የፕሮፌስር መራራ መራር ማንፌስቶ።


እንኳን ወደ ቀንበጥ ብሎግ በሰላም መጡልኝ።

„እንሆም ሁሉም እሾኽ ሞልቶበታል።
ፊቱንም ሳማ ሸፍኖታል፤ የድንጋዩም ቅጥር ፈርሷል።“
(መጽሐፈ ምሳሌ (ተግሳጽ) ምዕራፍ 24 ቁጥር 31)
የፕሮፌስር መራራ መር ማንፌስቶ።
ከሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
ከጭምቷ ሲዊዘርላንድ።
27.12.2019



·       እፍታ።

እንዴት ናችሁ የእኔ ቅኖች የኢትዮጵያ ቅኖችም ዛሬ የኦፌኮ ሊቀመንበር ፕሮፌሰር መራራ ጉዲና ከሰሞኑ በሰጡት መግለጫ ላይ እና ተያያዥ ጉዳያዎችን እንደ አንድ የአገር መሪ ያላቸውን ሰብዕና አክሎ እምለው ይኖረኛል። ትዕግስት ሲያልቅ ፍቅር ይሰደዳል እና።
በቅድሚያ ግን የእኔ ውዶች ይህን ፎቶ ልጋብዛችሁ። 

ትኩር ብላችሁ በማስተዋል በፈርጅ በፈርጁ ታስተውሉት ዘንድ በትሁት አክብሮት እለምናችሁ አለሁኝ። እዩት እስቲ። ፈትሹት እስቲ። የአንድ የአገር መሪ ቢሮ ነው። በመንፈሳችን መሪ ቢሆኑልን ብለን ስናስባቸው ስንናፍቃቸው፤ ስንመኝም ኑረናል። የሰው ልጅ እራሱን የሚያደራጀው በራሱ ልክ ነው። እራሱን የሚመራውም በራሱ አቅም ልክ ነው። ከቶ ኢትዮጵያዊ መሪነት እና የዚህ ቢሮ አደረጃጀት እና አያያዝ ተመጣጠኑ ይሆን።

የፈረደባት ኢትዮጵያ ስንቱን ገመና ተሸከሚ ብለን አሳሯን እንዳበላናት ዛሬ ላይ ሳስበው ይሰቀጥጠኛል። በዚህ ዘመን ያላዬነው መከራ፤ ያልሰማነው መስቃ የለምና። ደበደቡን። ሰለቁን። ሾከሾኩን እግዚአብሄር ይይላቸው። የምንፅናናበት የፖለቲካ ሊሂቅ የለንም። ተስፋ የምናደርግበት የፖለቲካ መሪም የለንም።

·       ዝርክርክነት ለአገር መሪነት ያበቃ ይሆን?

ወግ አይቀር አይዋ ኮንፒተር ጉብ ብሏል። አሁን ይህ ቢሮ ነው ወይንስ የከብቶች ማደሪያ? ወይንስ የቆሻሻ ወረቆቶች ማጠራቀሚያ በርሚል? ሥሩን ሁሉ እዩት የፈረደበት አሻንጉሊት ሁሉ አለበት። አሻንጉሊት ለምን ኖረ ሳይሆን አወዳደቁን አስተውሉት ለማለት ነው። አቧራ ለብሶ ኤሉሄ ይላል አሻንጉሊቱም „ከአጋም የተጠጋ ቁልቋል ዘውትር ሲያልቅስ ይኖራል" እንዲሉ ሆኖበት።

አንድ ማቀፊያ የለውም ወረቀቱ ሁሉ። በረንዳ አዳሪ ሆኗል። እብድ የዘራው አዝመራ ይመስላል ጠረቤዛው በሉት ክፍሉ። ይህቺ መከረኛ አገር አሳሯን የምትበላው እንደዚህ ምስቅልቅሉን በወጣ ቢሮ አዕምሮ ነው። 

