ዘመነ ቤርሙዳ ትርያንግልን ለመመከት #ጥንቃቄ በአደብ ይጠጣ። ኢትዮጵያ የከበደችን ለሁላችንም ነውና።
ዘመነ ቤርሙዳ ትርያንግልን ለመመከት #ጥንቃቄ በአደብ ይጠጣ። ኢትዮጵያ የከበደችን ለሁላችንም ነውና።
"የቤትህ ቅናት በላኝ።"
#እፍታ።
ወጀቡ አዬለ። አቅጣጫውም ድብ አለበት እናም ዘለግ ያለ ሃሳቤን ማጋራት ፈለግሁኝ። ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ አሊ ከመጡ ጉዳዬን በምዕራፍ ከፋፍዬ ስለምሰራ አስረአራተኛው ምዕራፍ ላይ እንገኛለን። ለቅኖች ለማስታወስ።
ፁሁፋ ዘለግ ያለ ነው። ለፌቡ አይሆንም። ግን ብሎግም ስላለኝ ለዛም ጭምር ነው እምሰራው። ለወሳኝ ፖለቲካዊ አቅጣጫ በጭልፋ የልብ አያደርስም እና ተያያዥ ጉዳዬወችን አክዬ፦ ወይንም እያጣቀስኩ አብረን እንሁን ስል ትህትናዊ አክብሮቴ ይጠይቃችኋል - ክብረቶቼን።
#ውስጤ።
ጥንቃቄ ያተርፋል እንጂ አያከስርም። ከአንደበት ጀምሮ ማናቸውም ኩነታችን ጥንቃቄ ይመራቸው ዘንድ ከእያንዳንዳችን በግል፤ ከሁላችን በጋራ የሚፈለግ የወል መስመራችን ሊሆን ይገባል ባይ ነኝ።
የትናንቱ የአዲስ አበባ የሽብር ክስተት አሳቻው ዘመን እና አሳቻው መሪ ዶር አብይ አህመድ አሊ ከመጡ ጀምሮ የተኖረበት የአዬር ፀባይ ነው። ባለመታደል። ትጋታችን መራራው የህዋህት ዘመን፤ በዘመናዊ የሽብር አገዛዝ እንዲሸጋገር አልነበረም። ቲም ገዱ ጥረታችን ለስልጣን አልታገልንም ብሎ በአፍጢሙ ከነበለው - እንጂ። አሁንም አዳኛችሁ ነኝ ሲል አዳምጣለሁኝ። የፊተኛውን በምን ቀበርከው በሻሽ፤ የኋለኛው እንዳይሸሽ"
ነገረ ኢትዮጵያ ከአንድ ጠቅላይ ሚር፦ ከአንድ ዩቱበር፤ ከአንድ ተጽእኖ ፈጣሪ፤ ከአንድ ጋዜጠኛ፤ ከአንድ ፖለቲከኛ፤ ከአንድ የፖለቲካ ድርጅት፤ ከአንድ ባለ ተመክሮ፤ ከአንድ አራት ዓይናማ ተናጋሪ፤ ከአንድ የዩትኛውም ደረጃ ተሸላሚ በላይ ነው። ኢትዮጵያኒዝም ፍልስፍናም፤ ሳይንስም፤ ዩንቨርስም፤ በመደበኛ ትምህርት ቤት ገብተው ሊማሩት የሚገባ ተፈሪ ግን ተወዳጅ ሳቢ ክስተት ነው። የእውቀትም ዘርፍ ነው። ሁሉ ያለው ለአለም ብቁ አብርክቶ ያለው ድንቅነት።
ስለሆነም ለጨዋታ ማሟያ፤ ለደጋፊ የመወድስ ክምር ተብሎ ኢትዮጵያዊነት ሊንጓጠጥም፤ ሊቃለልም አይገባም። "ኢትዮጵያ አቅም የላትም" የሚል ደፋር ድምጽ በዓውደ ምህረትህ ስትሰማ እንደ አንበሳ ልታገሳ ይገባል። ሊቆጠቁጥህ፤ ሊነዝርህ ይገባል። "ኢትዮጵያ የሚለው ስም ካልተመቼ እንቀይረዋለን" የሚል የታበዬ ቅንጡ ድምፀት በመድረክህ ደፍሮ ስትሰማ የከንቱ ሃሳቡን ስሜት አከርካሪ ሰብረህ ወደ እንጦርጦስ ልትልከው ይገባል። እውን ኢትዮጵያዊ ደም ከውስጥህ ከኖረ። ጀግንነት የዱር ቤተኔት ብቻ አይደለም እና።
እርግጥ ነው ይህ አሳቻ ዘመን የተመቻቸው፤ አብረውም ቀለበት ያሰሩ የሚያደንቁ፤ የሚወድሱ፤ ቅኔ የሚዘርፋለትም፦ ይህን የምጣትን ዘመን የሚንከባከቡ፤ ይህን የሚያፀድቁ ወገኖች እንዳሉ እሙን ነው። መብት ነው። ለዴሞክራሲ ለሚታገል ሰብዕና አሻሮውን ሃሳብም ገዢ ሆነ አልሆነ ማስተናገድ ግድ ነው። ሳይበሳጩ፥ ሳይግረጨረጩ በትእግስት አድምጦ በልኩ ማስታጠቅም ይገባል።
