የሰማይ እና የምድር ንጉሥ እዬሱስ ክርስቶስ "#ክንፍ" አለውን? የወሮ ዝናሽ ታያቸው ውኃ ያልነካው ፈጣጣ ፈንጣጣም አስተምህሮ ሃግ ሊባል ይገባል።

 

የሰማይ እና የምድር ንጉሥ እዬሱስ ክርስቶስ "#ክንፍ" አለውን? የወሮ ዝናሽ ታያቸው ውኃ ያልነካው ፈጣጣ ፈንጣጣም አስተምህሮ ሃግ ሊባል ይገባል።
ስለ ቃሉ ንሰኃ እገባበታለሁ አይደለም ብራና ዘርግቶ ሥንኝ ጽፎ በአደባባይ ለመዘመር ቀርቶ?
"አቤቱ ከድፍረት ኃጢያት ባርያህን ጠብቀኝ።

 
ወደ እግዚአብሄር አምላክ ለሚቀርብ ምስጋና እንዲህ በድፍረት እና በማናአለብኝነት ተንጠራርቶ ጥሰት ውስጥ መዘፈቅ የጤና አይመስለኝም። ለነገሩ የ፬ኪሎው ቤተ መንግሥት ሽብር፤ ጭንቅ ውስጥ እንደባጀ ያመሳጥራል። ሌላላው የሰማይ እና የምድርን ፈጣሪ አማኑኤል ለእነሱ ዬግፍ ሥልጣን ብቻ ምርቃት እንዳደረገም ያሳጣል።
ሥንኞቹ የባለቤታቸው የጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ አይደሉም። ዘዬው፤ ዘኃ ግራው የሳቸው የቀዳማዊዋ እመቤት ወሮ ዝናሽ ታያቸው ይመስላል። ምቱም በዚህው ዙሪያ ነው። ጭንቀት፤ መራድ፤ ሽብር እና ራድ ቤተመንግሥቱን መናጡን ያመሳጥራል።
ለምን ፈታ ደይሊ እንደዘለለው ሥንኙን አላውቅም። የአነበበውም አሟልቶ አይደለም። አንዷ ፊደል ስትጠብቅ፤ ስትላላ ብዙ እጅግ ብዙ ጉዳዮችን ታመሳጥራለች። አማርኛ ቋንቋ ቅኔም ነው የምለውም ለዚህ ነው።
ዘማሪ ዝናሽ ታያቸው አዲስ የዶግማ ፍልሰት መጥረቢያ ይዘው ከች ብለዋል። ጭብጡ እግዚአብሄር ክንፍ አለው ከሚለው አፈንጋጭ ዕምነት እና ዕሳቤ ይመነጫል። እዬገረመኝ ያለው ጉድ የኢትዮጵያ አንስት አማንያን በሃይማኖት ዙሪያ ያላቸው አሁናዊ ድፍረት ነው። ሎቱ ስብኃት። አበስኩ ገበርኩኝ። አሁን በዘመናችን ወደ አራት ተጠግተዋል። በአዲስ ፍልስፍና ፍልሰት ላይ ያሉት ማለቴ ነው።
አባቶቻችንም ሃግ አይሉም። እሱ ብቻ ሳይሆን አንጡራ ጥሪታቸው ለሌላ ሃይማኖት ተቋም መጠሪያ ሲሆንም አንተ ታውቃለህ ብለው ዝም ሆኋል ነገሩ።
የተቀባችሁ የዕድምታ ባለፀጋ አበው ለመሆኑ እኛ የማናውቀው፤ እናንተ ብቻ የምታውቁት የተመሰጠረ ገጽ በፈጣሪ አምላካችን በአማኑኤል አለን???? የመላዕክታን ሠራዊት፤ ሊቀ መላዕክታት፤ የመረጡ ብፁዑ ደጋግ አበው እና እመው ብቻ ናቸው ክንፍ ለቅድስና ተግባራቸው ቅባዓ የሚሰጣችው። የቅባዕው ጌታ መዳህኒተ ዓለም ግን እንደምን ብሎ "ክንፍ?" ኖረው???? ፈታ ደይሊ የዘለለውም ይህንኑ ነው።ፈታ ደይሊና ወርልድ የሰማማቸውን ዜናወች ቀማምሮ ጨማምቆ በራሱ አቀራረብ ያቀርባል። በመደበኛ እምከታተለው የዘገባ ሚዲያ ነው። የሆነ ሆኖ የዶግማ ጥሰቱን ስለምን እንደዘለለው አላውቅም። ከዶግማ ጥሰት በላይ አሻቅቦ መዳፈር፤ ህግ ጥሰትም ነው ለእኔ። እንደ አንድ የቅድስት ተዋህዶ ሃይማኖት አማንያን።
