#የአንከር ሚዲያ ሰሞናተ - ሙግቱ ይበል ያሰኛል። ሚዛን ግን ይጠይቃል ሰላሙ ለአማራ እናትስ ይላል።

 

#የአንከር ሚዲያ ሰሞናተ - ሙግቱ ይበል ያሰኛል። ሚዛን ግን ይጠይቃል ሰላሙ ለአማራ እናትስ ይላል።
 
"የቤትህ ቅናት በላኝ።"
 
 May be an image of text
 
ትናንት ጋዜጠኛ መሳይ መኮነን ከአቶ ሚኪ ተስፋዬ ጋር ቃለምልልስ ነበረው። ሙሁራን አቅርቦ ሲሟገት እከታተለዋለሁኝ። ተደማጭም ጋዜጠኛ ነው። እንግዶቹን ወደ እሱ ምልከታ ለማምጣት የሚያደርገው ፍልሚያም የጉድ ነው። ድሮ ድሮ በብዙ እሞግተው ነበር። አሁን ሙግት አቆሚያለሁኝ። እሚገርመኝን አመክንዮ ግን ማቅረብ ግድ ይሆናል። ከተደመጠ #ስርክርክ የሚሉ ዕሳቤወችን ማጽዳት ይገባል።
ጋዜጠኛ መሳይ መኮነን የትግል ሚዲያ ክፍሉ ይመስለኛል። ዝንባሌውም ወደዛ ነው። የሆነ ሆኖ ሰሞኑን ግን እሱን እራሱ በራሱ ሚዲያ የሚሞግቱት በርክተዋል። በተራው እዬተሞገተ ነው። ይህ ሸጋ ገጠመኝ ነው። የጠበቃ አርበኛ አስረስን ሙግትም አዳምጫለሁኝ።
 
ጠበቃው ቀላል አልነበረም። ፍላጎቱን አስከብሮ ነበር ውይይቱ የተጠናቀቀው - በእኔ ሚዛን አርበኛ አስረሱ አሸንፏል ባይ ነኝ።።። ብቁ ወጣት ነው ጠበቃ አስረስ። ለህይወቱ ግን #እሳሳለታለሁኝ። አይደለም ለአማራ ለኢትዮጵያም የሚጠቅም፦ እራሱን በአግባቡ መግለጽ የሚችል ወጣት ነው። በሚያምንበት ሃሳብ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ማሳ ቀለመ #ህብር ያደርገዋል እና። ሰላሙ ቢገኝ።
 
ትናንትም አቶ ሚኪ ተስፋዬም እንደ ጉድ ነበር የሞገቱት ጋዜጠኛ መሳይ መኮነንን። ኢትዮጵያ ውስጥ በዜግነት ፖለቲካ ላይ የሚሠራ #ሰላማዊ ታጋይ ይህን ያህል አቅም ያለው አለን ብያለሁኝ። ሚዛን ላይ ሆነው የሚያምኑበትን ፋክት አላስነካም ብለው በድፍረት፤ በእርግጠኝነት ወሳኝ በሆኑ አመክንዮወች ጋዜጠኛው እስኪበቃው ተሞግቷል። አልተበገሩለትም። ደስ የሚል ፍልሚያ ነበር።
 
መጨረሻ አንበሳው አቶ ሚኪ #አሸንፈዋል ብዬ አስባለሁኝ። ጋዜጠኛም፤ ፖለቲከኛም እንዲህ ቢሞገት ኖሮ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ወደ ተሻለ ዕድል መጓዝ በቻለ ነበር። "አትንኩት፦ አትንኳት" ቢቀር ዕውነት አለኝ የሚል ሁሉ ፊት ለፊት ቀርቦ ካለምንም ተጽዕኖ ቢሞግት ኢትዮጵያ የተሻለ ትውልድ የማግኜት በረከቷ #ፏ ይልም ነበር። 
 
ይሄ ጎዳና ሊለመድ ይገባል። አንድም ፖለቲከኛ፤ አንድም የሚዲያ ሰው፤ አንድም ተጽዕኖ ፈጣሪ ብቻ ሳይሆን ደጋፊወቻቸውም የሚደግፋት ሰብዕና እንዳይነካ ዙሪያውን ስለሚያጥሩት፦ የኢትዮጵያ ፖለቲካ እያደር ዘገምተኛ መሆን ቻለ። ጥራት እና ብቃት ጎደለው። አጓጉል ሆኖ #ጓጎለም#አጎፈረም። እንዲህ እንደ አቶ ሚኪ አንበሳ ሲገኝ ግን ያረካል፤ የልብም ያደርሳል።
 
