ኢትዮጵያ ምን ትፈልጋለች? አቅጣጫችን አዬሩ ምን ይሽታል? ምዕራፍ ዘጠኝ።
"መለዬትን የሚወድድ፦ ምኞቱን ይከተላል፥
መልካሙንም ጥበብ ሁሉ ይቃወማል።"
አመክንዮ ምን ይናፍቃል? እኛስ? እኔስ? ከአኔ ይጀመር። እሺ።
ድካም እና ዬአቅም ፍሰት ለስኬት ሊሆን ይገባል። ትናንት ባልተደራጀ የትግል ፍሰት ሲኦል ውስጥ ተቀርቅረናል። አውራ ነን ያሉትም አውራ መሆን ተስኗቸው የኦነግ አንጋች ሁነዋል። አሁንም ያ እንዳይደገም በጠራ መስመር መጓዝ ግድ ይላል።
እና።
እኔ እምታገልለት ወሳኝ አመክንዮ።
1) ዬጎሳ ፖለቲካ በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲታገድ።
2) ፀረ ሰው፤ ፀረ ተፈጥሮ፤ ፀረ ታሪክ፤ ፀረ ዜግነት የሆነው የአልባንያ ሶሻሊስት ዬዞግ ግዑዝ መንፈስ ጋር የተቃቀፈው ህገ መንግሥት እንዲታገድ።
3) ኢትዮጵያን ሊመራ የሚችል ሰዋዊ፤ ተፈጥሯዊ ግብረ ኃይል ዕውቅና አግኝቶ አመራሩን እንዲረከብ።
3.1 አሁን ያለውን ሥርዓት በኃይል መደምሰስ የሚለውን አልስማማበትም።
3.2 በምርጫ መቀዬር ይቻላል የሚለውን አልስማማበትም።
3.1 በኃይል ማስወገድ ስልጡን መንገድ አይደለም። በተጨማሪ ነገን አጎሳቋይም ነው። ዛሬንም ዬሚገድል። መስዋዕትነቱን ዬሚያከብድ። አቅም ዬሌላቸውን ዜጎችም ለፈተና ዬሚዳርግ።ለቀጣይ ሰዓታት ዬነፍስ ማሳደሪያ ዬሚሆን ዬሌላቸው፤ ሊለምኑ ያፈሩ ሚሊዮኖች፤ አልጋ ላይ ያሉ ወገኖች፤ ህፃናት ብዙ ችግርን ዬምታስተናግድ አገር ይህ ተመራጭ አይደለም።
3.1.1 በምርጫ። ይህን በጀርመንኛ ምርጫ በሰላም ተጠናቀቀ ሲባል ጽፌዋለሁ። አጣዬ ስድስት ጊዜ ተቃጥላ፤ ሽዋ ሮቢት፤ ሻሸመኔ፤ ዝዋይ፤ ሃረር፤ ጅማ፤ ነደው፤ ሚሊዮኖች በገፍ ተፈናቅለው ከደቡብ እስከ ማዕከላዊ ጎንደር፤ በጦርነት፤ በስጋት በጭንቅ ህዝብ ሌላ አማራጭ ዬለንም ብሎ እንዲያምን ሆኖ ጭንቅ ዳውን ሎድ ተደርጎ የተከናወነ ስለሆነ ነጮች ምርጫ ብለው ምንም ማዋለ ንዋይ እንዳያፈሱም በትህትና ከማሳሰብ ጋር በዚህ መንገድ ተስፋን ማጨት አይቻልም።
3.1.2 አዳዲስ የፖለቲካ ድርጅቶች አገር ቤት ሊፈጠሩ ይችላሉ። ህዝቤ አቅም አያፍስ። በቃ ይህ ላንቆሷዊ ጉዞ። ቢፈጠርም ጀንኖ ዬሞጋሳ ተጠማቂ ከመሆን ፈጽሞ አያመልጥም።
3.2.2 ተፅዕኖ ፈጣሪ ተቋማትን እንዴት እንደመከኑ፤ እንደ ሟሙ ያዬ ሰው ኢትዮጵያ ውስጥ በተዘጋ ተስፋ ተስፋን ሊያጭ አይገባም። ጊዜም ጉልበትም ማፍሰስ አይገባም።
3.1.3 መፍትሄው አዲስ መንገድ መከተል ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ዬፖለቲካ ድርጅት በቅለው ለስኬት ሳይበቁ ዬሚጨነግፋ ከሆኑ ምን ይደረግ??? ተፈጥሯዊ፤ ሰዋዊ ዬሆነ ግብረ ኃይል ማደራጀት ጠቃሚው መንገድ ይሆናል። ይህን ለማሳካት ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ አሊ ፈቅደው እንዲለቁ ማስደረግ ነው።
