#ብልህነት በጠራራ ጠሐይ #ሲያመልጥ - መልካም ዕድል ምልጥ። የBBC መረጃ ሊንክና ጭብጡን አያይዣለሁ፤ በቅድሚያ የእኔ ዕይታ።
የBBC መረጃ ሊንክና ጭብጡን አያይዣለሁ፤ በቅድሚያ የእኔ ዕይታ።
"የቤትህ ቅናት በላኝ።"



የቀደሙት የአበው እና የእመው ዊዝደም ጥንቃቄ እና ብልህነት እርቀቱ የትዬሌሌ ነው። የተከበሩ ወሮ ሳህለወርቅ ዘውዴን የፕሬዚዳንትነት ቦታ ለማስለቀቅ ጥድፊያ ነበር በአብይዝም ፖለቲካ። ከዛ በፊት ቦታውን ፈቅደው ይመኙት የነበሩት ነፍሳቸውን ይማረው እና ፕሮፌሰር ጴጥሮስ በዬነ በሥጋ መለዬትም #ጥድፊያ ነበር። በምን? እንዴት? ለምን?--------ሁሉም ያልገባኝ ሊገባኝም ያልፈቀድኩ ነበር በወቅቱ።
ምን ታቅዶ/ ምን ሊከወን እንደሚችል #በአሳቻው ሎሬት ጠሚር አብይ አህመድ አሊ በጨረፍታ ነጠብጣቦችን አያይዤ ዕውነት ፍለጋ ብማስንም፦ አሁን ያለውን የአፍሪካን የመሪነት ደረጃ ተጨባጭ ሁኔታ ጋር ለመድረስ አልቻልኩም ነበር። ኢትዮጵያ በአራቱም ማዕዘን በተወጠረችበት በዚህ ዘመን እንደ መሪ ኢትዮጵያን በአፍሪካ #ቁልፍ ፖለቲካ ባላ እና ወጋግራ ሊሆንላት የሚችል ሁነቶችን አደራጅቶ መምራት የግድ አስፈላጊ ነበር። ጠሚር አብይ አህመድ የማያውኩት፤ የማይነካኩት አመክንዮ የለም።
ለዚህም ነው በቀጠናው ትርምስ በዚህም በዚያም ኢትዮጵያ ሆኖ በማያውቅ ሁኔታ ወቀሳ የምታዳምጠው። በተለይ አሁን በግሎባላይዜሽኑም #ትራንፒዝም ተገማች ክስተት አይደለም። ይህን አስታግሶ በልኩ፤ ለልኩ ለመምራት የአፍሪካ ቁልፍ የመሪነት ቦታ ኢትዮጵያ በእጅጉ ያስፈልጋት ነበር። ጥበቡ በዊዝደም ቢልቅ ቢቀልም ኖሮ።
ኢትዮጵያ #ተፈሪ ተከባሪም አገር ናት። ተፈሪነቷ፦ ቀደምትነቷ በታሪክ መመዝገቡ ብቻ ሳይሆን ዛሬ -- ዛሬ በዘመነ አብይዝም ከፍቶ ብውዛው፤ አሉታዊ ዴሞግራፊው እዬናጣት ያለ ቢሆንም እሷነቷን ሊገልጡ፤ ሊያብራሩ፤ ሊያመሳጥሩ የሚችሉ የሚታዩ፤ የሚጨበጡ የዕውነት ዕውቀታዊ ማህደር እመቤት በመሆኗ ነበር። ድርሳኗ የተመዘገበ ነው። በዓለም አብያተ መፃህፍት ተግብቶ ማውደም የደርመስ ፈጽሞ አይቻልም። የጥንታዊው የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሚስጢራት ብቻ ከዚህ በኋላ ፲ትውልድን የማስቀጠል አቅም አለው።