በዚህ ውይይት ውስጥ ጋዜጠኛ መሳይ ደጋግሞ ስለትግራይ ዕንባማ እናቶች፤ ስለትግራይ ሰላም ማጣት በጽኑ ደጋፊ የሆኑ አስተያዬቶችን ሲሰነዝር አዳምጫለሁኝ። ለህዋትም የተሻለ ዝንባሌ አይቸበታለሁኝ። በሌላ በኩል ደግሞ ጋዜጠኛ መሳይ መኮነን #የፋኖ ንቅናቄ ትጉህም ጽኑም ደጋፊ ነው። ሰፊ የአዬር ጊዜ ያለገደብ የሚሰጠው አመክንዮ ቢኖር ፋኖነትን ነው። በዛ ውስጥ ሰላም የራባት የአማራ እናትስ የለችንም የእኔ ጥያቄ ይሄ ነው? ባለቤቱ ስለበዛ የአማራ ነገር ውስጣችን ተጠሞነ። በየሰከንዱ #ልጆቿ #የአፈር እራት የሚሆኑ፤ በስጋት የተጣበቡ፦ የማህፀኗ ፍሬወች የሉንም - የአማራ እናት? ይህን ሚዛን ይዳኜው ዘንድ ይገባል ባይ ነኝ። የጹሁፌ መነሻ ይህ አግራሞቴ ነው። 
 
የአማራ ፋኖ ተጋድሎ እንዲቀጥል፤ አንድ ሆኖ ለድል እንዲበቃ ሰርክ የሚማጸነው ጋዜጠኛ መሳይ መኮነን ጦርነት ህግ የለውም እና የክልሉ ሰላም ማጣት፤ የአማራ እናቴ የልጆቿ #የሰኔል እና ቹቻ ስንቀኛነት፤ የራሷም መገበርን እንደምን ይመለከተዋል ነው የጹሁፌ ጭብጥ። እርግጥ ነው በአማራ እና "በኦሮምያ ያለው ጦርነት ይቁም፤ ሰላም ይስፈን" ያሉ የሰላማዊ ታጋዮች ሰላማዊ ሰልፍ ጠይቀው ተከልክለው፤ ለትግራይ ሲሆን ለምን ተፈቀደ? እንዴትስ ተፈቀደ ነው ጉዳዩ? ጥያቄው አግባብ ቢኖርም አቶ ሚኪ የመንግሥት መዋቅር አካል ስላልሆኑ ጥያቄው ለገዢወች መጠዬቅ ነው የሚኖርበት ጋዜጠኛ መሳይ መኮነን፤ እንጂ አቶ ሚኪ ተስፋዬን ሊሆን አይገባም።
 
እኔ አንድ መርዶ ልንገረው። የማህበረ ኦነግ ሥርዓት ኢትዮጵያን እስከገዛ ድረስ ከኦሮምያ ክልል ፈቃድ ውጪ ምንም ዓይነት ህዝባዊ ሰልፍ ማድረግ አይፈቀድም። ለምን??? ጋዜጠኛ መሳይ ከመነሻው እንደ አንድ የትግል መንፈስ እንዳለው ጋዜጠኛ ቢያስበው አዲስ አበባ እኮ #ከመስከረም 5/2011 ዓም ጀምሮ #የኦሮምያ ሆናለች። አዲስ አበባ ነገር-ዓለሟ የሚቃኜው በኦሮሚያ ህገ - መንግሥት ነው። ይህን እጄ ባንቡራ እስኪያወጣ ድረስ ጽፌበታለሁኝ። ቢያደምጠኝ ኑሮ ብዙ አይደክምም ነበር። እሱ ብቻ አይደለም ፖለቲከኞችም ይህን ሃቅ መቀበል ይሳናቸዋል። የሪባን ቆረጣው እኮ ለዚህ መሰል ሥር ነቀል አሉታዊ ዲሞግራፊ #ግርዶሽ ነው። የክሪስማስ አንፖሉም ሆነ የውሃ ዳንሱ ዓላማውም ግቡም ይህው ነው። 
 
በዚህ አጋጣሚ እሱ እንደሚደመጠው ሌላውንም ለማድመጥ ቢፈቅድ መልካም ነው። አገር አገር ትሆን ዘንድ ከተፈለገ ብስል ከቀሊል፤ የክት እና የዘወትሩ አልጠቀመም። ወደፊትም አይጠቅምም። ብዙ በጣም ብዙ ዕድል ነው የኢትዮጵያ ፖለቲካ በተዛባ አያያዝ ሚስ የሚያደርገው። 
 
