#አለቀ! አበቃ! #መራራ ስንብት። በዲሞሽን ሽኝት። #አናርኪዝም #እራሱን #ያራባል።

 

#አለቀ! አበቃ! #መራራ ስንብት። በዲሞሽን ሽኝት።
 
"እግዚአብሄር በአንድም በሌላም ይናገራል፦
ሰው ግን አያስተውለውም።"
 
አናርኪዝም እራሱን ቢያራባ እንጂ እራሱን የሚቀጣ ክስተት አይደለም። የፕሬዚዳንትነት ሽኝት እና ስንብት ፕሮስጄራሊ እና ለትውልድ አትራፊነቱ ወይንም ኪሳራውን ለመዳሰስ እሻለሁኝ። ምዕራፍ ፲፬ በዚህ መልኩ ይቀጥላል። ከበረገገው ጋር መበርገግ፤ ከቆዘመው ጋር መቆዘም፤ ከሚርገበገበው ጋር መርገብገብ፤ ከዘበጠው ጋር አብሮ መነከር ፈቃድ አይሰጠውም። 
 
#ሰሞናቱ እና ትዝብቴ። 
 
የክብርት ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴን የሥራ ዘመን ቀድሞ መጠናቀቅ አስተዋልኩኝ። በብዙ ውስብስብ የፖለቲካ ዕድምታወች የተተበተበ ነው። ወደዛ የመግባት ፈቃድ የለኝም። እኔ እማነሳው ሥርዓታዊ አፈፃፀሙ ወይንም ፕሮስጂራሊ የተጠያቂነት እና የኃላፊነት ጣሪያ እና ግድግዳ በአስተውሎት መግለጽ ነው። 
 
ሥልጣን ላለው መንግሥትም፤ በለስ ቀንቶት ለሚተካውም አስፈላጊ ስለሆነ። ስለሆነም የአንድ አገር ሥነ መንግሥታዊ ሥርዓት ለአገር ክብር፤ ሞገስ እና ፀጋ ተክሊል ነው። ስለሆነም አካሄዱ ላይ ማተኮር ነው የምሻው። ኦ! መራራ ስንብትን ካነሳሁ ዘንዳ ፕ/ በዬነ ጴጥሮስ የሚፈቅዱት ኃላፊነት የነበረ ይመስለኛል የአገር ፕሬዚዳንትነት። በነበር ቀረ እንጂ።
የሆነ ሆኖ ጓዘ ቀላል ጥያቄ ላንሳ። ጥያቄ ህሊና ላለው #ቅን እና #ቀና ዜጋ በሙሉ ነው። 
 
1) ክብርት ፕሬዚዳንት ወ/ሮ ሳህለወርቅ ዘውዴ ሲሰናበቱ ከቀናቸው ቀድሞ ነው። ይፋዊ ዘመናቸው አልተጠናቀቀም። ይህ ለምን ሆነ? ጥድፊያው ስለምን ይሆን? ይህም ይሁን አምስት ዓመት ተሳስቼ አይደለም አምስት ዓመት ያልኩት፤ በሥራ ዘመናቸው በሙያ ያገለገሎ ደጎስ ያለ ተመክሮ፤ ዘለግ ያለ ብሄራዊ እና ዓለምዓቀፋዊ አገልግሎት ያበረከቱ፤ ሊቀ - ሊቃውንት፦ በሰብዕናቸው #በዲፕሎማቲክ #ዲስፕሊን የታነፁ፤ እናት፤ እህት፤ ሚስት፤ አክስት፤ #ምልክት፤ ግሎባል ተምሳሌ፤ የብቃት #መለኪያ፤ የተመክሮ አድማስ በዚህ መልክ ሲሸኙ የፓርላማው ጉዳይ ገርሞኛል። ደንቆኛልም።
 
ቢያንስ ያ የፌድሬሽን እና የፓርላማ ታዳሚ ከመቀመጫው #ብድግ ብሎ ቢቀበላቸው፤ ከመቀመጫው ተነስቶ #በክብር ቢሸኛቸው ምን ነበር? ይህ ሁለመናዋ ጥበብ ለሆነች አገር በሴቶች ልቅና አንቱ የተባሉ አናት ሲሰናበቱ ታሪክ ለትውልድ የሚፃፈው በከበረች አገር የከበረ ተግባር ሲፈፀም ነው። ፓርላማውም ይሁን የፌድሬሹኑ አባላት እራሱን #እንደቀበር ይሰማኛል። 
 