በአንፃሩ ይህ መንግስታዊ የሽብር ፖሊሲ ለትውልድ፤ ለፓን አፍሪካኒዝም፤ ለቡኒ ዓለም ዓቀፍ የፖለቲካ መገለጫ ሊሆን አይገባም ብለን የምንሞግት ሰወች ደግሞ አለን። እማዬው የአናርኪዝም ጠረን ነውና። ምሳሌ ላንሳ። እኔ ለመልካም ነገር እንኳን ሰርፕራይዝ የሚሉቱን ነገር አልወደውም። የረጋ፤ የታቀደ፤ የሰከነ ክስተት ነው ነፍሴን የሚገዛው።
ብቻ ከዚህ ላይ እማሳስበው መሪወች ከሌላ አገር መሪ ጋር ጫጉላ ላይ ሲሆኑ፤ ሲፋቀር አብሮ #እፍታ፤ ሲኮራረፍ ከንፈርን ዳቦ ማድረግ ለህዝባዊ ግንኙነት መልካም አለመሆኑን አስታውሼ፦ ውህድ ማንነት ላላቸው ወገኖቻችንም ጨዋነትን ብናዘክር ጥሩ ነው።
በሌላ በኩል ኢትዮጵያ ትናንት የነበረች ደልዳላ ቀደምት ልዕልት፤ ዛሬም ያለች መቅድም እመቤት፤ ወደፊትም የምትኖር እቴጌ ረቂቅ መንፈስ ያላት የዊዝደም አንከር አብነታዊ አገር ናት። አቅሟም የሚሰፈር እንደ - እህል፤ የሚለካ እንደ መሬት - በጋሻ፤ እንደ ነዶ - በሜትር የማይመተር የምዕት ቅኔ ናት። #ስዋሰውም። ጠቃሚው ጉልላታዊው አመክንዮ ትውልድን ማዋህድ ነው ለግሎባላይዜሽኑ ዘመንም የሚያግዘው። ለዚህ ደግሞ ሰላምን እንዲመራ መፍቅድ። ህግ አለመተላለፍን ማጽናት።
#ዛሬ እና ጉዳዩ ምልሰታዊ ቅኝትም።
የሆነ ሆኖ የኤርትራ መንግስት ሁሉን ትጥቅ አስፈትቶ ስለምን የኦነግን ሠራዊት ትጥቅ ሸልሞ እንደላከው የሚያውቀው እሱ እራሱ ነው። ሰሞኑን ደግሞ የኤርትራ መንግስት የኢትዮጵያን የችግር ምንጭ በጎሳ ህገ - መንግስት ስለመሆኑ፤ መፍትሄውም ከዛ መላቀቅ ስለመሆኑ አዘክሯል። የነፃ አውጪ ግንባር መጠለያ ከመሆን እስከ አስታጥቆ በአደባባይ መላኩንስ እንዴት አይቶ ይሆን የሚል ልባም፦ ጓዘ ቀላል ጥያቄ በአክብሮት ለኤርትራ መንግስት አቀርባለሁኝ።
ወደቀደመው ሃሳቤ ስመለስ ካስታወሳችሁ አቶ ለማ መገርሳ (ዶር) እና ዶር. ወርቅነህ ገበዬሁ ነበሩ ተደራዳሪወች። ሁለቱም ኦህዴዶች ነበሩ። የዛሬን ባላውቅም። ኦህዴዶች ወደ አስመራ ሲጓዙ ዜናው ጎልቶ፥ ደምቆ ነበር። ሲመለሱ ዜናው ጠፋ። ወይንም ተሰወረ። ለምን ብዬ ጠዬቅሁ። ጉልበቴ ብዕሬ ስለሆነች ፃፍኩኝ። ስምምነቱን እንወቀው ብዬም።
ለነገሩ የፕሬዚዳንት ኢሳያስ እና የጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ ለኖቤል ያበቃ ስምምነትም ተከዝኖ ነው የቀረው። የኬኒያውን የህወሃት እና የጠቅላይ ሚር አብይ የግል ስምምነትንም ህዝብ አያውቀውም። የሚታወቀው የደቡብ አፍሪካ ብቻ ነው። ያም ኃያሏ አሜሪካ እና አፍሪካውያን ስላሉበት። እሱም #ለፈንድ የታጨ ግጥግጦሽ ይመስለኛል።
ይህም ቢሆን አድኑኝ፤ ታደጉኝ ብሎ የተማፀነው አብይዝም፤ ለህዝቡ የስምምነቱ መንፈስ ተብራርቶ፤ ተተርጉሞ እንዲያውቀው አላደረገም። ደም ተገበረ። ሂደቱ ግን????
