼ ጠንካራ አይደለሁም። ከምትጥብቁት በላይ አዛኝ እና ሩህሩህ ነኝ።

ሌላው ደግሞ የማልችላቸው ጊዜያትም ሊኖሩ ይችላሉ። የጤናም ጉዳይ አለ፤ ድካም አለ። እንዲሁም በአመዛኙ ደግሞ እኔ ብዙ አትኩሮት ባጡ፤ ከእይታ ውጭ በሆኑ፤ የትርጉም ዝብት ባለባቸው፤ ባለቤት ባጡ ጉዳዮች ላይ ነው እምተጋው። ያው ድካሜ ግን አመድ አፋሽ ነው።

የቀድሞውን ፕሬዚዳንት የዶር ነጋሶ ጊዳዳን ነፍስ ይማር አማኑኤል። አሜን!


·       „የድምጻችን ይሰማ እና የስኬቱ ሚስጢር።“


ፎቶው ከሳተናው ድህረ ገጽ የተወሰደ።

„የድምጻችን ይሰማ“ የስኬቱ ሚስጢር ፈቃደ እግዚብሄር ያለበት እና የነበረበት ተጋድሎ እንደሆነ ነው የሚገባኝ። ስኬቱ በፆም፤ በሰጊድ፤ በንጽህና፤ በቅንነት፤ በእውነት የተቀመረ ስለሆነም ነው። ሴራ ስላልጎበኘው፤ በኢጎ ስላላጌጠ፤ መጠላለፍ ስላልነካው፤ ለሥም፤ ለዝና ለግለሰቦች ክብር ስላልነበር ተጋድሎው ለሃይማኖት ንጽህና ብቻ ስለነበረ ነው እንዲህ ለስኬት ስከነት የበቃው።

· ሮመዳን ገባ።

የዘገዬሁት ስከንት ያሰኘው ስለነበር ነው ይህን ብሄራዊ ድል ሰሞኑን ሳልነካካው የሰነባበትኩት። ጅው ጅው የሚል ሁኔታ ላይ ነው የሰነባበትነው። „በድምጻችን ይሰማ“ ቀለማም ተጋድሎ ብዙ በጣም ብዙ  ጽሁፎችን ጽፌያለሁኝ። ፆመ

እኔም ብቻ ነበርኩኝ „እኔም ድምጻችን ይሰማ ነኝ“ ብዬ አደባባይ የወጣሁት።ከአንስት ጸሐፈት ወገንም እኔ ብቻ ነበርኩኝ ብራና ላይ የተጋሁት። እነሱን ወደ ሌላ „የሽብርተኛ“ መንፈስ የሚነካካ ጹሑፍ ሲወጣም ጎሽ ነበርኩኝ። ጎሽ ለልጇ ስትል እንደሚባለው ብሂል። ያው ልፋቴ ግን አመድ አፋሽ ነው። እሱን ለታደሉት ልተዎው።

እኔ የተጋሁበት መሰረታዊ ምክንያቱም በኢትዮጵያዊነት ውስጥ የተቀመሙ ንጥረ ነገሮች ውስጣቸው ከእውነት ጋር በታረቀ ቁጥር፤ በረቂቅ ንዑድ መንፈስ ከታነጸ ስጋቱ የዶግ አመድ ስለነበር። በጸጋዬ ራዲዮም ሙሉ ሰላማዊ ሰልፎችን፤ ሙሉ ውይይቶችን እንዳለ አቀረበው ነበር። „በድምጻችን ይሰማ“ ታገድሎ „የሴቶች ተሳትፎም“ ድንቅ ነበር። የራሳቸው ጉባኤ ሁሉ አድረገው ነበር ውጭ አገር። ያ ለእኔ ድንቅ ነበር።

ተጋድሎው በጣም የተመሰጥኩበት ነበር። የሰው ልጅ ነፍስ አለችው። የዛች የነፍሱ ማረፊያ መተንፈሻ ሰላማዊ ቀዬዎ ደግሞ ሃይማኖቱ ነው። እስኪ አስቡት ሃይማኖት ምድር ባይኖራት ብላችሁ? ምን ትመስል ነበር ፕላኔታችን? ውሃ ሲሄድበት የከረመ አለት ትሆንም ነበር።

ስለሆነም የሃይማኖት ነፃነት ከተነፈገ የአንድ ሰብዕዊ ፍጥረት ነፍሱ ተወስዳበታለች ማለት ነው። ሃይማኖት ፍጹም የሆነ መጽናኛ ነው። ሃይማኖት ጽናት ነው። ሃይማኖት ተስፋ ነው። ሃይማኖት ሰው ሆኖ ስለመፈጠር ሚሰጢር ነው። ሃይማኖት ነፃነቱ ከተወሰደ ሰው ሆኖ የመፈጠር ሚስጢሩ ተወሰደ ማለት ነው።

ይህ ማለት ቀለም የሌለው እስክርቢቶ ወይንም ቀን የሌለው ሌሊት ማለት ነው። ሁሉ ነገር ልሙጥ ይሆናል። ስለሆነም ነበር ደፍሬ የገባሁበት። እንደዚህ ባሉ ፈታኝ ጉዳዮች ላይ ዘው ነው የእኔ ነገር። በፈተና ውስጥ የመኖሬ ንጥረ ነገር ያለው የመፈጠሬ ሚስጢርም ይኸው ነው። ለዚህም ነው የተፈጠርኩት። ፈተናን መፈር።