ከዚህ ምስቅልቅል የታመለ ክፍል በምን ስሌት እና ቀመር አገር አዳኝ የተደራጀ አቅም ይፍለቃል ተብሎ ይታሰብ? ስው ድርሽ የማይልበት ጠፍ ጫካ ይመስላል ጠረጴዛው እራሱ። ሁሉም መሳቢያም ክፍትፍት ብሏል፤ የሰነፍ ቡሆ ዕቃ መስሎ ተዝረክርኮ።

ከቶ የቱን ወረቀት ከዬትኛው ወረቀት እንዴት መለዬት ይቻላል? ውዶቼ እሰቡት ደጋግማችሁ አገር ከእኒህ ፕሮፌሰር መራራ ጉዲና እጅ ብትወድቅ ብላችሁ? በዛ ላይ የኢትዮጵያ ችግርም ከዚህ ቢሮ ምስቅልቅልነት በላይ ነው። አሁን ደግሞ ኦሮሙማ ምስቅልቅሉን በተደራጀ ቀውስ እያሳዋበው ነው በጭንቀት እና በስጋት እያስወረበ።

ታያችሁ አይደል ቅኖቼ? በተመሰቃቀለ ቢሮ የተመሳቀለ አገራዊ ችግር ሲፈታ?! እኔ ይገርመኛል ደረታቸውን ነፍተው ስለ አገር ጉዳይ፤ ስለ ፖለቲካ ድርጅቶች ሆነ ተቋማት ወቀሳ ሲያቀርቡ ፕሮፌሰር መራራ ጉዲና።

መጀመሪያ ለዚህ ምስቅልቅሉ ለወጣ ቢሮ መድህኑ ይሁኑ። ለማስተማር እራሱ መከራ ነው። ተማሪዎች ከዚህ በአናቱ በተዘቀዘቀ የቢሮ አያያዝ ምን ይማራሉ? ትምህርት ቤቶች እኮ የኑሮ ፊደል ገበታዎችም ናቸው። የፖለቲካ ሳይንቲስት እኮ ናቸው ፕሮፌሰር መራራ ጉዲና። የአገሪቱን የፖለቲካ ሁኔታ የሚመሩ ፍሬዎችን የሚያፈሩ የዕውቀት አባት። ግን በዚህ ዝክንትል የቢሮ አደረጃጃት ትውልድ ተኮትኩቶ ሲያድግ፤ ሲበቅል፤ ሲያሰብል? እም። ህም። ኦ አምላኬ!

 ፖለቲካ እኮ መጀመሪያ እራስን ማደራጀት ነው። ህሊናን ማደራጀት ነው፤ ሃሳብን ማደራጀት፤ ፍላጎትን ማደራጀት ነው። ራዕይን ማደራጀት ነው፤ ከዛ ህዝብን በሰከነ አዕምሮ እና የተደራጅ ህይወት እራስም እዬኖሩ ህዝብን ማስተዳደር ነው። እራሱን ማደራጀት ያልቻለ ነፍስ እንዴት ፍላጎትን፤ እንደምንስ ራዕይን እና በምን ችሎትስ ህዝብን ሊያደራጅ፣ ሊያስተዳደርና ሊመራስ ይችላል?

ኢትዮጵያ አገራችን ያልተሸከመችው የመከራ ዓይነት የለም። ለሰከንድ ከዚህ ቢሮ እንዴት ሃሳብ መፍለቅ ይችላል? ይቻላል ወይ?!  ለሰከንድ የሰው ልጅ ከዚህ ቢሮ ህሊናው ተረጋግቶ ሊቀመጥ ይችላል ወይ? ለሰከንድ ከዚህ ቢሮ እንዴት አገራዊ ኃላፊነት ሊደራጅ ይችላል? ቢሮው እራሱ ሰላማዊ ሰልፍ ላይ ነው። ፈርዶበት።

ይጨንቃል በውነት ይጨንቃል? ሥመ -ገናና የአገር መሪ ለአህጉርም የሚታጭ ግን መሬት ላይ በምታዩት ሁኔታ ነው አቅሙ። ይህን ቢሮ አይቶ መዳኜት ይቻላል የፕሮፌስር መራራ ጉዲናን አገር የመመራት አቅም። መቼስ ሜዳ ላይ ህዝብ አይመራ። ሜዳ ላይ ህዝብ አይስተዳደር። በነገራችን ላይ የአንድን ተቋም የውስጥ አካል ብቃት የቲም ወርክ ልዕልና ለመለካት ቢሮም የሂሳብ አያያዙ ወሳኝ ነው።

