"የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ማዕከላዊው መንግሥት በአማራ እና ኦሮሚያ ክልል የሚፈፀሙ እገታዎችን እንዲያስቆም ጥሪ አቀረበ። bbc

 https://www.bbc.com/amharic/articles/cgq2pq1e7ppo

 

3 መስከረም 2024

"የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ማዕከላዊው መንግሥት በአማራ እና ኦሮሚያ ክልል የሚፈፀሙ እገታዎችን እንዲያስቆም ጥሪ አቀረበ።

በሁለቱ ክልሎች ያሉ የሰብዓዊ መብት ሁኔታዎችን እየተከታተልኩ ነው ያለው ኮሚሽኑ፣ በተለይ እገታን በተመለከተ የሚቀርቡለትን አቤቱታዎች ተከትሎ ምርመራ ሲያደርግ እንደቆየ አሳውቋል።

ኮሚሽኑ ይህን መግለጫ ያወጣው በጎንደር ከተማ አንዲት የሁለት ዓመት ሕፃን በአጋቾች መገደሏን ተከትሎ በከተማዋ ቁጣ መቀስቀሱን በተሰማ ማግስት ነው።

ኮሚሽኑ በለቀቀው መግለጫ በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች ካለው የትጥቅ ችግር ጋር በተያያዘ በአንዳንድ አካባቢዎች የሕግ ማስከበሩ በመላላቱ ሰላማዊ ዜጎች በታጣቂዎች፣ በተደራጁ ቡድኖች እና በአንዳንድ የመንግሥት የፀጥታ አካላት የሚደርስባቸው እገታ ተባብሷል ብሏል።

ኢሰመኮ በምርመራው እንደተመለከተው አጋቾች፤ ሰላማዊ ዜጎች ጉዞ ላይ፣ ከመኖሪያ ቤታቸው አልያም ሥራ ላይ ሳሉ ታፍነው ተወስደው የማስቀለቀቂያ ገንዘብ ይጠይቃሉ። አክሎም ገንዘብ መክፈል ያልቻሉ ሰዎችን ግድያን ጨምሮ በርካታ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እንደሚፈፀምባቸው ገልጿል።

እገታዎች ለታጣቂዎች የገንዘብ ምንጭ ሆነዋል ያለው ኮሚሽኑ፣ በሌላ ወቅት ደግሞ ለበቀል ማስፈፀሚያ፣ ለፖለቲካ ዓላማ እንዲሁም የታገተን ሰው ለማስለቀቅ ጥቅም ላይ እየዋሉ እንደሆኑ አትቷል።

በተለይ በሁለቱ ክልሎች በተንሰራፋው የእገታ ወንጀል ምክንያት የዜጎች መሠረታዊ የሚባሉ በሕይወት የመኖር እና የመዘዋወር መብታቸው እየተጣሰ መሆኑን ተመልክቷል።

በተጨማሪም ሴቶች ለመደፈር እና ለተለያዩ ፆታዊ ጥቃቶች እየተጋለጡ መሆኑን ኮሚሽኑ ገልጿል።

ኮሚሽኑ ታጣቂዎች ከእገታ የሚያገኙትን ገንዘብ ተጠቅመው ተጨማሪ የጦር መሣሪያ ሊገዙ እንደሚችሉ በማሳሰብ ይህ ደግሞ ግጭቶች እንዲራዘሙ ምክንያት ሊሆን ይችላል የሚል ስጋት እንዳለው አስምሯል።