ኢትዮጵያ የህብረቱ #መቀመጫ ሆና፤ ኢንዲሁም #በኢጋድ ቁልፍ ቦታ ይዛ፦ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን #ሊቀመንበርነቱ ይገባታል፤ አይገባትም የሚለውን ህጉን አላውቅም፤ ህጉ እንደሚፈቅድላት ዕውቀቱ በውነቱ የለኝም። ነገር ግን ቦታው በዚህ ዘመን በእጅጉ ያስፈልጋት እንደ ነበር ይገባኛል። ለስድስተኛው የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ፕሬዚዳንትነት መወዳደር ትቻል /// አትቻል የሚግድ ነገር ከሌለ ይህን ቦታ ኢትዮጵያ በሰፋ የሎቢ ተግባር ቦታውን መያዝ ነበረባት።
ይህን ለማድረግ ደግሞ የኢትዮጵያ አዲሱ ፕሬዚዳንትን የቀድሞ ውጭ ጉዳይ ሚር አንባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴን በስክነት፤ በረጋ መንፈስ እቦታቸው ማቆዬት በሳል የበቃ የጥበብ ቃና ነበረው። እሳቸውን ማንሳት ቢፈለግ ደግሞ ወሮ ሳህለወርቅ ዘውዴን በቦታው ተክቶ ማቆዬት ይገባ ነበር። ብልህነት ማለት ይህ ነበር። አፍሪካም እንደ እማማነቷ እማማዋን ታገኝ ነበር። በበዛ ድምጽ የመረጥ አቅም ነበረው መንፈሱ። እርግጥ ነው በጀርባቸው ያለው ማንነት #አማራነት እና #የተዋህዶ ልጅነት ለማህበረ ኦነግ ሥርዓት ምቾት የሚሰጥ እንደማይሆን አውቃለሁኝ። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነቱም እንዲሁ።
ነገር ግን ኢትዮጵያን እንደ አገር አስከብሮ፤ አደላድሎ፦ በልቅና ለማሻገር ግን ብልህ አመራር ኢትዮጵያ ኑሯት ቢሆን ኖሮ ይህን የህብረቱን የመሪነት የሥልጣን ሽግግር ታሳቢ በማድረግ #ኢትዮጵያዊነትን #በጸና #አለት #መትከል ይቻል ነበር። ለማህበረ ኦነግ ፖለቲካ እና ፖለቲከኞች የኢትዮጵያዊነት ተፈጥሮ ሳይበወዝ መቀጠሉ ምንም ምቾት ባይሰጣቸውም እዬመሩ ነው ያሉት እና። ሌላው ቀርቶ የኢጋድ ቁልፍ ቦታ ተትቶ ይህን አህጉራዊውን የመሪነት ቁልፍ ቦታ መያዙ በጣም አትራፊ ነበር። ሁለቱንም ቦታ ኢትዮጵያ አራጣ ያዘች የሚል ሞጋች ሃሳብ ቢነሳ እንኳን።
ኢትዮጵያ የአፍሪካ ህብረት፤ ኢትዮጵያ - የኢጋድ፤ ኢትዮጵያ - የፓን አፍሪካኒዝም፤ ኢትዮጵያ የተመድ #የፊደል ገበታ #ቫወልም ናት። ይህ አቅሟ፤ ይህ ክህሎቷ ድርጅቱን ለአራት ዓመት ብቻ ሳይሁን ለተጨማሪ ዓራት ዓመታትም ለ፰ዓመታት የመምራት አቅም፤ አቅል፤ አደብ፤ ክህሎት፤ ልቅና፤ ልዕልና ነበራት።
ኢትዮጵያ በልጆቿ ልምድ፤ ተመክሮ፤ ዝቀሽ የዲፕሎማሲ ጥበብ የድርጅቱን ብቻ ሳይሆን አሁን ዓለም ያለበትን አዲሱን #የትራንፒዝም አዲስ መንፈስም ተሸክማ አፍሪካን #በአቻነት ልክ እንደሌላው አህጉራዊ ድርጅት አመራር የማሻገር ሙሉ አቅም ነበራት። የቀድሞዋ ፕሬዚዳንት ወ/ሮ ሳህለወርቅ ዘውዴ ሆኑ፤ የአሁኑ ፕሬዚዳንት አቶ ታዬ አጽቀሥላሴም ቢሆኑ እርጋታው፤ መጨመቱ፤ ልምድ እና ተመክሮው፦ የቋንቋው፦ ለዲፕሎማሲው ማህበረሰብ የሚመጥን ሙሉ አቅም እና ችሎታው ነበራቸው። እማናፍርባቸውም ናቸው። ኢትዮጵያም በትርፍ ታተርፍ ነበር። የፖለቲካ ውክልና ብዙ የቅብዓ በረከቶችም አሉት እና።