የአዲስ አበባ ከንቲባ ጽ/ ቤት ልክ እንደ "ፌድራሉ" ግዛት #እኩል ተጠሪነት #ለኦሮምያ ክልል አለው። #ሰሌዳው ፋክቱን የሚያቀርበው ይኽንኑ ነው። ለኦሮምያ የኢትዮጵያ ግዛት ዘመን የቱ ይጠቅማል ነው ጨዋታው። ፈቃድ የሚሰጠው ከዚህ አንፃር ነው። እነ አቶ አባይ ወልዱ አማራ ክልልን ጥሰው ገብተው በድርጅታቸው መንበር ላይ ህልፈትን ያውጁት እኮ በዚህ አግባብ ነው። አቶ ሽመልስ አብዲሳም ያላቸው ሥልጣን እስከዚህ ድረስ ነው። ስለዚህ ለእነሱ ፖለቲካ ምቾት የሚሰጠው አመክንዮ ይፈቀድለታል።
 
አንተ መርጠህ እንደምታቀርበው፤ መርጠህም #እንደምታርቀው አመክንዮ ማለት ነው። አንተ ከፍላጎትህ ጋር ዝንፍ ያለች #ዕውነት ቢሆን እንኳን አታቀርብም። የግል ግንኙነትህም በዛ ላይ የተመሠረተ ነው። እነሱም የሚሠሩት ይህንኑ ነው። ሚዛን የሚሞግትህ በዚህው ነው።
ዕውነት ብነግርህ ለትግራይ የተመኜኽውን ንጹህ ሰላም #ለአማራ ህዝብም ከልብህ ብትመኝ ደስ ይለኛል። በትናንት ቃለ ምልልስህ ይህን ፍሬ ነገር አላዬሁም። የአማራ ልጆችም #ከእናት ነውና የተፈጠሩት። የአማራ ህዝብ የ120 ሚሊዮን መከራ ግማድ የመሸከም ግዴታ የለበትም እና። ሁሉ ጫካው ዱሩ በቅርቡ ነው። የራሱን የነፃነት ትግል አድርጎ በኩል ግብር እኩል ብርሃን ማግኜት ግድ ይሆናል። ይህም ሆኖ ምኞቱ ቢሳካ አማራ አገር ይምራ ቢባል ስምምነቱ ይኖራል ወይ? ከውስጥ ስለማዳምጥህ ይህን ትፈቅዳለህ ብዬ አላስብም፤ ውህድ ማንነት ካልሆነ በስተቀር። ይህን የምታስበው ግን አንተ ብቻ አይደለህም። ብዙ ወገኖች አሉ። ብዙ ሚዲያወችም።
 
ሌላው ግን አንተ ማድረግ የማትሻውን፤ ሌላው እንዲያደርግልህ አትጠብቅ። እንዲያውም ዕድለኛ ነህ። በዕውነት ወፍ ያወጣህ ዕድለኛ። አንተ የፈለግኽውን #ስትደግፍም ሆነ በቃኝ ብለህም #ስትቃወምም ሺወች ከጎንህ ናቸው። ሚዛን ግን ሁልጊዜ ህሊናህን እንደሚጠይቅ ተስፋ አደርጋለሁኝ።
 
እግረ መንገዴን ላነሳልህ እምሻው ጉዳይ የኢትዮጵያኒዝም ምልክትነትህን እንዳታጣም #ጥሞና ብታደርግ፤ ብትጸልይበት ጥሩ ነው። ለኢትዮጵያውያን ከኢትዮጵያ በላይ ጉልላት፤ ክብር ግርማ እና ሞገስ የለንም። አንተም እንደምታውቀው ሥርዓቶች ይመጣሉ ይሄዳሉ። አብይዝም በተፈጥሮ ሂደት ሊከላ ይችላል። ክብራችን ግን አልፋ እና ኦሜጋ ለሁልጊዜም፤ ለምንጊዜም ኢትዮጵያዊነት ሊሆን ይገባል ባይ ነኝ። እንደ ንጽህ ህሊና እህት የማዳምጠው ወጣ ገብ ሁነት ስላለ ነው።
 
ሥረ - መሰረታችን ኢትዮጵያዊነት ነውና። ከኢትዮጵያ ይልቅ ፖለቲካው እና ሌላ ሁነትን ስትፈቅድ አስተውላለሁኝ። በአንድ ቃለ ምልልስህ ኢትዮጵያ የሚለው ሥያሜ ካልተስማማን ልንቀይረው እንችላለን ሲሉ እንግዳህ ወኔህን፤ ቁጣህን፤ ብስጭትህን ማድመጥ ፈልጌ አላገኜሁትም። ከውስጤም አዝኛለሁኝ። መሳዩ እና ኢትዮጵያዊነት??? 
 