ኮሚሽኑ በጋዜጣዊ መግለጫው ባጋራው አንድ ታሪክ ከእገታ ያመለጠ አንድ የደባርቅ ዩኒቨርሲቲ ተማሪን ልምድ በምሳሌነት አስቀምጧል።

ይህ ተማሪ የተሳፈረበት ተሽከርካሪ ገርበ ጉራቻ ከተማ ሲቃረብ በኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት [ኦነግ ሸኔ] ታጣቂዎች ቁጥጥር ሥር ውሎ እንደነበር ይናገራል። ቀጥሎም አንዳንድ የታገቱ ተማሪዎች በዱላ እየተመቱ ወዳልታወቀ ሥፍራ እንደተወሰዱ ተማሪው ለኮሚሽኑ ተናግሯል። ነገር ግን የሚሊሻ ዩኒፎርም እና ሲቪል የለበሱ የመንግሥታ የፀጥታ ኃይሎች ወደ ሥፍራው መጥተው የተኩስ ልውውጥ ሲከፈት እሱን ጨምሮ በርካታ ታጋቾች ማምለጣቸውን አስረድቷል።

ኢሰመኮ ያነጋገራት የደባርቅ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ተወካይ በዚህ ክስተት ታግተው የነበሩ ቢያንስ 50 ተማሪዎች መለቀቃቸውን ተናግራ፣ ነገር ግን አሁንም 7 በላይ ተማሪዎች አድራሻቸው እንደማይታወቅ ገልፃለች።

ተማሪዎች ለማስለቀቂያ እስከ 700 ሺህ ብር ድረስ እንደተጠየቁና ቤተሰብ መክፈል ባለመቻሉ ገንዘቡ ወደ 200 ሺህ ዝቅ እንዲል መደረጉን እንዲሁም 100 ሺህ እስከ 200 ሺህ ብር የከፈሉ ተማሪዎች መለቀቃቸውን ኮሚሽኑ አጋርቷል።

ኢሰመኮ የኦሮሚያ ክልል የሰሜን ሸዋ ዞን አስተዳዳሪዎችን አናግሮ ከታገቱት 156 የደባርቅ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች መካከል እስከ ሐምሌ 2 2016 ድረስ 138 እንደተለቀቁ መስማቱን ዘግቧል።

የኦሮሚያ ክልል መንግሥት የኮሚኒኬሽን ቢሮ ሐምሌ 3 2016 በሰጠው መግለጫ ከታገቱት 167 ተማሪዎች መካከል 160 የሚሆኑት እንዳስለቀቀ ገልጾ ነበር።

ኮሚሽኑ በርካታ ተማሪዎች እና ቤተሰቦቻቸው ባለባቸው የደኅንነት ስጋት ምክንያት መረጃ ለመስጠት ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ ምን ያክል ተማሪዎች በእገታ ሥር እንደሚገኙ ምን ያክሉ ደግሞ እንደተለቀቁ ማረጋገጥ አለመቻሉን አሳውቋል።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በተለያዩ ቀናት በኦሮሚያ ክልል በሰሜን ሸዋ፣ በምስራቅ ወለጋ፣ ደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን፤ በአማራ ክልል በሰሜን ጎጃም ዞን፣ በሰሜን ወሎ ዞን፣ በምዕራብ ጎንደር ዞን እንዲሁም በባህር ዳር ከተማ የተለያዩ እገታዎች እና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች መፈፀማቸውን አሳውቋል።

ኮሚሽኑ መንግሥት በፀጥታ አካላቱ ብቻ ሳይሆን በተለያዩ የታጠቁ ቡድኖች አማካኝነት የሚፈፀሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ለመከላከል እና ተጎጂዎች ፍትሕ እንዲያገኙ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርቧል።

ማዕከላዊው መንግሥትም ሆነ የክልል መንግሥታት በተደጋጋሚ እገታ በሚፈፀምባቸው ቦታዎች ጥበቃቸውን እንዲያጠናክሩ ያሳሰበው ኮሞሽኑ በተጨማሪ የተማሪዎችን ደኅንነት በጠበቀ መልኩ የማስለቀቅ ሥራ እንዲሠሩም አሳስቧል።

በመንግሥት የተቋቋመው ኮሚሽኑ ታጣቂ ኃይሎች ዓለም አቀፍ ሕጎችን እንዲያከብሩ እንዲሁም ከእገታ ድርጊት እንዲታቀቡም ጥሪ አቅርቧል።"

 


አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።