"ጎንደርን እያራደ ያለው እገታ እና ግድያ ምክንያቱ ምንድን ነው? በማንስ ነው የሚፈፀመው? bbc"

 https://www.bbc.com/amharic/articles/crrl8pepgn8o

 

"ጎንደርን እያራደ ያለው እገታ እና ግድያ ምክንያቱ ምንድን ነው? በማንስ ነው የሚፈፀመው?

 የኖላዊት እገታ እና ግድያ ነዋሪዎችን ያስቆጣ ሲሆን የጸጥታ ኃይሎች ሰልፈኞች ላይ በከፈቱት ተኩስ ቢያንስ አራት ሰዎች መገደላቸው ተዘግቧል።

6 መስከረም 2024, 07:05 EAT

ለቤተሰቦቿ ብቸኛ ልጅ የሆነችው ኖላዊት ዘገዬ ከመኖሪያ ቤቷ ግቢ ውስጥ ታግታ የተወሰደችው ነሐሴ 24/2016 . ረፋድ 330 ገደማ ነበር።

ኖላዊት ታግታ እንደተወሰደች የታወቀው አጋቾች ወላጆቿ ተከራይተው በሚኖሩበት ግቢ ውስጥ የጣሉት ማስታወሻ ወረቀት ከተገኘ በኋላ ነው። ወረቀቱምእኛ አግተን ወስደናታል እስከምንደውልላችሁ ታገሱየሚል ነበር።

ክስተቱን ተከትሎ በግቢው ውስጥ የተሰባሰቡ ሰዎች ካልተበተኑ እንዲሁም ለፖሊስ ሪፖርት ካደረጋችሁ እንገላታለን የሚል ማስፈራሪያ ጽሑፍም ግቢው ውስጥ ተጥሎ እንደነበር ስለክስተቱ ለቢቢሲ ያስረዱ የቤተሰብ አባል ተናግረዋል።

ከዚያም አጋቾቹ ሕጻኗን ለመልቀቅ አንድ ሚሊየን ብር ጠየቁ።ገንዘቡ ከታዳጊዋ ቤተሰብ አቅም በላይ መሆኑን በመግለጽ በተደረገ ድርድር 300 ሺህ ብር ለመክፈል ከአጋቾቹ ጋር ተስማሙ።ማሰባሰብ የተቻለው ገንዘብ ግን 200 ሺህ ብር ብቻ ነበር።

አጋቾች የተሰበሰበውን ገንዘብ ቢወስዱም ታዳጊዋን ገድለው ከወላጆቿ መኖሪያ ቤት ጓሮ መጣላቸውን የቤተሰብ አባሉ አስረድተዋል።ምን አልባት 100 ሺህ ብር በመጉደሉ ይሆናል የገደሏትይላሉ።

ሕጻን ኖላዊት ታግታ በተወሰደችበት ዕለት ሌሊትም በከተማው የእናት እና ልጅ ሕይወትን የቀጠፈ ሌላ ወንጀል ተፈፅሟል።

ለደኅንነታቸው ሲባል ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የሟቾች የቅርብ ዘመድ ማንነታቸው ያልታወቁ ታጣቂዎች ነሐሴ 24 ቀን ሌሊት 700 ሰዓት ገደማ እናት እና ልጅ የሚኖሩበትን ቤት ሰብረው መግባታቸውን ይናገራሉ።

በቁጥር ስድስት ነበሩ ያሏቸው ታጣቂዎች ሳሎን ውስጥ የነበሩ ዘመናዊ ስልኮችን እና ታብሌቶችን ዘርፈው ሊሄዱ ሲሉ የድረሱልን ጥሪ ባሰሙት የቤተሰብ አባላት ላይ መተኮሳቸውን የቤተሰብ አባሉ አስረድተዋል።

“ 'ለምን ትጮኻላችሁ' በሚል ከቤት ከወጡ በኋላ ነው የተኮሱባቸው።ይላሉ።

በዚህም 55 ዓመቷ አክስቱ መብራት ኪዳነማሪያም ወዲያውኑ ሲሞቱ 22 ዓመቷ ልጃቸው በአምላክ ደግሞ ሆስፒታል ከደረሰች በኋላ ሕይወቷ ማለፉን ተናግረዋል።

