እንኳን ወደ ከበቡሽ ሚዲያ በሰላም መጡልኝ።

 


ለዘመን ለትውልድ ጥላቻን ጥላቻ አያክመውም።

 

ዕለተ ሮብ ዕለተ ተናኜ

በከበቡሽ የቁራሽ እንጀራ ብራና

በሰብለ ህይወት አዝመራ

በቢሆነኝ ብራ

ለራህብ የሚራራ።

 እግዚአብሄርም ለሰሎሞን እጅግ ብዙ ጥበብ እና ማስተዋል በባህር ዳር እንዳለ አሽዋ የልብ ስፋት ሰጠው።

                                                                           (መጸሐፍ ነገሥት ቀዳማዊ ምዕራፍ 4 ቁጥር ፳፱)

         

·        ሃዘን ለሌላ ሃዘን በመገባበዝ እርካታ አያስገኝም።

·        ጥላቻን ጥላቻን ሊያክመው በፍጹም አይችልም።

·        በጥላቻ ውስጥ መዳን የለም።

·        በጥላቻ ውስጥ ምህረት የለም።

·        በጥላቻ ውስጥ ሥርዬት የለም።

·        በጥላቻ ውስጥ መድህን የለም።

·        በጥላቻ ውስጥ ማግሥት የለም።

·        በጥላቻ ውስጥ አገራዊነት አይኖርም።

 

·        በጥላቻ ውስጥ ተስፋ አይገኝም።

·         በጥላቻ ውስጥ ተፈጥሮ የለም።

·         በጥላቻ ውስጥ ዕምነት የለም።

·        በጥላቻ ውስጥ ሃይማኖት የለም።

·        በጥላቻ ውስጥ ሰብዕዊነት የለም።

 

·        በጥላቻ ውስጥ ማግሥት የለም።

·        በጥላቻ ውስጥ ዘመን የለም።

·        በጥላቻ ውስጥ ትውልድ የለም።


·        በጥላቻ ውስጥ ያለው ቂም ነው።

·        ቂም ደግሞ በቀልን የወልዳል።

·        በቀል አጥፊ እንጂ አትራፊ አይደለም።

·        የበቀል መንገድ ነገን ያቃጥላል።

·        ከሞት የሚገኘው አመድ ብቻ ነው።

 

·        ጥላቻ ሆነ በቀል ትንፋሹ የጸላዬ ሰናይ ነው። ከፈጣሪ ጋርም ያጠላል። አበሶ እኛን የሰጠን ፈጣሪያችን ያዝናል። ይረግመናልም።


·        ቅድስት ድንግል ማርያም እንደ እናትነቷ አብዝታ ታዝናለች።

 

·        ጥላቻን የሚያድነው ሀኪሙ፤ ዶክተሩ ፍቅራዊነት ነው።

 

·        ፍቅርን የሥነ - ልቦና ተግባር እንጂ የዓዋጅ አይደለም። ለዚህም ዘግይቷል። ግን አብዝተን ማተኮር እና በዚህ ዙሪያ መስራት አለብን።

 

አሁንም ቢሆን ከግብታዊነት ወደ መረጋጋት፤ ከስሜታዊነት ወደ መስከን ሊመልሰን የሚችለው ጸሎት ብቻ ነው። እነሱ አውሬ ይሁኑ፤ ጨካኝ ይሁኑ፤ ሌላው ይህን የአውሬነት እና የጭካኔ መንፈስ እንደ መልካም ነገር መጋራት አይኖርበትም። ለጭካኔም መፎካከር አያስፈልገውም። ለክህደትም እንዲሁ።

 

በጥላቻ በሰከሩ ሉባወች የሚመራ ህዝብ አጥፊዎችን አይተባበር። ቢያንስ እግዚአብሄርን አላህን መፍራት አለበት። ትእግስትን፤ በልክ መኖርን፤ ፈርኃ እግዚአብሄርን ፈርኃ አላህን ያስተምረውን ለሳተ መንፈስ ሁሉ ከፈጣሪ ቅጣት ይታዘዝበታል።

 

በዛ አረመኔያዊነት ክርፋት በነገሰበት ቦታ ላይ ህፃናት እና ነፍሰጡሮችም ይኖራሉ። በተጨማሪም ጨዋዎችም ይኖራሉ። ኢትዮጵያዊነት በዚህ ውስጥ ነው መታዬት ያለበት። ማስተዋል አብዝቶ ይጠይቃል። ድውዮች ጥበብ የላቸውም። የህሊና ዕውራን ናቸው።

 

