ዬየኔታ ጎዳና ያዕቆብ የተራራው፤ ጥቃት አውጪ፤ መካች፤ ቆፍጣና ቅዱስ ስብከት።

 

 

እንኳን ወደ ከበቡሽ ብሎግ በሰላም መጡልኝ።

·      ዬየኔታ ጎዳና ያዕቆብ የተራራው

·       ጥቃት አውጪ፤ መካች፤ ቆፍጣና  ቅዱስ ስብከት።

 

የኔታ እንዲህ ይላሉ …

„… ቅዱስ ፓትርያርኩ እንደ አበረ አዳሙ በልብ ጡንቻ ምናምን ብለው የሆነ ነገር ቢደርስባቸው ከአብይ አህመድ አሊ እራስ አንወርድም! ትን ብሏቸው ቢሞቱ ከአብይ አህመድ አሊ እራስ አንወርድም! መብረቅ ከሰማይ ወርዶ ቢገድላቸው ከአብይ አህመድ እራስ አንወርድም!“

በከበቡሽ የቁራሽ እንጀራ ብራና

በቢሆነኝ የተብራራ ብራ

በሰብለ ህይወት አዝመራ

ለራህብ የሚራራ

„አድርገህልኛልና ለዘላለም አመስግናለሁ፤

በቅዱሳንህም ዘንድ መልካም ነውና

ሥምህን ተስፋ አደርጋለሁ።“

(መዝሙር 51 ቁጥር 9)




ምርኩዝ ….


https://www.youtube.com/watch?v=nbgVgBLF_2I&t=1176s

#Reyot #AbiyAhmed #ShimelisAbdisa

Reyot - ርዕዮት : ተሰልቅጦ መጥፋት . . . | የኢትዮጵያ ፖለቲካ በታላቁ ደራሲ እይታ። ክፍል 4 (የመጨረሻው ክፍል) 05/11/21

Streamed live on May 11, 2021

ለሁሉም አይነት የህልውና ተጋድሎ እንዲህ አይነት ቆፍጣና፤ የደነገል ደግሞም የጨመተ እንደገናም የቆረጠ፤ ዲስፕሊኑን ሊሸከም የሚችል ሙሴ ያስፈልገዋል። ምስባክ ነው። ለእኔ የተራራው ቅዱስ ስብከት ነው። ለዚህም ነው ለታሪክ ቃል በቃል የተረጎምኩት። እራሱ የህልውና ድንጋጌም ነው። እንዲዚህ ባለ በጠራ መስመር ብቻ ነው ትውልድም አገርም ሊድን የሚችለው። አዘውትሮ ጋዜጠኛ ቴወድሮስ ጸጋዬ የሚለው ነገር አለው። „ኢትዮጵያ በቀደመ ዕውነቷ ትደናለች። እኔ የኔታ ጎዳና ያዕቆብ እራሳቸው የቀደመ ዕውነት ሆነው ነው ያገኜኋቸው። በሁሉም ዘርፍ የተደራጀ ሃሳብ ነው ያላቸው። የተደራጀው ሃሳብ ደግሞ ገዢ ነው። ይመስጣል፤ ያስተምራል፤ ያደራጃል፤ ይመራል። ውሳኔ ናቸው የኔታ ጎዳና። አሳዳጊያቸውን ፈጣሪ ይባርክ ይቀድስ አሜን። ቤተሰባቸውንም ይጠብቅ አሜን። ያጽናናሉ። አይዟችሁ ይላሉ።

·       አመክንዮዊ ውይይቱ  

እኔ ቃል በቃል የጻፍኩት የ16 ደቂቃ 51 ሰከንድ የጋዜጠኛ ቴወድሮስ መጠይቅ ተጨምሮ የወሰደውን ብቻ ነው። 

ወደ መነሻ ሃሳቤ ስገሰግስ የኔታ ጎዳና ያዕቆብ ከርዮትሚዲያ ከጋዜጠኛ ቴወድሮስ ጸጋዬ ጋር ለ4ኛ ጊዜ ሲሉ ሰምቻለሁ „በእንሰሳት አብዮት“ የትርጉም ሥራ ጉዳይ ሲወያዩ ነበር ይህን ቅዱስ መንፈስ ያለው ስብከት ያዳመጥኩት። ሦስቱን አላዳመጥኩትም። የሆነ ሆኖ የኔታዋ ጭንቅ ላይ ስለሆነች ታሳዝነኛለች። ብጹዕና ወቅዱሳን አባቶቼ፤ አገልጋዮቿ፤ ንዋዬ ቅድሳቷ፤ ማህበረ ምዕምኗ፤ መቅደሳዊ ሥፍራዋ፤ ቅርስ እና ውርሷ ውስጤ ነው።