ይህን ቢሮ ሳይ እኔ ምን ትዝ እንዳለኝ ታውቃለችሁ? ልጅ እያለን ባል እና ሚስት ብለን ድንጋይ ደርድርን በምንሰራው የዕቃ ዕቃ መጫወቻ ጊዜያዊ ቤት ስንጣላ የቅጠል እንጀራውን፤ የዋንዛ ጠላውን፤ ያነጣጠፍናቸውን ሻርፖች ሁሉ ፍልስልስ አድርገን „ጨዋታው ፈረሰ ዳቦው ተቆረሰ“ የምንለው ዓይነት ነገር ነው በምልሰት የመጣብኝ። ከዚህ ቢሮ አገር መምራት ሊተሰብ?! ምጥ በዳጥ ነው።

ይህ ቢሮ መሆን ቀርቶ የተቃጠሉ ወረቆቶች ማጠራቀሚያ መጋዘን ለመሆን እንኳን አቅም የለውም። የሚቃጠሉ፤ ጥቅም የማይሰጡ ወረቀቶች እራሱ በፈረጅ ፈርጁ፤ በመልክ መልኩ ተደራጅተው ነውና የሚሰናዱት። ተጠርዘው በወጉ።

እንዴት አድርገውም የሚፈልጉትን ወረቀት ማውጣት እንደሚችሉ ፈጣሪ ይወቀው? እንዴት መለዬት ይቻላል? ስንት ሰዓትስ ይፈጅባቸው ይሆን አንድ ሌጣ ጹሑፍ ለማውጣት? አግራፍም አያውቀውም ወረቀቱ ሁሉ። በዚህ ውስጥ ኢትዮጵያ?! ማህከነ!

·       የህግ ጥሰት እና ፕሮፌሰርነት።

ሌላው ከፕሮፌሰር መራራ ጉዲና ያዬሁት የመሪነት አቀበት ጉዳይ ለህግ ያላቸው ክብር እና ተገዢነት ቁልቁልት መሆኑን ነው። ያዬሁት አሳዛኙ ነገር ኢትዮጵያ ሁለት ጊዜ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጃ ነበር። ሁለቱንም የጣሱ ሪከርድ ሰባሪ ናቸው። ዛሬ ላይ ደግሞ ስታዳምጡ ህገ መንግሥቱ አይነካብን ባዩ የሳቸው ድርጅት ነው። የት እና መቼ ያከበሩትን ህገ መንግሥት?!

አንዲት ነገር ከዚህ ላይ ላንሳ በዛን ጊዜ ፕሮፌሰር አለነበሩም ልትሉ ትችላላችሁ።  ለእኔ ግን ነበሩ። እንዲህ ህጋዊ ዕውቅና ሳይሰጠው እኔ ፕሮፌሰር መራራ ጉዲና እያልኩ እጽፍ ነበር። የተገፉ ብዬ አስብ ስለነበር።

ወደ ቀደመው ነገር ስንመጣ በዚህም ስሌት ስንሄድ ምንም ይሁን ምንም በሰላማዊ መንገድ ህጉን አክብሬ እታገላለሁ ያለ ድርጅት ህግ ማክበር የመጀመሪያ ተግባሩ ሊሆን ይገባል። ህግ የማያከብር የፖለቲካ ድርጅት መሪ እንዴት ህግን ጠብቆ ህዝብ ሊመራ ይችላል ስትሉም ወና ነው። 

ህግ ጣሽ ህግ አስከባሪ መሆን አይቻለውም እና። ከህግ በላይ የሆነ ሰብዕናም የፖለቲካ ድርጅት መሪነትም ጋዳ ነው። የፖለቲካ ድርጅትም በህግ ሥር ነው የሚደራጀውም የሚመራውም።  