የአሁኑም የጃል ሰኒ እና የአቶ ሽመልስ አብዲሳ ስምምነት ምን እንደሆን አይታወቅም።
የተገበረው ተገብሯል በአሰቃቂ ሁኔታ። ሰቆቃው አማራ እና ሰቆቃው ኦርቶዶክስ ተዋህዶ። የተቃጠለው በቁሙ ተቃጥሏል። ኑሮው የተበተነው በግፍ ባበጃት አገር ተበትኗል። አጣዬ ለ10 ጊዜ ነዳለች። የሽዋ ሮቢትን አስራት ሚዲያ ከቦታው ሲዘግብ ለኦነግ ታጣቂወች ሙሉ የሎጅስቲክስ ድጋፍ ይሰጥ እንደነበረ ዘግቧል። የእርዳታ አገልግሎት መስጫ ትራንስፖርት ለኦነግ ታጣቂወች እንደነበረ ዘግቧል።
በኦሮምያም በስሜን ሽዋ የኖሩ ከተሞችን ማውደም፤ ህዝቡን ከባዕቱ መንቀል ፕሮጀክቱ ኢትዮጵያን #ለሙጦ አዲስ ኦነግ ሰራሽ ብልጭልጭ መሰንቀር ነው። ፀጥ ያለ ጫና፤ ፀጥ ያለ መስፋፋት፤ ፀጥ ያለ መዋጥ የአሉታዊ ዴሞግራፊ ፕሮጀክት ነው። ነባሩ እንደአለ ማስቀጠል፤ አዲሱንም ማስጀመር ሲቻል። በዬዘመኑ የፈሰሰው የህሊና፤ የፋይናስ፤ የፀሎት የድዋ በረከትም ስንቅህ አመድ ይሁን ተብሏል በአሳቻው ዘመን።
ብልሁ ጉዳይ አገር እኮ #በቀደመ ህዝብ ይበጃል፤ ታሪክም #በቀደመ ህዝብ ይፃፋል። በእኛ ግን ዘመን ተዘቅዝቆ የተሰቀለበት ሁነት ነው በየዘመኑ የሚታዬው። የቂም ክምችት የበቀል ግንባታን ያመጣል። በዬዘመናቱ ግብር አለ። ለዛውም የሰው ግብር። #የትርታ ግብር። ለነገሩ የጠቅላይ ሚር አብይ መንፈስ ህወሃት ደርግን ሲተካ የነበረው ኩነት እንዲመለስ አድርጎ ነው የቀረፀው። መንፈሱ እራሱ የጫካ አቅም እንዲኖር ታስቦ፦ ታቅዶ የተከወነ ነው ብዬ ነው እማስበው። በወቅቱም ጽፌበታለሁ።
ለ2013 ዓም ምርጫ የኦህዴድ ልዩ ሃይል ተሰናዳ፤ ምርጫው #በሽብር ጫና ተከወነ። ዓለም ዓቀፋ ማህበረሰብ፤ የእኛ አራት ዓይናማ ፖለቲከኞች ሳይቀሩ ምርጫው በሰላም ተከወነ ብለዋል። ጉዝጓዙ በሽብር፤ በስጋት፤ በጭንቀት ጥድፊያ ስለመከወኑ ያገናዘበ አልሰማሁም። የትኛው የተደራጄ የፖለቲካ ድርጅት ኑሮ ነው የሚያሸንፈው? ደንብ፤ ፕሮግራም፤ መሪ እቅድ፤ ጠቅላላ ጉባኤ የሌለው የዞግ ፓርቲ "ብልጽግና" እንዴት ሊያሸንፍ ይችላል? የጨነገፈ እኮ ነው። ሳይፈጠር የሞተ። በውራጅ አባላት እኮ ነው አለሁ ያለው። በዛገው የኢህአዴግ መንፈስን ወርሶ።
የሆነ ሆኖ የሰኒዝም ሰራዊት ደግሞ የቀጣዩ ኦነግ መራሽ "ብልጽግና" የሽብር ዓውደኛ ሆኖ ለቀጣዩ ምርጫ አህዱነት ነው የታለመው። አንድ ሁለት ያላስተዋላችሁት መራራ ስንብቶችም ነበሩ። ከዚህ የቀደሙ።
የሆነ ሆኖ ወደ ቀደመው ጉዳዬ ስመለስ አቶ ዳውድ ኢብሳ "ማን ትጥቅ ፈቺ፤ ማን ትጥቅ አስፈች" ያሉት ንግግርን አስመልክቶ እኔ ስጋቴን ፃፍኩኝ - በወቅቱ። ጋዜጠኛ ሲሳይ አጌና በኢሳት ሚዲያ ስጋት እንዳይደለ ሞገተ። የእኔን ሃሳብ የተጋራው አቶ ኤርምያስ ለገሰ ነበር። ሁለቱም የተሟገቱት በኢሳት ሚዲያ ነው። ኢሳት ክብራቸውም ሞገሳቸውም ነበር። እኔ የግል ታጋይ ስለሆንኩኝ ብዕሬን ይዤ ነው እምታገለው። እርግጥ ነው የፀጋዬ ራዲዮም፤ ብሎጌም ይታደማሉ። ያን ጊዜ ደጉ ዘሃበሻ እና ደጉ ሳተናው ድህረ ገጾችም ያግዙኛል። ወጀቡን ችለው።
የጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ መንግስት ወደ ስልጣን ሲመጣ በሰማይ ምልክት ነበር። ሌሊት ነበር ውጤቱ የታወቀው መጋቢት 18/2010 ዓም። ፍጥጫው የተቋጨው። በዛ ሌሊት ከመቀሌ አቅራቢያ የመሬት መራድ ታዬ። አድምጡት ብዬ የአጤ ሚኒሊክ ዘመነ መንግስትን ታሪክ አጣቅሼ ፃፍኩኝ። በተከታታይም ሰማይ ይናገር ነበር። በጉራጌ ዞን የመሬት መከፈል፤ ያልተለመደ የሰማይ ደወል ተከስቷል።
ጠቅላይ ሚር አብይ የ100 ቀን ትጋት ላይ እያሉ። አድማጭ ጠፋ እንጂ። ማድመጡ ጥንቃቄን እንድንጠጣ ይረዳን ነበር። አጓጉል አቅም እንዳናፈስም ያግዘን ነበር። ከቋያ ፀፀትም ያድነን በነበረ። የበረከተ አደብ እንድንገዛ ሟተት ይሆነን ነበር። በዬትኛውም ሁኔታ የሰማይ ምልክቶች ቢደመጡ #አቅል እንዲኖረን ይመክራል። ይህም መታደል ነበር።
እኔ እንደማስበው ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ አሊ ኢትዮጵያ ከተፈጠረችበት እለት ጀምሮ ያለፈችበት በጎም ይሁን ፈታኝ ወቅቶች ሁሉ እሳቸው #የነበሩበት፤ ከመፈጠራቸው በፊት በኢትዮጵያ ግንባታ፤ ሥርዓተ - መንግሥት ሁሉ እንደነበሩ ነባሩን ትውፊት እዬፈነቀሉ እሳቸውን ማስቀመጥ የሚተጉበት ተግባር ስለመሆኑ ቀደም ባሉት ፁሁፎቼ አመላክቻለሁኝ። ለዚህም ነው #አሳቻው መሪ እምላቸው።
በእሳቸው እሳቤ ከአንደኛው መቶ ክፍለ ዘመን እስከ ሃያ አንደኛው ክፍለዘመን ጠሐይም፤ ጨረቃም ናቸው። የነበሩ ያሉ የሚኖሩ፦ አልፋ እና ኦሜጋ። ለነገሩ ዲ/ ዳንኤል ክብረት "እግዚአብሄርን ዛሬ አዬሁት" ብሎናል እኮ። የብሎን ብዬዳ። ቅዱስ ሲኖዶስን ንጠው እሳቸው አስታራቂ ሆነው በቀረቡ ጊዜ ነው ይህን ያለው።
ጠቅላዩ በቀደሙት ዘመናት ሁሉ በፋንታዚያቸው ሲገዙ እንደ ኖሩ፤ ወደፊትም ሲገዙ እንደሚቀጥሉ ነው የምናባቸው #ስዕል። ዩዲትን፤ ግራኝን፤ አጤ ልብነድንግልን፤ አጤ ሱስኒወስን፤ የቀደመውን አጤ ዳዊትን፤ አጤ በካፋ እና ፋሲልን፤ አጤ የኋንስን እና አጤ ቴወድሮስን፤ ኮነሬል መንግስቱን፤ አቶ መለስን፤ ዘመነ አክሱም፤ ዘመነ ሮሃ፤ ዘመነ ጎንደር፤ ዘመነ አዲስ አበባን፤ ንግስት ሳባን፤ አብርሃወአጽባሃን፤ አባ ጅፋርን፤ ዘማናዊቷን ኢትዮጵያን፤ የጣሊያን፤ የሱማሌ፤ የኤርትራ የጦር ዓውደ ግንባሮችን ሁሉ የመሩ፤ ድል ያደረጉ፤ በሳቸው አሻራ የተገነባች ኢትዮጵያን እዬመሩ ለሺህ ዘመን እንደሚቀጥሉ ነው የምናባቸው #ንድፍ።
በአለምም ካዮዋቸው ክስተቶች ሁሉ የሳቸውም ተሳትፎ እንዲጣቀስ ይሻሉ። ይህን እኔ ዛሬ የፃፍኩት ሳይሆን በቀደመው ፁሁፌም እይታዬን አጋርቻለሁኝ። ለኢትዮጵያ ፖለቲከኞች #መላ ሊሆናቸው የሚችለውም የኢትዮጵያ መሪ ድርጊት ብቻ ሳይሆን #ፋንታዚውንም ማጥናት ይገባል። እሱ ሲጠና ስክነትን በጥንቃቄ መጠጣት ይቻላል። የዘመኑን የፖለቲካ ባህሪ ከአጠቃላዩ ተነስቶ የወቅቱ መሪ ሰብእናን አጥንቶ መነሳት ይገባል።