እዲህ ዓይነት ልጅ ሲኖራት ደግሞ እጽናናለሁኝ። ይህን ውሳኔ ቅዱስ ሲኖዶስ ደፍሮ የሚወስነው አይደለም። ለነገሩ አቶ ጎዳና ያዕቆብ ለሁሉም ሃይማኖት ያላቸው ክብር እና ልቅና ልዩ ነው። እኔ ሁሉንም ከውስጤ አድርጌ ሰለማዳምጥ፤ ስለምታዘብም እስካሁን ሁሉንም ሃይማኖት በክብራቸው ልክ ሲያከብሩ ነው የማስተውለው። ለዚህም ነው መደበኛ አድማጫቸው የሆንኩት። ሰው በሚለው ማዕቀፍ ሁሉም ነፃነት አለው። የወደደውን የማመን፤ ያለማመንም። ምንም ዓይነት ተጫኝ መንፈስ ሊኖር አይገባም ከሚሉት ወገን ነኝ እና። ነፃነት ክትር አያስፈልገውም። ኢ - አማንያን የሆኑትም ወገኖቼ ናቸው። ሰው ናቸው። ተፈጥሮ ናቸው።

ይህን ገለጻ ሳዳምጥ ሁለቱ የተፈጥሮ መስኮቶቼ ተከፍተው ፍሉን ካለፍቃዴ ነበር የለቀቁት። እኔ ወገኔ ሲገፋ፤ ሲገለል፤ ይከፋኛል። ብጹዑ ወቅዱስ አባታችን አቡነ ማትያስ እንደምን የጠቅላይ ሚኒስተር አብይ አህመድ ዓይን ሊያቸው እንደሚጸዬፍ ይገባኛል። ለዚህም ነው። ሁሉም ልብ ባላበት ወቅት ይህን ከበቡሽ ብሎጌ ላይ ይህን የጻፍኩት።

https://sergute.blogspot.com/2019/03/blog-post.html

እግዚኦ!

ስለምን ብፁዕ ወቅዱስ

አባታችን ይሳደዳሉ?

ማርች 4፣ ሰኞ 2019

 

ከብጹዑ አባቴ ከሳቸው ጎን በመቆም እኔ የመጀመሪያዋ ነበርኩኝ። እኔ ከደላቸው አልገኝም። እኔ እምገኜው ከተከፉት፤ ከተገፉት ነው። መከረኞች ናቸው ግጥሞቼ። ወደ ዛም ነው በድፍረት እምገሰግሰው። የማቀርበው ሰው መድላቱን ካዬሁ እሸሸዋለሁኝ። ሃዘን፤ መከፋት ሲደርስበት ደግሞ እቀርበዋለሁ። ሲሸነፍ አብሬው እሆናለሁ። በመከራ ሠልጥኜበታለሁ እና።

በዚህ ቅዱስ አቋም ብጹዑ ወቅዱስ ፓርትርያክ አባ ማትያስ የእኔ ድንግል ማርያም ውጽፍተ ወርቅ ብረት መዝጊያ የሚሆን ልጅ፤ ጠበቃ እንደሰጣቸው አውቀው ሊጽናኑ፤ ለመንፈስ ልዩ ልጃቸው ለየኔታ ጎዳና ያዕቆብም ሊጸልዩላቸው ይገባል። እንዲህ ያለ ፍቱን የሆነ፤ የተፍተታ ልጅ ከላይኛው ብቻ ነው የሚገኜው።

„አንዳንድ ሰሞንኛ ጉዳይን አንዳድንድ ነጥቦችን እናንሳ ብጹዕነታቸውን አስመልክቶ በሚል … ጫሪ ሃሳብ ጋዜጠኛ ቴወድሮስ፤ የነታ ጎዳና ያዕቆብን ጠዬቀ …

·      


… የኔታ ጎዳና ደግሞ እንዲህ መለሱ …  

„በመጀመሪያ ደረጃ ማለት ዬምፈልገው ነገር ከብጹዑ ወቅዱስ ፓትሪያርካችን አባታችን ጎን 100 /በ100 ከጎናችን እንደምንቆም፤ ብቻውን እንዳይደሉ፤ ማንኛውንም ተለጣፊ ሥም ደግሞ ለቅዱስ ፓትርያርካችን ሊሰጡ ለፈለጉ አካላት ከ50 ሚሊዬን በላይ የሚሆነው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ተከታይ ከጎናቸው እንደሆነ፤ ጁንታ ቢሏቸው እኔም ጁንታ አድርገው ይቁጠሩኝ፤ አባታችንነት በዛ ደረጃ የሚያሰቀምጡ ከሆነ እኛ ሁሉንም የትኛውን ሥም ሊሰጡ የሚፈልጉትን ሁሉ እኛ አብረናቸው እንዳለን ያነን ሥም እንደምንጋራ አሰታማሪው፤ ተማሪው ከአስተማሪው አይበልጥም ይላል ቅዱሱ መጽሐፍ እና እኛ አባታችን የቅዱስ ፓትርያርኩ ልጆች ነን።“