ህግ ጥሰት እኮ እራሱ መታበይ ነው። አይደለም ወይ? ይህም ብቻ አይደለም ትውልዱ ከእንዲህ ዓይነት ህግ ጣሽ የፖለቲካ መሪ የጥሰት ሞዴሎች ምን ይማራል? ጥሰት፤ ህግ ወጥነት፤ እንደምታዩት አሁን በእነሱ ዘመን አናርኪዝምን ወለደ። ይህም አይቆጫቸውም። እንዲያውም ተባባሪ ሆነው ማሰፈራሪያ አድርገውታል።

አሳዛኙ ነገር በኦፌኮ ምክትል በአቶ በቀለ ገርባ ላይም ድርጅታቸው ኦፌኮን፤ የወሰደው ምንም ዓይነት እርምጃ የለም። ኢ - ሰብዕዊው፤ ኢ - ተፈጥሯዊው የአቶ በቀለ ገርባ ማንፌስቶ ነው አሁን አገር እያመሰ የሚገኜው። ዘፍጥረትን በመታበይ የደረመሰው የባቢሎን ግንብ አናጢው አቶ በቀለ ገርባ ለኢትዮጵያ ክፉ፤ ጥቁር፤ ጠንቅ የሆነ ማንፌስቶ አርቅቀው አውጀው ሥራ ላይም እዬዋለ ነው።

ባሌ ሮቤ ላይ በዋለው ህዝባዊ ስብሰባ ላይ በይፋ በአደባባይ ህዝብ ተሰብስቦ በጋሞ እና በአማራ ህዝብ ላይ የበቀለ ጭራቃዊ ማንፌስቶ ተግባር ላይ እንዲውል ውል ተዋውሏል። ፕሮፌሰር መራራ ጉዲና ባልደረባቸውን ከኃላፊነት እስከዚህ ቀን ድረስ አላገዱም፤ አልገሰጹም፤ አላስተባበሉም። አላወገዙም። ማህበር ጠንቅነት በስምምነት።

በነገራችን ላይ ስለ አቶ በቀለ ገርባ ከተነሳ እሳቸውም በህግ ጣሽነት የወጣላቸው ናቸው። ፍርድ ቤት ላይ ላዳኞች እልነሳም ብለው ነበር፤ ዛሬ እንዲህ ከህውሃት ጋር ፍቅር በፍቅር ክንፍ ሊሉ፤ ይህም ብቻ አይደለም የነቀምት መከራ እንዲህ እንዲቀጥል ሁለተኛው አሰቸኳይ ጊዜ አዋጅን ጥሰው ከፕሮፌሰር መራራ ጉዲና ጋር የተገኙ ሁለተኛ ሰውም እሳቸው ነበሩ። መታበዩ ጨንቋቸው ነው እንጂ መሬትን ባይረግጧት ይወዳሉ።

የመሰከረሙ 5ቱን የኦነግ የአደባባይ ስብሰባ እና ንንግር ማዳመጥ ነው በምልሰት። ከዚህ አንጻር በመታበይ ላቅ ያለውን ድርሻ ከኦሮሞ ሊሂቃን አቶ በቀለ ገርባ ይወስዳሉ ባይ ነኝ። ባዬሁት እና ባስተዋልኩት።

ዕውነት ለመናገር በአቶ ለማ መገርሳ መታበይ አይቻባቸው አላውቅም። ስክነታቸውም ከፕሮፌስር መራራ ጉዲና ጋር በተመሳሳይ ማዬት ይቻላል ዝግ ያሉ ናቸው አቶ ለማ መገርሳ።

·       የመራራ መራር ማንፌስቶ።


Ethiopia - ESAT Wekitawi - / መረራ ጉዲና "አዲስ አበባን እየሩሳሌም ባያደርጉ ጥሩ ነው" December 18, 2019

የፕሮፌሰር መራራ ጉዲና ድርጅት ኦፌኮን ከአምስቱ የኦሮሞ የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር በመሆን  አዲስ አባባን በሚመለከት ባወጣው ጨካኝ ኢሰብዕዊ የስጋት ማምረቻ መግለጫ ድርጅታቸው አለበት።

