ርግቦቼ። ያዬሁትን ላጋራችሁ።

  May be an image of pigeon and mourning doveMay be an image of pigeon and mourning dove

ግቦቼ። ያዬሁትን ላጋራችሁ።

"………ርግብ ባሏ ከሞተ በኋላ ከሌሎች አዕዋፋት ጋር አትገናኝም። #በጥፍሯም #ምላስዋን #ትሰነጥቃለች

ሌላ ወፍ ስንኳን ሊቀርባት ቢፈልግ በታላቅ ጩኽት ጓደኞቿን ጠርታ ሁሉም ተረዳድተው ይገድሉት የለምን ………"

(ድርሳነ ሚኬኤልና ሩፋኤል በግዕዝና በአማርኛ ዘሰኔ ምዕራፍ ፳፱ እና ገጽ ፼፸፱)

 

ከመታደል በላይ ምን ይባላል። ታማኝነት፤ ፍፁም ታማኝነት ተማላ ያልሆነ፦ ምነው ለሰው ልጆች በሆነ።

የእኔ ፯ኛ መጽሐፌ "#ርግብ #በር" ይላል። ደጉ ንጉሥ ከአነፁት ፋሲል ግንብ መግቢያ በሮች ውስጥ አንዱን ወስጄ ነው። ፀጋዬ ድህረ ገጽም መክሊት የሚለው ክፍል #ርግብ ከእነ ጎጆዋ ነበር። በሌላ በኩል በፀጋዬ ራዲዮ ለረጅም ጊዜ መግቢዬ ዬርግብ ድምጽ ነበር። ለምን? ስለምን ብላችሁ አትጠይቁኝ። እኔም አላውቀውም እና።

 አሁን ከሆነ በምኖርበት ገዳማዊት ከተማ #ቪንተርቱር ርግብ በስፋት አያለሁ። ከዓመት በፊት ድርስ ምልስ ይሉ የነበሩ ርግቦች በእኛ ጣሪያ ነበሩ። ቋሚ መኖሪያቸው አላደረጉትም ነበር። አሁን ከሆነ ወደ እኔ ቤት ጎራ ማለት አዘወተሩ። ስድስት ወራት ይሆናቸዋል። በቋሚነት ያዘነ፤ የተከዘ ርግብ ብቻውን ለረጅም ጊዜ ነበር። ስለሚያሳዝነኝ የአጃ ክክ ገዝቼ መስኮቴ ላይ መመገብ ጀመርኩኝ። ከዛ በለታት አንድ ቀን #ጠፋብኝ የት አባቴ ልፈልገው???

 ሥም አውጥቼ #ቀለሜ እለዋለሁ። ሙሉ ግራጫ ነው። እግሩ እንሶስላ የሞቀ ይመስላል። ከተወሰነ ቀን በኋላ #ገብስማ የደስ ደስ ያላት ርግብ አስከትሎ መጣ። ቀለል ያለች ቀልጣፋ ቢጤ ናት። እኔ አስብ የነበረው የትዳር አጋሩን አጥቶ ብዬ ነበር። ለካንስ ትዳር አልነበረውም። ለዛም ነው የበዛ በጣም የበዛ #ብቸኝነት ይሰማው የነበረ።

 አንዳንድ ጊዜ ከእኔ መስኮት ለመመገቢያ ካሰናዳሁለት የመመገቢያ ባዝ ኩርምት ብሎ ያድራል። እማደርግለት ሁሉ ይጨንቀኛል። በተለይ ወጀብ ዝናብ ሲኖር። ሲያመሽም እስከ ምሽቱ ሦስት ሰዓት ይቆያል።

 የሚገርመው አጋሩን ካገኜ በኋላ ሁሉ #መከፋት ቀረ። በምን ቋንቋ ተግባብተው አስከትሏት እንደመጣ ሁሉ ይገርመኛል። የፈጣሪ ሥራ ፍፁም ዕፁብ ድንቅ። እሱ #ርጉ ነው። እሧ ፈጣንም #ቀበጥም ናት። #እምትቀልጥበት ሁሉ ይመስለኛል። እሱ #በርከት አድርጎ ይመገባል እሷ #ቀለል አድርጋ ትመገባለች። እሱ ሆዱ ከሞላ ብዙም መብረር አይፈልግም። እሷ ግን መብረር፤ መብረር ነው።

 ብዙ ጊዜ ምግብ ስመገብ ማን እንደሚጠራቸው አላውቅም ይመጣሉ። የሚገርመኝ ከምግብ ቦታቸው ምግብ ተቀመጦ መስኮቱን እንድከፍትላቸው ይፈልጋሉ። ከከፈትኩ - ይገባሉ። ሲወጡም አይረብሹም። አሁን አሁን መስኮት ከፍቼ መውጣቱን አቁሜያለሁ። ሊያጠፋ ስለሚችሉ።