በዛም ምክንያት በዬአቅጣጫ ሰፊ የሆነ ወጀብ በርክቶብኝ ነበር። „አሸባሪ“ ደግፍሽ ተብዬ። እውነት ትሳካ ከተበላ ያ ተጋድሎ ለፖለቲካ ትርፍ ሳይሆን ስለ ነፃነት ትርጉም የገባው ነፍስ ሁሉ ካለምንም ገደብ እና ቅድም ሁኔታ ሊደግፈው፤ ከጎኑ ሊቆም፤ ሊያበረታታው የሚገባ አርያዊ፤ ተምሳሌታዊ እንደ ሮል ሞዴል ሊወሰድ የሚገባው ፍጹም ሰላማዊ፤ ሉላዊ እና ብሄራዊ ተጋድሎ ነበር። ቅን ንቅናቄ ነበር።

·       ወርት እና ታገድሎ አይለካኩም።

የፖለቲካ ትርፈኞች አይጸኑም። ለወቅቱ ይጠቀሙበት እና ሌላ ደግሞ ደጎስ ብሎ ሲወጣ ያንን የያዙትን ይለቁን ሳያጠነክሩ፤ በውስጡም ሳሰርጹም// ሳሰርጹም፤ በውስጡ ሳሰክኑ፤ ተከታዮቻቸውን ሳያሰክኑም ለወረተኛው ተጋድሎ ደግሞ እጃቸውን ሰጥተው ተፍተፍ ሲሉ ከሁሉም ሳይሆኑ እንሱም ባክነው፤ ያን መከረኛ ትውልዱንም አባክነው ይቀራሉ፤ ለዚህም ነው በዬዘመኑ ፈሰው የሚቀሩት።

„ከድምጻችን ይሰማ“ ወደ „ኦሮሞ ንቅናቄ“ „ከኦሮሞ ንቅናቄ“ ወደ „አማራ የህልውና የማንነት ተጋድሎ“ „ከአማራ ተገድሎ ወደ ኢህዴጋዊ ጥገናዊ ለውጥ … በዚህ ውስጥ ትርፋና ኪሳራውን፤ ጉግስና ጦርነቱን፤ ስኬት እና ስርገቱን መለካት ነው፤ ህሊና ሚዛን ማንዘርዘሪያ ስላለው። የህዝብ ዳኝነትም መስታውት ስለሆነ። የፈለገ ይምጣ ይሂድ አንድ ንቅናቄ በተፈጠረበት ልኩ ላይ ጸንቶ እስከ መጨረሻው ድረስ መቆም ከተሳነው አተርፍ ባይ አጉዳይ ነው የሚሆነው። 

„የድምጽችን ይሰማ“ ስኬት በተነሳበት ግልጽ እና ቀጥተኛ፤ እንዲሁም ባልተንዛዙ ቁልፍ ጉዳዮቹ ብቻ ጸንቶ ተጋድሎውን መቀጠሉ ነው ለስኬት ያበቃው። በወጀብ ለመናጥ አልፈቀደም። ተጋድሎውንም ለማስጠለፍም፤ እራሱም ለመጠለፈም አልወደደም።
ሲሞቅ ሳይሞቅ፤ ሲፈላ ሳይፈላ፤ ሲንተከተክ ሳይነተከተክ አለተዘባረቅም። 

ሲፈጠር በነበረው ልክ ቀጥ ብሎ በብቁ የአማራር ጥበብ ተጋድሎውን ጀመረ መጨረሻውን ያሳምረው እና ፍጻሜውም እንዲህ አማረ። የሰከኑ፣ የረጉ ሊሂቃንም አሉት። ብቃት ብልጽጎ፤ ሰልጥኖ የታዬበት ተጋድሎ ነው።

መቼም እኔ እንደ አንድ የነፃነት ታጋይ ያን የመሰለ ወጥ አመራር፤ ወጥ ራዕይ፤ ወጥ ግብ፤ ወጥ ሥነ - ምግባር፤ ወጥ መንፈስ፤ ወጥ እውነት፤ ወጥ ቅንነት፤ ወጥ ንቅናቄ አኃቲ መንፈስ ያለው ጽናት አላዬሁም። የሚያኮራ ተገድሎ ነው የነበረው።

የባለቤትነት የኮፒ ራይት ጉዳይም ስላልገጠመው፤ ያንንም ተጋድሎ ለማስነጠቅ ሆነ ለማስደፈር ስላልፈቀደ በድሉ ውስጥ እንሆ ሰከነ። በዚህ ውስጥ ብዙ ብልህ ነገሮችን በማስተዋል መመርመር ያስፈልጋል። ልደር ልዋል ያለበት ቅጥያ መንፈስ አልነበረውም። እስኪ ልሞክረው ያለውም ነገር አልነበረም። ተጋድሎውን መሞከሪያ ጣቢያ እንደ ጥንችል አላደረገውም፤ መስዋዕትነቱንም በከንቱ አላፈሰሰውም፤ በተፈጠረበት ተፈጥሮው ልክ ታገለ ሰብሉንም አፈሰ።   

እኔ ዘሀበሻ ፈቅዶልኝ ስሜቴን፤ ውስጤን፤ ተስፋዬን በዛ ወቅት በድፍረት ስጽፍ ያለምንም ገደብ አውጥቶልኛል። ለዚህም እጅግ አድርጌ አመሰግናዋለሁኝ። በኋላ ላይም ሳተናው እንዲሁ በቅንነት አሰተናግዶልኛል። እሱንም እጅግ አድርጌ አመሰግነዋለሁኝ።