·       ይቀጥላሉ የኔታ ጎዳና ያዕቆብ …

 „… ስለዚህ ብቻውን እንዳሉ፤ የተነጠሉ መስሏቸው ከሆነ ባትሞክሩት ጥሩ ነው። ባትሞክሩት ጥሩ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ዕውነተኛ ማጆረት ካለ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስትያን ነው። በዘመኗ አክባሪ ስለሆነች፤ ከነገሥታቱም መሸሽ ስለምትፈልግ ለብዙ ስደት ተዳርጋለች። የትኛውም ዓይነት ስደት ግን አጥፍቷት አያውቅም። በመሃመድ ግራኝ ጊዜ አልጠፋችም፤ በአብይ አህምድ ዘመንም አትጠፋም። ስደት ቤተ ክርስትያንን እንደ ወርቅ የሚያነጥር የሚጠነክር ነገር መሆኑን፤ አውቃችሁ ትላንት በትዕግስት ዝም ተብሎ ሲታለፍ የነበረውን ነገር፤ አሁን እኛን ገፍታችሁ ገፍታችሁ …. ተጠንቀቁ። የህልውና ጉዳይ ነው። ህልውና ደግሞ ሥነ - መንግሥትን የሚቀድም ተፈጥሯዊ የሆነ መብት ብቻ ሳይሆን ግዴታ ነው።“

·       ይቀጥላሉ የኔታ ጎዳና ያዕቆብ

 „ኦርቶዶክስ እንደ ተቋም፤ ቅዱስ ፓትርያርኩ ደግሞ እንደ ተቋሙ መሪ ሊከበሩ ይገባል። መንግሥት ከሳቸው ላይ እጁን-  አጁን -እጁን ሊያነሳ ይገባል። በውስጧ ሆነው ደግሞ እንደ ዳንኤል ክብረትም ይሁኑ ሌሎችም ይሁኑ በነገራችን ላይ የቤተክርስትያኗን ለስደት የሚዳርጉ ጠላቶች ከውስጥም ይሁኑ ከውጭ ልዩነት የለም። እንዲያውም ከውስጥ ባለው ይብሳል። እዚህ አገር ማንኛውም ቃለ ማሃል ሲገባ ህገ መንግሥት ፕሮቴክት የምናደርግበት በውስጥም ካለ በውጭም ካለ የሚሉትን በጣም የምወድላቸው ነው።ስለዚህ እጃችሁን አንሱ፤ እጃችሁን ሰብስቡ። በራሳችሁ ላይ ጦስ እንዳታመጡ። እኔ ለአብይ አህድ አገዛዝ እና ለጀሌወቹም የምለውም ነገር አይጥ ሞቷን ስትሻ ስታበዛ ሩጫ ሄዳ ታሸታለች የድመት አፍንጫ ነው። አሁን በአይናችን መጥተኃል፤ ስለዚህ እረፍ። እ … እረፍ እነ ዳንኤል ክብረትም ደግሞ ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያንን አጥፍቶ የሚገኝ ሥልጣን እና ምቾት እንደሌለ ቢያውቁ ይሻላል።“

·       ይቀጥላሉ የኔታ ጎዳና ያዕቆብ …

„… በምንም መልኩ የሚጠብቃቸው፤ የሚያድናቸው ምድራዊ ኃይል የለም። ኢትዮጵያ ደግሞ መፍረስ መጥፋት ዕጣ ፈንታዋ ከሆነ አሁን የሚሄዱበት መንገድ የሚያጠፋቸው ነው የሚሆነው። አገር የሚበትን ነው የሚሆነው። ስለዚህ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያንን በማክበር፤ የሃይማኖት ነፃነትን በማክብር፤ እንኳን ባይሆን አንባገነኑም ለግል ሥልጣኑም ሲል መላ የኢትዮጵያ ህዝብም አገር አልባ እንዳይሆን ከቅዱስ ፓትርያርኩ ላይ እጃቸውን ቢያነሱ፤ ከኦርቶዶክስ ተዋህዶ ላይ እጃቸውን ቢያነሱ ጥሩ ነው። ምክንያቱም እኔ አሁን እያደረጉት ያሉትን ነገር እንደ „ትሬት“ እንደ ችግር አላዬውም። የሚያስተባብረን፤ አንድ የሚያደርገን የሚያደራጀን ዕድል ነው እዬፈጠራችሁ ያላችሁት። እናንተ ቤት የዘነበ ብልግና እኛ ቤትም የሚጠፋ እንዳይመስላችሁ። ኃይል እና ጋጠ ወጥነት እኛም እንሞክረው ካልን አናጣውም፤ ስለዚህ ሥርዓት ባይሁራችሁ፤ ለጥቅማችሁ፤ ለሥልጣናችሁ ስትሉ ከቤተክርስትያን ላይ እጃችሁን አንሱ። ነው እምለው አንድ። 