መተማመን በሚመለከት አብሶ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ ጠሚር አብይ አህመድን እንደ እንቁላል የሚንከባከቡ፤ የሚሳሱላቸው ዓይነት ሁነት ነው እኔ ከፊድባኩ እምታዘበው። ግን ለጠሚር አብይ አህመድ የኢትዮጵያ ልዕልና ሳይሆን በውስጣቸው የቆጣጠሯቸው #ሸቀጣሸቀጦች ስለአሉ ዕድሉ እንዲህ አመለጠ። ብልህነት በጠራራ ጠሐይ ሲያመልጥ ብልህነት ምልጥ።
ከሳቸው በላይ በአፍሪካ ጎልቶ የሚታይ ኢትዮጵያዊ ማዬት ፈጽሞ??? በፌድራሉ እና በህወሃት ጦርነት፤ በግድቡ በነበረው እሰጣ ገባ የዶር ስለሺ፤ የዶር ገዱ፤ የአንባሳደር ታዬ ዓለም ዓቀፍ ዕውቅና መፍለቅ እረፍት ስለነሳቸው ቲሙን ብትንቱን ነው ያወጡት። አቅል የት ይሸመት ይሆን??
አሁን ቢሆን ዶር ቴወድሮስ አዳህኖም የዓለም ጤና ድርጅት ዴያሪክተርነቱን አያገኙም ነበር። በዘመነ ህወሃት ዶር ቴወድሮስ አዳህኖም ዞጋቸው አማራ ቢሆን አያገኙትም ነበር። ህወሃት ለድርጅቱ ተልዕኮ ስኬት እንጅ ለኢትዮጵያዊነት ልዕልና፦ ልቅና ብሎም አልነበረም በሰፋ የሎቢ ጥረት ያን ዕድል ያሳካው።
አቤቱ ህወሃት የዶር ቴወድሮስ አዳህኖም በዓለም ደምቆ መታያት ለድርጅቱ ወይንም ለዞጉ እንደ ክብር ያያው እንደሆን እንጂ እንደ ተቀናቃኝ ተጽዕኖ ፈጣሪነት ሲያዬው አላዬሁም። ለጠሚር አብይ አህመድ የአርቲስት ዲሽታ ጊና ብቅታ እንኳን አጀንዳቸው ነው አይደለም የሌላው። እሳቸው ወደ ሥልጣን ከመጡ እኮ አይደለም አዲስ ነባር ተጽዕኖ ፈጣሪወች ድብዛቸው ነው የጠፋው። አቶ ኦባንግ ሜቶ የት ነው ያለው????? ጠይቁ ………
የሆነ ሆኖ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ለኢትዮጵያዊነቱ መቼ ጥብቅና ሊቆም እንደሚችል አብዝቶ ይናፍቀኛል። ሊያመልጠን የማይገባ ግን ከእጅ የገባ ወርቅ ቀልጦ ፈሷል። ለቀጣይ አራት ዓመት የጠሚር አብይ አህመድ መንግሥት ከዘለቀ የልብ፦ ውስጣቸው፤ የበኽራቸው፤ ስስታቸው፤ የውጭ ጉዳይ ሚር ዶር ጋዲዮንን ጢሞቲወስን ያወዳድሩ ይሆናል። ለዚህም መሰናዶ ይሆናል አጅሬ ይህን ያደረጉት። ፍትህ ሚር በጉልቻ በአንድ ሳሎን ነው የሚመራው።
ዶር ጌዲዮን ጢሞቲወስ ከደቡብ፤ በሃይማኖትም መሰል ስለሆኑ ለአብይዝም ሰላም ይሰጣሉ። ለመሪነትም የሚያሰጉ አይደሉም። ደቡቦች ጭምተኛ ናቸው። እስከ አራት ዓመታት እስከዛው ድረስ ከዲፕሎማሲው ማህበረሰብ ጋርም ብርቱ ልምምድ ያደርጋሉ።