ለዛውም የእኔን ጹሁፍን ፈቅዶ እስከ ፎቶዬ ማውጣት ዋጋ ያስከፍላል። ግን የሁለቱም ድህረ ገጽ አዘጋጆች ደፋሮች ናቸው። ይገርመኛል ሁልጊዜም ሳስበው። ሃሳብን ስትፈቅደው እንዲህ ስኬት ሲገኝ ህሊናን አይጎረብጥም። ምን ለማለት ነው፤ እነዚህ ድህረ ገፆችም ተጋድሎውን በቅንነት በማዬት የጎላ ድርሻ አበርክተዋል እንደማለት … የስኬቱ ባለቤቶችም ናቸው።

በዬትኛወም የጹሁፌ አዋራ ጭብጥም ለናሙን „ድምጻችን ይሰማን“ እነሱን ሳለነሳ ያቀረብኩበት ጹሁፍ እንብዛም ነው። ይናፈቃኛል የሂደቱ መሳጭ ተደሞ። የጽናታቸው እውነት በሌላ አካል፤ ወይንም ቡድን ሳይጠለፍ ተጋድሏቸው በጽናቱ ልክ ባለፈው ሳምንት ምዕራፍ ሦስት ለስኬት በቅቷል።

1.               ምዕራፍ አህድ።

የመጀመሪያው ስኬት የድምጻችን ይሰማ የነፃነት ጀግኖች ከእስር መለቀቅ የመጀመሪያው ምዕራፍ ልንለው ይገባል።

2.               ምዕራፍ ክለት።
ምዕራፍ ሁለት ደግሞ ሁለቱን ለማገናኘት በጠ/ሚር ቢሮ የተካሄደው የመጀመሪያ የንግግር ሂደት ነው።
3.               ምዕራፍ ሰለስት።
ሦስተኛው ምዕራፍ ደግሞ በሸኘነው ሳምንት የነበረው„ተቋማዊ ለውጥ እና የአንድነት ሀገር አቀፍ ስብሰባ ውጤት“ ማለት ይቻላል።

ይህ የሰሞናቱ ንጥር ስኬት ተጋድሎው አርበኞች የቅንነታቸው ልኬታው የነጠረ እውነት ስለነበር ስኬቱም በሮማዳን ጾም ዋዜማ ነው የሆነው። ታስታውሱ እንደሆን የውጭ አገሩ „የሰላም ፋውንዴሽን አመታዊ ስብሰባ“ ቀኑ ከጠ/ሚር አብይ የስሜን አሜሪካ ጉዞ ጋርም ግጥጥም ነበረው። በወቀቱ ጽፌበት ነበር። አምላካዊ ፈቃድ አለበት ብዬ።

ለዚህም ነው በሁለቱ ኃይማኖት በኢትዮጵያዊ እስልምና እና በኢትዮጵያዊው ኦርቶዶክስ ተዋህዶ የተጀመረው ጥረት ስኬት ከሁሉም ነፍስ ያለው ስኬታማ ሆኖ የሚገኘው። እኔ አሁን በቅድስት ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ባለው ጉዳይ የነቁጥ ያህል ተለያይተን እንደነበር ሁሉ አላስታውሰውም። ትዝ ብሎኝም አያውቅ። ይህ የእኔ ሃይል አይደለም የእውነቱ ሃይል ያደረገው እንጂ …

·       መማሪያ ሰነድነቱ።

አገር ከሚመራው ድብርት ላይ ካለው ከኢህአዴግ ጀምሮ፤ ከዘመኑ አውራ የኢህዴግ መሪ፤ በተዥጎረጎረ አቋም ሱናሜውን ሲለቅብን ከባጀው ድርጅት ኦዴፓን አክሎ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ድርጅቶች ሁሉ መማር ካለባቸው ስለ እውነት፤ ስለ ዓላማ ጽናት፤ ስለነጻነት ድንቅነት፤ ስለ ህሊና ቅንነት ድንግልና፤ ስለ ብርታት ስኬት፤ ስለ ንጹህ ራዕይ ሰብላማነት፤ ስለ ንጹህ ግብ ሰፋኒትነት፤ ስለ አመራር ጥበብ ብጡልነት፤ ስለ አደረጃጀት ልባምነት፤ ስለ ጽናት ድልነት ቁጭ አድርገው ፊት ለፊታቸው „ከድምጻችን ይሰማ“ አንከሮች መማር ያለባቸው ይመስለኛል።

እንዲያውም እኔ አንደ ሥርጉተ ሥላሴ መሪዎችን ዕድሉን ሰጥቶ ለተፎካካሪ/ ተቃዋሚ/ ተቀናቃኝ የፖለቲካ ድርጅቶች ኢህዴግን ጨምሮ፤ ለሚዲያ ሰዎች፤ ለሥነ - ጥበብ ሰዎች፤ ለአክቲቢስቶች፤ አንድ አውደ ጥናት ቢሰጥበት እውዳለሁኝ እብደትን ተማሩ ብሎ ቤተመንግሥት ለነምንትሶ መድረክ ከሚያዘጋጅ

ተዝቆ የማያልቅ ተመክሮ ነው ያለው። የእዝ ሰንሰለቱ እራሱ እኮ ግርም ድንቅ ነው የሚለው በትንፋሽ፤ በዓይን ጥቅሻ ቀጥ፤ ጸጥ የሚል፤ የሚያደርግም የሰራዊቱ ስምሪት ነው የነበረው። የድንቆች ድንቅ ተጋድሎ ነው „ድምጻችን ይሰማ“ ማለት።