በአምላክ አብርሃ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሶፍትዌር ሳይንስ የሦስተኛ ዓመት ተማሪ ነበረች።

ከሞቱት በተጨማሪ የቤት ሰራተኛቸውም በጥቃቱ አንድ ዓይኗ እንደጠፋ እና ለተሻለ ሕክምና ወደ አዲስ አበባ መወሰዷን የቤተሰብ አባሉ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

ቤተሰቡ ሰላማዊ እና የተከበረ ነውየሚሉት የቤተሰብ አባሉ፣የተሻሉ የኢኮኖሚ ደረጃ ላይ የሚገኙ በመሆናቸው በታጣቂዎቹ ኢላማ ሳይደረጉ እንዳልቀሩ ገምተዋል።

ድርጊቱ ሲፈፀም በቤት ውስጥ የነበሩ ሕጻናት ላይ የደረሰ አካላዊ ጉዳት ባይኖርም፣በተፈጠረባቸው ድንጋጤ እዚያ መቆየት ባለመቻላቸው ከተማውን ለቀው ለመውጣት ተገደዋልም ብለዋል።

 

የፎቶው ባለመብት, Family

የምስሉ መግለጫ, 22 ዓመቷ በአምላክ አብርሃ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሶፍትዌር ሳይንስ የሦስተኛ ዓመት ተማሪ ነበረች።

ከወራት በፊትም በዚያው ከተማ፣ ቀበሌ 18 አንድ ታዳጊ ከእናቱ እጅ ተነጥቆ ለማስለቀቂያ 4 ሚሊየን ብር እንደተጠየቀበት አንድ የቅርብ የቤተሰብ አባል ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ድርጊቱ የተፈፀመው ግንቦት 12/2016 . ከሌሊቱ 7 ሰዓት ገደማ ነበር።

እናት ከልጇ ጋር አገር ሰላም ብለው ተኝተዋል።ድንገት አካባቢው በተኩስ ከተናጠ በኋላ አጋቾች መኖሪያ ቤታቸውን ሰብረው በመግባት ታዳጊውን ያዙ።

እናቱ እና በግቢው ውስጥ የነበሩ ተከራዮች ጩኸት ቢያሰሙም የደረሰላቸው አልነበረም።

ልጇን ለማስጣል ስትተናነቅ የነበረችው እናት ላይ ጥቃት በመሰንዘር 9 ዓመቱን ታዳጊ ይዘውት እንደሄዱ የቅርብ ዘመድ እንደሆኑ የገለጹት አቶ ታደሰ ተናግረዋል።

ቤተሰቡ ገንዘብ አለው በሚል ኢላማ እንደተደረገ የገለጹት አቶ ታደሰ፣ የአጋቾቹን ማንነት መለየት ባይችሉም ሁሉም መሳሪያ የታጠቁ እና ፊታቸውን በጭንብል የሸፈኑ እንደነበሩ ገልጸዋል።

ታዳጊው ወዴት እንደተወሰደ ያላወቁት ቤተሰቦች 7 የሰቀቀን ቀናትን ካሳለፉ በኋላ ነበር ከአጋቾቹ ስልክ የተደወለላቸው።

አቶ ታደሰ እንዳሉት አጋቾቹ ታዳጊውን ለመልቀቅ አራት ሚሊዮን ብር የጠየቁ ሲሆን በድርድር 550 ሺህ ብር ተስማሙ።ሆኖም ገንዘቡን ለማሰባሰብ ቀናት ወሰደባቸው።

ታዳጊው ስልክ ሲያስደውሉት እያለቀሰብር አልሞላላችሁም? ቶሎ አስወጡኝይል ነበርይላሉ።

ገንዘቡ ከተሰባሰበ በኋላ ባጃጅ ተከራይተው ወደሚነግሯቸው ሥፍራ እንዲወስዱ በአጋቾቹ ትዕዛዝ ተሰጣቸው።

የታዳጊው አባት የተባለውን በመፈፀም ማንነታቸውን ማየት በማይችልበት ሁኔታ ገንዘቡን አስረክቦ ልጃቸው አመሻሽ 1200 ላይ እንደሚለቀቅ ነግረውት ተመለሰ።