ትልቅ አገራዊ በጎ ህሊና፤ ቅን መንፈስ አልፎታል፤ አምልጦታልም ብዬ አስባለሁ። ልጆች ከሚሰሙት ይልቅ በሚዩት ነገር ይማራሉ። ይመሰጣሉ። ይተማመናሉ እና። በዚህ የሥልጣን ሽግግር ዕውነትን፤ ፋክትን፤ የአገርን ሉዓላዊነት እና ልዕልና፥ የሚነበብት፤ የሚተረጎምበት፤ የሚመሳጠርበት ትልቅ አጋጣሚ እንዲህ እንደ አልባሌ ገጠመኝ #ዳጥ እና #ልሙጥ ሆኖ አለፈ። 
 
በእያንዳንዷ ብሄራዊ ጉዳይ #ትውልድን ማሰብ ይገባል። ለቀጣዩ ትውልድ #የቤት ሥራ መስጠት ይገባ ነበር። ለእኔ ሥርዓቱ #ዝርግ እና #ልሙጥ ሆኖ ነው ያዬሁት። ጥንቃቄም ስልትም የነጠፈበት። "የእነ ቶሎ ተሎ ቤት ግድግዳው ሰንበሌጥ።" ለእኔ በጠፋ ጥፋቶች፤ በሚጠፋ ጥፋቶች፤ ወደፊትም በሚሠሩ ግድፈቶች ውስጥ ሆነ መልካም ክንውኖች ቢያንስ ለትውልድ፤ ለታሪክ፤ ለአደራ #ቅርብ አለመሆን የኢትዮጵያ የፈተና ጣሪያ ይመስለኛል።
 
2) ለእኔ ክብርት ወ/ሮ ሳህለወርቅ ዘውዴ የአገልግሎት ዘመናቸው አምስት ዓመት እንደሆነ ይሰማኛል። በለማውም በጠፋውም ጉዳይ ኃላፊነት እና ተጠያቂነት ከኖረ 5: በዓምስት ዓመት የሥራ ዘመናቸው ሊሆን ይገባል። ምክንያቱም ቤተ - መንግሥት ተቀምጠው፤ ፕሮቶኮሉ ተሟልቶ፤ በጀት ተመድቦ፦ የፕሬዚዳንት ቢሮ ተደራጅቶ ሙሉ ድፍን 5 ዓመት እያሉ፤ እዬነበሩ #አልነበርሽም#የለሽም የሚል ዕውነት ነው ያዬሁት ፕሮስጄራሊ ጉዳይ  
 
#በመፋለስ ነው እራሱን የገለጠው።
? #ለምንድን ነው አደብ የተሸሸው?
?#ስለምን አቅለቢስ ተሆነ?
?#ምንስ የሚያጣድፍ ነገር ኖረ???
 
ግጥግጥ፤ ሠርግና መልስ የሚመስሉ ክስተቶች ከምርጫው ውጤት ሹመት እና ሽልማት በፊትም በወቅቱም አስተውል ስለነበር እንዲህ አይነት ድንገቴ ማዬቴ ቢገርመኝም፦ አልፎ አልፎ ክብርት ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴን ብሞግትም ከሰባዕዊነት አንፃር፤ ከአጽናኝነት ሁኔታ ጋር፦ መጨረሻው የከፋ፦ ትውልድ ሊማርበት የሚችል ፋይዳ ሳይኖረው ተደመደመ። ፕሬዚዳንቷ #ተቀደሙ። ብዙ የዊዝደም ቀናቶች አላፏቸው። 
 
አልፎ አልፎ በሚያነሷቸው ነጥቦች ልክ ቆርጠው ከውሳኔ ደርሰው ቢሆን ክስተቱ አናባቢ የመሆን አቅም ይኖረው ነበር። የዳበረ፦ የተደላደለ ሰብዕና ስላላቸው ዕድሉ ባያመልጥ መልካም ነበር። 
 
ተጠያቂነት እና ኃላፊነት በሚመለከት አንድ ዓመት ስለተቀነሰላቸው ዕድለኛ ናቸው። በ2016 (2024) አልነበርሽም የሚል ውሳኔ ስለተወሰነላቸው። መርጉን የተሸከሙት ክቡር አዲሱ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ ግን እንደ #ምርቃት ያዩት ይመስላል። ገራሚው ክስተት ይህ ነው። 
 