በዛን ወቅት ለነፃነት ትግሉ የከፈተው ቧ፤ ፏ ያለ በር፤ ለሰላማዊ ተጋድሎ የሰጠው ጥንካሬ እና ብርታት ረቂቅ ስለመሆኑ ማንም አያወቀውም። መለኪያ፤ መመዘኛ፤ ማመጣጠኛ ቋት የለንም።

እኛ ወረተኞች ስለሆን፤
እኛ የሚበልጠንን መንፈስ ተቀናቅነን ስለመንነሳ፤
እኛ ማድነቅም እርማችን ስለሆነ፤
እኛ አቅም አለ ሲባል ያን አረም ለማስወረር ስለምንተጋ እንጂ „የድምጻችን ይሰማ ተጋድሎ“ ለኢትዮጵያ የሰላማዊ ተጋድሎ ልዩ ፍጹም የሆነ አዲስ ካሪክለም የነደፈ ልዩ ሊጠና የሚገባው ሌሰን ነበር።

ሌላው ቀርቶ የአንድነቱ በህወሃት ሴራ „የሚሊዮኖች ድምጽ“ ሳይዘልቅ ቀረ እንጂ። የሰማያ ፓርቲ የጣይቱ ልጆች የመጀመሪያው ብሄራዊ ትንግርታዊ አንስታዊ ሰላማዊ ሰልፍ አስተምህሮታቸው ልቅናው ረቂቅ ነው። ብዙም ሲነሳሳ ሰምቼ አላውቅም እኔ። የእኛ ነገር እንዲህ ነን ያዝ ለቀቅ ነው …

·       የድምጻችን ይሰማ የተጋድሎ ስልት። 

ወደ ቀደመው ምልሰት ሳደርግ የድምጻችን ይሰማ የትግል ስልቱ ራሱ አስደማሚ ነበር። ተውኔት ነበር ለዛውም ልብን ቀልብን አሳምሮ በፍቅር የሚገዛ። የዕድሜ ልኩን የፖለቲካ ሊሂቃን ተመክሮ ሁሉ ፈተና ላይ ያስቀመጠ ነበር።

የእኛ የነፃነት ትግል የሚከፈለው መስዋዕትነት  ሲፈርስ ሲሰራ፤ በአራስ ቤቱ ሲሳራ ሲፈርስ፤ በጫጉላ ጊዜው ሲዋህድ ሲበተን፤ ለጎጆ ሳይበቃ ተብትኖ ሲዋህድ፤ ግጥግጥ ላይ ሲያፍስ ሲለቅም፤ በፍርሻ ለቅሞ ሲያፍስ … የትካዜ ድንኳን ሲያስታቅፈን … ነው ያኖረን።

 በአፉም በሙርጡም ቀዳዳ ለሆነው የተግባር ቋታችን ታላቅ ተቋምም ነው „የድምጻችን ተጋድሎ“ ትውፊት። ወረተኛ አልነበረም። አልተከፋፈለም፤ እንደ አልረጋ ወተት አልተበጣጠሰም፤  እንደ ሰባራ ብርሌ አልተሰነጣጠቀም፤ አንድ ወይራ ፍልጥ አልተተረተረም። በቀደመው በተነሳበት ዓላማ ጸና። ጽናቱ ለአቅመ አዳም እና ለአቅም ህይዋን የበቃ ስለነበር ከግብ አስደረሰ።

የድምጻችን ይሰማ ሥልጡን የሆነ፤ ሞደርን የሆነ፤ ኢሌጋንት የሆነ፤ ጨዋ ኢኖሰንት የሆነ፤ የረጋ ተጋድሎ ነው የነበረው። መጽሐፍ እኔ ብጽፍለት ሁሉ እውዳለሁኝ። እንቁ ነውና።  
„ድምጻችን ይሰማ“ እንደ ቄብ ዶሮ በዬደረሰበት ቦታ አልመደመደም። 

በወጥ፣ ብቁ፤ የነጠረ መረቅ አመራር ቀጥ ብሎ ታገለ፤ በጽናቱ፤ በንጽህናው፤ በእውነት ፈላጊነቱ፤ በርትህ መሻቱ ልክ ይኸው ልድል በቃ። የተስፋ ጽላት ነው ለእኔ። መከራን ደፍሮ ፊት ለፊት የተጋፈጠ፤ ደሙን፤ ኑሮውን፤ ሰላሙን፤ ወጣትነቱን ገብሮ ግን ለሰከነ ድል የበቃ አነቱ አምድ።

ድሉ እነሱ እንደሚሉት ለኢትዮጵያዊው የእስልምና ተከታዮች ብቻ ሳይሆን ድሉ የእውነት ንጽህና እና ቅድስና፤ የኢትዮጵያዊ አመክንዮ ድንግልና፤ የሉላዊ ዓለም የሰላም ምልክትነትም ድል ነው።

ተጋድሎው በዬትኛውም የፖለቲካ ድርጅት ፍላጎት ሳያስጠልፍ፤ ለዛም ሳያጎበድድም፤ ተጋድሎውን በስሜት ሳያስጋልብ ወደ አልሆነ አቅጣጫ እንዲዘነጠል ሳይፈቅድም፤ ኢትዮጵያዊ ተፈጥሮውን ህብረ ቀላማቱን ሳይስለቅቅ፤ በተጨማሪም ታገድሎውን ለፖለቲካ ሸቀጥ ሳያውል ለቆመለት እና ለተነሳለት ዓላማ በጥራት እና በቁርጠኝነት ጸንቶ ታገለ፤ … እንሆ ለፍሬ በቃ አሰበለ

ሳስብው እራሱ ሐሤት አገኝበታለሁኝ። ሽው፤ እንዲያው ሽው፤ ትዝ እንዲያው ትዝ ነው የሚለኝ ሂደቱ፤  ቀላማሙ የእውነት አንባሳደር የተጋድሎው ማንነቱ። ማንነት የነበረው ተጋድሎ ነበር። ማንነቱን አጉልቶ እና አብልጽጎ ምዕራፍ አንድን፤ ምዕራፍ ሁለትን፤ ምዕራፍ ሦስትን አሳክቶ ለምዕራፍ አራት መንገድ ጀምሯል። ይቅናው!