ሆኖም ታዳጊው በተባለው ሰዓት ሊለቀቅ አልቻለም።

ቤተሰቡ በጭንቅ ሰዓታትን አሳለፉ።በዚህ ሁኔታ ሳሉ አጋቾቹ ሌሊት ላይ ስልክ ደውለውጠዋት 1130 ላይ ጊዎርጊስ ማዞሪያ አምጥተን እንጥልላችኋለንእንዳሏቸው አቶ ታደሰ ያስታውሳሉ።

ሌሊቱ እንደምንም ነግቶ ወደ ሥፍራው ቢያቀኑም ታዳጊውን ማግኘት አልቻሉም።

ስናጣው ገድለው ጥለውታል ብለን በየሥርቻው እየፈለግን ሳለን በአንድ ባጃጅ እራፊ ጨርቅ ለብሶ እየተንቀጠቀጠ ሲመጣ አየነውይላሉ።

የባጃጅ አሽከርካሪው ታዳጊውን አንድ ግለሰብ አሳፍሮት ወደ ጊዮርጊስ እንዲያደርሰው 20 ብር እንደተከፈለው እንደነገራቸው አቶ ታደሰ ገልጸዋል።

እናት 12 ቀናት በኋላ የተለቀቀው ልጇ እጆቹ ፣እግሮቹ፣ ከንፈሮቹና ጆሮዎቹ ቆሳስለውና ከሰው ተራ ወጥቶ ስታየው ራሷን ሳተች የሚሉት አቶ ታደሰ፣ በእገታው ወቅት እጇ ላይ በስለት የደረሰባት ጉዳትም ተባብሶ ሆስፒታል እስከመተኛት እንደደረሰች ተናግረዋል።

ታዳጊው ሌሊት ላይ ሲቃዥ ነው የሚያድረው፤ የመላዕክት ሥዕላትን ሳይዝ አይተኛም። መሣሪያ ከሌለው ሰው ጋርም አይተኛምበማለትም የደኅንነት ስጋት ውስጥ መቆየቱን ገልጸዋል።

አሁን ላይ እናት እና ልጅ ቀያቸውን ጥለው ወደ አዲስ አበባ በመሄድ ኑሮን እንደ አዲስ ጀምረዋል።

እነዚህ ታሪኮች በከተማው ውስጥ የሚፈፀሙ እገታዎችን እና ግድያዎችን ለማሳየት እንደ አብነት የቀረቡ እንጂ ሕጻናትን ጨምሮ ጥቂት የማይባሉ ሰዎች ተመሳሳይ ወንጀል ተፈፅሞባቸዋል።

ከተማ አስተዳደሩም በዚህ ዓመት ብቻ 60 በላይ የእገታ ወንጀሎች መፈፀማቸውን አስታውቋል።እነዚህ የእገታ ወንጀሎች ለፖሊስ ሪፖርት የተደረጉ ብቻ በመሆናቸው ቁጥሩ ከዚህም ሊበልጥ እንደሚችል ይገመታል።

በጎንደር ከተማ እገታ ለምን ተበራከተ?

በታሪካዊቷ እና የቱሪስት መዳረሻዋ ጎንደር ከተማ አካባቢው መሰል ክስተቶች አልፎ አልፎ ሲያጋጥሙ ቢሰሙም፣ ካለፉት ስድስት ወራት ወዲህ ግን ባልተለመደ እና አስደንጋጭ በሆነ መልኩ እገታ እና ግድያ መባባሱን ነዋሪዎች ይናገራሉ።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው ሦስት የከተማዋ ነዋሪዎች ለዚህ ሁሉ ምክንያቱ የጸጥታ ሥርዓቱ መላላቱ እና የሕግ ከላለ አለመኖሩ ነው ይላሉ።