አንግዲህ ከዛች ቅጽበት ጀምሮ አዲስ አበባ በምን አይነት ግዞት ውስጥ እንዳለች ኗሪው ያውቀዋል። እኔ እዚህ ላሉ ነጭ ጓደኞቼ ስነግራቸው አፓርታይድ ይሉታል። ዕውነትም ነው አፓርታይድ። በኦሮሞ ክልል ስለሚኖሩት የአማራ ልጆች ቁጥር ብዛት እና አንድም የፖለቲካ ውክልና አለመኖር ሳጫውታቸው ድርብ አፓርታይድ ይሉታል። 

ይህም ላይበቃ ሰሞኑን በሰጡት መግለጫ አዲስ አበባን ከ አውሮፓ አገሮች፤ ከእስራኤል ጋር አያይዘው ያቀረቡበት መርዛዊ ቀፋፊ ትንተና እኒህ ሰው የኢትዮጵያ ጠላትነታቸውን አስረገጠው ነገረውናል።

አዲስ አበባ የኮዝሞ ፖለቲክ ከተማ ናት። 4ኛ የዓለም ከተማ ናት። አንደኛ የአፍሪካ ልዕለ ከተማ ናት። አዲስ አበባ የሁሉም መናህሪያ ከተማ ናት። በሳቸው ትንተና ደግሞ ማስፈራሪያ አዋጁን ይጀነጅኑታል። አያስፈራሩን።

የሚገርመው „አብረን ከቀጠልንም“ ይላሉ። ፕላን ኤ እና ፕላን ቢ አሰናድተው ነው እዬተጓዙ ያሉት። በሌላ በኩል ለአዲስ አባባ ከንቲባነትም ተጨማሪ ቋንቋ መቻል አለበት ሲሉ ተደምጠዋል።

ይህን መርዝ እሳቤ፤ ይህን ነቀርሳዊ እሳቤ ይዘው ነው እኛ አጤ አድርገን ከብክበን ነፍሳቸውን በፖለቲካ ዕውቅና ልዕልና ያቆዬናቸው። የሚገርመው አዲስ አበባ  የዕልቂት መናህሪያ እንድትሆንም ምኞታቸውን አሳይተውናል። አዲስ እሳት እንዲነድ ይሻሉ። እንዴት ነቀዝ እንደምንስ አረንዛ እንደሆኑ እራሳቸውን ገልጠው አሳይተውናል።

ቅንነት መልካም በመሆኑ ባይቆረቁርም ከእንግዲህ አቅምን ባለማባከን ጠንቃቃ እንሆን ዘንድ ተቋም ተከፍቶልናል። ከእስር ሲፈቱ ያን ያህል ክብር እና ሞገስ በውጭ አገር ማህበረሰቡ የተቸራቸው ከሜዳ የታፈሰ አይምሰላቸው። የአማራ ልጆች በሰራነው ተከታታይ የሎቢ ተግባር ነበር። ምንም እንኳን አማራ እጁ አመድ አፋሽም ቢሆንም።

ለነገሩ „ለማ ፊቱ ኦሮሞ“ ይመስላል ሲሉ ሰው ባሊህ አላለውም ነበር። እኔ ግን ለቀንበጥ ብሎግ ታዳሚዎቼ መርዛዊ ዕሳቤ መሆኑን ጽፌበት ነበር። ለማ ለእኔ ያለው የሰው ፊት ነው። በቃ። የሆነ ሆኖ ወጣቶቹ የታሪክም፤ የትውፊትም አብሮነት የለንም፤ አልነበረንም ቢሉ ስለምን ይፈረድባቸዋል? ከማን ይማሩት እነዚህ መከረኞች የቁቤ ትውልድ ቤተኞች።

ገራሚው ነገር ኢትዮጵያ ያለው እሳቸው የወጡበት ማህበረሰብ የታሪክ የትውፊት ምንም ግንኙነት የለንም እያሉ ተረበኛው ጠቅላይ ሚኒስተር መቼም የተመቻቸው ናቸው ልጆቻቸውን ሳይገሩ „ የጋራ ታሪካዊ ምዕራፍ እናክብር“ በሚል መሪ ቃል ከ ኤርትራ ጋር የጋብቻ ታህድሶ እዬከወኑ ነው። ቤት ሳይጸዳ ጓሮ። ያደክማል የኦሮሙማ ድንገቴ ዝንፍ ፖለቲካ።