ለነገሩ በማይመለከታቸው ጉዳይ ሁሉ እሳቸውን እንደ ጨው ማጣፈጫ ነው ጠሚር አብይ አህመድ የሚጠቀሙባቸው። ከደቡብ ሰፊ እጁን ካቢኔ ውስጥ፥ እና በተለያዩ ቁልፍ የፖለቲካ ውክልና ሊሂቃኑ አግኝተዋል። የከንባታ እና የሃድያ ቀደምት ህዝብም በስሚ ስሚም ቢሆን ብርቱ ድጋፍ ለዶር አብይ አህመድ አላቸው ሲባል እሰማለሁኝ።
ከማህበረሰብ አማራ እና ጉራጌ፤ ከሃይማኖት ቅድስት ኦርቶዶክስ ተዋህዶ በአብይዝም ተገፋ ከምል #ተገፈተሩ - #ተደፋም ብል ይቀለኛል። በጥርስ የተያዘው፦ ሞግቶ እጅግ በላቀ ጥበብ እና ብልህነት ህወሃትን ከመንበሩ ፈቃዶ እንዲሸኝ ያደረገው አመድ አፋሹ አማራ አባ ቅንዬ ግን ሁልጊዜም መገፍተር ነው። ነገም ይህው ነው።
ለዚህም ነው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ብልህነት ድርቅ መቶት፦ ከዓመት ዓመት፤ ከዘመን ዘመን እንዲህ #በፍቀት እዬዳኽ የሚገኜው። ግብጽ በዬዘመኑ በማያልቅ አጀንዳ እያመሰች ያለችበት አመክንዮም ይኽው ነው። ብዙ የኢትዮጵያ ሊቃናት ግብጽ የአባይ ግድብ በመሠራቱ ብቻ ይመስለዋል ኢትዮጵያን የምትጋፋ።
እንደ እኔ እንደ ሥርጉትሻ ግን የነገረ ግብጽ ተቀናቃኝነት ግድቡ ብቻ አይደለም። ግብጽ በአፍሪካውያን ካርታ ውስጥ ያሉ አገሮች ለኢትዮጵያ ያላቸው ክብር እና ፍቅር ያስቀናታል። ከአፍሪካ አህጉርም አልፎ እንደ ጃማይካ ባሉ አገሮች የኢትዮጵያ #አምልኮ ጉዳይ የግብጽ የፖለቲካ ሊቃናት ነፍስ ያባትታል።
የግብጽ የፖለቲካ ሊቃናት የአፍሪካ አንከር የመሆን ህልመኛ ናቸው። ኢትዮጵያ በሁሉም መስክ ብቅ እንድትል አይሹም። በታሪክም፤ በትውፊትም፤ በባህል እና በወግም፤ በፖለቲካ አቅም እና ተመክሮም ቢሆን የኢትዮጵያ ልቅና እና ልዕልና ለግብጽ የፖለቲካ ሊቃናት ህመም ነው። ይህ መልካም ነገር ሆኖ ለትውልዱም የሚያወርሱት የቅናት #ዛቢያቸው ነው።
ከእኛ በጣም በቀደሙት ዘመንም ይኽው ነው። የግብጽ የፖለቲካ ሊቃናት ሁልጊዜ ኢትዮጵያ ከበታች እነሱ ከላይ ሆነው መጋለብ ይሻሉ። የማይገናኝ ህልም እልም ስልምልም ምኞት። የሚገርመኝ የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች ከኢትዮጵያ የዬዘመኑ ፖለቲካ ጋር በተኮራረፋ ቁጥር ግብጽን እንደ መዳኝ የመፍትሄ አማራጭ መውሰዳቸው ነው።