·       ይቀጥላሉ የኔታ ጎዳና ያዕቆብ …

„ … ሁለት ደግሞ ቅዱስ ፓትርያርካችን የተናገሩት ነገር ሁሉ ዕውነት ነው። የተረጋገጥ ፋክት ነው። በትግራዋይ ላይ እዬተደረገ ያለው፤ በህግ ማስከበር ሰበብ እዬተደረገ ያለውን ነገር የጦር ወንጀል ነው። ስለዚህ ይህ ሁልጊዜ ጉዳችሁን ለመሸፋፍን ከመጮኽ ይልቅ ቤታችሁን ማጽዳት፤ እምታደርጉትን ነገር ማወቅ፤ ቢያንስ ቢያንስ አስተካክላችሁ ማስተዳደር እና መስራት ቢያቅታችሁ በቅጡ ማበላሸት ይጠበቅባችኋል።“

·       ይቀጥላሉ የኔታ ጎዳና ያዕቆብ …

 ስለ አማራ ጭፍጨፋ ስለ ትግራዋይ ጭፍጨፋ ሞት እራህብን እንደ መሳሪ አድርጎ መጠቀም ወሲባዊ ጥቃት፤ ሰው ዝም እንዲል ከፈለጋችሁ ጉዳዩን ከማድረግ ማቆም እና ማቆም ብቻ ነው፡ ወራሪ የውጭ ኃይል፤ የኤርትራ ሠራዊት፤ ከአገር ማስወጣት ነው የሚያዋጣው፤ ከዛ ውጪ ከተገኙበት ማህበረሰብ ብቻ አግልለን ቅዱስ ፓትርያርኩን እናጎሳቁላለን ለሚሉ ሁሉ ከሳቸው ጎን የቆምን እኛም ትግራዋይ፤ እኛም ጁንታ እንደሆን አውቃችሁ ተሰብሰቡ! በሳቸው እና በቤተክርስትያን ህልውና መጥቶ የምንቀበለው ሥም ሁሉ እንደ ትልቅ ክብር ነው እንጂ የምንቆጥረው የምንሸማቀቅበት፤ አንገት የመንደፋበት ነገር እንዳልሆነ ዕወቁ። ነብር አየን በሉ! ለራሳችሁ ስትሉ እላለሁ ቴዲ።“

„ሁለተኛ ግን አንድ ማለት አምፈልገውም ነገር አለ።“ ያው ሦስተኛ መሆኑ ነው …

·       ይቀጥላሉ የኔታ ጎዳና ያዕቆብ …

የሰባዕዊ መብት ኮሚሽን እ …. በኦሮሞያ ላይ እዬተደረገ ስላለው የሰብዕዊ መብት ጥሰት፤ ህፃናት፤ እናቶች፤ አባቶች የታሰሩበት፤ ሪፖርት ወጥቷል።  ይሄ አሁን በኦሮሞ ሥም የሚምለው የሚገዘተው የአብይ አስተዳደር መንግሥት በኦሮሞ ተወላጆች ላይ እያደረገ ያለው የሰባዕዊ መብት ጥሰት አስነዋሪ ብቻ ሳይሆን  ከእነሱ የምንጠብቀው ነው።  ለዚህም ነው ኦሮሙማ እና ኦሮሞነት አንድ አይደለም፤ ለፖለቲካ ግብ እና ለፖለቲካ ትርፍ ነው እንጂ የሚምሉት፤ እናቶችን ባሎቻቸውን አምጡ፤ ልጆቻችሁን አምጡ ተብለው ከመታሰር አላገዳቸውም። እምጫቶች ከአራስ ልጆቻቸው ጋር እስር ቤት ከመታጎር አላዳናቸውም። የ9 ዓመት ልጅ  ከእስር ቤት ከመታጎር አላዳነውም። በዬቦታው የሚጠፋው „የሰው ልጅ“ ሞት ብዛት፤ የሚገደለው ሰው ብዛት፤ የምናውቀው ነው። እንዲያውም መንግሥት ለኦሮሞ ህይወት ምን ያህል ግድ እንደ ሌለው የምታውቀው አብይ አህመድ ጃዋር ተከበብኩ ባለበት ጊዜ የሞቱት ሰወችን በፕርሰንት ሲያወጣ 57% ኦሮሞ ስለሆነ የተገደለው አይዟችሁ ሰላም ለእናንተ ይሆን ያለው አዝ ኢፍ የኦሮሞ ህይወት ህይወት እንዳልሆነ ሁሉ።  ኛ በስማችን የሚምል የሚገዘት ሳይሆን ኢትዮጵያን አንድ አድርጎ፤ አስማምቶ የህይወት ደህንነት የሚያስከብር መንግሥት ነው የሚያስፈልገን። እላለሁ ቴዲ አመሰግናለሁ።“