ወደ ቀደመው ምልሰት ሳደርግ አሁን ያስደመጡን የፕሮፌስር መራራ ጉዲና ይሁን የኦሮሞ ፖለቲከኞች የባጁብን የመስቃ እና የመከራ በረድ የዚህ ሁሉ ጥጋብ መነሻው ሆነ መድረሻው የመጋቢት 18 ቀን 2010 ብአዴን የሸለማቸው ኃላፊነት የጎደለው እርምጃ እንዲህ መታበይን አንገሰላቸው።

ያ ቀን በውነቱ ኢትዮጵያ ፍዳን ተንበርክካ ትዝቅ ዘንድ ድምጽ የተሰጠበት ቀን ነበር። ቢያንስ ተጠያቂነት እና ኃላፊነት በሌለው ሁኔታ ያለ ምንም ቅደመ ሁኔታ ብአዴን ባሸከማቸው የጠቅልሌ ሎተሪ እንዲህ ይዘባነናሉ።

ዛሬ ምን አለባቸው ያለ አንዳች ከልካይ ደህንነቱን፤ የፖሊስ ኃይሉን፤ የቤተ -መንግሥት ጋርዱን፤ አዬር ሃይሉን፤ አዬር መንገዱን፤ ባንክና ኢንሹራንሱን፤ የገቢዎች ሚኒስተርን፤ የጉሙሩክ ባለስልጣንን፤ መከላከያን የተቆጣጠረው የኦነግ መንፈስ የልብ ልብ ሰጥቶ እንዲህ እንዲፏልሉ አድርጓቸዋል።

በዚህ በሰሞኑ አጫራሽ የመራራ መራር ማንፌስቶ ላይ ልባሙ ርዕዮት ሚዲያ ውስጤ ባሰበው መልኩ ሞግቶታል። በጥሞና ትከታተሉት ዘንድ እጋብዛችሁ አለሁኝ። በዝርዝር ያልሄድኩበትም ለዚኽው ነው።  

መረራ ጉዲና ሳያድግ ያረጀ ፖለቲካ አራማጅ12/23/2019
Dec 23, 2019

መግለጫውም ብዙ ስንክሳር አለበት። እሱንም ትታደሙበት ዘንድ ተጋብዛችኃል። ለዛው ምጥጥ ያለ አኞ ነገር ነው።  

ማደማጡ የተገባ ነው። ምክንያቱም ፌስ ቡክ ላይ የሳቸው አንደበት የሆኖ አቅለሽላሾች ያላሉትን አሉ እያሉ ዲሪቶ ሲደርቱ ውለው ስለሚያድሩ መመከቻ ይሆናችሁ ዘንድ ማዳመጡ መልካም ነው። 

ባለፈው ሰሞንም እኔ በሳቸው ዙሪያ እንዲሁ አንድ አጭር ጹሑፍ ለፌስ ቡክ ታዳሚዬዎቼ አካፍዬ ነበር። በቅኔ የተለወሰ መርዝ አራማጅ ናቸው ብዬ።

የሚገርመው አሁን በሦስት ዕድል ነው እዬተንቀሳቀሱ ያሉት „በጋዲሳ ኦሮሞ“ „በኦፌኮ“ በመድረክ“ የሚገርመው ብጥብጥ ጠማኝ መሆነቸው እጅግ የሚያሳዝነው አዲሱ ሰብዕናቸው ነው።

እርግጥ ነው ሁለቱንም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሲጥሱ ጫና ለመፍጠር ሆን ብለው ያደረጉት ቢሆንም አሁን ግን ከጉለሌው ኦነግ ያለነሰ የከተማ ውስጥ ጦርነት ናፋቂነታቸውን አውጀዋል። ትምክህታቸውም ጣሪያ ነክቷል። በህገ ወጡ ቡድን ትክሻ መታመን አብቅለዋል። ማን ጌታ አለባቸው ለቁንጩው ቤተ መንግሥትም ማስፈራሪያው ይኸው የሽፍታ ቡድን ነው። 