የምናያቸው አዳዲስ እጅግ የሚያርዱ አረማዊ ክስተቶች ሁሉ እንደ ጥንቸል ቤተ ሙከራ የሆነችው ኢትዮጵያ እና የልጆቿ ሰቆቃ ምንጩን አጥንቶ መነሳት ይጠይቃል። ጭካኔ ቀሰማ ተደርጎበታል። ያ ቀሰማ ደግሞ ሁሉም እንዲጠራበት ይፈለጋል። ሁሉንም የዘመን አይነት፤ ሁሉንም የስርአት አይነት፦ ሁሉንም የመሪ አይነት መሆን ለሚሻ የኢትዮጵያ የወቅቱ መሪ ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድን ለማወቅ በግልብልብ ጉዞ አይሆንም። አይታሰብም። አቃሎ ማዬትም አይገባም። እሳቸው ለእኔ #ቤርሙዳትርያንግል ያህል የተመሰጠሩ ናቸው።
አደብ - የሰለቀጠ፤ ጥበብ - የተዋህደው፤ ክህሎት - የረበበት፤ ጎርፍ የማያስደነፋው ወይንም የማያስበረግገው ጥንቁቅ የሃሳብ ልዑቅ ትጥቅና ስንቅ ያስፈልገዋል ለኢትዮጵያ ፖለቲካ። ግን ኢትዮጵያ የከበደችን ለሁላችንንም ነው።
አንድ ምሳሌ ልንገራችሁ። እንደምን የሚዲያውን መስመር መሃንዲሱ ዶር አብይ እንደቀወጡት። " #ሰበር " ዜና መጠሪያ ሆኗል። እኔ በምኖርበት አገር ሰበር ዜና ተምጦ የሚወጣ ቃል እንጂ ተለምዷዊ ሆኖ ወደ ባህል የተሸጋገረ አይደለም። ሰምቼም አላውቅም። ባህል ማለት እኮ እንደ እኔ ትርጉም የሰወች ድርጊት ዕድሜ ጠገብ ሲሆን ነው። ጠቅላይ ሚር አብይ ከመጡ ጀምሮ እንኩት አድርጎ መንፈስን የሚያነክት ዜና ነው በዬሰዓቱ " በሰበር " የሚደመጠው። ሰበር ዜና ባህል ሆኗል ፈጠራው የአብይዝም ነው - ኮፒራዩቱም እንዲሁ።
ያ ሙሉ ክህሎት በሙሉ ተመክሮ የተገነባው አዋዜ ሚዲያን እራሱ እዩት። በመደበኛ የተደራጀውን ኢትዮ 360 ተመልከቱት፤ ከእነኝህ ሚዲያወች የሚያንሱትም የሚበልጡትም የወል መለያቸው "ሰበር" ሆኗል። የመንግስቶቹም እንዲሁ። ጥገኞችም እንዲሁም። አንድአፍታ እንዲያውም ዜናው ላይ " ጉድ " የሚል ቅጥያም አለው።
የሰው ልጅ ሞት ትንፋሽ ሆኗል። ከእንሴክትም ያነሰ ግምት ነው ለሰው ልጅ መራር ስንብት የሚሰጠው። መፈናቃል መኖር ሆኗል።
መታፈን መደበኛ ተግባር ሆኗል። መስጋት ትዳር ሆኗል። ታግቶ፤ የታጋቹ ሰው ሽያጭ ገንዘብ በህጋዊ ባንክ ሽግግር ህጋዊ ነው። ማፍያነት - ሥርአተ አልበኝነት መንግስት መር ሆኗል። የሞገድ ጋዜጣ ልበወለድ መፃህፍ ታሪክ ተፈፃሚ ሆኗል። ሽብሩም ስኬቱም ዜናውም እኩል ይወጣል። በዚህ ዙሪያ ብዙ ጽፌያለሁኝ። የዘመኑን የፖለቲካ ባህሬ ከልብ እንድታደምጡት በማስላት።
ታዋቂ፤ ተፅዕኖ ፈጣሪ ታሞ ከሆስፒታል ሲሄድ በሬሳ ሳጥን ወደ ቤቱ ይመለሳል፤ ተኝቶ ሲነሳ መርዶ ነው። ተዘርዝረው የማያልቁ የተዳበሉ ሳይሆኑ እኔ ነኝ ያሉ አዳዲስ ሰቅጣጭ፦ አስፈሪ፦ አስደንጋጭ ክስተቶች የኢትዮጵያ ፖለቲካ መደበኛ መለያ ሆነዋል። ለዚህም ነው እኔ #አሳቻው ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ የምላቸው።