3.1.2 ሥልጣኑን እሚረከበው አካል ዬዬትኛውም የዞግ፤ ወይንም ዬፖለቲካ ድርጅት አባል አካል ያልሆነ ሊሆን ይገባል። ምክንያት። ዬማንነት ቀውስ ስለሚፈጥር። አብዘኞቹ የፖለቲካ ድርጅት መሪወች ችግራቸው የማንነት ቀውስ ነው። ወይ ከውህድ ማንነት መፈጠር፤ ወይንም በቁጥር አነስ ካለ ማህበረሰብ መፈጠር። ይህ ቀውስ ነው ብዙ ያሳጣን። ከህልማችን ጋርም ያፋታን።
4.ኢትዮጵያ ወደ ቀደመው አስራሦስት ክፍላተ አገራት የአደረጃጀት መስመር መመለስ። ያ ተፈጥሯዊ ነው የነበረው። እያንዳንዱ ባዕት የሁሉም ስለሁሉም ነበር። በመንፈስም በአካልም።
5. ኢትዮጵያ ከትውስት አይዲወሎጂ ሙሉ ለሙሉ ወጥታ በራሷ አይዲወሎጂ መመራት የምትችልበት ሁነትን ማመቻቸት። ይህ ማለት ኢትዮጵያ ኢትዮጵያኒዝም የሚል ፍልስፍና አላት። ለተፈጥሯዋ ልክ ዬሆነ። ኢትዮጵያኒዝም ትምህርት ቤት ገብተው ሊማሩት የሚገባ ዬዕውቀት ዘርፍ ነው።
6. ብሄራዊነትን ሊያሰፍን የሚችል አዲስ መንገድ መቀዬስ። ከመቆራረጥ አልፎ ተበጣጥሷል።
7. የህሊና መላሸቁ ድዌው በጥላቻ ወተት የተገነባ ስለሆነ ይህን የሚያፀዳ ተቋም መፍጠር። ሁሉም የሥነ ልቦና በሽታ ሰለባ ነው። ጥላቻ ምንም ሳይሆን የማንነት ቀውል የሚፈጥረው የበታችነት ስሜት ነው። በቁጥር ብዙ ሲሆን በታሪክ እኩያ መሆን ላይኖር ይችላል፤ በታሪክ ዲታ ተሁኖ በቁጥር አናሳም ሊሆን ይችላል፤ ሃይማኖታዊ ሁነቶችን ሳላክል ይህም የኢትዮጵያን ፖለቲካ ዬሚንጠው ሌላው ሰቅ ነው። ስለዚህ ከሥር የጀመረ ወደ እራስ የመለስን ተግባር ዬሚከውን ተቋም እና ሰብዕናን ይጠይቃል።
8. ሙሉ 50 ዓመት የውድቀት ብቻ ሳይሆን እራስን ያራገፈ ክስተት ስለሆነ ዛሬም እንደ ዱር እንሰሳ በመጠቃቃቃት ላይ ያለው የሴራን ድር ጥሶ መውጣትን ይጠይቃል። አቅም ስለባከነ ዬትናንቷ ኳታርን፥ ዬትናንቷን ቻይናን ማነፃፀር ይቻላል። የፈለገ በምኞት ላይ ዬተንሳፈፈ በጎ ሃሳብ ቢኖር መሪ ካላገኜ ከንቱ ነው። ስለዚህ እያንዳንዷ ቀን ለፕሮፖጋንዳ ሳይሆን ውርዳ።ዴታችን ገምግሞ በቁጭት በእልህ እራስን አርሞ መነሳትን ይጠይቃል።
9. ዬአማራ ዘር ማፅዳት ዘመቻ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲቆም ማስደረግ፤ የመልሶ ማቋቋም ርጉ ፕሮጀክት መጀመር።