·       ቁርጥ ያለውን ውሳኔ ይቀጥላሉ የኔታ ጎዳና ያዕቆብ …  

„ይቅርታ ቴዲ አንድ ጊዜ አንድ ደቂቃ ትጨምርልኝ“  … ቅዱስ ፓትርያርኩ እንደ አበረ አዳሙ በልብ ጡንቻ ምናምን ብለው የሆነ ነገር ቢደርስባቸው ከአብይ አህመድ አሊ እራስ አንወርድም!!! ትን ብሏቸው ቢሞቱ ከአብይ አህመድ አሊ እራስ አንወርድም!!!! መብረቅ ከሰማይ ወርዶ ቢገድላቸው ከአብይ አህመድ አሊ እራስ አንወርድም!!!!  በህይወታቸው ለሚመጣ ማንኛውም አደጋ፤ በደህንነታቸው፤ በክብራቸው ለሚመጣ ማንኛውም አደጋ የ ብይ አህመድ አስተዳደር እና አብይ አህመድ በግል ተጠያቂ እንደሚሆን ከአሁኑ ሊያውቁት ይገባል። እላለሁ አመሰግናለሁ።“

ይቅርታ የምጠይቀው የቃል በቃል ጹሑፍ ላይ እንግሊዘኛው አልተደመጠኝም፤ በጎን ትርጉሙን የሰጡበትን ጽፌ ሌልኛውን በጥቅስ ውስጥ አስገብቻለሁኝ።

·       መከወኛ።

ብጹዑ ወቅዱስ አባታችን የቃለ አዋዲን በተለያዬ ትርጉም መተርጎሙን አስምልክቶ አንድ ዝግጅት ላይ ተገኝተው አያቻቸዋለሁኝ። በቀደመው ክብራቸው፤ በቀደመው ለዛውቸው፤ በቀደመው ሞገሳቸው ሆነው ስላዬኋቸው ሐሤት አግኝቻለሁኝ። እንዲያውም አባ ማስክ ለብሰው አይቼ አላውቅም ነበር። ማስክ ሁሉ ለብሰው አይቻለሁኝ።

የሳቸው የማያርሱኝ ቀናት የውጩ ሲኖደስ ሲጋባ ያሳዩት ፍቅር፤ ክብር፤ ቅንነት፤ ደግነት፤ ፈቃደኝነት፤ ቸርነት፤ ቅድስና፤ አረሳውም። ፈጽሞ። የልጆቻቸውን ስቃይ ሲጋሩ እጃቸው እዬተንዘፈዘፈ እንባቸውን ሲረጩ አሁን እንኳን ሳስበው እንባዬን መቆጣጠር አልችልም። የፈለገ ይምጣ፤ የፈለገ ይሁን እኔ ትናንትም ዛሬም ከአቤቴ ጎን ነኝ። ይህን ወዳጅም ጠላትም እንዲያውቅ እሻለሁኝ። መሽቶ እስኪነጋ አላምናቸውም። ፈጽሞ። ኢትዮጵያ ብሆን ረዳቸው ነበር የምሆነው። ህይወታቸው መጠበቅ አለበት። በዕድሜዬ አቡነ ጴጥሮስን ደግሜ አያለሁ ብዬ አላሰብኩም ነበር። ፈጣሪዬ እና ንጉሤ ግን አደረገው። ተመስገን።

 

የኔታ ጎዳና ያቆብ ቃለ ህይወት ያሰማልን። ብያለሁኝ።


ሥርጉተ©ሥላሴ

Sergute©Selassie

17.05.2021  

ስለ የኔታዋ ዝም አልልም!

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።