ትናንት የኦነግ ታጣቂ የጫካው የቤተ- መንግስት መመኪያ አዲስ አበባን በሽብር ሲንጣት ለጠቅላይ ሚኒስተር አብይ አህመድ ፋንታዚ ልዩ #ኢቤንት ነው። እሳቸው አርባምንጭ በሞተር ሳይክል ቅልጥ እና ቅብጥ ሲሉ በዋዜማው ሰነባብተዋል። ከሰኔ 15ቱ የባህርዳር የቀራኒወ ዕለት በኋላ እሳቸው አስመራ ላይ ሲፍለቀለቁ እንደነበረው የዛሬን አያድርገው እና። የትናቱ ትእይንት ከመስከረም 5/2010 የኦነግ አቀባበል ጋር ተጋብቶ የ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን አልጋወራሽነታቸውን ያመሳጥርላቸዋል። ቤተ - መቅደሶች ሲነዱ ዩዲት እና ግራኝ፤ ጦርነት ሲቀጣጠል ሙሶሎኒ፤ አጤ ልብነድንግልን ይሆናሉ እራሳቸው ጠሚ አብይ አህመድ አሊ።
ለእኛ የሚያስደነግጠን የሳቸው የእቅዳቸው ማመሳከሪያ ስለሆነ የተመቸው ቃል ሚዲያቸው ላይ ወጥተው ያበስሩታል። "ሰው ይሙት። ችግኙ መጠለያ ጥላ ይሆነዋል፤ ተማሪ ጎሳ የለውም፤ ግብጽ ትሞክረው ስራ ፈት ወጣቶቻችን እንማግድበታለን፤ ይጀምሩት የከተማን ውጊያ እናሳያቸዋለን" ወዘተ ዘና፦ ፈታ ብለው አቅለው ይናገሩታል። አጽናኝ ቃል ጋር ተደፋፍረው አያውቁም። ከአይዟችሁም አብነት ጋር ጥል ላይ ናቸው። በሳቸው ዘመን የተጎዳም፤ ያዘነም የለም። የሳቀ የተደሰተ በፍሰኃ የፈረሼ ህዝብ ነው እየመሩ የሚገኙት።
እግዚአብሄር ቀኑን አሳለፈው በቀላሉ እንጂ ታጣቂወች የሰኒዝምወሽመልዚም ታጣቂወች እስር ቤት ገብተው ያሻቸውን ቢያደርጉ ትናንት #ሃግ ባይ አልነበራቸውም። ለዚህ ነው እኔ የእስረኞች ጉዳይ መደበኛ ተግባሬ የሆነው። ብዙወቻችሁ እኔ ስጽፈው ሊሰለቻችሁ፤ ሊያደክማችሁ ቢችልም አንድ ነገር ቢፈጠር የመጀመሪያ ተጠቂ እስረኞች ነው የሚሆኑት።
ትናንት በታለመ ጥይት መሃል አዲስ አበባ ነፍስ እንደ ጠፋ ሰምቻለሁ። ኦነግ አዲስ አበባን ሲረግጥ አምስት አዲስ አበባ ነዋሪወች በአደባባይ ተረሽነዋል፤ አንዲት ሙሽራ፤ አንድ ባተሌ ወጣት፤ በኋላም አርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ተሰውተዋል። 1300 እስረኞች ጦላይ ተወርውረው፤ አብዛኞቹ ሲፈቱ ቀሪወቹ ጠያቂ አልቦሽ ካቴና ላይ ይገኛሉ። ኦነግ ከአስመራ እስከ ኢትዮጵያ ጫካ እስከ ሰላም ምልሰት ሲደርስ እነኛ ምስኪኖች እስር ቤት ይማቅቃሉ። በሃይማኖታቸው በዞጋቸውም ሊሆን ይችላል።
ትናንት ለተፈጠረው ጫን ተደል የታቀደ የሽብር ድርጊት ከዛም በላይ ታጣቂወች ቢያደርጉ ስልጣን ላላው አሳቻ ስርአት ምቾት ይሰጠዋል። ሻሸመኔ፤ ሽዋ ሮቢት፤ ዝዋይ፦ አጣዬ፤ ሽዋ ሮቢት ሲቃጠሉ "ተኙ" ነው የተባሉት የየከተሞች ሹማምንቶች። ያን ጊዜ በተቆጡ ወጣቶች ተመሃኜ። ዛሬ እርእሰ መዲናዋን አዲስ አበባ በእሳት እና በህጋዊ አፍራሽነት #አና ብለው ተያይዘውታል የማፍረሱን ሂደት። በሙሉ አዲስዬን ያፈርሷታል። ቆይቶ ወደ ካቴድራልም አይቀሬ ይሆናል።