ባልነበሩበት ጉዳይ ቆፍጠን ብለው ዘገባውን ሲያቀርቡት የፍትህ ያለህ ብያለሁኝ። ሊሆን ሊደረግ የማይገባው የታሪክ እጥፋት ነው የተፈፀመው። እንደ መንግሥት አቅምም፦ አቅል ቢኖር መብቱ የክብርቷ ነበር። ህጉም ሥርዓቱም ያ ነው። አንድ የአገር ጠሚር በጥቃቅን ጉዳዮች ላይ አገር ተሸክሞ አኩራፊነቱ ህግ ጣሽ ሲሆን ማህፀንን እንደ ዱባ ይቀረድዳል። አንድ ሰዓት ለማይሞላ ኢቬንት እንዴት መታገሥ አይቻልም??? ይህን ያህል በህግ ጥሰት መጪ ብሎ እራስን ከማጋለጥ። 
 
3) ለእኔ ለክቡር ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ ስዬማ ሳይሆን ምደባ ነው። ሹመት ሳይሆን #ዲሞሽንም ነው። ክብር ሳይሆን ማግለያ በደህንነት በታጠረ የቁም እስር ነው። ያ ሁሉ ተመክሮ እንዲህ ተፍተልትሎ ሲቀርብ ያሳዝናል። ከካቢኔ ውጭ ሆኖ መቀመጥ ዕድገት አይደለም። ከፖለቲካዊ ዓለም ዓቀፍ ፋክት ጋርም መፋታት ነው።
 
መጣያ ሲታጣ የሆነ ቦታ ተፈልጎ መሸጎጫ ለመሸጋገሪያ ምቹ መሆን ለቆፍጣናው ኢትዮጵያዊነት መጣኝ አይደለም። ። የፕሬዚዳንትነት ቦታ ለሴሪሞኒያዊ ጉዳይ ብቻ ስለሆነ ለመቀመጥ መቀመጥ መማሩ፤ #መላቁ፤ ደርባባ ተመክሮ ማካባቱ ለምን እና ለማን ይጠቅማል? ለትውልድ? ለታሪክ? ለአደራ??? ከጠቅላይ ሚር ቦታ ቀጥሎ ያለው እኮ የውጭ ጉዳይ ሚር ነው። ነፃነቱ - ከኖረ። 
 
እንዲያውም በጠሚ አብይ አህመድ ዘመን በቂ ዕውቅና ያልተሰጠው ቦታ ነበር ማለት ይቻላል። አንድ ሰው ምክትል ጠሚር እና ውጭ ጉዳይ ሚር ሆኖ ሲላገጥበት ነበር የተባጀበት። አብዛኛውን የዲፕሎማሲ ተግባር የውጩ ዲያስፖራው ነው ሲከውነው የኖረው። ግደፈቱን በማረም ላፒስ የነበረው ዲያስፖራው ነበር። ያረገረገ መከራ ነው የነበረው። ባልሰከኑ ክስተቶች ስንት ጥላሸት ተስተናገዱ? 
 
ሁልጊዜ ጥገና እና ጋራጅ ውስጥ ነበር የከረመው ተቋሙ። አሁን እንደ ጽኑ የብልጽግና መንገድ ደጋፊ ፕ/ ዶር ብሩክ ኃይሌ ዓይነት ሊቃናት ውጭ ጉዳይ ሚር በባለሙያ እዬተመራ ነው የሚለው መንፈስም #ጨነገፈ። ከምኔው እንዲህ ድብልቅልቁ ወጣ? ለሰሚም ግራ ነው። የእርስወም ይሞክሩት የዳማ ጨዋታ ነው የሆነው። በጣም የተማመኑበት ፕ ብሩክ በቀጣይ ምን አልባት እሳቸው ካልታጩበት። እንደ አመሉ ያፈሳል። 
 
4) በዬትኛው አገር ልምድ ይሆን በቦታው ያልነበረ ሰብዕና በተሰዬመበት ቅጽበት ባልነበረበት የኃላፊነት፤ የተጠያቂነት ቦታ ሳይኖር በምናብ በህልሜ ፕሬዚዳንት ሆኜ አገልግያለሁ፥ ለዛውም ውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነቱንም ደርቤ ብሎ ያልነበረበትን ዘገባ ሊያቀርብ እንደምን ይችላል??? የህግ ጥሰትም ነው። 
 
ስለሆነም የአዲሱ የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት የሥራ ዘመን ትናንት ሳይሆን የተጀመረው ከ2016 እኢአ ጀምሮ ነው ብዬ መደምደም እችላለሁ። ከ2016 እኢአ(2023) ዘመን ጀምሮ ሲቆጠር ለፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ ሁለተኛ የሥራ ዘመናቸውን ጀምረዋል። በ2016(2023) ለለማውም፤ ለጠፋውም፤ ለወንጀሉም፤ ለሽልማቱም ኃላፊነቱን እና ተጠያቂነቱን ፈቅደው እና ወደው ለወሰዱት አዲሱ ፕሬዚዳንት እግዚአብሄር ጥናት መቀነቱን ይስጠወት ማለት እሻለሁኝ። እግዜብሄር ያጽናወትም። አፈ ጉባኤው እንዴት እና እንደምን እንደሆኑም ሙሉ ግብረ መልሱ ይገልጥ ነበር። ሰው ሰው መሆኑ ቀርቶ እንደ ማንኛውም ዕቃ በሰው እጅ ሲንከላወስ መጥኔ ለአገረ ኢትዮጵያ እና ለትውልዱ ያሰኛል። ጥሰት አገርን ሲመራ እግዚኦ ነው። 
 