·       የትውልድ የመሆን ብላሽነት። ተተኪ የማያፈራ መሃን ድርጅት ኦፌኮ።

የፕሮፌሰሩ ድርጅት የፖለቲካ ባህሉ የትውልድ የመሆን አቅሙም ንቅዝት አለበት። እስካሁን አንዲት አንስት የፖለቲካ ሊሂቅ የማፍራት አቅም የለውም። ዜሮ! እስከ አሁን እሳቸውን የሚተካ አንድም ወጣት ተተኪ አላፈራም። ዜሮ! 

ሲኦሉ አቶ በቀለ ገርባ ቢሆኑ ከሌላ ድርጅት የመጡ ወዶ ገብ እንጂ በተስተካከለ የፖለቲካ አቅም እንደ አንድ ፖለቲካ ሳይንስ መምህርነታቸው አዲስ ቡቃያ በማፍረት እረገድ መሃን ናቸው።

ከዚህ አንጻር ለትወልዱ የመተካካት መስመርም ሲታሰቡ ፕሮፌስር መራራ ጉዲና አቅማቸው ምድር በዳ ነው። አንድ ሙሁር ከ23 ዓመት ላለነሰ ቆይቶ አንድ እሱን የሚተካ አቅም ለመፍጠር አለመቻል አለመታደልም ብቻ ሳይሆን እርግማንም ነው።

ለዚህ ነው በአብን አመራር ቅናት ውስጥ ሆነው የአብን አመራር ተለቅመው ይታሰሩ ዘንድ ነገር ሲያቀበሉ የባጁት። „አብን ይመከር“ ሲሉ ተደምጠዋል። አቶ ጃዋርን መሃመድን የመሰለ የአገር መከራ እያንቆለባበሱ። ዘረ ኦነጎችም ምን ያህል ትርምስ እንደሚፈጠሩ ያውቃሉ። የራሳቸው አካል አቶ በቀለ ገርባ ምን ያህል አረመኔዊ ማንፌሰቶ እንዳወጡም ያውቃሉ።

የሚገርመው አማራ ክልል ተገኝተው ገላጭ ነበሩ ፕሮፌስር መራራ ጉዲና ከአቶ ክርስትያን ታደለ ጋር ነበር። አቶ ክርስትያን ታደለን እንዲሰልሉ ነው የተላኩት። መቼም በእሱ ሙሉ አቅም የማይቀና ሰው ፈልጎ ለማግኜት ይቸግራል።
  
ወጣቱን ሳተና አጠኑት አቀበሉት ለመሰሉ ማህበረ ደራጎን። ስለምን? እሳቸውማ አንድ የሚታይ፤ አፍ ሞልቶ የሚያናግር፤ የሚደመጥ በተግባሩም በአንደበተ ርዕቱነቱም የሚታይ ወጣት የማፍራት አቅም ከዬት ይምጣ? ያልፈጠረባቸውን።

ይህ ከኦህዴድ በስተቀር ሁሉም ኦነጋውያን የሚጋሩት አረም መንገድ ነው። ኦህዴድ አረረም መረረም ወጣቶችን ለመተካት ጥረት አድርጓል። አንደበታቸውም ምግባራቸውም እሾኽ መሆኑ ደግሞ ከቀደምቶቹ የፖለቲካ አዛውንቶች የተማሩት ይህን ስለሆነ አይፈረድባቸውም። ከዬትኛው ባለ ሞራል እንዚህ ወጣቶች ይማሩ?