„የድምጻችን ይሰማ“ ራሱን ያቸለ ሚዲያም ነበረው። ቢቢኤን ራዲዮም የቴሌቪዥን ፕሮግራም። ለነጻነት ትግሉ የበኩሉን አስተዋፆ አድርጓል። አብሶ ለ አማራ የህልውና ተጋድሎ በቂ ሽፋንም ሰጥቶታል። ሚዲያው የተነሳበት ሃይማኖታዊ ስለነበር  ተልዕኮው መልክ መያዝ ሲጀምር እነዛ የነጻነት አርበኞች ሲፈቱ የሚዲያ ስርጭቱን አቆመ። ይቀጥሉት አያቀጥሉት ወደፊት ባላውቅም አሁን እረፍት ላይ ነው።

ስለምን? ብዬ እኔ ሳስብ መንፈስን ላለማውክ፤ መንፈስን ላለመበትን ከፈጣሪ ጋር መንፈሳቸውን በንጽህና አገናኝተው በድንግልና ቀጣይ ተጋድሏቸው በጥሞና ለመቀጠል ያሰቡ ይመስለኛል።

በሌላ በኩል መሪዎችም ራሳቸው በባለቤትነት፤ በኃላፊነት ባዕት ላይ ስላሉበት፤ መሬት ላይ የኃላፊነት ክፍፍሉንም አሳምረው ሁነውበታል። ትግልም ታገድሎም እንደነሱ ከሆነ ምን አለ ቢደከምለት …

አሁን አንዳንድ የፖለቲካ ድርጅቶች አባሎቻቸው በሚዲያ መንፈስን ወጥ ያደርጉና ወጥተው ደግሞ ብራና ላይ በሚጽፉት ሙግት ይገጥማቸው እና በወጥ ሚዲያቸው አህቲ ያደረጉት መንፈስ ሲበተን፤ ሳንክ ሲገጥመው፤ ጥያቄ ውስጥ ሲገባ ይስተዋላል።

በዚህ ሂደት ከትርፍ ብዙ ኪሳራ ነው የሚዛቀው። በዚህ ዘርፍ „ድምጻችን ይሰማ“ በብዙ ሁኔታ ቁጥብ መሆኑ ረድቶታል። ከመግለጫዎች ውጭ የግል ዕይታዎችን አምቆ መያዝ ብዙ አትራፊ ነው ያደረገው።

ብዙ ድርጅቶችን አቅም የበላው ከፍተኛ አመራር አካላቱም ሳይቀሩ ስሜታቸውን መቆጣጠር እዬተሳናቸው፤ አባላቱም እንዲሁ የግል ዕሳቤያቸውን በገለጡ ቁጥር ስንጥቅ እዬፈጠረ ድርጅታቸውን ተልዕኮ አቅምን ተፈታትኗል። ይህን ከሥነ ምግባር ውጪ የሆኑ ጉዳዮች ባሊህ ማለት የተገባ ነው ለአንድ ነፃነት ለራበው ተጋድሎ። ዲስፕሊን የሚባል ነገር አለ።  

„ድምጻችን ይሰማ“ ግን ብዙም በዚህ ዘርፍ ከጥቂት ጊዜያት ውጪ ለዚህ መሰል ነገር ብዙም አልተጋለጠም፤ ይህም ረድቶታል … መሬት ላይ ያለውን የሰላማዊ ተጋድሎ አቁሞ ሌላ የትግል ስልት የተከተለበት ጥበብ በራሱ ረቂቅ ነበር።

„ድምጻችን ይሰማ“ በውነቱ መሪ አግኝቷል። ሳይዝረከረክ እንደተከበረ ለስኬትም ያበቃው ይኸው የመሪ ክህሎት ጥበብ እና ብቃት ነው። መሪውም ባለ አዎንታዊ ቅብዕ እንዳለውም አምናለሁኝ።

መሪዎቹ ስክነትን ወደው እና ፈቅደው ስለዋጡት ይደማመጣሉ። እርስ በእርሳቸው በኢጎ ውድድር ውስጥ ስላልነበሩ ይዋዋጣሉ። እርስ በእርሳቸው ይከባባራሉ፤ እርስ በእርሳቸውም ይተማመናሉ። የሚገርመው ማን መሪ፤ ማን ተመሪ፤ ማን አስተባባሪ፤ ማን ተባባሪማን የፊት ለፊት ረድፈኛ፤ ማን የጀርባ አጥንት፤ ማን ፒላር  እንደሆኑ አይታወቅም። የተከደነ ሲሳይ ነበር ሂደቱ። 