የቀደመ ነገር ማዬትም፤ መስማትም አይሹም ዘመነኞች። ያልተደፈረችው፤ ወደፊትም የማትደፈረው ትግራይ ብቻ ናት። ጨረፍታ ብቻ ነው በጦርነቱ ወቅት የጎበኛት። ብዙ የታመቀ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ የስልጣኔ በኽረ ብራና ናት ትግራይ። ተመስገን ነው እንደ ሌሎቹ በበቀል አልታረሰችም። ልብ ቢኖረው ህወሃት የቀደሙትን ጥበብ ውጥ አደራውን በተወጣ ነበር። አሁን አሁን ለራሱ መሆን ተስኖት እንዳለ ነው የማስተውለው።
#ብልህነት ቢታጭ።
ብዙ ጊዜ ምኞተኞች አሉ። አብዮት ኢንፖርት እና ኤክስፖርት ማድረግ የሚቻል የሚመስላቸው ቅጽበተኞች። ቢሞከርም ከተጨባጭ ሁኔታው ጋር ስለማይጣጣም ስኬቱ አፈንጋጭ ይሆናል። የዚህ ጥማት ያላቸው ሰብእናወች እንደ አሉ አውቃለሁ። በዬጊዜው የህዝባችን መገበርም ከዚህ መሰል ፋንታዚ የጉም ሽንት እሳቤ የሚመነጭ ነው። ሰሞኑን ደግሞ ሶርያን መናፈቅ እንደሚመጣ አውቃለሁ። ቀደም ባለው ጊዜ የአረብ እስፕሪንግ እንደ ተናፈቀው ሁሉ።
ኢትዮጵያ ውስጥ የህዝብ ማህበራዊ ንቃተ ህሊና ይበልጣል ከፖለቲከኞች ንቃተ ህሊና ይልቅ። ውራጅ አያስፈልግም። የንቅናቄ ኢንፖርት አያስፈልግም። ፋኖን የፈጠረው የህዝብ ማህበራዊ ንቃተ ህሊና ልቆ እና ደምቆ በመውጣቱ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ፈርታይል ሁኔታ አለ። መስዋዕትነትን የሚቀንስ ምራቁን የዋጠ ልኩን ያወቀ፤ በልኩ የሆነ #የዊዝደም ጥማት ግን የፋኖ ንቅናቄ አለበት።
ከዚህም ላይ አንድ ምሳሌ ላንሳ ትውልዱ ስለሚያሳዝነኝ። ሁለት ትጉኃን ጋዜጠኞች ትዳር ላይ እያሉ የገጠመ ፈተና ለማህበረሰቡ ሲቃ ሆኗል ብዬ አምናለሁ። ጋዜጠኛ አቶ ምናላቸው በጊዮን ሚዲያ የእነ ዘኔን ፋኖ ይደግፋል፤ ባለቤቱ ጋዜጠኛ እዬሩስ ደግሞ የእስኬውን ፋኖ በኢትዮ 360 ትደግፋለች። መብታቸው ነው።
ግን ከቤታቸው ዕንቁ ልጆች አሏቸው። ነገ ተመድን፤ ወይንም ኢትዮጵያን ሊመሩ ይችላሉ እነኝህ ልጆች። "የልጅ እና የጢስ መውጫው" አይታወቅም እንዲሉ። እና ጎጆው ወጥ ሃሳብ ማስተናገድ ሳይችል ሜዳ ላይማ እንዴት?? በዚህ ፍልሚያ የልጆች አእምሮ ምን ያህል እንደሚባትል እሰቡት። አክሰሱ ላላቸው ልጆች አደባባይ የወጡ ወላጆቻቸው እና የአድማጭ አሉታዊ ግብረ መልስ በቀጣይ ህይወታቸው ላይ የሚኖረውን ተጽዕኖ አስሉት።
ይህን እንደ አገር ስታሰሉት #ማግስት ተስፋውን ፍለጋ መባዘኑን ታስተውሉበታላቸው። እኛ የራሳችን ውስጣችን፤ የኢትዮጵያ ገዢወችን ማህበረ ኦነግን እና ደጋፊወቻቸውን ዋናው ባላቸው ግርባው ብአዴንን፤ ይህ አልተመቸንም የምንለው ብዕረኞች፤ የሚዲያ ባለቤቶች፤ ካቴና ላይ ያሉ ወገኖች፤ ከባሩድ ጋር ዱር ቤቴ ያሉ ወገኖች፤ ዝምተኛው ማህበረሰብ ሳይለንት ማጆሪቲ የሚባለውንም፤ ከቋያው ያለው ሚሊዮን ህዝብ፦ የታገቱ፤ የታፈኑ፤ ነገም የሚታገቱ፤ የሚታፈኑ ወገኖችን፦ ጎዳና መጠለያ የሆናቸው የእኛወችን፤ የተፈናቀሉ ምንዱባንን፤ ሊለምኑ ያፈሩትን ውስጦቻችን ሁሉንም በያፈርጁ መዝኑት።