5) ልምድ ምንድን ነው? ተመክሮስ ምንድን ነው? ለሥርዓት መገዛት ከተሳነው? ፕሮሲጀራሊ ያዬሁት ፍፁም የሆነ አናርኪዝም ነው። የመርኃዊነት ሙሉ ጥሰት ነው የተፈፀመው። ለዛውም የገዘፈ። መከበር በመርኽ ነው። ያ ኢትዮጵያ ለአዲሱ ፕሬዚዳንት ያፈሰሰችው ጊዜ፤ መዋለ ንዋይ ጥበብ ሁሉ እንደፈሰሰ ነው የምቆጥረው። ዕድሜውን ሙሉ ለተጋ ባተሌ እንደምን ተጽፎ የተሰጠውን አንብቦ አንበሳ፤ አንበሳ ልሽተት ይላል???? 
 
ዘገባውን ጠሚር አብይ አህመድ አሊ ቢያነቡት ያምርባቸው ነበር። እራሳቸውን አስመራጭ ኮሜቴ አድርገው ያስመረጡ፦ የሥርዓት ጥሰት በፓርቲ አደረጃጀት መርሆ ጨፍላቂነት ከውጥኑ እስከ እርገቱ ስላዬሁኝ፤ የለመድነው ስለሆነ አይደንቅም ነበር። ሃግ የሚልም የለም። የምርጫ ቦርድም የጥሰት ተባባሪ። 
 
በዚህ የሥርዓት ጥሰት ውስጥ ትውልድ እንዴት በሥርዓት መገንባት ይቻላል ነው ጭብጤ። እጅግ በስመ አብ እስክል ድረስ የገረመኝ ግን ነባሩ የውጭ ጉዳይ ሚ/ር፤ የዲፕሎማት ሰብዕ በዚህ ዝብርቅርቅ፤ ዝንቅንቅ፤ ዝልግልግ ጉዳይ መነከራቸው ነው። እኔ ዕውነት ለመናገር ወደ አገር የተመለሱበት አመክንዮም አላሳመነኝም ነበር። የሰውነት፦ የተፈጥሯዊነት ማዕከላዊነት ከተናደ ምኑ ይናፍቃል - ሹመትስ፦ ሽልማቱ? እንደ ሽሮ ትክተካ በአፍላ ለሚከንፍ ፍላጎት ይህን ያህል ማረግረግ ለዬትኛው ዕድሜ?
 
ከሁሉ የገረመኝ የጋዜጠኞች፤ የሚዲያ ሰወች ጉዳይ ነው። " ኃይል የመጠቀም መብት ከእንግዲህ የመንግሥት ብቻ ነው" አሉ አዲሱ የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት። ኧረ በህግ???? በትርጉም ቢቃና ይህን ያሉት ጠሚር አብይ አህመድ ቢባል ያስኬዳል። #ዕብለትን #ማቅበጥ #ፋክትን #ማቅለጥ ሆኖ ነው ያገኜሁት። ቤቴ እስኪነቃነቅ ድረስ ነበር የሳቅኩት። እርእሱን ገና ሳዬው። ለሚዲያ ብልጭልጭታ ይሆናል። በሥርዓት ጥሰት የሚገነባ ትውልድ የለም። ትርፋ አናርኪዝም ነው። 
 
ህዝባችን አሳሩን እያዬ ያለውም በዚህው መንገድ ነው። ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ ይህን አሉ፦ ያን አሉ ?? ባልነበሩበት? በሌሉበት? ለዛውም የጠሚ/ር ንግግር ቢሆን የፖሊሲ ምንጭ ሊሆን ይችላል ይባል። የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት ምን አቅም አለውና??? ለመሆኑ አዲሱ ፕሬዚዳንትነት ዘመኑ ዕድሜውስ ምን ያህል ይሆን? በህይወት መኖሩ ከተፈቀደ???
በዚህ ሥርዓተ- አልበኝነት አካሄድ፤ በሥርዓት - አልበኝነት አመራር ውስጥ ፍትህ- ዕውነት -:መርኃዊነት - ሞዴል ማጣት ለማግሥት ድርቀት ነው። 
 