የሚገርመው መሰናዶው በተከናወነበት ቦታም ሌላ ብሄራዊ ጉዳይ የሁሉም ሃይማኖት አማኞች ይሳተፋበታል። አዳራሹ የብልጽግና ወንጌል መዘመሪያም መቀረጫም ብሄራዊ ጉዳይም መከወኛም። ዝብርቅርቅ የሆነ ገመና። ማን ይፈራ???
#ፀናሁ። ከዘማሪ ዝናሽ ታያቸው። (Zinash Tayachew New Gospel Music Vidio 2016/2023)
"በምድር ሰልፋ ቢበረታ
አንዱን ሳልፍ ሌላኛው ቢተካ"
"አልፈራም አልሰጋም ኧረ ለምን ብዬ
ነገሬን የያዝከው እያለኽ ጌታዬ (2)"
"የማታሳፍር ጽኑ መሠረት
የማትናወጥ በጠንካራ አለት
ንፋሱ ገፋኝ ኧረ እኔ አልወደቅኩኝም
#በርትቶ #ማዕበሉ አለሁ አልሰመጥኩም።"
"ሁሉን ያለፍኩት በአንተ ነው
ፀንቼ የቆምኩት በአንተ ነው
"እንደ ዐይንህ ብሌን ጠበቅከኝ
"#በክንፎችህ #በታች #ሰወርከኝ።" ቀጣዩ አላስፈለገኝም።
ሰማይ አይታረስ ንጉሥ አይከሰስ ካልሆነ በስተቀር አወያይ ዳጊን፤ አርቲስት ጀሚን፤ ዶር ወዳጄነህን ፊት ለፊት አቅርባችሁ እንደምትሞግቱት ሁሉ እነ ሣድስ፤ እነ ሀሌታ፤ እነ እግረኛው ሚዲያ እስኪ ይህን ፈጣሪ አምላክን የተዳፈረ አዲስ አስተምህሮ ሞግቱት።
ተቆርቋሪነት ደንበር ወሰን የለውም። ኃላፊነት የክት እና የዘወትር የለውም። ተጠያቂነት ታናሽ እና ታላቅ የለውም። ወሮ ዝናሽ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ናቸው። በህግ ፊት እንደ አንድ ዜጋ ሊታዩ ይገባል። ይህ የተፋለሰ አስተምህሮ የሚቀበለው ኃይማኖታቸው ከሆነም ጥርት ብሎ ይውጣ።
ቅድስት እናታችን ኦሮቶዶክስ ተዋህዶ፤ ማህበረ የክርስትና እምነት ተከታዮችም ሁሉም "እግዚአብሄር ክንፍ አለው" የሚል አዲስ አስተምህሮን መሞገት ይኖርባቸዋል። ግን አለውን?????
እኔ በህይወቴ በጣም የማልደርስበት ዘርፍ ነው እንዲህ ያሉ ጉዳዮችን። ግን ሰምቼው ልተኛ ብል መንፈሴ አሻም አለ። መንፈሴ አሻም እያለ ፈቃዱን ባልፈጽም ምርቃቴ ተነስቶ ልሙጥ ልሆን እችላለሁኝ። ስለዚህ ቢያንስ ስሜቴን ለአደባባይ ማውጣት ግድ አለኝ። በፈጣሪ ሥራ፤ በማይመረመር ኃይለ ሥልጣኑ ይህን ያህል ድፍረት የት ያደርስ ይሆን???? ዘመናይነት፤ ቅልጣን? ቅብጠት? ማን አለብኝነት? ደረጃውን ማውጣት አልቻልኩም።
ስሜቱ እራሱ ለአንድ ወዳጅ የሚዜም ዓይነት ነው የሆነብኝ እጅግ ቀለለብኝ። አዝናለሁ። ምድሪቱ አልበቃቸው ብላ ሰማይን እዮርን መንቀል ጀመሩ። ምን ዓይነት የጉድ ቲም ነው??? ኢትዮጵያ ውስጥ ያልታጨ፤ ያልተጎረጎረ አንድም ቀደምት የዕሴት ዘርፍ የለም። አበስኩ!
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
15/08/2023
"ህግ ተላላፊወችን ጠላሁ"

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።