ስለሆነም  የእነሱን ድንብርብር እንደ መውጫ መንገድ፤ እንደ መካሻ ማዬት አይገባም። ህግን ተላልፎ በወል መፈረጀም አይገባም። እያንዳንዱ ሰብዕና የ እኔ የሚለው የራሱ ጸጋ አለው። በጸጋው ልክ ነው መመዘን ያለበት።፡

 

ይህን የፈተና ጊዜ ማለፍ የሚቻለው አብዝቶ በመታገስ እንጂ የጭካኔ ብድር በመመላለስ አይደለም። በጥፋት ላይ ዝብሪት ፈጽሞ አስፈላጊ አይደለም። ሰከን ማለት ያስፈልጋል። ትንፋሽን መሰብሰብ ያስፈልጋል። በተደሞ ማስተዋልን ምራኝ ገስጸኝ ማለት ያስፈልጋል።

     

·                      ምን መደረግ አለበት?

 

እኔ ይህንን ኃላፊነት ሊወጣ የሚችለው የኃይማኖት አቨው ሊሆኑ ይገባል የሚል ዕሳቤ አለኝ። ለመሞት መፍቀድን ይጠይቃል። ሰማዕትነት። የማዬው ነገር ሁሉ እንኩሮ ብቻ ነው።

 

የተበተነ፤ የተበጣጠሰ፤ የጓጎለ ሁኔታ ነው እማዬው በማንኛውም ሁነት። የተደራጀ ሃሳብ እንኳን የለም። ከ ዕለተዊ ሰበሮች ያለፉ በሳል ክንውኖችን አላይም።

 

በዚህ ጤነኛ ሆኖ የታዩ በሌላው ሁኔታ ታሞ ታገኙታላችሁ። በዚህ የእኛ ስትሉት በሌላው ሁኔታ ተነጥሎ ወጥቶ ባዕድ ነኝ ይላችኋል።

 

የእኛ ስትሉት አይደለሁም ካለ ምንም ሙግት አያስፈልግም። የራስን አዲስ ጎዳና መጀመር ብቻ ነው። ሃሳብን አደራጅቶ ለመመከት አህዱን መወጠን። በድሪቶ ላይ ድሪቶ ግን ከአተላ ወደ አተላ፤ ከአንቡላ ወደ አንቡላ ነው የሚሆነው።

 

የጠራ ሃሳብ፤ የጠራ ጎዳና ያስፈልገናል። ያ ደግሞ በደነገለ መንፈስ እንጂ በውራጅ ቅርጥምጣሚ ለጠፋ ለጠፍ የሚሆን አይደለም። በትውስት ፖለቲካ 50 ዓመት ነደደ። እንሆ አመድ ታፈሰ። ትውልድም ታጨደ።

 

አቅምን ቆጥቦ መንቀሳቀስ ያስፈልጋል። አቅምን ለጠራ አቅም ብቻ መመገብ። አቅምን ኢትዮጵያን ቁምነገር ለማድረግ ለውጠነ ብቻ ነው መለገስ ያለበት።

 

ብክነት አያስፈልግም። በጭምትነት ራስን ገዝቶ መራመድ ይጠይቃል ዘመኑ። ዘመኑ ለግልብልብ የሚሆን አይደለም። ግርግር አገርን አይፈጥርም ማፍረስ ወይ መናድ እንጂ። ግርግር እንኳን አገርን የራስን ጎጆ ለማሸነፈ እንኳን አያስችልም። ፈጽሞ።

 

ጥድፊያ ላይ ያሉ ሰብዕናወች ለኢትዮጵያዊነት መክሊት ልክ አይደሉም። ስኩን መንፈሳችን በእርጉዎች ላይ ማስፈን ይገባናል። አቅማችንም ለ እነሱ ለመመገብ መቁረጥ ይገባል።

 

እራሳቸውን ከድነው የተቀመጡ ግጥማችን ሊሆኑ ይገባል። በዛ ሰብዕና ውስጥ ኢትዮጵያ ከእነ ዙፋኗ ከብራለች እና። ኢትዮጵያችን ርጉም እዩኝ እዩኝም የማትል ናት። 

 

እግዚአብሔር ይስጥልኝ።


ሥርጉተ©ሥላሴ

Sergute©Selsssie

 03.03.2021

 ከጭምቷ፡ ሲዊዘርላንድ።

 

 

ኢትዮጵያዊነት ከመፈጠሩ በፊት ፈተናን አሸንፎ የተፈጠረ ሚስጢር።

 

 

ቸሩን ያሰማን ፈጣሪያችን። አሜን። 

 

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።