ጉዳዩ የዝና እና የኢጎ ቁልል ትውር ስላለበት። እውነት ለመናገር እኔ ከልቤ ሆኜ ሳስተውለው ቅን፤ ንጹህ የነበረ ተጋድሎ ስለነበረ በሰው አቅም ሳይሆን በፈጣሪ / በአላህ አቅም ለስኬት በቅቷል ብዬ አስባለሁኝ። ምዕርፍ አንድም// ምዕራፍ ሁለትም፤ ምዕራፍ ሦስትም ተሳክቷል፤ ምዕራፍ አራትም „ባላደራው ባለ ፅኑ የነፃነት ባለ ራዕይ“ ለፍጻሜ አብቅቶ አንዲሳካላቸው ምኞቴ ነው።

በንጽህና የተጀመረ ስለሆነ ሦስቱም ምዕራፎች ጸሎቱም በንኡድና እንሆ አረገ። ወደፊትም ለአላዛሯ ኢትዮጵያም ባለፈም ለአፍሪካም የሰላም መተማመኛ ተምሳሌታዊ ጉልላት ይሆን ዘንድ ፈጣሪ /// አላህ ይርዳቸው። እኛንም ይርዳን። አሜን። መስክሬ ያላሰፈረኝ ተጋድሎ ቢኖር „የድምጻችን ይሰማ ብቻ ነው“

·       የ2011 የሮመዳን ፆም የታወከውን አዬር ይጠርግ ዘንድ …  

ምኞት አያልቅምና የ2011 የሮመዳን ፆም የታወከውን ኢትዮጵያዊ አዬር ያጠራ፤ ይጠርግ ዘንድ ነው ዛሬ ይህን ጹሁፍ እንድጽፍ ያነሳሳኝ መሰረታዊ ምክንያት። አንድ ብልህ ቁምነገር ስላለኝም ነው።

በስሜት ውስጥ ለሚባዝነው የፍላጎታችን ድፍርስ የጎሼ ብጥብጥ እና አንባጓሮ ላይ ለተንጠለጠለው ነፍሳችን እነሱን ፈጣሪ ይሰማቸዋልና ይህን ፆመ ሮመዳን ይህ በሁሉ ላይ ሰፍሮ ያለውን ህውከት ላይ የሚገኘውን ራዕያችን ፈጣሪ // አላህ ያሰክነው ዘንድ ልክ እንደ „ድምጻችን ይሰማ“ ተልዕኮ በንጹህ መንፈስ ሆነው፤ በአቲ መንፈስ ሆነው እንዲጸልዩት ለኣላዛሯ ኢትዮጵያ በአክብሮት ላሳስባቸው ነው።

አላዛሯ ኢትዮጵያ ጭንቅ ላይ ናት። ሃይማኖት የሚኖረው አገር ሰላም ስትሆን ነው። ዛሬ ኢትዮጵያ በሰላሟ ውስጥ አይደለችም። ሰላሟ አጉርፏል፤ ሰላሟ አደምኗል፤ ሰላሟ ታውኳል፤ ሰላሟ አልጋ ላይ ውሏል።

ኢትዮጵያ በመኖሯ ውስጥ አደጋ ውስጥ ናት። አደጋውን እራሱ ያስተዋለው የለም። በጭፍጫፊው፤ በቅርጥምጣሚው ላይ ነው አትኩሮቱ።

እኛ በጊዜያዊ ሐሤት ስንጨፍር እሷ ግን በግራ በቀኝ በ100 ሚሊዮን ፍላጎት ተዥጎርጉራ ክፉኛም ተወጥራ ልትፈነዳ ደርሳለች። አንድ ነፍስ ወዘተረፈ ፍላጎት ነው ያለው፤ ሌላው ደግሞ ድንኳን አጥቶ ሜዳ ፈሷል። 

ፍላጎት የሌላው ነፍስ በምድር የለም። የፍላጎቱ ደግሞ ዥንጉርጉር ቱማታ የሰገረበት ነው። ብስጭት ድንፋታ ያደራበትም ነው። ሴራው ቡፌ ነው። ሸሩ በቦንዳ ነው፤ ተንኮሎ ውቅያኖስ ነው፤ ሉዕላዊነቷ እራሱ ቀይ መሰመር እዬረገጠ ነው። አገር ሰላም ውላ የምታድረው በኪነ ጥበቡ ነው።  

·       በምልሰት ቅኝት።

ውዶቼ የጹሁፌ ታዳሚዎች፤ እና አድማጮቼ እኔ የጎንደር ልጅ ነኝ። የጎንደር አራት ዓይናማ ሊቀ ሊቃውንት አሉ ከሚባሉት ውስጥ የልጅ ልጅ ልጅ ነኝ። እኔ ሳድግ አንድ ከበድ ያለ ነገር ሲፈጠር በክብር ነው መልዕክት የሚላክላቸው ለሊቃናቱ የእስልምና አበው „በድዋ እባካችሁ እርዱን“ ተብለው።

ዝናብ ሲጠፋ፤ ያው ጦርነት የማያጣው መከረኛ ባዕት ስለሆነም መንፈስ በጦርነት ግለት ሲናጥ … ትውልድ ሲታጨድ እባካችሁ „ድዋ ያዙ ተብለው አበው ይለመናሉ። ምህላውን በድዋ ደግፉልን ይባሉ“ ነበር። እንዲህ እንደ እኔ ከሳት ከውሃ የሚሉ፤ ፈተናን የሚደፍሩ ወጣት ልጆች የገጠማቸው ወላጆችም ደግሞ ለሃጂዎች፤ ለሼኾች ሹክ ይሏቸዋል። እኔ ብዙ ድዋ ተይዞልኝ ያውቃል።