ለደኅንነታቸው ሲባል ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈቀዱት ነዋሪዎቹ እንዲህ ዓይነት ክስተት አጋጥሞ ለፖሊስ ሪፖርት ሲደረግምአቅም የለንም፤ ያው መደራደር ነው። ሌላ ምንም ማድረግ አንችልም።የሚል መልስ እንደሚሰጥ ተናግረዋል።

ነዋዬ ፍቅር ተበራክቷልየሚሉት አንድ ነዋሪ፣ ከተማው እንዳይረጋጋ እና እንዲበተን የሚፈልግ ኃይል ያለ እስከሚመስል ድረስ ሕገ ወጥነት መንሰራፋቱን ያስረዳሉ።

አደባባይ ወጥተን ፍትህ ስንጠይቅም በጥይት ዝም ለማሰኘት የሚፈልግ አካል ነው ያለው። የተያዙ ሰዎችም በዋስ ይለቀቃሉ። ጠበቅ ያለ ውሳኔ አይሰጥምሲሉም የፍትሕ ሥርዓቱ ደካማነት ወንጀሉን እንዳባባሰው ተናግረዋል።

ይህምማን አለብኝነትንበመፍጠር ማንም ያሻውን የሚፈፅምበት ከተማ እንዲሆን እንዳደረገው የገለጹት ነዋሪው፣ በሰላም ወጥቶ መግባት እንዳልተቻለ አስረድተዋል።

በክልሉ ከሐምሌ 2015 .. መጨረሻ ጀምሮ በመንግሥት እና በፋኖ ኃይሎች መካከል የትጥቅ ግጭት ከተጀመረ በኋላ ጎንደር ከተማን ጨምሮ የተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች ሰላም እና መረጋጋት ርቋቸዋል።

በተለያየ ጊዜ በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች በሚከሰቱ ግጭቶች የበርካታ ሰላማዊ ሰዎች ሕይወት ከመቀጠፉ በተጨማሪ የነዋሪዎች የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ አጣብቂኝ ውስጥ ገብቷል፤ እገታን ጨምሮ የሚፈፀሙ ወንጀሎችም ተበራክተዋል።

ባለፈው ወር በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኤምባሲም በማኅበራዊ ገጹ ባሰፈረው ጽሑፍ በክልሎች የሚካሄዱ ግጭቶች ወንጀለኞችን እንዳደፋፈሩ እና የሕግ የበላይነትን እንዳዳከሙ ያሳያል ብሏል።

 

ቤታችን ከመግባት ውጭ ሌላ ምን ጥንቃቄ እናደርጋለን?”

ቢቢሲ ያነገጋራቸው ነዋሪዎች በከተማዋ በሰላም ወጥቶ መግባት ብቻ ሳይሆን በሰላም ገብቶ ለማደርም ዋስትና የለም ይላሉ።

ስሟ እንዲጠቀስ ያልፈቀደች አንድ ነዋሪ፣ ከተማዋ አሁንም ድረስ በኮማንድ ፖስት ሥር መሆኑን እና የሰዓት እላፊውም ተግባራዊ እየተደረገ እንዳለ በመግለጽ፤በጊዜ ቤታችን ውስጥ ከመግባት ውጭ ምን ዓይነት ጥንቃቄ ልናደርግ እንችላለን?” ስትል ትጠይቃለች።

በጊዜ ልትገቢ ትችያለሽ። ልትጠነቀቂ ትችያለሽ፤ ነገር ግን ሰው ቤቱ ገብቶ ከምን ሊጠነቀቅ ይችላል? የጎንደር ሕዝብ ቤቱ ውስጥ ጭምር ነው እየታፈነ ያለው።ስትልም ነዋሪዎች ስጋት ላይ መውደቃቸውን ገልጻለች።

ላለፉት ሁለት ዓመታት ስጋት ላይ ነው ያለውየምትለው ነዋሪዋ በተለይ ከስድስት ወራት ወዲህ የከተማው ሕዝብ አስፈሪ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ እና የቻለም ከተማውን ለቆ እየወጣ መሆኑን ትናገራለች።