10. ዬኢትዮጵያ ፖለቲካ እና ፖለቲከኞች ከሶሻሊዝም ርዕዮታዓለም ዶክተሪን ጋር የሚፋቱበት ሁኔታ ሊፈጠር ይገባል። መገዳደል፤ መበቀል። ምህረት አልባነት። ሴራ። አዲስ ቡቃዬን ማዬት ማዕት እንደመጣ መቁጠር ወዘተ የዛ በሽታ ውጤት ነው። እንደ ሥርዓት ሶሻሊዝም ውስጥ ጠቃሚ ጉዳዮች ቢኖርም ተምሮ ላልተማረ፤ በግሎባል ዘመን ድንጋይ ዘመንን ካልተከልኩ ብሎ ለሚሰቃይ ወፈፌ መንፈስ ብዙ ጥሰቱ መሰረቱ ይህ ስለሆነ፤ ስላልሰለጠነም የዘመኑ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ሁለት ትውልድ አልቆ ሦስተኛው ተጀምሯል። ጤናማ ነገር በሽታው፤ በሽታ መርሆ ሆኖ መዝለቅ የለበትም።
11. በሥርዓቷ ከፍፅምና በላይ የሆነችውን ቅድስት ተዋህዶን ማወክ እና ጋጥ ለማድረግ የሚደረገው መውተፍተፍም መቆም አለበት።
12. ሙሉ 32 ዓመት በአማርኛ ቋንቋ ላይ ዬኖረው ያለው ዘመቻም ሊቀጣ ይገባል።
13. በብሄራዊ ሰንደቃችን ላይ ያለው ውግዘት እና ማንአህሎኝነትም ሊታገድ ይገባል።
14. ታሪክ በነባር ህዝብ ብቻ ይሰራል። ይህን ዕውቅና የሚሰጥ ተከብሮ ዬሚያስከብር ሥርዓት መፍጠር ግድ ይላል። አውቆ አበዱ ይሁን ወፈፌው፤ ወፈፌው ይሁን አዋኪው፤ አዋኪው ይሁን ፋንታዚው ቢመጣ እና ቢሄድ፤ እድል ቢያገኝ እና ለበትረነት ቢበቃ ዬማይናወጥ ሥርዓት ግንባታ ላይ አተኩሮ መስራት ይኖርበታል።
15. ጠላትን አቅዶ መሻት፤ መለመንም እንደምርቃት የሚታይበት የአስተሳሰብ አዟሪትም ሊበጣጠስ ይገባል።
17. የፕሮፖጋንዳ ፋክክር፤ አዬሩን የመቆጣጠር ሁነት ተገርቶ ለዘላቂ የተረጋጋ ሥርዓት፤ ለሰከነ ዬማህበረሰብ ቡቃያ ልንተጋ ይገባል። የእኔ መስመር ይህ ነው። በማናቸውም ሁኔታ አቅም እምመግበውም በዚህ ዙሪያ ብቻ ይሆናል።
18. መታሰር በብዙ ሁነት ይገለጣል። እያንዳንዱ እራሱን ጠርንፎ ነው ለሌላው ነፃነት እተጋለሁ ዬሚለው። ሁሉም እስረኛ ነው። ከእስር እራሱን ያስፈታ።
17. ኢትዮጵያ ኢመርጀንሲ ሩም ውስጥ ናት። ይህን ተቀብሎ እራስን ገርቶ በዲስፕሊን መጓዝ ከእያንዳንዱ በግል፤ ከሁሉም በጋራ ይጠበቃል።
18. ነገረ አዲስ አበባ ፓን አፍሪካ ሙቭመንት ይጠይቃል። ሉላዊ አትኩሮትም።
ድቀት ስኬት አይደለም።
ውርዴትም ብልጽግና አይደለም።
ሽብርም ልቅና አይሆንም።
ቃጠሎም ብርሃን አይሆንም። በድብልቅልቅ አቅም እና ፋንታዚ ዛሬ አልተገኜም። በሰከነ፤ አቅምን በአማከለ ዬተደራጀ ጉዞ እንራመድ።
ዬሰዓት በፊቱ መሰናዶ ይሄው ነው። መልካም የንባብ ጊዜ።
መሸቢያ አብሮነት። አሜን።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ። አሜን።
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
11/05/2023
ኢትዮጵያዊነት ከመፈጠሩ በፊት ፈተናን አሸንፎ የተፈጠረ ሚስጢር ነው።
ትውልዳዊ ድርሻችን በህብረት እና በስክነት እናወጣ።
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