ሌላው ቀርቶ የቅድስት ኦርቶዶክስ ሊቀ - ሊቃውንት አያቶቼ ማዕድ ቀርቦ „አላህ አክብር!“ ሲባል „አያችሁ እኛ ማዕድ ላይ ነን። እነሱ ግን አሁን በዚህች ቅጽበት መንፈሳቸው ከፈጣሪ ጋር ነው ሲሉ“ ታላላቅ የአገር አድባር፤ የአገር ጉልላትም የሆኑ አያቶቼ ሲናገሩ እያዳመጥኩኝ ነው ያድግኩት።

ቅድስት ኦርቶዶክስ ተዋህዶ በሁሉም ሃይማኖቶች ፍልስፍና ላይ የራሷ የሆኑ የዕድምታ መጻህፍት ሁሉ አላት። የእስያኑ እምነት ሳይቀር። ይህን የረቀቀ መስተዋድድ ዘመን እያደረቀው፤ ዘመን እይፈለሰው እንሆ ዛሬ ዓለማችን ጉማም፤ አስፈሪ እዬሆነች መጣች። አገራችንም እንዲሁ።

እርስ በእርስ መደማመጥ ከስቶ እንሆ በአገር ውስጥ የተፈናቀይ ህዝብ ብዛት መጀመሪያ ረድፍ ላይ አገራችን ትገኛለች፤ በድህነት ደግሞ ከአፍሪካ ከመጨረሻዎች አገሮች ተርታ አንዷ ናት። ይህ ኩራታችን ነው ለእኛ¡ 

እውነትን ፈርተን ስለ እውነት እንሰብካለን፤ እውነት መሆን ሳንችል ቀርተን እውነት ተዛባ ብለን ሌሎችን እንከሳለን። እውነት መሆነን ተሰነን

የሆነ ሆኖ ያ በተመስጦ እከታተለው የነበረው „የድምጻችን ይሰማ“ የእውነት ውሃ ልክ የለጋ ስኬት የሮመዳን ወቅት ለአላዛሯ ኢትዮጵያ ከልቡ ሆኖ ይጸልይ ዘንድ በአክብሮት እና በትህትና ላሳስብ እሻለሁኝ።

እንደ ወትሯቸው ሁሉ ሆነው በፍቅር ለእናታቸው ይጸልዩላት ዘንድ በትህትና አሳስባቸዋለሁኝ። የኢትዮጵያ ነገር ይጨንቀኛል። አሁን እኮ በፋጋ ሳይቀር ሆኗል እምንጣላው … ፋጋ ከቅል የተሰራ የቤት ውስጥ መገልገያ ዕቃ ነው … ዕድሜውም አጭር የሆነ የቤት ውስጥ ቁስ ነው …

·       ስኬት ከእውነት ጋር ሲገናኝ።

ጠ/ሚር አብይ አህመድ ከተሳካላቸው አንዱ ይኸው በሁለቱ ኃይማኖት የጀመሩት ጥረት ዳር መድረሱ ነው። እርግጥ የቤተ - አምልኮ መቃጠል እና የሰማዕታቱ ቁጥር የኪሳራ ዕሴቱን አመጣጥኖ መለካት ባይቻልም። በዚህ ሐሤት ውስጥም የመንፈስ እንደ አዋዜ መደቆስ አለ አድባራት ሲቃጠሉ፤ መስጊዶች ሲቃሉ ውስጣችንም አብሮ ቅጥል ነው የሚለው። ራሱ ስንት ነፍስ እንደጠፋ መረጃው እንኳን በቅጡ የለንም።

በአውንታዊ ትርፉ መንግሥት በኃይማኖት ነፃነት ላይ ጣልቃ ሳይገባ፤ ነፃነቱን ከጠበቀ በአንጻሩም በውስጥ ሰላም መንፈስ ልዑል እግዚአብሄር በዚህ ጽናት ልክ ይህ የታመመውን የፖለቲካ መንፈስ ይፈውስ ዘንድም ቅንነትን አምጦ በመውለድ እውነት ሆኖ ለመገኘት ይቻል ዘንድ ፈጣሪ ይርዳን። አሜን።

ለፖለቲከኞች አያታያቸውም እንጂ ያለንበት ወቅት በወዘተረፍ ድግሥ የምንስታግሰው አይደለም። በስብሰባ በኮሜቴ ብዛትም የመንቀርፈውም አይደለም። እውነትን ውጡ በጠራ ፍላጎት አመድ ነስንሶ፤ ንስኃ ገብቶ በቅንነት እና በንጽህና ወደ ፈጣሪ አቤት የምንልበት ወቅት ነው።

ተስፋ መቅረብ እና መራቅ፤ ተስፋ መራቅ እና መቅረብ፤ ተፈጥሮ መሳቅ እና ማለቀስ፤ ተፈጥሮ ማልቀስ እና መሳቅ ትውልድን አያበረክትም። ሰው መሆናችን እዬተነነ ነው። መፈጠራችን ስለምን ስለመሆኑ ተዳባልቆብናል። ግራጫማ ተስፋ ነው ያለን። ሲቃ ያዬለበት።

ሞትን ታቅፍን መኖርን እናውከዋለን። ነፍሳቸውን ይማረውና የቀድመው ፕ/ የዶር ነጋሶ ጊዳዳ በቁም ሄደው ሬሳቸው መመለስ፤ በቀያችን ያን የመሰለ አውሮፕላን አደጋ መከሰተ ሁሉ አላስተማረንም፤ እንዲያስተምርንም ስለማንፈቅድለት። ዝም ብለን በሞተ አዬር ላይ እንገልባለን … ተንሳፈን ያለበት ሁኔታ አልገባንም። መሬት እንያዝ።