ነዋሪዋ እንደምትለው በከተማዋ በተጣለው የሰዓት እላፊ ከቀኑ 1200 ሰዓት እስከ ሌሊቱ 1000 ድረስ መንቀሳቀስ አይቻልም።በዚህ ሰዓት የሚንቀሳቀሱት የፀጥታ አካላት ናቸው።

ሆኖም መሀል ከተማ ውስጥ ሌሊት ላይ ሰው እየታፈነ፣ እየተጮኸ የሚደርስ አካል እንደሌለ ትዝብቷን ለቢቢሲ አጋርታለች።

በጠራራ ፀሐይም ቢሆን ሊያፍኑሽ ከመጡ ወይ መሞት ወይ መታፈን ነውስትል በሰላም የመኖር መብት ጥያቄ ውስጥ መግባቱን ትገልጻለች።

ይህ ነው ተብሎ የማይገለጽ ሁኔታ ውስጥ ነው ያለነውየሚሉት ሌላ ነዋሪም፣ ሰው ደጅ ብቻ ሳይሆን ቤቱ ውስጥ ሆኖም ከስጋት መላቀቅ እንዳልቻለ ተናግረዋል።

እገታውን የሚፈፅመው ማን ነው?

በጎንደር ከተማ በተገባደደው ዓመት ብቻ 64 የእገታ ወንጀሎች መፈፀማቸውን የከተማዋን ፖሊስ መምሪያ ኃላፊ ረዳት ኮሚሽነር አየልኝ ታክሎን ጠቅሰው የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

በዚህ ወንጀል የተጠረጠሩ 31 ግለሰቦችም በቁጥጥር ሥር መዋላቸውንና ሌሎች ተጠርጣሪዎችን ለመያዝ ክትትል እየተደረገ እንደሆነም ዘገባው ጠቅሷል።

የክልሉ መንግሥት ከትናንት በስቲያ ነሐሴ 28/2016 . በሰጠው መግለጫ ከሰሞኑ በጎንደር ከተማ የሕዝብ ቁጣን በቀሰቀሰው ግድያ እና እገታ የጸጥታ አስከባሪዎች ተሳታፊ መሆናቸውን ገልጿል።

መግለጫውን የሰጠው የክልሉ የሰላም እና ጸጥታ ቢሮው በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች ግድያ እና እገታ መኖሩን ጠቁሞ፣ በጎንደር ከተማ ከተፈፀመው እገታ እና ግድያ ጋር በተያያዘ 14 የጸጥታ ኃይሎች ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር ውለዋል ብሏል።

ሆኖም ቢሮው ስለ ምርመራው፣ በቁጥጥር ሥር አዋልኳቸው ስላላቸው የጸጥታ ኃይሎች ደረጃም ሆነ በየትኛው የጸጥታ መዋቅር እንዳሉ አልጠቀሰም።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው ነዋሪዎችም በከተማዋ በሚፈፀሙ ወንጀሎች በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ የጸጥታ አካላት እጅ አለበት ይላሉ።

አንዲት ነዋሪ፣እንዲህ ዓይነት እገታዎች ተፈፅመው ለፖሊስ ሪፖርት በሚደረግበት ወቅት አጋቾቹ መረጃ የሚደርሳቸው ወዲያውኑ ነው።ደውለው ያስፈራራሉ።ይህም የሚያሳየው ግንኙነት እንዳላቸው ነውስትል ምክንያቷን አስረድታለች።

የሕዝብን ሰላም ማረጋገጥ የመንግሥት ተቀዳሚ ሥራ ነው የምትለው ነዋሪዋ፣የሕዝቡ ሰላም መከበር ካልቻለም ተጠያቂው መንግሥት ነው።ስትል ጉዳዩ ከመንግሥት ራስ እንደማይወርድ ትገልጻለች።