ምን ተብሎ እንደሚታሰብ እራሱ ይገርመኛል። #ሙጃ ሃሳብ ነው ከግብጽ ጋር የፖለቲካ ጋብቻ። "አጥፊን ደርምሽን ምሪን ነውን?" የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች በመሪወች ከተከፋ ከኡጋንዳ፤ ከኬንያ ጋር መወዳጀት ቢሹ ምንም አይደለም። በቅናት እርር ኩምትር ከሚሉት ጋር ግን ጎንድ ያሰኛል። ስሰማው እራሱ እኔ ያመኛል። የግብጽ ፖለቲከኞች ለደቂቃ ለኢትዮጵያ ፍሰኃ ተመኝተው አያውቁም።
ከፖለቲካ ውጪ ያሉት ግን በአጫጭር ኮርሶች፤ በአንዳንድ ፕረዘንቴሽን ሳገኛቸው እንደ ቤተ ዘመድ ነው የሚዩን። ለዚህ ነው የፖለቲካ ሊሂቃኑን ለይቼ ማዬት የፈለግኩት።
የሆኖ ሆኖ ጁቡቲ ዝቃለች። እንኳን ደስ አላቸው አቶ መሃሙድ አሊ የሱፍ፤ መልካም የሥራ ዘመን። ተሰናባቹ አቶ ሙሳ ፋኪም መልካም የእረፍት ዘመን ይሆንላቸው ዘንድ እንደ አህጉሩ አንድ ዜጋ እመኛለሁኝ።
#ስለተሳሳተ ካርታ ሰምቻለሁኝ።
የማህበረ ኦነግ ኦሬንቴሽን ይህ ስለሆነ በዚህ ዙሪያ ብዙ ሲናገሩም ስለማደምጥ እኔ በ6/12/ 2019 ጽፌበታለሁኝ። የአብይዝም ዶክተሪን አሉታዊ ዴሞግራፊ ስለሆነ ጊዜ ይመልሰው ባይ ነኝ።
ቸር አስበን፦ ቸር እንሁን። አሜን።
ቅን አስበን፤ ቀና እንሁን። አሜን።
ግን ደህና ናችሁ ማህበረ ቅንነት? ኑሩልኝ። አሜን።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ። አሜን።
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
16/02/2025
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።
«የጂቡቲው ማህሙድ አሊ ዩሱፍ ስድስተኛው የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሆኑ"
15 የካቲት 2025
"ተቀራራቢ ፉክክር በተካሄደበት ምርጫ የጂቡቲው ዕጩ ማህሙድ አሊ ዩሱፍ ስድስተኛ የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሆነው ተመረጡ።"
"ከኬንያው የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር እና የተቃዋሚ መሪ ራይላ ኦዲንጋ ጋር ለስድስት ዙር በተካሄደ የምርጫ ሂደት የጂቡቲው ተወካይ አሸናፊ ሆነዋል።"
"የ60 ዓመቱ ማህሙድ አሊ ዩሱፍ ለ20 ዓመታት የጂቡቲ የውጭ ጉዳይ እና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር ሆነው እየሠሩ የሚገኙ ሲሆን፣ የኅብረቱ ኮሚሽን ሊቀመንበር መሆናቸውን ተከትሎ የሚኒስትርነት ሥልጣናቸውን ይለቃሉ።"
"አፋርኛ፣ ሶማሊኛ፣ ፈረንሳይኛ፣ እንግሊዝኛ እና አረብኛ አቀላጥፈው የሚናገሩት ማህሙድ አሊ ዩሱፍ፣ ወሳኝ በሚባለው የቀይ ባሕር የንግድ መሥመር ላይ ከሶማሊያ የባሕር ዳርቻ በመነሳት የባሕር ላይ ውንብድና የሚፈጽሙትን በመከላከል ላበረከቱት አስተዋጽኦ በአውሮፓ ኅብረት ተሸልመዋል።"