ጉዳዬም ይኽው ነው ማፍለስ። እኔ የተሾመ ቢሾም፤ የተሻረ ቢሻር አጀንዳዬ አይደለም። በሂደቱ ትውልድ ምን ያተርፍበታል ነው ጉዳዬ። አትኩሮቴ። ጥሪዬም። ለባለ ሚዲያወች እማሳስበው ግን ፋክት መር፤ ሙያ መር ቢሆኑ ትውልድ ያተርፋል። በስተቀር ጥረቱ የቹፌ እከክ ይሆናል። የቹፌ እከክ ቀን ይሰወራል፣ ማታ ደም እዬተፋ አቅል ይሰውራል። ከኢትዮጵያ ፖለቲካ ጋር ሥርዓተ - አልበኝነት መንፈስ የተገባ አይመስለኝም። አወዳደቁም ቅርስ ውርስ አልባ መራራ ስንብት ነው እዬሆነ የታዬው። ካለፈው አለመማር።
 
ሪፖርቱን በሙሉ ነው ያዳመጥኩት። የጠቅላይ ሚር ቢሮ ያዘጋጀው ዘገባ ነው። ስለሆነም ለአዲሱ ፕሬዚዳንት ልጥፍ እንጂ ውህድ አይደለም። ውራጅም ነው። ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስተርነት ማግለያ ሽተዋል። ፈልገዋል። ቀድመው የገዘፈ ግን ያልተገለጠ ፖለቲካዊ መሰናዶም ድርጊትም ፈጽመዋል። እራሱን ያጨም ከነበረም እንደሚሆን አድርገውታል። ይህ የማግለያ ቦታ ለቀደመው የውጭ ጉዳይ ሚር የታጨ ነው። ሌላው ትርፍ ነገር ነው። ማሟሟቄያ። ለውጭ ጉዳይ ሚር ቦታ አዲስ እጮኛ አለ። በኽረ ጉዳዩ ይህ ነው። 
 
ለዚህ ነው እኔ ዘመኑም // ጠቅላይ ሚኒስተሩም አሳቻ ናቸው ብዬ ለረጅም ጊዜ የፃፍኩበትም፤ ያመንኩበትም። ጥያቄው ለውጥ ፈላጊው ይህን ቀድሞ ታቅዶ የሚከወን የፖለቲካ ሂደት የሚመጥን አቅም አለው ወይንስ በድንገቴ አጀንዳ አውሎ መናጡ ይቀጥላል?????ለውጥ መሪ፤ ለውጥ አቀናጅ፤ ለውጥ አደራጅ ካለ ጥያቄዬን ባይመልስልኝም እራሱን ይገምግም።
 
ከሁሉ መስውዕትነት ቀንሶ ለትውልድም // ለአደራም የሚሆን አቅም ይጠንሰስ፤ ካለም ይደርጅ። ህዝብ ስቃይ ውስጥ ነውና። ሥጋቱ፤ ፍርኃቱ ምርጫ ከመምጣቱ በፊት በጫን ተደል በነፍስ ወከፍ ስለሚታደል። መራራ ስንብቱም በአበባም፦ በሜዳልያም፦ በዕንባም እንዲሁ። 
 
መሰናዶው ለቀጣዩ ምርጫ፤ የአላህ የእግዚአብሄር ፈቃድ ለኢትዮጵያ ፖለቲካ አጀንዳ አይደሉም። ማዘን፤ አጽናኝነት እና አይዟችሁ ባይነትም እንዲሁ። ተፈጥሯዊነትም ጥሰቱ ቀጣይ ነው። ትውልድ ይታሰብ። ማግስት ይታቀድ። ሥርዓት ይከበር። አናርኪዝም እራሱን ያራባልና በሥርዓት ለመራመድ ይወሰን። በየትኛውም ሂደት መርኃዊነት አጀንዳ ይሁን እንላለን እኔ እና ባተሌዋ ብዕሬ።
 
የእኔ ክብሮች ቸር አስበን፤ ቸር እንሁን።
ቅን አስበን፤ ቀና እንሁን።
ከፖለቲካ ወጀብ ጋር ከመንጎድ በራሳችን ጥሪ ላይ በጥሞና፤ በአቅል እና በዲስፕሊን እንቁም።
 
 ኑሩልኝ። ደህና እደሩ። አሜን። ምዕራፍ ፲፬ በዚህ መልኩ ይቀጥላል። መኖሩ ከተገኜ።
 
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
08/10/2024
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።
#አናርኪዝም #እራሱን #ያራባል።

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።