ሌላ አንድ ነዋሪም የአካባቢው የጸጥታ ኃይል ሥራውን በአግባቡ መወጣት ቢችል ይህ ሁሉ አይኖርም ነበር ይላሉ።

በጠራራ ፀሐይ የሚፈፀምን ወንጀል መንግሥት እያየ እና እየሰማ ካልደረሰ ለማንስ ሪፖርት ይደረጋል?” ሲሉ ይጠይቃሉ።

ቤተሰብ የታገተባቸው ሰዎች ለፖሊስ ሪፖርት ለማድረግ ሲያስቡምበሰላም እንዲወጡ አትፈልጉም ማለት ነውመባል እየተለመደ መጥቷል የሚሉት ነዋሪዎቹ፣የታጋች ቤተሰቦችም እምነት ከማጣታቸው የተነሳ ጉዳዩን በዝምታና እና በራሳቸው መንገድ ለመፍታት ሲጥሩ እንደሚስተዋል ተናግረዋል።

ታዳጊ ዘመዳቸው ታግቶባቸው የነበሩት አቶ ታደሰም ከስጋት የተነሳልጁ እስከሚለቀቅ ድረስ ስለአጋቾቹ ክፉም ደግም አንናገርም ነበር።ብለዋል።

ታዳጊው ከቤት በተወሰደበት ሰዓት ለፖሊስ ሪፖርት ተደርጎ እንደነበር የሚያስታውሱት አቶ ታደሰ፣እኛ አቅም የለንም።በዚህ ሰዓት መምጣት አንችልም።ያው የምትጠየቁትን መክፈል ነው እንግዲህየሚል መልስ እንደተሰጣቸው ገልጸዋል።

በዚህም ምክንያት በአንዳንድ የጸጥታ አካላት እና ሕዝቡን በሚያንገላቱ አካላት መካከል ትብብር እንዳለ ለማመን ተገድጃለሁ ብለዋል።

በታጣቂዎች የተገደሉት እናት እና ልጅ የቅርብ ዘመድ በበኩላቸው በከተማው 'ስድስቱ' ተብሎ የሚጠራ የተደራጀ ዘራፊ ቡድን መኖሩን መስማታቸውን ተናግረዋል።

ግለሰቡ ቡድኑ ምን ያህል አባላት እንዳሉትና ከማን ጋር ግንኙነት እንዳለው ባያውቁም፣የቡድኑ አባላት ከታጣቂ ቡድኑ ፋኖ አደረጃጀት ጠፍተው የመጡ እና የመንግሥት የጸጥታ ኃይል አባል የሆኑ ግለሰቦች እንደሆኑ በከተማዋ በስፋት ይወራል ብለዋል።

ሌላ አንድ የከተማ ነዋሪምከፋኖ የተቀነሱ፣ የተባረሩ እና ያኮረፉ ታጣቂዎች፣ አንዳንድ የጸጥታ አካላት እንዲሁም ቀድመው በነበሩ ግጭቶች መሣሪያ በእጃቸው የገባ ሥራ አጥ ግለሰቦች በከተማ ለተንሰራፋው እገታ፣ዘረፋ እና ግድያ ተጠያቂ አድርገዋል።

የክልሉ ሰላምና ጸጥታ ቢሮ በክልሉ እየተፈጸመ ላለው ግድያ እና እገታ ጥቂት የጸጥታ ኃይሎች እጃቸው እንዳለበት ያመነ ሲሆን በስም ያልጠቀሰውንታጣቂ ቡድን ከሷል።

ቢሮው በመግለጫው ስለታጣቂ ቡድኑ በዝርዝር ያለው ነገር የለም።

በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች የፋኖ ታጣቂዎች የሚንቀሳቀሱ ሲሆን ለፖለቲካ ዓላማ ጋዜጠኞችንና የመንግሥት ባለሥልጣናትን በማገትና በመግደል ይከሰሳሉ።ከዚህም ባሻገር ግለሰቦችን በማገት የማስለቀቂያ ገንዘብ እንደሚጠይቁ የሚያመለክት ሪፖርት ወጥቷል።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ግንቦት 20/2016 .. ባወጣው መግለጫ የፋኖ ታጣቂዎች ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ለጉልበት ሥራ ወደ ታላቁ ሕዳሴ ግድብ ሲጓዙ የነበሩ 274 በላይ ሰዎችን አግተው ለረዥም ጊዜ ካቆዩ በኋላ ክፍያ ጠይቀው መልቀቃቸውን ገልጿል።