"ከኬንያ እና ከማዳጋስካር ከተወከሉ ዕጩዎች ጋር ለኅብረቱ ሊቀመንበርነት የተፎካከሩት ጂቡቲያዊው ዕጩ ማህሙድ ከባድ ፉክክር የገጠማቸው ከኬንያው ራይላ ኦሞሎ ኦዲንጋ ነበር።"
"እስከ ሦስተኛው ዙር ድምጽ አሰጣጥ ድረስ ከማዳጋስካር የተወከሉት ዕጩ ሪቻርድ ራንድሪያማንድራቶ ዝቅተኛ ድምጽ በማምጣት በፉክክሩ ውስጥ የቆዩ ሲሆን፣ ከሦስተኛው ዙር በኋላ ወጥተዋል።"
"የቀሩት ማህሙድ እና ኦዲንጋ በተቀራራቢ የድምጽ ልዩነት በጂቡቲው ዕጩ መሪነት እስከ 6ኛው ዙር ድረስ ተፎካክረው የኬንያው ዕጩ ከውድድሩ በመውጣታቸው ጂቡቲያዊው ዕጩ የብዙኃኑን 33 ድምጽ አግኝተው የሊቀመንበርነቱ ፉክክር አሸናፊ ሆነዋል።
የአፍሪካ ኅብረት የአህጉሪቱ ዋነኛው ተቋም ሲሆን፣ በአፍሪካ ውስጥ ያሉ የፖለቲካ፣ የምጣኔ ሀብት እና ሌሎችን ቁልፍ ችግሮችን ከመፍታት አንጻር አቅሙ ደካማ ነው በሚል ይተቻል።"
"በኢትዮጵያው ንጉሥ አጼ ኃይለ ሥላሴ ጥረት እና መሪነት በግንቦት 16/1955 ዓ.ም. የተመሠረተው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት በዋናነት አፍሪካውያንን በማስተባበር በቅኝ ግዛት ስር የነበሩት የአህጉሪቱ አገራት ነጻ እንዲወጡ መርዳት ዋነኛ ዓላማው ሆኖ ለአራት አሥርት ዓመታት ያህል ሠርቷል።"
"በአውሮፓውያኑ 2000 ላይ የሊቢያ መሪ በነበሩት ሙአመር ጋዳፊ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ከዘመኑ ጋር በሚሄድ አዲስ ድርጅት እና አወቃቀር ወደ አፍሪካ ኅብረት እንዲሸጋገር ያቀረቡት ሐሳብ ተቀባይነት አግኝቶ ከሁለት ዓመታት በኋላ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ወደ አፍሪካ ኅብረትነት ተሸጋገረ።"
"የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ወደ አፍሪካ ኅብረት ከተሸጋገረ በኋላ አሁን የተመረጡትን ጂቡቲያዊውን ሊቀመንበር ጨምሮ ስድስት የኮሚሽኑ ሊቀመናብርትን አስተናግዷል።"
"በዚህም የመጀመሪያው የኅብረቱ ሊቀመንበር አይቮሪኮስታዊው አማራ ኤሴ የነበሩ ሲሆን እሳቸውን ተከትሎም፣ ማሊያዊው አልፋ ኦማር ኮናሬ፣ ጋቦናዊው ጂያን ፒንግ፣ ደቡብ አፍሪካዊቷ ንኮሳዛና ድላሚኒ ዙማ እና የአሁን መንበራቸውን የሚያስረክቡት ሙሳ ፋኪ ማሐማት የኮሚሽኑ ሊቀመንበር ሆነው አገልግለዋል።»
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