መዳን - መፍትሄ በጤነኛ ርጉ የሃሳብ ልቀት፤ መስዋዕትነትን ቀንሶ በሚራመድ ዲስፕሊንድ ፍላጎት ለቀኑ ቀን ሰጥቶ ከተስፋ ጋር ለመገናኜት ለጥሞና ጊዜ ቢሰጠው ባይ ነኝ። ንዴትን፤ እልህን፤ ቁጣን ቀጥቶ ማግስትን በስክነት አቅዶ በርጋታ ለማግኜት ጥሞና።
#እርገት።
የአቅማችን ልኬታ የሚያስፈልገው ቅንነትን ከጥንቃቄ ጋር ማጋባት፤ በፍላጎታችን ውስጥ እግዚአብሄርን አላህን የማስቀደም ጉዳይ መሰረታዊ ጉዳይ ይመስለኛል። ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ #አሳቻ መሪ ናቸው። አሳቻነትን ማጥናት በጥንቃቄ የፖለቲከኞች ተግባር ሊሆን ይገባል። ይህ በድረስ ድረስ፤ በግልብልብ፤ በጥድፊያ የሚሆን አይደለም።
ከምዕተ ዓመት አህዱ እስከ ምዕተ አመት 21 የደረሰ #የአለሁበት የአብይዝምን ፋንታዚ ፕሮጀክትን ለመመከት ጠንቃቆች በማስተዋል የተገራ ጥበብ እንዲኖራቸው ይጠይቃል። ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድም እኮ ይባትላሉ። ማፍረሱም እኮ የብትልናቸው አካል ነው።
በኮንስትራክሽን ዘርፍ ቱሪዝምን ከስሜን ወደ ደቡብ የማምጣትም ብትልናቸውን እንዴት ሃንድል እናድርገውም ጥበብ ነው። ስሜኒዝም የቅርስ የውርስ ኃይለ ኪዳን ነው። ግን በጦርነት?????? እና ደግሞ ነገ ጠቃሚውም ከአልጠቃሚውም በበቀል እንደሚቀዳድ ሥራዬ ብሎ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ነገ ስለሚያያዘው፤ ዛሬም በመንፈሱ ስለሚጠየፈው ከአሁኑ አጀንዳ ይሁን እንደማለት። የነገ መሪ፤ የነገ ቀዳማዊ እመቤት ለመሆን እራሳችሁን ላጫችሁ ነው ትሁት ማሳሰቢዬ።
ከሁሉ በላይ ኢትዮጵያ የተሰራችበት ድር እና ማግ ረቂቅ ሚስጢር ነው። እዚህ የበሞቴ ልዕልቴ እናቴ መጥታ በነበረ ጊዜ ስጋ እንድትበላ ጠዬቅኋት። "አልበላም" አለችኝ። ጳጳሳቱ እኮ ይበላሉ ስላት "እኔ የምጠዬቀው በጳጳሳቱ ነፍስ ሳይሆን በእኔ ነፍስ ነው። አዬሽ ልጄ ኢትዮጵያ #ሳሩ የተባረከ ነው እንኳንስ ከብቱ" አለችኝ።
ቅኔ አገር ቅኔ ህዝብ ያላት አገርን ለመምራት ሆነ ችግሯን ከስር ለመፍታት የሰከነ ቅንነት በቅኔነት፤ የረጋ ጥንቃቄ በብልህነት ይጠይቃል። የታረመ አንደበት፤ አቅምን የለካ ፍላጎትም። ደግሜ እምገልፀው፤ ኢትዮጵያ የከበደችን ለሁላችንም ነው።
ቸር አስበን፦ ቸር እንሁን። አሜን።
ቅን አስበን፦ ቀና እንሁን። አሜን።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ። አሜን።
ሸበላ ጊዜ። አሜን።
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergure©Selassie
09/12/2024
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።
ዕውነት ጋራጅ አያስፈልገውም።
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