 የሚገርመኝ በምን ቋንቋ እንደሚጠራሩ አላውቅም። ሴቷን #ተስፍሽ ነው እምላት። ተስፍሽን ብቻዋን ሳያት ምግብ እሰጣታለሁ። በዛው ፍጥነት #ቀለሜ ይመጣ እና ማዕዱ #ግርማ ያገኛል። ቀለሜን ብቻውን ሳዬው ደግሞ እህል ሳደርግለት ተስፍሽ ትመጣ እና ማዕዱ #ሞገስ ይኖረዋል።

 የእርግቦች #ክንፍ ድምጽ እጅግ #አስፈሪ ነው። አንድ ቀን ቀለሜ ከውጭ እንደበረረ በቀጥታ በድንገት ወደ ቤቴ ገባ ደንግጬ #ጮኽኩኝ #ድሮን የተላከብኝ ነው የመሰለኝ። በጣም ያስፈራ ነበር። ደንግጬ ስለጮኽኩኝ ከዛ አልተመለሰም። #አኮረፈ ወይንም ደነገጠ። ለሁለት ቀን ጭራሽ በሰፈራችንም ሁለቱም አልነበሩም። በጣም አዝኜ ነበር። በኋላ ግን አብረው ተመለሱልኝ። እንጃ ሳያቸው ደስ ይሉኛል። ለማዶች ናቸው። በልጅነቴ የእናቴ እናት ኤሊወች ነበሯት፤ ከብት፤ ውሾች ነበራቸው። እኔ ግን ጥጃ እና ጫጩት እወድ ነበር። እናቴ ዶሮ ታረባ ነበር። የዛ ፍቅር መሰለኝ እንዲህ ተመስጦ ያለኝ። ከእኛ ቤት እንቁላል #ሽሮ ማለት ነበር።

 ርግቦች ብቅል ከተመገቡ ተሎ አይመለሱም። ሽንብራ፦ አተር አይበሉም። ማንኛውንም ዱቄት አይበሉም። ብዙ ውሃ አይጠጡም። ምግብ ሲበቃቸው ትተው ይሄዳሉ። ከመጠናቸው በላይ አይመገቡም።

 #ማህበረ ሰላም እምላቸው ግር ብለው የሚመጡም የርግብ እንግዶች አሉኝ። እነሱ ሲመጡ ተስፍሽ ኃይለኛ ስለሆነች ዓናት አናታቸውን ብላ ታባራቸዋለች። እነ ተስፍሽ ሳይኖሩ ሲመጡ ከቤት ካለሁ ምግባቸውን አቀርባለሁ።

አሁን በሥነ - ሥርዓት ምግብ በመደበኛ እዬገዛሁ ነው። ማልደው ነው የሚነሱት ከንጋቱ 11-12 ሰዓት ከች ይላሉ። ያንኳኳሉም። ምግብ አዘጋጅቼላቸው ስለምተኛ መጥተው ሲመገቡ እነቃለሁኝ። ብሥራት ናቸው። ቅንነት - ርህርህና - ምህረት - ሰላም እግር አውጥቶ የመጣ ሁሉ ይመስለኛል።

በርህርህና እርስ በርሳቸው ተደጋግፈው፦ ተከባብረውም ኑሯቸውን የሚመሩበት አርት ይገርመኛል። አይጣሉም። አይጋጩም። አይጯጯሁም። በለጡን። ሴቷ ስታጉረመርም እሱ ሲያባብላት የሚደንቅ የተፈጥሮ ትዕይንት ነው።

! የማድመጥ አቅማቸው የጉድ ነው። መስኮት ተዘግቶ መጋረጃ ስከፍትና ስዘጋ ጆሯቸውን ቀጥ ያደርጋሉ። ይሰማሉ። መስኮት ስዘጋ ስከፍትም እንዲሁ።

እንዴት አደራችሁ? እንዴት ዋላችሁ? የት ቆያችሁ? ደህና እደሩ ስላቸው ሁሉ #ምግቡን #ትተው እኔን ያደምጣሉ። እኔ ሳስበው በአንጎላቸው ውስጥ ንቃት የሚሰጥ ተፈጥሮ እንዳላቸው አስባለሁኝ።

ተሎተሎ ወደ ቤቷ መሄድ የምትወደው ሴቷ ናት። ከቤታቸው ሆነው የምግብ ሥፍራቸውን ይጠብቃሉ። ዘበኞችም ናቸው። በጣም የሚገርመኝ ግን ሰንበት ላይ ያላቸው ቁጥብነት። ለቀው ሄዱን እስክል ድረስ ትውር አይሉም። ቢመጡም አፍታ አይቆዩም እፍ ነው የሚሉት። ሴቷ ርጋታ ያነሳት ብትት// ብትት የምትል ሲሆን ወንዱ ደግሞ የሰከነ // የማይደነግጥ ነው። ከሁሉ አስፈሪው ግን የክንፋቸው ግዝፈት ጩኽት ነው።

 እግዚአብሄር ይስጥልኝ።

የእኔ ውቦች ደህና እደሩልኝ። አሜን።

ሥርጉተ©ሥላሴ

Sergute©Selassie

03/07/024

የሁሉ ጌታ አማኑኤል አባቴ ተመስገንልኝ። አሜን።

 

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።