ወደ ቀደመው ምልሰት ሳደረግ የድምጻችን ይሰማ ስኬት ለመላ አፍሪካም መድህን ነው፤ ከዚህም ባለፈ ለዓለምም።

ሰው በእምነቱ ልክ ሳይቆራረጥ፤ ሳይበጣጠስ፤ ሳይቃጣጠፍ ነፃነቱን ማግኘት ይኖርበታል። ሰው በእምነት ጽናቱ ልክ ነፃነቱን ማግኘት አለበት። የተፈጥሮ ነፃነቱ ሰው ሰራሽ አይደለም። ሰው ሆኖ ሲፈጠር ነፃነቱን ፈጣሪው/ አላህ ሰጥቶታል። የሰው መፈጠር ምርቃቱ ነፃነት ነው። ይህ ግን በጉልበተኞች መነጠቅ ነው ሰላምን የሚያውከው።

የፈጣሪ/ የአላህ ስጦታ መነጠቅ ነው የህውከት ሁሉ ምንጩ። የሰላም ዕጦት መንስኤው የነፃነት ነጠቃ ነው። በዚህ ነፃነት ውስጥ አንድ ሰው ያለው ነፃነት በሌላው ሰው ነፃነት እግር ሥር መውደቅ የለበትም። ይህ ስግብግብነት ነው።

የኢትዮጵያ ፖለቲካ ቅኝት ትናንትም ሆነ ዛሬም ይህ ስግብግብነት ነው። በሁሉም ዘርፍ ከዚህ ስግብግብነት ቢዳን አገር ሰላም መሆን ትችላለች። ካለምንም ወጪ። የሰው ልጅ በተፈጠረው ልክ ነፃነቱን ከተሰጠው ውስጡም፤ መኖሪያውም አካባቢውን ሰላም ይሆናል።  
በመጨረሻ ለህብራዊው የኢትዮጵያ የእስልምና ዕምነት ተካታይ ወገኖቼ መልካም የሮመዳን ፆም እንዲሆን እመኛለሁኝ።

የኢትዮጵያ የእስልምና አማንያን እናታቸው ሲከፋት አብረው ሲከፉ፤ እናታቸው ስትጎሳቆል አብረው ሲጎሳቀሉ፤ እናታቸው መከራ ሲደርስባት አብረው ጥቁር ሲለብሱ፤ እናታቸው ስትጋፋ አብረው ሲገፉ፤ እናታቸዋ ትፍዊፊቷ ሲፈልስ አብረው ሲፈልሱ፤ እናታቸው ነፃነቷን አጥታ ስትሰደድ አብረው ሲሰደዱ ኖረዋል።

ስለዚህም በእናታቸው ውስጥ ስለመኖራቸው ታላቁ ማህተሙ የሃይማኖት ነፃነታቸው በሙሉ መከበር ሲችል መሆን ይገባዋል። ጅምሩ ጥሩ ነው። መጨረሻውን ደግሞ ፈጣሪ/ አላህ ይጨርሰው።

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ባህል ስግብግብ ስለሆነ አሁንም እርግጠኛ የማያደርግ ነገር ሳላለ ነው እኔ ጅምሩ ጥሩ ነው ብዬ ገርበብ አድርጌ መተው የፈልገኩት፤ ፖለቲከኞች እጃቸው አያርፍም፤ መንፈሳቸው አያርፍም፤ ስክነት ክፋላቸው አይደለም ለፖለቲካ ሊሂቃን፤ ግጭት አውሌያቸው ይመሰለኛል። ማተረማመስ ይወዳሉ።
    
በዚህ „የድምጻችን ይሰማ ተጋድሎ“ ሁሉም የድርሻውን ቢወጣም የጎላውን ድርሻ አጉልቶ፤ አጎልብቶ፤ አብልጽጎ፤ አክብሮ፤ አብክሮ ብሄራዊ፤ ዓለምአቀፋዊ አድርጎ አድምቆና አፍልቆ ያወጣው ግን የሐምሌ 5 /24 ቀን 2008 የጎንደር የአማራ የማንነት የህልውና አብዮት ነበር።

የአማራ የህልውና የማንነት ተጋድሎ „ድምጻችን ይሰማ“ መሪ ሞቶው ነበርና ስኬቱም የአማራ የህልውና የማንነት ታገድሎ ጭምር ነው ማለት እችላለሁኝ።

ከዛ ቀደም ብሎም የኢንጂነር ይልቃል ጌትነት ሰማያዊ ፓርቲም ቀለማም ተሳትፎ አገር ቤት በመሬት ላይ እንደ ነበረው እውነትን መካድ አይቻልም። በጉልህ መሬት ላይ ይደግፈው ነበር ፓርቲው፤ እንዲህ አርበኞቹን ገባብሮ ፈርስኩኝ ብሎ ሊያውጅ።

·       እርገት።


የሰውልጅ ሰው ሆኖ መፈጠሩ ምርቃቱ ነፃነቱ ነው።
ነፃነት የግለሰቦች ችሮታ ሳይሆን የፈጣሪ ስጦታ ነው።
የሰው ልጅ የፈጣሪን ጸጋ ነፃነትን ከማወክ መቆጠብ ይኖርበታል።

በድምጽ ደግሞ ሊንኩ ይኸውና። 



"የድምፃችን ይሰማ የስኬት ተመክሮ ዕድምታ እና የሥርጉተ ዕይታ።" (07.05.2019)


Published on May 7, 2019


የኔዎቹ ኑሩልኝ።
መሸቢያ ጊዜ።

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።