እርግጥ ነው የኢትዮጵያ እናቶች፤ አሳሩ የገዘፋባት የአማራ እናትም አምላክ አላቸው። አላህ አለላቸው። ኢትዮጵያም የፈጠራት አምላክ አላህ አለላት። እንደ ዜጋ፦ እንደ አገር ልጅነት ከደከምን፦ ከተጋን አይቀር ደግሞ በገፍ ፍቅር ለሚቀልብ ማህበረሰብ ህሊና፤ ቅን መንፈስ መጠንቀቅ ይገባል። ዳታውን ማቅረብ ባልችልም ተጀምሮ እስኪጨረስ ለአንተ #ተጽዕኖ ፈጣሪነት፦ #ገኖ መውጣት የሚሊዮን አማራ ልጆች ድጋፍ ሚዛን ይደፋል ብዬ አስባለሁኝ። ገጥሞኛልም እንግዳዬ ቁማ ስታዳምጥህ። የሚገርምህ ለአንገተ ደፋታ ልጆቹ የአማራ ህዝብ እኮ ትዝ አንላውም። እኛ ሁልጊዜም ከእሱ ጋር ነን። እርግጥ ነው ዘመን እራሱ የከዳው፤ ድካሙ አመድ አፋሽ ቢሆንም ነገረ አማራ።
#እንደ እርገት …… ውስጥ እንደ ጋዜጠኛ ለሁሉም እኩል ቦታ ድርሻ ሊኖረው ይገባል።
 
• ሙግቱ ይበል ያሰኛል፥ ሚዛን ግን መጠየቁ አይቀርም።
 
------/////------///------////
 
አዬህ ልጅ መሳይ መኮነን (ጋዜጠኛ)በዚህ ሁሉ የውጊያ ዓውድ አማራ ከሥሩ እዬተነቀለ ነው። 5 ሚሊዮን ተማሪ ከትምህርት ገበታ ውጪ??? የአማራ እናትም እሷ፤ መኖሯ፦ ማህፀኗ #እዬነደደ፤ እዬተንቀለቀለ ነው። ሰላሟ ጥግ አጥቶ እዬተሰደደ ነው። እናት ትታሰብ። አንድ ጊዜ ሳዳምጥህ ጎጃም ከተማ ውስጥ ወጣቶች መኖራቸው እንዳልተመቸህ ስትገልጽ ደንግጬያለሁኝ። 
 
ሁሉም የዶግ አመድ ይሁኑ ማለት ነው? ዘር አይትረፍ ነውን ብያለሁኝ - በወቅቱ። የአማራ መከራን ስትጋራ ስለቀጣዩ ትውልድ የመትረፍ ተስፋ መፍትሄውንም ውስጥህ ማድረግ ግድ ነው። ከ35 ሚሊዮን በላይ ሊሰደድ አይችልም። ቢልም አይችልም። ጥቂት ሊንኮችን ደግመህ አዳምጣቸው። የትናንቱን የአቶ ሚኪንም እንዲሁ። የህሊና ዳኝነቱን እራስህ ዳኜው። እግዚአብሄር ይስጥልኝ። አሜን።
 
"«Anchor Media የአዲስ አበባው የትግራይ ተወላጆች ሰልፍ፥ እውነተኛ የህዝብ ድምጽ ወይስ የብልጽግና የፖለቲካ ቲያትር?»
Anchor News Update ''ማንም አማራ ነገ ሰልፍ እንዳይወጣ'' የፋኖ መሪዎች
Anchor Media የወሎ ግንባር የሰሞኑ ተጋድሎዎች
''ፋኖ የምድር ድሮን ሆኗል። የአብይ አህመድ ሰራዊትን ብትንትኑን እያወጣ ያለ ሃይል ነው። ሰራዊቱ ተንዷል። የቀረው የሰማዩ ብቻ ነው''
Anchor Media የዛሬው የጎጃም የውጊያ ዘገባዎች፥ በርካታ አከባቢዎች ተይዘዋል"
 
ዕለቱን በዚህው እንከውነው። ውዶቼ መልካም ሰንበት። አሜን።
 
ቸር አስበን፤ ቸር እንሁን። አሜን።
ቅን አስበን፤ ቀና እንሁን። አሜን።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ።
 
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
08/02/2025
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።
ዕውነት ጋራጅ አያስፈልገውም።

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

የእኔ እማ ልዕልቴ እንዴት ነሽ?