የሚገርመው ወጣቱ ምን ዓይነት ተስፋ እንደሚያደርግባቸው እራሱ ይገርመኛል። እነሱ መቃብር ቤትም ሆነው ቦታውን አንለቅም ባዮች ናቸው። ወጣቱ በዕድሜው እራሱ እዬተጫዋተ ነው የሚገኜው። ለዚህም ነው የኦሮሞ ፖለቲካ 50ዎቹን አስቆጥሮ የቅንድብ ጸጉር ሆኖ የቀረው።  ውሃ ቅዳ ውሃ መልስ ሲያስመልስ። ውሃ ቅዳ ውሃ መልስ ዝርክርክን ሲቀድስ። የነፍስ ማረፊያ ነው የጠፋው።  

·       ኢትዮጵያዊው ዛሬ አሳር አዬ።

ኢትዮጵያዊው ዛሬ መከራ ላይ ነው። ኢትዮጵያዊው ዛሬ አሳሩን እዬበላ ነው። ኢትዮጵያዊው ዛሬ ፍዳውን እያዬ ነው። በዛሬ ውስጥ ነገ አለ። ነገም አሳሩን እያዬ ነው። ነገም ፍዳውን እየበላ ነው። ውርሱ ቅርሱ አሳር እና ፍዳ ሆነ። በነገም ውስጥ ትውልድ አለ።
የዛሬ 20/30 ዓመት ትወልዱን ስታስቡት ተስፋ ይርቃችኋል። 

ስለምን? ኢትዮጵያዊው ዛሬ በጠና ታሟል፤ አልጋ ላይም ውሏል እና። እሚደመጥ የኦሮሙማ ሊሂቅ ነው የጠፋው።

አሁን እራስ እግሩ እንሱው ናቸው። ሹፌሮችም፤ ካፒቴኖችም፤ ባለመርከቦችም እነሱው ናቸው። እነሱ ደግሞ እንደምታዩት የፖለቲካ ድቀት ውስጥ ናቸው። ድቀቱ ተሻጋሪ ሲሆን ደግሞ ነገ ከመምጣቱ በፊት ክው ብሎ ደርቆ ይታያችኋል። በዚህ ውስጥ የትውልዱ ብክነት ቀጣይነት ሲታሰብ ያቅታል ያቃቅታልም።

ቢገነጠሉ ሩብ ዓመት አብረው አይቆዩም። እርስ በእርሳቸው ተገዳድለው ዓለም በተውኔቱ ታዳሚ ትባል በነበረ እንደ ፈረደባት። አሁን እንደሆን ማስትሽ የሆነ ቅዱስ መንፈስ ስላለ ነው፤ እንዲህ የሚዘማነኑትም። ያም ገናናው ኢትዮጵያዊነት።   

ስማሚያ ለአብነት ሃድራ።

  
·         ቅኔቹ ዬፌስ ቡክ ልቦቼ ብለጌን ትከታተሉ ዘንድ ሊንኩ ይህ ነው። ወደ ብሎጌ ጎራ ስትሉ ብርቱካናማ ቦክስ ዲያሎግ ይመጣል፤ ያን ስትጫኑት በሩ ይከፈታል። ሊንኩ ይሄው ነው። ዘለግ ያለ ሙግት ሲኖረኝ በብሎጌ ከች እላለሁኝ።

·         ብሎጌ ህሊናዎች ደግሞ በዚህ የመግቢያ በር ካለምንም የእልፍኝ አስከልካይ መግባት ይቻላል። አጫጭር ጹሑፎች ሲኖሩኝ ፌስ ቡክ ላይ አዘውትራለሁኝ። ፌስ ቡክ እድሜውን ያርዝመው እንጂ ለአጭር ትጥቅ ልዩ ስጦታ ምቹ ማሳ ነው። ካለዘጉት እውነት ፈሪው ጠሚር አብይ አህመድ። ቢያዘጉትም በሌሎች ብቅ ይባላል። ዛሬ አለም ብዙ አማራጭ አላት።

·         በድምጥ ሲያሰኜን ደግሞ ይኸው እና ቁጥር አንድ ዩቱብ ቻናሌ  በአገርኛ በአውራው ሉላዊ ቋንቋ በእጬጌ አማርኛ።


·         ስለ ፍቅራዊነት ብናውቅስ ለምትሉ ቅኔዎቼ ደግሞ ይኸውና ቁጥር ሁለት ዩቱቤ።


ትእግስት ሲያልቅ ፍቅር ይሰደዳል።
ፍቅርም ሲያልቅ ትዕግስት ይሰደዳል።

የኔዎቹ ኑሩልኝ። መሸቢያ ጊዜ።

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።