ሆኖም በጎንደር በተከታታይ የተፈፀሙትን እገታዎች እና ግድያዎች ተከትሎ በአካባቢው የሚንቀሳቀሰው ፋኖ በወንጀሎቹ እጁ እንደሌለበትና ማንነታቸውን ባይጠቅስም 'እገታ የሚፈፅሙ አካላትን' እንደደረሰባቸው ከታጣቂ ቡድኑ ጋር ግንኙነት ያላቸው የማኅበራዊ ሚዲያ ገጾች ጽፈዋል።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በአማራ፣በኦሮሚያ እና በትግራይ ክልል ሕጻናትን ጨምሮ ሰላማዊ ሰዎችን በማገት ገንዘብ መጠየቅ እና መግደል እየተበራከተ መጥቷል።

በቅርቡ ከአማራ ክልል ደባርቅ ዩኒቨርሲቲ ተነስተው ወደ አዲስ አበባ በማቅናት ላይ የነበሩ 100 በላይ ተማሪዎች በኦሮሚያ ክልል፣ ገብረ ጉራቻ አካባቢ ታግተው የማስለቀቂያ ገንዘብ ሲጠየቅባቸው እንደነበር ይታወሳል።

በትግራይ ክልልም እንዲሁ 11 ወራት ውስጥ 12 ሴቶች ላይ የግድያ ወንጀሎች መፈፀማችውንና ከእነዚህ መካከል ታግተው ተወስደው ገንዘብ ሲጠየቅባቸው የነበሩ እንደሚገኙበት ከአንድ ወር በፊት የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ለቢቢሲ ገልጾ ነበር።

በአገሪቱ እስካሁን ምን ያህል ሰዎች እንደታገቱ እና በእገታ ሥር ሳሉ እንደተገደሉ የሚገልጽ ሪፖርት ባይኖርም ጥቂት የማይባሉ ዜጎች የወንጀሉ ሰላባ እንደሆኑ ይታመናል።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ባወጣው ሪፖርት የሕግ ማስከበሩ በመላላቱ ሰላማዊ ዜጎች በታጣቂዎች፣ በተደራጁ ቡድኖች እና በአንዳንድ የመንግሥት የጸጥታ አካላት የሚደርስባቸው እገታ ተባብሷል ሲል ማዕከላዊው መንግሥት ድርጊቱን እንዲያስቆም ጥሪ አቅርቧል።

በተለይ በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች በተንሰራፋው የእገታ ወንጀል ምክንያት የዜጎች መሠረታዊ የሚባሉ በሕይወት የመኖር እና የመዘዋወር መብታቸው እየተጣሰ መሆኑን ኮሚሽኑ ጠቅሷል

ባለፈው ወርም የአሜሪካው አምባሳደር ኧርቪን ማሲንጋ ኢትዮጵያ ውስጥ ገንዘብ ለማግኘት እየተፈጸሙ ያሉ የሰላማዊ ሰዎች እና የተማሪዎች እገታዎች እንዲቆሙ ጥሪ አቅርበው ነበር።

አምባሳደሩበኦሮሚያ እና በአማራ ክልሎች በቅርቡ እና በተደጋጋሚ የሚፈጸሙት እገታዎች እየተካሄዱ ያሉት ግጭቶች ምን ያህል ወንጀለኞችን እንዳደፋፈሩ እና የሕግ የበላይነትን እንዳዳከሙ ያሳያሉብለዋል።

በአገሪቷ በተለያዩ አካባቢዎች ስለሚፈፀሙ እገታዎች እስካሁን በፌደራል መንግሥቱ በኩል የተባለ ነገር የለም።

በጎንደር ከተማ ስለተፈፀሙት እገታዎች እና ግድያዎች ቢቢሲ ከክልሉ እና ከከተማው ባለሥልጣናት ዝርዝር መረጃ ለመጠየቅ ያደረገው ጥረትም ስልካቸው ባለመነሳቱ አልተሳካም።"

 

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።